የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም

Wednesday, 26 February 2014 12:59

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ- ያሳስባል!

በሚል ርዕስ ለተፃፈው ከተቋሙ የተሰጠ ምላሽ

    

በዚሁ በሰንደቅ ጋዜጣ ረቡዕ የካቲት 05/2006 ዓ.ም ከላይ በተጠቀሰ ርዕስ ድንበሩ ስዩም በተባሉ ፀሀፊ የተፃፈውን አንብበናል። ከፅሁፉ ለመረዳት እንደሚቻለው ፀሀፊው በተቋሙ ቤ/መፃህፍት የሚጠቀሙ መሆኑን የሚጠቁሙ ነጥቦችን አንስተዋል። በተቆርቋሪነታቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ነገር ግን ፀሀፊው ይህንን ፅሁፍ ከማውጣታቸው በፊት የተቋሙን ዳይሬክተር! የቤ/መፃህፍት ኃላፊ ወይም የሙዚየሙን ኃላፊ አነጋግረው ቢሆን ኖሮ የነበረባቸውን የመረጃ ክፍተት ሊያጠቡ ይችሉ ነበር። በዚህ ጉዳይ ብቻ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ መረጃ ለሕትመት በቅቷል እላለሁኝ።

በቀድሞ ዘመን የነበሩ ኃላፊዎች የሠሩትን ስራ ሲጠቅሱ በየመስሪያ ቤቱና በየግለሰቡ ቤት እየሄዱ መፃሕፍት ያሰባሰቡ እንደነበረ ፅፈዋል። አሁን ይህ አይነቱ ስራ እንደተቀዛቀዘ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ከ2000ዓ.ም ወዲህ እንኳን የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ለማወቅ የፈለገ ሰው የሚከተሉት ስራዎች ተከናውነው ያገኛቸዋል። በአሜሪካን ሀገር የሚገኝ የክርስቲያን ሰን ፈንድ በሰጠው የገንዘብ እርዳታ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በኢትዮጽያና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ የተፃፉ አያሌ መፀሀፍት ተገዝተው ወደ ቤተመፃህፍቱ ገብተዋል። በቅርቡ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የሆኑት ሚስስ ፓትሪሽ ኤም.ሀስላሽ ለጥናትና ምርምር ጠቀሜታ ያላቸውን 93 (ዘጠና ሦስት) መፃህፍትን ለተቋሙ ቤ/መፃህፍት በስጦታ አበርክተዋል። በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግሥት በጀነራልነት ማዕረግ ያገለገሉ የጦር መኮንኖች የማዕረግ ልብሶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በተደረገ ግንኙነት ወደ ተቋሙ ሙዚየም እንዲገቡ ተደርጓል። የዝነኛው ጥላሁን ገሰሰ ልብሶችና ዊልቸር ወደ ተቋሙ የገባው አሁን በኃላፊነት ላይ ያሉት የተቋሙ ሰራተኞች ከቤተሰቡ ጋር ባደረጉት ግንኙነት ነው። እንዲሁም የፀጋዬ ገ/መድህን፣ የመንግሥቱ ለማ፣ የማሞ ውድነህ፣ የሀዲስ አለማየሁ አልባሳትና ዶክመንቶች ወደዚህ ተቋም የገቡት በቅርብ ጊዜ ነው። በዚሁ ዩኒቨርስቲ የተማሩና አሁን በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ሰዎች በየጊዜው የሚፅፉአቸውን መፃህፍት ኮፒዎች በየጊዜው ለተቋሙ እያበረከቱ ለቤ/መፃህፍቱ ተጠቃሚዎች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ በዕርዳታና ማስተባበሪያ መስሪያ ቤት ሲሰሩ የነበሩ የመምሪያ ኃላፊ ለጥናትና ምርምር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰነዶች ለተቋሙ ያበረከቱ ሲሆን ከነዚህ ዶክመንቶች ጋርም በወቅቱ የዕርዳታ አሰጣጡን ሁኔታ የሚያሳዩ አያሌ ፎቶግራፎችም በስጦታ ተበርክተዋል። በደርግ ያገዛዝ ወቅት የኢህአፓ አባል ሆነው የታገሉና አሁን በስደት በአሜሪካና በሌሎችም የአለማችን ክፍሎች የሚገኙ ሰዎች በዚያን ጊዜ በሁለቱም ጎራ ስለነበረው የፖለቲካና ወታደራዊ ትግል መፃህፍት እየፃፉ ሲሆን ለተቋሙ እየላኩ የተቋሙ ቤ/መፃህፍትም ለተጠቃሚዎች አዘጋጅቶ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ተቋሙ በነሪቻርድ ፓንክረስት ጊዜ የተሰበሰቡ መዛግብቶች ላይ ብቻ የቆመ ሳይሆን በየጊዜው በነበሩት አመራር ሥር በሚሰባሰቡ መዛግብቶች አቅሙን እያጎለበተና እያሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል። ምናልባት ፀሀፊው በቅርብ ጊዜ ወደተቋሙ የገቡ መዛግብትን ተጠቅመው ስለማያውቁ ይሆናል። በተቋሙ ውስጥ ያሉት መዛግብቶች በፓንክረስት ጊዜ የተሰባሰቡ ብቻ ናቸው ብለው ለመፃፍ የደፈሩት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የለውጥ ሂደት ትግበራ ላይ እንዳለ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ላይ ደግሞ የሠራተኞች ዝውውር ስለተከናወነ በአንዳንድ ስራዎች ላይ አዲስ የተመደቡ ሠራተኞች ቦታውን እስኪይዙ ድረስ ክፍተት በመፈጠሩ የግዥ ሂደቱ ወቅቱን ጠብቆ ሊካሄድ አልቻለም። አሁን ግን ተገዝተው የሚገቡት ጋዜጦችና መፅሔቶች ወደተቋሙ ቤ/መፃህፍት በመግባት ላይ ይገኛሉ።

በእርግጥ ተቋሙ ለሚሠራቸው ስራዎች በየበጀት ዓመቱ የሚያስፈልገውን በጀት ሰርቶ ያቀርባል። ነገርግን የጠየቀው በጀት ሁሉ ያገኛል ማለት አይደለም። ተቋሙ ማንኛውንም አይነት መዛግብት ለማግኘት የራሱን ጥረት ከማድረግ ውጭ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማትን ማስገደድ አይቻልም። የሚታተሙ ማንኛውም የህትመት ውጤቶች በታተሙ በአንድ ወር ውስጥ ለብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍት ኤጀንሲ መስጠት አለባቸው። ይህ በአዋጅ ስልጣን በተሰጠው መስሪያ ቤት ብቻ ነው ማስገደድ የሚቻለው። የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የመዛግብት ማሰባሰብ ሥራ ይሰራል እንጂ የሚያስገድድበት ስልጣን የለውም።

ተቋሙ በግዥና በስጦታ የሚያሰባስባቸውን ጋዜጦችና መፅሔቶች እያስጠረዘ ለተጠቃሚው በሚመች መልክ አደራጅቶ ያስቀምጣል። ይህንን የጥረዛ ስራ የሚሰራለት በክፍያ ሌላ አካል ነው። ተቋሙ ክፍያም ፈፅሞ በጥራዝ ዕቃዎች እጥረት ምክንያት እስካሁን ድረስ ሥራው ሳይከናውን ቀረ እንጂ በተቋሙ ኃላፊዎች ድክመት አለመሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን። ተቋሙ የራሱ የጥራዝ ሥራ የሚያከናውንበት ክፍል ኖሮት ሳይሰራ ቢቀር ኖሮ በእርግጥም የተቋሙ ኃላፊዎች ድክመት ይሆን ነበር።

የመዛግብት የማሰባሰቡ ሥራ የእያንዳንዱ ኢትዮጽያዊ ስራ ስለሆነ እርስዎ በግል ተነሳስተው ለተቋሙ የሰጡት መዛግብት አለን? በኢትዮጽያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ያሉ የብራና መፃህፍትና መዛግብት ዲጂታይዝድ ተደርገው በመቀመጣቸው ተጠቃሚዎች የብራና የመዛግብት ኮፒ ቢፈልጉ በተቋሙ መመሪያ መሠረት በሲዲ ተገልብጦ መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል።

አሁን ያሉት የተቋሙ ዳይሬክተር ከሚያዚያ 2004 ዓ.ም ከተመደቡ ወዲህ በርካታ ስራዎች በተቋሙ ውስጥ ተሰርተዋል። ከነዚህም ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው ታዋቂው የተቋሙ ጆርናል እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ያሉትን እንዲታተሙ ተደርጓል። ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋሙ የሚገኘው ሙዚየም ዓለም አቀፋዊ ወርክሾፕ አካሂዷል። 18 (አስራ ስምንተኛው) አለም አቀፍ የተቋሙ ኮንፈረንስ በድሬደዋ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። ቤ/መፃህፍቱና ሙዚየሙ ለሠራተኞቹ የሥራ ላይ ስልጠናዎች በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሰጥተዋል። አሁን በኃላፊነት ላይ ያሉት የተቋሙ ዳይሬክተር ከተቋሙ አባላት ጋር በተረጋጋ ሁኔታ በመሥራት ሥራና ሠራተኛን እያገናኙ ነው። ውዝፍ ሥራዎችን ቀድሞ ከነበሩት አመራሮች ቢረከቡም ያለ ምንቸገረኝነት ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን በመገንዘብ ያሉትን ቀዳዳዎች ከሠራተኞቹ ጋር በመሆን ሸፍነዋል። እየሸፈኑም ነው። ሙዚየሙንም ሆነ ቤ/መፃሕፍቱን ለማሳደግ ጥናትና ምርምሩም መልክ እንዲይዝ እያደረጉ ነው። የተቋሙ ሰራተኞችና ሕብረተሰቡም እየረዳቸው ነው።

     እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ክንውኖች ከብዙ በጥቂቱ የተሰሩ ሲሆን አሁንም የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ትግበራ እየተገባ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት በተለያየ የሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች የራሳቸውን ጥረት ሲያደርጉ ባለድርሻ አካላት ደግሞ የራሳቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለታሪክ ጠቀሜታ አለው ብሎ የሚያምንባቸውን መረጃዎች ለተቋሙ እንዲያበረክት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10057 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us