የኢትዮጵያ ቅዱስ መሪ ማን ነው?

Friday, 08 January 2016 12:18

 

በጥበቡ በለጠ

አንድ የሐገር መሪ እንዴት ቅዱስ ሊሆን ይችላል ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። መሪነት ከባድ ነው። በውስጡ ብዙ ምስጢሮች አሉበት። ስንት ነገር አለ፤ በመሪው የግዛት ዘመን ውስጥ ሰዎች ይታሠራሉ፤ ይገደላሉ፤ ይሠቃያሉ፤ የፍትህ እና የመብት ረገጣዎችም እነሰም በዛ ይኖራሉ። ጭቆናው ስደቱም ይኖራል። በአገዛዝ ዘመን ውስጥ ብዙ ጥፋቶች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ቅድስና ደግሞ ሌላ ነው። ቅዱስ መባል ወደፍፁምነት ይወስዳል። አንድ ሰው ቅዱስ ከተባለ እጁ ላይ ደም የለም። በአገዛዝ ዘመኑ ስቃይ የለም። እንግልት የለም ታድያ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅዱስ መሪ ወይም ቅዱስ ንጉስ  ነበረ ወይ?

ኢትዮጵያ ቅዱስ ንጉስ (HollY king) ነበራት፤ ነበሯት ማለትም ይቻላል። እነርሡም ቅዱስ ይምርሀነ ክርስቶስ፤ ቅዱስ ሀርቤይ፤ ቅዱስ ላሊበላ፤ ቅዱስ ነአኩቶለብ ናቸው። ኢትዮጵያ አራት ቅዱሣን መሪዎች ነበሯት። አይገርምም? ኢትዮጵያ ውስጥ ቅዱሳን መሪዎች ነበሩን ስንል ማን ያምነናል?

ለማንኛውም ከነዚህ ውስጥ ለዛሬ አንዱን እንውሠድ። ስለ እሡ እናውጋ። ስለሱ የምናወጋው በብዙ ምክንያቶች ቢሆንም በዋናነት ግን ነገ የልደት በዓሉ ስለሆነ ቅዱስ ላሊበላን እናነሣሣዋለን።

 

በኢትዮጵያ ውስጥ የጌታችን የመድሃኒታችን የእየሡስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት ቀን ተመሣሣይ በመሆኑ እጅግ በደመቀ ሁኔታ በጋራ ይከበራል።

ኢትዮጵያዊያኖች የገና በዓልን ወደ ላስታ ላሊበላ በመጓዝ ያከብራሉ። ላላስታ ላሊበላ ውስጥ አንድ ተአምር አለ። አንድ ድንቅ የሆነ ጥበብ አለ። እዚህ ጥበበኛ ቦታ ላይ ኢትዮጵያዊያኖች ይሠበሠባሉ። ይህ የጥበብ ቦታ 10 ድንቅ አብያተ-ክርስትያናትን ላለፉት 800 አመታት ጠብቆ የኖረ የክርስትና እምነት ማዕከል የሆነ ነው። በዚህ ቦታ ላይ የተሠሩት እነዚህ አብያተ-ክርስትያናት የቅዱስ ላሊበላ ናቸው። ቅዱስ ላሊበላ እነዚህን ሕንፃዎች ሲሠራ ዳግማዊት እየሩሳሌም በማለት ነው። ስለዚህ የክርስቶስን ልደት ለማክበር ላስታ ላሊበላ መጓዝ እየሩሳሌም እንደመሔድ ይቆጠራል።

 

ቅዱስ ላሊበላ እነዚህን ፍፁም ምስጢራት የሆኑ አስደማሚ ኪነ-ሕንፃዎችን ለምን ሠራ ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ቅዱስ ላሊበላ በዋናነት ዳግማዊት እየሩሳሌምን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የፈለገበት ምክንያት የሐገሩ የኢትዮጵያን ዜጐች ከሞት እና ከስቃይ ለመታደግ በሚል ነው። ከቅዱስ ላሊበላ ወደ ሥልጣን መምጣት በፊት አያሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች የገናን በዓል እና ጥምቀትን ለማክበር በእግራቸው ወደ እየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። በዚህ ጉዞ ወቅት ብዙዎች ይሞታሉ፤ ይዘረፋሉ፤ በአውሬ የበላሉ፤ በሽፍታ መከራና ስቃይ ይደርስባቸው ነበር። በተለይ ግብፅን አቋርጠው እየሩሳሌም ድረስ እስከሚደርሡ ሰቆቃው ብዙ ነው። ወደ እየሩሳሌም ሊሣለም ከሚጓዘው ሕዝብ ውስጥ አብዛኛው በሕይወት ወደ ሐገሩ አይመለስም ነበር። እናም የዚህን ሕዝብ ሞት እና ስቃይ ለማቆም ቅዱስ ላሊበላ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ላስታ ወረዳ፤ ሮሃ ከተባለች ቦታ፤ በሠው ልጁ አእምሮ ውስጥ እስካሁን ድረስ መልስ ያልተገኘላቸውን ብርቅዬ ኪነ-ሕንፃዎችን አሠራ። እየሩሳሌምን በኢትዮጵያ ፈጠረ። ጉዞ ቀረ፤ ሞት ስቃይ ቆመ። ሕዝቡን ታደገ። እንግዲህ የመሪነት አንዱ ሐላፊነት ሞትን፤ ስደትን፤ መከራን ማስቆም ነው። ቅዱስ ላሊበላ ማለት ይሔ ነው።

 

ቅዱስ ላሊበላ

የላሊበላ ቤተሠቦች የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ነገስታት ናቸው። አባቱ ዠን ሥዩም ይባላል። እናቱ ኪዮርና ትባላለች። የተወለደው ቡግና አውራጃ ላስታ ውስጥ በ1101 ዓ.ም እንደሆነ የቤተ-ክርስትያን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተወለደ ጊዜም ንቦች እንደከበቡት ይነገራል። ንቦች ማር ባለበት ቦታ አይጠፉም። እናም ላሊበላ ማር ሆኖ ሣይታያቸው አልቀረም። አፈ-ታሪክ እንደሚያወሣው ላሊበላ የሚለው መጠሪያ ስሙም የተገኘው ከዚሁ ከማር ጋር በተያያዘ ነው። ላል ማለት ማር ሲሆን፤ ላሊበላ የሚለው ሥም ማር ይበላል የሚል ትርጉም እንደሚሠጥ ይነገራል። ይህ እንግዲህ ከዛሬ 800 አመታት በፊት በነበረው የአገውኛ ቋንቋ ውስጥ ያለ ትርጉም መሆኑ ነው።

 

ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ስለ እሡ ብዙ ነገር ይነገር ነበር። ይህም የአባቱን ዙፋን እንደሚወርስ፤ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚነግስ፤ ሀገርና ሕዝብ እንደሚመራ፤ ታላቅ ሠው እንደሚሆን በስፋት ይነገር ነበር። በዚህ ምክንያት ያባቱ ልጆች የሆኑት ወንድሙ እና እሕቱ ይጠሉት ነበር። ላሊበላን ለማጥፋት ይጥሩ ነበር።

ላስታ ውስጥ ታዋቂ የቤተ-ክሕነት ሰው የሆኑት አፈ-መምህር አለባቸው ረታ እንደሚተርኩት ከሆነ ያባቱ ልጅ እህቱ፤ ለላሊበላን መርዝ አበላችው። እንዲሞት። እናም ሞተ፤ ግን ደግሞ ከሞቱም ነቃ። ምክንያቱም ፈጣሪ ጊዜህ አልደረሠም አለው። ጌታም እንዲህ አለው፡- አንተ ላሊበላ፤ በስሜ አብያተ-ክርስትያናትን ታንፃለህ፤ ላንተም መጠሪያ ይሆናሉ። የክርስትያኖችም መሠብሠቢያ ትሠራለህ ይለዋል።

 

ላሊበላም ለጌታ እንዲህ ይጠይቀዋል፡- ጠቢቡ ሰለሞን እንኳን እየሩሳሌምን ሲሠራ ዝግባውንም፤ ፅዱንም ከፋርስ እና ከልዩ ልዩ ቦታዎች እያመጣ ነው። እኔ በየትኛው አቅሜ ነው አብያተ-ክርስትያናትን የማንፀው? ይለዋል።

ጌታም እንዲህ መለሠ፡- ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈለፍላለህ። አንተ ላሊበላ አነፅካቸው እንድትባል ነው እንጂ የማንፃቸው እኔ ነኝ አለው። ከዚያም ላሊበላ ከሞተበት ነቃ ይላሉ አፈ-መምህር አለባቸው ረታ፤ የቤተ-ክርስትያንን ገድለ ላሊበላን እየጠቃቀሡ።

ሌላው የላሊበላ ታሪክ እንደሚያወሣው በወንድሙ እና በእህቱ አማካይነት ችግር ቢደርስበትም ራዕይ ታይቶት ትዳር ይመሠርታል። ባለቤቱ መስቀል ክብሯ ትባላለች። የተጋቡት በቁርባን ነው። ነገር ግን ከወንድሙ እና ከእህቱ የሚደርስበትን ጫና ለመቋቋም ከባለቤቱ ጋር ሆኖ ተሠደደ። እሡ ወደ እየሩሳሌም ሔደ፤ ባለቤቱ ደግሞ አክሡም ውስጥ አባ ጴንጤሊዮን ከሚባል ገዳም ገባች።

 

ላሊበላ በእየሩሳሌም 12 አመታት ያሕል ቆየ። በዚህ ጊዜ በርካታ ትምህርቶችን ቀሠመ። እብራይስጥ እና አረብኛን መናገር መፃፍ ቻለ። ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝ።

እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ላሊበላ እንዲሠደድ ምክንያት የሆነው ወንድሙ ንጉስ ሐርቤይ በፀፀት ውስጥ ገብቷል። መንፈሡ ተረብሿል። ፈጣሪ እየወቀሠኝ ነው ይላል። ወንድምህ ላሊበላ እንዲሰደድ አድርገሃል፤ ይሔ ሐጥያት ነው፤ ስለዚህ ወንድምህን ፈልገህ ወደ ሐገሩ አምጥተህ፤ ይቅርታ ጠይቀህ ዙፋኑን ለእሡ ስጥ ይለዋል።

 

በመጨረሻም ላሊበላ ከእየሩሳሌም ወደ ሐገሩ መጥቶ አባ ጴንጤሊዮን ገዳም ውስጥ የምትገኘውን ባለቤቱን መስቀል ክብሯን ይዟት ወደ ላስታ ይመጣል። ወንድሙ ሐርቤይ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሠብስቦ ጠበቀው። ድንጋይ ተሸክሞ ይቅርታ ጠየቀው። “ወንድሜ ላሊበላ እንድትሠደድ ያደረኩ እኔ ነኝ። ለዚህም ስራዬ ጌታ ሲገፅፀኝ ቆይቷል፤ እናም ይቅር በለኝ” አለው። ላሊበላም ይቅርታ አደረገለት። ሐርቤይም የኢትዮጵያን ንጉስነት ትቶ ለላሊበላ ሠጠው። “ጌታ ነግሮኛል። የኢትዮጵያ ንጉሥ አንተ ላሊበላ ነህ” አለው። እናም የስልጣን ሽግግሩ ከሐርቤይ ወደ ላሊበላ በሠላም ተሸጋገረ።

 

ንጉሥ ላሊበላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ሕይወት ውስጥ በ1157 ዓ.ም ብቅ አለ። ላሊበላ ቄስ እና ንጉስ ነው። እጁ ላይ መቋሚያና መስቀል፤ አንደበቱ ላይ ትህትናና አስተዳደር የበዙበት የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ መሪ ሆኖ መጣ።

 

ቀደም ሲል በፈጣሪ እንደተነገረው የሚታወቀውንም የአብያተ-ክርስትያናቱን ግንባታ ጀመረ። በ23 አመታት ውስጥ 10 አብተ-ክርስትያትን ከአለት ፈልፍሎ ሠራ። እነዚህ አብያተ ክርስትያናት ዛሬም ድረስ የሠው ልጅ ምስጢራት ሆነው አሉ። እንዴት እንደታነፁ፤ በግንባታው ላይ ማን እንደተሣተፈ፤ እንዴትስ እንደታሠቡ ወዘተ የሚተነትን የኪነ-ሕንፃ ፈላስፍ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት የብዙ ጭቅጭቆች እና ውዝግቦች ምክንያት ሆኖ ለበርካታ አመታት ቆይቷል።

የአብያተ-ክርስትያናቱ የአሠራር ምስጢር ባለመታወቁ የተነሣ የሐይማኖት ሠዎች መላዕክት ላሊበላን እያገዙት በ23 አመታት ሠርቶ አጠናቀቃቸው ይላሉ። ቀን እሡ እየሠራ፤ ሌሊት መላዕክት እሡ የሠራውን አጥፍ እያደረጉለት ተሠርተው ተጠናቀቁ የሚሉ በርካታ የቤተ-ክርስትያን መረጃዎች አሉ።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ የውጭ ሀገር የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች ናቸው የሠሯቸው የሚሉ ፀሐፍትም አሉ። የላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎች ለመጀመሪያ ጊዜ መጥቶ በማየት እና ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ ፖርቹጋላዊውን ቄስ ፍሪንሲስኮ አልቫሬዝን የሚደርስ የለም። አልቫሬዝ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከጐበኘ በኋላ The Portuguese  Mission to Abyssinia (1520-26) የተሠኘ ግዙፍ መፅሃፍ አሣተመ። በዚህ መፅሃፍ ውስጥ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር የሚከተለውን ብሏል፡-

 

“ስለ ላሊበላ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተሰሩ አብያተ-ክርስትያናት ላላያቸው ሰው ይህንን ይመስላሉ ብዬ ብጽፍ የሚያምነኝ ሰው አይኖርም።እስከ አሁን ያልኩትን እንኳ በቦታው ተገኝተው ያልተመለከቱ ሰዎች ውሸት ነው ይሉኛል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ እውነት ለመሆኑ በሐያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ” በማለት ፅፏል። አልቫሬዝ ያየውን ነገር ማመን አልቻለም ነበር። ላላዩዋቸው ሰዎች ደግሞ ይህን ይመስላሉ ብሎ ማስረዳትም ከባድ ነው። ማንም አያምነኝም ብሎ ሠጋ። እናም ቄሡ አልቫሬዝ ማለ፤ ተገዘተ።

 

በአልቫሬዝ መፅሃፍ ውስጥ ሌላው አጨቃጫቂ ጉዳይ አብያተ-ክርስትያናቱን ማን ሠራቸው የሚለው ነገር ነው። አልቫሬዝ እንደፃፈው ማነው የሠራቸው ብሎ ሲጠይቅ ግብጾች ናቸው የሠሯቸው ብለው ቄሶች ነገሩኝ ብሏል።

ታዲያ ከዚያ በኋላ የመጡ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ፀሐፍት አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ፈረንጆች ሠሩት ወደሚለው እምነት አዘንብለው ቆይተው ነበር።

የሐገራችን ታዋቂ ፀሐፊዎቸ ሣይቀሩ የላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎቸ የሠሯቸው የውጭ ሀገር ሠዎች እንደሆኑ ጭምር ፅፈዋል። ለምሣሌ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወ/ስላሴ በ1921 ዓ.ም ባሣተሙት ዋዜማ በተሠኘው መፅሐፋቸው፤ ተክለፃዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ አክሱም ኑቢያ ዛጉዌ በተሠኘው በ1951 ዓ.ም ባሣተሙት መጽሐፍ፤ ብርሃኑ ድንቄ አጭር የኢትዮጵያ ታሪክ ብለው በ1941 ዓ.ም ባሣተሙት መጽሐፍ፤ ዶ/ር ሥርገው ሀብለስላሴ Ancient and Medieval Ethiopian History Histry of Ethiopia  በተሠኘው መጽሐፋቸው እና ሎሎችም ጎምቱ የኢትዮጵያ የታላላቅ የታሪክ ፀሐፊዎች የላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር ላይ የውጭ ሀገር ሠዎች መሣተፋቸውን ፅፈዋል። እነዚህ ደራሲያን ለፅሁፋቸው የተጠቀሙበት ምንጭ የውጭ ደራሲያንን ፅሁፍ ነው።

 

እነዚህን ፅሁፎች ሁሉ ያነበበችው እና ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ሲልቪያ ፓንክረስት በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት አሠራር ላይ ሠፊ ጥናትና ምርምር ጀመረች። ከጥናቷ ውስጥ ዋነኛው ጉዳይ አለምን መዞር ነበር። እንደ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ጋር የሚመሣሠሉ ኪነ-ሕንፃዎች በሌሎች ሐገሮች መኖርና አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ አለምን አሠሠች። ከዚያም አንድ ውጤት ላይ ደረሠች።

 

ሲልቪያ ፓንክረስት Ethiopia :- A Cultural History የተሠኘ ግዙፍ መጽሐፍ አሣተመች። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የቅዱስ ላሊበላ አብተ-ክርስትያናት አሠራር የአለማችን ብርቅዬ ጥበቦች መሆናቸውን ገለፀች። በአለም ላይም በየትኛውም ሀገር ይህን መሳይ ጥበብ እንደማይገኝ ፃፈች። እንደ ሲልቪያ አባባል እነዚህ የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች የኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ጥበቦች ናቸው በማለት ገለፀች። የውጭ ሀገር ሰዎች ሠርተዋቸው ቢሆን ኖሮ ተመሣሣያቸውን በሌላ ሀገር ማግኘት ይቻል ነበር። ነገር ግን አላገኘሁም፤ እያለች ሲልቪያ ፅፋለች።

 

ሲልቪያ ስትገልፅ ላሊበላ የአክሡም ዘመን ቀጣይ ኪነ-ሕንፃ ነው።ይህ ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ እና እየበለፀገ መጥቶ ላሊበላ ዘንድ ሲደርስ በእጅጉ ፍፁምነትን ተላብሶ መውጣቱን ፅፋለች። ሲልቪያ ላሊበላን ጨምሮ አያሌ የኢትዮጵያን ታሪኮች በመፃፍ በአለም ላይ ያስተዋወቀችን ታላቅ እንግሊዛዊት ናት። ሲልቪያ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ስትወረር ለሐገራችን የታገለች የቁርጥ ቀን ወዳጃችን ናት። ወደ ኢትዮጵያም መጥታ እዚሁ ኖራ ነው ይህችን አለም በሞት የተሠናበተችው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖትም ተጠምቃ የክርስትና ስም ወጥቶላት ኖራለች። ቀብሯም የተፈፀመው እዚሁ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው።

 

የሲልቪያ ፓንክረስት ብቸኛ ልጇ የሆኑት አንጋፋው የታሪክ ሊቅ ኘሮፌሠር ሪቻርድ ፓንክረስትን ስለ ላሊበላ አብተ-ክርስትያናት አሠራር ተደጋጋሚ ቃለ-መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። እርሣቸው ሲናገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከላሊበላ በፊት ከ150 በላይ አብያተ-ክርስትያናት ከቋጥኞች እየተፈለፈሉ ተሠርተዋል። ያ ጥበብ እያደገ መጥቶ ነው ላስታ ቡግና ውስጥ ቅዱስ ላሊበላ ካለምንም የኮንሥትራክሽን ስህተት ብርቅዬ ኪነ-ሕንፃዎችን የገነባው። ይሔ ጥበብ የመነጨው ከዚሁ ከኢትዮጵያ ውስጥ ነው በማለት ሪቻርድ ፓንክረስት ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ እስራ ምዕት/ሚሊኒየም/ን በማስመልከት አንድ ዶክመንተሪ ፊልም በ1999 ዓ.ም ከጓደኞቼ ከኤሚ እንግዳ እና ከአመለወርቅ ታደሰ ጋር በመሆን ሠርተን ነበር። ፊልሙ የ1፡30 የሚፈጅ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎችና ታሪክ ላይ ነበር። የፊልሙ ርዕስ Lalibela:-Wonders and Mystery ይሠኛል። በአማርኛ ላሊበላ ትንግርትና ምስጢራት ልንለው እንችላለን።

 

በዚህ ፊልም ውስጥ በርካታ የታሪክ ሠዎች፤ የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች እና ተንታኞች  ተሣትፈውበታል። ፊልሙ እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም ለንደን የሚገኘው የብሪትሽ ሙዚየም ምርጥ የአፍሪካ ዶክመንተሪ ብሎት ለንደን ውስጥ ቀኑን ሙሉ እንዲታይ አድርጐታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በልዩ ልዩ የአውሮፓ ከተሞች አንዲሁም በአሜሪካ የአለም ባንክ ጽ/ቤት እና በበርካታ ስቴቶች እንዲታይ ተደርጓል።

ይህ ፊልም የተወደደለት የአቀራረፅ ጥራቱ እና ቴክኖሎጂው የረቀቀ ሆኖ አይደለም። ፊልሙ የተወደደው በውስጡ ባለው የቅዱስ ላሊበላ ታሪክ ነው። በሠው ልጅ ታሪክ ውስጥ ኘላኔቷ ካሏት ትንግርቶች መካከል አንዱ ላሊበላ በመሆኑ ነው።

 

ላሊበላ ፎቅ ቤትን ወደ ላይ አይደለም የሰራው። አለት እየፈለፈለ ወደ ታች ነው የሠራው። ሰዓሊ እና ቀራፂ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጥበብ መምሕር የሆነው በቀለ መኮንን ሲናገር የሰው ልጅ ወደ ታች ፎቅ ቤት የሠራው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይላል። እሡም ቅዱስ ላሊበላ ነው።

 

ዶ/ር አያሌው ሲሣይ፡- የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መንግንስት ታሪክ የተሠኘ መፅሐፍ አላቸው። በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ስለ ዛጉዌ ሥርወ መንግሥት እና ስለ ነገስታቱ ብዙ ማብራሪያ ሠጥተዋል። በተለይ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ሲፅፉ የዚህ ንጉስ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን እንደነበር አውስተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ደግሞ በላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር ጥበብ በፍቀር የወደቀ ሠው ነው። ምክንያቱም የአብራኩን ክፋይ ልጁን ቤተ-ላሊበላ በማለት ስም ሰይሞለታል። ላሊበላ ለራሡ ማረፊያ የሚሆን ቤት አልሠራም። ቤተ-መንግስቱ የት እንደሆነ አይታወቅም። ነገር ግን በርካታ አብያተ-ክርስትያናትን አሣንጿል። የአሠራራቸው ምስጢር እስከ ዛሬ ድረስ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ስለዚህ ፋሲል የላሊበላን ቅንነት እና ጥበበኝነት ለማስታወስ የልጁን ስም ቤተ-ላሊበላ በማለት ሰየመው።

 

ላስታ ውስጥ ተወልደው ለከፍተኛ ደረጃ ከደረሡ ሰዎች መካከል አንዱ ዲያቆን መንግሥቱ ጐበዜ ነው። መንግሥቱ ጐበዜ በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪውን ሲሠራ በላሊበላ ላይ ነው ጥናቱን ያደረገው። ሁለተኛ ድግሪውን በአርኪዮሎጂ ሲሠራም መንግሥቱ ጐበዜ ጥናት ያደረገው በላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች ላይ ነው።

የዚህች ኘላኔት ድንቅዬ ስራ ነው ላሊበላ በማለት የሚናገሩት ኘሮፌሰር ዴቪድ ራፍካይንዳ ናቸው። ኘሮፌሰር ራፍካይንዳ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የታወቁ የአርክቴክቸር /የኪነ-ሕንፃ/ ታሪክ ተመራማሪ ናቸው። እርሣቸው ሲናገሩ ላሊበላ እንዴት እንደተሠራ ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ። ለምሣሌ አለተ ሲፈለፈል ምን ታስቦ ነው? አርክቴክቱ ማን ነው? ምን ላይ ዲዛይኑ ተሠራ? የመሣሠሉት ጥያቄዎች በሙሉ ሊመለሱ አይችሉም። ስለዚህ ምስጢር ወይም Mystery ነው በማለት ኘሮፌሰር ዴቪድ ራፍካይንድ ይገልፃሉ።

 

ላሊበላ ሀገሩ ኢትዮጵያን 40 አመታት መርቷታል። በዘመነ ስልጣኔ የሐገሩን ዜጐች መብትና ጥቅማቸውን ጠብቆ የኖረላቸው መሪ ነበር። ግብፆች በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የበላይነት ያስቆመም መሪ ነበር። አባይን እገድባለሁ እያለ በየጊዜው ስለሚነሣ ግብፅ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚገባውን ወሮታ በየጊዜው ትከፍል ነበር።

ላሊበላ ቄስ ሆኖ ሲቀድስ፤ ንጉስ ሆኖ ሀገረ ኢትዮጵያን የመራ፤ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስመ ገናና መሪ ነበር።

ኢትዮጵያን በአለም ላይ ስመ ገናና እንድትሆን ካደረጓት ስራዎች መካከልም የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል ኪነ-ሕንፃዎቸ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ እፁብ ድንቅ ከሆኑ የሠው ልጅ ስራዎች መካከል አንዱ አድርጓቸው በአለም ቅርፅነት ከመዘገባቸው ቆይቷል። ላሊበላ በሠራቸው ስራዎች ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች። መልካም መሪ በሰራው ስራ ትውልድ ሁሉ ይጠቀማል። ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ቱሪስት አብዛኛው ላሊበላን ለማየት ነው። ሀገርም ትውልድም በላሊበላ ስራ ይጠቀማል።

 

ዛሬ ምሽት ላይ የገና በአል ላስታ ላሊበላ ውስጥ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ከሐገሪቱ ልዩ ልዩ ስፍራዎቸ የመጡ ምዕመናን እና ከአለም ዙሪያ ገናን ላስታ ውስጥ ለማክበር የሚመጡ ሠዎች 10 የላሊበላን ረቂቅ ኪነ-ሕንፃዎችን ያያሉ።

 

በአንደኛው ምድብ፡-

1ኛ ቤተ-መድኃኔ ዓለም

2ኛ ቤተ-ማርያም

3ኛ ቤተ -መስቀል

4ኛ ቤተ-ደናግል

5ኛ ቤተ-ደብረ ሲና /በጣራው ሥር ቤተ-ሚካኤል፤ ቤተ ጐሎጐታና የሥላሴ መቅደስ አሉ/

 

በሁለተኛው ምድብ

6ኛ ቤተ-ገብርኤልና ሩፋኤል /በአንድ ጣሪያ ውስጥ ያሉ/

7ኛ ቤተ-መርቆርዮስ

8ኛ ቤተ-አማኑኤል

9ኛ ቤተ-አባሊባኖስ

 

ሦስተኛው ምድብ በብቸኛነት ራሡን ችሎ የሚገኝ

10ኛ ቤተ-ጊዮርጊስ ናቸው።

ዛሬ ምሽት በተለይ የቅዱስ ላሊበላ እና የጌታችን የመድሃኒታችን የእየሡስ ክርስቶስ ልደት በቤተ-ማርም ቅፅር ግቢ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ይከበራል።

ዶ/ር አያሌው ሲሣይ በመጽሐፋቸው ሲገልፁ የአከባበሩ ሥነ-ሥርዓት በሌሎች የኢትዮጵያ አብያት ክርስትያናት በሙሉ ከሚደረገው ለየት ያለና እጅግ በጣም የደመቀ በጣሪያ -የለሸ ቦታ ላይ የሚከናወን ነው። የአስሩ የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናትና የዙሪያ ገቡ አድባራት፤ ካህናት፤ መዘምራን፤ ዲያቆናት፤ ቀሳውስት፤ በጥንግ ድርብ፤ በሸማ፤ በካባ፤ በማጌጥ እና በማሸብረቅ፤ መቋሚያ፤ ፀናጽል፤ ከበሮ፤ መስቀል፤ ጽንሐሕ፤ ዣንጥላ እና የመሣሠሉትን ይዘው ግማሾቹ ማሚጋራ ተብሎ በሚታወቀው በቤተ-ማርያም የቋጥኘ አጥር ዙሪያ ከላይ ወጥተው በመደርደር ሲሰለፉ፤ ቀሪዎቹ በበኩላቸው ከታች ከግቢው ከወለሉ በመሆን ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ ይላሉ። ሲተረጐምም የዓለም መድሐኒት ዛሬ ተወልደ  የሚለውን የቅዱስ ያሬድን ዕዝል ዜማ ተራ በተራ እየተቀባበሉ ይወርብታል። ይዘምሩታል።

ላሊበላ ኪነ-ሕንፃው ተአምር፤ ሐይማኖታዊው ክብረ-በዓል መንፈስን የሚያፀዳ፤ ቦታው የተባረከና የቅዱሣን ደብር ነው። ላሊበላ ፍጹም ደግ እና መንፈሳዊ ሰብእናው በእጅጉ ጎልቶ የወጣ ሰው በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ብለዋለች። እናም ላስታ ላሊበላን እንያት። መልካም የልደት በአል ይሁንላችሁ።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
17684 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us