በበኩሌ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃሁ

Wednesday, 25 November 2015 14:56

 

ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ

የአትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ም/ፕሬዘደንት

በጥበቡ በለጠ

ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የደርግ መንግሥት ምክትል ኘሬዘደንት የነበሩ ናቸው። ደርግን ለ17 አመታት ከመሩት ከፍተኛ ሀላፊዎቸ አንዱ ናቸው። በ1983 ዓ.ም ደርግ በኢሕአዴግ ተገርስሶ ከወደቀ በኋላ ለ20 አመታት በእስር ቆይተው ተፈተዋል። ያለፈውን የሕይወት ተሞክሯቸውንና ውጣ ውረዳቸውን ደግሞ አብዮቱና ትዝታዬ በሚል ርዕስ 598 ገፆች ያሉት ግዙፍ መጽሐፍ አሣትመዋል። ይህንንም መጽሐፋቸውን ባለፈው ቅዳሜ ሕዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ሐረር ግሪል አዳራሽ አያሌ ታዳሚያን በተገኙበት ሥነ-ሥርአት አስመርቀዋል። በመፅሃፋቸው ላይም ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ተጋብዘው ነበር። ከዚያም ከጋዜጠኞችና ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር የቃለ-መጠይቅና የውይይት መርሃ ግብር አድርገዋል።

 

በዚሁ አብዮቱና ትዝታዬ ብለው ባሣተሙት መፅሃፋቸው ዙሪያ እና ኮሎኔሉ በግል ሕይወታቸው ዙሪያ በአስተሣሰባቸውም ጭምር ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሸ ሠጥተዋል። የእለቱ መድረክ መሪ አርቲስት ደሣለኝ ኃይሉም ውይይቱንም ሆነ ቃለ-መጠይቁን በተገቢ ሁኔታ አስተናግዶት አርፍዷል።

 

ለሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹን በጥቂቱ ለመዳሰስ ሞከራለሁ።

ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስርአት መውደቅ እና ለደርግ መተካት ዋነኛው ምክንያት የነበረው 1965 ዓ.ም ድርቅ ነበር። በድርቁ ምክንያት አያሌ ዜጐች አለቁ። ተሠደዱ። ይህ የሆነበት ምክንያት ድርቁ በመደበቁ ነው። ለሕዝቡ ይፋ ባለመደረጉ ነው በሚል በኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሚመራ መርማሪ ኮሚሽን በጃንሆይ መንግስት ላይ እንደተቋቋመ ይታወቃል። ደርግ ደግሞ በአንዲት ምሽት ከ54 በላይ ሠዎችን ገድሎ ቀብሯል። ለዚህ ግድያ ዋናው ምክንያት አድርገው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መርማሪ ኮሚሽኑን ጠቅሠው ነበር። ለመሆኑ የነ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርም አስተዋፅኦ ምን ነበር ተብለው ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ተጠይቀው ነበር።

ኮሎኔሉ ሲመልሱ “መጽሐፌ ውስጥ በግልፅ አስቀምጭዋለሁ” ብለዋል። መፅሃፋቸው ውስጥ የገለፁትም እንዲህ በሚል ነበር፡-

 

“በንጉሡ ባለስልጣናት ላይ የፖለቲካ ውሳኔ እንዲሠጥ መሠረት የሆነው  የመርማሪ ኮሚሽን የምርመራ ውጤት ነበር። የመርማሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም በንጉሠ ነገሥቱ የታዘዘው መጋቢት 17 ቀን 1966 ዓም ቢሆንም አዋጁ ታትሞ የወጣው ግን ሰኔ 16 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር። ዓላማውም አንድ ባለሥልጣን በሆነ መንገድ ያፈራው ሃብትና ያባከነው የመንግሥት ገንዘብ ንብረት እንዲሁም በዳኝነቱ እና በአስተዳደር ያደረሰው በደል ቢኖር ለመመርመር ነበር። አባላቱም የሚከተሉት ነበሩ፡-

1.    ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም           ከዩኒቨርሲቲ

2.    ዶ/ር በረከት ኃብተሥላሴ                 ከግል

3.    አቶ ጃሃድ አባቆያስ                      ከማእድን ሚኒስቴር

4.    ዶ/ር መኮንን ወልደ አምላክ               ከዩኒቨርሲቲ

5.    አቶ ጌታቸው ደስታ                     ከጠቅላይ ኦዲተር

6.    አምባሣደር ዘነበ ኃይሌ                   ከውጭ ጉዳይ

7.    አቶ ሁሴን እስማኤል                    ከመምህራን ማሕበር

8.    ኮማንደር ለማ ጉተማ                    ከባሕር ኃይል

9.    ኮ/ል ነጋሽ ወልደማካኤል                 ከፖሊስ ሠራዊት

10.  ሻለቃ አለማየሁ ወልደሚካኤል             ከክቡር ዘበኛ

11.  ሻለቃ ምትኪ ደምሴ                     ከአየር ኃይል

12.  ሻለቃ መርሻ አድማሱ                    ከምድር ጦር

13.  ሻምበል ሰላመ ህሩይ                     ከብሔራዊ ጦር

14.  አቶ መዋዕለ መብራቱ                    ከፓርላማ /የኤርትራ እንደራሴ/

15.  አቶ ሠይፉ ተክለማርያም                 የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ

እነዚህ ስማቸው ከላይ የተዘረዘረው ሠዎች የጃንሆይን ባለስልጣናት ወንጀል እንዲመረምሩ መሾማቸውን ኮ/ል ፍሥሃ ደስታ ይገልፃሉ። ከዚያም ኮ/ል ፍሥሐ የሚከተለውን ፅፈዋል።

 

“ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ሥራውን እንደጀመረ የደረሠበትን ደረጃ እንዲያስረዱ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና ዶክተር በረከት ሃብተስላሤ በአስተባባሪ ኮሚቴው ተጠርተው ነበር። አላማውም በውጤቱ ንጉሡን ለማውረድ መቀስቀሻ እንዲሆን ነበር። ሁለቱም በጉዳዩ ብዙ እንዳልገፉበትና ንጉሡን ለማውረድ የኮሚሽኑ ውጤት አስፈላጊ እንዳልሆነ፤ ሕገ መንግሥቱ  ወረቀት ስለመሆኑ፤ ጠበንጃው ያለውም በእጃችሁ ስለሆነ ይልቁንም ጊዜ በወሰደና በቆየ ቁጥር ከፍ ያለ አደጋን ሊያስከትል ስለሚችል ንጉሡን በአስቸኳይ ማውረድ አለባችሁ በማለት በተለይ ዶ/ር በረከት ኃብተሥላሴ ምክራቸውን ለግሰው ሄዱ”

ሲሉ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ፅፈዋል። በርግጥ ይህ ነጥብ እጅግ በጣም አጠያያቂ ነው። በተለይ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አያሌ መጣጥፎችን እና መፃሕፍትን ሲፅፉ እንዲህ ያለውን  የሕይወት ገጠመኛቸውን አለመግለፃቸው አስገራሚ ነው።

 

ታዲያ ይሕ በእንዲህ እያለ የግድያው ዋና አቀነባባሪ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም እንደሆኑ ፍሥሐ ደስታ ይገልፃሉ። መንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ አባላትን ሰብስበው እንዲህ አሉ፡- መርማሪ ኮሚሸኑ ድርቁን በመደበቅ ተጠያቂ ናቸው ባላቸውና በከፍተኛ  ወንጀልና ለሀገሪቱ ውድቀት ተጠያቂ በሆኑት ላይ ውሣኔ ወደ መስጠት እናምራ አሉ። ከዚያም ስም እየተጠራ በ59 ሰዎች ላይ የሞት ውሣኔ ተላለፈ። ደርግ በደም ተጨማለቀ።

 

ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ ከጋዜጠኞታ የቀረበላቸው ሌላው ጥያቄ ወደር የማይገኝለት ድንቅዬ ደራሲና ጋዜጠኛ ስለነበረው የበዓሉ ግርማ ግድያን በተመለከተ ነው። እርሣቸውም ሲመልሱ የሚከተለውን ብለዋል፡-

 

ከደርግ ውድቀት በኋላ በእስር ላይ እያለን “በዓሉ ላይ ለምን እርምጃ ተወሰደ?” በማለት ተስፋዬን ጠየኩት። እሡም “መጽሐፉ ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ሻዕቢያ በሬዲዮ ጣቢያው በማስተላለፍ በሠራዊቱ ላይ ለከፍተኛ ቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳ ይጠቀምበት ጀመረ። በዚህ ምክንያትም የፖለቲካ የደሕንነት ሠራተኞችና አዛዦች ከፍተኛ እሮሮና ተቃውሞ ስላሰሙ በተለይ በአመራሩ ላይ ቅሬታቸውን ስለገለፁ ነው” የሚልና መገደሉን የሚያረጋግጥ መልስ ሰጠኝ። የፈሰሰ ውሃ ላይታፈስ የሞተ ላይመለስ መገደል ነበረበት ወይ የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ በእርግጥ ኘሬዘደንት መንግሥቱ እንዳሉት ወቅቱን ያልጠበቀ በሥራው ኃላፊነት ያገኘውን ምስጢር በማውጣቱ ከፍተኛ አቧራ እንደሚያስነሣ ግልፅ ነበር። ፍርድ ቤት ስንቀርብም አንድ የደሕንነት መሥሪያ ቤት ሾፌር በ1976 ዓ.ም በአሉን ከአንድ ቦታ አሣፍሮ ደርግ ጽ/ቤት ወደነበረው የምርመራ ክፍል እንደወሠደው ቃሉን ሰጥቷል።

በማለት ፍሥሐ ደስታ ፅፈዋል።

ባጠቃላይ በዓሉ ግርማ በሕይወት አለመኖሩን ኮ/ል ፍሥሐ አረጋግጠዋል። የት እንደተገደለ፤ አፅሙ የት እንደሚገኝ ግን እኔም ሆንኩ መንግሥቱ ኃይለማርያምም የሚያውቁ አይመስለኝም ብለዋል። የሚያውቀው ግድያውን የፈፀመው ሠው እና የቀበረው ሠው ብቻ እንደሆኑ ነው የተናገሩት።

 

ስለዚህ የበዓሉ ግርማ ባለቤት በዓሉ እንደወጣ ስለቀረ የሚመጣ ይመስለኛል በማለት ላለፉት 32 አመታት ስትጠብቀው ነበር። አሁን ግን የለም! ሞቷል።

 

ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በሌሎችም ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ፍፁም ትሕትና በተሞላበት ሁኔታ ማብራሪያ ሠጥተዋል። መፅሃፋቸው ውስጥ አያሌ ጉዳዮች ተካተዋል። ይቅርታም አቅርበዋል። እንዲህም ብለዋል፡-

 

 

የአትዮጵያ አብዮት ሰፊ፤ ፈጣንና ውስብስብ የነበረ ቢሆንም በግሌ ተካፋይ የነበርኩበትን፤ በዐይኔ ያየሁትንና በማስረጃ ያረጋገጥኳቸውን እውነታዎችን በተቻለ መጠን ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ በዚህ መጽሀፍ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ። የኔ ምኞትና ፍላጎት እኩልነት፣ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ አንድነቷና ልዐላዊነቷ የተጠበቀና የበለጸገች አንዲት ኢትየጵያን ማየት ነው። ዓላማ በመንደር ልጅነት፣ በጎሳና በዘር የሚለወጥ አይደለም። በዚያ የአብዮት ወቅት የተጋረጠብኝን ሴራና ተንኮል በመቋቋም፤ የገባሁትን ቃል ኪዳንና መሀላ ጠብቄ በንጹህ ህሊናና ቅንነት ሐገሬንና ሕዝቤን አገለግላለሁ። ደርግ በወሰዳቸው በጎ እርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ፤ በማወቅ በድፍረት፤ ባለማወቅና በስህተት ለተፈጸሙት ደግሞ፤ ሙሉ ሀላፊነትን በመውሰድ፣ በበኩሌ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃሁ።

ብለዋል።

 

መጽሀፋቸው በደርግ ዘመን ውስጥ ስለነበረው ክስተት በደንብ ሊያስረዳ የሚችል ሰነድ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ብዙ ያነጋግራል። በመጽሀፋቸው ዙሪያም በሰፊው እንጨዋወታለን።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
9017 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us