“ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብያለሁ”

Wednesday, 25 November 2015 15:00

 

ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

የቀድሞው የኢሕአፓ አባል

በድንበሩ ስዩም

ባለፈው ቅዳሜ ሕዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል አዳራሽ ውስጥ የቀድሞው የደርግ መንግሥት ም/ኘሬዘዳንት የነበሩት የሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ የተሰኘው መጽሐፍ ይመረቅ ነበር። በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ የደርግ መንግሥትን ከመሠረቱትና ከመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሻምበል ፍቅረሥላሴ የወግደረስን ጨምሮ አያሌ የደርግ መንግሥት ሹማምንቶች ታድመዋል። ሌሎችም በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ እየተባለ የሚጠራው ፓርቲ አባላት እና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ሰዎችም በምረቃው ላይ በጥቂቱም ቢሆን ተገኝተዋል። በዚሁ የደረግ መንግሥት ባለሥልጣናት በብዛት በታደሙበት የመፅሃፍ ምረቃ በአል ላይ አወያይ ሆነው ቁጭ ያሉት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የሰሜን አሜሪካ ቅርንጫፍ ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉትና በኢሕአፓ አባልነታቸውና ወኔያቸው የሚታወቁት ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ነበሩ። ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ከዚህ ቀደም በየመድረኩ ሽንጣቸውን ገትረው ስለ ታላቅ አላማው ይናገሩለት የነበረውን ኢሕአፓን ባልተጠበቀ መልኩ ጥፋተኛ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል። በዚሁ የደርግ ባለስልጣናት በታደሙበት መድረክ ላይ ኘሮፌሰሩ ገብሩ ታረቀ  ሲናገሩ “ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብያለሁ” ብለዋል። በአዳራሹ ውሰጥ የነበሩ ታዳሚያንም ይህንን የኘሮፌሰሩን ንግግር ሲሰሙ በጭብጨባ አሙቀውላቸዋል።

 

ይህ የኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ገለፃ ለብዙ የኢሕአፓ አባላት ለነበሩ አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በታሪክ ምሁርነታቸው የሚታወቁት እኚህ የቀድሞው የኢሕአፓ አባል የደርግ ባለሥልጣናት መድረክ ላይ ተገኝተው ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና እንደነበረው መግለፃቸው ብዙ ትርጓሜ ሊያሠጥ እንደሚችልም ይታመናል። ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና ከተጫወተ ደርግ ትክክል ነበር ማለት ነው? የዚያ ሁሉ ትውልድ እልቂት መገለጫው ይሔ አፍራሽነት ሆነ? አንድ ትውልድን የበላው የቀይ ሽብር ዘመን እንዴት ነው መገለፅ ያለበት? ብዙ ነገሮች አሰብኩ፤ ግን ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የኢሕአፓን የአፍራሽነት ሚና በምን ስሜት ውስጥ ሆነው ተናገሩት የሚለው ጉዳይ ዋናው ጥያቄ ይመስለኛል።

 

ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን የገለፁበት አጋጣሚ የሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ መጽሐፍ ምረቃ ላይ መሆኑ ነው ጉዳዩን በተለየ መልኩ እንዳየው ያደረገኝ። ምክንያቱም ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ የደርግ ሥርአት ሁለተኛው ሰው ወይም መሪ ናቸው። በእሳቸው ስርአት አማካይነት ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢሕአፓ አባላት ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተገርፋዋል፤ ለአካልና ለመንፈስ ጉዳት ተዳርግዋል። ቤተሠባቸውም ክፉኛ ተጐድቷል። ሐገራዊ ምስቅልቅል ተከስቷል። ይሔ የታወቀና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። ግን ደግሞ ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ እና የሚመሩት መንግሥት ባጠፋው ጥፋት 20 አመታት ያህል ታስረው ተፈቱ። ቀጥሎም አብዮቱና ትዝታዬ ብለው መጽሐፍ አሣተሙ። ይህን መፅሃፋቸውን ሁለት ሰዎች እንዲገመግሙት /ሒስ እንዲሰጡበት/ ተጋበዙ። አንደኛው የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ካሣሁን ብርሐኑ ናቸው። እርሣቸው መፅሃፉ የተፃፈበትን የታሪክ ርዕሰ ጉዳዮችን እንዲቃኙ ነው እድሉ የተሠጣቸው። ሁለተኛው ገምጋሚ ገጣሚና ፀሐፌ-ተውኔት የሆነው አያልነህ ሙላቱ ነው። አያልነህ የፍሥሐ ደስታን መፅሃፍ ከቋንቋ አንፃር እንዲገመግም ነበር የተጋበዘው። ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ደግሞ የግምገማውን እና እሡን ተከትሎ የሚመጣውን ውይይት እንዲመሩ መድረኩ ተመቻቸ።

 

ይህ መድረክ በጣም አስገራሚ ነበር። ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑ እና አያልነህ ሙላቱ ከወደ መኢሶን እና ደርግ በኩል ያዘነበለ አቋም ያላቸው ናቸው። የመድረኩ አወያይ ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የኢሕአፖ አባል ሲሆኑ የመፅሃፉ ደራሲ ሌ/ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ደግሞ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ መሪ የነበሩ ናቸው። ከዚህ የመድረክ ቅንብር ውስጥ ትልልቅ የሃሣብ ፍጭቶች እና አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ ብዬ አስቤ ነበር። ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑ እና አያልነህ ሙላቱ መፅሃፉን ሲያደንቁ ቆዩ። ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀም አድናቆታቸውን ገለፁ። በሰዎቹ መካከልም ልዩነት አጣሁ። በመጨረሻ ግን ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ከራሱ አባል ሲሰማ በርገግ ማድረጉ አይቀርም።

 

ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ “ኢሕአፖ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብያለሁ” ያሉት የአስማማው ኃይሉን መፅሐፍ ካነበብኩ በኋላ ነው ብለዋል። አስማማው ኃይሉ /አያ ሻረው/ ኢሕአሠ  /የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት/ የሚል መፅሃፍ አሣትሟል። መጽሃፉ ሁለት ቅጾች ሰኖሩት የኘሮፌሰር ገብሩን አመለካከት የቀየረው ግን ቅፅ ሁለት ነው። ይህንን የአስማማው ኃይሉን ኢሕአሠ ቅፅ ሁለትን መፅሃፍ ካነበቡ በኋላ ኘርፌሰር ገብሩ ታረቀ ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብለሁ ሲሉ አብላጫው የደርግ መንግሥት ባለስልጣናት በታደሙበት መዳረክ ላይ ይፋ አድርገዋል።

 

ግን ኘሮፌሰር ገብሩ ያላብራሩት ጉዳይ አለ። አፍራሽ ሚናው ምን ነበር የሚለው ነው። በዘመኑ የነበረው ግጭት በሺዎቸ የሚቆጠሩ ወጣቶች ደም የፈሠሠበት መስዋዕትነት የተቀበሉበት ሲፃፍም ሆነ ሲነገር ጥንቃቄ የሚጠይቁ ማስረጃዎችን በመያዝ መሆን ይገባው ነበር። ለምሣሌ አስማማው ኃይሉ ምንድን ነው የፃፈው? ስለ ኢሕአፓ የአፍራሽነት ሚና ምን ብሏል? ኘሮፌሰሩን አመለካከታቸውን ያስቀየረው የአስማማው አፃፃፍና ገለፃ የትኛው ነው? አንድን የታሪክ ምሁር ለዚያውም የኢሕአፓን ታሪክ ሲያደንቅ እና ሲያወድስ የነበረን ተመራማሪ አስማማው ኃይሉ እንዴት ቀየረው? አስማማው ኃይሉ የኢሕአፓ የጫካ ታጋይና ተዋጊ ነበር። አመራር ውስጥ ያልነበረ ነው። የፃፈውም ነገር ስለ ጫካ ትግሉ ነው። እሱ ራሱ ታች ያለ ታጋይ መሆኑን በሠፊው ፅፏል። ታዲያ ይህ ሰው ለመላው የኢሕአፓ ትግል እና ርዕዮተ አለም ወካይ መሆን ይችላል ወይ? ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን አስማማው ኃይሉ ራሱ አያምንም። በመፅሃፉ ውስጥም ሆነ በቃለ-መጠይቆቹ አስማማው ስለ ኢሕአፓ የተጨናገፈ ሕልም እንጂ ስለ አፍራሽነት ሚናው የገለፀበት አጋጣሚ የለም። ስለዚህ ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ይህን አባባላቸውን በደንብ እንዲገባን ቢያብራሩልን ጥሩ ይመስለኛል።

 

አስማማው ኃይሉ በመፅሃፉ ውስጥ ሲገልፅ ኢሕአፓ የቅዱሣንና የመላክት ፓርቲም እንዳልነበር ያስታውሣል። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የተሣሣታቸው ነገሮች እንዳሉ ፅፏል። ግን አፍራሸ ሚና መጫወቱን አልፃፈም። እንደውም እንዲህ ይላል፡-

በአርሶ አደሩ መካከል የፖለቲካ ሥራ ሲያከናውኑና ከደርግ ጋር በከተማዎች በተካሔደው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉ ጓደቻችንም በወደቁበት ጐዳና በተጓዝን ቁጥር ጀግንነታቸውን ከመኖራችን ጋር በማገናዘብ ልናስታውሣቸው የሚገባን ባለውለታዎቻችን ናቸው። /ኢሕአሠ ቅፅ ሁለት ገፅ 11/ ይላል።

አስማማው ኃይሉ ከዚህም ያክልና እንዲህ ይላል።

 

 

ለተከፈለው መስዋዕትነት ዋጋ መንሣት ትክክል አይደለም። ተወደደም ተጠላ አሁን በአገራችን ላለው ሥርዓት ሕልውና የዚህ ድርጅት አባላት አስከሬን ዛሬ የምንራመድባቸው ጐዳናዎች ላይ ቀኑን ሙሉ ተሰጥቶ ስለመዋሉ ሕዝብ ይመሰክራልና /ገፅ 16/ ይላል።

 ታዲያ ኘሮፌሰር የገለፁት የኢሕአፓ የአፍራሽነት ሚናው ከየት መጣ? እያልኩ አሠብኩ፤ መልስ ግን አላገኘሁም።

ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን ተቀብየዋለሁ ከማለታቸው በፊት አንድ ገለፃ ሠጥተው ነበር። ገለፃቸው በቀድሞው የኢትዮጵያ ኘሬዘዳንት በኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ንግግር ላይ ያነጣጠረ ነበር። ኮ/ል መንግሥቱ ኢሕአፓን በቆራጥነቱ አድንቀውታል በማለት ገብሩ ተናገሩ። ከዚም እንዲህ አሉ “ለቆራጥነቱ የእምነት ፅናት፤ የመንፈስ ፅናት፤ ሀገር የመውደድ ፅናት ነበረው በበኩሌ አልጠራጠርም” በማለት ኘሮፌሰሩ ተናገሩ። ከዚሀ በኋላ ነው ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና መጫወቱን የተናገሩትና ንግግራቸው በጭብጨባ የደመቀላቸው።

በዚሁ በሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ በተሠኘው የመፅሃፍ ምረቃ ላይ አወያይ የነበሩት ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ እንደተናገሩት ከሆነ የደርግ ባለስልጣናት የ17 አመታት ጉዟቸውን ውጣ ውረዳቸውን ነግረውናል ብለዋል። ገብሩ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ እንዲህ አሉ፡-

 

“የመጀመሪያው ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትግላችን በተሰኘው መፅሃፋቸው ሁለተኛው ሻምበል ፍቅረሥላሴ የወግደረስ እኛ እና አብዮቱ መፅሃፋቸው፤ የሻምበሉ ከኮሌኔሉ በእጅጉ የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋልሁ። አሁን ደግሞ ኮ/ል ፍሥሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ የተሰኘውን መፃሃፋቸውን አቅርበውልናል። ከስፋትና ከጥልቀት አንፃር፤ ከድርሰት አቀነባበር ከሚዛናዊነት አንጻር ያልዳሠሡተ ነገር የለም። ከመረጃ አጠቃጠም ያልተሟላ ቢሆንም ከሚዛናዊነት የኢሕአፓ ሀተታቸውን ወደ ጐን ትተን የኮ/ል ፍሥሐ ከሁለቱ መሪዎች የተሻለ ነው። በቋንቋ አጠቃቀም እዚህም እዛም የሠገሠጓቸው የአበው ብሒሎች እና አይን ሣቢ ፎቶዎች ለመፅሃፉ ተጨማሪ ድምቀት ሠጥተውታል። በቋንቋ ውበት የሚመጥናቸው እኛ እና አበዮቱ ይመስለኛል። ስለሆነም ሦስቱ ደራሲያን በእጅጉ ሊደነቁ ሊመሰገኑ ይገባለ።/ ጭብጨባ/ ሦስቱም ተጨማሪ መፃሕፍትን እንደሚያቀርቡልን የጠቆሙን ይመስለኛል። ቃላቸውን እነዲያከብሩልን እያሣሰብኩሌሎች ጓደኞቻቸውም የነሱን ምሣሌነት ተከትለው እንደሚፅፉ ተስፋ አደርጋለሁ”በማለት ተናግረዋል።

ኘሮፌሰር ገብሩ በዘመነ ደርግ አብዮተኛ እና ፀረ አብዮተኛ የሚሉ አባባሎቸ መኖራቸውንም አስታውሠዋል። ደርግን እንደ አብዮተኛ መቁጠር ኢሕአፓን ደግሞ ፀረ-አብዮተኛ አድርጐ ማቅረብ። ይህ አቀራረብ ትክክል እንዳልሆነም ኘሮፌሰሩ ተናግረዋል። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም በመጀመሪያ ደረጃ ሶስት አብዮተኞች ነበሩ ብለዋል። እነዚህም ኢሕአፓ መኢሶን እና ደርግ ናቸው። እነዚህን መቀበል አለብን ካሉ በኋላ አንድ ትውልድን ስለበላው ነጭ እና ቀይ ሽብር የመራን ግን ብዙ ምክንያቶች አሉ ብለው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

በዚሁ በሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ በተሠኘው መፅሃፍ ምረቃ ላይ መፅሃፉን ይገመግማሉ የተባሉት ሁለት ምሁራንም የረባ ነገር አላቀረቡም። የአንድ ትውልድ እና ስርአት ታሪክን የያዘ መፅሃፍ የብዙ አመለካከቶች ማዕከል የሆነን መፅሃፍ የአያሌዎች ደምና ሕይወት ያለበትን መፅሃፍ የገመገሙበት መንገድ ከነርሱ የማይጠበቅ ነበር።

 

ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑ የመፅሃፉን ርዕሶች አየጠቀሡልን ልክ አንድ መምህር የትምህርት ቢጋር (Course Outline) ለተማሪዎቹ ሠጥቶ ከዚያም የምንማራቸው እነዚሀ ናቸው እያለ እንደሚያብራራውና አንደሚገልፀው ነው ያቀረቡት። ግን አንድ ምሁር አንድን ትልልቅ ጉዳዮችን የያዘን መፅሃፍ እንዲህ ነው መገምገም ያለበት? ግምገማው ለደራሲውም ሆነ ለታዳሚው የሚሠጠውን ጥቅም ያጣሁበት ነበር። ባጠቃላይ ደካማ ሒስ ነበር።

 

አያልነህ ሙላቱም የመፅሃፉን የቋንቋ አጠቃቀም ለመገምገም ቢጋበዝም አርፍዶ በመምጣት ይቅርታ ጠይቆ ተቀላቀለ። ያረፈደውም በድህነቱ ምክንያት  ድሃው ከከተማ ይውጣ በሚለው መርህ መሠረት መኖሪያዬ ሰበታ ስለሆነ በጥዋት ብነሳም ልደርስ አልቻልኩም ብሏል። ከዚያም በሀገራችን ሀያሲ እንደሌለ ተናግሮ እሱም ሂስ እንደማይሰጥ ግን የራሱን ምልከታ እንደሚሞክር ገለፀልን። እሱም ቢሆን ስለ መፅሃፉ የቋንቋ አጠቃቀም የገለፀልን የረባ ማብራሪያ የለም። በመሠረቱ መፅሃፉ የታሪክ እንጂ የቋንቋ መፅሃፍ ስላልሆነ ለአያልነህ የተሰጠው ርዕስ በራሱ ብዙም ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። ይህ መፅሃፍ መገምገም ያለበት ከታሪክ፤ ከፖለቲካ፤ ከታማኝነት፤ ከግልፅነት፤ ከሕግ ወዘተ አንፃር ነው።

 

በዚሁ የመፅሃፍ ምረቃ ላይ ትህትናን እና ስርአትን ተላብሰው ያገኘኋቸው ደራሲውን ኮ/ል ፍሥሐ ደስታን ነው። ፍሥሐ ደስታ ለጠፋው ጥፋት ይቅርታ ጠይቀው ወደፊትም ሐገሪቷ የቂም መቋጠሪያ እና የደም መፋሰሻ እንዳትሆን በሁሉም ወገኖች እርቅ /ብሔራዊ እርቅ/ የሚኖርበትን መንገድ እንደሚሹ ገልፀዋል። መፃሃፋቸው ምንም ቢፅፉ በተቻላቸው መንገድ አውነቱን ለማውጣት እንደሞከሩና ሚዛናዊም ሆነው ነገሮችን አይተው ያዘጋጁት እንደሆነ አውስተዋል።

 

ሌላው አሣዛኝ ጉዳይ የመድረክ አወያዩ ነገር ነው። ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የአወያይነት ሚናቸውን በስርአት ተወጥተው አላገኘኋቸሁም። አስተያየት የሚሠጡ ትልልቅ ሰዎችን ሲያመናጭቁና እድልም ሲነፍጓቸው ለመታዘብ ችያለሁ። አወያዩ በዚያች አዳራሽ ውስጥ ያሉትን ታዳሚያን ስሜት ተቆጣጥረው ውይይቱን ፍሬያማ ማድረግ ተስኗቸዋል። ለምሣሌ ከታዳሚው የተነሱትን ጥያቄዎች እንኳን ኮ/ል ፍስሐ ደስታ እነዲመልሱዋቸው አላደረጉም። ቁጣ ተግፃፅ… ታዳሚው ላይ አበዙ። በጣም ገረመኝ። እንዲት አዳራሸ ውስጥ ያለን ስሜት አቻችለን መምራት ያልቻልን ሰዎች እንዴት ሀገር ለመምራት ታገልን እያልኩ አሠብኩ። እናንተዬ፤ ሐገር መምራት እንዴት ከባድ መሆኑን በሒልተን ሆቴል የኮ/ል ፍሥሐ ደስታ መጽሐፍ ምረቃ ላይ ገባኝ።

 

በዚሁ የመጽሐፍ ምረቃ ላይ አንድ ነገር ጭንቅላቴ ውስጥ መጣ። ይህ የታደምንበት ታሪክ ትውልዳችንን የበላ ነው። ትውልዱ በነጭ እና በቀይ ሽብር ያለቀብን ነው። ባክኖ የቀረ ባተሌ ትውልድ ነው። ደሙ በየጐደናው በየቤቱ ደጃፍ የትም የወደቀ ትውልድ። ታዲያ ምናለ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን ብድግ ብለን የሕሊና ጸሎት ብናደርግለት እያልኩ አሠብኩ። ግን እኔ የውይይቱ መሪ አልነበርኩ። ምን ማድረግ ችላለሁ? ተውኩት።

በዚሁ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና መሪዎች በብዛት በታደሙበት የመፅሃፍ ምረቃ ላይ ስሜቴን የነካው ኢሕአፓ ካለምንም የተደራጀ ማብራሪያ እና ገለፃ አፍራሽ ሚና የተጫወተ ፓርቲ መሆኑን በኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ መገለፁ ነበር። ይህን አባባላቸውን ደርጐች ፊት ከማለታቸው በፊት በአንድ ወቅት በEBS ቴሌቪዥን አርአያ ሰብ በተሰኘው ኘሮግራም ቀርበው ስለ ኢሕአፓ የሚከተለውን ብለው ነበር፡-

 

“በሕይወት መኖር የሚደገም ቢሆን ኖሮ ያንን ዘመን ለመድገም ደስታውን አልችልም ነበር። ዳግም የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴን በልበ ሙሉነት ለመቀላቀል ለአንድ ሰከንድም አላመነታም። ልዩ ጊዜ ነበር። የሚያንቀሣቅሡን ነገሮች በኔ ግምት ሁለት ናቸው። ሐገራዊ ፍቅር፤ ሕዝብዊ ፍቀር፤ ምኞታችን ፍላጐታችን አገራችን አድጋ ሕዝባችን በልፅጐ በአለም የሚገባቸውን ቦታ እንዲይዙ ለማድረግ ነበር። ያ ትውልድ በሐሃር ወዳድነቱ በሕዝባዊነቱ እስከ አሁን ድረስ የሚስተካከለው አላየሁም፤ ልዩ ነበር”

ሲሉ ኘፎፌሰር ገብሩ ተናግረው ነበር።

አሁን የመጣው የአፍራሽነት ገለፃቸው ቀድሞ ከነበረው ንግግራቸው ጋር አልሔድ አለኝ። የኢሕአፓን የትግል ታሪክ እንድወደው ካደረጉኝ ሠዎች መካከል አንዱ ኘ/ር ገብሩ ታረቀ ናቸው። የአሁኑ ገለፃቸው ደግሞ ግራ አጋባኝ። ኢሕአፓ አፍራሽ ሚና ነበረው?

 

ኘሮፌሰር ገብሩ በአሜሪካ የሆባርትና ስሚዝ ኮሌጅ ከ30 አመታት በላይ ታሪክን ያስተማሩ ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው። ሁለት ስመ ገናና መፃሕፍትን ያሣተሙ ናቸው። አንደኛው Ethiopia: Power and protest peasant revolts in the Twentieth  century ይሠኛል። በዚህ ርዕስ እንዲፅፉ ያደረጋቸውና የገፋፋቸው ራሱ የኢሕአፓው መስራችና መሪ ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ ነበር። እርሣቸው የባርነት ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እንደነበር ሊፅፉ የታዘዙትን ሃሣብ ያስቀየራቸው ሟቹ የኢሕፓ መሪ ተስፋዬ ደበሣይ ነው። ሁለተኛው መፅሃፋቸው The Ethiopia Revolution- War in the Horn of Africa የሚሠኝ ነው። ይሔም ግሩም መፅሃፍ እንደሆነ ይነገርለታል። ግን ሁለቱንም መጽሃፍት በሀገራቸው ቋንቋ ባለመፃፋቸው በሠፊው የኢትዮጵያ አንባቢ ዘንድ አይታወቁም።

ኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በኢሕአፓ ውስጥ በነበራቸው ድርሻ በእጅጉ እንደሚኮሩበት እንደማይፀፀቱ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ የቆዩ ታላቅ የታሪክ ምሁር ሆነው ሣለ የጫካ ታጋዩ አስማማው ኃይሉ በፃፈው መጽሃፍ ድንገት የአቋም ለውጥ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ጉዳይ ምን ይሆን እያልኩ በመጠየቅ መልሣቸውን እጠብቃለሁ።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
15988 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us