“ኧረ በቃችሁ በለን!”

Wednesday, 18 November 2015 14:01

 

 

በጥበቡ በለጠ

ከሰሞኑ እግር ጣለኝና ጠይቄ የማላውቀውን ወዳጄን ለመጠየቅ ወደ ቤቱ ጐራ አልኩ። ወዳጄ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ በሣሎኑ ቁጭ ብሎ ይጨዋወታሉ። ቡና ተፈልቷል። ቁርጥ ሥጋ ጠረጴዛ ላይ ጐረድ ጐረድ ተደርጐ ቁጭ ብሏል። ክትፎውና ሌላ ሌላውም ቤቱን አጨናንቆታል። እኔ እንደምመጣ ስላወቁ በሠበቡ ግብዣ መሆኑ ታወቀኝ። የቆየ ሠላምታችንን ተለዋውጠን ወደ ምግብ ጠረጴዛው ክብ ሠርተን ቁጭ አልን። ቤት ያፈራውን ግብዣ እየተቀማመስን ሣለ በሣሎኑ ግድግዳ ላይ ተንሠራፍቶ የተዘረጋው ቴሌቪዥን የBBCን ዜና ሊያበስር መግቢያውን እያሟሟቀ ብቅ አለ። የተሟሟቀው የመግቢያ ጽምፅ አልቆ ዜና አንባቢው ብቅ ሲል ኢትዮጵያን ዋናው ርዕሠ ጉዳይ አድርጐ አወጀ። ጓደኛዬ ቤተሰቡ ፀጥ እንዲል አድርጐ ዜናውን በእርጋታ አየነው። ሰማነው። በድርቅ የተጐሣቆለውን የሰሜን ኢትዮጵያን አጠቃላይ ገፅታ አቀረበና ጨረሰ። ዝም ፀጥ አልን።

የጓደኛዬ እናት ሌላ ማብራሪያ ፈለጉ። ምንድን ነው ነገሩ? አሉ።

“የ8 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ለድርቅና ለረሃብ መጋለጣቸውን ነው ያቀረበው” አላቸው ጓደኛዬ።

 እርሣቸውም “ኧረ በቃችሁ በለን” አሉ። ወደ ላይ እጃቸውን ዘርግተው አንጋጠጡ። አምላካቸውን ጠየቁት። የምግብ ስሜታችን ጠፋ። ጠረጴዛው ላይ የተደረደሩት ልዩ ልዩ የፍስክ ምግቦች በፍቅር የምናጣጥማቸው ሊሆኑ አልቻሉም። ተውናቸው። በነርሡ ምትክ የድርቅ ጉዳይ ርዕሠ ወሬያችን ሆነ። ልዩ ልዩ ጉዳዮችን አንሥተን አወራን። እኔም የመቆያ ጊዜዬ አለቀና ወዳጄን ተሠናብቼ ወጣሁ። ያመራሁት ወደ ቢሮዬ ነበር። ነገር ግን ጆሮዬ ላይ እየደጋገመ የሚመጣ ድምፅ ነበር። የጓደኛዬ እናት ድምፅ። “ኧረ በቃችሁ በለን” የሚለው ድምፅ።

የድርቅ ወሬ፤ የረሃብ ወሬ፤ ከኢትዮጵያ ላይ መቼ ነው የሚያበቃው? መቼ ነው የሚቆመው? ኢትዮጵያ እና ድርቅ መቼ ነው የሚለያዩት? መቼ ነው የሚፋቱት? መቼ ነው የማይተዋወቁትና የሚረሣሡት?

በኢትዮጵያ ላይ ለሚደርሰው የድርቅ አደጋ የፈጣሪ ድርሻ ምን ያህል ነው? የኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድርሻስ ምን ያህል ነው? የአስተዳደራችንስ ድርሻ የቱን ያህል ነው እያልኩ አሠብኩ። ኢትዮጵያን በየአስር አመቱ ድርቅ ይጐበኛታል፤ ካልጠፋ አገር ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ምነው ሙጭጭ አለ? እያልኩ አሁንም አሠብኩ። በድርቅና በረሃብ ዙሪያ የተፃፉ መፃሕፍትን፤ የተሠሩ ፊልሞችን እና የጥናትና የምርምር ወረቀቶችን ማገላበጥ ጀመርኩ።

መቼም አዕምሮ የሚያስበው አያጣምና አእምሮዬ ፈጣሪን አሠበ። ኢትዮጵያ የሐይማኖት ሀገር ናት ትባላለች። በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው ሀይማኖት ከፊት ረድፍ ውስጥ ከሚጠቀሡት ውስጥ ናት። ኢትዮጵያ የፈጣሪ ሀገር ናት፤ ፈጣሪ የሚወዳት ምድር ነች እየተባለ በአባቶች ሲነገር ቆይቷል። የዚህ ሁሉ አማኞች ሀገርስ ሆና ለምንድን ነው በድርቅና በረሃብ የምትመታው?

በመፃሀፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ የተነሣ ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ነች። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች” (ዳዊት 69፡31) የሚለው ጥቅስ ሁሌም የምናስታውሰው ነው። ይህ ጥቅስ የተስፋ ምግባችን ነው። የሐገሬ ገበሬ ለሀይማኖቱ ለክሩ ሟች ነው። ለፈጣሪው የተገዛ ሕዝብ ነው። ሰንበትን ለፈጣሪው የሠጠ፤ በሠንበት የማያርስ ፤የማይቆፍር፤ አምላኩን ማመስገኛ ቀን አድርጐ የሚቆጥር ፅኑ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ በየአስር አመቱ የድርቅና የረሃብ አደጋ ለምን ይመታዋል? ምንድን ነው የጐደለው? የሚያስቀድስ የሚቆርብ አያሌ አብያተ-ክርስትያናትን እና ገዳማትን የመሠረተ፤ የቅዱሣን የመላዕክት የፈጣሪ ወዳጅ ሕዝብ ምነው ስሙ ከድርቅና ከረሃብ ጋር ይነሣል? የፅላተ-ሙሴው፤ የግማደ መስቀሉ ሀገር ኢትዮጵያ ለምን ከድርቅ ጋር ስሟ ይነሣል?

በኢትዮጵያ እምነት ውስጥ ድርቅ ምንድን ነው? ረሃብ ምንድን ነው? የሃይማኖት አባቶች ድርቅን እንዴት ይገልፁታል? ጳጳሳት ቀሣውስት ልዩ ልዩ የሃይማኖት መሪዎች ድርቅ ሲመጣ ምን ያስተምራሉ? ለአማኙ ሕዝብ ምን ይሉታል? መቼም በየአስር አመቱ የሚደጋገም አደጋን ለመቅረፍ ቤተ-እምነቶች አንድ መመሪያ ወይም አስተምሮ ሊኖራቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ግን ስለ ድርቅ ስለ ረሃብ ሲያስተምሩ አልሠማሁም። በEBS ቴሌቪዥን እንኳ ከሚተላለፉ የሃይማኖት ስብከቶች አንዱም ስለ ድርቅና ረሃብ አላስተማረንም።

ልጅነቴ ደግሞ ትዝ አለኝ። ድሮ ዝናብ አልመጣ ሲል፤ አየሩ ደረቅ ሲሆን እናቶችና አባቶች ወደ ቤተ-ክርስትያን ሰብሰብ ይሉና እግዚኦ …እግዚኦ መሀርነ ክርስቶስ እያሉ በሕብረት ፈጣሪያቸውን ሲማፀኑ አስታውሣለሁ። ዝናቡም ሲዘንብ ትዝ ይለኛል። እንደውም በአንድ ወቅት ሦስት ቀን ሙሉ እግዚኦ ሲባል ቆይቶ በዚው በሶስተኛው ቀን እግዚኦ እየተባለ ከላይ ዶፍ ዝናብ መጣ። ሠውም ግማሹ ዝናቡን ሸሽተው ወደ መጠለያ ሲሔዱ አባቶች ተቆጥተው ሲመልሱዋቸው ትዝ ይለኛል። ፈጣሪን ጠይቃችሁ የመጣላችሁ ዝናብ ፀበል ነው። ተጠመቁት። ብለው ሙሉ ዝናብ እላያችን ላይ ሲወርድ በልጅነቴ አስታውሣለሁ። በወቅቱ ሠውና ፈጣሪ ቅርበት ነበራቸው መሠለኝ። አሁንስ እግዚኦታ ይኖር ይሆን?

ኢትዮጵያ እና ድርቅ ከመቼ ጀምሮ ነው የተዋወቁት የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ መጣ። ግን እኮ ድርቅ ያልመታው የአለማችን ሕዝብ የለም። እኛ ላይ ጉዳዩ ለየት የሚያደርገው ረሃብ መሆኑ ነው። መራብ፤ የሚበላ የሚጠጣ ማጣት፤ ከዚያም ለስደትና ለሞት መጋለጥ። ግን መቼ ነው ረሃብና ኢትዮጵያ የተዋወቁት?

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ፅሁፎች ያበረከቱት ታላቁ ሊቅ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1985 ዓ.ም The history of famine and epidemics in Ethiopia prior to the twentieth century  በሚል ርዕስ ፅፈዋል። ከሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ስለነበረው የረሃብ እና የወረርሽኝ በሽታዎች ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደነበር የፃፉበት እጅግ ጠቃሚ ሰነድ ነው።

እንደ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አፃፃፍ ከሆነ ታሪኩን ወደ አንድ ሺ አመታት ይወስዱታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ስም እና ዝና ያለውን መፅሐፈ ስንክሣርን ይጠቅሳሉ። በዚህ መፅሃፍ ውስጥ የድርቅ እና የወረርሽኝ ዋና መንስኤ የሰዎች መጥፎ ድርጊት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣው የእግዜር ቁጣ እንደሆነ ጥንታዊው መፅሃፈ ስንክሣር እንደሚገልፅ ኘሮፌሰር ራቻርድ ፅፈዋል። የመጻፉን ዝርዝር ጉዳይ ወደፊት አቀርባለሁ።

ከኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቀጥሎ የኢትዮጵያ ረሃብ ላይ  ጥናት የሠራው ስለሺ ለማ ነው። ስለሺ ለማ እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቋንቋዎች ጥናት ተቋም በማስትሬት ድግሪ የተመረቀ ነው። ታዲያ በዚያ ወቅት ለመመረቂያው እንዲያገለግለው የሰራው ጥናት የኢትዮጵያ ረሃብተኞች በሚገጥሟቸው ግጥሞች /ስነ-ቃሎች/ ላይ ነበር። ርዕሡ A thematic approach to famine-inspired Amharic oral poetry ይሠኛል። ረሃብተኛ ውስጥ ገብቶ የረሃብተኛውን የውስጥ ራሮት፤ መከራ ፤ችግር፤ ቸነፈር ከቃል ግጥሙ ውስጥ ሠብስቦ የኢትዮጵያ ረሃብተኛ እንዲህ ነው ያለበት ጥናቱ ነው።

ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ደግሞ ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል? የሚል ድንቅ ግጥም ከ40 አመታት በፊት የፃፈ ሠው ነው። ፀጋዬ በዚህ ግጥሙ ውስጥ ራሱ ረሃብተኛ ነው የሚመስለው። የተራበ፤ በጠኔ የወደቀ ሰው ሆኖ መፃፍ ማን እንደ ፀጋዬ! ? ገጣሚውን ፀጋዬ ደጋግመን ባለቅኔ ልንለው ከቻልንባቸው አጋጣሚዎች አንዱ እንዲህ አይነት አስደማሚ ግጥሞችን ስለሠጠን ነው።

ረሃብ ቀጠሮ ይሠጣል?

ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል

“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል”

ይባላል፤ ድሮም ይባላል

ይዘለዝላል ይከትፋል

ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ ሆድ ለሆድ ይሰጣል?

ወተት አንጀት ነጥፎ ሲሳብ

ሆድ እቃ ደርቆ ሆድ ሲራብ

ተሟጦ አንጀት በአንጀት ሲሳብ

የጣር ቀጠሮው ስንት ነው?

ለሠው ልጅ ሠው ለምንለው

ላይችል ሰጥቶ ለሚያስችለው

ስንት ቀን ነው? ስንት ሌት ነው?

የፀጋዬን ግጥም ከዚህ በላይ ከዘለቅነው ሌላ ነገር ማሠብ እናቆማለን። ግጥሙ ላይ ምንም ማለት አይቻልም። አልቅሶ እና አድንቆ ዞር ከማለት ውጭ ቃል የለኝም።

ይሔ ድርቅ፤ ረሃብ፤ ጠኔ፤ ችጋር ወዘተ እያልን የምንጠራው ጉዳይ ኢትዮጵያን በመጥፎ ገፅታ ከሚያስጠሩት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው።

እ.ኤ.አ በመስከረም ወር 1973 ዓ.ም ላይ ግን፤ ኢትዮጵያ ስሟ በእጅጉ ተበላሸ። የቢቢሲ ጋዜጠኛ የሆነው ጆናታን ዲምብልቢ ወደ ኢትዮጵያ በተለይም ወደ ሰሜን ክልል ተጉዞ ፊልም ቀረፀ። ከዚያም በቢ.ቢ.ሲ ቴሌቪዥን The Unknown Famine /የማይታወቀው ችጋር/ ብሎ የ30 ደቂቃ ዶክመንተሪ ፊልም አቀረበ። አለም በጥንታዊ ስልጣኔዋ እና የረጅም ዘመን የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምድር እያለ የሚያቆለጳጵሳት ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ በረሃብ እየረገፉ መሆናቸውን ጆናታን ድምብልቢ በሰራው ዶክመንተሪ በመስከረም ወር እ.ኤ.አ 1973 ዓ.ም ይፋ አደረገው።

ነገሮች ተቀጣጠሉ። ረሀቡን መሰረት አድርገው ሁለት ፊልሞች በተከታታይ ተሰሩ። Seeds of Despair እና Seeds of Hop የሚሉ።

አለም በሣይንስና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ በእጅጉ በፍጥነት እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያዊን በረሃብ እየረገፉ ነበር። እናም የአለም ሕዝብ ለእርዳታ ተንቀሣቀሠ። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ጉዳዩ ወደ ፖለቲካ ተለወጠ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሰማንያ አመት ልደታቸውን ኬክ ቆርሠው እያከበሩ እንዴት ሕዝቡ በረሃብ ይረግፋል በሚል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተነሡ። ድርቁ እና ረሃቡ የትግል መቀስቀሻ ሆኖ ብቅ አለ። አብዮት መቀጣጠል ጀመረ።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ራሣቸው ጉዳዩ ምርመራ ይደረግበት አሉ። የድርቁ መንስኤ ሰው ሰራሽ ነው ወይስ የተፈጥሮ? ድርቁ እንዴት ተደበቀ? ማን ደበቀው? ለሞትና ለስደት ተጠያቂው ማን ነው? የሚሉ ጉዳዮች በረከቱ። በዚህም ምክንያት መርማሪ ኮሚሽን የሚባል ተቋቋመ። የዚህ የመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተመረጡ። እናም ኮሚሽኑ ምርመራ ጀመረ። እነ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ምርመራቸውን ማድረግ የጀመሩት በጃንሆይ ዘመን ውስጥ ትልልቅ ባለስልጣናት የነበሩት ሰዎች ላይ ነበር። እነዚህ ባለስልጣናት የሰሜን ኢትዮጵያን ድርቅ ለምን ሸሸጉ? ለምን ለአለም አልገለፁም? የድርቁ መንስኤ ምንድን ነው? እየተባለ ምርመራው ቀጠለ። በዚህ ግዜ ደግሞ የአብዮቱ እንቅስቃሴም እየፈጠነ ነበር። ተማሪው፤ ወታደሩ፤ ሰራተኛው፤ ታክሲ ነጂው…. አመጽ ውስጥ ገባ። የነ ፕሮፌሰር መስፍን ምርመራ ሳይጠናቀቅ የጃንሆይ መንግሥት ተገርስሶ ደርጐች ወደ ስልጣን መጡ።

ጃንሆይ እና ባለስልጣኖቻቸውም ወደ እስር ቤት ገቡ። ጃንሆይ ያቋቋሙት መርማሪ ኮሚሽን ሳይፈርስ እንዲቀጥል ደርግ ፈቀደ። ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም በደርግ ዘመን የመርማሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። ስራቸውንም ቀጠሉ።

መርማሪ ኮሚሽኑ የጃንሆይን ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድን ጨምሮ ሁሉንም እየጠሩ መመርመር ጀመረ። ለምሣሌ አክሊሉ ሀብተወልድ ተመርምረው ወንጀለኛ ተብለዋል። ወንጀለኛ ያስባላቸው ደግሞ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ደን ባለማስተከላቸው፤ አካባቢው ተራቁቶ አልቆ ነው የሚል አንደምታ ያለው ውሣኔ ላይ ተደረሰ። ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ደን ማስተከል ነበረባቸው ተባለ። እናም አክሊሉ ሐብተወልድ የአካባቢ ፀር ናቸው ተብለው ለድርቁ ሰበብ ሆኑ። ሌሎችም ባለስልጣናት እየተጠሩ የድርቁ ሰበብ መሆናቸው እየተነገራቸው ወደመጡበት እስር ቤት ይሔዱ ነበር። ጉዳዩ  አሣዛኝ እና ስህተት የተሞላበት ምርመራ ነበር። ወደፊት በዝርዝር እፅፈዋለሁ።

የኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርምን ስም እና ዝና የሚያጐድፈውም ከነዚህ ከጃንሆይ ባለስልጣናት ምርመራ እና ግድያ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጉዳይ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ኘሬዘደንት የነበሩት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ገነት አየለ ባዘጋጀችው የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ መንግስቱ ስለ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያወራሉ። እንደ ኮ/ል መንግሥቱ አባባል፤ ስልሣዎቹን የጃንሆይ ሚኒስትሮችን ጉዳይ በተመለከተ ኘሮፌሰር መስፍንን አንዳማከሯቸው ይገልፃሉ። እነዚህ የንጉሡ ባለስልጣናትን በተመለከተ ምርመራ ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ፤ ባለስልጣናቱን ምን እናድርጋቸው ብለው መስፍን ወልደማርምን እንደጠየቁ መንግሥቱ ኃማርያም ይናገራሉ። ከዚያም ኘሮፌሰር መስፍን መሣሪያው ያለው በእጃችሁ ነው እንዳሏቸውም መንግሥቱ ለገነት ነግረዋታል። ቀጥሎም 60ዎቹ የጃንሆይ ባለስልጣናት በአንዲት ቀን ተረሸኑ። የአትዮጵያ ድርቅ ሰበብ የሆነው ግድያ፤ ጭፍጨፋ፤ አረመኔነት ብንለው ይሻላል።

ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሚፅፏቸው መፃሕፍት ውስጥ የዚህን የምርመራ ኮሚሽን ስራቸውን እና አስተዋፅኦዋቸውን በዝርዝር አላቀረቡልንም። የእነ ኘሮፌሰር መስፍን የምርመራ ውጤት ምን ይላል? ከደርግ ጋር የነበራቸው ንክኪ እንዴት ነበር? 60ዎቹ ባለስልጣናት ላይ የተደረገው ምርመራ ለደርግ ግድያ አላጋለጠም ወይ? ኘሮፌሰር መስፍን መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ብለው ሲፅፉ፤ አዳፍኔን ሲፅፉ የመርማሪ ኮሚሽንን ጉዳይ አላቀረቡልንም። መንግሥቱ ኃይለማርያም በ60 ሰዎች ግድያ ውስጥ የኘሮፌሰሩ አስተዋፅኦ አለ ሲሉ መስፍን ወልደማርም ዝርዝር መረጃ ሊሠጡን ይገባ ነበር ብዬ አስባለሁ።

ይህን ሁሉ ያፃፈኝ የድርቁ ጉዳይ ነው። ድርቅ በ1965 እና 1966 ዓ.ም ያስከተለው መዘዝ ነው። ንጉሡን ጨምሮ 60ዎቹን ባለስልጣኖቻቸውን በልቷል።

የእነኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርም መርማሪ ኮሚሽን፣ ባለስልጣናትን ብቻ አልነበረም የመረመው። ጋዜጠኞችም ጭምር ተመርምረዋል። ታላቁ ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ፤ ብርሃኑ ዘሪሁን፤ ነጋሽ ገብረማርም፤ ማዕረጉ በዛብህ እና ሌሎችም ታዋቂ ጋዜጠኞች በመርማሪ ኮሚሽኑ አማካይነት ስለ 1965 እና 1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድርቅ ሁኔታ ምርመራ ተደርጎባቸዋል። ምርመራው የተደረገባቸው ለምን ድርቁን አላጋለጣችሁም? ለምን ስለ ድርቁ አልፃፋችሁም? ድርቁን ሕዝብ እንዲያውቀው ለምን አላደረጋችሁም? እየተባሉ ተመረመሩ። ስለዚህ ስለ ድርቅ እና ረሃብ አለመናገር በራሱ ያስጠይቃል ማለት ነው።

ከኛ ይልቅ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ፊልም እየሰሩበት የሀገራችንን ድርቅ ለነሱ መታወቂያ ለኛ ደግሞ ማፈሪያ እየሆነ መጥቷል። እ.ኤ.አ በ1987 አ.ም ቢቢሲን ጨምሮ በቻናል ቲቪ በቶማስ ቲቪ እና በብሪትሽ ኢንዲፔንደንት ቲቪ የተላለፈ ሌላ ዶክመንተሪ ፊልም ነበር። ርእሱ Living After the Famine ይሰኛል። ከረሃብና ከችጋር በኋላ ሰዎች እንዴት እየኖሩ እንዳሉ የሚያሳይ ነው።

ዮርክሻየር ቲቪ የተሰኘው ጣቢያ እ.ኤ.አ በ1986 አ.ም Tigray the Unofficial Famine የተሰኘ ዶክመንተሪ ሰርቶ አስተላልፏል። በወቅቱ ትግራይ ውስጥ እምብዛም ስላልተነገረለት ድርቅ የተሰራ ዶክመንተሪ ነው።

እ.ኤ.አ በ1987 አ.ም ደግሞ ቸርች ዎርልድ ሰርቪስ በተባለ የሃይማኖት ተቋም አማካይነት Ethiopia Hunger on the Front Lines የተሰኘ የድርቅ ፊልም ሀገራችን ላይ ተሰራ። ይሄን ተከትሎም ኢትዮጵያ በመዝገበ ቃላት ላይ ሳይቀር የድርቅ ምሳሌ ሆና ብቅ አለች።

ሌሎች አያሌ የረሀብ ፊልሞች ተሰርተውብናል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

1-       The Land Reaching

2-       The people of Sand

3-       Living with Hunger

የተሰኙ ፊልሞች የኢትዮጵያን ገጽታ ክፉኛ ያጠፉ ናቸው። ግን ደግሞ እውነታው አለ። ድርቅ አለ። ሁሌም በየ አስር አመቱ ብቅ ይላል። ይህን አዙሪት እንዴት እንቀልብሰው የሚለውን ጥያቄ በተግባር መመለስ ግድ ይላል።

የበርታ ኮንሰትራክሽን ባለቤት የሆኑት ኢንጂነር ታደሰ ኃይለስላሴ በ1990ዎቹ ውስጥ አንድ አስገራሚ ጥናት አቅርበው ቃለመጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። የጥናታቸው ርእስ «ረሀብንና ድህነትን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት የተደረገ ጥናት» ይላል። የእርሳቸው ትኩረት መስኖን በመጠቀም ኢትዮጵያን እንዴት ማበልጸግ እንደሚቻል የጻፉበት ነው። ተጻፈ እንጂ ወደ ተግባር የመለወጥ እንቅስቃሴ አልተደረገበትም።

ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅን እና ረሃብን በተመለከተ ድንቅ ፅሁፍ ካበረከቱ ሰዎች መካከል ዶ/ር ፈቃደ አዘዘን ሣልጠይቅስ ማለፍ አልችለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የቋንቋ እና የሥነ-ፅሁፍ መምህር የሆነው ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አንድ ለየት ያለ መፅሃፍ አሣትሞ ነበር። ርዕሡ «Unheard Voices Drought Famine and God in Ethiopa» የሚሰኝ ነው። ይህን መፅሃፍ ራሡ ፈቃደ አዘዘ ወደ አማርኛም መልሶት ብዙ ነገሮችን አካቶ አሣትሞታል። በአማርኛ «ሰሚ ያጡ ድምፃች፡- ድርቅ ረሃብና እግዜር በኢትዮጵያ» ብሎታል።

የፈቃደ አፃፃፍ ልዩ ነው ያልኩበት ምክንያት ሰውየው በኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ላይ ሠፊ የሆነ ጥልቅ ጥናት ያካሔደ የዚህች ሀገር ምሁር በመሆኑ ነው። ፈቃደ አዘዘ በድርቅ የተጐዱ ገበሬዎች ምን ይላሉ? በግጥሞቻቸው ምን ይነግሩናል በማለት የቃል ግጥሞቻቸውን ሰብስቦ ከዚያም ትንታኔ ሰጥቶ ያሣተመ ምሁር ነው። ግጥሞቹን የሰበሰበው በሚያዚያ ወር 1984 እና በጥቅምት 1987 ዓ.ም መካከል ነው። የሰበሰበበት ቦታም ባብዛኛው ከሰሜን ሸዋ በተለይ ከማፉዳ ነው።

የድርቅ እና የረሃብ አደጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ያስከተለውን አደጋ ግጥሞችን ሠብስቦ ያሣየን ሰው ነው። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የድርቅና የረሃብ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሠም ያሣየናል። በዚህ መፅሐፍ እና በሌሎች በድርቅ ላይ ስለተሠሩት ዶክመንተሪ ፊልሞች ጉዳዮቸ ላይ ሣምንት እቀጥልበታለሁ። 

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
9573 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us