የኃይማኖት ትምሕርቶች በEBS ቴሌቪዥን

Thursday, 24 December 2015 11:13

 

በጥበቡ በለጠ

በኢትዮጵያ ውስጥ ኃይማኖቶች ረጅም እድሜ አስቆጥረዋል፤ ከአለም ሀገራትም ኃይማኖት የተሰበከባት ጥንታዊት ሐገር እያልን ብንጠራትም ሐይማኖትን ግን በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን መስበክ አልተፈቀደላትም። በኢትዮጵያ የሚዲያ ሕግ የሐይማኖት ስብከት እና ትምሕርት በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን አልተፈቀደም። ያልተፈቀደበት ምክንያት የራሱ የሆነ ዝርዝር መልሶች ሊኖሩት ይላሉ። በዋናነት ግን ሐይማኖት ስሡ (Sensitive)  የሆነ ተቋም ስለሆነ በቀላሉ የሰውን ልጅ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ የመቀስቀስ ባሕሪ ስላለው ጥንቃቄ ሊወሠድበት እንደሚገባ ከ15 አመታት በፊት የብሮድካስት ሕግ ሲረቀቅ ይነገር ነበር። ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ሚዲያ በተለይ በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ሐይማኖትን መስበክ ሲከለከል የሐይማኖት ተቋማቱ ዝም አላሉም። ሌላ አማራጭ ፈለጉ። ይህ አማራጭ ደግሞ ከውጭ ሀገር ሆነው ወደ ሐገር ውስጥ ሐይማኖታዊ ጉዳዮችን ማሰራጨትን ዋናው መፍትሔ አድርገው ወስደውታል።

በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ሌላ አማራጭ ሆኖ እያገለገለ ያለው EBS የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። EBS በተለይ ለመካከለኛው እና ለከፍተኛው የኑሮ ጣሪያ ላይ ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ ጥሩ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። ለመካከለኛው ኑሮ ውስጥ ላሉት የተለያዩ ትምሕርታዊ እና የመዝናኛ ኘሮግራሞችን ያቀርባል። ቶክ ሾው፤ የኃይማኖት ስብከቶችና ፍልስፍናዎች ኪነ-ጥበባት እና የመሣሠሉትን መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ (Middle Class Communities) ያቀርባል።

የከፍተኛ ጣሪያ ላይ ላሉ  የገቢ ምንጫቸው ንሮ የልጆቻቸውን ልደት በቴሌቪዥን ለሚያቀርቡት ኢትዮጵያዊያንም ያገለግላል። የሀብታም ልጆችን የኑሮ ጣሪያም ያሣየናል። ከአርባ አመታት በፊት ንጉስ ኃይለሥላሴ ልደታቸውን 80 ሻማ አብርተው ኬክ ቆርሰው አከበሩ ብሎ ያ-ትውልድ ከስልጣናቸው አወረዳቸው። የያ ትውልድ ልጆች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ልደታቸውን ኬክ እየቆረሱ ከእድሜያቸው በላይ ትዝታቸውን እያወጉ በቴሌቪዥን ያቀርባሉ፤ ይቀርባሉ። EBS እነዚህን የኢትዮጵያዊያንን የኑሮ ወርቅ እና ሰም ገፅታዎች እያሣየን ነው።

ግን አንድ ነገር ሁሌም ይገርመኛል። ያለፈውን ስርዓት የኮነንበት አይንህ ላፈር ብለን ከመቃብር ከከተትነው በኋላ የእሡን ድርጊት መልሰን እንቀጥለዋለን። ቁጭ ብዬ ሣስበው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያውም የመጨረሻቸውን ልደት አከበሩ ተብለው ሕዝብ በድርቅ እየተሠደደ እና እየሞተ እርሣቸው ልደት ያከብራሉ እየተባሉ ሲወቀሡ ቆይተዋል። ከዚያም ይሕች ምክንያት ሆነችና ሌባ ተብለው ከመንበረ ሥልጣናቸው ወርደው ተገደሉ። ልደትን ማክበር ዛሬ በቴሌቪዥን እየተላለፈ ነው። ዛሬም ኢትዮጵያ በድርቅ ውስጥ ነች። ሰዎች ችጋር አጋጥሟቸዋል። የተራቡ ልጆች አሉ። ልደታቸውን ድል ባለ ድግስ የሚያቀርቡ አሉ። ሕይወት ያለፈውን መድገም ነው።

ወደ ዋናው ቁም ነገሬ እመጣለሁ ብዬ የዘመን ክፍተት ውስጥ ዋኘሁ። ቁም ነገሬ ስለ ኃይማኖት ስብከት ትምሕርትና ፍልስፍና በተለይ በ EBS ቴሌቪዥን ጣቢያ መተላለፍ ከጀመሩ ሰንበትበት ከማለታቸው አንፃር የተወሠነች ነገር ጣል ማድረግ ፈልጌ ነው።

ቀደም ሲል አንደገለፅኩት ኃይማኖታዊ ጉዳዮችን በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ማሠራጨት በሐገሪቱ ሕግ አይፈቀድም። በ EBS የሚተላለፍበት ምክንያት አንደኛ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ ከሰሜን አሜሪካ የሚመጣ በመሆኑ ይመስለኛል። ሁለተኛው ምክንያት እነዚህ የኃይማኖት ኘሮግራሞች አጫጭር ስለሆኑ እና ሁሉም የራሱ የሆነ የአየር ሰዓት ሣይዳላ ስለተሠጠው እምብዛም አጨቃጫቂ ጉዳዮች አልተከሠቱበትም። ሦስተኛው ምክንያት የሚመስለኝ የሚተላለፉት የኃይማኖት ኘሮግራሞች እርስ በርሣቸው አልተጣሉም። አንዱ ሌላውን አልነቀፈም። በዚህ የተነሣ እርስ በርሣቸው ኮሽታ ሣይሠማባቸው ለተወሠኑ ጊዜያት ቆየተው ነበር።

አሁን አሁን ደግሞ ድንገት አስደንጋጭ ሁኔታዎች እየተከሠቱ ነው። ከሚተላለፉት ኘሮግራሞች ውስጥ ሦስቱ ተቋርጠዋል። እነዚህም የማሕበረ ቅዱሣኑ፤ ታኦሎጐስ እና ቃለ-አዋዲ የተሰኙት ናቸው። የተቋረጡበት ምክንያት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በተፃፈ ቅሬታ ነው። ስለ ኘሮግራሞቹ መቋረጥ ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልቀረበበትም። ለምሣሌ ምን አጠፉ? ምን ወንጀል ሠሩ? ማነው የሚያግዳቸው? በእገዳው ምክንያት የሚፈጠር ሌላ ችግርን ማነው ኃላፊነት የሚወስደው? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትንፍሽ ያለ የለም።

እንዲቋረጡ ትዕዛዝ ከተላለፈባቸው ውስጥ ሁለቱ ማለትም ታኦሎጐስ እና ቃለ-አዋዲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተቃውሞ ፊርማ ሲሠባሠብባቸው ነበር። የፊርማው ማሠባሠቢያ ኃሣብ እንደሚገልፀው እነዚህ ሁለቱ የቴሌቪዥን ኘሮግራሞች የቤተ-ክርስትያኒቱን ስርአተ-አምልኮ አይጠብቁም በሚል መንፈስ ነው።

ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ኃይማኖት ስሡ (Sensitive)  ነው። በቀላሉ ሠዎችን በብዛት ሊያንቀሣቅስ የሚችል ተቋም ነው። በብዙ መልኩ ኃይማኖት ተጠየቅ (Logic) የለውም። ጉዳዩ ማመን ነው። በብዛት ሆነው ያመኑበት እንደ ትክክል ይቆጠራል። የብዙሃን ድምፅ (Majority Vote)  አለው ኃይማኖት። ቃለ-አዋዲ እና ታኦሎጐስ የዚያ ሰለባ ሣይሆኑ አልቀሩም።

ለመሆኑ ኃይማኖት ነፃነት የለውም? ተብሎም ሊጠየቅ ይችላል። በሐገሪቱ ውስጥ የኃይማኖት ነፃነት ተፈቅዷል። ማንኛውም ሠው የፈለገውን እምነት መከተል ማቋቋም ወዘተ ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናም ሆነ እስልምና ብሎም የጁዳይዝም እምነት በዋናነት ሕጋዊ መሠረት ኖሯቸው ለበርካታ አመታት ኖረዋል። ከ1983 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ቀድሞ እንደ ባዕድ አምልኮ ይቆጠሩ የነበሩ እምነቶች ሁሉ ሕጋዊ ነፃነት ተሠጥቷቸው መንቀሣቀስ ይችላሉ።

ጥያቄው የመጣው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖት ስም ከቤተ-ክርስትያኒቱ ቀኖና እና ዶግማ ውጭ መስበክ ማስተማር ጉባኤ መምራት አይቻልም የሚለው ነው። የተቃውሞ ፊርማም የሠበሠቡት አካላት ዋነኛው ጥያቄያቸው ይሔ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለቱ ኘሮግራሞች መጀመሪያውኑ የመስበክ፤ የማስተማር፤ ጉባኤ የመምራት ኃላፊነትን የሠጠቻቸው ቤተ-ክርስትያኒቱ አይደለችም። እነርሱ ራሣቸው የቤተ-ክርስትያኒቱ ልጆች ነን፤ በእሷ አስተምህሮት ያደግን ነን፤ ብለው የራሣቸውን መንገድ የተከተሉ ናቸው። ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ ከሌላ የእምነት ተቋም ምድብ ውስጥ ያስገቧቸዋል።

የዚያ መወነጃጀል ትርፉ ምንድን ነው? በመወነጃጀሉ መካከል ምን ይፈጠራል? ማን ይጐዳል? ትርፍና ኪሣራው ተሠልቷል ወይ?

የመወነጃጀሉ ፍፃሜ በቤተ-ክርስትያኒቱ ውስጥ ሕጋዊ ተቋም የነበረውን የማሕበረ ቅዱሣንን የቴሌቪዥን ኘሮግራም ጨምሮ ቃለ አዋዲ እና ታኦሎጐስ የተሠኙት ኘሮግራሞች ሁሉም እንዲቋረጡ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያንም ከስንትና ስንት አመታት በኋላ ያገኘችውን የቴሌቪዥን ስርጭት ተዘጋባት። የቤተ-ክርስትያኒቱ ተከታዮች የሚከታተሉትን ኘሮግራሞች አጡ። ሰአቱ ባዶ ሆነ።

በአንፃሩ ደግሞ የሌሎቹ ኃይማኖቶች የቴሌቪዥን ስርጭት እንደቀጠለ ነው። በልዩ ልዩ የኘሮቴስታንት ኃይማኖት ተቋማት እና አብያተ-ክርስትያናት የቴሌቪዥን ኘሮግራሞች እየቀረቡ ነው። ኦርቶዶክስ በፀብ እና በንትርክ ዝግትግት ስትል ሌሎቹ ደግሞ እየደማመቁ ነው። ቴሌቪዥን ጣቢያው EBS ሚዛናዊነት ባጣው በዚህ ጉዳይ የተቸገረ ይመስላል። ምክንያቱም የአየር ሰአቱን በተመለከተ የተፈጠረውን ችግር እየፃፈ መግለጫ ይሠጣል።

በኃይማኖት ውስጥ ትርፍና ኪሣራ የለም እስካልተባለ ድረስ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች እየተጐዱ ነው። በአያሌው ኦርቶዶክሶዋዊ መረጃዎች የዳበረው የማሕበረ ቅዱሣን የቴሌቪዥን ኘርግራም በመታገዱም ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ወጣቶች ከአንድ የኃይማኖት ተቋም ብቻ የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ኘሮግራሞችን እንዲከታተሉ ግድ ሆኖባቸዋል። የኃይማኖት ሜዳው ተመጣጣኝ አልሆነም። ለዚህ አለመመጣጠን ተጠያቂው ማን ነው?

ለመሆኑ የእነዚህ የቴሌቪዥን ኘሮግራሞች እንዲቋረጡ ለምን ተወሠነ? ጥፋታቸው ወደ ብሮድካስት ኤጀንሲ ሔዶ ታይቶ ነው  የፀደቀው? ማን ነው ጥፋተኝነታቸውን ያረጋገጠው? ቤተ-ክርስትያንን፤ ሀይማኖትን፤ አማኒያኑን እና አማኒያቱን የጐዳ ምን ድርጊት ፈፀሙ? የነዚህ ኘሮግራሞች መኖር ወይስ መዘጋት ነው የሚጠቅመው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ከዚህ ቀደም በውስጥዋ ብዙ ነገሮች እየተከሠቱ በጭቅጭቅ እና በንትርክ አያሌ ነገሮች አልፈዋል። ለምሣሌ የቀድሞው ፓትርያርክ አቡን ጳውሎስ ለምን ነጭ ልብስ ይለብሣሉ በሚል ብዙ እሠጣ-አገባ ነበር። ግን መፍትሔ ሣያገኝ አልፏል። የአቡነ ጳውሎስ ፎቶዎች በየ አብያተ-ክርስትያናቱ ሲለጠፉ ጉምጉምትዎች ተሠምተው ነበር። “ይሔ ጉዳይ ልክ አይደለም፤  የቤተ-ክርስትያኒቱን ስርዓት የጠበቀ አይደለም” የሚሉ ድምፆች ይሠሙ ነበር። ያስተናገዳቸው የለም። ፎቶዎቻቸው እስከ አሁን ድረስ ተሠቅለው ይገኛሉ። አቡነ ጳውሎስ ቦሌ መድኃኒያለም ቤተ-ክርስትያን ፊት ለፊት በሕይወት እያሉ ሐውልት ቆመላቸው ።

ለሐይማኖት መሪ ሐውልት አይቆምም፤ የቤተ-ክርስትያኒቱም ስርዓት አይደለም ተብሎ ብዙ ግር ግር ነበር። ለዚህ ግርግር መፍትሔ ተሠጥቶ ነበር። ያንን መፍትሔ እስከ አሁን ድረስ ተፈፃሚ ያደረገ የለም። በቤተ-ክርስትያኒቱ ውስጥ የሚታዩት ልዩ ልዩ ምዝበራዎች እስከ አሁን ድረስ እልባት አላገኙም። የዲያቆናት፤ የቀሣውስት፤ የጳጳሣት ስደት ከምን ግዜውም በላይ ብሷል። ቤተ-ክርስትያኒቱን በርካታ ፈተናዎች ገጥመዋታል። በነዚህ ሁሉ ችግሮች ውስጥ ያለችውን ቤተ-ክርስትያን ድምጿን እና ገፅታዋን ከቴሌቪዥን ላይ ማጥፋት ለምን አስፈለገ?

EBS ቴሌቪዥን ጣቢያ ከብሮድካስት ባለስልጣን ዘንድ ትዕዛዝ እስካልመጣለት ድረስ ቤተክርስቲያኒቱ በፃፈችው ደብዳቤ ብቻ እነዚህን ኘሮግራሞች ማቋረጠ ያለበት አይመስለኝም።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
16055 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us