ማርያም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

Wednesday, 03 February 2016 15:04

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

የዛሬ ጽሁፌን እንዳዘጋጅ የገፋፋኝ ባሳለፍነው ቅዳሜ የተከበረው የአስተርዮ ማርያም አመታዊ ክብረ-በአል ነው። በአሉ በመላው ኢትዮጵያ እጅግ ደማቅ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ማርያም ናት፤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዋነኛዋ መገለጫ በመሆንዋ ነው። የማርያም ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ነው። ለምሳሌ ገና በልጅነታችን ሰውነታችን ላይ አንድ ጠቆር ያለ ነገር ካለብን ማርያም የሳመችው እየተባልን አድገናል። በልጅነታችን ጨዋታ ወቅት የማርያም መንገድ ስጠኝ እየተባባልን አድገናል። ትንሽዋን የእጃችንን ጣት የማርያም ጣት እንላለን። እናታችን ሆድ ውስጥ እያለን እናታችን በማርያም እጅ ተይዛለች ትባላለች። እናታችን ስትወልደን ደግሞ የማርያም አራስ ትባላለች። ተወልደን ሊጠይቁ የሚመጡ ሰዎች እናታችንን እንኳን ማርያም ማረችሽ ይሏታል። ጠይቀዋት ሲወጡ ማርያም በሽልም ታውጣሽ ይሏታል። ገና እናታችን ምጥ ሲመጣባት ሁሉ ማርያም ማርያም ነው የሚባለው። አራስ ቤት ውስጥ ገና በጨቅላ ወራቶቻችን ወቅት ፈገግ ስንል እናቶች እንዲህ ይላሉ፡- ማርያም ስታጫውተው ይሉናል። እናታችን አራስ ቤት እያለች መጀመሪያ የምትመገበው ገንፎ ነው። ግን በባህሉና በእምነቱ አጠራር የማርያም ምሳ ተብሎ ነው የሚጠራው። ማርያምን ገና ሳንወለድ እና ተወልደንም ስምዋን እየሰማን በማደጋችንም ጭምር ይመስለኛል፤ በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ግዙፉን ቦታ የያዘችው።

በማርያም ስም የሚጠሩ ኢትዮጵያዊያንም የትየለሌ ናቸው። ኃይለማርያም፤ ቤተ ማርያም፤ ኪዳነ ማርያም፤ መንበረ ማርያም፤ አስካለ ማርያም… እየተባለ አያሌ አትዮጵያዊያን በማርያም ስም ይጠራሉ። ማርያም ከሀበሾች ጋር ከእምነቱ ባለፈ ተወዳጅና የቅርብ እናት ካደረግዋት ነገሮች መካከል እነዚህ ሰዋዊ እና መንፈሳዊ ትስስሮች ይመስሉኛል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ሀይማኖት ውስጥ በእጅጉ ተወዳጅ ስለሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም አንዳንድ ጉዳዮችን እንድናወጋ ፈለኩኝ።

በኢትዮጵያ ውስጥ የኦርቶዶክስ ሐይማኖት የመንግሥት ሐይማኖት ሆና ለሺ አመታት ከቆየች በኋላ ከ40 አመታት በፊት ስልጣኗን አጥታለች። መንግሥትና ሐይማኖት ለየብቻ ናቸው የሚል ኮምኒስታዊ መርህ በመቀንቀኑ በመንግስት እና በሐይማኖት መካከል ልዩነት ተፈጠረ። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሐይማኖት የለውም ተባለ። ጉዳዩ ብዙ ነገር ያዋራል። ግን ወደ ዋናው ርዕሠ ጉዳያችን እንድንደረደር ስለዚህችው ኦርቶዶክስ ሐይማኖት እንጨዋወት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐይማኖት ከሌሎቹ የክርስትያን ሐይማኖቶች በፅኑ ተለይቶ የሚቆምበት መገለጫው በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ያለው ከፍተኛ ፍቅር እና ስርዓት ነው ማርያም በሐይማኖቱ ስርዓት ውስጥ ዋነኛዋ ማጠንጠኛ ናት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የበአላት አከባበር ውስጥ ማርያምን በተመለከተ የሚደረጉ ስርዓቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ለምሣሌ ሕዳር 21 ቀን አክሡም ጽዮን' መስከረም 21 ቀን ግሸን ማርያም' ጥር 21 አስትርዮ ማርያም' የካቲት 16 ኪዳነ ምሕረት፤ እነዚህ ግዙፍ የሆኑ የቅድስት ድንግል ማርያም አመታዊ ክብረ በአሎች ናቸው። በእነዚህ በአላት ወቅት ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ መስሪያ ቤቶች አይዘጉም እንጂ በሐይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ግን ትልልቅ ክብረ-በአሎች ናቸው። ባለፈው ጥር 21 ቀን የተከበረውም የአስትርዮ ማርያም ክብረ-በዓል ከግዙፎቹ መካከል ዋነኛው ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በማርያም የአማላጅነት እና የተራዳይነት ሚና እንዳላት በጥልቀት ይታመናል። በመሆኑም በሐገሪቱ ውስጥ ከታነፁ አብያተ-ክርስትያናት ውስጥ ቅድስት ድንግል ማርያም ዋነኛውን ቁጥር ትይዛለች። ገና ክርስትና በሐገሪቱ ውስጥ ሲሠበክ የጽዮን ማርያም ቤተ-ክርስትያን አክሱም ውስጥ ታነፀች። የጽላተ ሙሴውም መኖርያ በዚህች በጽዮን ውስጥ ከሆነ ከ1600 አመታት በላይ ሆኖታል።

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ካደረጓት ነገሮች መካከል የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ስርዓት እና ቅርሶች ዋነኞቹ ናቸው። ወደ ሐገሪቱ የሚመጡ ቱሪስቶች አብላጫዎቹ የሚጐበኙት ታሪክ ባሕል ቅርስ እና ማንነት በሐይማኖቱ ውስጥ ለዘመናት የተከማቹትን ጉዳዮች ነው። ታዲያ በሐይማኖቱ ውስጥ ከሚጐበኙት ውስጥ የቅድስት ድንግል ማርያም ኪነ-ሕንዎች ቅርሶች እና ታሪኮች አሁንም ግዙፉን ስፍራ ይዘው ይነሣሉ።

ለምሣሌ ከቀዳሚዎቹ ብንነሣ አክሱም ጽዮን ማርያምን ማስታወስ እንችላለን። ጽዮን ማርያም ከጥንታዊነቷ ባሻገር በክርስትና ሐይማኖት ውስጥ የሚታወቀው ጽላተ-ሙሴ የሚገኝባት ምድር ስለሆነች ሁለመናዋ ገዝፎ ይታያል። የአለምን የክርስትና ሐይማኖት ምስጢር ጠብቃ ለሺ ዘመናት የቆየች ደብር ናት። አስርቱ ትዕዛዛት የተፃፈበት የዋናው ጽላት መኖሪያ ስፍራ ስለሆነች ትልቅነቷን በቃላት ብቻ ገልጾ መጨረስ አይቻልም። ለዚህም ነው አክሡም ጽዮን ከዋናዎቹ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዷ የሆነችው።

ወደ ዘመነ ዛጉዌ ስርአት ስንመጣ ደግሞ 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አስገራሚ ታሪክ ይዛ ብቅ ትላለች። በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ገናና መሪ የነበረው ቅዱሰ ላሊበላ ካነፃቸው አብያተ-ክርስትያናት የመጀመሪያዋ የነበረችው ቤተ-ማርያም እየተባለች የምትጠራው እጅግ ውብ ኪነ-ሕንፃ ነች።

ቤተ-ማርያም አለት ከላይ ወደ ታች እየተፈለፈለ የተሠራች ባለ ፎቅ ኪነ-ሕንፃ ነች። የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አለትን ፈልፍሎ ወደታች ፎቅ ቤት መስራት የጀመረው ቤተ-ማርያምን ነው። የሰው ልጅ ምንም አይነት የግንባታ ስህተት ሣይኖረው ፍፁም (Perfect) ሆኖ የምድር ውስጥ ኪነ-ሕንፃን ያነጸው ቤተ-ማርያምን ነው።

በቤተ-ማርያም ግድግዳዎች ላይ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተአምራዊ ስዕሎችን እናገኛለን። ሣይወይቡ እና ሣይደበዝዙ ቆይተው ኢትዮጵያ እንዲህ ነበረች እያሉ ላለፉት 850 አመታት መስክረውላታል። የቤተ-ማርያም ስዕሎች ይዘታቸው ሠፊ ጥናትና ምርምር የሚጠይቁ ናቸው። የአለማዊ እና የመንፈሣዊ ሕይወትን ግጭቶች ፍጭቶች የሚያሣዩ ተምሣሌታዊ (Symbolic) ይዘት ያላቸው ስዕሎች ግድግዳውን ሞልተውታል። ላለፉት 850 አመታት በነጭ ኢትዮጵያዊ ሸማ ተሸፍኖ ያለው አልፋና ኦሜጋ ያለበት ፅሁፍ በዚህችው በቤተ-ማርያም ይገኛል።

ቤተ-ማርያም ውስጥ ስዋስቲካ ተብሎ የሚታወቀው ጥንታዊ ምልክት በሁለመናዋ አቅፋ ይዛለች። ስዋስቲካ የፀሐይ  ምልክት ነው። የብርሃን የተስፋ የሃሴት የማበብ ምልክት ነው።

ቤተ-ማርያም “ክሩዋፓቴ” የሚሠኘውንም ምልክት የያዘች ቤተ-ክርስትያን ናት። ክራዋፓቴ በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ተከስቶ በነበረው የመስቀል ጦርነት ወቅት ተዋጊዎቸ ይይዙት የነበረው የመስቀል ምልክት ነው። ይህ የአለም ምልክት የተፈጠረው በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ግርሃም ሃንኩክ The Sign and the Seal በተሠኘው መጽሐፉ ውስጥ ገልፆታል። ነገር ግን ይህ ገለፃ ስህተት ነው። ምክንያቱም ይህ ምልክት በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። አሁንም አለ። ያለበት ቦታ ደግሞ አክሡም ነው። የአፄ ካሌብ የመቃብር ድንጋይ /የድንጋይ ሣጥን/ ላይ ተቀርፆ ይገኛል። የ“ክሩዋፓቴ” ምልክት መገኛ አክሱም ኢትዮጵያ ነው። ቅዱስ ላሊበላ ይህን ምልክት የዛሬ 850 አመታት ከአክሡም የድንጋይ ሣጥን ላይ ወስዶ ቤተ-ማርያም ላይ በውብ ቅርፅ ሠርቶ አስቀመጠው። ይህ የክሩዋፓቴ ቅርፅ/ምልክት/ መገኛው ኢትዮጵያ ነው። ፀሐፊያን ግን የአክሡምን የአፄ ካሌብን መቃብር ሣያዩ በመቅረታቸው የአውሮፖ ምልክት አድርገውት ነበር። ግን ስሕተት ነው። ምልክቱ የኢትዮጵያ የመስቀል ቅርጽ ነው። ቤተ-ማርያም ላይ ቁጭ በማለቱ ግን አዲስ የመወያያ አጀንዳ ከፍቷል።

በዚህችው የቅዱስ ላሊበላ የመጀመሪያው አስደማሚ ኪነ-ሕንፃ በሆነችው ቤተ-ማርያም ውስጥ እጅግ የከበሩ ቅርሶች በውስጥዋ አሉ። ከቤተ-ክርስቲያኗ ጐን ደግሞ በርሷ ቁመት ልክ ጥልቀት ያለው ፀበል አለ። ፀበሉ ውስጥ መካን ሴቶች/ልጅ እምቢ ያላቸው/ በጠፍር ገመድ ታስረው ይጠመቃሉ። ቃል-ኪዳን ነውና ልጅ እንደሚወልዱ በሠፊው ይታመንበታል።

ከቤተ-ማርያም ወጣ ስንል በተራራ አናት ላይ ተገማሽራ የምናገኛት ደግሞ ጥንታዊቷን አሸተን-ማርያም ቤተ-ክርስትያን ነው። ከላስታ ላሊበላ ከተማ በበቅሎ እና በእግር ወደ ሦስት ሰአታት ተራራውን ወጥተን አሸተን-ማርያምን እናገኛለን። ላሊበላ አስጀምሯት አፄ ነአኩቶለአብ /1207-1247/ ያስጨረሳት ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍላ የተሠራች ነች። በአሸተን-ማርያም ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በጨርቅና በእንጨት ገበታ በውሃ ቀለም የተሣሉ ስዕሎች ይገኛሉ። ስዕሎቹ ባሕላዊውን የቀለም አሰራር የተከተሉ በመስመሮችና በወዝ የተሰሩ ናቸው። /የብርሃንና ጥላ አጣጣልን የሚያሣይ ስዕል በወዝ የተሠራ ይባላል።/

ቅድስት ድንግል ማርያም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ውስጥ ግዙፍ ሆና ከምትታይባቸው ቦታዎች አንዱና ትልቁ ግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ውስጥ ነው። በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ዳግማዊት እየሩሳሌም እያሉ ይጠሯታል። ምክንያቱም እየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ ተሰቅሎበት ነበር የሚባለው መስቀል የቀኙ ክንፍ በክብር ያረፈው በዚህች ገዳም ውስጥ እንደሆነ በከፍተኛ ደረጃ ይታመናል።

ግሸን ማርያም በስድስተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ከነበሩት አፄ ካሌብ ጀምሮ የተመሰረተች ብትሆንም በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቅዱስ ላሊበላ እጅም እንዳረፈባት ፀሐፊን ይገለፃሉ። ከፍተኛ ግርማ ሞገስ ያገኘችው ግን በአፄ ዘርአያእቆብ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። በውስጥዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቅርሶችን ይዛለች። እነዚህ ቅርሶቿ በዚያው በገዳሟ ውስጥ በሚገኘው መጽሐፈ ጤፉት በተሠኘው የብራና ፅሑፍ ላይ በዝርዝር ቀርበዋል።

ከዚህ ሌላ ለግሽን ደብረ-ከርቤየተፃፈ ተአምረ-ማርያም የተሰኘ የብራና ፅሁፍ አለ። የተፃፈው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ፀሐፊው አፄ ዘርአያቆብ ነው። ይህ ተአምረ ማርያም ትልቅ ቅርስ የሚያስኘው አሠራሩ ነው። ለምሣሌ የማርያም ስም ያለበት ቦታ የተፃፈው በወርቅ ነው። ወርቅ እየተነጠረ የማርያም ስም ተፅፎበታል። እሡ ብቻም አይደለም። ንጉሡ አፄ ዘርአያቆብ የአይናቸውን እንባ ከወርቁ ጋር እያላቆጡ የማርያምን ስም በወርቅና በእንባቸው ፅፈውታል። ይህ ታሪክ በተአምረ ማርያም የመፅሐፉ መግቢያ ላይ ሠፍሮ ይገኛል።

አፄ ዘርአ ያቆብ/1433-1467/ በማርያም ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪ በኢትዮጵያ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። የማርያምን አማላጅነት እና ፍቅር በኢትዮጵያዊያኖች ውስጥ እንዲሠርፅ አያሌ መፃሕፍትን የደረሡ ንጉስ ናቸው። ጥንቆላን' ሟርትን' ዛርን ለማጥፋት በሰው ሕይወት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ለውጥ ያመጡ ናቸው። አያሌ ታሪክ ፀሐፊዎች አፄ ዘርአ ያዕቆብን ሲገልጽዋቸው “ደራሲው ንጉስ” ይሏቸዋል። መፅሐፍትን ስለደረሱ ነው።

የቅድስት ድንግል ማርያም ታሪክና ቅርስ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ማበብ ግዙፍ አስተዋፅኦ ካጐናፀፉ እውነቶች መካከል አንዱ ነው። ለምሣሌ ወደ ጀመዶ ማርያም ገዳም እንጓዝ። ጀመዶ ማርያም ገደም ከወልድያ ከተማ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከዋጃ ከተማ ተገንጥሎ በሚወስደው አስቸጋሪ የእግር መንገድ የሰአታት ጉዞን የሚጠይቀው የግዳን ወረዳ ውስጥ ትገኛለች። እንደ ገዳሟ የሃይማኖት አባቶች ገለፃ ጀመዶ ማርያም ከተመሠረተች 1000 ዓመታትን አስቆጥራለች። ገዳሟ የምትገኘው ከትልቅ የባልጩት አለት ገደል ስር ርዝመቱ 15 ሜትር፤ ወርዱ 7 ሜትር፤ ቁመቱ ደግሞ በአማካይ 20 ሜትር ከሚሆን ዋሻ ውስጥ ነው።

በዋሻው መሀል በልዩ የግንባታ ጥበብ የታነፀውና ዙሪያውን በቅዱሣን ስዕል ያሸበረቀው የገዳሟ ቤተ-መቅደሰ የረቂቅ ጥበብ አሻራ መሆኑን ፀሐፊያን ይገልፃሉ። ከስዕሉ መካከል በወንጌላዊው ሉቃስ እንደተሣለች የሚነገርላትና ምስለ ፍቁር ወልዳ በሚል መጠሪያ የምትታወቀው የቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል የገዳሟ ልዩ የክብር ምንጭ ናት። በየአመቱ ጥቅምት 4 እና ግንቦት 1 ቀን በሚውሉት ክብረ-በአላት የምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል በመጋረጃ ተሸፍና በሦስት ቀሣውስት በጥንቃቄ ተይዛና በዝማሬ ታጅባ መሸፈኛው ተገልጦ ስዕሏ ለምዕመናን እንድትታይ ከቀኝ ወደ ግራ ሦስት ጊዜ ይዞራል። ምዕመናን ለምስለ ፍቁር ወልዳ ያላቸውን ሃይማኖታዊ ክብር በእልልታ በሆታና በስግደት ይገልፃሉ። ጥንታዊ የብራና መፃሕፍት መስቀሎች የተለያዩ ነዋየ ቅዱሣት በተለይም ከ950 አመት በላይ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት መቋሚያ ከጀመዶ ማርያምውድ ቅርሶች ጥቂቶቹ ናቸው።

ገነተ-ማርያምእየተባለች የምትጠራው ቤተ-ክርስትያንም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ነች። ገነተ ማርያም ከወልድያ መንገድ በመገንጠል 2 ኪ.ሜ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ከላሊበላ ከተማ 31 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ናት። ቤተ-ክርስትያኗ ከአንድ አለት ተፈልፍላ የተሠራች ናት። የሕንፃዋ የግድግዳ ስዕሎች ዛሬም ተመልካችን እንዳማለሉ ረጅሙን ጉዞ እየተጓዙ ነው።

ከታሪካዊ አብያተ-ክርስትያናት አንዷ የሆነችው መርጡለ ማርም ናት። መርጡለ ማርያም በእነብሴ ሳርምድር ወረዳ ከምድር ወለል 2600 ሜትር ከፍታ ባለው ኮረብታማ ስፍራ ላይ እንደምትገኝ የአማራ ክልል ታሪክ ያስረዳል።

ይህች ቤተ-ክርስትያን በአራተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን በወንድማማቾቹ ነገስታት በአብርሃ እና አጽብሃ ዘመነ መንግሥት እንደታነፀች ይነገራል። ከክርስትና መምጣት ቀደም ሲል በቦታው ለኦሪት እምነት መስዋዕት ይቀርብ እንደነበርና በዚያን ዘመን የስፍራው መጠሪያ ጽርሃ አርም ይባል እንደነበር ከአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል። ነገስታቱም ቤተ-ክርስትያኒቱን ካነፁ በኋላ ስሙን መርጡለ ማርያምወይም የማርም አደራሸ ብለው እንደሰየሙት ይነገራል።

ይህች ቤተ-ክርስትያን ፍርስራሿ ነው የሚታየው። የፈረሠችው በ16ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ላይ በነበረው የነ ግራኝ አሕመድ ጦርነት ወቅት ነው። ግን የአፄ ዘርአያዕቆብ ባለቤትና ኋላም የአፄ ልብን ድንግል ሞግዚት የነበሩት ንግስት እሌኒ በ1507/08 ዓ.ም አካባቢ በአራት ማዕዘን ቅርፅ በስፍራው አሰርተውት እንደነበር የሚነገርለት ድንቅ ቤተ-ክርስትያን የወደመው በዚሁ በነ ግራኝ ጦርነት ነው።

መርጡለ ማርያም በቱሪስቶች ከሚጐበኙ ታላላቅ የእምነት ስፍራዎች መካከል አንዷ ናት። በውስጥዋ የጦረኛው የግራኝ አሕመድ ካባ ይገኛል። የግራኝ ካባ እስከ አሁን ድረስ አለ። ከዚህ ሌላ የነገስታት መጐናፀፊያዎችና አልባሣት አክሊሎች የራስ ቁሮች የብራና መፃሕፍትና መስቀሎች ከብርና ከቀንድ የተሠሩ ዋንጫዎች ሌሎችም ቅርሶች በመገኘታቸውና በታሪኳ መርጠለ ማርያም የኢትዮጵያ አንዷ የጉብኝት ማዕከል ነች።

ጐጃም ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ አብያተ-ክርስትያናት ከሚባሉት እና በማርያም ስም በተሠሩት ውስጥ ደብረ-ወርቅ ማርያም አንዷ ናት። ከዲማ ጊዮርጊስ ተመልሠው ወደ ሞጣ በሚወስደው የመኪና መገንጠያ 10 ኪ.ሜ ያህል እንደተጓዝን የደብረ-ወርቅ ከተማን እናገኛለን። ከዚህች ከተማ ዳርቻ ምስራቃዊ አቅጣጫ ክብ ቅርፅ ባለው ኮረብታ ላይ ጥንታዊቷ የደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም ትገኛለች።

ይህችን ገዳም መስዕብ ካደረጓት ውስጥ የሕንፃዋ ቅርጻ ቅርፆች፤ የግድግዳ ስዕሎች፤ የነገስታት ገፀ-በረከቶች የደብረ ወርቅ ማርያምን ግዙፍነት የሚመሠክሩ ናቸው። በአንድ ወቅት በዚችው ቤተ-ክርስትያን ተገኝቼ ባሠባሠብኩት መረጃ ስዕሎቿ እና በውስጥዋ ያሉት የነገስታት ገፀ-በረከቶች አያሌ መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ።

ሌላዋ አስገራሚ የጐጃም ቤተ-ክርስትያን አገው ግምጃ ቤት ማርያም ናት። የአገው ግምጃ ማርያም ገዳም የተመሠረተችው በተለምዶ ፃዲቁ እየተባሉ የሚጠሩት ቀዳማዊ አፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት /1660-1674/ ነው። ይህች ታቦት ንጉሡ ከመናገሻቸው ከጐንደር እየተነሡ ያደርጉት በነበረው የመስፋፋት ዘመቻ ሁሉ አጅባቸው የምትሔድና ለንጉሡ ድል አድራጊነት ተአምራት ትሠራ እንደነበር የቤተ-ክርስትያን መረጃዎች የሚመሠክሩላት ነች።

የኢትዮጵያ ታላላቅ ምስጢራት ከሚገኙበት ስፍራ አንዱ የጣና ሃይቅ ውስጥ ባሉት ገዳማት ነው። ከነዚህ ውስጥ ደብረ ማርያም አንዷ ናት። ከባሕር ዳር ከተማ የሰሜን ምስራቅ አቅጣጫን በመያዝ በጀልባ ለሃያ ደቂቃ አሊያም በእግር ለአንድ ሰአት ተኩል በመጓዝና የአባይን ወንዝ በታንኳ በማቋረጥ የደብረ ማርያም ገዳም ወደምትገኝበት ደሴት መግባት ይቻላል። የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘችው የደብረ ማርያም ገዳም በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት /1307-1337/ ዓ.ም እንደተመሠረተች ይነገራል። አባይ ወንዝ ጣናን ሠንጥቆ በሚያልፍበት ቦታ ላይ ያለችው ይህቸ ቤተ-ክርስትያን ከዋነኞቹ የቱሪዝም ማዕከል ውስጥ አንዷ ነች።

በዚሁ በጉደኛው ጣና ሃይቅ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት ውስጥ ደብረ ሲና ማርያም ሌላኛዋ ተጠቃሽ የክርስትና ማዕከል ነች። ከጐንደር ጐርጎራ ወደብ ክበብ በአጥር ብቻ የተለየችውና በጣና ሃይቅ ዳርቻ የምትገኘው ደብረ ሲና ማርያም ቤተ-ክርስትያን በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጤ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት አባ ኤስዲሮስ በሚባሉ ባሕታዊ እንደተመሠረተች የቤተ-ክርስትያኗ ካሕናት ያስረዳሉ። አባ ኤስዲሮስ አመጣጣቸው ከሸዋ ደብረ ሲና ስለነበር ቤተ-ክርስትያኗም ደብረሲና ማርያም ተብላ ትጠራለች።

በዚሁ በጣና ሃይቅ ላይ ከሚገኙት አብያተ ክርስትያናት መካከል ዑራ ኪዳነ ምሕረት ተጠቃሽ ናት። ቤተ-ክርስትያኒቱ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ መሠራቷ ይነገራል። ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ አንድ ሠአት ከተጓዝን በኋላ የምናገኛት ውብ ገዳም ናት። ሰሜን ኢትዮጵያ የሄደ ቱሪስት ሁሉ ጐራ የሚልባት ይህችው ገዳም በውስጥዋ አያሌ ቅርሶችን ሸሽጋ የኖረች የኢትዮጵያ መድመቂያ ጌጥ ነች።

የማርያም አብያተ-ክርስያናት ብዛታቸው እጅግ ብዙ ነው። ሁሉንም መጥቀስ አይቻልም። ከጥንታዊዎቹ ዋሸራ ማርያም፤ ደብረሲና ማርያም፤ ናዳ ማርያም፤ ዋልድቢት ማርያም፤ ዑራ ኪዳነ-ምህረት፤አትሮንስ ማርያም፤ ተድባበ ማርያም፤ ሎዛ ማርያም፤ ማህደረ ማርያም፤ ቁስቋም ማርያም፤ ጎንደሮች ማርያም፤ ጣራ ማርያም፤ ደረስጌ ማርያም፤ ቆሮቆር ማርያም፤ አረፈደች ማርያም ወዘተ የመሳሰሉ እጅግ ድንቅ ታረክ ያላቸው አብያተ-ክርስትያናት በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ። ሁሉንም በዝርዝር ማቅረብ ሰፊ ቦታ ይወስዳል። መጎብኘቱን ላንባቢዎች እተወዋለሁ።

ባጠቃላይ ሲታይ የማርያም ተጽእኖ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ውስጥ ግዙፉን ቦታ ይዞ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስም ዋነኛዋ መለያዋ የሆነችው ማርያም ናት። አንዳንድ ታላላቅ ጸሀፊያን ሳይቀሩ ቅድስት ድንግል ማርያም በስደትዋ ወቅት ከልጅዋ ከእየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጣና ገዳማት ውስጥ ኖረዋል ብለው ጽፈዋል። የጣናም ሰዎች ማርያም እና እየሱስ ጣና እንደኖሩ እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ ማስረጃዎችን እያቀረቡ ያስረዳሉ። ጉዳዩ ለጥናትና ምርምር የሚጋብዝ ነው።¾

ይምረጡ
(13 ሰዎች መርጠዋል)
10383 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us