ነብዩ መሐመድ እና ኢትዮጵያ

Thursday, 24 December 2015 11:08

 

በጥበቡ በለጠ

ዛሬ የታላቁ የነብዩ መሐመድ ልደት ነው። ይህ የልደት ቀን በመላው ዓለም ያሉ የሙስሊም እምነት ተከታች በሙሉ ማለት ይቻላል የሚያከብሩት ነው። በመካከለኛው ምስራቅ ከምን ግዜውም በተለየ መልኩ ሰላም የታጣበት ወቅት በመሆኑ በርካታ የሙስሊም ኃይማኖት ተከታዮች ችግር ውስጥ ናቸው። ከአፍሪካዊቷ ሐገር ከሊቢያ ብንነሣ ማሊ፤ ናይጄሪያ፤ ሶማሌያ፤ ግብፅን አክለን ወደ የመን፤ ሶርያ፤ ኢራቅ እያልን በርካታ ሀገራትን እና ሕዝቦችን ብናነሣ በአያሌ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀዋል። እናም የዘንድሮው በዓል ብዙ የሚፀለይበት ሰላም በምድሪቱ ላይ እንዲሰፍን ፈጣሪ የሚለመንበትም ወቅት ሊሆን አንደሚችል ይገመታል።

የነብዩ መሐመድ ስም እና ታሪክ በተነሣ ቁጥር የኢትዮጵያ ስም እና ታሪክም አብሮ ብቅ ማለቱ አይቀርም። የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያወሣው ነብዩ በሕፃንነታቸው እናታቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ሞግዚቶች ተቀጥረውላቸው ነበር። ከነዚህ ሞግዚቶች መካከል ለነብዩ ቅርብ የነበሩት ኢትዮጵያዊቷ እሙአይመን ነበሩ። ኢትዮጵያዊቷ እሙአይመን ከአክሱም አካባቢ ወደ መካ ሔደው ነብዩን ጡት ሁሉ እያጠቡ ያሣደጓቸው እንደነበር በርካታ የታሪክ ፀሐፍት ገልፀዋል።

አቶ አማረ አፈለ ብሻው የተባሉ ፀሐፊ ኢትዮጵያ የሰው ዘር የተገኘባት የእምነትና የሥልጣኔ ምንጭ ናት በተሰኘው መፅሃፋቸው ውስጥ ይሕን ጉዳይ በተመለከተ በርካታ መረጃዎችን ሰብስበው አሣትመዋል። እንደርሣቸው አባባል ነብዩ መሐመድ ጡት አጥብተው ካሣደጓቸው ከእሙ አይመን ሌላም ከበርካታ ኢትዮጵያዊያን ጋር ወዳጅነት እንደነበራቸው እየዘረዘሩ ፅፈዋል።

ኧሰት የባሕልና የታሪክ መሠረት በተሰኘው መፅሃፍ ውስጥ ነብዩ በሕፃንነታቸው ከእናታቸው ጡት በተጨማሪ ጡትዋን አጥብታ ያሣደገቻቸው አሙአይመን ከኢትዮጵያ ሐበሻ ወደ አረብ የተወሰደች ኢትዮጵያዊት ናት ሲል በገፅ 226 ላይ መፃፉ ይታወቃል። ይህንኑ አባባል የኢትዮጵያዊነት የታሪክ መሰረቶችና መሣሪያዎችእስልምና እና የታላቁ ነብይ የመሐመድ ታሪክ የተሠኙትም መፃሕፍት አስረግጠው ያስረዳሉ።

ነብዩ መሐመድ በኚሁ አሣዳጊያቸው አማካይነት ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቋንቋ የነበረውን የግዕዝ ቋንቋን ይናገሩ ነበር ተብሎም ተፅፏል። ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በሕፃንነታቸው ጀምሮ ሲሠሙ እንዳደጉ ይነገራል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን አጥብቀው ይወዱ ነበር። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊቷ እሙአይመን የቀድሞ ስማቸው ባሕሯ እየተባለ ይጠራ ነበር።

የእስልምናን ሐይማኖት በአለም ላይ እንዲስፋፋ ካደረጉት አካላት መካከል ኢትዮጵያዊያን ግንባር ቀደም ቦታ ይይዛሉ የሚሉ ፀሐፍት አሉ።

ነብዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና በተሠደዱበት ወቅት /ሂጃራ/ ከተከተሏቸው ጠንካራ የእስልምና እምነት ከተከታዮች አንዱ ኢትዮጵያዊው ቢላል ነበር። አንድ ቀን ነብዩ መሐመድ ከጥቂት ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዕለታዊ ተግባራቸውን ለማከናወን ሲዘዋወሩ ድንገት የሆነ ደስ የሚል ድምፅ ከጆሮዋቸው ጥልቅ ይላል። ድምፁ ወደ መነጨበት አካባቢ ነበረና የሚጓዙት የበለጠ ሣባቸው። ከዚያም ስለ ቢላል  ጠይቀው ተረዱ። ድምፀ መረዋውን ቢላል ተዋወቁት። እርሡም ወደዳቸው። አብሯቸውም ሆነ።

የሶላት/የፀሎት/ ሰዓት ሲደርስ አዛን ማሠማት የተጀመረው በኢትዮጵያዊው ቢላል ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ አላህ ዋአክበር…. ብሎ ሶላት ያሰማ ኢትዮጵያዊ ቢላል። እስልምናን ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ ያወጀው ኢትዮጵያዊው ቢላል ነው። የጥንት ስሙ በላይ ነው እየተባለ በፀሐፍት ተገልጧል። ስለዚህ እስልምናን ከፍ አድርጐ በአለም ላይ በማወጅ በመጥራት ቢላልን ማን ሊስተካከለው።

ከነብዩ መሐመድ ዘንድ ቢላልም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ከጐናቸው ነበሩ። አብረዋቸው እስልምናን አስፋፍተዋል። ነብዩ ከሌሎች ወገኖች የሚደርስባቸው ጥቃት ለመቋቋም ቤተሰቦቻቸውን የላኩት ወደ ኢትዮጵያ ነበር። “ጥሩ ንጉስ አለ፤ በእሡ ግዛት ሠላም ነው፤ ክፉ አይነካችሁም” ብለው ልጃቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ። ዛሬ ትግራይ ውስጥ ያለው አልነጃሺ የተሰኘው መስኪድ በዚያን ዘመን የተመሠረተ ነው። የነብዩ ቤተሠቦች የነበሩበት ቦታ ነው። የቀብር ቦታቸው ሁሉ በዚሁ መስኪድ ውስጥ ተጠብቆ ይኖራል። መስኪዱን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሠፋ ያለ የፊልም ቀረፃ አድርጌበት ነበር። ታሪኩ እንደሚያስረዳው በአለማችን ላይ ካሉ ቀደምት መስኪዶች መካከል አንዱ ነው። ግን የማስተዋወቅ ሥራ አልተሠራለትም።

ነብዩ መሐመድ ኢትዮጵያን ማንም እንዳይነካት እንዳይተናኮላት እንዲወዳት የተናገሩ እና የፃፉ ናቸው። የእስልምናን ኃይማኖት የሚከተሉ ሁሉ የእርሣቸውን ቃል እንዲተገብሩ ግዝት አለ። ቃል አለ።

በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ የክርስትናውንም ሆነ የእስልምናውን ኃይማኖት አስቀድማ በመቀበልና በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ታሪክ ያላት ነች። ነገር ግን ሐይማኖት በዚህች ሀገር ውስጥ የሚዲያ ነፃነት ስለሌለው በየጊዜው ሊሠራበት አልቻለም። የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሐይማኖቶች የሬዲዮ ጣቢያ፤ የቴሌቪዥን ጣቢዎች መኖር አለባቸው። በነዚህ ተቋማት ልክ በአረቡ አለም እና በሌላው የክርስትያን አለም እንደሚደረገው ሁሉ ኃይማኖቶቹን የማስተዋወቁ ተግባር እየተስፋፋ ይመጣ ነበር። ወደፊት የራሣቸው የሚዲያ ተቋማት ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለማንኛውም መልካም የመውሊድ በአል እንዲሆንላችሁ ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ወገኖቼ እመኝላችኋለሁ።

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
11000 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us