በዓለ ጥምቀት

Friday, 22 January 2016 12:48

 

ከዲያቆን ብርሐኑ አድማስ

 

      ጌታችን ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ከተገለጠ በኋላ ሰው የሆነበትን የማዳን ስራውን የጀመረው በጥምቀት ነው። የተጠመቀው በሠላሳ ዘመኑ ሲሆን አጥማቂውም የካህኑ የዘካርያስ ለጅ ቅዱስ ዮሐንስ ነበር። ጌታችን በተጠመቀበት ጊዜ አብና መነፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነቱን መስክረዋል። አብ በደመና ሆኖ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ሲል መንፈስ ቅዱሰ ደግሞ በነጭ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ዐርፎ የባሕርይ አንድነታቸውን መስክሯል። ማቴ 3፤17 ዮሐ1፤32-34።

የጥምቀት በዓል የሚከበረው ከላይ የተገለፀውን የእግዚአብሔርን ማዳን ለመመስከር ነው። ይህንም ቤተ ክርስቲያናችን በዐራት ዘርፍ ትዘረዝረዋለች። እነዚህም

·         ስለዚሁ የተነገረው ትንቢት እንዲፈፀም

·         ውኃን ለመቀደስ

·         ለጥምቀት ኃይልን ለመስጠት

·    ለእኛ አርአያና መሳሌ ለመሆን ያሳየውን ትሕትና ለመመስከር እንደሆነ ቤተ ከርስትያን ትገልጻለች። የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንም ለዚሁ ለአንጽሖተ ማይ /ውኃውን ለመቀደስ/ እና ምእመናኑንም በጥምቀት /በልጅነት/ የቀደመ ኃጢአታቸው የተሠረየላቸውን ያህል በዚህ ዕለትም የሠሩት ኃጢአት ይሠረይላቸዋል ትላለች። ይህ ማለት ግን ጥምቀት ትደግማለች ማለት አይደለም። እንደ አቡነ ጎርጎርዮስ /ሊቀ ጳጳስ ዘሸዋ/ ገለጻ በረከተ ጥምቀቱን ለምእመናን በማድረስ ማሳተፍ ሥርየተ ኃጢአትን መስጠት እንጂ መላልሶ ማጥመቅ አይደለም። ልጅነት/መወለድ/ አንድ ጊዜ ብቻ ነውና።

 

የአከባበር ሥርዓቱንም ስንመለከት ከሌሎቹ በዓላት የሚለይበት መንገድ አለው። ይኸውም ታቦታቱ በዋዜማው ከቤተ-ክርስቲያን ወጥተው በሕዝብ ታጅበው እግዚአብሔርም እየተመሰገነ ወንዝ ዳር ይወርዳሉ። በዚያም ዳስ ተጥሎ/ድንኳን ተተክሎ/ ከተራም ተከትሮ ሌሊቱን መዘምራኑ በማኀሌት ካህናቱ በሰዓታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ። ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሔዱ ምሳሌ ነው። ሲነጋም ፀሎተ ቅዳሴው ተጠናቅቆ ወደ ወንዙ/የግድብ ውኃም ከሆነ ወደ ተገደበው ውኃ/ በመሔድ ፀሎተ አኮቴት ተደርሶ ዐራቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል። ወንዝም ሲሆን እየገቡ ሊጠመቁ /ሰዎች/ ይችላሉ። ይህ የሌሊት ቅዳሴም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የታዘዘ መሆኑ በፍትሐ ነገሥት ተገልጿል። “ወይኩን ገቢረ ቁርባን በልደት ወጥምቀት መንፈቀ ሌሊት”፡-  በልደትና በጥምቀት ቅዳሴው /ቁርባኑ/ በመንፈቀ ሌሊት ይሁን ተብሏል። በግብፆችም ከእስልምና መግባት /ከ6ኛው ክ/ዘመን/ በፊት ዓባይ ወንዝ በመውረድ በድምቀት ይከበር ነበር። ከዐረቦች መግባት በኋላ ግን በከሊፋዎቹ /በሱልጣኖቹ/ ስለ ተከለከሉ በዚያው በቤተ ክርስቲያን ብቻ ለማክበር ተገድደዋል። ይህም ሆኖ በድሮው ዘመን በድምቀት ያከብሩት እንደነበር የእስላም ታሪክ ፀሐፊዎች ሁሉ በሰፊው ዘግበውታል። ለዚህም አልማሱድ(Almas’udi) 94 ዓ.ም የጻፈው ሊጠቀስ ይችላል።

 

ይህ በዓል የሚከበረው ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ነው። ምዕራባውያን ግን ድሮ ከልደት ጋር ደርበው በሚያከብሩበት ዕለት ታህሳስ /ሃያ ስምንተ ወይም ሃያ ዘጠኝ/ ቀን (January 6) ማክበር እንደጀመሩና ትውፊቱንም ከመሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት እንደወሰዱት መዛግብት ያስረዳሉ።

 

በዓሉ የሚውልበት ዕለተ ረቡዕ ወይም አርብ ቢሆን እንኳ አይጾምም። ነገር ግን በዋዜማው ያሉት ዕለታት ረቡዕ ከሆነ ማክሰኞ አርብ ከሆነ ደግሞ ሐሙስ ይጾማሉ። ይህ ጾም የገሀድ ጾም ይባላል። ይህም የበዓሉን ዐቢይነት ወይም ቤተ ክርስቲያን ስለ በዓሉ ያላትን አመለካከትና ቦታ ያሳያል። በዚህ ዕለትም ሥጋዊ ሥራ ፈጽሞ የተከለከለ ነው። እጅግ እንድናከብረው ታዝዟልና። ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት ይህን አስመልክተው

 

ወደእምድኅረ ዝንቱ ግበሩ በዓለ ኤጲፋንያ ዘውእቱ በዓለ ጥምቀት ወይኩን በኃቤክሙ ክቡረ እስመ ቦቱ ወጠነ እግዚአነ ከመያርኢ አመ ተጠምቀ በውስተ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንሰ፡-

ከዚህ በኋላ የጥምቀት በአል የሚባለውን በዓለ ኢጲፊንያን አክብሩ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ የባሕርይ ልጅነቱን ይገልጽ ዘንድ የጀመረበት ቀን ነውና ብለዋል። ሰለዚህም በሀገራችንም በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

 

በአሁኑ ጊዜ እንዲያውም በቱሪስት መስሕብነት ከሚያገለግሉት የሀገሪቱ ሀብቶች መካከልም አንዱ ጥምቀት ነው።ከሀገሪቱ ብሔራዊ በዓላትም አንዱ ነው። ወደ ሀገራችን የሚገባው የጎብኝ ቁጥርም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው በዚህ ወቅት ነው። ስለዚህም ለመንፈሳዊ በረከቱም ሆነ ለብሔራዊ ጥቅሙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱና ባሕላዊ ወጉ አንደተጠበቀ ሊኖር የሚገባው ነው። የጥምቀጸ ባህር ቦታዎችን በግዴለሽነት አሳልፎ ለሌላ ጉዳይ ማዋልም ከሃይማኖታዊ ግዴለሽነቱ ይልቅ ብሔራዊ ቅርስና ታሪክን ማጥፋት መሆኑ ጎልቶ ይታያል። እነዚህን አካላት እንዲያስፈጽሙለት የሾማቸው መንግሥትም ሆነ የሚገለገለው ሕዝብ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ሊያሳስብ ከጥፋታቸው ሊያርማቸውና የሀገር መንፈሳዊ ሀብት መጠበቂያ ሆኑትን ቦታዎች እንዲጠብቁ ሊያሳስባቸው ይገባል።

 

             ከዲያቆን ብርሐኑ አድማስ

             በዓላት ከተሰኘው መጽሀፍ የተወሰደ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15500 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us