Print this page

ታቦታቱን ስናጅብ

Friday, 22 January 2016 12:45

 

በድንበሩ ስዩም

 

ወቅቱ ጥምቀት ነው። ሕዝበ ክርስትያን በነቂስ ወጥቶ ጥምቀትን ያከብራል። ሁሉም በተቻለው አቅም ነጭ ፀአዳ ለብሶና ተጫምቶ አምሮበት ነው የሚወጣው። ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ የሚሠኝ አባባል ሁሉ አለ። ታቦታቱን የምናጅበው ፍፁም በደስታ ነው። በእልልታ' በዝማሬ' በሽብሸባ 'በሆታ'በጭብጨባ ነው። ይሔ የዘመናት አከባበራችን ነው። ወደፊትም ይቀጥላል። ግን ደግሞ ቆም ብለን አንድ ሃሣብ እናስብ፤ ታቦታቱን ስናጅብ አንድ ነገር ብናክልበትስ?

 

ታቦታቱን ስናጅብ ኢትዮጵያን እናስብ። ይህ ሁሉ ሕዝበ ክርስትያ ያለባት ጥንታዊት ሀገር ምነው ድሃ፤ የድሆች ድሃ ሆነች? ታቦታቱን ሰናጅብ የብዙ የቃል ኪዳን ሐገር ናት የምንላት ኢትዮጵያ ለምን ጉስቁልናዋ በዛ? ለምን የአለም ጭራ ሆነች? ወንጌል ቀድሞ የተሠበከባት ጥንታዊ ሀገር ለምን በምፅዋት ትኖራለች? የብዙ ሺ አድባራት ገዳማት መኖርያ የሆነች ሐገር ለምንስ የችጋር እና የችግረኞች ሀገር ሆነች?

 

ታቦታቱን ስናጅብ ፈጣሪን ስለ ኢትዮጵያ እንለምነው፤ እንማፀነው። ታቦታቱን ስናጅብ ኢትዮጵያ ሐገረ እግዚአብሔር እያልናት ለምን በድህነት ምች ትመታለች? ፈጣሪ አንተው ጐብኛት፤ ዳሣት እያልን እንማፀነው።

ታቦታቱን ስናጅብ ፈጣሪን ስለ ሀገራችን ተንበርክከን ተደፍተን እንለምነው። ኢትዮጵያን የረሃብ የችጋር የድህነት የተመፅዋች ሀገር አታድርጋት እንበለው። ሕፃናት የሚራቡባት' ወላጆች የሚራቡባት' በጠኔ የሚወድቁባት አታድርጋት እያልን እንለምነው። አቤቱ ሆይ ይህችን የአማኞች ሀገር ጐብኛት፤ ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት አድርጋትና በልተው የሚያድሩባት ሕፃናት ተመችቷቸው የሚቦርቁባት የሐሴት ምድር አድርጋት እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ ጥንት ከአለም ቀድማ የብዙ ስልጣኔዎቸ መጠቀሻ የነበረችው ኢትዮጵያ ለምን ወደቀች? ለምን የስልጣኔዎች ጭራ ሆነች? እባክህ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያን ባርክ፤ ለሕዝቦቿም አእምሮ ስጣቸው። እንዲያው እንዲመራመሩ እንዲፈጥሩ ሐገራቸውን ከተመፅዋችነት እንዲያወጡ ጥበብ ስጣቸው እያልን እንፀልይ።

 

ታቦታቱን ስናጅብ አቤቱ ጌታችን መድሃኒታችን እየሡስ ክርስቶስ ሆይ በየመንገዱ የወደቁትን' ጐዳና የተኙትን' ሀገሩን እየሞሉ ያሉትን የኔ ቢጢዎች አስባቸው። እንደሠው አድርጋቸው፤ እንደ ፍጡር እነሡም እንዲኖሩ አድርጋቸው፤ ከወደቁበት የሚነሡበት ሀይልና ብርታት ስጣቸው፤ ጥበብ ስጣቸው፤ ረድኤት ስጣቸው እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅበ፡- ፈጣሪ ሆይ ሕክምና አጥተው፤ የሚታከሙበት አጥተው በብዙ ደዌዎች እየተሠቃዩ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ጐብኛቸው። በየ ሆስፒታሉ ተኝተው ከመድሃኒቱ ጋር ያልተገናኙትን ዳብሣቸው፤ ታሞ መዳን የጠፋባትን ኢትዮጵያን የፈውስ ምድር አድርጋት እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ እንዲህም እያልን እንማፀነው፡- ሐኪሙ በሽተኛውን የማይዘርፍበት ሐገር አድርጋት፤ ሐኪሙ ሕሙማኖችን የሚፈውስባት ሀገር አድርጋት፤ መሪዎቸ የማይዋሹባት' የሕዝባቸውን ሕይወት የሚለውጡባት' ሕዝባቸውን የማያሠቃዩባት' ሙሰኞች የማይገኙባት' ሕዝቡን የማይጨቁኑባት አድረጋት። አቤቱ ሆይ ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ምድርህ ናትና ሕዝቦቿን ነፃ አድርጋቸው። ከሐሣብ ከጭንቀት ገላግላቸው። ከውዥንብር እና ከድንጋጤ ከመሸማቀቅ ሕይወት አውጣቸው። በነፃነት እንዲያስቡ እና እንዲሠሩ ጥበብና ሐይልን ስጣቸው እያልን እንማፀነው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ፡- በየቀኑ ስለሚሠደዱት ኢትዮጵያዊያን እንለምነው። ሀገሩን ጥሎ ባሕር እያቋረጠ ያለቀው አልቆ ከስደት ምድሩ የሚደርሰውን ኢትዮጵያዊ አስበው። አቤቱ ሆይ የስደት ሕይወቱ ሣያንስ በሔደበት ምድር የሚገረፈው' የሚሠቀለውን' የሚገደለውን አስበው። ጌታ ሆይ የስቃይ ሰለባ የሆኑ ስደተኛ ወገኖቻችንን ዳብሣቸው፤ ሀይልና ብርታት ስጣቸው፤ ኢትዮጵያም ዜጐቿ የሚሠደዱባት የችግር አገር አታድርጋት። ኢትዮጵያ የሠዎች መሠባሠቢያ የአንድነት የብልፅግና የአብሮ የመኖር የቸርነት እና የረድኤት ሐገር አድርግልን እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ፡- እንዲህም እያልን እንማፀነው፡-አቤቱ ሆይ ለኢትዮጵያዊያን ልቦና ስጣቸው፤ በዘር እንዳይቧደኑ' በጐሣ 'በጐጥ' በቀበሌ' በሰፈር አጥር እየሠሩ ሠው የመባላቸውን ፍቅር እንዳያጠፉት ጥበብን ስጣቸው። አንድ ሆነው ኢትዮጵያዊያን ነን ብለው፤ በፈጣሪ አምነው በፍቅር በመተሣሠብ መንፈስ ተሣስረው ሀይልና አንድነታቸውን አደርጅተው ኢትዮጵያ የምትባል የጥንቷን ገናና ሀገር ዛሬም ስሟን እና ዝናዎን አስከብረው የሚኖሩባት ምድር አድርገህ ባርካት እንበለው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ፡- በመካከላችን ያለውን የሸር' የጥላቻ' የምቀኝነት' የሰብቅ' የውሸት' የዝሙት' የሐጢያት መንፈስ አወላልቀን የምንጥልበትን ፀጋ ስጠን። ከላያችን ላይ የተገፈፈውን ላመኑበት ጉዳይ መኖርን፤ መታገልን፤ እራስን አሣልፎ መስጠትን፤ መልሠህ አጐናፅፈን። አቤቱ ሆይ፡- ቀጣፊ ትውልድ እንዳይፈጠር የተፈጠረውም እንዳይበዛ አድርግልን እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ፡- ለሐይማኖት መሪዎቻችንም ልቦና ስጣቸው የፈጣሪን ቃል እና ትምርቶችን እንዲያስተምሩ አድርጋቸው። በአለማዊው ሀሣብ እየተታለሉ ሕዝባቸውን እንዳይሸነግሉ እንዳይዋሹት አድርጋቸው። አቤቱ ሆይ፤ኢትዮጵያ አቡነ ጴጥሮስ የተሰኙ የሐይማኖት መሪ የተፈጠሩባት የሀቅ የእውነት የእምነት እና የመስዋዕትነት ሀገር ነችና ለሐይማኖት መሪዎች የአቡነ ጴጥሮሣዊነት መንፈስ በሁሉም የእምነት መሪዎች ውስጥ ታጐናፅፍ ዘንድ እንለምንሃለን። ሀገርን ወገንን ታሪክን የሚጐዳ ድርጊት ሲፈፀም የማይዋሹ የማይቀጥፉ የሀይማኖት መሪዎችን አብዛልን እያልን እንለምነው።

 

ታቦታቱን ስናጅበ፡- ፈጣሪ እምነታችንን እንዲባርክልን እንለምነው። የብዙ ሺ አድባራት እና ገዳማት መኖርያ የሆነች ኢትዮጵያ፤ የብዙ ሺ ቀሣውስትና የሐይማኖት መሪዎች መፈጠሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የብዙ አማኒያን ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ቀሣውስት ጥለዋት ወደ ውጭ የማይሠደዱባት አድርጋት። ጳጳሣት የማይሠደዱባት ሕዝባቸውንም የማይከፋፍሉባት የሕብረት ምድር አድርጋት። ፈጣሪ ሆይ በሐይማኖት መሪዎቸ ውስጥ የገባውን የመከፋፈል የመበታተን ክፉ መንፈስ በቸርነትህ እና በረድኤትህ ዳብሰው፤ አስተካክለው እያልንም እንማለደው።

 

ታቦታቱን ስናጅብ፡- ስለ መጪው ዘመንም እንለምነው። የእምነት ሐገር ኢትዮጵያ የግብረ-ሰዶማዊያን መስፋፊያ ምድር እንዳትሆን ጐብኛት እንበለው። የሐይማኖተኞች ምድር ናት በምንላት ኢትዮጵያ የግብረ-ሰዶማዊያን ጉባኤ በግልፅ ሲደረግባት በግላጭ የተቃወመ ሀይማኖተኛም ሆነ ዜጋ የጠፋባት ምድር ስለሆነች ፈጣሪ ሆይ አንተ ለሁላችንም ልቦና ስጠን፤ ሀይል ስጠን፤ የሐጢያት ፅዩፍ አድርገን እያልን አንለምነው። 

 

ታቦታቱን ስናጅብ በየ አስር ቤቱ የሚገኙትን ዜጎችም፡- አቤቱ ጌታችን አስባቸው፤ጎብኛቸው፤ጽናትን አርነትን ስጣቸው እያልን እንለምነው። ታቦታቱን ስናጅብ ፈጣሪን እንዲህ እያልን እንጠይቀው፡- ይህች የጻድቃን የሰማእታት የነቢያት መኖሪያክ የሆነችው ኢትዮጵያ ምነው ድህነትዋ በዛ? ምነው መከራዋ በዛ? መቼ ነው ከችጋር የምትወጣው? ፈጣሪ ሆይ፡- ለክብርህ መገለጫ ይሆን ዘንድ ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ በእልልታና በፍጹም ደስታ ጥምቀትህን የሚያከብረው ለእምነቱ በመገዛት ነው። ፈጣሪ ሆይ ላንተ እንዳላቸው ፍቅር አንተም አስባቸው፤ አስበን፤ አሜን።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15615 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin