ማንበብ ለምን ይጠቅማል? ቀሽሙ ጥያቄ!

Wednesday, 13 January 2016 14:26

 

            

ከጥበቡ በለጠ

 

የ2007 እና 2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ የንባብ አምባሳደር ተብዬ ከሌሎች 11 ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተመርጫለሁ። እነዚህም ኢትዮጵያን ኬሚካል ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ፤ ደራሲና ሀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፤ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ አቶ ታደሰ ጥላሁን የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ፤ ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ፤ የበርካታ ቤተ-መጻህፍት መስራችዋ ወ/ሮ ማህሌት ኃይለማርያም፤ ፕሮፌሰር ዓለምጸሀይ መኮንን፤ አንጋፋው ድምጻዊ አለማየሁ እሼቴ፤ አክቲቪስቷ የትነበርሽ ንጉሴ፤ ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም እና ሰአሊ በቀለ መኮንን ናቸው። ሁላችንም የተመረጥነው በየተሰማራንበት ሙያ ህዝባችን እንዲያነብ ግፊት የማድረግና የመቀስቀስ ስራ እንድንሰራ ነው። እኔም የተሰማራሁበት ሙያ ጋዜጠኝነት ስለሆነ በዚሁ ሙያዬ አነሰም በዛ እየሞከርኩ ነው ብዬ አስባለሁ።

በዚህች ኢትዮጵያ እያልን በምንጠራት ሀገር የንባብ ባህል በከፍተኛ ሁኔታ የወደቀበት ነው። 90 ሚሊየን ለሚገመት ህዝብ አምስት ሺ ኮፒ መጽሀፍት ታትሞ የሚቀርብባት ሀገር ናት። ጋዜጣና መጽሄትም እጅግ በሚገርም አነስተኛ ቁጥር የሚታተምባት ሀገር ናት። ንባብ በወደቀበት ሀገር ትምህርት አያድግም። ስልጣኔ አይኖርም። የችግርና የችጋር ሀገር ይሆናል። ስለዚህ ንባብ ለምን ይጠቅማል ብሎ መጠየቅ የጅል ጥያቄ ሳይሆን ይቀራል?

ሀምሌ ወር 2007 ዓ.ም በማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ አማካይነት በተዘጋጀው ንባብ ለህይወት በተሰኘው ዝግጅት ላይ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር። ይህን ጽሁፍ አምባሳደር ስለሆንኩም ጭምር እስኪ ለናንተም ላውጋችሁ ብዬ እነሆ እላለሁ።

ብዙውን ጊዜ ተደጋግሞ የሚነገር ጉዳይ አለ። ይህም ስለ መጻህፍትና ንባብ ነው። በልዩ ልዩ ሀገራት ስለ እነዚህ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ተጽፎባቸዋል፣ ብዙ ውይይትና ጥናት ተደርጐባቸዋል። በሀገራችንም ቢሆን አንድ ጊዜ በመፈክር፣ አንድ ጊዜ በውይይት፣ ሌላ ጊዜ በጽሁፍ አያሌ መድረኮች ተከፍቶላቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ እየተዘጋጀ የጉዳዩ አሳሳቢነት በሁላችንም ዘንድ እየሰረፀ በመግባት ላይ ይገኛል።

በ1987 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል ውስጥ ተጋብዞ የመጣውን ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን አንድ ተማሪ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበለት፡-

“ጋሽ ስብሐት የመጽሐፍት ንባብ ለምን ይጠቅማል? እስኪ ይህን ጉዳይ አስረዳን?” አለው።

ጋሽ ስብሐት ሲመልስ፤ “ይህን ቀሽም ጥያቄህን ወዲያ ተውና ይልቅ አንድ ታሪክ ላጫውትህ…” ብሎ ወግ ጀመረ።

ስብሐት ጥያቄውን ለምን ‘ቀሽም’ አለው?

የስብሐት ወግ ምን ነበር?

እስኪ ካወራው ወግ ልጀምር።

የስብሐት ወግ ያተኮረው ሰር ዋልተር ስኮት ስለተባለ ሰው ነበር። ይህ ሰው በዚህች ምድር ላይ ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ከመፃሕፍት ጋር አሳልፏል። ዋልተር ስኮት በዓለም ላይ የተፃፉ ታሪኮችን ሁሉ ሲያነብ ሲመራመር የኖረ ሰው ነው። እርሱ ያልኖረበትን፣ ከወዲያኛው ዓለም የነበረውን የሰው ልጅ ታሪክ አንብቦ፣ እርሱ ያለበትን ገሀድ ዓለም በመፃህፍቱ አማካይነት አይቶ፣ መጪውንም ዘመን ተረድቶ ይህችን ዓለም የሚሰናበትበት የመጨረሻዋ ሰዓት ደረሰች። ታዲያ በዚህች ሰዓት ቄስና ሽማግሌ ጠርቶ ኑዛዜ ውስጥ አልገባም። ይልቅ ወደ ቤተ-መፅህፍቴ ውሰዱኝ አለ። እዚያም በዊልቸር ወሰዱት። መፃህፍቶቹን አያቸው። አመሰገናቸው። ውስጤ እንዳይጐድል አደረጋችሁኝ፣ ሰብእናዬን ሞላችሁት፣ እናም ሳልሳቀቅ ወደ ሌላው ዓለም ደግሞ ልጓዝ ነው። እዚህ ሙሉ ሠው ስለነበርኩ እዚያ ጐድዬ የምታይበት ምክንያት የለም። ችርስ ብሏቸው ነው የተሰናበታቸው በማለት ስብሐት ያጫወተን ወግ ዛሬም አይረሳኝም።

ስብሐት “የመፃሕፍት ንባብ ለምን ይጠቅማል?” ተብሎ ሲጠየቅ ለምን ቀሽም ጥያቄ ነው አለው? ምናልባት ይህን ጥያቄ ስብሐት የሚያየው “ምግብ ለምን ይጠቅማል?” ከሚለው ጋር ሊሆን ይችላል። የምግብን ጠቀሜታ የምናስረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ ምግብን ሊመገብ ለፈለገ ሰው መሆን አለበት።

ስለ ምግብና ስለ መፃሕፍት ካነሳን ዘንዳ አንድ ሰው ትዝ ይሉናል። ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ። እኚህ ሰው የብዕራቸው ለዛ እና ማራኪነት ተጠግቦ አያልቅም። ከ17 በላይ መፃሕፍትን ለንባብ ያበቁ ናቸው። በሙዚቃው ዓለም እንኳ ለታላቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ “የትዝታዬ እናት” የሚለውን ዘፈኑን ጨምሮ 22 ግጥምና ዜማ ያዘፈኑት የጥበብ ሊቅ ናቸው። እርሳቸው በ1972 ዓ.ም “የእውቀት አውራ ጐዳና” በሚል ርዕስ ስለ መፃህፍትና ንባብ ግሩም የሆነ ጽሁፍ አሳትመዋል። በዚህ ጽሁፋቸው ውስጥ ስለ ሰው ልጅ የእድሜ ዘመን ሲገምቱ ምናልባት 70 ዓመታትን በዚህች ምድር ላይ ቢቆይ ለስጋው ምግብ፣ ለህሊናው መፃህፍት እንደሚያስፈልጉት አስረድተው አንድ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። ይህም አንድ ሰው በምድር ላይ 70 ዓመታት ቢቆይ 100 ቶን ምግብ ይመገባል። ይህን መቶ ቶን ምግብ ለመመገብ 41 ሺህ 400 ሰዓት ማላመጥ እንዳለበት ጽፈዋል። መፃህፍት ግን በደራሲያን ተዘጋጅተው፣ ታትመው ለንባብ ብቻ የመጡ ናቸው። ምንም ዓይነት ማበጠር፣ ማንፈስ እና ማስፈጨት ሳያስፈልጋቸው ገጾቻቸውን በማገላበጥ ብቻ እያነበብን የሕይወትን ስንቅ፣ የኑሮን ማዕዘን የምናቆምባቸው ዓምዶች መሆናቸውን ፀሐፊው ይገልፃሉ።

እኚሁ ታዋቂ የኢትዮጵያ ደራሲ ስለ መፃሕፍትና ንባብ ሲጽፉ፣ ትልልቅ ምሳሌዎችን እያነሱ ነበር። የኋለኛውን ዘመን ብናየው እንኳ ታላላቅ ስልጣኔዎች እየታዩ የከሰሙበት፣ ጀግኖች እና አዋቂዎች፣ ፈላስፋዎች፣ የፈጠራ ሰዎች፣ ሊቀ-ጠበብቶች ብቅ እያሉ ያለፉበትን የሕይወት አውራ ጐዳናን እንታዘባለን። ታዲያ በዚህ ውስጥ የተገነቡ ታላላቅ ኪነ-ህንፃዎች በዘመን ሩጫ እና ግልምጫ ደክመው ይወድቃሉ፤ ይፈርሳሉ። የዓለምን ሕግ የቀየሩ ሊቃውንትም በአፀደ ሥጋ ይለዩናል። ከመጣው የሰው ዘር ጋር ሁሉ በመኖር ሕያው ምስክር በመሆን የሚዘልቁት መፃህፍት ናቸው።

የግሪኮቹ የአቴና ጥንታዊ ኪነ-ሕንፃዎች፣ የጥናትና የምርምር ማዕከሎች ዛሬ የሉም። የሮማውያን አስደማሚ ግንባታዎች ፍርስራሻቸው ካልሆነ ዋናው ግንባታ ዛሬ የለም። የባቢሎና ኢራቅ ውሰጥ የታየው ያ ስልጣኔ ለምስክርነት እንዳይበቃ እየፈራረሰ ነው። የሶርያ እና የፐርሺያ አጓጊ ጥበቦች በልዩ ልዩ ምክንያት ከስመዋል። ነገር ግን ያለፈውን ሁሉ እንዲህ ነበር እያሉ የሚያወጉት መፃሕፍት ናቸው። መፃሕፍት በቀላሉ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ የሚችሉ ሀብቶች በመሆናቸው እንደዋዛ የሚጠፉ አይደሉም። ለዚህም ነው ብዙ ፈላስፋዎች ስለ መፃሕፍትና ንባብ ሲገልፁ ትልቅ ቦታ እና ክብር የሚሰጧቸው።

መፃሕፍት የትውልድ ድልድይ ሆነው ሩቁን ከቅርቡ ብሎም ከመጪው የሰው ዘር ጋር የሚያገናኙ ናቸው። ያልኖርንባቸውን ዘመናት እያሳዩን የሚያስተምሩን፣ ከብዙ ልሂቃን፣ ጠቢባን፣ ፈላስፋዎች፣ ደራሲያን፣ ሳይንቲስቶች ጋር ጓደኛ የሚያደርጉን ልዩ ገፀ-በረከቶች ናቸው። መፃሕፍትን ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል፤ የተሟላ ሰብዕና ይሰጣል የሚባለውም ለዚህ ነው። ከምሁራን አደባባይ እና ሸንጐ ላይ አስቀምጠው የዚህችን ዓለም ምስጢር ወለል አድርገው ያሳዩናል።

አንዳንድ ጠቢባን ሲናገሩ፤ በዓለማችን ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩን ንባብን ሳይሆን ማንበብ እንደምንችል ነው። ስለዚህ ከዩኒቨርሲቲ መመረቅ ብቻውን ሙሉ ሰው አያደርግም። የተሟላ ሰብዕና የሚሰጠው ንባብ ነው ሲሉ ይደመጣል። ታዲያ በዚህ አባባል እንድንረጋጋ የሚያደርገንንም አንድ ኢትዮጵያዊ የንባብ ጀግና ለምን አናስታውሰውም።

ጳውሎስ ኞኞ። ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ፀሐፊ፣ ዲስኩር አዋቂ እና የብዙ ችሎታዎች መገለጫ የሆነ ሰው። ጳውሎስ የቀለም ትምህርቱን እስከ አራተኛ ክፍል መማሩን ያወቀ አንድ ሰው “ስንተኛ ክፍል ነህ?” ብሎ ጠየቀው። ጳውሎስም ሲመልስ፤ እኔ የምለው አንብቡ፤ አንብቡ፤ አንብቡ፤ ነው!  ብሏል።

ጳውሎስ ኞኞ በንባብ ብቻ የታላላቅ ሰዎች ሸንጐ ላይ መቀመጥ የቻለ ከኢትዮጵያ ውስጥ ቦግ ያለ የዕውቀት ብርሃን ነበር። ጳውሎስ አዘውትሮ በማንበቡ ብቻ ምርጥ የታሪክ ፀሐፊ የሆነ፣ ምርጥ ጋዜጠኛ የነበረ እና የተዋጣለት ደራሲ ጭምር ሆኖ ያለፈ በትውልዶች ታሪክ ውስጥ ሁሌም ስሙ የሚጠራ ባለዝና ነው።

ዛሬም በሕይወት ያለውን ኢትዮጵያዊ የስዕል ሊቅ ወርቁ ማሞን መጥቀስም ይቻላል። ወርቁ ማሞ በልጅነቱ የወደቀ ነገር አግኝቶ ሲቀጠቅጥ፣ ነገሩ ቦምብ ነበርና ፈንድቶ ሁለቱንም እጆቹን እንዲያጣ ምክንያት ሆነው። ታዲያ ወርቁ ሁለት እጆቹ ባይኖሩም ከምሁራን ሸንጐ ላይ መቀመጡን የከለከለው አንዳች ነገር የለም። አነበበ፤ መፃፍን ተማረ፣ ስዕል ጀመረ። በንባብ ውስጥ የሚያገኛቸው እውቀቶች እያየሉ መጥተው ወርቁ ማሞን እስከ ሩሲያ ድረስ ወስደውት የስነ-ስዕልን ጥልቅ ምስጢር ተምሮ፣ በሙያውም አንቱ የተባለ ሊቅ ለመሆን የበቃ ነው። መፃሕፍት የተስፋ ምርኩዝ ሆነው ከወደቅንበት አዘቅት አንስተው የሀሴት ማማ ላይ የሚያደርሱን ረዳቶቻችን መሆናቸው በወርቁ ማሞ ሕይወትና ሥራ እንማራለን።

አርተር ካቫና የተባለ የአየርላንድ ዜጋ እጆች እና እግሮች አልነበሩትም። ግን እርሱም ቢሆን በማንበቡ ብቻ ለብዙ ታላላቅ መድረኮች የበቃ ብሎም በፓርላማ ውስጥ እስከ መማክርት አባል እስከመሆን የደረሰ ሰው ነው። ታላቁ ደራሲ ጆን ሚልተን እና ሆሜር ዓይነ-ስውራን ነበሩ። ሔለን ኬለር ዓይነ-ስውር እና መስማት የተሳናት ሴት ነበረች። ታዲያ ሔለን በእጆቿ እየዳሰሰች ማንበብን ተማረች። በማንበቧ ብቻ ታላቅ ሰው ሆና ዓለምን አስደምማ ለሰው ልጆች ሁሉ መነቃቂያ ሆና አልፋልች።

መፃሕፍት በዓለም ላይ ሁሉ እንደፈለግን መግባትና መውጣት እንድንችል የሚያደርጉን ቪዛ ያላቸው ፓስፖርቶች ናቸው። የየሀገሩን ወግና ልማድ፣ ታሪክና ፍልስፍና፣ የሕዝቦችን አስተሳሰብና ባህሪ ወዘተ እንደልባችን እንድናይ እንድናውቅ የሚያደርጉን ከልካይ የሌለባቸው ዘላለማዊ ሀብቶቻችን ናቸው።

ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ በምንኖረው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ቆም ብለን ስለ መፃሕፍትና ንባባችን ባሕል ማየት ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ ነው። ዛሬ በሕይወት ላለነው ኢትዮጵያውያን አያሌ የጋራ መኖርያ ቤቶች እየተገነቡልን ነው። ሪል ስቴቶችም አያሌዎች ናቸው። እነዚህ ቤቶች መኝታ ክፍል፣ እንግዳ መቀበያ ሳሎን፣ ኪችን እና መፀዳጃ ቤት ሲኖራቸው የመጽሐፍት ቤት ግን የላቸውም። መፃሕፍት ውስጥ ብዙ ሰዎች አሉ። ታላላቅ ምሁራን፣ ነገስታት፣ ሕዝቦች፣ ማኅበረሰቦች ወዘተ ውስጣቸው ይርመሰመሳሉ። ሀገራት በመፅሐፍት ውስጥ ይገነባሉ፣ ጦርነቶች ይካሄዳሉ፣ አሸናፊና ተሸናፊዎች ታሪክ ይጽፋሉ። ሕዝብ ፍርድ ይሰጣል። ወንዞች ይፈሳሉ። ማዕበሎች ይነሳሉ። መፅሕፍት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ያለባቸው የሕይወት ድርሳን ናቸው። ስለዚህ ለመፃሕፍቶቻችንም የክብር ቤት፣ አንዲት ክፍል ያስፈልጋቸዋል። የመፃሕፍት ቤት የሌለው ሕንፃ መስኮት እንደሌለው ቤት ጨለማ ነው ይባላል።

ሌላው ራሳችንን የምንጠይቀው ጥያቄ ምን ያህል መፅሐፍት እናነባለን? በወር ስንት መፃሕፍት? በዓመት ምን ያህል ይሆናሉ? በሕይወት ዘመናችንስ ስንት መፃሕፍት እናንብብ? የሚሉት ነጥቦች መሠረታዊ ናቸው። አንድ ሰው ባለማንበቡ ምን ያጣል? ያላነበበ ምን ይሆናል? ባለማንበቤ ምን እሆናለሁ ብለው ዛሬም የሚጠይቁ ‘የዋህ’ አሉ። ምን እንበላቸው?

ታላቁ ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ ባላነብ ኖሮ አልባሌ ሰው ሆኜ እቀር ነበር ብሏል። በማንበቤ ስሜቴን ገዛሁ፤ አስተዋይ እና አመዛዝኜ የምሰራ ሰው ሆኛለሁ ሲል ጽፏል። የመፃሕፍት ንባብ ከጭካኔ ያርቃል፣ ከፍርደ-ገምድልነት ይሰውራል። ለሰው ልጅ ያለንን ከበሬታና ፍቅር ይጨምራል። ትሕትና ይሰጣል። ከጭንቀት፣ ከድብርት፣ ከስቃይ ይገላግላል። ንባብ ሕይወት እንዳትከብደን ማቅለያ መሣሪያ መሆኑን ነግረውን አያሌዎች እየፃፉ አልፈዋል።

ኢትዮጵያም የኪነ-ጥበብ ሀገር እንደሆነች ይታወቃል። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ በቅርቡ 12 ጥንታዊ የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሁፍ ሀብቶች የዓለም ድንቅ ቅርሶች ናቸው በማለት በዶክመንተሪ መዝገብ ውስጥ አስፍሯቸዋል። ገና ብዙ የጥበብ ቅርሶችንም ሊመዘግብ በሂደት ላይ ነው። ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የጽሁፍ ቅርሶችን ሰርተው ሲያልፉ አሁን ያለነው ትውልዶች ዛሬ ላይ ምን እየሰራን ነው ብለን ማሰብ የሚገባን ወቅት ነው።

በገሃድ እየታየ የመጣውን የአንባቢ ቁጥር መጨመርን መሠረት አድርገው መጽሐፍትን ለመሸቀጥ ብቻ እጅግ የወረዱ የብልግና ጽሁፎችን ይዘው ብቅ የሚሉ ሰዎችም ተከስተዋል። እነዚህ ሰዎች እስከ አሁን ስንነጋገርበት የነበረውን ርዕሰ ጉዳይ አይወክሉም። ግን እየተገነባ ላለው የንባብ ባህላችን ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከአሁኑ ሃይ ካልተባለ ‘የዝሙት ሥነ-ጽሁፍን’ ሊያስፋፉ ይችላሉ።

ስለ መፃሕፍትና ንባብ አንስቶ መጨረስ አይቻልም። ማለቂያ የሌለውን ጨዋታ ነው ያነሳሁት። አንድ ግዜ ጓደኛችን ከዩኒቨርሲቲ ተመረቀና አርቲስት ስዩም ተፈራን መንገድ ላይ አገኘው። ጓደኛችንም ደስ ብሎት “ስዩሜ ትምህርት ጨረስኩ!” እያለ አቀፈው። ስዩምም “የማያልቀውን ጨስከው?” አለው። እኔም ስለ መፃህፍትና ንባብ የማያልቀውን ርዕሰ ጉዳይ ነው የጀመርኩት። ብቻ የተወሰነ ነገር እንዲህ ከተወራወርን በቂ ይመስለኛል። የመፃሕፍት ዓውደ-ርዕዩም ለተጨዋወትነው ሁሉ የመአዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግለናል። ለአዘጋጆቹ ለነቢኒያም ከበደ ታላቅ ክብርና ምስጋና አለኝ።

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
17310 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us