“እነዚህ ሁለት የፍልስፍና ጽሁፎች ከኢትዮጵያዊ አእምሮ የሚፈልቁ አይደሉም”

Wednesday, 24 February 2016 14:36

 

 

-    ኢትዮጵያዊውን ፈላስፋ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት

በጥበቡ በለጠ

ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ጓደኛዬ ደራሲ ዳንኤል ወርቁ በ2007 ዓ.ም ያሳተመው መጽሀፍ ነው። መጽኀፉ የሁለት ኢትዮጵያዊያንን ፈላስፋዎች ጽሁፍ የያዘ ነው። መጽሀፉ ሐተታ ዘርዓያቆብ እና ሐተታ ዘወልደ ሕይወት ይሰኛል። በተለይ ፈላስፋው ዘርዓያቆብ ከፍተኛ የሆነ አለማቀፋዊ የመነጋገሪያ አጀንዳ ነው። ክርክሩ ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐያቆብ በመፅሐፉ ላይ የሚከተለውን ጽፏል።

 

“ጥንት የተወለድሁት ከአክሱም ካህናት ነው። በአክሱም አውራጃ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በነሐሴ 25 ቀን አፄ ያዕቆብ በነገሰ በ3ኛው ዓመት ከአገሬ ተወለድሁ። በክርስትናም ዘርዐያቆብ ተብዬ ተሰይሜያለሁ። ሰዎች ግን ወርቄ እያሉ ይጠሩኛል በማለት ፅፏል። ይህ ሰው ከጽሁፉ መግለጫ እንደምንረዳው ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነው። ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የያዛቸው ፍልስፍናዎች እጅግ የመጠቁ በመሆናቸው የፃፈው ሰው ኢትዮጵያዊ አይደለም ተባለ። ታዲያ ማነው ሲሏቸው አውሮፓዊ ነው ይላሉ። ለመሆኑ እነማን ናቸው እንዲህ የሚሉት? በምንስ ጉዳይ ነው እንዲህ የሚናገሩት? ዛሬ ይህን ሃሳብ እናብላላዋለን።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከተነሱ ፈላስፎች መካከል ዘርዐያዕቆብ እስከ ዛሬ ድረስ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ከዚሁ ከዘርዐያዕቆብ ጋር አብሮ ስሙ የሚጠቀሰው ሌላው ፈላስፋ ወልደህይወት ይባላል። ይህ ፈላስፋ የዘርዐያዕቆብ ደቀመዝሙር /ተማሪ/ ነበር። እጅግ አስገራሚው ነገር ዘርዐያዕቆብ ወልደህይወትን ለ59 ዓመታት አስተምሮታል። ይህ ምናልባት በምድራችን ላይ የረጅም ጊዜ “መምህርና ተማሪ” በሚል መጠሪያ ሊመዘገብ የሚችል ነው። አንዳንድ ቀልደኛ ፀሐፊዎች ወልደህይወት 59 ዓመት ሙሉ የተማረው ትምህርቱ አልገባው ብሎ ነው ወይ? እያሉ ያፌዛሉ። ነገር ግን አንድን ፈላስፋ ለመፍጠር 59 ዓመታት ጥቂት ናቸው። ፈላስፎች የሚፈጠሩት በምዕተ ዓመታት ውስጥ ስለሆነ ነው።

 

ዘርዐያቆብ ሀብቱ የተባለ ሰው ቤት በመምህርነት ተቀጥሮ ነው ወልደህይወትን ያስተማረው። ሀብቱ የወልደህይወት አባት ነው። በሀገራችን ተረት “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” የሚባለው ምሳሌያዊ ንግግር ለዘርዐያቆብና ለወልደህይወት በሚገባ የሚሰራ ነው። ምክንያቱም ወልደህይወት ደግሞ እጅግ የመጠቀ ፈላስፋ ነበር። ወልደህይወት ሲጽፍ፤ “ራሴ አግኝቼው እውነት መስሎ ካልታየኝ ከመጽሐፉና ከሰው የሰማሁት እውነት ነው ብዬ አልቀበልም ይላል”።

 

ለመሆኑ የነዚህ ፈላስፎች ጽሁፍ ምንድን ነው ማለታችን አይቀርም። ፍልስፍናቸው በእምነት ላይ ተመርኩዞ የሚፃፍ ነው። እውነት አንድ ናት ብለው ያምናሉ። ይህም ፈጣሪ አንድ እውነት ሆኖ ሳለ ይሄ ሁሉ ሃይማኖት ከየት መጣ ብለው ይጠይቃል። የሃይማኖቶች መብዛት ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ። የሰው ልጅ አንድ እውነት እያለችው እንዴት በዚህ ሁሉ ሃይማኖት ተከታይ ይሆናል? እያሉ ለዛ ባለው ብዕራቸው ከ370 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈላሰፉ ነበር።

 

“አንድ ቀን ወደ ማን ልፀልይ አልኩ። በእውነት የሚሰማኝ እግዚአብሔር አለን? ብዬ አሰብኩ። በዚህም ሃሳብ በጣም አዝኜ እንዲህ አልሁ፤ ዳዊት እንዳለው፤ “እንዴት ምንኛ ልቤን በከንቱ አፀደቅሁዋት?” ኋላም አሰብኩ፤ ይህ ዳዊት እንዲህ የሚለው፤ ጆሮን የተከለ አይሰማምን? በእውነት እንድሰማበት ጆሮን የሰጠኝ ማን ነው? አዋቂስ አድርጐ የፈጠረኝ ማን ነው? ወደዚህስ ዓለም እኔ እንደምን መጣሁ? ከዓለም በፊት ብኖር ኖሮ የሕይወቴን መጀመሪያ እና የእውቀቴን መጀመሪያ በአወቅሁም ነበር። እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርሁን? ነገር ግን እኔ በተፈጠርሁ ጊዜ ባልኖርሁም። አባቴና እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ለወላጆቼና ለወላጆቻቸው ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደዚህ ዓለም የመጡ እንጂ እንደኛ አልተወለዱም። እስከ ፊተኞች እስኪደርሱ ድረስ ፈጣሪያቸው ይፈልጋል።

ፈላስፋው ዘርዐያቆብ የራሱንም እምነት በተመለከተ የሚከተለውን ብሏል።

 

“እኔም ከሰዎች ጋር ከርስቲያናዊ እመስላቸው ነበር። ነገር ግን በልቤ እርሱ እንዳስታወቀኝ የሁሉ ጠባቂ እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር አላምንም። አማኝ ሳልሆን አማኝ ስለምመስል በእግዚአብሔር ዘንድ አበሳ ይሆንብኝ ይሆን? ብዬ አስባለሁ። ሰዎችን እንዲህ አድርጌ ሳታልል ሰዎች ሊያታልሏቹህ ይገባልን? ብዬ አሰብኩ። እውነቱንም ብገልፅላቸው ለትልቅ ጥፋት እንጂ ጥቅም የለውም። ከመሳደብና ከማሳደድ በስተቀር የምናገራቸውን አይሰሙኝም። ስለዚህ እንደነርሱ ሆኜ ከሰው ጋር እኖራለሁ ብዬ አሰብሁ።

 

እርሱ እንዳስታወቀኝም በእግዚአብሔር ዘንድ ኖርሁ። ከኔ በኋላ የሚመጡ እንዲያውቁኝ ግን እስከ ሞት ድረስ በኔ ዘንድ ሸሽጌ የምይዘውን ይህን መጽሐፍ ልጽፍ ወደድሁ። ከሞቴ በኋላ አዋቂና መርማሪ ሰው ቢገኝ በኅሳቤ ላይ ኅሳብ እንዲጨምርበት እለምነዋለሁ። ይኸውና እኔ ከዚህ በፊት ያልተመረመረውን መመርመር ጀመርሁ።”

የዚህ ፊላስፋ ታሪክ ፈረንጆቹ ወደ አውሮፓ ይወስዱታል። ኢትዮጵያዊ አይደለም ይላሉ። ይህ ጉዳይ የተከሰተበት አጋጣሚ የሚከተለው ነው።

 

በ1859 ዓ.ም ላይ እ.ኤ.አ ማለት ነው ዳባዲ የሚባል ፈረንሣዊ ከሰበሰባቸው የብራና ጽሁፎች ውስጥ የዘርዐያዕቆብ እና የወልደሕይወት የፍልስፍና ጽሁፎች ይገኙበታል። እነዚህን ጽሁፎች ተራየቭ የተባለ ሩሲያዊ ወደ አውሮፓ ወስዷቸው በሰፈው እንዲታወቁ አደረጋቸው። የሚገርመው ነገር እነዚህ ሁለት ጽሁፎች ወደ አውሮፓ ከመወሰዳቸው በፊት ንብረትነታቸው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካከል በኢትዮጵያ ይኖር የነበረ የአንድ ሮማዊ መነኩሴ Giuste da Urbi   እንደነበረ ተራየቭ ጽፏል።

 

ኰንቲ ሮሲኒ የተባሉ የኢጣሊያ ሰው ደግሞ በ1920 ላይ በፃፉት መጽሐፍ እነዚህ ሁለት የፍልስፍና ጽሁፎች ከኢትዮጵያዊ አእምሮ የሚፈልቁ አይደሉም። ከዚህ በፊትም በሀገሪቱ ውስጥ ተጽፈው አያውቀም። ኢትዮጵያዊ ሊያስባቸው አይችልም። እንዲህ ዓይነት ጽሁፍ ሊጽፍ የሚችል አውሮፓዊ ነው ብለዋል። ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረቡት እጅግ የተዛቡ ኅሳቦችን ነው።

 

ኰንቲ ሮሲኒ ከአውሮፓዊ አእምሮ የፈለቁ ኅሳቦች ናቸው ሲል የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጧል። ከነዚህም ውስጥ፡-

   1.      በሮማ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የነበረ ተክለሃይማኖት የሚባል ኢትዮጵያዊ ጂዊስቶ ዳ ኡርቢኖ የተባለ ሰው አንድ መጽሐፍ እንደደረሰና የዚህም መጽሐፍ ስም “ወርቄ” የሚባል እንደሆነ ተናግሯል ይላሉ። በሐተታ ዘርዐያዕቆብ ውስጥ እንደምናነበው “ወርቄ” የዘርዐያቆብ የመጠሪያ ስም ነው።

ይሄ የኰንቲ ሮሲኒ ገለፃ አደገኛ አባባል እና የዓለም ሕዝብን ያሳሳተ ነው። ምክንያቱም አባባሉ በውስጡ ግዙፍ ስህተት አለው። ኰንቲ ሮሲኒ የጠቀሱት ተክለሃይማኖት የተናገረው ዳ ኡርቢኖ ወርቄ የሚባል መጽሐፍ አለው እየተባለ ይነገራል። በወቅቱ ዳ ኡርቢኖ ጐንደር /በጌምድር/ ውስጥ ይኖር ነበር። ሁለተኛው ማስረጃ ዳባዲ የተናገረው ነው። ዳባዲ ያለው መነኩሴው ዳባዲ የነዘርዐያቆብን የፍልስፍና ጽሁፍ ከአንድ ወታደር ላይ አግኝቶ መግዛቱን ከዚያም እያባዛው ለሰው ሁሉ አደለ። በዚህም ምክንያት ወርቄ የሚባል መጽሐፍ ፃፈ ተባለ።

ይህ ሰው እያባዛ ሲያከፋፍል እርሱ እንደፃፈው ተደርጐ ተወራ። የሚከራከረው ጠፋ። ምክንያቱም በወቅቱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ጽሁፉን ስለማያውቁት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከሀይማኖት አንፃር የዘርአያቆብ አፃፃፍ በቤተ-ክህነት አካባቢ ያን ያህል ተወዳጅ ስላልሆነ ዳ ኡርቢኖ የኔ ነው ሲል የሚሞግተው አልነበረም።

 

   2.     ኰንቲ ሮሲኒ የኢትዮጵያዊ ጽሁፍ ሳይሆን የአውሮፓዊ ፍልስፍና ነው ያሉበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ፍልስፍና ያላቸው ጽሁፎች ባለመኖራቸው ነው ይላሉ።

እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይቻላል። ለመሆኑ ኰንቲ ሮሲኒ ሁሉንም የኢትዮጵያ የብራና ጽሁፎች አንብበዋቸዋል? ምክንያቱም 500 ሺ የብራና ጽሁፎች በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ነው።

 

  3.     በሦስተኛ ደረጃ ኰንቲ ሮሲኒ ያስቀመጡት ምክንያት በኢትዮጵያ ሊቃውንት ከአንዳንዶቹ በስተቀር ይበልጡ ስለ ዘርዐያቆብና ስለ መጽሐፉ አያውቁም ይላሉ።

ይሄም ሚዛን የማይደፋ መከራከሪያቸው ነው። ምክንያቱም የዘርዐያቆብ ፍልስፍና አጥባቂ ክርስቲያን በበዛባት ኢትዮጵያ በየአውደምህርቱ ስለማይነገር ኢትዮጵያዊያን በስፋት ሊያውቁት አይችሉም።

 

  4.     አራተኛ ምክንያት አድርገው ያስቀመጡት ደግሞ የመጽሐፉ እድሜ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ አይሄድም የሚል ነው።

 

ይሄ አባባል ደግሞ ኰንቲ ሮሲኒ ግዙፍ ስህተት ላይ መውደቃቸውን የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም የዘርዐያቆብን ፍልስፍና ያነበቡ ሁሉ አይመስሉም። ዘርዐያቆብ የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፀሐፊ ነው። በአፄ ሱስንዮስ እና በአፄ ፋሲለደስ ዘመን እንደኖረ ነው የፃፈው። የተወለደበትንም ዓ.ም በግልፅ ጽፏል። እና ኰንቲ ሮኒሲ ከየት አምጥተው ነው ከ200 ዓመት በላይ ክፍተት የፈጠሩት? ስለ ኰንቲ ሮሲኒ ጽሁፍ ከዚህ በላይ መናገር ውጤት የለውም።

አንድ አይጌን ሚትሾክ የተባለ ጀርመናዊ ደግሞ በግዕዝ ቋንቋ የሰዋሰው ሕግ መሠረት የዘርዐያቆብ ፍልስፍና ብዙ ስህተት ያለው ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የፃፈው አይደለም ብሎ የዐ.ነገሮችን ምሳሌ ጽፏል።

 

ነገር ግን አይጌን ሚትሾክ ያቀረባቸውን የዐ.ነገር ስህተቶች /እሱ ስህተት የሚላቸው ማለት ነው/ በቋንቋው ሕግ ሲመዘኑ ስህተት አይደሉም። የግዕዝ ቋንቋን ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚባሉት ዛሬ በሕይወት የሌሉት ባለቅኔው ደራሲ ዓለማየሁ ሞገስ ሚትሾክ ያስቀመጣቸው ዐ.ነገሮች በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ስህተት አለመሆናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስን የግዕዝ ትርጉም ሁሉ እያጣቀሱ አቅርበውለታል። ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ አና በግዕዝ ቋንቋ ሊቅ የሆነው ጀርመናዊው ዲልማንም ሚትሾክ ያቀረባቸው መከራከሪያዎች ውድቅ እንደሆኑ ጽፈዋል።

 

በአጠቃላይ ሲታይ እነ ኰንቲ ሮሲኒ የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሁፍ እና የፍልስፍና ታሪክ ለማጥፋት ዘመቻ ያደረጉ ይመስላል። የዘርዐያቆብ ፍልስፍና ከኢትዮጵያዊ አእምሮ አይፈልቅም ብሎ መናገር ክብረ-ነክ ጉዳይ መስሎ የሚታይ ነው።

 

ኰንቲ ሮሲኒ ከተሳሳቷቸው ገለፃዎች ውስጥ አንዱ የፈላስፋው ዘርዐያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍናዎችን አንድ ሰው የፃፋቸው ናቸው ማለታቸው ነው። ነገር ግን ሁለቱ ሰዎች የተለያዩ ናቸው። ዘርዐያዕቆብ እና ወልደህይወት በአስተሳበባቸው የተለያዩ ናቸው። እርግጥ ነው ዘርዐያዕቆብ የወልደህይወት የቤት ውስጥ አስጠኚ ወይም መምህር ነበር። ወልደህይወት ከዘርዐያዕቆብ በላይ እጅግ ጠያቂና ተጠራጣሪ ነው።

 

የነ ዘርዐያቆብ እና የወልደህይወትን የፍልስፍና ጽሁፎች ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንዲደርስ ያደረጉትን ደራሲ ዘመንፈስ ቅዱ አብርሃ /1984/ እና ፍልስፍናዎቹን በተከታታይ ያሳተመውን ዳንኤል ወርቁን ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
9335 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us