“የማይፋቅ መርገምት አለብን!”

Wednesday, 16 December 2015 13:24

 

በጥበቡ በለጠ

የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔና ቀደምትነት እያስታወሰ የሚቆረቆር ንድ ባለቅኔ ነበር። እሱም ኃይሉ ገብረዮሀንስ/ ገሞራው/ ነው። ስርአተ ቀብሩ የዛሬ አመት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመው ይህ ድንቅ ባለቅኔ 40 አመታት በሙሉ በስደት ተንከራትቶ ያለፈ ከያኒ ነው። እሱን መሰል ጓደኞቹ ተሰደው ሲንከራተቱ ሲያይ፤ ኢትዮጵያ ሁሌም ከድርቅና ከችጋር ጋር ስሟ ሲጠራ ሲሰማ፤ ከእርዳታና ከተመጽዋችነት አልወጣ ብላ በየአመቱ በልግስና ስትደጎም ሲያስተውል፤ መቼ ይሆን ሀገሬን የምኮራባት እያለ ሲያስብ መልስ አጣ። እናም ተስፋ ቆረጠ። ወደ ኋላ ሄዶ አሰበ። አንድ ነገር ጠረጠረ። ኢትዮጵያ ተረግማለች ብሎ ደመደመ።

ይህ ግዙፍ የስነ-ጽሁፍ ስብእና ያለው ባለቅኔ እንዴት በእርግማን አመነ? የማናድገው እርግማን ስላለብን ነው ብሎ ካመነ መፍትሄው ምንድን ነው? ጉዳዩን እናስብበት። ግን ለመሆኑ ማን ነው የረገመን? እነማን ናቸው መርገምት የለቀቁብን? ባለቅኔው ኃይሉ ገ/ዮሀንስ /ገሞራው/ እኛ ኢትዮጵያዊያንን ማን እንደረገመን ከአስር አመታት በፊት ገልጾት ነበር። ገሞራው ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፡-

 

 

“….አበው እንደሰጡኝ ምላሽ ከሆነ “የማይፋቅ መርገምት አለብን!” የሚል ነው። የወረደብንን መርገምትም ምንነት ሲያብራሩ ከባለፈው ምእተ አመት መገባደጃ ምዕራፍ ዘመን ላይ ይጀምራሉ። ከነገስታቱ የነ አፄ ቴዎድሮስ አርግማን፤ የነ አፄ ዮሐንስ፤ የነ አፄ ምኒልክ፤ የነ አፄ ኃይለ ስላሴ፤ ከሕዝባውያኑ ደግሞ የነ አቡነ ጴጥርስ፤ የነ በላይ ዘለቀ፤ የነ መንግስቱ ነዋይ እርግማን ይጠቅሳሉ። ቴዎድሮስ ሐገር አንድ ላድርግ ብሎ ቢነሳ ካህናት  ሳይቀሩ በመስዋዕት ውስጥ የእባብ ጭንቅላት አድርገው ሊገድሉት እንደሞከሩና በተለይም ለመንገስ ሲሉ የራሱ ሀገር ሰው የሆኑት አፄ ዮሐንስ የጠላት ጦር /እንግሊዞችን/ መቅደላ ድረስ እየመሩ አምጥተው ሊያስገድሏቸው ሲዘጋጁ በማወቃቸው “ይችን የኢትዮጵያ ኩሩ ነፍስስ የውጭ ጠላት አይገድላትም!” ብለው፤ ራሳቸው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሊገድሉ ሲሉ፡- “ኢትዮጵያን ወንድ አይብቀልብሽ!!!”  ብለው ረግመዋታል።

 

 

ቀጥሎም ኢትዮጵያን ከመጣባት ወረራ ለማዳን ከድርቡሽ ጋር አፄ ዮሐንስ በተፋጠጡ ጊዜ የሸዋው አፄ ምኒልከና የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት ለእርዳታ እንዲደርሱላቸው ጠይቀው ባለመምጣቸቸው የጦርነቱ አውድ ገብተው አንገታቸው ተቆርጦ ከመሞታቸው በፊት፤ “ኢትዮጵያ ዘር አይብቅልበሽ” ብለው ረግመዋል።

 

 

ከዚያም አፄ ምኒልክ እንደልጃቸው ያዩት የነበረውን የልጅ ልጃቸውን አቤቶ ኢያሱን ለማንገስ ፈልገው “ልጄን ተቃውሞ ለዙፋኔ የማያበቃ ቢኖር ጥቁር ውሻ ይውለድ!” ብለው በመርገማቸው ያው እንዳየነው ንጉስ ተፈሪ ኢያሱን ገድለው ዙፋኑን ቢወርሱ ያን ፋደት የደርግ ጥቁር ውሻ ወልደው አንድ ንፁህ ትውልድ አስበሉ።

 

 

ራሳቸው ንጉስ ኃይለስላሴም በተራቸው ከሞቀ ዙፋናቸው ወርደው 4ኛ ክፍለ ጦር ታስረው ሳሉ ምግብ ተመግበው ከጨረሱ በኋላ ታጥበው ፎጣ ለማድረቂያ ሲሰጣቸው እምቢ ብለው ጣቶቻቸውን ወደ ታች አድርገው የታጠቡበትን ውሃ እያንጠባጠቡ “ይህን አስተምሬው የከዳኝን ትውልድ ደሙን እንዲህ አንጠብጥብልኝ..!” እያሉ መርገማቸውን ያየ የሰፈሬ ሰው በደብዳቤ ገልፆልኛል።

 

 

እንዲሁም አባት ጴጥሮስ ለጠላት ጣልያን የሚገዛ ውጉዝ ይሁን! መሬቱም ሾክ አሜከላ ታብቅል! ብለው ሊረሸኑ አቅራቢያ ረግመዋል። በላይ ዘለቀም መስቀያው አጠገብ እንዳለ “አንቺ ሀገር! ወንድ አይውጣብሽ!” ብሎ ተራግሟል። ጀኔራል መንግስቱም ከተሰቀለበት የተክለሃይማኖት አደባባይ ላይ ሕዝብ እየሰማው “አንቺ አገር..” ብሎ በማማረር ተራግሞ አልፏል። ወዘተ

 

እንግዲህ እኛ የዛሬዎቹ ይህ ሁሉ የግፍና የደይን የፍዳና የመከራ የመቅሰፍትና የመአት ማዕበልና ናዳ የሚወርድብን ያን ሁሉ እርግማን ቆጥሮብን ይሆን?

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
11767 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us