“የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእሡ እንዳይገዛ ውግዝ ይሁን”

Wednesday, 10 February 2016 13:30

 

አቡነ ጴጥሮስ

የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ባለፈው እሁድ ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም በጊዜያዊነት ከተቀመጠበት ከቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለስልጣን መስሪያ ቤት በክብር ተነስቶ፣ ተጉዞ፣ የቀድሞው ቦታ ላይ አርፏል። በእለቱም ከፍተኛ የሆነ አጀብና ድምቀት የነበረው ይህ ስነ-ስርአት ቆሜ ብዙ እንዳስብ አደረገኝ። ለካ ሰማዕታቶቻችን የማክበር የመከዘር ልምዳችን እያደገ መጥቷል እያልኩ ከሰው ፊት ሁሉ አተኩሬ እመለከት ነበር። ሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለቀላል ባቡር ግንባታ ተብሎ ከቦታው ተነስቶ ሲሔድ ብዙዎች ቅሬታ አሠምተው ነበር። ብዙ ሲፃፍበትም ቆይቷል።

 

የቅሬታዎቹ መነሻ ለአቡነ ጴጥሮስ ያለን ፍቅር እና ታላቅነት መግለጫ ነበሩ። እኚህ አባት ታላቅ የሐይማኖት መሪ ሕይወታቸውን ለፋሽስት ኢጣሊያ መስዋዕትነት ቤዛ ያደረጉት ለኢትዮጵያ ፍቅር ሲሉ ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን አባትነት ሲያሣዩ ነው። እጅና እግራቸው ለካቴና ደረታቸውን ለጥይት የገበሩት። የእርሣቸው መንፈስ ታላቅ ነው። አይነኬ ነው። ስለዚህ የሰው ተቃውሞ ለዚህ የመስዋዕት ክብር መገለጫ ነበር።

 

አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር እንደ እንደ አንዳንድ የሐይማኖት ሠዎች አድማቂ አልነበሩም። እግዚአብሔር ለኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሰጣት ብለው አላመኑም፤ አልሰበኩም። ይሔ የእግዚአብሔር ስራ ነው፤ በርሱ ስራ ጣልቃ አልገባም ብለው ኢትዮጵያን አልሸጡም። መራጭ እና አንጋሽ ፈጣሪ ነው ብለው ኢትዮጵያን ለፋሽስት ሠራዊት አልሠጡም። ይልቅስ ኢትዮጵያ በአርዮሶች እጅ መውደቅ የለባትም ብለው መንፈሣዊ ትግል የጀመሩ የመንፈሣቸውንም ልዕልና አንዲት ሕይወታቸውን በመስጠት ያረጋገጡ አባት ናቸው። የትውልድ ሞዴል የሰው ታላቅነት መገለጫ፤ የሐገርና የሕዝብ ፍቅር ማለት ምን እንደሆነ ማሣያ፤የአማኝነት የሐይማኖት የእምነት መሪ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ያሣዩ የቁርጥ ቀን ስብእና ናቸው።

 

የአቡነ ጴጥሮስ የሕይወት ታሪክ እንደሚያስረዳው የተወለዱት በ1875 ዓ.ም በሠላሌ አውራጃ በፍቼ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ስማቸውም ኃይለማርያም ይባል ነበር። የልጅነት ጊዜቸውን ያሣለፉት በታላቁ ገዳም ደብረ- ሊባኖስ ውስጥ ነው። የቤተ-ክሕነቱን ትምህርትም በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል።

 

ከ1917 ዓ.ም እስከ 1919 ዓ.ም በዚያን ጊዜ አልጋ ወራሽ የነበሩት በኋላ አፄ ኃይለሥላሴ በእርሣቸው ትዕዝዝ አምስት ሠዎች ተመርጠው የቄርሎስ (Cyril) የመፅሃፍ ትርጉም ሥራ ሠሩ። ከአምስቱ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ /ሐይለማርም/ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው።

 

የሐይማኖት ትምህርታቸውን አየገፉበት ሲመጡ በ1900 ዓ.ም ወደ ምንኩስና ሕይወት ገቡ። በተለያዩ ገዳማትና አድባራትም እየተዘዋወሩ ትምህርት ይሰጡ ነበር።

 

በ1921 ዓ.ም ደግሞ አራት ኢትዮጵያዊያን መነኮሳት ወደ ግብፅ አሌክሣንደሪያ ሔደው የፓትራያክነት የጵጵስናን ትምህርት እንዲማሩ ሲደረግ እርሣቸው አንዱ ነበሩ። ከዚያም አቡነ ጴጥሮሰ ተብለው ወደ ሐገራቸው መጡ።

 

ወዳጄ ጋዜጠኛ በልሁ ተረፈ የአብሲኒያ ፈርጦች በሚል ርዕስ ታሪካቸውን ከፃፈላቸው ሠዎቸ መካከል አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። እርሱ እንደሚገልፀው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር አቡነ ጴጥሮስ ከአርበኞች ጋር በመሆን ጦርነቱን ለመቀልበስ ወደ ማይጨው ዘምተዋል። ከማይጨው ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ሲፈታ ወደ መሀል አገር ተመለሱ። ሚያዚያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ። ገዳሙ ውስጥ ሆነውም የሠላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ነበር።

 

በዚህ ወቅትም ለኢጣሊያ ያደሩ የሐይማኖት አባቶች አቡነ ጴጥሮስን እየተከታተሉ ያሉበትን ይጠቁሙ ነበር። በኋላም አቡነ ጴጥሮስ ከገደሙ ወጥተው ወደ አዲሰ አበባ መጡ። ከአርበኞች ጋር ሆነው አዲሰ አበባ ዙሪያን ከጠላት ለማስለቀቅ በሚደረገው ብርቱ ሙከራ አድርገው ነበር። በኋላ ተማረኩ።

 

ፓትሪክ ሮበርትስ ሐምሌ 30 ቀን 1928 ዓ.ም ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባስተላለፈው ሪፖርት እንዲህ ፃፏል፡-

… የኢትዮጵያን ሐይል በምዕራብ በኩል አጠቃ። ኢትዮጵያዊያኖች የሚያሰገርምና ከባድ ውጊያ አደረጉ። ወደ አዲስ አበባም እየተጠጉ ሲመጡ ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣሊያን ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው። ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው ኢትዮጵያዊያን ይዘውት የነበረውን ቦታ ትተው ሲመለሡ ጳጳሡ አቡነ ጴጥሮሰ ተማረኩ። አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ ከአርበኞች ጋር አብረው የመጡ ናቸው። የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ነው…

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምስራቅ ኢትዮጵያ አጭር ዜና የሚሠኘው መፅሃፍ እንዲህ ይላል።

 

… ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም ከሠራዊቱ ጋር ሆነው እስከ ሚቻላቸው ድረስ ሠርተው በሳቸው በኩል የነበረው የጦር ሠራዊት መመለሡን በተረዱ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሮሜ ከተማ በሮማውያን እጅ እንደተገደለና ክብርንም እንደወረሠ እሣቸውም በጠላት እጅ ተያዙ.. ሲል ይገልፃል።

 

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከዋሉበት የጀግንነት ሜዳ በጠላት ጦር እንደተማረኩ አንድ የሃይማኖት አባት እንዲህ ብለዋል፡-

--- ይማፁኑባት የነበረችውን የኪዳነ ምህረት ፅላት ይዘው ወንጌላቸውን እንደ ጋሻ መክተው መስቀላቸውን እንደ ከባድ መሣሪያ ከፍ አድርገው ይሄው--- አለሁ። ብለው ለፋሽስት ሠራዊት አስታወቁ.. ብለዋል።

 

አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስቶች እጅ ከወደቁ በኋላ ሃሣባቸውን ለማስቀየር እነ ማርሻል ግራዚያኒ ብዙ ጥረዋል። ከኢጣሊያ አገር ምን የመሠለች አውቶሞቢል ይመጣልዎታል፤ ትልቅ ጳጳስ አድርገን እንሾምዎታለን፤ ቤት ንብረት እንሠጥዎታለን፤ በየሀገሩ እየተዘዋወሩ ይመጣሉ ወዘተ-- እየተባለ ተለመኑ፤ በመጨረሻም እንዲህ አሉ፡-

 

..ነፃነቴን ሐይማኖቴን ቤተ-ክርስትያኔን በጥቅም አልለውጥም፤--የፋሽስትን የበላይነትም አልቀበልም። ዕውነተኛውን ነገር ትቼ ሐሠቱን አልናገርም። ለሥጋዬም ፈርቼ ነፍሴን አልበድላትም። አንተም መግደል የምትችል ሥጋዬን እንጂ ነፍሴን አይደለም። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የወረረችው በማይገባ ነው እንጂ በሚገባ አይደለም--አሉ።

 

ከዚያም የጦር ፍርድ ቤት ተቋቋመ። ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው።

በወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ዜና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ፓጂያሌ ሁኔታውን አስመልክቶ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል፡-

 

ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸው ዘለግ ያለ አዋቂነታቸው እና ትህትናቸው ከገፃቸው የሚነበብ ሲሆኑ በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብስ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭካ የተበከለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎቱ ቀረቡ። ለፍርዱም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖች እና የጦር ሹመኞች ነበሩ። የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር። የቀረበባቸውም ወንጀል-- ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራሳቸውም አምፀዋል፤ ሌሎችም እንዲያምጹ አድርገዋል የሚል ነበር። ዳኛውም-- ካህናቱም ሆኑ የቤተ-ክህነት ባለስልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቂርሎስም የኢጣሊያን መንግስት ገዥነት አሜን ብለው ሲቀበሉ፤ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ? በማለት ጥያቄ አቀረበላቸው። አቡነ ጴጥሮስ የሚከተለውን መለሱ.. አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው። ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ሀላፊነት ያለብኝ የቤተ-ክርስትያን አባት እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ስለ ሀገሬ እና ስለ ቤተ-ክርስትያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሠናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አተንኩ አሉ።

የሞት ፍርዱ ተፈረደ። ሕዝብ በተሠበሠበበት የአሁኑ አደባባይ ላይ እንዲገደሉ ተወሠነ። በወቅቱ እዚያው ነበርኩ የሚለው ጋዜጠኛ ፓጂያሎ እንዲህ ይገልፀዋል።

 

የመግደያው ቦታ ተዘጋጁቶ ጴጥሮሰ ተወሠዱ። ፊታቸውን ወደ ተሠበሠበው ሕዝብ አድርገው ቆሙ። በሕዝቡና በጴጥሮስ መሀል ያገር ተወላጅ ወታደሮቸ ቆመው ሕዝቡ እንዳይጠጋ ይከላከላሉ። አቡነ ጴጥሮስ ሰአታቸውን አውጥተው አዩ። ወዲያውም አጠገባቸው ያለውን ጣሊያናዊ ለመቀመጥ እንዲፈቀድላቸው ጠየቁት። ቀና ብለው ሠገነት ላይ ወደተቀመጥነው ጋዜጠኞችና መኳንት አይተው የመቀመጥ ጥያቄቸውን ትተው ቀና ብለው ቆሙ። ከፊታቸው ለቆሙት ገዳዮቻቸው ተመቻቹላቸው። አቡኑ ረጋ ብለው ተራመዱ፤ ካራሚኚየሪዎቹም ከመግደያው ቦታ እስኪቆሙላቸው ጠበቁ። ከቦታው ሲደርሱ አስተርጓሚ ተጠግቶ አይንዋ እንዲሸፈን ይፈልጋሉን አላቸው። እሣቸውም ሲመልሡ የእናንተ ጉዳይ ነው፤ እንደወደዳችሁና እንደፈለጋችሁ አድርጉ፤ ለአኔ ማንኛውም ስሜት አይሠጠኝም አሉ። ከዚሀ በኋላ ጴጥሮስ ፊታቸውን ወደ ግድግዳ እንዲያዞሩ ተደረገ። እሣቸውን ቀድሞ በመግደል ክብር የሚፈልጉት ስምንት ካራማኚያሪዎች ከጴጥሮስ 20 እርምጃ ያህል ርቀው በርከክ አሉ። በአስተኳሹም ትዕዛዝ ተኮሱ። ጴጥሮሰ ጀርባቸው በጥይት ተበሳሳና ከመሬት ወደቁ። ሬሣቸውም ከከተማ ውጭ ተወስዶ በሚስጢር ተቀበረ-- በማለት በዐይኑ ያየው ጋዜጠኛው ፅፏል።

ሌሎች ሠዎችም የተመለከቱትን እንዲህ ብለው ፅፈዋል

 

ከሚገደሉበት ስፍራ ሲደርሱ አራቱን ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ። ከኪሣቸው መፅሃፍ ቅዱስ አውጡ። ሰአታቸውን አዩ፤ መጽሐፍ ቅዱሱንም አገላብጠው ተመለከቱ፤ ከዚያም በሕዝቡ ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፤ ፋሽስቶች የአገራችን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት አይምሠላችሁ፤ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር፣ የሠውን እርስትና ሃብት የሚቀማ፣ አብያተ-ክርስትያናትን የሚያቃጥል፣ ደም የሚያፈስ፣ ይህ በመካከላችሁ የቆመው አረመኔ የኢጣሊያ ፋሽስት ነው-- የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእሱ እንዳይገዛ ውግዝ ይሁን ። የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን። ብለው አማተቡ፤ ሲጨርሱም በጨርቅ አይናቸውን እንዲሸፍኑ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ሞትን ፊት ለፊት ገጥሜ ድል መንሣት ስለምፈልግ ባትሸፍነኝ ደስ ይለኛል። በማለት መለሱ። ከዚያም አቤቱ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ የእኔን ሞት ለኢትዮጵያ ሰማዕታት ደም መፍሰስ የመጨረሻ አድርገው፤ ወገኖቼ ብዙ ሳይቀሰፉ ፀሎታቸውን ስማ። ይቅር በለን ብለው ፀሎታቸውን እንደፈፀሙ፤ ስምንት ወታደሮች አነጣጠሩባቸው፤ ካፒቴኑ ተኩስ የሚል ትዕዛዝ ሲሠጥ ስምንቱም ተኩሡባቸው። ወደቁ። ከአንገታቸው በታች ሠውነታቸው ተበሣሣ። ካፒቴኑ አገላበጣቸው። ነፍሣቸው አልወጣችም ነበር። ካፒቴኑም ከወገቡ ያለውን ሽጉጥ መዞ በሦስት ጥይት መታቸው። ሕይወታቸውም አለፈች።

 

ይህ የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ለኛ ነው። ለኢትዮጵያ ነው። ትልቅ መንፈሣዊነት፤ ትልቅ ልዕልና፤ የከፍታ ማሣያ ስብዕና ናቸው።

 

እኚህን የሐገር ፍቅር መገለጫን ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ1961 ዓ.ም ጴጥሮስ ያቺን ሰአት በሚል ርዕስ ታላቅ ትራጄዲ ፅፎላቸው ለመድረክ አብቅቷል። ፀጋዬ የአቡነ ጴጥሮስ የመንፈስ ልዕልና ሕያው እንዲሆን ያደረገ የጥበብ አባት ነው።

 

በነገራችን ላይ ልክ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣሊያ አንገዛም፤ ብለው በመቃወም ሕዳር 24 ቀን 1929 ዓ.ም ኢሉባቦር ጐሬ ከተማ በግፍ የተገደሉ ሌላ ሰማዕት አሉን። እርሣቸውም አቡነ ሚካኤል ይባላሉ። ከጵጵስና በፊት የነበራቸው ስም መምህር ሀዲስ ተብለው ይጠሩ ነበር። ወደፊት ስለ እኚሁ ሰማዕትም አጫውታችኋለሁ።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
11359 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us