ወይ አዲስ አበባ፤ ወይ . . . . . .

Wednesday, 30 December 2015 13:50

 

 

በጥበቡ በለጠ

አዲስ አበባ የፀብ መነሻ ሆና ሰነባበተች። በእሷ ሳቢያ ሰዎች ሞቱ፤ ቆሰሉ፤ ቤት ንብረታቸውን ተቃጠለ፤ ማስተር ፕላንዋ ምክንያት ሆነ ተባለ። አዲስ አበባችን ትንሽ ግራ አጋብታን ቆየች። ለመሆኑ አዲስ አበባ የማን ናት? ባለቤትዋ ማን ነው? የአፍሪካ መዲና የምንላት አዲስ አበባ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ናት ወይስ የኦሮሚያ ክልል? በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ያለው ልዩነት እና እንድነት ምንድን ነው? የኦሮሚያ ዋና ከተማ ማን ነው? የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ማን ነው? የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ልዩነት እና አንድት ምንድን ነው? አዲስ አበባ የቱጋ ያልቃል? ፊንፊኔ የቱጋ ይጀምራል? ማስተር ፕላን ለመስራት እና ለማጽደቅ ማን ነው የሚፈቅደው? ብዙ መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ። እኔም ለወሬ ምክንያት አገኘሁና ስለ አዲስ አበባ ከተማ ላወጋችሁ ነው፡-

አዲስ አበባ ዕድሜዋ 130 ዓመት እየተጠጋ መሆኑ ይነገርላታል። ግን ደግሞ እንደ ሌሎች ሀገራት ከተሞች ስትታይ ገና ልጅ ናት የሚያሰኛትም ነው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባን 130 ዓመቷ ነው ያለው ማን ነው?

ጉዳዩ ከአፄ ምኒልክ እና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ካያያዝነው በተለይ ከስሟ ጋር/ ትክክል ሊሆን ይችላል። እቴጌ ጣይቴ ስም ካወጡላት ጀምሮ አዲስ አበባ ብለው ከጠሯት ዘመን ከተነሳን ልክ ልንሆን እንችላለን። እንደዋና ከተማነትም ታስባ መገንባቷን ካነሳን ልክ ነን። ግን ከዚህ ሁሉ ነገር ወጣ ስንል ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ በታሪኳ አስገራሚ ነገር አለ።

በአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ የተጀመረው ከዛሬ አንድ ሺ ዓመት በፊት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ደግሞ ምን ተሰራና ነው ይህ ጉዳይ የመጣው ሊባል ይችላል።

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ቅድመ ታሪክ እንደሚያሳየው የአክሱም ነገስታት የነበሩት ሁለቱ ወንድማማቾች ኢዛና እና ሳይዛና በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገናና መሪዎች ነበሩ። ዛሬ አክሱም ከተማ ላይ ተገማሽረው የምናገኛቸው የጥንታዊ ስልጣኔ ማሣያዎች የሆኑት ሀውልቶች የታነፁት አብዛኛዎቹ በነዚህ ነገስታት ዘመን ነው።

በኢትዮጵያ ታሪል ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስትያን የሆነው ንጉሥ ኢዛና ነው። ከዛሬ 1600 ዓመታት በፊት። ኢዛና ክርስትያን ሲሆን የፃፈው ፅኁፍ አሁንም አክሱም ከተማ ውስጥ በድንጋይ ላይ ተቆርፆ ይታያል። እኔ ንጉስ ኢዛና ከዛሬ ጀምሮ ክርስትያን ሆኛለሁ ይላል። ድንጋይን አንድ ወረቀት እያጣጠፉ በሚፅፉ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች እጅ የተፃፈ ነው።

ታዲያ ንጉስ ኢዛና ወደ አዲስ አበባ ከዛሬ 1600 ዓመታት በፊት መጥቶ ነበር። መጥቶ የሠራው ኪነ-ሕንፃ አለ። ይህ ኪነ-ሕንጻ ዛሬ የካ ብለን በምንጠራው አካባቢ ወደ ኮቴቤ መስመር ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት ባለ መንገድ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ስሙም ዋሻው ሚካኤል ይባላል።

ይህ ኪነ-ሕንጻ የአክሱማዊያን ዘመን ጥበብ ነው። ንጉስ ኢዛና የግዛት መጠኑ ምን ያህል ሰፊ እንደነበርም ያሳያል። ይህ ኪነ-ሕንጻ በተለያዩ የኪነ-ሕንፃ ተመራማሪዎች ዘንድ በዘመነ አክሱም ስልጣኔ ወቅት እንደተሰራ ይነገራል። መንግሥታት የትምህርት የሣይንስ እና የባህል ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት አጥኚ ቡድን እያሰማራ በዓለም ቅርስነት ሊመዘግበው በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ለማንኛውም ይሄን መንደርደሪያ ያደረግነው አዲስ አበባ ከተማችን ከአፄ ምኒልክ በፊት በአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት አካባቢ የኢትዮጵያን ነገስታት ቀልብ ስባ ከአክሱም መጥተው ኪነ-ሕንፃ ያቆሙባት ምድር ነች። በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት እነማን ይሆኑ? በዚያን ወቅት ተቃውሞ ይኖር ይሆን? በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የታሪክ ዲፓርትመንታችን ምን ፅፎ ይሆን?

ከ1500 ዓመታት በኋላ አፄ ምኒልክ የእንጦጦ ማርያምን ቤተ-ክርስትያን አሰርተው አጠናቀቁ። ከዚያም ሰፊ ድግስ ተደርጎ የምረቃ ሥነሥርዓት ተከናውኗል። በዚህ የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ ንጉሱ ንግግር አድርገው ነው። ፀሐፊ ትዕዛዛቸው ገብረስላሴ እንደፃፉት ከሆነ ምኒሊክ ሲናገሩ ዛሬ የመረቅነው ቦታ የአያት የቅድመ አያቶቻችን መኖሪያ የነበረው ግዛት ነው ማለታቸው ይታወቃል። ይህ ማለት እንጦጦም ሆነች አዲስ አበባ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነገስታት የትኩረት አቅጣጫ ቦታ መሆኗን ነው። ስለዚህ የአዲስ አበባን ዕድሜ ስንቆጥር የኋላ ታሪኳንም ማስታወስ ግድ ነው። ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሣይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO/ የካ የሚገኘው ዋሻ ሚካኤልን በቅርስነት ቢመዘግብ የከተማዋ ዕድሜ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ አይቆጠርም። ወደ 1600 ዓመታት ከፍ ተብሎም የአዲስ አበባ ታሪክ መነገር ይጀምራል።

ከዚህ ሌላ አዲስ አበባ ብዙ የአርጂዮሎጂ ምርምርና ጥናትም የሚያስፈልጋትም ከተማ ነች። በምሳሌ የረር ተብሎ በሚታወቀው የአዲስ አበባ ክፍል መሬት ውስጥ የተቀበሩ ታቦታት፣ የቤተክርስቲያን መገልገያ እቃዎች የቀሳውስት አጽሞች ወዘተ ተገኝተዋል። በባለሙያዎች አስተያየት እነዚህ ግኝቶች ወደ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከወደምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የተነሳው ግራኝ  አሕመድ ጦርነቱን እየገፋ ሲመጣ ቀሳውስት ከአብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ንብረቶች ጋር እንደሸሹና በየዋሻውም እንደተሸሸጉ ጥናቶች ያሳያሉ። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የረር አካባቢ የተገኙትም የቤ-ክርስትያን መገልገያዎች የዚያ ዘመን የጦርነት ውጤቶች እንደሆኑ ይገምታሉ። ስለዚህ አዲስ አበባ ከተማ ቀደምት ታሪክ በመቶ ዓመት ውስጥ ብቻ የሚጠራ ሳይሆን መርማሪ ካገኝ ብዙ የታሪክ ሀቆች እንደሚኖሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ።

የረር የሚባለው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኘው ተራራም በውስጡ በርካታ እና አዳዲስ ግኝቶች በቅርቡ ይሰጡናል ብለን እንገምታለን። በአጠቃላይ አዲስ አበባ እንደ ዋና ከተማነት ወደ 130 ዓመታት ብታስቆጥርም በውስጧ ግን በሺ ዓመት የሚቆጠሩ ታሪካዊ ቅርሶች ያሏት ነች።

እናም የአዲስ አበባ ኦርጂናል ሰፋሪዎች እነማን ናቸው? አዲስ አበባን እድሜዋን ከየት ጀምረን እንቁጠረው? ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ተነስተን እንቁጠር ወይስ ከዚያ በፊት? ወይስ ከአፄ ምኒልክ ዘመን?

ለአንድ የሀመር ብሔረሰብ አዲስ አበባ ምኑ ናት? ለአንድ የዳሰነች ብሔሰብ አባልስ? ለአንድ አማራስ? ለአንድ ትግሬስ? ለአንድ ኦሮሞስ? አዲስ አበባ የማን ናት? ይህን ጉዳይ ብዙ ሳናስቀምጠው ቶሎ ብለን መልሡን ሠርተን ማሳረም አለብን። ወደፊትም የግጭት መንስኤ መሆን የለበትም።

ይህን ካልኩ ዘንዳ እስከ ዛሬ እስኪ ዛሬ ዘመናዊት ናት ስለምትባለው አዲስ አበባ ድንገተኛ እድገት እና ስልጣኔ በተመለከተ የተወሰኑ ነገሮችን እንጨዋወት፡-

አለቃዬ አንድ ቀን እንዲህ አለኝ። “እስኪ ስለ አዲስ አበባ የኮንስትራክሽን ታሪክ አንድ መጣጥፍ ለአንባቢዎቻችን ብታቀርብላቸው ምን ይመስልሃል?” ሲል ሀሳብ አቀረበልኝ። እኔም ነገሩ ቀላል ነው በማለት እሺ አልኩት። ወደ ስራዬ ለመግባት የተለያዩ ሰነዶችን ማገላበጥ ነበረብኝ። ነገሩ ከጠበኩት በላይ ከባድ ሆኖብኝ ሰነበተ። ዋናው ማነቆ የሆነብኝ የተለያዩ የጥናት ጽኁፎችና መጻሕፍትን ለማግኘት አዳጋች ነበር። የተቀናበረ የመረጃ መሰነጃ /Archive Centre/ ስለሌለን በአንድ ጊዜ ሁሉንም ጉዳይ ማግኘት የማንችል ህዝቦች ነን። ከሌሎች ሀገሮችም የሚለየን ይሄ ነው። ብቻ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የቤ-መፃህፍት ሰራተኞ ምስጋና ይግባቸውና ዛሬ የማጫውታችሁን ታሪካችንን እንድንፅፍ ብዙ ተባብረውኛል። አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ደግሞ ለተለያዩ ጥያቄዎቼ መልስ ስለሰጠኝ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ጎዶሎነቴን የሞላልኝ ታታሪ ባለሙያ ነው። እናም እስኪ እንጨዋወት።

መቼም ሀገራችን ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ታሪክ ሲነሳ በታሪክ ውስጥ ከፊት የምትሰለፍ ናት። የሚገርመው ደግሞ ድህነቱም ሲነሳ መጥታ ከፊት ትሰለፋለች። የሚያበሸቀው ድህነቱ እኛ አሁን በሕይወት ያለነው ትውልዶች ባለንበት ወቅት በመሆኑ ነው። ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን እያልን ነው። ቶሎ ብናደርገው ጥሩ ነበር። እስኪ ለዛሬ ድህነቱን እንተወውና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሳለፍናቸውን የታሪክ ክስተቶች እንጨዋወት።

ታሪክ ስንናገር ሁል ጊዜ ከመጀመሪያው ዘመን መጀመር የለብንም። የአክሱምን፣ የላሊበላን፣ የጎንደርን አንስተን ማውጋት አይጠበቅብንም። እነዚህን የኪነ-ህንፃ ልዩ ጥበቦች፣ ዓለም ሁሉ አክብሮ የተቀበላቸው ናቸውና ለጊዜው ስለ እነርሱም እናንሳ። ይልቅ ከመቶ ዓመት በፊት ስለተቆረቆረችው አዲስ አበባ የግንባታ ታሪኳን እናውጋ፡፤

አዲስ አበባ ስትነሳ አፄ ምኒልክ አብረው ብቅ ይላሉ። ዛሬ በሕይወት የሌለው ድንቅዬ ጋዜጠኛ እና ታሪክ ፀሐፊ የነበረው ጳውሎስ ኞኞ በአንድ ወቅት ሰዎች እንዲህ አሉት። “ጋሽ ጳውሎስ፣ አንተ ስትፅፍም ስትናገርም አፄ ምኒልክን ሳትጠቅስ አታልፍም” ይሉታል። እርሱም ሲመልስ፣ “ምን ላድርግ ብላችሁ ነው፤ እኔ አንድ ነገር ልፅፍ ወይም ልናገር ስነሳ ከኔ በፊት አፄ ምኒልክ በጉዳዩ ላይ ብዙ ነገር አድርገው አገኛለሁ፤ ወድጄ አይደለም፤ ምኒልክ እጃቸው ያልገባበት ስልጣኔ የለም” ብሏል። ጳውሎስ እንደተናገረው ስለ ኮንስትራክሽንም ስናነሳ አፄ ምኒልክ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

በእኛ የዘመን አቆጣጠር በ1966 ዓ.ም፤ በፈረንጆቹ ደግሞ በ1974 ዓ.ም የወጣው “ላሴቴማና ኢንግሚስቲካ” የተባለው የኢጣሊያ መፅሔት በ44ኛ ዓመት ቁጥር 2258 ላይ “የማይታመኑ እውነቶች” በሚል ርዕስ ስለ አፄ ምኒልክ ጽሁፍ አቅርቦ ነበር። ፅኁፉ በካርቱን ፎቶ የተደገፈ ነው። ካርቱኑ የሚያሳየው አፄ ምኒልክ ከፊታቸው ያለውን ረጅም ድልድይ በእጃቸው መትተው ሲሰብሩት ነው። ስዕሉ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም፤ ጽሑፉ የሚከተሉትን ሀሳብ የያዘ ነው።

አፄ ምኒልክ የተባሉት የኢትዮጵያ መሪ አንድ የተሰራን ድልድይ እ.ኤ.አ. በ1902 በእጃቸው መትተው ሰበሩት። ከዚያም ለመሀንዲሶቹ ይሄ ቀሽም ድልድይ ነው አሉ። ሌላ ድልድይ እንደገና መቱ። እሱ አልተሰበረም። ከዚያም ይሄ ጠንካራ ነው አሉ የሚል ሃሳብ የያዘ ፅሑፍ ነው። መፅሔት ጉዳዩን አጋኖ አቀረበው እንጂ እውነታው ግን የሚከተለው ነው።

አጤ ምኒልክ አልፍሬድ ኤልግ የተባለ የስዊዝ ተወላጅ የሆነ አማካሪ መሐንዲስ ነበራቸው። ይሄ ሰው ታዲያ አንድ ቀን በከተማዋ ውስጥ ወደፊት መሰራት ስላለባቸው ድልድዮች ሞዴል ሰርቶ ያቀርብላቸዋል። ምኒልክ ሞዴሎቹን ከተመለከቱ በኋላ ጥንካሬያቸውን ማረጋገጥ ፈለገ። እናም ሁለቱንም የድልድይ ሞዴሎች በጡጫ በተራ በተራ መቷቸው። አንደኛው ተሰበረ። ሁለተኛው አልነበረም። ምኒልክም ወደ አልፍሬድ ዞር አሉና “ያልተሰበረው ጠንካራ ነው። እሱ ይሰራ” እንዳሉት የኮንስትራክሽን ታሪካችን ያወሳል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መናገሻ ከመሆኗ በፊት ይህ ነው የሚባል የግንባታ ታሪክ የለንም። በዘመነ ጎንደር በተለይም ከእቴጌ ምንትዋብ ሞት በኋላ በተከሰተው ዘመነ መሣፍንት አስተዳደር ኢትዮጵያ ብትንትኗ ስለወጣ ዋና መቀመጫ ቦታ የለም ነበር። ዘመነ መሣፍንትን የጣለው አፄ ቴዎድሮስ ራሱ የመንግሥቱን መቀመጫ የሚያደርግበት ቦታ ጠፍቶት አንዴ ጎንደር፣ ሌላ ጊዜ ደብረታቦች፣ ቢቸግረው ደግሞ እጅግ ሰንሰለታማ በሆነው በመቅደላ አምባ ላይ አደረገው። ይሁን እንጂ የዋና ከተማን ጠቀሜታ የተረዳ መሪ ነበር። ያው ዘመኑን ሁሉ በጦርነት አሳለፈና የእርጋታ ጊዜ ሳያገኝ አለፈ።

ከርሱ በኋላ የመጡት አጤ ዮሐንስም መቀሌን ርዕሰ ከተማ አደረጓት። የእርሳቸው ዘመንም የተረጋጋ አልነበረም። ከሸዋው መንግሥት ጋር የነበረው ልብ ለልብ ያለመናበብ ተደምሮ ሌላ ጦርነትም መጣባቸው። ከሱዳን ከመጡት ድርቡሾች ጋር ሠራዊታቸውን ይዘው ሲዋጉ ቆዩ። በኋላም ለሀገራቸው ክብረ ተሰው። ደርቡሾች አንገታቸውን ቆረጡ። ትልቅ ወንጀልና ጭካኔ ፈፀሙ።

ከአፄ ዮሐንስ በኋላ የመጡት አጤ ምኒልክ፣ የኢትዮጵያን መንበረ ሙሴ ተረከቡ። በቴዎድሮስም ሆነ በዮሐንስ ዘመን የነበሩትን የሀገሪቱን ክስተቶች በሚገባ የተረዱ ነበሩ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለመቆም ምን ያስፈልጋታል የሚለውን አስበው ጨርስታል። የመንግሥታቸውን መቀመጫ ወደ መሐል ኢትዮጵያ ማለተም ወደ ሸዋ አደረጉ። በደቡብ በምስራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ የአገዛዝ ስርዓታቸውን አስፋፉ። እጅግ ጠንካራ የሚባ የጦ አርበኞችን ከጎናቸው አሰለፉ። በየትኛውም የጦርነት ቀጠና ድል ማድረግ መለያቸው ሆነ። የሰለጠነ የጦር ሠራዊት እና በርካታ ጀነራሎን ይዞ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ባልተጠበቀ ፍጥነት ድምጣማጡን አጠፉት። ቀሪዋን ኢትዮጵያ በፍቅርና በሰላም መግዛትጀመረ።

ከዚህ በኋላ ነው የግንባታ ታሪካችን ብቅ የሚለው። ምኒልክ የእንጦጦ ተራራ ላይ ቤተ-መንግሥታቸውን አገማሽረው ከቆዩ በኋላ አንድ ቀን ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቴ አንድ ነገር ይታያቸዋል። እንጦጦ ላይ ሆኖ ቁልቁል የሚታየውን ለጥ ያለ መሬት ለዋና ከተማነት መረጡት። በዚያ ላይ ደግሞ ፍል ውሃ አለው። እናም ቤተ-መንግሥታቸው ወደዚሁ አካባቢ እንዲሀን ሀሳብ አቀረቡ። ሃሳባቸው የሚጣል ስለማይኖው እሺ ተባሉ። ምኒልክ ቤተ-መንግስታቸውን ወደዚሁ ስፍራ አደረጉ። ጣይቱም ይህን ስፍራ “አዲስ አበባ” በማለት ሰየሙት። የዛሬዋ መዲናችን የዚያን ጊዜ መቆርቆር ጀመረች።

ጥለዋት የመጧት እንጦጦም ግንባታ የፈሰሰባት ከተማ ነች። በተለይ ዛሬን ጨምሮ ጥንትም የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ የሆነው የጥንቱ ቤተ-መንግሥታቸውና የተለያዩ ድንቅ አብያተ ክርስትያናት ይገኙበታል። እነዚህ ግንባታዎች የተካሄዱት ከጎንደር በመጡ የኪነሕንፃ ጥበበኞች አማካይነት እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ምኒልክ አዲስ አበባ ላይ ግን በአብዛኛው የተጠቀሙባቸው ባለሙያዎች የውጭ ሀገር ሰዎችን ነው።

እርግጥ ነው አጤ ምኒልክ የዘመናዊነትን ፅንፍ እንዲይዙ ያደረጋቸው ሐኪም ወርቅነህ እሸቱ ናቸው ይባላል። ሐኪሙ አውሮፓ አድገውና ሰልጥነው ስለመጡ የስልጣኔን ቁልፍ ለምኒልክ ሰጥተዋቸዋል የሚሉ አሉ። እርግጥ ነው ይሄ አንዱ መላምት ቢሆንም፤ ምኒልክ በተፈጥሮአቸውና እንዲሁም ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ ቤት በማደጋቸው የሀገራችንን ችግሮች በሚገባ የተረዱ ሰው በመሆናቸው ለስልጣኔ ቅርብ ሆኑ የሚሉ አሉ። ብቻ የ19ኛውን ምዕት የአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት የደረሰበት ጎዳና ዘመናዊ አስተሳሰቦችን በመቀበላቸው መሆኑ ምኒልክ በተለያዩ መንገዶች ገብቷቸዋል።

ታዋቂው የሀገራችን ኢትዮጵያ አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ አንድ ግዙፍ መፅሐፍ ከዴኒስ ዥራልድ ጋር በመሆን በጋራ አሳትሟል። የመፅሐፉ ርዕስ /The City and Its Architectural Heritage/ ይሰኛል። በውስጡ የያዘው በርካታ ፎቶግራፎችን እና ፅሁፎችን ነው። ከዚህ ሌላ የዲዛይን ስራ ሁሉ በውስጡ አካቷል። መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ታሪኮች በሙሉ የኢደስ አበባን ውልደትና እድገት የሚዘክሩ ናቸው። አይተናቸው የማናውቃቸው በርካታ ፎቶግራፎችን እናገኛለን በመፅሐፉ። ይህን መፅሐፍ ያዘጋጁት አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ በህይወት ዘመን ሊሰራ የሚችል ትልቅ ገፀ-በረከት ለሀገራችንም ሆነ ለተመራማሪዎች አበርክተዋል። ታዲያ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ አፄ ምኒሊክ ዋነኛው የግንባታ ታሪክ ገፀ-ባህሪ ሆነው ተቀምጠዋል። እናም ፋሲል ጊዮርጊስን ጠየኩት። ለምን ምኒልክ ልዩ ሆኑ? አልኩት።

እሱም ሲመልስ “ምኒልክ የተለዩ ሰው ናቸው። የዋና ከተማ አስፈላጊነት በጣም የገባቸው ናቸው። በተለይ ደግሞ ለኮንስትራክሽን በጣም ወዳጅ ነበሩ። መንገድና ድልድይ ሲሰራ ቆመው ያያሉ። አንዳንድ ጊዜ ድንጋይ ተሸክመው ሁሉ በስራ ያግዛሉ። ግንበኞችን ሰራተኞችን እየሰሩ ያበረታታ። እርሳቸውን እያየ ህዝቡ ደግሞ በግንባታው ስራ ይሰማራ ነበር። ስልክ፣ ፖስታ፣ መኪና፣ ብስክሌት፣ ውሃ፣ መብራት ወዘተ የገባው በእርሳቸው ዘመን ነው። ይሄ ሁሉ ስልጣኔ ኮንስትራክሽን ይጠይቃል። ለዚህም ነው እርሳቸው ገነው የወጡት” በማለት ፋሲል ያስረዳል።

ከዚህ ሌላ አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገር ባለሙያዎችን አምጥቶ በመቅጠርና ያላቸውን ክህሎት ኢትዮጵያ ላይ እንዲያፈሱ ያደረጉትን ጥረት በጣም እንደሚያደንቀው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ይናገራል። ከውጭ ሀገር ካስመጧቸው ባለሙያዎች መካከል የስዊዝ ተወላጁ አልፍሬድ ኤልግ ዋነኛው እንደሆነና የምኒልክም የምህንድስና አማካሪ እንደነበር የፋሲል መፅሐፍ ያወሳል። ለምሳሌ በ1897 አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ድልድዮች እንዲሰሩ ያማከራቸው ይህ ሰው ነበር።

ስለ አዲስ አበባ የኮንስትራክሽን ታሪክ ሲነሳ የውጭ ባለሙያዎች እርዳታና ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ሞንዡር ፋለር የተባለው አውሮፓዊ የተለያዩ የከተማዋን ዲዛይኖች እየሰራ ለምኒልክ አቅርቦላቸዋል። ቤተ-መንግስትንና የሌሎች ግንባታዎችን የወደፊት ገፅታ እየነደፈ አሳይቷቸዋል። ከዚሁ ሰው ጋርም በመሆን አርመኖች፣ ግሪኮችና ኢጣሊያኖች ለምኒልክ ብዙ ዘመናዊ ሃሳቦችን ሰጥተዋቸዋል።

ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ በመፅሐፉ ውስጥ እንደገለፀው አጤ ምኒልክ የባቡር መንገድ ለማሰራት በፈለጉ ጊዜ ከነገስታቶቻቸው ጋር የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎች አውጥቷቸዋል። በደብዳቤዎቹ መሠረት የባቡር መንገድ ለማሰራት ምኒልክ አዋጅ አውጥተው ነበር። አዋጁ የሚለው የባቡር መንገድ ስለሚሰራ የኢትዮጵያ ህዝብ መዋጮ እንዲያወጣ የሚያስገድድ ነው። መዋጮው ደግሞ የሚወስነው ሰው ባለው የከብት ብዛት ሆነ። በአንድ ከብት አንድ ብር ተወሰነ። መቶ ከብት ያው መቶ ብር ክፈል ተባለ። በዘመኑ አጠራር በከብት የሚለው “በጭራ አንድ ብር” ይባል ነበር።

እናም በብዙ ውጣ ውረድ ገንዘቡ ተዋጣ። ታዲያ አንድ ጊዜ ይህን የተዋጣውን ገንዘብ ብዛት አዩና ራስ ወሌ ከጀሉ። አፄ ምኒልክን ከተዋጣው ገንዘብ ላይ ብድር ስጡኝ ብለው ራስ ወሌ ደብዳቤ ፃፉ። አጤ ምኒልክም ነገሩ ስላላማራቸው እንዲህ በማለት መለሱ። “ወሌ ሙት አላበድርህም፤ የህዝብ ገንዘብ ግዝት ነው! እኔ መሓላ አለብኝ። የህዝብ ገንዘብ ላመንካት። ይልቅ አንተጋ ያለውን የተዋጣውን ብር ቶሎ ብለህ ላክልኝ” በማለት ምኒልክ ለደብዳቤው መልስ ሰጥተዋል። ሙስና የሌለባቸው መሪ እንደነበሩ ደብዳቤያቸው ያስረዳል።

ምኒልክ ይሄን ከህዝብ የሰበሰቡትን ብር ይዘው ጎበዝ ጎበዝ ባለሙያዎችን እያስመጡ ወደ ግባታው ገቡ። ከባቡር መንገዱ ሌላ በቤቶች ግንባታ ላይም ተሰማሩ። ለምሳሌ በእንጨት የሚሰሩ ቤቶችን የሚያንጸውን ህንዳዊውን ሀጂ ካዋስን አስመጡ። ከሐጂ ካዋስ ጋር ሌሎም አጋዥ የሆኑ ህንዶች መጥተው ነበር። እነዚህ ህንዶች ሙስሊሞች ነበሩ። ይሁን እንጂ ጥበብ በሃይማኖት ስለማትለይ ህንዶቹ በአብያተ ክርስትያናት ግንባታዎች ላይ ሁሉ እንደተሳተፉ የኮንስትራክሽን ታሪካችን ያወሳል።

በዚህም የተነሳ በዚያን ዘመን የተሰሩት ኪነ-ህንጻዎች እስላማዊ ጥበብ /Indo-Islamic Architecture/ ተፅዕኖ እንደነበራቸው አጥኚዎች ይገልጻሉ። ሌሎችም በርካታ የጥበብ ተፅዕኖዎች ያሉባቸውን ኪነ-ህንጻዎች ወደፊት በዝርዝር እናያለን።

ምኒልክ ካመጧቸው የኪነ-ህንጻ ባለሙያዎች መካከል ሚናስ ከሀርበጉያን፣ አቫኪያን አውጎርልያን እና ሳርኪስ ቴሬዚያን ከአርመን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በእንጨት ስራ ላይ ተሰጥኦ የነበራቸው ባለሙያዎች ነበሩ። በእነ ፋሲል ጊዮርሲስ መፅሐፍ ውስጥ ከእነዚህ አርሜኒያዊያን ውስጥ በርካታ ስራዎችን ለኢትዮጵያ የሰራው ሚናስ በሀርበጉያን እንደሆነ ፅፈዋል። ሚናስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በ1881 ሲሆን በርካታ አብያተ-ክርትያናት፣ መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ እና ቤቶችን ሲቀይስ እስከ 1895 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል። አበሾች በዚያን ጊዜ “. . . ሚናስ ብቻ ቀረ ቤት እያፈረሰ” ብለው ይገጥሙበት ነበር። ሚናስ አዲስ አበባን በቅያስ ያተራመሳት ሰው ነበር ይባላል።

ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እየዋወቀች መጣች። የመጀመሪያው የሸክላ ፋብሪካ በ1900 ዓ.ም ተቋቋመ። የምኒልክ አማካሪ አልፍሬድም የመጀመሪያውን የብረትና የእንጨት ቅርፅ ማውጫ ማሽን አስተዋወቀ። የብረት ቆረጣ እና ስራ በ1901 ዓ.ም ለባቡር ሐዲዱ ሲባል ተጀመረ። እንዲህ እያለ አለማዊው ግንባታ በሰፊው መካሄድ ጀመረ። የውሃው፣ የስልኩ፣ የመ/ቤቱ ወዘተ ግንባታ ሲፋጠን የሃይማኖት ሰዎች ደግሞ ማጉረምረም ጀመሩ። ቤተ ክርስትያን ተረሳች አሉ።

አጤ ምኒልክ የሃይማኖት ሰዎችንም ጥያቄ ችላ አላሉም። ማስተናገድ ጀመሩ። በዘመነ ምኒልክ የተሰሩ ኪነ-ህንጻዎች አብዛኛዎቹ ባይኖሩም አብያተ ክርስትያናት ግን አሉ። አብያተ ክርስትያናት የህዝብ ንብረት ስለሆኑ ዛሬም ድረስ አሉ። ስለዚህ የዚያን የምኒልክን ዘመን የኪነ-ህንጻ ጥበብ ለአሁኑ ትውልድ ለማስቃኘት በኔ በኩል እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት መርጫለሁ። ከዚያም ሌሎች ጥበቦችን እናያለን።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ከግንባታዎች ሁሉ የሚቀድመውና በጥንቃቄ የሚሰራው ቤተ-ክርስትያን ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የቤ-ክርስትያን አሰራር በአብዛኛው ክብነው። ክብ ቅርፅ የሚዘወተርባት ሀገር ነች። ጎጆ ቤቱ፣ ዘፈን ስንዘፍን፣ ሕፃናት ሲጫወቱ፣ ምጣዱ፣ አክንባሎው፣ ረከቦቱ፣ ምድጃው. . . ሁሉ ክብ ነው። ሽምግልናም ስንቀመጥ ክብ ነው። እና ይሄ የክብ አባዜ ከየት መጣ? እርግጥ ነው የክብ የቤተክርስቲያን አሰራር ብቅ ያለው ከ14ኛው መቶ ክፍ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ የስነ መለኮት ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት ከደሴ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው በሐይቅ እስጢፋኖስ አካባቢ እንደተጀመረ ያስረዳሉ። ዝርዝሩ ውስጥ ስንገባ ብቻ የክብ ቤተክርስትያን አሰራር በሀገሪቱ የተለመደ መሆኑን እንያዝ።

የክብ ቤተ-ክርስትያን አሰራር የራሱ የሆኑ ሕግጋትና ደንቦች አሉት። አሰራሩ በተለይም በውስጠኛው የቤቱ አካል በሶስት ክፍሎች የተወቀረ ነው። ይህም የመጀመሪያው “ቅኔ ማህሌት” ሲባል፣ ሁለተኛው ደግሞ “ቅድስት” ሲባል ሦስተኛው “መቅደስ” በመባል ይለያል።

“ቅኔ ማህሌት” የሚባለው ወደ ቤተ-ክርስትያን የሚገቡት አማንያን ሁሉ የሚያመልኩበት ቦታ ነው። ሁለተኛው “ቅድስት” የሚሰኘው ደግሞ ዲያቆናትና ቄሶች ብቻ የሚገቡበት ክፍል ነው። ሦስተኛው ማለትም “መቅደሰ” የሚባለው ታቦት የሚያርፍበት ክፍል ሲሆን፤ የሚገቡትም ለታቦት ቅርብ የሆኑ ቄሶችና ነገስታት ብቻ ናቸው። ይህ ክፍል በልዩ ልዩ ስነ-ጥበባት ስራ ያጌጠ ነው። እና ይሄ የክብ አሰራ ሌሎች ተፅዕኖዎች ሲመጡበት ምን ይሆናል? በአጤ ምኒልክ ዘመን ከተለያዩ ሀገሮች ጥበበኞች በአብያተ ክርስትያናት ግንባታዎች ላይ በመሰማራታቸው የክብ ቤተክርስትያን አሰራር ለየት ባለ መልኩ ሲሰራ ታይቷል።

ለምሳሌ አውሮፓ ውስጥ የጥበብን ትንሳኤ የሚያሳዩ ቅርፆች ይዘወተሩ ነበር። ይህም Renalssance-Style European forms በመባል ይታወቃሉ። እናም ከአውሮፓ የመጡት ጥበበኞች በአብያተ ክርስትያኖቻችን ላይ ይሄን ጥበብ አንፀባርቀዋል። ለአስረጅነት የአራዳ ጊዮርጊስን ቤተክርስትያንና የእራት ኪሎዋን ባዕታ ለማርያምን ቤተክርስትያን መጥቀስ ይቻላል።

የአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን አገነባብ ላይ የታየው HP Octagounal form የሚባለው ሲሆን፤ አውሮፓዊ ተፅዕኖ ያለበት ስራ ነው። ይሁን እንጂ ውስጣዊ ገፅታውን ቅኔ ማህሌትን፣ ቅድስት እና መቅደስን በስርዓት የያዘ ነው። ውጪአዊ ቅርፁ እንጂ ውስጣዊ ቅርፁ ከጥንታዊው ክብ ቤተ-ክርስትያን አልተለየም።

መቼም እየተጨዋወትን ያለነው ነገር ታሪክም ነውና ስለ አራዳ ጊዮርጊስ አሰራር የማውቀውን ላጫውታችሁ ልለፍ።

የአድዋን ድል ለማስታወስ ራስ ዳርጌ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ-ክርስትያን ቢራቢራሳ በተሰኘ ቦታ ላይ አሰሩ። የመጀመሪያው የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቢርቢርሳ ላይ የተሰራው በ1897 ሲሆን፣ ይህም በ1529 ዓ.ም በግራኝ አህመድ ጦርነት ወቅት የተቃጠለውንም ለመተካት ነበር ራስ ዳርጌ ይህን ያደረጉት። ራስ ዳርጌ የምኒልክ አጎት ናቸው። የራስ ዳርጌ ሦስተኛ ትውልድ የሆኑት ልጅ እንግዳ ገብረክርስቶስ መሿለኪያ አካባቢ ዛሬም አለ።

አሁን አራዳ ላይ ውበትን ተላብሶ የቆመው የጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን የተሰራው እ.ኤ.አ. ከ1906 እስከ 1911 ነበር። የተሰራውም በኢጣሊያዊ መሐንዲስ ካስታግና እና በበላይ ተቆጣጣሪ አርክቴክት በግሪካዊው ኦርፋናዲስ ነበር። ይህ አውሮፓዊ ስልጣኔን የሚያሳየው አክታጎናል ቅርፅ ያለው ውብ ቤተ-ክርስትያን በቅርፅ ግቢው ውስጥ የመጀመሪያውን የጦር ሚኒስትር የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አስክሬን ይዟል።

የጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን በ1929 ዓ.ም በኢጣሊያ ወራሪ ወቅት በፋሽስቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፤ ቀሳውስቱም ታቦቱን አሸሽተው ወደ ይፋት ወስደውት ነበር። ከዓት በኋላ ጣሊያኖቹ ራሳቸው ጠግነውት ነበር። ይሁን እንጂ ቤተ-ክርስትያኑ በስርዓት የተጠበነው ከወረራው በኋላ በኢትዮጵያዊያኖች ሲሆን፤ ታቦቱም ከይፋት ተመልሶ ገብቷል። ዛሬ በከተማችን ካሉት ምርጥ ሙዚየሞች ውስጥ አንዱን የያዘው የአራዳው ጊዮርጊስ ቀደም ሲል ቅኔና ዜማ የሚማሩበት ደብር ሲሆን፣ ምኒልክና ጣይቱም ዘውድ ደፍተውበታል።

በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ መስኪዶችም የተሰሩበት ከተማ እንደነበረች አብዱልፈታህ አብደላ፣ የአዲስ አበባ መስኪዶች ታሪክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል። ታታሪው ደራሲ ብርሃኑ ሰሙ ደግሞ ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ (ከ1879 እስከ 2000 ዓ.ም ) በተሰኘው መፅሐፉ፣ አዲስ አበባ ከተማ ከተመሰረተች በ11ኛው ዓመት አካባቢ 2ሺህ ያህል የእስልምና እምነት ተከታዮ በከተማው ውስጥ እንደነበሩ ይገልጻል። አጤ ምኒልክም የሀጂ ወሌ መሐመድ መስኪድን ጨምሮ ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ ብዙ ሰርተዋል።

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን እመለስ። የአፄ ምኒልክ የኪነ-ህንጻ ግንባታ ትኩረቱን በአብያተ -ክርስቲያናትና በቤተ-መንግሥቶች ላይ አደረጉ። በቤተ-ክርስትያናት ላይ ያሉት አሻራዎች ዛሩም ቢኖሩም ግን አንዳንድ ነገሮቻቸው ተቀይሯል። የቀየሩት ደግሞ ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ ናቸው።

ንግሥት ዘውዲቱ አባታቸው አጤ ምኒልክን እጅግ በጣም ይወዷቸው ነበር። ምኒልክ ሲያርፉ ዘውዲቱ ተተኩ። ታዲያ ዘውዲቱ በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ቤተ-ክርስትያናት በማነፅ ይታወቃሉ። አባታቸው ምኒልክ ያሰሯቸውን ቤተ-ክርስትያናት በማሳደስ ለአባታቸው ያላቸውን ፍቅር በወቅቱ ይገልፁ ነበር። ነገር ግን ያን ዋናውን የምኒልክን የኪነ-ህንጻ ኦርጅናል ግንባታ በተወሰነ ደረጃ እድሳቱ ለውጦታል።

በአንዳንድ ታሪክ ፀሐፊዎች ምኒልክ ያሰሯቸውን አብያተ -ክርስትያናት ሁሉ ዘውዲቱ ናቸው ያሰሯቸው እየተባለ ተፅፏል። እርግጥ ነው ሙሉ እድሳት ሲያደርጉ “ኮፒ ራይቱ” ለዘውዲቱ ተሰጠ። እንዲህ አይነት ሁኔታ በዘመነ ጎንደርም ታይቷል። በስነጥበብ ርቀታቸው አይንን የሚያማልሉት ስዕሎች ያሉበት ደብረብርሃን ስላሴ በቴክርስትያን መጀመሪያ ያሰሩት አድያም ሰገድ እያሱ ነበሩ። ቤተ-ክርስትያኑም ክብ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን በመብረቅ አደጋ ጉዳት ይደርስበታል። በወቅቱ አድያም ሰገድ እያሱ በዙፋ ላይ አልነበሩም። የነበሩት ልጃቸው አፄ ዳዊት ናቸው። እናም አፄ ዳዊት ጉዳት የነበረውን ባለ አራት ማዕዘን አድርገው /Rectangular/ ቤተ-ክርስትያን አድርገው ዛሬ ጎንደር ከተማ ላይ የሚታየውን አቆሙት። ጥያቄው ደብረብርሃን ሥላሴን ማን ሰራው ሲባል ማን ይባል? ኢያሱ ወይስ ዳዊት?

ልክ እንደዚያው ሁሉ በምኒልክና በዘውዲቱ መሀል ታሪክ ፀሐፊዎች ሲወዛገቡ ይታያሉ። ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ቀራንዮ መድሃአለምን ቤተክርስትያን መጀመሪያ ያሰሩት ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ነበሩ። አጤ ምኒልክ ደግሞ እንደገና አሳድሰው አሰሩት። ከዚያ ደግሞ ንግስት ዘውዲቱ አሰሩት። ማን አሰራው የሚለው የሚያምታታው እዚህ ላይ ነው።

የቅዱስ ሩፋኤልን ቤተክርስትያን መጀመሪያ ያሰሩት ምኒልክ ናቸው። ይህ ቤተ-ክርስትያን እንደገና በዘውዲቱ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርገውለት ተሰርቷል።

ከዚህ ሌላ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስትያን ጥንት ያቆሙት ምኒልክ ናቸው። በኋላ ልጃቸው ዘውዲቱ እንደገና አሰሩት። ማን ሰራው ሲባል ግማሹ ምኒልክ ይላል። ሌላው ዘውዲቱ ይላል።

እንጦጦ ማርያም ቤተክርስትያን የተሰራችው አዲስ አበባ ከመቆርቆርዋ በፊት ነው። የተገነባችውም አጤ ምኒልክ በ1890 የጎጃሙን ንጉሥ ተክለሃይማኖትን በእንባቦ ጦርነት ድል ካደረጓቸው በኋላ ነበር። ታቦቱም መጥቶ የገባው በጎጃም ነበር። የመጀመሪያዋ እንጦጦ ማርያም ቅርጿ ክብ ሲሆን በድንጋይ፣ በሞርታር፣ እና በሌሎም የመገንቢያ ቁሳቆሶች የታነፀች ነበረች። እንደ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ገለፃ ከሆነ በምርቃቷ ቀን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ከብቶች ታርደው ሀበሻ ሲደሰት ቆይቷል። ይህችን የእንጦጦ ማርያምን ቤተክርስትያን እንደገና አሳድሰው ያሰሯት ንግሥት ዘውዲቱ ናቸው። በውስጧም ውብ ስሎች እንዲሳሉ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት የምናያቸውን ስዕሎች የሳሏቸው አለቃ ኅሩይ የተባሉ የስነ-ጥበብ ባለሙያ ነበሩ። እና ምኒልክን እና ዘውዲቱን እንዴት እንግለፃቸው?

እርግጥ ነው ዘውዲቱ ብቻቸውን ያሰሯቸው አብያተ-ክርስትያናት በርካታ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ የመርካቶውን ደብረአሚን ተክለሃይማኖት፣ የጉለሌውን ጴጥሮስ ወጳውሎስ እና ቁስቋምን እና ቅዱስ ዮስፍ አብያተ ክርስትያናት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፤

በአጠቃላይ ግን እነዚህ አብያተ-ክርስትያናት የኪነ-ህንፃ ጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ስራዎች ናቸው። ዛሬም ድረስ በውበት አጊጠውና ከምዕምናን አልፈው የጎኝዎችን ቀልብ የሚገዙት በስርዓት ተጠብቀው የተሸጋገሩ ጥበቦች ስለሆኑ ነው። በዘመናቸው ቀላል የማይባል ዕውቀትና የሰው ሃይል የፈሰሰባቸው ናቸው። የአብያተ ክርስትያናት አሰራር በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኞቹ የቱሪስት መስህቦችም እንደሆኑ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በጥናታቸው ላይ ይገልጻሉ።

ከዚህ ሌላ በአዲስ አበባ ከተማ የኪነ-ህንጻ ታሪክ ውስጥ የጎላ ስፍራ የሚሰጣቸው ታላላቅ ቅርሶች አሉ። እነዚህን ቅርሶ The City znede its Architectural Heritage በተሰኘው በነአርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ መፅሐፍ ውስጥ በሚገባ ተዘርዝረዋል። ጥቂቶቹን ላስታውሳችሁ።

የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ቤት

ይህ ቤት ከአራዳው ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ፊት ለፊት የሚገኘው ዛሬ ፍርድ ቤት የሆነው ወይም ደግሞ የጥንቱ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሚባለው ነው። ቤቱ የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ነበር። የተገነባው በ19ኛ ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር። የዛሬን አያድርገውና በዘመኑ እጅግ ውብ የሚባል የኪነ-ህንፃ አሻራ ያረፈበት ነበር።

ቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ የምኒልክ የቅርብ ሰው ከመሆናቸው በላይ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴ ሆነው አገልግለዋል። እጅግ ሀብታምም ነበሩ። በ1916 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዙፋን ላይ ሲወጡ ቢትወደድ እና ልጅ እያሱ የጠበቀ ጓደኝነት ስለነበራቸው በአፄ ኃይለሥላሴ የተጠሉ ሆኑ። ከዚያም ቤታቸው ወደ ማዘጋጃ ቤትነት ተቀየረ። ዛሬ ከፍተኛ እድሳትን ጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

የሼህ ሆጆሌ ቤት

የሼህ ሆጀሌ ቤት የሚገኘው ጉለሌ ቅዱስ ሩፋሴል ቤተ-ክርስትያን አካባቢ ነው። ቤታቸው አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ የግል መኖሪያ ቤቶች በትልቅነቱ ወደር ያልተገኘለት ነው። ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለው ርዝመቱ 90 ሜትር ነው። ወደ ላይ ደግሞ 10 ሜትር ነው። በቤቱ ያሉትን የእንጨት ስራዎች የሰሩት ህንዶች ሲሆኑ ቀሪውን ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

ሼህ ሆጆሌ ከቤንሻንጉል የመጡ ሲሆን የአሶሳ ህዝብ ባህላዊ መሪ ነበሩ። ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በበርካታ ሰዎች ታጅበው ነበር። በጣም ሀብታምም እንደነበሩ ይነገራል። ወደ አዲስ አበባ ወርቅ እያመጡ ይነግዱ ነበር። አጤ ምኒልክ ራስ ላድርግህ ቢሏቸው የምጠራበት ማዕረጌ “ሼህ” ይሻለኛል ብለው እምቢ አሉ። ምኒልክም ተገርመው እንደነበር ይነገራል። ይህ የሼህ ሆጀሌ ቤት ዛሬ ከፊሉ ት/ቤት ሲሆን ቀሪው ደግሞ የሰዎች መኖሪያ ቤት ነው። ከከተማችን ቅርሶች መካከል ልዩ የሆነው ይህ ቤት ከፍተኛ እንክብካቤ ያስፈልገዋል።

የራስ ብሩ ወልደገብርኤል ቤት

ከመስቀል አደባባይ ጀርባ ያለው ቦታ ሁሉ የእርሳቸው ነበር። ዛሬ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ የሆነው የርሳቸው ቤት ነው። ራስ ብሩ ኮንታ፣ ከፋ፣ ሲዳሞና ወለጋን ያስተዳደሩ የምኒልክ ቅርብ ሰው ነበሩ። ጥንት እርሳቸው በመኪና ሲሄዱ በርካታ አጃቢዎች በፈረሶች መኪናቸውን አጅበው ይጓዙ እንደነበር ተፅፏል። ይሄ የራስ ብሩ ቤት በተሻለ ሁኔታ ከተጠበቁ የአዲስ አበባ የኪነ-ህንጻ ጥበቦች መካከል አንዱ ነው። 

በዛሬ ፅሁፌ ሁሉንም ነገር ለኮፍ ነው ያደረኩት። እያንዳንዱ ሀገር የኪነ-ህንፃ ታሪክ አለው። የእኛም አዲስ አበባ አልጠበቅንላትም እንጂ በርካታ የሚነገሩላት ታሪኮችንና ቅርሶች አሏት። በሌላ ጽሁፌ እነርሱን አስተዋውቃችኋለሁ። ለምሳሌ የምኒልክን ዋነኛ አማካሪ የአልፌሬድ ኤልግ ቤትንና አሰራሩን፣ የአፈንጉሥ ነሲቡን ቤት፣ የአፈንጉሥ ጥላሁን ቤትን፣ የደጃዝማች አያሌው ብሩን፣ የራስ ከበደ መንገሻን፣ የራስ ናደው አባ ወሎ፣ የፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስን እና ልዩ ልዩ ታሪካዊ ኪነ-ህንጻዎችን አስተዋውቃችኋለሁ። ቀጥሎም ዘመነ ኃይለስላሴ፣ ዘመነ ኢጣሊያ ወረራን፣ ዘመነ ደርግንና ዘመነ ኢህአዴግን የኮንስትራክሽን ታሪካችንን እናወጋለን። የነገ እና የወደፊት ሰው ይበለን።

      

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
11585 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us