ጽዮን ማርያም

Wednesday, 02 December 2015 14:34

 

በጥበቡ በለጠ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን እምነት ውስጥ ከሚከበሩት ታላላቅ በዓላት መካከል በትናንትናው ዕለት በጥንታዊቷ አክሱም ከተማ ውስጥ የተከበረው የጽዮን ማርያም አመታዊ ክብረ-ንግሥ አንዱ ነው። ጽዮን ማርያም ለኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ዋነኛዋ መሠረት ነች። የእምነት ቋሚው፤ ግድግዳው እና ማገሩ እንዲሁም ጣርያው የቆመው የዛሬ ሶስት ሺ አመት እዚህችው አክሱም ከተማ ላይ ነው። ዛሬም በርካታ አማኒያን እና አማኒያት እንዲሁም ጐብኚዎቸ ጽዮን ማርያም ላይ ተሰባስበው ስለሚገኙ  እኛም እዚህች ከተማ ላይ አረፍ ብለን አንዳንድ ነገሮችን እንጨዋወታለን። መንፈሣችንን ፀጋና መባረክ ባለበት ስፍራ ላይ እንወስደዋለን።

 

አክሱም ከተማ በተለያዩ የሥራና የጥናት አጋጣሚዎች ሔጃለሁ። ተመላልሼባቸው ካልጠገብኳቸው ስፍራዎች መካከል አክሱም አንዷ ነች። የአክሱም ነዋሪዎች ረጋ ደርበብ ያሉ ናቸው። የሐይማኖታቸው መሠረት የሆነው ጽላተ-ሙሴው መቀመጫው እዚህችው ከተማ በመሆኑ የነዋሪዎቿ ጠባይና ምግባር አክሱምን ከኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ ለየት ያደርጋታል። የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑ የዚህች ኘላኔት ዜጐች ሁሉ መመሪያ የሆነው አስርቱ ትዕዛዛት የተፃፈበት የሙሴ ጽላት መቀመጫው  አክሱም ናት። በዚህም ሣቢያ ላለፉት እጅግ በርካታ ዘመናት የሰው ልጅን ቀልብ እየሣበች የኖረች ቅዱስ ስፍራ ነች።

 

አንድ ግዜ በዚህችው ከተማ ውስጥ ስላሉት ምስጢራት ዶክመንተሪ ፊልም በምንሠራበት ወቅት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሀገር ጐብኚዎችን ቃለ-መጠየቅ እናደርግላቸው ነበር። ከነዚህ ውስጥ በተለይ ከሰሜን አሜሪካ ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩ እና የሚማሩ አያሌ ጥቁር አሜሪካዊያኖችን አገኝን። ከነርሱ ጋር በነበረን ቆይታ እፊታቸውና የውስጥ ስሜታቸው ላይ የመታደስ ስሜት እንደነበረባቸው ዛሬም ድረስ ከፊልሙ ላይ የማየው ገፅታቸው ይነግረኛል። እነዚህ አሜሪካዊያንን የገረማቸውና ያስደነቃቸው ጉዳይ እንዲህ ነው።

 

የእነሱ የቀደመው ትውልድ ከአፍሪካ በባርነት ተግዞ ነው አሜሪካ የሔደው። ከዚያም ለረጅም ዘመን ሲቀነቀን የኖረው ጥቁር ሕዝብ ምንም እንዳልሆነና እንደ ሰውም የሚቆጠር አልነበረም። መላው አፍሪካም ለነጮች የበላይነት በኰሎኒያሊዝም አፈና ውስጥ ለረጅም ዘመን ወድቋል። ስለዚህ ጥቁር ሃይማኖት አልባ እንደሆነ ሁሉ በአሜሪካ ማሕበረሰብ ውስጥ ብዙ ተፅፎ ነበር። ምንም እንኳ ያ አስተሣሠብ ዛሬ በግላጭ ባይታይም ጥቁርን አሣንሶ መመልከት በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ይታያል። በዚህ ስር የሰደደ ችግር ውስጥ ተወልደው ያደጉት ጠቁር አሜሪካዊያን የዘር ግንዳቸው ከተመሠረተበት ከአፍሪካ ምድር ተገኝተዋል። አክሱም ከተማን አይተው ጽዮን ማርያምን ለግማሽ ቀን ጐብኝተው አገኘናቸው። መላው አስተሣሠባቸው ተቀይሯል። ሁሉም ለካሜራችን ተናጋሪዎች ሆኑ። ስሜታቸውን ገልፀው አልወጣ አላቸው።

 

“ኢትዮጵያ የአለም ሕዝብ ሁሉ መሠረት!፤ የክርስትና መሠረት፤ የክርስትያን ጠባቂ፤ የእግዚአብሔር የአስርቱ ትዕዛዛት መኖሪያ፤ ቅድስት ሀገር፤…” እያሉ ብዙ ትንታኔና ማብራሪያ ሰጡን። በተለይ ጥቁሮች ወደ አክሱም ከተማ መጥተው ከጐበኙ በኋላ የጐደለው መንፈሣቸው ሞልቶ ይሔዳል። በተፅእኖ የተናቀው ማንነታቸው ለምልሞ እና አብቦ የሚወጡበት ሥፍራ ቢኖር አክሱም ጽዮን ማርያም ምድርን ከረገጡ በኋላ ነው።

 

በርግጥ ከነዚህ ጥቁር አሜሪካዊያን በፊትም የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር ሄነሪ ሉዊስ ጌትስ አፍሪካን ከጐበኙ በኋላ እጅግ አስገራሚ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተዋል። እኚህ ሰው ጥቁር አሜሪካዊ ሲሆኑ የሚያስተምሩት ደግሞ የክርስትያን ሥነ-ልቦና ነበር። ታዲያ በሚያስተምሩበት ወቅት ሁሉም የክርስትና ታሪኮች ከነጮች ጋር እና በተለይ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የተገናኘ ብቻ ነበር። ጥቁር በክርስትና ውስጥ ያለው ቦታ በታሪክ መዝገብ ላይ እምብዛም አልሠፈረም። ታዲያ ኘሮፌሰር ሄነሪ ሉዊስ ጌትስ ወደ አፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያ መጥተው አክሱምን እና ጐንደርን ካዩ በኋላ መንፈሣቸው ተቀየረ። አስተሣሠባቸው ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረ። በመጨረሻም በአለም አቀፍ ደረጃ በእጅጉ የታወቀላቸውን Wonders of the African World የተሰኘውን ረጅም ዶክመንተሪ ፊልም ሠሩ። የፊልሙ መነሻ ሃሣብም የተፀነሠው ከዚሁ ስፍራ ነው።

 

በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው በትውልድ ኬንያዊ የሆኑት እና በአሜሪካ ብሎም በመላው ጥቁሮች ዘንድ በእጅጉ የሚታወቁት ምሁርና ፈላስፋ፤ ኘሮፌሰር አሊ መሐዙሪ እርሣቸውም ብዙ ሽፋን የተሠጠላቸውን ዶክመንተሪ ፊልም ሠርተዋል። የእርሣቸው ፊልም The Africans የሚሰኝ ሲሆን በፊልሙ አማካይነት ከኢትዮጵያ ተነስተው አፍሪካን የሚያካልሉበት የእምነት፤ የባህል፤ የታሪክ፤ የማንነት ወዘተ… መገለጫ የሆነ ተወዳጅ ዶክመንተሪ ፊልም ነው።

አክሱም ከተማ ውስጥ ያለችው ጽዮን ማርያም የበርካታ ተመራማሪዎችን፤ የታሪክ ሰዎችን እና ፊልም ሰሪዎችን ቀልብ የምትስብ ናት። ጋዜጠኛው ግርሃም ሀንኩክ The sign and the seal የተሠኘውን መጽሐፉን ከማሣተሙም በላይ በጽዮን -ማርያም ዙሪያ እውቅና ያስገኘለትን ዶክመንተሪ ፊልም ሠርቷል።

ከዛሬ አንድ መቶ አመታት በፊት በ1903 ዓ.ም ጀርመናዊው የሥነ-ቁፋሮ /አርኪዮሎጂ/ ባለሙያ ኢኖ ሊት ማን ወደ አክሱም መጥተው ምርምርና ጥናት አካሒደው ነበር። ከዚያም Expedition on Axum የተሰኘውን ግዙፍ ተከታታይ መጽሐፋቸውን ካሣተሙ ጀምሮ አያሌ ተመራማሪዎች አክሱም ላይ ብዙ ሲፅፉና ሲሠሩ እስከ አሁን ድረስ አሉ። እነርሱን ሁሉ መጥቀስ አንችልም። ግን ብዙ ዕውቀት ስላስተላለፉልን አናመሠግናቸዋለን። እነ ዴቪድ ፊልፕሰንን ሳንረሳ ማለት ነው።

 

ንግሥተ ሣባ ከጠቢቡ ሰለሞን ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳ፤ ቀዳማዊ ምኒልክም በ22 አመት እድሜው አባቱን ንጉስ ሰለሞንን ለማየት ወደ እየሩሳሌም ሔደ። አባቱን አይቶ እና ተዋውቆ በመጨረሻም ወደ ሐገሩ ኢትዮጵያ ሊመለስ ሆነ። አባቱ ሰለሞንም ልጄ ብቻውን ወደ ሐገሩ አይሔድም በማለት የእስራኤል የካህናትና የመኳንንት የበኸር ልጆች ከምኒልክ ጋር እንዲሔዱ አዘዛቸው።

 

እነዚህ የመኳንንት እና የካህናት ልጆች ታቦተ ጽዮንን ጥለን አንሔድም በማለት የጽላቷን ተመሣሣይ አሠርተው ዋናውን ጽላት ሰርቀው ተመሣሣዩን አስቀምጥው ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ እንደተደረገ አያሌ የአፈ-ታሪክ ሰነዶች ያሰረዳሉ። በዚሁ አጋጣሚም ጽላተ-ሙሴ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣች ይነገራል። በመጀመሪያም በጣና ደሴት ከዚያም አክሱም፤ ቀጥሎም ዝዋይ ሀይቅ ላይ እንዲሁም ሸዋ ውስጥ ልዩ ልዩ ቦታዎች ከተዘዋወረች በኋላ አሁን ያለችበት አክሱም ከተማ ውስጥ እንደተቀመጠች ጥንታዊ ሰነዶች ያመለክታሉ።

 

አንዳንድ ሰዎች ይህ ጽላት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን የሚጠራጠሩ አሉ። ነገር ግን አያሌ የመካከለኛው ምስራቅ ተመራማሪዎች ለብዙ ዘመናት የዚህን ጽላት አድራሻ በልዩ ልዩ ቦታዎች ውስጥ አስሠው አጥተውታል። መደምደሚያቸውም ኢትዮጵያ ውሰጥ ያለው ጽላተ-ሙሴ ከጠቢቡ ሰለሞን ሐገር ከእስራኤል የተሠረቀው እንደሆነ ገለፀዋል። በተለይ ደግሞ ጽላቱን ይዘው የመጡት የቤተ-እስራኤላዊያን ታሪክ በራሱ ዋነኛው ማስረጃም እንደሆነ በልዩ ልዩ ዶክመንተሪ ፊልሞቻቸውና ፅሁፎቻቸው ገልፀውታል።

 

የጥንቷ አክሱም ጽዮን ማርያም ብዙ ታሪክ አላት። ጥንት አስባ በኋላም መዝበር እየተባለ በሚጠራው እዚያው አካባቢ በሚገኘው ቦታ ላይ በድንኳን ውስጥ ተቀምጣ ነበር የምትኖረው። በ315 ዓ.ም ገናናዎቹ ወንድማማች የኢትዮጵያ መሪዎች አብርሃ እና አጽብሐ ሕንፃ አሠሩላት። በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የአይሁድ እምነት ተከታይ የነበረችው ዮዲት/ጉዲት/ በአክሱም መንግስት ላይ ተነስታ ሕንፃውን አወደመችው። ቀጥሎም ንጉስ አነበሳ ውድም እንደገና አሠራው። ከዚያም በኦቶማን ቱርኮች በሚመራው በግራኝ አሕመድ ጦር በ16ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ተቃጠለ። ቀጥሎም የጐንደር መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ጥበበኛው አፄ ፋሲል ድንቅ የሆነ ኪነ-ሕንፃ አክሱም ላይ አሠሩ።

 

በተጨረሻም እስከ አሁን ድረስ የበርካታ ሀገር ጐብኚዎችን ቀልብ የሚገዛውን ኪነ-ሕንፃ ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አሠሩት። ይህ ሕንፃ የስለት ሕንፃ ነው እንደሆነም ይነገራል። የስለት ሕንፃ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በ1929 ዓ.ም ትወረራለች። ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ከዙፋናቸው ተነስተው ይሠደዳሉ። ሀገር አልባ ይሆናሉ። ግን አንድ ነገር ለጽዮን ማርያም ይሣላሉ። “በሕይወት እያለሁ የሀገሬን የኢትዮጵያን ነፃነት አሣይኝ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ቆማ ማየት እመኛለሁ። መንግሥቷ ተመልሶ ከቆመ ህዝቧ በነጻነት ከኖረ የጽዮን ሕንፃሽን መልሰን ባማረ መልኩ እናቆመዋለን” በማለት ተስለው ነበር። እናም ፋሽስቶች ወደቁ። የኢትዮጵያም ነፃነት ተመልሶ ቆመ። ጽዮንም በሚያምር ግርማ ሞገስ ቆመች። ታዲያ የአክሱም ጽዮን ማርያም እምነት ብቻ ሣትሆን የኢትዮጵያም የትንሣኤ በገለጫም ነች።

 

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሕንፃው ተሠርቶ ሲጠናቀቅ በምረቃው ላይ ተገኝተው የሚከተለውን ታሪካዊ ንግግር ማድረጋቸውን አቶ በሪሁን ከበደ የዐጼ ኃይለስላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሀፋቸው ውስጥ አስቀምጠውታል። በዚህ የምረቃ በአል ወቅት ዛሬም ድረስ ያሉት የእንግሊዝዋ ንግስት ኤልሳቤጥ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር። ጊዜውም ጥር 30 ቀን 1957 ዓ.ም ነበር። የጃንሆይ ንግግርም የሚከተለው ነበር፡-

 

ታሪክ እንደሚመሰክረው የአክሱም ከተማ የተቆረቆረችው ከክርስቶስ ልደት በፊት 2550 ዓመት ግድም ኢትዮጲስ በተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ950 ዓመት ውስጥ ቀዳማዊ ምኒልክ ሌዋውያንና ከ12ቱ የእሥራኤል ነገድ የበኩር ልጆች ይዞ ወደ አክሱም መጥቶ ቤተ መቅደስን መሥርቶ ሕገ እግዚአብሔርን አቋቋመ።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ 330 ዓ.ም ውስጥ ክርስትናን የተቀበሉት አብርሃና አጽብሐ ለማሠራት የአሰቡትን ቤተ-ክርስቲያን ዳግማዊ አጽብሃ በነገሠ ጊዜ በ372 ዓ.ም ግድም ተጀምሮ በ424 ዓ.ም ውስጥ በንጉሥ ዩአብ ተጠናቀቀ። ሁላችሁም እንደምታውቁት በ1535 ዓ.ም በግራኝ ዘመን የአክሱም ቤተ-ክርስቲያን ተቃጥሎ ነበር። አክሱም ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ብቻ ሳትሆን የሃይማኖት መዲናና የሕግጋት መነገሪያ ሆና የኖረች ቦታ መሆኗ የታወቀ ነው።

ቀዳማዊ ምኒልክና እናቱ ንግሥተ ሳባ ሕገ ኦሪትን እንደ ተቀበሉ አሁን ይህን ቤተ-ክርስቲያን በሠራንበት ቦታ ላይ ታላቅ ቤተ-መቅደስ ሠርተው አምልኮተ እግዚአብሔርን ይፈጽሙብት ነበር።

ጥንታዊት ኢትዮጵያ ሰፊ ግዛት ያላትና ልዩ ልዩ ነገዶች የሚኖሩባት አገር ነበረች። በታሪክ የታወቁ ብዙ ከተማዎችና ታላላቅ ሥራዎች የተፈፀሙባቸው ቦታዎች ነበሯት። ከነዚሁም ውስጥ እነ መርዌን እነ ኑብያን እነ ሳባን እናስታውሳለን።

እንዲሁም ከደሴቶቿና ከወደቦቿ እነ አዶሊስን ብናነሣ ታሪክ ይደግፈናል። አክሱም ሥልጣኔ የገባባት ታላቅ የኢትዮጵያ በር ናት። የፊደላትና የቅርጻ ቅርጽ አቅድ የተገኘው በአክሱም ዘመነ መንግሥት ነው።

አክሱም የግሪክ የፊኒክስ የባቢሎን ሥልጣኔ ከኢትዮጵያ ሥልጣኔ ጋር በማቀነባበር ይታይባት የነበረች ዕውቀት በሰፊው ይሸመትባት፤ ሕዝብ እንደአሻው ይገባባት ይወጣባት የነበረች ከተማ ናት።

አክሱም የሃይማኖት መዲና በመሆኗ ያለማቋረጥ ሕገ እግዚአብሔር የተነገረባት ከተማ ናት። አክሱም በኦሪትም በሐዲስም ተከብራ የኖረች የኢትዮጵያ ነገሥታት ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩባት ግዳጃቸውን የፈጸሙባት ሕያው ታሪከ አላት።

ስለዚህ ነገሥታቶቿ ሁሉ አንዳንዶቹ ቤተ-መቅደስን፤ አንዳንዶቹ ልዩ ልዩ ሐውልቶችን፤ አንዳንዶቹ ልዩ ልዩ መታሰቢያዎችን የሠሩላት ስለሆነች እነዚህ ሁሉ እስከ አሁን ድረስ ቀዋሚ ምስክር ሆነው ለጐብኝዎች ሁሉ አስረጅዎች ናቸው።

አክሱምን ስናነሳ የመጀመሪውን የአክሱምን ክብር የአስገኘውን ሕገ-ኦሪትን ወደ አገሩ ያስመጣው፤ ኢትዮጵያን ሀገረ እግዚአብሔረ ያሰኘውን ቀዳማዊ ምኒልክን እንዲሁም ክርስትና ወደ ሀገራቸው እንዲገባ አክሱም የክርስትና ፀሐይ መውጫ እንድትሆን የሠሩትን ለሥነ ጽሑፋችን መልክ የሰጡትን ቅዱሳን ክርስቲያናውያን ነገሥታትን አብርሃና አጽብሃን በዚህ ሰዓት እናነሣቸዋለን።

ለኢትዮጵያ ስፋት ለወገን ኩራት በመሆን ሥርዓተ ቤተ-ክርስቲያንን የወሰኑትን የሥልጣኔና የነጻነት ደጋፊ የነበሩትን እነ ዐፄ ካሌብን፤ እነ ዐፄ ገብረ መስቀልን ልናስታውሳቸው እንወዳለን። በኋላም ዘመን ቢሆን የአክሱም ቅርስ እንዳይጠፋ ይህን ሁሉ በመመልከት እስከ እኛ ዘመነ-መንግሥት ድረስ ለአክሱም የተለየ አስተያየት መደረጉ ታሪካዊም ሥራ መሠራቱ አልቀረም።

ለምሳሌ በጐንደር መንግሥት ጊዜ ዐፄ ፋሲል ይህን አሁን የሚገኘውን ሕንፃ በዘመናቸው ታላቅ ተብሎ የተገመተውን በጥብቅ ሥራ ሠርተውት እናገኘዋለን። በቅርቡም ዐፄ ዮሐንስ ጽዮን የሚለውን ማዕረግ ወስደው አክሱምን የቀድሞውን ክብሯን እመልሳለሁ፤ ታሪኳን አድሰዋለሁ የማለት ምኞት ነበራቸው። እኛም ከነገሥንበት ዘመን ጀምሮ ይህን መንፈሳዊ ተግባር ለመፈፀም ያላሰብንበት ጊዜ የለም። ነገር ግን ታላቅ ሥራ ለመሥራት ሰፊ ጊዜና ረጅም ጥናት የሚጠይቅ ስለሆነ እስከ አሁን ቆየን። አሁን ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ አሳባችን ተፈጽሞልን ይህ መርቀን የምንከፍተው ካቴድራል በታላቅነትም በዘመናዊነትም ከሌሎች ካቴድራሎች የበለጠ ለአክሱም ተስማሚ ይሆናል ብለን ያመንበት ነው።

የአክሱም ካቴድራሉን ብቻ በመሥራት አልተወሰንም። እንደ ጥንቱ የዕውቀት ምንጭ፤ የጥበባት መገኛ የሃይማኖት መዲና እንድትሆን በማሰብ ወጣቶች ትምህርትን የሚገበዩበት ትምህርት ቤት፤ ሕዝቡ ጤናው የሚጠበቅበትን ሆስፒታል እንዲሠራ አድርገናል።

ለቤተ ክርስቲያኑም አገልግሎት የሚያስፈልገውን ንዋዬ ቅድሳት አልባሳትና መጻሕፍት ለጊዜው የሚስማማ በሙሉ ሰጥተናል።

በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ከፍ ወደአለ ሥራ ለማድረስ አርኬዎሎዥስቶች መርምረው እየተቆፈረ ከነገሥታቱ መቃብር ውስጥ አብሮ የተቀበረው ወርቅ ተገኝቷል። የአክሱምን የአለፈውን ታሪኳንና ክብሯን በሰፊው ገልጦልናል።

ይሁን እንጂ አክሱም በጥንቱ የሥልጣኔ መልክ ካልተገኘች የቀድሞ ታሪኳ የሚበቃ አይደለም። ስለዚህ ካህናቱ በምስጋና በፀሎት በመማርና በማስተማር ለሌሎች አዳባራትና ገዳማት ምሳሌ ሁናችሁ ካልተገኛችሁ ከሌላው የተለየ ታላቅነት ሊኖራችሁ ወይም ሊያሰጣችሁ አይችልም።

ስለዚህ በዚህ ካቴድራል የሚፈፀመው አገልግሎት በውስጥም በውጭም የሚደረገው አስተዳደር ተሻሽሎ ካልተሠራ ላለን ምኞትና ለቀደመው ታሪክ ተቃራኒ ሆኖ እንዳይገኝ ያሠጋል።

“ሕግ ይወጽእ እምጽዮን” እንደ ተባለው ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትምህርት ከአክሱም ጽዮን ይመነጭ እንደነበረ የታወቀ ነው። አሁንም እንደዚያው ሆኖ መገኘት በስም አይደለም። አክሱም በሥራ እንጅ በስም ብቻ ታላቅነት ሊኖራት እንደማይችል አምናችሁ ለሥራችንም ለአሳባችንም ተባባሪ እንድትሆኑ ተስፋችን ነው።

እግዚአብሔር ትክክል አድርጐ በፈጠራቸው ወንድና ሴት መካከል ልዩነት ማድረግ ታላቅ ስሕተት ነው። ስለዚሀ ሰው ወይም ልማድ ሠራሽ በሆነ ምክንያት ሴቶች ሊለዩ የማይገባ ስለሆነ ይህ ልማድ ከዛሬ ጀምሮ ቀርቷል።

በዚህ በአሠራነው ካቴድራል ወደፊት የጾታ ልዩነት ሳይኖር ወንድም ሴትም በአንድ እምነት ባንድ ትምሕርት እንደየ ዕድሉ ሊጠቀምበት፤ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ሊያስመክርበት ይችላል። ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ማንኛዋም ሴት መንፈሳዊ ስሜቷን ለማርካት ሕይወቷን በመንፈሳዊ ጐዳና ለመምራት እንድትችል ወደ ካቴድራሉ ገብታ የመፀለይ ዕድል እንዲኖራት ወስነናል። የሴት ልጅ መብት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ እንዲጠበቅ የምንደግፈው ነው። የሴት ቅዱሳት በብዙባት አገር የሕዝብ ኑሮ ቅድስናን እንደሚያጐናጽፍ ሴቶች መንፈሳዊ ስሜት ያላቸው እንደሆነ ለልጆች ቅድስና አላፊዎች እንደሚሆኑ በቅዱስ መጽሐፍትና በታሪክም ጐልቶ የሚታይ ነው። በብሉይም በሐዲስም የወንዶችንና የሴቶችን እኩልነት ማን ሊሽረው ይችላል? ሴቶች ገዳም የማይገቡበት እነሱም ራሳቸው ገዳም አቋቁመው የመንፈሳዊውን ሥራ እንዲሠሩ በማሰብ ብቻ ነው።

አክሱም ጽዮንን ለማየት የሚመጡ ጐብኝዎች ብዙዎቸ ናቸው። ከሚያዩትና ከሚሰሙት ሁሉ አንዳንድ ነገር ተምረውና አጥንተው ለመሄድ የሚችሉበት መሣርያው በእጃችሁ ነው።

ለቦታው ጽዳት ለታሪኩ ታላቅነት ሁላችሁም እንድትደክሙበት ቢሆን ጥቅሙ የአክሱም ጽዮን ሲሆን በተለይ የመላው ኢትዮጵያ ነው።

ለስማችን ማስጠርያ ያህል ቤተ-ክርስቲያንን ሠርተን የምንተወው እንዳልሆነና ከፍ ያለ ጥናት እንዳለን ባለፈው ተናግረናል። አሳባችንን ወደ ፍጻሜ ለማድረስ የናንተ የመላ ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍና አገልግሎት ያስፈልጋል።

ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ይህን ታላቅ ሕንፃ አስጀምሮ ለማስፈፀምስለአበቃን ስሙ ቅዱስ ይሁን። (ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ፤ ጥር 30 1957 ዓ.ም)

ይህ የንጉሱ ንግግር ውስጡ አያሌ ታሪኮች አሉበት። እውቀት አለበት። ትእዛዝና ጥቆማ አለበት። አዲስ ፍልስፍናም አለው። ይህ ፍልስፍና ቤተ-ክርስትያን ስለ ሴቶች የምትከተለውን ደንብ የሚቃወም እና አዲስ አተያይ ያንጸባረቁበት ንግግር ነው። የሴትን ልጅ መብትም ያስከበሩበት በተግባርም ሕንጻ ሰርተው የሴቶችን ነጻነታቸውን ያስከበሩበት ነው። 

 

 

በነገራችን ላይ አንዳንድ የኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ሴቶች እንዳይገቡ ዛሬም ሲከለከሉ ይታያል። ይህን ክልከላ በተመለከተ ብዙ የሀይማኖት ሰዎችን ጠይቄ ነበር። ነገር ግን ትክክለኛውን መልስ ማገኘት አልቻልኩም። አንዳንዶች እንደሚሉት አክሱምን ዮዲት ጉዲት ካወደመቻት ጊዜ በኋላ ክልከላው እንደመጣ ይናገራሉ።

ላስታ ላሊበላ ውስጥ ያሉት የቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ሊቅ የሆኑት አፈ-መምህር አለባቸው ረታ እንደገለጹልኝ ከሆነ፤ ሴቶች በፍጹም መከልከል የለባቸውም ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ አጠገቡ ሆነው የመከራው ተካፋይ የነበሩት ሴቶች ናቸው፤ ስለዚህ መከልከል የለባቸውም ሲሉ ነግረውኛል።

ባጠቃላይ የዛሬ 51 አመት የተመረቀችዋ አዲሷ ጽዮን ማርያም ለሕንጻዋ ማሰሪያ የወጣው ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺ ብር ነበር። ዛሬ ቢሆን ዋጋው እጅግ የትየለሌ ነበር።

 

 

አክሱም በውስጥዋ እንዳላት ቅርስ አልተዋወቀችም። ምንም ያልተነገረላት የፕላኔታችን ምስጢራዊ ስፍራ ናት። ጽላተ-ሙሴን ያህል የሃይማኖት መገለጫ ጠብቃ የያዘች ምድር። ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰው ልጅ ጥንታዊ ስልጣኔን የሚገልጹ አስደማሚ ቅርሶች ባለቤት ናት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያያት ሊጎበኛት ይገባል። ያመት ሰው ይበለን!

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
11776 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us