ደራሲ አስማማው ኃይሉ ተዘከረ

Wednesday, 02 December 2015 14:31

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ ውስጥ በጫካ ታጋይነታቸው ከሚታወቁት አንዱ የሆነውና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደራሲ አስማማው ኃይሉን የሚዘክር ዝግጅት ባለፈው ቅዳሜ ሕዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተካሒዷል።

በዚሁ ዝክረ-አስማማው ኃይሉ ዝግጅት ላይ ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ፣ አብሮ አደጎቹ እና የቀድሞው የኢሕአፓ አባላት ተገኝተዋል። በዝግጅቱ ላይም የአስማማው ኃይሉ የሥነ-ፅሁፍ ርቀት እና ጥልቀት በተለያዩ ባለሙያዎች የተቃኘ ሲሆን፤ ደራሲው አስማማው እንደ ሰው ደግሞ ምን አይነት ስብዕና እንደነበረውም ከጓደኞቹ ዘንድ ምስክርነት ተሰጥቷል።

አስማማው ኃይሉ ያለውን ሁሉ ለሰው በመስጠት እና ባዶውን በመቅረት የሚታወቅ ስብዕና ያለው መሆኑን አንድ ጓደኛው የተናገሩ ሲሆን ሲያክሉም የሚከተለውን ብለዋል።

“አስማማው ኃይሉን ደግነት፣ ቸርነት፣ ቅንነት አይገልፁትም። ይልቅስ ደግነት፣ ቸርነት እና ቅንነት የሚገለፁት በአስማማው ነው” ብለዋል።

በዝክረ አስማማው ኃይሉ ዝግጅት ላይ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ የአስማማውን የደራሲነት ስብዕና ከልዩ ልዩ ማዕዘናት አይቶ አቅርቧል። ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም ታጋዩን እና ደራሲውን አስማማው ኃይሉን የገለፁት ሲሆን፤ በዲስኩር አዋቂነቱ ዝነኛ የሆነው በኃይሉ ገብረእግዚአብሔም በአስማማው ኃይሉ ሕይወትና ስራዎች ላይ ከተናገሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ገጣሚያኑ ደምሰው መርሻ እና ባንቺ አየሁ ከአስማማው የግጥም ስራዎች ውስጥ የተወሰኑትን አቅርበዋል።

አስማማው ኃይሉ ሐምሌ 8 ቀን 1947 ዓ.ም ከእናቱ ከወ/ሮ ዓለሚቱ ገረመው እና ከአባቱ ከአቶ ኃይሉ ጓንጉል በጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ እንደተወለደ የሕይወት ታሪኩ ያወሳል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ከ1966-1969 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በስታስቲክስ መስሪያ ቤት ተቀጥሮ በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ መስራቱም ተነግሯል።

ከዚያ በኋላም ኢሕአፓን በመቀላቀል ወደ በረሃ በመውረድ ደርግ ላይ መሣሪያ አንስቶ ሲዋጋው የነበረ ታጋይ እንደሆነ የሕይወት ታሪኩ ያወሳል። የኢሕአፓን ትግል ካቆመ በኋላ ወደ ሱዳን ተሰድዶ ለአምስት ዓመታት ቆይቷል። ከዚህም ወደ አሜሪካ ተሰድዶ ኑሮውን በመጀመሪያ ፊላደልፊያ ቀጥም በዋሽንግተን ዲሲ፣ በኮሎምቦስ፣ በኦሃዩ፣ በሂውስተን፣ ዳላስና ቴክሳስ እና ቨርጂኒያ በማድረግ በኬዝ ወርከርነት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪነት በተለይም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላትን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ የተጻፈለት የሕይወት ታሪኩ ያወሳል። በአሜሪካ የተወለዱ ወጣቶች የአገራችውን ባህልና ቋንቋ እንዲያውቁ በማስተማር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉም ይነገራል።

አስማማው ኃይሉ ይድረስ ከአያ ሻረው በተሰኘው የግጥም ሲዲው የሚታወቅ ሲሆን ይህም ስራው በአሜሪካ ኮንግሬስ ላይብረሪ እውቅና ተሰጥቶት ተቀምጧል። ከዚያ በኋላም ከደንቢያ ጎንደር እስከ ዋሽንግተን ዲሲ የተሰኙ የልቦለድ መፃሕፍትን ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለትን አሳትሟል። ቀጥሎም የኢሕአሠ ታሪክ ከ1975-1978 እና የኢሕአሠ ታሪክ ከ1978-1980 የተሰኙ ሁለት ተከታታይ መፃሕፍትን አሳትሟል።

አስማማው ኃይሉ በድንገት በተፈጠረ የጤና እክል ፊላደልፊያ በሚገኘው የፔንስልቫንያ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ገብቶ ሲታከም ቆይቶ ረቡዕ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም በተወለደ በ61 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን እና ጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም አሜሪካ በሚገኘው የደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን አያሌ ወዳጅ ዘመዶቹና የትግል አጋሮቹ በተገኙበት የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ መፈፀሙ ይታወሳል።

አስማማው ኃይሉ በሕመሙ ወቅት ፅፎ ያጠናቀቀው የልቦለድ መፅሐፍ የሕትመት ብርሃን የሚጠብቅ ሲሆን፤ ሌሎችም አያሌ ያልታተሙ የሥነ-ግጥም ስራዎቹ በልዩ ልዩ ሰዎች እጅ እንደሚገኙ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
9042 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us