ጴጥሮስ ያቺን ሰአት

Wednesday, 10 February 2016 13:30

 

በጥበቡ በለጠ

ከኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን፣ 1961 ዓ.ም

አዬ' ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?

ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?

እስከመቼ ድረስ እንዲህ'መቀነትሽን ታጠብቂባት?

ልቦናሽን ታዞሪባት?

ፈተናዋን'ሰቀቀንዋን'ጣሯን ይበቃል ሳትያት?

አላንቺ እኮ ማንም የላት….

አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን'በፋሽታዊ ነቀርሳ

ታርሳ'ተምሳ' በስብሳ

ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን'እንደኰረብታ ተጭኗት

ቀና ብላ እውነት እንዳታይ'አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት

ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት

ሥልጡን'ብኩን'መፃጉዕ ናት፤…

እና ፈርቼ እንዳልባክን'ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን

አንቺ ካጠገቤ አትራቂ'በርታ በይኝ እመ ብርሃን

ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት'እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን።

አዎን'ብቻየን ነኝ ፈራሁ

እሸሸግበት ጥግ አጣሁ

እማፀናበት ልብ አጣሁ

እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ'ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ…

አዋጅ'የምሥራች ብዬ'የትብት ምግቤን ገድፌ

ከናቴ ማኅፀን አልፌ

በኢትዮጵያ ማኅፀን አርፌ

ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ

ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ

ከወዟ ወዜን ቀፍፌ

በሕፃን እግሬ ድሄባት'በሕልም አክናፌ ከንፌ

እረኝነቴን በሰብሏ'በምድሯ ላብ አሳልፌ

ከጫጩትና ከጥጃ'ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤

በጋው የእረኛ አደባባይ'ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ

የገጠር የደመና ዳስ'በገደል ሸለቆ አዳራሽ

ከቆቅና ከሚዳቋ' ከዥግራ ጠረን ስተሻሽ

በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ

ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስንገጥም'ከቀበሮ ድብብቆሽ

ለግልገሌ ካውሬ ከለል

እማሣው ሥር ጐጆ መትከል

ለፀሐይ የሾላ ጠለል'ለዝናብ የገሳ ጠለል

ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ

የግጦሽ ሣር ሲለመልም'ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ

አዝመራው ጣል ከንበል ሲል'ከብቱ ለሆራ ሲነዳ

ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ'ከወፎች ዜማ ስቀዳ

ልቤ በንፋስ ተንሳፎ'በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ..

ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት

እመ ብርሃን እረሳሻት?

ያቺን የልጅነት ምስራች? የሕፃንነት ብሥራት

የሣቅ የፍንደቃ ዘመን ይምኞት'የተሥፋ ብፅአት

ያቺን የልጅነት እናት?

አዛኚቱ እንዴት ብለሽ'ጥርሶችሽን ትነክሽባት?

ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ'ባገልግሎትሽ ስዋትት

ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት'ከድጓ ቤት እመጻሕፍት

ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ'ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ

ከቀፈፋ ደጀሰላም'ከቤተልሔም ቅዳሴ

አኰ'ቀፎ ዳባ ለብሶ

ቅኔ ዘርፎ ግሥ ገሦ

መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ

በልብስ ተክህኖ አጊጦ'በብር አክሊል ተሸልሞ

እመ ብርሃን ያንች ጽላት'ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ

የመናኒው ያባተድላ' ሆኜ አብሮኝ ታድሞ

ሕይወቴ እምነትሽን ፀንሶ

ሥጋ ፈቃዴ ታድሶ

ለሕፃንሽ መዲና ቆሞ'ለክብርሽ ድባብ ምሶሶ

ሥሜን በስምሽ ሰይሜ'ሆነሽኝ የእምነቴ ፋኖስ

በዋዜማሽ ግሸን ማርያም' ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ

ስሮጥ'በወንበሩ አኖርሺኝ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ

ታዲያን ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ' ከምትሰጪኝ ለፍርሃት ጦስ

ምነው በረኝነት ዕድሜ ዓይኔን' በጓጐጣት የሎስ

የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ'ወርዶ በጭለማ በርኖስ

ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ' ባክሽ መስለ ፍቁር ወልዳ

ጽናት ስጪኝ እንድካፈል' የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ'

ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ' ከነደደችበት እቶን

የሷን ሞት እኔ እንድሞታት'ገላዋ ገላዬ እንዲሆን።…

አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ

እፀናበት ልብ አጣሁ።…

ሕፃን ሆኜ የእርግብ ጫጩት'አንዳንዴ ራብ ሲያዳክማት

ችጋር ከጐጆዋ ገብቶ' እዛፍ ግርጌ ሲጥላት

እናቷ በርራ ደርሳላት

በአክናፏ ሙቀት ታቅፋት

እፍ እያለች ግንባሯ ላይ'ሕይወት ስትነፍስባት

ወዲያው ነፍስ ትዘራለች

ሽር -ብር-ትር እያለች።

ባክሽ አንቺም አትራቂብኝ

እመ ብርሃን እናቴ'ትንፋሽሽን እፍ በይብኝ

ፅናትሽን እፍ በይብኝ'

ወይም ይቺን የሞት ጽዋ'ጥላዋ ነፍሴን ካፈናት

እንዳልጠጣት አሳልፊያት

መራራ ክንፏን ገንጥለሽ'ቀጠሮ'ቃልዋን ግደፊያት፤..

አለዚያም ጽናትሽን ስጪኝ'ልጠጣው ኪዳነ-ውሉን

የኔ ፈቃድ እምነትሽ ነው'ያንች ፈቃድ ብቻ ይሁን

እንደ ጳውሎስ እንድፀና'በፍርሃት እንዳልታሰር

በውስጤ ከሚታገለኝ'በሥጋ አውሬ እንዳልታወር

ለየዕለቱ ሞት እንዳልሰንፍ

የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥፍ

ቃልሽ በሕሊናዬ ዲብ ኃይልሽ በሕዋሴ ይረፍ

ፍርሃት ቢያረብብብኝም'አንቺ ካለሺኝ አልሰጋም

ኩርምት ብዬ እችልበት'እሸሸግበት'አይጠፋም

የግማደ መስቀሌን ጉጥ'እታገስባት አላጣም

አለዚያማ ብቻዬን ነኝ'ኢትዮጵያም ያላንቺ የለች

አንቺ አፅኚኝ እንድፀናላት'

አሥርጪብኝ የእምነት ቀንጃ'ለሥጋቴ አጣማጅ አቻ

ለጭንቀቴ መቀነቻ።..

ባክሽ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ

እሸሸግበት ጥግ አጣሁ

እምፀናበት ልብ አጣሁ…

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
16012 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us