“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ግዜ አበሻ”

Wednesday, 02 March 2016 13:25

 

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ የቃል ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ በሁለት ስንኞች ግጥም መግጠም እጅግ የተዘወተረ ነው። እንደ ቀላል ነገር በሁለት ስንኞች የሚገጠሙት ጉዳዮች በውስጣቸው ከአንድ መፅሐፍ በላይ ኀሣብ ይይዛሉ። ከነዚህ ግጥሞች መካከል ለዛሬ ጽሑፌ እንደ ርዕስነት የወሰድኩት ሁለት መስመር ግጥም እምቅ ኀሣብ የያዘ ነው። ሲተነተን፣ ሲዘረገፍ ከአበሻው ንጉሥ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ቅኝ አገዛዝ ስርአት እና ለነፃነት የተከፈለን ዋጋ ያብራራል። በሁለት ስንኞች የሚገጡ ግጥሞችን ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ‘መንቶ’ ይላቸዋል። የእንግሊዝኛውን Couplets  የሚለውን ቃል ለመተካት የተጠቀመበት ትርጉም ይመስለኛል። ባጠቃላይ ሲታይ በዛሬዋ እለት የምናከብረው የአድዋ ድል ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የቅኝ አገዛዝን ሙከራ በግማሽ ቀን ጦርነት ድል አድርጋ ያሣየች እና ለወረራ' ለመረገጥ' ለባርነት ፈፅሞ የማትንበረከክ ሀገር መሆኗን ያሣየችበት ዕለት ነው። ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነፃነት መታገያ ተምሣሌት  ሆና ብቅ ያለችበት ድል ነው። ዛሬ አድዋን እያነሣሣን እንጨዋወታለን።

የክረምት ወራት እንዳለፈ ምኒልክ ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ። መስከረም 1 ቀን 1888 ዓ.ም ነጋሪነት እየተጐሰመ ሕዝብ እንዲሰበሰብ ተጠራ። ከቤተ-መንግስት ፊት ለፊት በተተከለ እንጨት ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሎ ጃንጥላዎች ቀሣውስት ዘርግተው የተለመደውን ልብሰ ተክሕኖ ቀሚሣቸውን ለብሰው ቆመዋል። የምኒልክ ቤተ-መንግሥት ጠባቂዎችም ጋሻና ጐራዴያቸውን አንግተው አዋጁ ከሚነገርበት ቦታ ተሰብስበዋል። ከዚያም የሚከተለው አዋጅ ተነበበ፡-

#ጦር እንዲሰበሰብ ነጋሪት ተጐስሟል። እንግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህ ለሀገሬ ስል ብሞት ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሣፍሮኝ አያውቅም። አሁንም ያሣፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። ንግሥናዬ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። አሁን ደግሞ አገር የሚያጠፋ፤ ሀይማኖት የሚያስለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ሆይ፤ ካሁን ቀደም ያስቀየምኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። እናም የሀገሬ ሕዝብ ሆይ፤ አሁን ጠንካራ የሆንክ በጉልበትህ እርዳኝ። ደካማ የሆንክ ለልጆችህ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በፀሎትህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ልብ አድርግ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማሪያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። እናም ዘመቻዬ በጥቅምት ወር ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ በወረኢሉ ከተህ ላግኝህ$

ይህ የዳግማዊ ምኒልክ የክተት አዋጅ ነው። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ካለበት ነቅሎ መጣ። ምኒልክና ጣይቱ ጦራቸውን ይዘው ወደ አድዋ ጉዞ ማድረግ ጀመሩ።

 

እዚህ ላይ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር አለ። ታላቁ ንጉስ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ የመንግስታቸው መቀመጫን አዲሰ አበባን ቤተ-መንግሥታቸውን መንግስትነ ታቸውን ይዘው ወደ አድዋ ሲጓዙ ስልጣናቸውን ለማን ነበር ያስረከቡት? በምኒልክ ቦታ ኢትዮጵያን የሚመራው፤ ቤተ-መንግሥቱን የሚያስተዳድረው ማን ነበር? ማን ነው በእርሣቸው ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ተጠባባቂ ንጉስ የሆነው? ኢትዮጵያን አደራ ብለውት ያስረከቡት ማንን ነው? ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ተወርቶበት አያውቅምና በጥቂቱ አንዳንድ ነጥቦችን አነሣሣለሁ።

የአበሻው ንጉሥ አፄ ምኒልክ ስልጣናቸውን ያስረከቡት ለራስ ዳርጌ ነው። ምናልባት ምኒልክና ሰራዊታቸው ያልተጠበቀ ውጤት ገጥሟቸው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያን የሚመሩት ራስ ዳርጌ ነበሩ። ለመሆኑ ይህ ታላቅ ኃላፊነት የተሰጣቸው ራስ ዳርጌ ማን ናቸው?

 

ራስ ዳርጌ የንጉሥ ሳህለስላሴ ልጅ፤ የንጉሥ ኃይለመለኮት ወንድም፤ እና የአፄ ምኒልክ አጐት ናቸው። ዳርጌ በዘመናቸው እንደ እርሣቸው የሚወደድ እና የሚከበር የሸዋ ሰው የለም ይባል ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ዘምተው ሸዋን አሸንፈው ምንሊክን ማርከው ወደ ጐንደር ሲሔዱ ዳርጌም ተማርከው ነበር። በኋላ ቴዎድሮስ ወደመጡበት ሲመለሱ ሸዋን ለማስተዳደር ለዳርጌ ሊሰጡ አስበው ነበር። አማካሪዎቻቸው ደግሞ ዳርጌ እጅግ ተወዳጅ የንጉስ ልጅ ነው። እንዴት ሆኖ ነው ለርሱ የሚሰጡት በኋላ ሌላ ፈተና ያመጣብናል ብለው ስለመከሯቸው ቴዎድሮስ ዳርጌን ይዘው ሔዱ።

 

አፄ ቴዎድሮስ ከሸዋ ከማረኳቸው ንጉሳዊያን ቤተሰቦች ገና የ12 አመት ልጅ የሆኑት ምኒልክ እና ጐልማሣው ራስ ዳርጌ ይገርሟቸው ነበር። ሁለቱም እንደየ እድሜያቸው ሰፊ አውቀትና አስተሣሰብ የነበራቸው ናቸው። በዚህ ምክንያት ቴዎድሮስ ወደዷቸው። ወደ ስልጣናቸውም አቀረቧቸው። ለኢትዮጰያ ያላቸውን ሕልም አወጓቸው።

 

ታዲያ ምን ያደርጋል ምንልክን ከቴዎድሮስ እጅ ለማስመለጥ ሸዋ ዶለተ፤ አሴረ። እዚያ ሴራ ውስጥ ዳርጌም ዋና መሪ ነበሩ። ምኒልክን ከቴዎድሮስ ቤተ-መንግስት አስመለጡ። ዳርጌ ለራሣቸው ህይወት ሣይሰስቱ ምኒልክን የማስጠፋት ስራ ውስጥ ገቡ። ምኒልክም አመለጡ። የቴዎድሮስ ቀዬ ታወከ። ብዙ ሰው ተገደለ። ቴዎድሮስ ዳርጌንም ይዘው መቅደላ አምባ ላይ አሠሯቸው። የታሠሩት ከእንግሊዞች ጋር ነበር። ታዲያ በዚያ የእስራትም ወቅት ያገኟቸው እንግሊዛዉያን በፅሁፎቻቸው የዳርጌን ብልህነትና አስተዋይነት አስፍረዋል። ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሣቸውን ሲሰው ዳርጌ ከመቅደላ ወደ ሸዋ መጥተው ከምኒልክ ጋር ተገናኙ።

 

ራስ ዳርጌ ለአፄ ምኒልክ የአገዛዝ ዘመን ውስጥ በማማከር በማስታረቅ በመሸምገል በመገሰፅ ምኒልክን አስተካክለው ያሣደጉ አጐት ናቸው ይባላል። ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጭ አገር ዜጐች በፃፏቸው ማስታወሻዎች ራስ ዳርጌ ቅን ታማኝ የዘመነ አፄ ምኒልክ አስተዳደር ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሰው ነበሩ እያሉ ፅፈውላቸዋል። ምኒልክም በራስ ዳርጌ ሙሉ እምነት ስለነበራቸው ዳርጌ የተናገሩትን በሙሉ ሣያወላውሉ ይፈፅሙ እንደነበር ፀሐፍት ይገልፃሉ። ለዚህም ነው አጤ ምኒልክ ወደ አድዋ ጦራቸውን ይዘው ሲዘምቱ ለኚህ በእድሜና በልምድ የዳበረ የአስተዳደር ብቃት ላላቸው ሰው ኢትዮጵያን ጠብቁ ብለው ሰጥተዋቸው የሔዱት። መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ያረፉት ራስ ዳርጌ፤ አድዋን ባነሣን ቁጥር ልናስታውሣቸው የሚገባ የኢትዮጵያ ጠባቂና ባለአደራ መሪ ነበሩ። የራስ ዳርጌ አራተኛ ትውልድ ልጅ እንግዳ ገብረክርስቶስ መሿለኪያ አካባቢ ዛሬም አሉ።

ወደ አድዋ ድል ስንመለስ አያሌ ነገሮች ከፊታችን ድቅን ይላሉ። ይህ ድል 120 ዓመቱ ነው። ትልቅ በዓል ነው። ይህች አገር በነፃነት እንድትኖር፤ እኛም የነፃ ሐገር ዜጐች ነን ብለን በታሪክ ውስጥ ደረታችንን ነፍተን እንድንጓዝ ያደረጉትን የአድዋ ጀግኖችን ክብራቸውን ሁሌም ማወደስ ይገባናል።

 

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የአጤ ምኒልክ ሠራዊት ለቅኝ ግዛት ጦርነት የመጣውን የኢጣሊያን ሠራዊት በግማሽ ቀን ጦርነት ድል አድርገው ነፃነትን አወጁ። ሠራዊታቸው ባገኘው ድል ተደስቶ መዝፈን፤ ማቅራራት፤ መሸለል፤ መጨፈር ጀመረ። አጤ  ምኒልክ ይሔ ጭፈራ ይቁም ብለው አዘዙ። ገሠፁ። እነዚህ የአዳም ዘሮች ካለ ሀገራቸው፤ ካለ ምድራቸው፤ በባዕድ ሀገር መጥተው ሲያልቁ ያሣዝናሉ። እናም መዝፈን የለብንም፤ ይልቅስ የወዳደቀውን አስክሬናቸውን አንስተን በክርስትያን ስርዓት ቀብራቸውን እንፈፅም በማለት ምኒልክ ተናገሩ። ስርአተ ቀብራቸውም በፀሎት ተፈፀመ። የአበሻው ንጉስ አዛኝ እና ርሁሩህ ከመሆኑም በላይ ሃይለኛ ጀግና ነው እያሉ ጣሊያኖቹ ፅፈውላቸዋል።

 

የተለያዩ የወቅቱ ፀሐፊያን እንደገለፁት አፄ ምኒልክ ለማረኳቸው የኢጣሊያ ጀነራሎች፤ የጦር ሰራዊቶች ምህረት አድርገዋል። እንደውም ምርኮዎቻቸው ከእርሣቸው ጋር ሆነው ከአድዋ እስከ አዲስ አበባ መጥተዋል። ሲመጡም በጉዞው ወቅት ከአጤ ምኒልክ ወታደሮች ጋር እያወሩ፤ ስላለፈው ጦርነት እያወጉ፤ እየተደሰቱ ነበር፡ አዲስ አበባ ሲደርሱ በዚያ ወቅት እስር ቤት ባለመኖሩ ምክንያት በየሰው ቤት ተልከው ምርኮዎቹ ሰው ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት።

 

በዚህ አይነት የሰብዐዊ መብት አያያዛቸው የሚደነቁት ምኒልክ ሀገሪቱን ለከዳ ባንዳ ደግሞ ምህረት አልነበራቸውም። የኢጣሊያን ወራሪ እየመሩ የመጡ እና ወገናቸውን የወጉትን ኢትዮጵያዊያን ባንዳዎችን ቀጥተዋል። ለምሣሌ በጦርነቱ ወቅት ለኢጣሊያ ያደሩ 1500 ባንዳዎች ተይዘው ነበር። ራስ አሉላ እና ራስ መንገሻ ባንዳዎች ይገደሉ አሉ። ራስ መኮንን ራስ ሚካኤል ንጉሥ ተክለኃይለማኖት እና ፈረንሣዊው የምኒልክ አማካሪ ካፒቴን ክሎቼቲ ምህረት ጠይቀው ነበር። በጉዳዩ ላይ እንደገና ውይይት ተደረገ። በኋላ አንድ ውሣኔ ተወሰነ። ሀገራቸውን የከዱ፤ የወጉ፤ ለጠላት አሣልፈው የሰጡ ባንዳዎች የቀኝ እጃቸው ይቆረጥ ተባለ። ፍርዱም መወሰኑን ፀሐፊያን ይገልፃሉ።

 

አድዋ የኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል እና ያለመቀጠል ፍልሚያ የተካሔደበት የነፃነት ክብር ማሣያ ቦታ ነው። አጤ ምኒልክ እዚያው የድሉ ቦታ ላይ ሆነው የሠራዊታቸውን ጭፈራ ካስቆሙ በኋላ ይህች ቀን ወደፊት ትውልድ በየአመቱ የሚያስታውሣት ይሆናል ማለታቸውም ተጽፏል። አድዋ ከባርነት መውጫ ተምሣሌት የሆነ የጥቁር ሕዝቦች የመታገያ መቆስቆሻ ነው።

 

በአድዋ ጦርነት ወቅት ደቡብ አፍሪካ 200 አመታት ያህል በነጮች የቀለም አገዛዝ ውስጥ መከራዋን የምታይ ነበረች። ደቡብ አፍሪካዊያን ከዚያ መከራ ውስጥ ሊያወጣቸው የሚችል ተአምር አጥተው ተስፋ ቆርጠው ተቀምጠው ነበር። ነገር ግን የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ዕለት የዛሬ 120 አመት አድዋ ላይ ጥቁር ሕዝብ ሆይ ብሎ ወጥቶ የነጭን ወራሪ በግማሽ ቀን ጦርነት ፍርክስክሱን አወጣው የሚሉ ዜናዎች በአለም ላይ ናኙ።

 

ለካ ነጭን ማሸነፍ ይቻላል የሚል አስተሣሰብ ደቡብ አፍሪካዊያን ውስጥ ገባ። ኢትዮጵያ ጦርነቱን እንዴት አሸነፈች ብለው ማሰብ ጀመሩ። ኢትዮጵያዊያኖች በወቅቱ ለሀይማኖታቸው ፅኑ ነበሩ። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ታቦታት ወደ ጦርነቱ ቦታ ይዘው ሔደው ነበር። ቀሣውስት የሐገሪቱን ሃይማኖት ይዘው ጦር ሜዳ ላይ ነበሩ። ንጉሡ አጼ ምኒልክ ከባለቤታቸውና ከባለሟሎቻቸው ጋር ሆነው ለፈጣሪያቸው ይፀልያሉ። ከጦርነቱ  በፊትም ፀልየዋል። እናም ወደ ጦርነቱ ገቡ። ድልን በድል ላይ ተቀናጁ ። ስለዚህ የኢትዮጵያን፤ ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር ሁሉ ደቡብ አፍሪካዊያን መውሰድ ጀመሩ። ከነዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ሐይማኖት መከተል በግንባር ቀደምትነት የሚታወሰው ተግባራቸው ነበር።

 

የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ እና ፀሐፊ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በ2005 ዓ.ም ለአፍሪካ ሕብረት ሃምሣኛ አመት ክብረ በዓል ላይ ላዘጋጀነው JUBILEE በሚል ርዕስ ላሣተምነው የሕብረቱ መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፍ አሣትመው ነበር። የጽሑፋቸው ርዕስ Ethiopian Echoes in Early Pan-African Writings የሚሰኝ ነው። በዚህ ፅሁፋቸው ደቡብ አፍሪካዊያን ከአድዋ ድል በኋላ ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ከዚያም በርካታ አብያተ-ክርስትያናትን በኢትዮጵያ ስም መመስረት እንደጀመሩ ኘሮፌሰር ሪቻርድ በዝርዝር ያቀርባሉ ደቡብ አፍሪካዊያን ከመሠረቷቸው አብያተ-ክርስትያናት መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

1.  African United Ethiopian Church

2.  The Ethiopian Mission in South Africa

3.  The National Church of Ethiopia in South Africa

4.  St. Philip’s Ethiopian Church of south Africa

5.  Ethiopian Church Lamentation in South Africa

6.  The Ethiopian Church of God the Society of Paradise

 

እነዚህ ከላይ የሠፈሩት አብያተ-ክርስትያናት በኢትዮጵያ ድል ላይ በመደሰት ደቡብ አፍሪካዊያን ራሣቸው የመሠረቷቸው ናቸው። ከዚያ በኋላም እነዚሁ በቀለምና በዘር መድልዎ መከራቸውን የሚያዩ ሕዝቦች ኢትዮጵያን ለነፃነታቸው መታገያ ተምሣሌት አድርገው ረጅም አመታት የፈጀ መከራ አሣልፈው ነጻ ወጡ። ሌሎች የፍሪካ ሀገራትም በአድዋ ድል ምክንያት የመነቃቂያ ደወል ሰምተዋል። በሰሜን አሜሪካም ውስጥ የሚገኙ ጥቁሮች ከባርነት መውጫ መንገዳቸው ልክ እንደ አድዋ ጀግኖች በቆራጥነት መታገል እንደሆነ አምነው ተቀበሉ። ከዚያም ይህ ሁለ የጥቁር አለም ነፃ የወጣው አድዋ በሰጠው የድል ብስራት ነው።

 

ከአድዋ ድል በኋላ የአለም መገናኛ ብዙሃን ብዙ ሽፋን መስጠት ጀመሩ። አትላንታ ኮንስቲትውሽን የተሰኘው መጋቢት 4 ቀን 1888 ዓ.ም እንደዘገበው 3ሺ የኢጣሊያ ወታደሮች በግማሽ ቀን ጦርነት ውስጥ መገደላቸውን እና የኢጣሊያ ጀነራሎች በእጅጉ መዋረዳቸውን ፅፏል።

 

ኒውዮርክ ወርልድ እና ቺካጐ ትሪቢውን የተሰኙ ጋዜጦችም የአፄ ምኒልክን ምስል ሁሉ እያወጡ አስገራሚ ድል መሆኑን ዘግበዋል።

 

ቫኒቲ ፌይር በመባል የሚታወቀው የዚያን ግዜው ታላቅ ጋዜጣ እንደዘገበው ምኒልክን ከአለማችን ታላላቅ ሰዎች ተርታ አስቀምጧቸዋል። ለምሣሌ ሣይንቲስቱን ቻርልስ ዳርዊንን፤ ሩሲዊውን አሌክሣንደርን፡ ናፖሊዮን ሣልሣዊ እና አፄ ምኒልክን ፎቶዎቻቸውን እኩል አንድ ላይ አሣትሟቸዋል።

 

ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ አውሮፓ ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት ስማቸው ምኒልክ እየተባለ መጠራት እንደጀመረም ተዘግቧል። ወደ ኢትዮጵያም ለአፄ ምኒልክ የሚላኩ የአድናቆት ደብዳቤዎች እየበረከቱ መምጣታቸውም ተዘግቧል። የጥቁር ሕዝብ የትንሣኤ ክስተት መምጣቱን የሚናገሩ የሚፅፉ በርካታ ኘሬሶች ነበሩ። ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ወደ ልዕለ ሃያላን አገራት ጐራ ትገባለች በማለትም አስተያየት የሰጡም ነበሩ።

 

ለምኒልክ ከደረሷቸው በርካታ የአድናቆት ደብዳቤዎች ውስጥም አስቂኝ ደብዳቤዎች ነበሩ። ለምሣሌ የገንዘብ ብድር የጠየቋቸው አውሮፓውያን ሴቶች ነበሩ።

ኢትዮጵያ ላይ ፀሐይ መውጣት የጀመረችው በአፄ ምኒልክ በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ ነው። አፄ ቴዎድሮስ የፈራረሰችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ዘመናቸውን በጦርነት ጨረሱ። አፄ ዮሐንስም የቴዎድሮስ ሞትን ተከትሎ የመጣውን የሉዐላዊነት ችግር ለማስተካከል ሲሉ በደርቡሾች አንገታቸው ተቀልቶ ሞቱ። ቀጥሎም ኢትዮጵያን የማስተዳደር ስራ እጃቸው የገባው አጤ ምኒልክ ጦርነቶችን ሁሉ በድል እየተወጡ መላዋን ኢትዮጵያን ከባዕዳን ወራሪዎች ጠብቀው በነፃነት አቆሟት። ይባስ ብለው አድዋ ላይ ታላቁን የአውሮፓ ገናና መንግስት ኢጣሊያን ድባቅ መቱ።ከዚህ በኋላ ሁሉም የአውሮፓ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ዲኘሎማሲያዊ ግኑኙነት መፍጠር ጀመሩ። ኢትዮጵያን አክብሮ እና በሕጓ ተዝቶ አብሮ ለመስራት አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ ፈረንሣይ ወዘተ በተደጋጋሚ ከምኒልክ ጋር ውል መግባት ጀመሩ። የንግድ ግንኙነቶች ተጀመሩ።

 

Raymond Jonas የተባለ ታሪክ ፀሐፊ  The Battle of Adwa Africa Victory in the Age of Empire በተሰኘው ግዙፍ መጽሐፉ ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ አለማት ውስጥ ምን እንደተባለች ዘርዝሮ ፅፏል። እንዲሁም ደግሞ Harold Marcus, the Life and Times of Minilik II በማለት ባሣተመው መፍሐፍ ውስጥ የኚህን የግዙፍ ስብዕና ባለቤት የሆኑትን መሪ ታሪክ እናገኛለን።

 

ወደ ፀሐፊያን ጉዳይ ስመጣ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተው የሰጡንን ሠዎችም መጠቃቀስ ግድ ይለኛል። ከሁሉም በላይ ግን ምኒልክን በተመለከተ የጳውሎስ ኞኞን ያህል አስተዋፅኦ ያደረገ ሰው ያለ አይመስለኝም። ይኸው ብርቅዬ ጋዜጠኛ፤ ደራሲ፤ ታሪክ ፀሐፊ የሆነ ሰው በየካቲት ወር 1984 ዓ.ም አጤ ምኒልክ በሚል ርዕስ 509 ገፆች ያሉት እጅግ ውብ ታሪክ የተጻፈበትን መጽሐፍ አሣትሟል።

 

ከዚያም በመቀጠል በ2003 ዓ.ም በአስቴር ነጋ አሣታሚ ድርጅት አማካይነት ሁለት ግዙፍ የጳውሎስ ኞኞ መፃሕፍት ታትመዋል። አንደኛው አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች የሚሠኝ ሲሆን፤ ይህም 622 ገፆች ያሉት መፅሐፍ ነው። ሁለተኛው አጤ ምኒልክ በውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች በሚል ርዕስ የተዘጋጀና 337 ገጾችን የያዘ ነው። ጳውሎስ ኞኞ ስለ አጤ ምኒልክ ከነዚህ መፃሕፍቱ በተጨማሪ ልዩ ልዩ መጣጥፎችን በማሣተም ግዙፍ ውለታ አበርክቶ ያለፈ ሰው ነው። አድዋ በተነሣ ቁጥር ጳውሎስ ፊቴ ድቅን ይላል።

 

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን አድዋ ከተሰኘው ድንቅ ግጥሙ በተጨማሪ ምኒልክ የተሰኘ ትልቅ ቴአትር ፅፏል። ይህ ቴአትሩ እስከ አሁን ድረስ በመድረክ ላይ አልተሰራለትም። ልክ እንደዛሬዋ ዕለት 120ኛ አመት የአድዋ በአል ሲከበር አንዱ ቴአትር ቤት ይሠራዋል ብዬ ነበር። ግን አልተሰራም። ለካ ቴአትሩም ከፀጋዬ ጋር ሞቷል።

 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ ከንግሥተ ሳባ እስከ አድዋ ጦርነት ብለው ፅፈው ያዘጋጁት መፅሃፍ፤ የኘሮፌሰር አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የተሰኘው መጽሐፍ ይጠቀሣሉ። በነገራችን ላይ አፈወርቅ ገብረእየሱስ የአድዋን ጦርነት ያመጡ ሰው ናቸው። በወቅቱ እርሣቸው ኢጣሊያ አገር ለትምህርት ሔደው ነበር። እርሣቸው ባሉበት ከተማ ጣሊያኖች ተደስተው ይጨፍራሉ። ጉዳዩ ምንድን ነው ብለው ቢጠይቁ የውጫሌ ውል ኢትዮጵያ እና ኢጣሊያ ተፈራርመው ነው ተባለ። ውሉን ሲያዩት የትርጉም ስህተት እንዳለበት አፈወርቅ ጠረጠሩ። ከዚያም ለአጤ ምኒለክ ደብዳቤ ፃፉ። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ስር እንደሆነች የሚገልፀውን ሀረግ ዘርዝረው ፃፉላቸው። ምኒልክም በኢጣሊያኖች አጭበርባሪነት ተበሣጩ። በዚህ አፈወርቅ በፃፉት ደብዳቤ እና ከርሱ ጋር ተያይዞ ባለው በውጫሌ ውል የተነሣ የአድዋ ጦርነተ ተነሣ። እናም አፈወርቅ ገብረእየሱስ በታሪክ ውስጥ ዋናው የአድዋ ጦርነት አብሪ ጥይት ናቸው ማለት ይቻላል። ግን ምን ያደርጋል ጣሊያን ከ40 አመት በኋላ ቂም ቋጥሮ 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሲወር አፈወርቅ ባንዳ ሆነው አረፉት። እንዳስቀመጡት መግኘት ከባድ ሆነ።

ተክለፃዲቅ መኩሪያም አጤ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚል ርዕስ ያዘጋጁልን መፅሃፍ እርሣቸውን ዘልአለማዊ ካደረጉዋቸው ስራዎቻቸው መካከል አንዱ ነው።

 

ተክለሃዋርያት ተክለማርያም ስለ ራሣቸው የሕይወት ታሪክ በፃፉት መፅሃፍ ድንቅ የሆነ የአድዋ ዘመቻ ትዝታቸውን ያወጉበት ፅሁፍ ምን ግዜም አይረሣም። አድዋ ላይ በ17 አመት እድሜያቸው ተሣትፈው አንዲት ጥይት ሣይተኩሱ ጦርነቱ በግማሽ ቀን አለቀባቸው። እናም በጣም ተቆጭተው የፃፉት ፅሁፍ ከስነ-ፅሁፋዊ ውበትነቱ በተጨማሪ ታሪኩ ያስደስታል።

 

እጅግ አያሌ ፀሐፊያን አድዋን እንድናስታውሰው አድርገውናል። በሙዚቃ እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ን የሚያክል ድንቅ ስራ የሰራ የለም ብል ሌላውን መውቀሴ አይደለም። ጂጂ አድዋን ፍፁም ነብስና ስጋን አላብሳ የሠራች ድምፃዊትና ባለቅኔ ነች። ቴዎድሮስ ካሣሁን /ቴዲ አፍሮ/ ለአድዋ ሙዚቃው ጥራትና ወጪ ምንም ሣይሰስት ላበረከተው አስተዋፅኦ የጀግኖቹ መንፈስ ይመርቀዋል። ኘሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ Adwa An African Victory በማለት የሰራው  ፊልም ብዙ ነገሮች ቢቀሩትም ጥሩ መነቃቂያ የፈጠረ የኪነት ሰው ነው።

 

ሙሉቀን ታሪኩ የተረጐመው አፄ ምኒልክና የአድዋ ድል የተሰኘው መጽሐፍ፤ አምባቸው ከበደ የተረጐሙት የአሌክሣንደር ቡላቶቪች ከአፄ ምኒልክ ሠራዊት ጋር የተሰኘው መፅሃፍ፤ ኧረ ሌሎችም  እጅግ በርካታ ፅሁፎች ገናናውን መሪ እድንቀው ድላቸው ዘክረዋል።

 

አድዋ የነፃነት መንፈስ በጥቁር ሕዝብ ላይ ሁሉ ያጐናፀፈ የድሎች ሁሉ ድል ነው። ዘልአለማዊ ክብር ለአድዋ ጀግኖች ሁሉ እመኛለሁ። መልካም በዓል!

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
16354 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us