የኢትዮጵያን ጨለማ የገፈፈች ብርሃን- ሲልቪያፓንክረስት

Wednesday, 27 January 2016 12:46

 

 

ከጥበቡ በለጠ

ከሰሞኑ ሲስተር ክብረ ተመስገን ወደ ቢሮዬ መጣች። ለብርቱ ጉዳይ እንደምትፈልገኝ ነገረችኝ። ለመስማትም ጓጓሁ። ሲስተር ክብረ የታላቁ ደራሲ እና አርበኛ የተመስገን ገብሬ የመጀመሪያ ልጅ ናት። አባትዋ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የአጭር ልብ-ወለድ መጽሐፍ የሆነውን “የጉለሌው ሰካራም” የተሰኘውን ድርሰት ያሳተመ ነው። 1941 ዓ.ም። መጽሐፉ ታትሞ ሲሰራጭ ግን ተመስገን ገበሬ አላየም። መጽሀፉ ልክ ሲታተም እሱ ከዚህች አለም በሞት ተለየ። የዚያን ግዜ ሲስተር ክብረ የ 5 አመት ህጻን ልጅ ነበረች። የእስዋን ታሪክ ሌላ ጊዜ አጫውታችኋለው። አሁን ግን ቢሮዬ የመጣችው ስለ ሲልቪያ ፓንክረስት ልትጠይቀኝ ነው። የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ለሀገራችን ውለታ በዋሉ ታላላቅ ሰዎች ስምና ምስል ቴምብር ያሳትማል። ከዚህ በፊት ለተመስገን ገብሬ፤ ለዮፍታሄ ንጉሴ፤ ለሀዲስ አለማየሁ እና በሌሎችም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ስም እና ምስል ቴምብር አሳትሟል። ከሰሞኑ ሲስተር ክብረ ወደ ኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ጎራ ብላ ከስራ ኃላፊዎቹ ጋር ተነጋግራ ነበር። የተነጋገረችው ስለ ሲልቪያ ፓንክረስት እና ስለ አልፈሬድ ኤልግ ነበር። ሲልቪያ ፓንክረስት በዜግነት እንግሊዛዊት ናት። ነገር ግን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ ስትወረር ከኢትዮጵያ አርበኞች ጎን ቆማ ሀገራችንን ከባርነት መቀመቅ ውስጥ ካስወጡ የቁርጥ ቀን ወዳጆች መሀል አንድዋ ናት። አልፈሬድ ኤልግ ደግሞ በዜግነት ሲውዘርላንዳዊ ነው። በዘመነ አጤ ምኒልክ ወቅት አማካሪ ሆኖ የመጣ ነው። ለኢትዮጵያ የዘመናዊነት እንቅስቃሴ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው። እነዚህ ሁለት የውጭ ሀገር ተወላጆች ለዚህች ሀገር የዋሉት ውለታ ግዙፍ ነው። እናም የኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት ውለታቸውን ቆጥሮ በቴምብሮቹ እንዲዘክራቸው ሲስተር ክብረ ሀሳብ አቀረበች። ፖስታ ደርጅቱም ውለታ ላበረከቱ ሰዎች ውለታ መላሽ መሆኑን በመንገር የእነዚህ ባለውለተኞች ታሪክ ተጽፎ እንዲቀርብለት ለሲስተር ክብረ ነገራት። እስዋም ወደ እኔ ዘንድ መጣች። ሁኔታውን ከአስረዳችኝ በኋላ እባክህ የሲልቪያ ፓንክረስት እና የአልፍሬድ ኤልግ የተጻፈ ታሪክ ይኖርህ ይሆን አለችኝ። እኔም በ1999 ዓ.ም ስለ ሁለቱም ሰዎች ታሪክ መጻፌን ነግሬያት ታሪኮቻቸውን ሰጠሁዋት። በጣም ተደሰተች። ከሰጠዋሁት ታሪኮች ውስጥ ለሰንደቅ አንባቢዎች ለዛሬ የማካፍላችሁ በ1875 ዓ.ም በማንቸስተር ከተማ እንግሊዝ ውስጥ ስለተወለደችው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ስለ ሲልቪያ ፓንክረስት የጻፍኩትን እነሆ እላችኋለው።

አንዳንድ ጊዜ ዘመን ራሱ ይጨልማል። ብሩህ ዘመን እንዳለ ሁሉ ጨለማ ዘመን አለ። የስቃይ የመከራ። ኢትዮጵያ ሀገራችንም ከፍተኛ ሰቆቃ የደረሰባት በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ነበር። ወረራው ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖር ከመገርሰሱም በላይ በሀገሪቱ ውሰጥ ሠላምና መረጋጋት ጠፋ። ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ በዱር በገደሉ ፋሽስቶችን ለመፋለም ገቡ። አብዛኛዎቹም ምርጥ ኢትዮጵያዊያን በትጥቅ ትግሉ ትንቅንቅ ወቅት ሕይወታቸው አለፈች። ምድር በየቦታው በደም ራሰች። ሴቶች ተደፈሩ። ቤቶች ተቃጠሉ። ሕፃናት የማንነት እጦት ገጠማቸው። ጐምቱ ኢትዮጵያዊያን ተሰደዳ። ሱዳን/ገደሪፍ/ ውስጥ ተከማቹ። ግማሹ ተማርከው ወደ ጣሊያን ሀገር በመጋዝ ወህኒ ወረዱ። ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ደግሞ በየሀገሩ እየዞሩ ሀገሬን አድኑልኝ ይላሉ። ትልቁ ዓሣ ትንሹን ይዋጠው የምትሉ ከሆነ መዘዙ ብዙ ነው፤ ነግ በእናንተ ይደርሳል እያሉ የዓለም መንግሥታትን ድረሱልን ይላሉ።

በወቅቱ ጆሮ ሰጥቶ ያዳመጣቸው የለም። በአሁኑ አጠራሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚባለውና በወቅቱ ደግሞ ሊግ ኦፍ ኔሽን በመባል ይታወቅ በነበረው የስብሰባ ማዕከል ውስጥ ከአንዲት የአፍሪካ ጥንታዊት ሀገር አንድ ንጉሥ መጥቷል። ንጉሡ 3000 ዓመታት በራሷ የመንግሥት ሥርዓት ከምትተዳደር ሀገር የመጣ ነው። አዳራሹ ውስጥ ደግሞ ጥቁር ያን ያህል ቦታ ተሰጥቶት መድረክ ላይ ወጥቶ የሚናገርበት ዘመን አይደለም። ግን ይህ ከምድረ ጥቁር የመጣው ንጉሥ ንግግር እንዲያደርግ ፈቃድ ተሰጠው። ወደ መድረኩ የመጡት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ነበሩ። ሀገራቸው በጣሊያኖች ተወራ ሀገር አልባ ሆነው በስደት ላይ ነበሩ። በዚያ በሊግ ኦፍ ኔሽን ስብሰባ ላይ የድረሱልኝ ጥሪ ለማሰማት ወደ መድረኩ ብቅ ሲሉ የኢጣሊያ ዜግነት ያላቸው የስብሰባው ተሳታፊዎች አዳራሹን መረበሽ ጀመሩ። ጃንሆይን ይሰድቧቸው ጀመር። አብዛኞዎቹ ፀያፍ ስድቦች ነበሩ። ጃንሆይ ደግሞ ከማዳመጥ ሌላ የሚያደርጉት ነገር አልነበረም። መድረኩ ላይ ቆመው ተሳዳቢዎቹን በግርምት ያዩዋቸዋል። አዳራሹ ሥርዓት አጣ ። ቀጥሎ ምን ሊመጣ እንደሚችል ማወቅ አልተቻለም። እጅግ ከሚያስቀይም ድባብ ካለው አዳራሽ ውስጥ የፀጥታ አስከባሪዎች ገቡ። እናም ጃንሆይን በስድብ አላናግር ያሏቸውን ስርዓት ቢሶች የፀጥታ ሰዎች ይዘዋቸው ወጡ። እየተወራጩ ጃንሆይን በፀያፍ ስድብ እየዘለፏቸው አዳራሹን ለቀቁ። አሁን ሠላም ሆነ። ጃንሆይ ለተሰበሰበው ሕዝብ እጅ ነሱ። አዳራሹ በጭብጨባ በደስታ ተሞላ። ሕዝቡን ያስደተሰው የጃንሆይ ፍፁም ትዕግስተኛነትና ስርዓተኝነት እንዲሁም እርጋታና ድባባቸው ነበር። ጃንሆይ ወረቀታቸውን ዘረጉ። ሕዝቡን ቀና ብለው አዩ። ቀጥለው ጐንበስ አሉ። ታሪካዊውን ንግግራቸውን ማሰማት ጀመሩ። የሐገራቸው በእብሪተኞች መወረር ሥርዓተ-መንግሥቱ ተንዶ በባዕዳን ቁጥጥር ስር መግባቱ ሕዝቡ ከፍተኛ እልቂትና መከራ ውስጥ መግባቱን እና ሌሎችንም ፍዳዎች ተናገሩ። ጃንሆይ አንድ ነገር አከሉ። ትልቁ ዓሣ ትንሹን ይዋጠው የምትሉ ከሆነ ነግ በናንተ ሲደርስ ታዩት የለምን አሏቸው። በመጨረሻም ይህን ተናገሩ፡- እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ አሏቸው። God and History Will Remember your Jujment ተብሎም ወዲያውኑ ተተርጉሞ በዓለም ላይ ተሰራጨ። ምርጥ ንግግር ነበር። ይሁንና በወቅቱ አቅሙ እና ብቃቱ የነበራቸው ኃያላን መንግሥታት ለጃንሆይ ንግግር ምላሽ ደፋ ቀና አላሉም። ኢትዮጵያውያን አርበኞች ግን የመርዝ ጋዝ ከሰማይ እየወረደባቸው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እያለቁ ናቸው። ግማሹ እቤት ለቤት እየታደነ በመጨፍጨፍ ላይ ነው።

ከወደ እንግሊዝ ሀገር ግን አንዲት ፀሐይ ወጣች። የኢትዮጵያን የጨለማ ዘመን በአንድነት ሆነን እናብራው የምትል። ጨለማው ይገፈፍ፤ ስቃይ ሰቆቃ ቶርቸር እንግልት ይቁም ብላ ግንባሯን ለጥይት፣ እጇን ለካቴና እየሰጠች ኢትዮጵያን እናድን የምትል ሴት የተጋረደውን አድማስ ሰንጥቃ ወጣች። ይህች ታሪካዊት ሴት ሲልቪያ ፓንክረስት ትባላለች። ሲልቪያ ፓንክረስት ወደዚች ምድር ስትመጣ የነፃነት ታጋይና ተሟጋች ሆና ነው። ገና በጨቅላዎቹ ዕድሜዎቿ በምድረ እንግሊዝ የምታያቸውን ኢፍትሀዊ የሆኑ አሰራሮችና ደንቦችን በተለይም ደግሞ ችላ የተባለውን የሴቶችን መብት ለማስከበር ከዕድሜዋ በላይ ድምጿ የሚሰማ አርበኛ ነበረች። ሲልቪያ የሙያ ጥሪዋ ኪነ-ጥበብ (Art) ነው። የተማረችው የስዕል ጥበብን ቢሆን ምርጥ ጋዜጠኛ፤ ምርጥ ፀሐፊ ነበረች። የሲልሺያ ብዕር የአንባቢን ቀልብና

መንፈስ ገዝቶ ከመጓዙም በላይ የእርሷም ሰብዕና ደግሞ ይበለጥ እኛነታችንን ወደርሷ የሚያቀርብ አንዳች ኃይል አለው። ለነፃነት ለፍትህ ለዲሞክራሲ ለሰብአዊ መብት እራሷን አሳልፋ የሰጠች.. እንደገና ደግሞ የኢትዮጵያን የጨለማ ዘመን ለመታደግ ማንነቷን ለኢትዮጵያ የሰጠች የቁርጥ ቀን ልጅ ዛሬ ልናነሳሳት ነው።

ሲልቪያና ኢትዮጵያ በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ፍፁም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያን ወረረች። ሞሶሎኒ ሮም ላይ በሚሊየን ለሚቆጠረው ሕዝቡ ኢትዮጵያን መውረሩን አበሰረ። አድዋ ላይ ድባቅ የተመታው የኢጣሊያ ጦር አርባ ዓመት አገግሞ ተጠናክሮ ቂም በቀሉን ቋጥሮ ኢትዮጵያን በመዳፉ ስር ሊከት ታላቁን ደረጃ ያዘ። ኢትዮጵያ ላይ ቁንጮ ሊሆን በቁጥጥሬ ስር ነች አለ። ኢትዮጵያ እንደ መንግሥት የመቀጠሏ ሁኔታ ጠፋ። መንበረ ሙሴው ከሥልጣን ተወግዶ ባዕዳን ኢጣሊያዊያን በግራዝያኒ ፊት-አውራሪነት ወንበሩ ለኛ ይገባል አሉ። የኢትዮጵያ ሥርዓተ-መንግሥት ፈረሰ። ንጉሡም ተሰደዱ። ሀገር አልባ ሆኑ፤ ተነስተው እንደተራ ሰው ስደተኛው ባይተዋር ሆኑ። በምድረ እንግሊዝ ስደታቸው ስለ ሀገራቸው ኢትዮጵያ መወረር አዕምሮዋ የቆሰለው ሲልቪያ

ፓንክረስት እና ሌሎች 32 የኢትዮጵያን ወዳጆች ጃንሆይ ከባቡር ሲወርዱ ንግግር አደረጉላቸው። በተለይም የኢትዮጵያ መወረር በጣም እንዳሳዘናቸው እና ወረራውንም ለመቀልበስ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ እነ ሲልቪያ ለጃንሆይ ተናገሩ። የጀመሩት የሠላም መንገድ ጥሩ ነው አሏቸው ። በተለይም ሲልቪያ ፀረ- ፋሽስት ትግሉ ወደፊትም ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ድምጿን ስታሰማ ቆይታለች። እናም በስደት አንገታቸውን የደፉትን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ባለሟሎቻቸውን አይዟችሁ ከጐናችሁ ነን። ባይተዋርነት አይሰማችሁ። ትግሉ የሁላችንም ነው ብላቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ወደፊት እንዲቀጥል ትልቅ ደጀን የሆነችው ሲልቪያ ፓንክረስት ከወደ እንግሊዝ ትጠቀሳለች።

ሲልቪያ ፓንክረስት ምርጥ የሰብአዊ መብት ታጋይ ናት። የተፈጠረችበት ስራ ደግሞ ስዕል ነው፤ ግጥም ነው፤ ጽሕፈት ነው፤ ብቻ የኪነ-ጥበብ ሰው ነች። ፅሁፎቿ ዛሬም ነገም ልብ እንዳማለሉ የሚነበቡ ናቸው። ይሄ ስብዕናዋም ነው በዚህ እንዳነሳሳት ግድ የሚለኝ። በአፃጻፍ ቴክኒኳ ውብ የሆነ የገለፃ ጥበብ ያላት ፀሀፊዋ ሲልቪያ በምድረ እንግሊዝ እና በሌላውም ዓለም ብዕሯ ፀረ-ፋሽስታዊ ተጋድሎውን አጠንከሮ ቀጠለ። New Times እና Ethiopia News በተሰኘው የወቅቱ ጋዜጣ ስለ ወራሪዋ ኢጣሊያ የተለያዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መጣጥፍ አቅርባለች። ሲልቪያ የምትፅፋቸውን ፀረ-ፋሽስታዊ መጣጥፎቸ በሙሉ ለእንግሊዝ መንግሥት የፓርላማ አባላት ታከፋፍል ነበር። ሁሉም በየዕለቱ ጉዳያቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሆን ለማድረግ ያልማሰነችው ሙከራ የለም። ከዚህ ሌላም በሞሶሎኒ የግፍ አገዛዝ ለሚሰቃዩ ኢጣሊያዊያንም ሌላኛዋ ተቆርቋሪ ነበረች። በስደት ወደ እንግሊዝ የገቡትን የኢጣሊያ ዜጐች ከመከራው አገዛዝ እንዲላቀቁ የማታንኳኳው በር የለም። የሲልቪያ ሰብዕና ለታረዙ ለተገፉ ለተጨቆኑ ሁሉ እኩል መቆም ነው። ብቻ ፋሽዝምን የመታገል ኃይሏ አይሎ የወጣ የክፍለ ዘመኑ ጀግና ብዕረኛ ነበረች። በምትፅፍበት New Times እና Ethiopia News ጋዜጣ ላይ ስታስተጋባ የነበረው ፋሽዝም ከምድረ ኢትዮጵያ እንዲጠፋ እና ኢትዮጵያዊያንም ነፃ እንዲወጡ የነፃነት አቀንቃኝ ሆና ነው ሲልቪያ የምትታየው። ከዚህም በመቀጠል የዓለም ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ የነፃነት እጦት እነዲገነዘብና ፀረ- ፋሽስታዊ ትግሉ እንዲፋፋም እንግሊዝ ውስጥ ሰልፍ ጠራች። በተለይም የሴቶቹ እንቅስቃሴ የእንግሊዝን መንግሥት በወቅቱ ይነቀንቀው ስለነበር የሲልቪያም የሰልፍ ጠሪ በነዚሁ ሴቶች በኩል የሚደረግ ነበር። እናም እንግሊዛዊያት ፀረ-ፋሽዝም የተፃፈባቸውን መፈክሮች በማንገብ ዓለም ኢትዮጵያን እንዲታደግ ሰለፍ ወጡ። ሀገሪቷ ከዳር እስከ ዳር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውይይት ገባች።

የሲልቪያ ትግል እንዲህ በመላው ሴቶች ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከመላው እንግሊዛዊ ጋር የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲያደርግ ከጫፍ እስከ ጫፍ የትግል መረቧን እየዘረጋች ነበር። ከቤተሰቧ ጀምሮ በወቅቱ ገና ጨቅላ የነበረው ልጅ ሪቻርጅ ፓንክረስት /የዛሬው ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት/ ጭምር ፀረ-ፋሽስታዊ ተጋድሎ ውስጥ እንዲገቡ አድርጋለች። የኢትዮጵያ አርበኞች ከጃንሆይ ጋር በደብዳቤም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሲገናኙ ከሲልቪያ የተደበቀ ነገር የለም። የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ የራሷ የሙሉ ጊዜዋ ጉዳይ ሆኖ አረፈው። ሲልቪያ በመንፈስ ፍፁም ኢትዮጵያዊት ሆነች። ከዳር እስከ ዳር የምታደርገው ቅስቀሳ (LobbY) ኢትዮጵያ በተለይም በእንግሊዝ መንግሥት ዘንድ ትኩረት እንዲሰጣት ማድረግ ቻለች። እንግሊዝ ኢትዮጵያን እንድትረዳ እና ለነፃነትና ለፍትህ የሚደረገውን የኢትዮጵያዊያኖችን ትግል እንድትደግፍ መስመር ውስጥ ያስገባች ብርቱ ሰው ነበረች ሲልቪያ ።

የአርበኞቹም ትግል እየገፋ መጣ። በየቦታው ፋሽስቶች ድል እየተመቱ መጡ። በእንግሊዝ የሚደደገፈውም ጃንሆይን የያዘው ሌላው የጦር ምድብ ከሰሜን በኩል እየተጓዘ መጣ። ጣሊያን የአምስት ዓመቱን የወረራ ዘመን በአሳፋሪ ሽንፈት ተከናንባ ወደቀች። መላው ጣሊያን አዘነ። እንግሊዝ ውሰጥ ደግሞ ሲልቪያና ደጋፊዎቿ የደስታ ዓለም ውስጥ ገቡ። ትግላቸው ፍሬ አፈራ። ኢትዮጵያ በብዙ መስወእትነት ነጻ ወጣች። ሲልቪያ ፓንክረስት ያቺን ለነፃነቷ የታገለችላትንና እንደ አይኗ ብሌን ስትጠብቃት የኖረችውን ኢትዮጵያን ለማየት ተነሳች። ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ልትጓዝ ነው። ጊዜው እ.ኤ.አ 1943 ዓ.ም ሲልቪያ ከለንደን ተነስታ ወደ ኢትዮጵያ በረረች። ያቺ የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጅ ሲልቪያ

ኢትዮጵያ ገባች። ምድረ ሀበሻ ወጥቶ በእልልታ እና በሆታ ተቀበላት፤ ተዜመላት። ባለቅኔዎች ቅኔ ተቀኙላት፤ አዝማሪዎች አሞገሷት። የክፉ ቀን ደራሿ ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ስታያት ፍፁም ፍቅር ያዛት። በቀረበቻት ቁጥር ከመንፈሷ ጋር ወግ ጀመረች። ሁለት ጊዜ ለንደን ደርሳ መጣች። በመጨረሻም በኢትዮጵያ ፍቅር ወድቃ ጓዟን ጠቅልላ መጣች። ከዚህ በኋላ ነው ሌላኛው የሲልቪያ ፓንክረስትና የኢትዮጵያ ቁርኝት እያየለ የሚመጣው። ከነፃነት በኋላ ኢትዮጵያ እንደደረሰች የሀገሪቱን ሁለመና ማወቅ ጀመረች። የማታየው የማትጐበኘው የማትጠይቀው ነገር የለም። ኢትዮጵያን ባወቀቻት ቁጥር አፈሯን ምድሯን ወደደቻት። የሚያስገርም የታሪክ ደሴት መሆኗን በልዩ ልዩ መጣጥፎቿ መግለፅ ጀመረች። የብሔረሰቦቿን ብዛትና በአንድነት የመኖር ምስጢር፤ የመዓት ባህሎች ስብስብ መሆኗ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቀደምት ስልጣኔዋ ሲልቪያን ኢትዮጵያ ምርኰ ካደረገችባቸው ነጥቦች ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ሲልቪያ የጥበብ ሰው ናት። እናም ይሄ ጥበበኝነቷ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ወዳሉት ኪነ-ሕንፃዎች ቀልቧ ተሳበ።  የአክሱማውያን የስልጣኔ ደረጃ አለም አስከንድቶ ትልቅ እርከን ላይ ደርሶ የነበረበትን ዘመነና የሕውልቶቹን ፋይዳ ይበልጥ ለዓለም ማስተዋወቅ ጀመረች። ከዚህም ሌላ ረጅም ጊዜ ስትደመምባቸው የቆየችበት ኪነ-ሕንፃዎች በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተሰሩት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ናቸው። የነዚህ አበያተ- ክርስትያናት የኪነ-ሕነፃ አሰራር በየትኛውም ዓለም እንደማይገኝ እና ኢትዮጵያም በዓለም ላይ በነዚህ ቅርሶቿ አስደናቂ ምድር እንደሆነች ፃፈች። ሲልቪያን ልዩ የሚያደርጋት ነገር ቢኖር በተለይም በነዚህ በላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ላይ ያደረገችው አስገራሚ ጥናት ነው። ይህም ኢትዮጵያን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጐብኝቶ የሔደው ፖርቹጋላዊው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ የላሊበላን አብያተ-ክርስትያናት ፈረንጆች እንደሰሩት እዚያ ያሉት ቄሶች ነገሩኝ ብሎ ፅፎ ነበር። ከዚያም በኋላ የመጡት ታሪክ ፀሐፊዎች አብያተ-ክርስትያናቱ በውጭ ሀገር ሰዎች እንደተሰሩ ገልፀዋል። በዚህኛውም ዘመን አሁን በሕይወት የሌሉት ታላላቅ ታሪክ ፀሐፊዎች፡- ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ፤ ተክለፃዲቅ መኩሪያ፤ ብርሃኑ ድንቄ፤ ስርግው ሀብተስላሴ፤ አፅንኦት ሰጥተው ያመለከቱት ነገር ቢኖር የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ከግብፅ ሀገር ተሰደው በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመጡ ሰዎች መሰራታቸውን ነበር። ሲልቪያ ደግሞ ፍፁም የተለየ ነገር ይዛ ቀረበች። እንደ እርሷ አባባል ከአለት ላይ ፈልፍሎ ቤት የመስራት ጥበብ የኢትዮጵያ ብቻ ነው። ይህ ጥበብ ከአክሱም ጀምሮ እያደገ እያጐለበተ የመጣ ነው። ከመቶ በላይ አብያተ- ክርስትያናት ከድንጋይ ተፈልፍለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰርተዋል። ነገር ግን በላሊበላ ዘመን የጥበቡ መራቀቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ፍፁም (Prefect) ሆነው ተሰሩ ትላለች። ስታክልበትም እንደነዚህ አይነት አብያተ-ክርስትያናት በየትኛውም ዓለም አልተሰሩም። የየትኛውም ሀገር ባህል አይደሉም። ይህ የኢትዮጵያዊያኖች ብቻ የሆነ የግላቸው ጥበብ ነው በማለት ለመጀመርያ ጊዜ የተለየ ጥናት የፃፈች የታሪክ ፀሐፊ ነች።

ሲልቪያ እነዚህ አበያተ-ክርስትያናት የዓለም ልዩ ቅርሶች በመሆናቸው ስማቸው ታውቆ በዓለም ሕዝብ ዘንድ እንዲጐበኙ Monolithic Churches of Lalibela- Great Wonders of the World ብላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፈች ሰው ናት። ፅሁፉን ከፍተኛ ምርምርና ጥናት አድርጋበት የፃፈችው በመሆኑ ተቀባይነቱ ወደር የለውም። ዛሬ ሲልቪያ በሕይወት የለችም። የዛሬ 57 ዓመት ሕይወቷ አልፏል፡ በእርሷ ዕድሜ እኔ ባለመኖሬ በአካል አላውቃትም። ግን ስራዎቿ ዛሬም ከጐኔ ቁጭ ብላ እንደምታወጋኝ ያህል ያናግሩኛል። ፍፁም ኢትዮጵያዊ ለዛና ፍቅር ያለው ብዕሯ የዘመን ኬላን ገና ተሻግር ይጓዛል። የሲልቪያ ቤተሰብ በኢትዮጵያ የሲልቪያ ዘር ከኢትዮጵያ ጋር ተዋህዶ ዛሬ የኢትዮጵያን ደምና ስጋ ተላብሷል፡ ሲልቪያ ከወደ እንግሊዝ ነቅላ ስትመጣ በጣም የምትወደው ልጇ ሪቻርድ ፓንክረስትም አብሯት መጥቷል። ከባለቤቱ ሪታ ፓንክረስትም ጋር ሆነው እዚህ ኢትዮጵያ የገቡት የዛሬ 50 ዓመት ነው። ሪቻርድ እና ሪታ የታሪክ ሰው ናቸው። በተለይ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላጠኑት ያልፃፉት ጉዳይ የለም። ሁለት ያብራካቸውን ክፋይም ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። አንድ ወንድ ልጅና አንድ ሴት ልጅ። ወንዱ ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ይባላል። እሱም ሶሻል አንትሮፖለጂስት ነው ። እህቱም ሆነች እርሱ አማርኛ ቋንቋን ሲናገሩ ስርዓቱንና ደንቡን ጠብቀው ከማንም በተሻለ ሁኔታ ነው። ጥንታዊውን የግእዝ ቋንቋን በሚገባ የሚያውቁም ናቸው። የአሉላ ባለቤት ኢትዮጵያዊቷ ቆንጅት ናት። ልጅም ወልደዋል። ስለዚህ ሲልቪያ ሪቻርድን ወለደች። ሪቻርድና ሪታ አሉላን ወለዱ። አሉላ ደግሞ ከኢትዮጵያዊት ጋር ተጋብቶ ኢትዮጵያዊያን ልጆች አገኘ። እና ሲልቪያ በልጅ ልጇ ተዋልዳ ኢትዮጵያዊ ሆነች። ኢትዮጵያ ውስጥ የሲልቪያ የክርስትና ስም ወለተ-ክርስቶስ ተብሎ በቀሳውስት ይጠራም ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሲልቪያ እና ቤተሰቦቿ እጅግ ትልቅ ክብርና ማዕረግ ሊሰጣቸው የሚገባ እንደሆኑ ተዘርዝሮ የማያልቀው ውለታቸው ቋሚ ምስክር ነው። የሲልቪያ ብዕር ስለኢትዮጵያ ሲልቪያ ፓንክረስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን እና ታሪኳን ባህሏን ሕዝቦቿን ለማስተዋወቅ ያደረገችው ብርቱ እንቅስቃሴ ሀገሪቷ በሌላው ዓለም ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት እንድታገኝ አድርጋለች።

ጊቦን የተባለ ፀሐፊ ኢትዮጵያዊኖች አንድ ሺህ ዓመት በራቸውን ዘግተው ከዓለም ተገልለው አንቀላፍተዋል ብሎ የፃፈውን ታሪክ ሲልቪያ ቀይራዋለች። የእንቀልፍ ዘመን የተባሉትንና ከዚያም በፊት የተሰሩትን የኢትዮጵያዊያንን አስደናቂ ተግባሮች ለዓለም አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን አላንቀላፉም፤ ያንቀላፋው የኢትዮጵያውያዊያንን ስራ ማየት ያልቻለው ነው በሚል ስሜት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሉትን ድንቅ የኢትዮጵያ ቅርሶች ባህሎች ታሪኮች እምነቶች… እነሆ እያለች በገላጭ ብዕሯ ስታሳይ ቆይታለች። አንተ ጊቦን፤ ለመሆኑ አይንህ ይህን ሁሉ ሥልጣኔ አይቷል ወይ በሚያሰኝ የብዕር ለዛ ብዙ ፅፋለች። ከሲልቪያ ፅሁፎች ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ 735 ገጾችን የያዘው መፅሐፏ ነው። ርዕሱ Ethiopia a Cultural History ይሰኛል። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ሲልቪያ ያልዳሰሰችው ማነነታችን የለም። እኛ ኢትዮጵያዊያን እስከ ዘመነ ሲለቪያ ድረስ ምን እንደምንመስል ቁልጭ ብሎ ይታያል። መፅሐፉ የሀገሪቱን ታሪክ፤ ሥነ-ፅሁፍ፤ ሥነ-ጥበብ /አርት/፤ ሥነ-ሕንፃ (Architecture)፤ ሥነ- ግጥም (Poetry)፤ ሙዚቃ እና ትምህርትንም በተመለከተ በርብሮ ይገልጽልናል።

የሲልቪያ አፃፃፍ ተደጋግሞ የሚታየውን የሀገራችንን የታሪክ አፃፃፍ በተለየ መልኩ ያሳደገ ነው። ይህም ብዙውን ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲባል ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የነበሩትን መሪዎች በመደርደር ማን እንዴት እንደገዛ እንዴት እንደተዋጋ እንዴት እንደወደቀ እና ቀጣዩም እንዴት በትረ ሙሴውን እንደጨበጠ በመዘርዘር የሚተነትን ነበር። ሲልቪያ ግን ሥነ-ፅሑፋችንን፤ ኪነ-ጥበባችንን በአጠቃላይ በመዳሰስ ከመሪዎች ታሪክ ባለፈ የሕዝቦችንም ማንነት በመፅሐፏ ውስጥ ለማሳየት ብርቱ ሙከራ አድርጋለች። በጠቅላላው የማህበረሰብ ታሪክ (Social History) ላይ ትኩረት ያደረገች ዘመናዊት ፀሐፊ ነበረች።

ሌላው ከኢትዮጵያ ጋር እጅጉን አቆራኝቶ ሲልቪያን እና ኢትዮጵያን በጣም የሚገልፀው

Ethiopia Observer የተሰኘው የእንግሊዝኛ መፅሔት ነው። በዚህ መፅሔት ላይ ሲልቪያ የልማት ሚኒስቴር ትመስላለች። ከዘመነ ፋሽስት ወረራ በኋላ የሚሰሩትን ሆስፒታሎች፤ ት/ቤቶች፤ መንገዶች፤ ፋብሪካዎች ወዘተ እየተዘዋወረች ያላቸውን ፋይዳ ትፅፋለች። ሌሎች

መሰራት የሚገባቸውን ነገሮች ደግሞ ትጠቁማለች። ከዚህ ባሻገር ደግሞ የሀገሪቱን ታሪክ በበሰለ እና በተጠና ሁኔታ አያሌ የታሪክ መዛግብትን በማገላበጥ ጥልቅ ትንታኔ ታደርጋለች። ሲልቪያ ስትፅፍ የተጠቀመችባቸውን የፅሁፍ መረጃዎች ማለትም መፃህፍትን፤ ርዕሶቻቸውንም ሆነ ስሞቻቸውን ስለምታሰፍር በእያንዳንዱ ፅሁፏ ውስጥ ብዙ ባለታሪኮችን እንተዋወቃለን። ከዚህኛው ባሻገር ደግሞ ራሷ ሲልቪያ ሰዓሊ ነች። ከዚህም አልፎ የስዕል ሀያሲት ነች። እና በርሷ ብዕር ያልተበረበረ ስዕልና ሰዐሊ የለም። የኢትዮጵያን ባሕላዊ ስዕሎች ከየአብያተ-ክርስቲያናቱ እና ገዳማቱ ፎቶ ግራፍ እያነሳች በመፅሔቱ ላይ ታሳያለች። ከዚያም በውስጣቸው የያዙትን ሃይማኖታዊ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ጉዳዮች ትተነትናለች። ከሌሎቸ የአሳሳል ጥበቦች ጋር እንዴት እንደሚገናኙ እና እንደሚለያዩ ታብራራለች።

የሲልቪያ የስዕል ሃያሲነት ዛሬ በሕይወት የሌለውን ሃያሲ ስዩም ወልዴን፤ ዛሬ በምድረ አሜሪካ የሚገኘውን ባለቅኔ ሰለሞን ደሬሳን ሳይፈጥር አልቀረም። በ1950ዎቹ መባቻ ገና ለጋ ወጣት የነበሩትን አንጋፋውን ባለቅኔ መንግሥቱ ለማን ምን ያህል የስዕል ችሎታ እንደነበራቸው ያስተዋወቀች ሲልቪያ ፓንክረስት ነበረች። ዛሬ መላው ዓለም በስዕል ችሎታቸው አንቱታን ደራርቦ የሰጣቸው አፈወርቅ ተክሌ በወጣትነት ዘመናቸው ላይ ሲልቪያ ታላቅ ሰው እንደሚሆኑ አብራርታለች። ከወጣቶቹም ከአንጋፋዎቹም እየጠቃቀሰች የኢትዮጵያን የስዕል ጥበበኝነት ያብራራች ድንቅ ፀሐፊ ሲልቪያ ፓንክረስት ከ50 ዓመት በፊት ብዙ ገልፃለች። ሲልቪያ ገጣሚ ነበረች። አያሌ ግጥሞችን ፅፋለች። በተለይም ስለ ነፃነት ፍትህ ርዕትዕ… ተቀኝታለች። ሌላው የሕይወት ገጠመኟ ሌላ ምዕራፍ የያዘበት አጋጣሚ፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ ነው። ሁሉም ነገር ይገርማታል። በአያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግጥም ስትፅፍ ኖራለች።  Addis Ababa ብላ ተቀኝታለች። በሐረር ላይ ፅፋለች። ምኒልክ ከአውስትራሊያ ባስመጡት ባህር ዛፍ ተደንቃ ብዙ ስንኞች ደርድራለች። እናም የነፍሷ ጥሪ ወደ ሆነው ሥነ-ግጥም ውስጥ የሚዋኙትን ዋናተኞች ጓደኞቿ አደረገች። መንግሥቱ ለማ ግንባር ቀደሙ ናቸው። ከቤተሰቧም ጋር ቤተኛ ነበሩ። አፍላ የግጥም ነበልባል በውስጣቸው ሲንበለበል የነበሩትን የዚያን ጊዜዎቹን ወጣቶች በቅኔ ዓለም እንዲምነሸነሹ የጥበብ ማዕድ የዘረጋች ፀሐፊ ነበረች ሲልቪያ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
10924 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us