በብሔረሰቦች ቀን ላይ ትኩረት የሚሹ ሃሣቦች

Wednesday, 09 December 2015 13:49

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

 

በየአመቱ ሕዳር 29 “የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን” በሚል መከበር ከጀመረ አስር አመታትን አስቆጠረ። ይህ በዓል መምጣቱን የሚያበስሩን ደግሞ ጥቂት የማስታወቂያ ባለሙያዎች መልካቸውና ድርጊታቸው በየአመቱ ተመሣሣይ የሆኑ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ይህ በዓል የእነርሱ የግላቸው ስራ እስኪመስለኝ ድረስ ተቆጣጥረውታል። የፌደራል ስርአቱ ማስታወቂያዎችና ዝግጅቶች በሙሉ የእነርሱ ይመስለኛል። ማን እንደሚሠጣቸውና በምንስ ምክንያት እነርሱ ብቻ እንደሚመረጡም የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን ሁሌም የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል እንዲሁም በየክልሉ የሚከበሩ በዓላትና ባዛሮች በመጡ ቁጥር እነዚሁ የማስታወቂያ ሰዎች ልብሶቻቸውን እየቀያየሩ ብቅ ይላሉ። ስለ በዓሉ ይነግሩናል። ጉዳዩን ተመሣሣይ በሆነ ቃና ሁሌም ያወሱናል። ለመሆኑ ሌላ ሠው በሐገሪቱ ውስጥ ጠፍቶ ነው ተመሣሣይ መልኮች ይህን ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ የወከለው? እያልኩ በዓሉን አከብራለሁ።  


ይህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ በዓል አንደምታው በጣም ጥሩ ነው። በሐገሪቱ ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን አንድ ላይ ማገናኘት እና ማስተዋወቅ በራሱ ትልቅ ጉዳይ ነው። ከዚህም ባለፈ ልዩ ልዩ የየብሔረሰቦቹ እሴቶችም ሊተዋወቁ የሚችሉበትን አጋጣሚ ይፈጥራል። ብቻ የበዓሉ መከበር ሠፊና ጥልቅ ጠቀሜታዎች አንደሚኖሩት በግሌ አምናለሁ።


በዚህ የበዓል አከባበር ላይ የማያቸው ተደጋጋሚ ቅሬታዎቼንም መግለፅ እወዳለሁ። በዚህ በዓል ላይ ለመታደም የሚጋበዙ ሰዎች በየአመቱ ተመሣሣይ ናቸው። የሚጠሩትም ተቋማት ተመሣሣይ ናቸው። በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሣለ ምነው በየአመቱ ተመሣሣይ ሰዎች የሚጋበዙት? የሚታደሙት? እያልኩ እጠይቃለሁ። የተለያዩ ሰዎችን በየአመቱ እንዲታደሙ ማድረግስ አይገባም ወይ እያልኩ አሰባለሁ።


በየአመቱ ከሚጋበዙት ሰዎች መካከል የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችም አሉ። በሐገሪቱ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፓርቲም ሆነ ሀገራዊ ክብረ-በዓላት ሲኖሩ እነዚህን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ናቸው ተብለው የታሰቡትን ሰዎች ይዞ መሔድ እየተለመደ መጥቷል። እነሱ የሚጋበዙበት ምክንያት በሙያቸው አማካይነተ ያዩትን፣ የታዘቡትን፣ ውሰጣቸው የገባውን የጥበብና የፈጠራ ለዛ አላብሰውት መልሰው ለሕዝብ ያቀርባሉ በሚል ግምት እንደሆነ በአንዳንድ መድረኮች ላይ ሰምቻለሁ። ጥያቄው ግን እነዚህ የኪነት ሙያ አላቸው እየተባሉ የሚጋበዙ ሠዎች ስለ ተጋበዙበት ጉዳይ ምን አዲሰ ነገር ይዘውልን ቀርበዋል የሚለው ነጥብ መታየት አለበት። ወጪ አስወጥቶ ድግሱን በልቶ ጠጥቶ ከመውጣት ውጭ ያደረጉት አስተዋፅኦ ካለ ማየቱ ጥሩ ነበር። ነገር ግን በበኩሌ የማየው አዲስ ለውጥ ስለሌለ ትክክለኞቹ ሙያተኞች የሚመረጡ አይመስለኝም። የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ ይህን ሁሉ ድግስ በልተው ያሣዩን ወይም ያመጡልን የጥበብ ስራ አለመታየቱ ቆም ተብሎ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል።


በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አከባበር ላይ በተደጋጋሚ የማይጠሩ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ባሕል ታሪክ ወግ ቋንቋ ወዘተ ላይ በተደጋጋሚ የሚመራመሩና የሚፅፉ ናቸው። ለምሣሌ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን በተመለከተ የምርምርና የጥናት ሥራዎችን ያበረከቱ ሰዎችና ተቋማት ሲጠሩ እና መድረክ ተሰጥቷቸውም ሲናገሩ አላየሁም። ይህ ችግር የሚመነጨው በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም በዋናነት ግን በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ላይ ማን ምን ሠራ ብሎ በጥልቀት የሚመረምር አዘጋጅ አለመኖሩ ይመስለኛል። መቼም ሁል ጊዜ እየተጋበዘ በልቶ ጠጥቶ አበል ተቆርጦለት የመጓጓዣው ወጪ ተሸፍኖለት ወንበር አሙቆ ከሚመጣ ተጋባዥ ነገ አዲስ ነገር ሊፅፍና ሊመራመር የሚችልን ባለሙያ መጋበዝ የተሻለ እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው።


ይህን የባለሙያዎችን ግብዣ ስኬታማ ለማድረግ ቀላል ይመስለኛል። በየጊዜው በኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ብሎም ሕዝቦች ላይ መሠረት አድርገው የታተሙ የተፃፉ ሰነዶችን የሚያጠና ቡድን መመስረት ያሰፈልጋል። ያ ቡድን እነማን ናቸው በዚህ ዙሪያ የፃፉ የተመራመሩ ብሎ ጋዜጦችን በማንበብ መፅሔቶችን፣ ጆርናሎችን በማየት፣ በየ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተከማቹ የጥናትና የምርምር ፋይሎችን በመፈተሽ ምሁራንን በመጠየቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሠቦችን እና ሙያተኞችን ማግኘት ይቻላል። እነዚህን ሙያተኞች በእንዲህ አይነት በዓል ላይ መጋበዝ ትርፉ ብዙ ነው። ሌሎችንም የጥናትና የምርምር ውጤቶችን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንዲሠሩ ያበረታታል፤ መንገድም ይቀይሣል።


ይህ እንኳ ባይሆን በየ አመቱ ሕዳር 29 ቀን በሚከበረው በዚህ በዓል ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሰዎችን እና ተቋማትን መዘከር/ ማስታወስ/ በእጅጉ ይገባል። ካለበለዚያ በየአመቱ በዓሉን ስናከብር አንድ የተጨበጠ ነገር ሰራን ብለን የምንናገረው ሚዛን የሚያነሣ ነገር ላይኖረን ይችላል።


የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ትልቅ በጀት ተመድቦለት በየአመቱ የሚከበር በዓል ነው። ከዚህ ባጀት ውስጥ ምን ያህሉ ለጥናትና ምርምር ውሏል የሚለውም መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው። ሁል ግዜ ተመሣሣይ በሆኑ ሂደቶች ውስጥ በጀቱ ወጥቶ ከሚያልቅ ነገ ለሁሉም ዜጋ የሚጠቅም አንድ የተጨበጠ ተግባር ተከናውኗል ወይ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።


ለምሣሌ በዚሁ የበዓል አከባበር ወቅት የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ማንነት የሚያሣይ መፅሃፍ ታትሟል ወይ? ብሔረሰቦቹ የት አንደሚኖሩ፣ ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ፣ የሚናገሩት የቋንቋ አይነት፣ በውጣቸው ያሉት የሚዳሠሡ እና የማይዳሰሱ የባሕል መገለጫዎች፣ ፍልስፍናቸው ታሪካቸው ወዘተ በቀላሉ የሚገኝበት መፅሃፍ አለን ወይ? ፅፈናል? መዝግበናል? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች ገና አልተመለሡም።


በእርግጥ እኔ እስከማውቀው ድረስ በኢትዮጵያ ብሔረሰቦቸ ላይ በተለያዩ ሰዎች አማካይነት አያሌ የጥናትና የምርምር ስራዎች ተሠርተዋል። ቀደም ባለው ዘመን ስለ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንነትና ባሕል የሚፅፉ የነበሩት የውጭ ሀገር ዜጐች ነበሩ። ከ40 አመታት ወዲህ ባሉት ዘመናት ደግሞ በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና የሥነ-ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ከተቋቋመ በኋላ የኢትዮጵያዊያን ድርሻ በእጅጉ እየሠፋ መጥቷል።


በዩኒቨርሲቲው ውሰጥ የተጠኑ ጥናትና ምርምሮች ከግቢው ውጭ ወጥተው ለሚመለከተው ሕዝብ ገና አልቀረቡም። ዘላለማዊ መቀመጫቸውን ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ አድርገዋል። እነዚህ ጥናትና ምርምሮች በእንዲህ አይነት የብሔረሰቦች በዓል ላይ ወጣ እያሉ ነፋስና አየር ብሎም ሠው ቢያያቸው ቢያነባቸው ጥሩ ነበር። ለነገሩ ጉዳዬ ብሎ የሚያያቸው አካል ያስፈልጋል።


የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች እንደ ብዛታቸው ሁሉ አያሌ ባሕሎች ታሪኮች ፍልስፍናዎች …. ያሏቸው ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ለዘመናት ሲጠኑ ሲመረመሩ ቆይተዋል። እነዚህ ጥናቶች ተሠብስበው በአንድ ትልቅ አርካይቨ ውስጥ አልተቀመጡም። የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መረጃ የሚሠጥ ትልቅ ሙዚየም ገና አልገነባንም። አብዛኛዎቹ የብሔረሰቦቻችን የጥናትና የምርምር ውጤቶች በውጭ ሀገራት አብያተ-መፃሕፍትና መዘክሮች ውስጥ ናቸው። ገና አልተሠበሠቡም። ስለዚህ ብዙ ስራ የሚጠበቅብን ሠዎች ነን። ለበዓሉ የሚመደበውን ገንዘብ ለእንዲህ አይነት ተግባራትም እንዲውል ማድረግ ይጠበቅብናል።


ለምሣሌ ጀርመኖች በ1919 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ፊልም ቀርፀዋል። ፊልሙን የቀረፁት ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሔደው ነው። የሔዱት ዲሜ እየተባሉ ከሚታወቁት ማሕበረሰቦች ዘንድ ነው። የሔዱበትና የቀረፁት ፊልም ደግሞ የዲሜዎችን የመአድን አወጣጥ ጥበብ ነው። ዲሜዎች መሬትን ቆፍረው ከመሬት ውስጥ ባወጡት መአድን ብረት አቅልጠውና ቅርፅ አውጥተው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን እና መገልገያ ቁሣቁሶችን እንዴት እንደሚያዘጋጁ የተቀረፀ ነው። በወቅቱ ይህ ጉዳይ ጀርመኖችን ሥቦ እዚህ ድረስ ያስመጣቸው አንድ የሚፈልጉት ጥበብ በመኖሩ ነው። ታዲያ እንዲህ አይነት የኢትዮጵያን ቅርሶች ቢያንስ ኮፒያቸው የሚገኝበትን መንገድ መፈለገ ግድ የሚሆንበት ወቅት ነው።
ከነ ግሪካዊው ሆሜር ጀምሮ ከዛሬ ሦስት ሺ አመታት በፊት የተፃፉ ቅርሦችን እየሠበሠብን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሙዚየም የመገንባት ሥራ መሠረቱ መጣል ያለበት ዘመንም ነው። ሕዳር 29 ኝን ከማክበርና ከመዘከር ባለፈ ዘላለማዊውን ሙዚየም ስለ መገንባት የምንነጋገርበትም ዘመን መሆን አለበት።


ለምሣሌ Hodson, Hronold Wienhot የተባለ ሰው Seven Years in Southern Abyssinia በሚል ርዕስ በ1919 ዓ.ም ፅፏል፤ አሣትሟል። ይህ ሰው ስለ ምን ፃፈ? ሰባት አመታት ሙሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖር ምን ታዘበ? አያሌ ነገሮችን የምናገኝበት መፅሃፍ ነው። ግን ይህን መፅሃፍ ሠብስበነዋል ወይ? አለን ወይ?ችሩሊ (Cerulli) Ernesta የተባለ ሠው በ1919 ዓ.ም ላይ Peoples of South West Ethiopia የተሰኘ መፅሃፍ አዘጋጅቶ ዛሬ በለንደን የአፍሪቃ አለማቀፍ ኢንስቱትዩት ውስጥ ይገኛል። መዘርዘር ይሆንብኛል እንጂ ሌሎችንም በርካታ መፃሕፍት፣ ፊልሞችን፣ መጠቃቀስ ይቻላል። እነዚህ ሁሉ በተለያዩ ዘዴዎች ተሠብስበው ቃላቁን ሙዚየም ለመገንባት ሃሣብ መጠንሠሻ መሆን አለባቸው።

 

ሌላው ትኩረት ሊሠጠው የሚገባው ነገር ብዬ የማስበው የቋንቋና የባሕል ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ሁሉም የሐገሪቱ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ግፊት ሲደረግ ነበር። ይህ ውሣኔም ቀላል የማይባል ክርክርና እሠጣ ገባ ያስከተለ ነበር።


በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርትን ማስተማር ጠቀሜታ እንዳለው በስፋት ቢነገርም ተፈፃሚ ለማድረግ ግን ብዙ ውጣ ውረዶች አሉት። ውጣ ውረዶቹ ምንድን ናቸው? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም።
በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስተማር ዝም ብሎ ተነስቶ የሚገባበት ጉዳይም አይደለም። በዚያ ቋንቋ ትምህርት ለማስተማር ከተፈለገ መጀመሪያ ቋንቋውን ለትምህርት ማብቃት ወይም ማሣደግ ያስፈልጋል። ትምህርት ሊሠጥበት በታሠበበት ቋንቋ መፃሕፍትና አጋዥ የሆኑ ሌሎች ሠነዶቸ ማዘጋጀት የግድ ይላል። እንደሚታወቀው ትምህርት አለማቀፋዊ ባሕሪ አለው። አያሌ የሣይንስና የቴክኖሎጂ ስያሜዎችን የያዘ ነው። እነዚህ ስያሜዎች በሙሉ ትምህርት ሊሠጥበት በታሠበበት ቋንቋ መተርጐም አለባቸው። መዝገበ ቃላት መዘጋጀት አለበት። ቋንቋው ወደ መደበኛ (Standard) ቋንቋነት ማደግ አለበት። መምህራን በሠፊው መሠልጠን አለባቸው።

 

ሌላው ነገር የትምህርቱም ግብ (Target) መታወቅ አለበት። እነዚህ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርት የሚሠጣቸው ልጆች መጨረሻቸው ምንድን ነው? የሚለውም መታየት አለበት። በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ተምረው ምን ይሆናሉ? የት ይደርሳሉ? ዕውቀት የውድድር ባሕሪም ስላለው ከሌሎች ጋር ተወዳድረውበት የተሻለ ደረጃ መድረስ ይችላሉ ወይ? በትምህርታቸው ምክንያት ሌላም ቦታ ሔደው ሊማሩበት ይችላሉ? በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርትን መስጠት እስከ ምን ድረስ ነው የሚሉት ሁሉ በዝርዝር ተጠንተው ከተለዩ በኋላ ነው ትምህርቱ ሊሠጥ የሚችለው። አንዳንድ በዚህ ርዕስ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሠዎች እንደፃፉት ከሆነ አንድ ቋንቋ ለትምህርት ማስተማሪያነት እንዲውል ለማድረግ ቢያንስ ከአስር አመታት በላይ ይወስዳል ይላሉ። ቋንቋውን ለትምህርት መስጫነት ለማድረስ ብዙ ነገሮች መሠራት ስላለባቸው ጉዳዩ በቀላሉ ዘው ተብሎ የሚገባበት እንዳልሆነ ፅፈዋል።


ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነገሩ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ውስጥ ከ25 ቋንቋዎች በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደሚሠጡ ይነገራል። እንግዲህ እዚህ ላይ ቆም ብለን አንድ ነገር እናስብ። በአሉ የጥናትና የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት በዓል መሆን አለበት። በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ሲሠጥ ምን ጠንካራ ጐን ነበረው? ምንስ ችግር ታይቷል? በቀጣይነትስ ምን መደረግ አለበት? የሚሉት ጉዳዮች በእንዲህ አይነት በዓል ላይ ጥናቶች ሊቀርቡበት ይገባል።
ለምሣሌ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጡ ክልሎች በሚያስተምሩበት ቋንቋ ምን መፃህፍት ተዘጋጁ? ስንት መዝገበ ቃላት ታተሙ? ስንት የትምህርት አጋዥ የሆኑ መፃሕፍትና ልዩ ልዩ ሰነዶች ታተሙ? ቋንቋው ፊደል አለው? ፊደል ተቀርፆለታል? የተቀረፀው ፊደል ጠንካራና ደካማ ጐኑ ምድን ነው? በቋንቋው የግጥም፣ የልቦለድ፣ የታሪክ መፃሕፍት ታትመዋል? በቋንቋው ጋዜጣና መጽሔት ይታተማል ? ፊልም ይሠራበታል? የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ኘሮግራም አለው? እነዚህና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎቸ ለውይይት መቅረብ አለባቸው። አንድ ቋንቋ ከነዚሀ ከላይ ከሠፈሩት ውስጥ በርካታዎቹን ካላሟላ ለትምህርት መስጫነት ገና አልተዘጋጀም ብሎ መናገር ይቻላል።


ሌላው በትምህርት አለም ውስጥ የወላጆች ሚናም ትልቅ ነው። ወላጆች በልጆቻቸው የትምህርት ምርጫ ላይ የወሣኝነት ሚና አላቸው። ልጄ በዚህ ቋንቋ ይማርልኝ ብለው የመምረጥ መብት አላቸው። ስለዚህ በወላጆች ምርጫስ ትምህርት የሚሠጥበት የቋንቋ አማራጭ አለ ወይ? የሚለውም መዳሠስ የሚገባው ነጥብ ነው።


ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚሠጠው መብት እንዳለ ሆኖ ከእርሱ ባልተናነሠ ሁኔታ ደግሞ የልጆቹ ወላጆችም ለአብራካቸው ክፋዮች የሚማሩበትን ቋንቋ የመምረጥ እኩል መብት እንዳላቸው ልዩ ልዩ አለማቀፋዊ ኮንቬንሽኖች ያስረዳሉ። ስለዚህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸው የሚማሩበት ቋንቋ እነሱ በመረጡበት ቋንቋ ነው ወይ? የሚለውም የመወያያ ነጥብ መሆን አለበት።


ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሠው ጥያቄ የብሔራዊ ቋንቋ (National Language) ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ የላትም። ያላት የሥራ ቋንቋ ነው። አማርኛ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ መሆኑ ነው የተፃፈው።
በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክልሎች ባሉ የአክራሪነት ባሕሪ ባላቸው ሰዎች አማርኛን የመጥላት ዝንባሌ ይታያል። አማርኛ ቋንቋ ነው። መግባቢያ ነው። ያውም ይህን ሁሉ ኢትዮጵያዊ አግባብቶ ያነጋገረ ያስተሣሠረ ቋንቋ ነው። በምንም መመዘኛ አንድ ቋንቋ አይጠላም። ግን የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናችሁ በሚል ሠበብ የተጐዱ የዚህች ሀገር ዜጐች አሉ። ይህ ጉዳታቸውም መቆም አለበት። ሀይ ብሎ የሚከለክል አካል ያስፈልጋል።


አማርኛ ቋንቋ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንደሆነ ቢገለፅም በተዘዋዋሪ መንገድ ብሔራዊ ቋንቋም እንደሆነ የሚገልፁ ሁኔታዎች አሉ። አንድን ቋንቋ ብሔራዊ ነው ሊያሰኙ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ፓርላማው ነው። ፓርላማው የሚያወራበት ቋንቋ ምንድን ነው? አዋጆች፣ ደንቦች፣ ሕጐች፣ መመሪያዎች ተፅፈው ለውይይት የሚቀርቡት በአማርኛ ቋንቋ ነው። የሐገሪቱ ኘሬዘዳንት እና ጠቅላይ ምኒስትር ለሕዝባቸው ንግግር የሚያደርጉት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ለሀገሪቱ ሕዝብ መመሪያ የሚሰጠው በአማርኛ ነው።


ብሔራዊ ቴሌቪዥኑ፣ ሬዲዮኑ፣ ጋዜጣው፣ መጽሔቱ፣ ሁሉ በአማርኛ ቋንቋ ነው። ቴአትሩ፣ ፊልሙ፣ መፃሕፍቱ ወዘተ ሁሉ በአማርኛ ቋንቋ ናቸው። ስለዚሀ አማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ነው ተብሎ ባይቀባም አገልግሎቱ ግን የብሔራዊ ቋንቋ ሚና አለው።


ስለዚሀ አንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ አድጐ የሚኖር ሠው አማርኛ ቋንቋ ካልቻለ የሚጐዳው ነገር አለ። መረጃ እንደ ልቡ ላያገኝ ይችላል። ፓርላማው ስለ ምን እያወራ መሆኑን እንኳ አለማወቅ ትልቅ ጉዳት ነው። ልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን ወክለው በፓርላማ ወንበር ይዘው ያሉ እንደራሴዎች የሚናገሩበትና የሚያነቡት ቋንቋ አማርኛ ነው። ስለዚሀ አማርኛ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ለመግባቢያነት ያስተሣሠረ ቋንቋ ነው።


ይህ ቋንቋ እንደ አገልግሎቱ ተገቢው ትኩረትና እንክብካቤ ያልተሠጠው ነው። አማርኛ ቋንቋ በዘመነ ኃይለሥላሴ ወቅት እስክ ዩኒቨርሲቲ ድረስ መደበኛ ትምህርት ሆኖ ይሠጥ ነበር። አማርኛ ለኮሌጅ ደረጃ የተሰኘ ትምህርት ነበር። አማርኛ ከእንግሊዝኛ ጋር ሆኖ በቋንቋ ትምህርትነት ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ይማረው ነበር። ይህ ሂደት በዘመነ ደርግ የተወሰነ ሂደት ኖሮት ሣለ በኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቶችን ሁሉ በአማርኛ ቋንቋ የማድረግ እቅድ ነበር።


አማርኛ ቋንቋ በጣም አድገዋል ከሚባሉ ቋንቋዎች ምድብ ውስጥ ነው። የቋንቋ እድገቱ የሚለካው ምን ያህል ጥናትና ምርምር ተደርጐበታል? ምንስ ያህል ተናጋሪዎች አሉት? በቋንቋው መፃሕፍት ይታተማሉ? ግጥሙ፣ ሥነ -ፅሁፉ ልቦለዱ፣ ቴአትሩ፣ ፊልሙ ወዘተ በዚህ ቋንቋ ይዘጋጃል? ጋዜጣው፣ መጽሔቱ፣ ሬዲዮኑ፣ ቴሌቪዥኑ ወዘተ ምን ያህል በቋንቋው ይዘጋጃሉ የሚለው ነጥብ የአንድን ቋንቋ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚያሣዩ ናቸው።


አማርኛ ቋንቋ የራሱ ፊደል ባይኖረውም ፊደል የተዋሠው ከግዕዝ ቋንቋ ነው። የግፅዝን ፊደላት ወስዶ የራሱን የተወሠኑ ፊደላት ጨማምሮ ሀገራዊ ወዝና ደርዝ ይዞ የተነሣ ነው። በዚህ ረገድ ትግርኛ' ጉራግኛ፣ አደርኛ፣ አርጐብኛ ብሎም የኤርትራው ትግርኛ ቋንቋዎች ፊደላቸውን የተዋሡት ከግዕዝ ነው። እነዚህ ቋንቋዎች የአንድ ቤተሠብ ቅርንጫፎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም ሴሜቲክ በሚባለው የቋንቋ ምድብ ውስጥ ናቸው። ግን ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የላቲን ፊደላትን ሙሉ በሙሉ ከሚጠቀሙ የግዕዙን ፊደል ቢዋሡ ጥሩ ነበር በማለት አስተያየት የሚሠጡ የዘርፉ ባለሙያዎቸ አያሌ ናቸው።


በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለፅሕፈት (Orthography) የሚጠቀሙበት የላቲን ፊደልን ነው። እዚህ ውሣኔ ላይ እንዴት ተደረሰ ብለው የሚሞገቱ አሉ። የላቲን ፊደልን ለመጠቀም ምን አይነት ጥናትና ምርምር ተደርጐበት ነው ለውሣኔ ተደረሶ ተፈፃሚ እንዲሆን የተደረገው? የቋንቋ ምሁራንና አጥኚዎች ተሣትፈውበታል ወይ? የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው። የላቲን ፊደልን መጠቀም ጥቅሙና ጉዳቱ ታይቷል? ያስከተለው ችግር ምንድን ነው? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች አሁንም መወያየት ያስፈልጋል።


የላቲን ፊደላት ከነ አናባቢ (Vowels) ጋር ስለሚፃፉ ብዛት እንዳላቸው ይታወቃል። የግዕዝ ፊደላት ደግሞ አናባቢዎችን በውስጣቸው ይዘው ስለሚፃፉ እጥር ምጥን ይላሉ። ስለዚህ ከጊዜም አንፃር ከቦታ ቁጠባ አንፃር የላቲን ፊደላት ችግር እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ይገለፃል። ታዲያ መቼ ነው በግልፅ ተነጋግረን ያሉትን ችግሮች የምንቀርፈው? እንዲህ አይነት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሲከበር ከላይ ባነሣኋቸው ርዕስ ጉዳዮች ላይ መነጋገርና የመፍትሔ ሃሣቦችን ማምጣት ይገባል።


ሌላው እየጠፉ በመምጣት ላይ ያሉ ቋንቋዎቸ ጉዳይም ትኩረት ሊሠጠው ይገባል። የቋንቋ ሞት (Language Death) የሚባል ጉዳይም አለ። የቋንቋ ሞት በልዩ ልዩ ምከንያቶች ይከሠታል። በዋናነት ግን በተደጋጋሚ የሚታየው ችግር የቋንቋው ተናጋሪዎች ቋንቋቸውን እየተው አጠገባቸው ያለውን ሌላ ቋንቋ በመናር (Language Shift) በመፈጠሩ ሣቢያ ነው። ከዚህ አንፃር በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ያሉትን የኦንጐታ ብሔረሰብ አባላትን ጉዳይ ማንሣት ይቻላል።


ኦንጐታዎቸ ቋንቋቸው በሞት አፋፍ ላይ ያለ፤ በቋንቋ አዋቂዎቸ ዘንድ ሞቷል ተብሎ የሚገመት ነው። ምክንያቱም ከቋንቋው ተናጋሪዎች ውስጥ የቀሩት ስድስት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሌሎቹ የዚህ ብሔረሰብ አባላት ቋንቋቸውን ወደ ፀማኮ ቀይረዋል። የእነዚህን የቀሩትን ስድስት ስዎች ኢጣሊያዊው የቋንቋ ሊቅ ኘሮፌሰር ግራዚያኖ ሣቫ ወደ አዲስ አበባ ይዟቸው መጥቶ ሁለት ቀን ሙሉ ድምፃቸውና ዘፈናቸውን ስንቀርፅ ውለን አድረናል። ኘሮፎሰር ግራዚያኖ እንዲህ ያደረገበት ምክንያት እነዚህ የቀሩት ስድስት ሠዎች ከሞቱ ሙሉ በሙሉ ቋንቋው ስለማይኖር ከዚያ በፊት ዶክመንት ላድርገው ብሎ ነው። ኘሮፌሰር ግራዚያኖ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ (Documentary Linguistics and Culture ) የተሠኘው የትምህርት ክፍል ውስጥ መምህር ነበር። ዛሬ ኑሮውን ወደ መጣበት አውሮፓ አድርጓል። በነገራችን ላይ ኘሮፌሰሩ የዶክተሬት ድግሪውን የሰራው በፀማኮ ቋንቋ ላይ ነው።


እንደ ኦንጐታ ቋንቋ ሁሉ ጥንታዊው ግዕዝም በከፍተኛ የሞት ጠርዝ ላይ ሆኖ ቆይቶ ነበር። አሁን አሁን ግን ሕክምና እያገኘ ግዕዝ የመተንፈስ ደረጃ ላይ እየመጣ ነው። በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋዎች ጥናት ክፍል ለግዕዝ ቋንቋ ሕመም ማስታገሻ እየሠጠው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን በተለይም ማሕበረ ቅዱሣን በመምህር ደሴ ቀለብ ሀኪምነት ግዕዝን እየፈወሡት ይገኛሉ። ግዕዝ ማገገም ጀምሯል። የኦንጐታ ቋንቋም መታከም ቢጀምር ከሞት ጠርዝ ላይ ማውረድ ይቻል ነበር። ሌሎችም በርካታ ቋንቋዎች አሉ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው።


በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባሕሎች ላይ አያሌ ሰዎችና ተቋማት ሥራ ሠርተዋል። ከአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብንነሣ እነ ኘሮፌሰር ባየ ይማም፣ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ ዶ/ር ዘላለም ልየው እና ሌሎችም በርካታ ምሁራን አያሌ አበርክቶዎች አሏቸው። የሠሯቸው ስራዎች መታተምና መሠራጨት አለባቸው።


ኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ ፅፋ ወደፊት ይፋ ታደርገዋለች የሚባል ጉዳይም አለ። ፖሊሲው ተረቋል። አሁን ያነሣኋቸው ጉዳዮች ሁሉ በፖሊሲው ውስጥ ተካተው መፍትሔ ያገኛሉ የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።
በተረፈ ለሁልም የኢትየጵያ ብሔረሰቦች መልካም በዓል እመኝላቸዋለሁ።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11739 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us