አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም

Wednesday, 09 March 2016 13:30

በጥበቡ በለጠ

በኢትዮጵያ የትግል እና የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ የካቲተ 12 ቀን ሁሌም ትዘከራለች። እንድትዘከር ካደረጓት ሦስት ሠዎች መካከል አንዱ አብርሃ ደቦጭ ነው። አብርሃ ደቦጭ እና ሞገሰ አስገዶም ቦምብ ግራዚያኒ ላይ ወርውረው ጉዳት በማድረሳቸው 30 ሺ ያህል የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ አልቋል። ጣሊያኖች ሕዝቡን ፈፅሞ የሰው ልጅ ያደርግዋል በማይባል ጭካኔ ጨፍጨፉት።

 

ይህ የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የቦምብ ውርወራ ድርጊት በተለያዩ ሠዎች የተለያዩ አስተያየቶች ይሠጡበታል። አብርሃ ደቦጭ አና ሞገስ አስገዶም ስለ ቦምብ ውርወራ፤ ስለ ቦምብ አፈታት፤ ስለ ቦምብ አጠቃላይ ሁኔታ የት ተማሩ፤ ማን አስተማራቸው፤ እነዚህ ሁለት ሠዎች ለዚህ ተግባራቸው ያነሣሣቸው እውነተኛው ምክንያት ምንድን ነው? ቦምቡን ከመወርወራቸው በፊት ምን ነበሩ? እነዚህ ከላይ የሠፈሩት ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር ኘሬዘዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በቅርቡ መግለጫ ሰጥተው ነበር። መግለጫቸው እንደሚያስረዳው በሚያዚያ ወር 2008ዓ.ም ለአብርሃ ደቦጭ አና ለሞገስ አስገዶም የመታሰቢያ ቴምብር እንደሚታተምላቸው የሚያወሣ ነው። እንደ እርሣቸው ገለፃ እነዚህ ሁለት ሠዎች ለፋሽስት ኢጣሊያ የአዲስ አበባው መሪ ግራዚያኒ ላይ ያደረጉት የቦምብ ውርወራ ታላቅ ተጋድሎዋቸውን የሚያሣይ መሆኑን እና የመስዋዕትነት ምሣሌ መሆናቸውን ብዙ ሠዎች ይናገራሉ።

 

አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ቦምብ ባይወረውሩ ኖሮ የኢጣሊያ ወረራ ይራዘም ነበር የሚሉ አሉ። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም በወቅቱ የኢጣሊያ አቅም ትልቅ ስለነበር እና የተደራጀ የጦር ኃይል ስለነበራት አርበኞች እየተዳከሙ ነበር። ለኢጣሊያ በባንዳነት የሚያድሩ አርበኞችም እየበረከቱ መጥተው ነበር። ነገር ግን አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ቦምቡን ከወረወሩ በኋላ ነገሮች ተቀየሩ። ፋሽስቶች ወዳጅ ጠላት ሣይሉ ያገኙትን የአዲስ አበባ ሕዝብ ሁሉ ይጨፈጭፉት ገቡ። ሕዝብ አለቀ። ፋሽስት ደም ተቃባ። በሕይወት የተረፈው አርበኝነት ገባ። አርበኛ የነበረው ይህን ግፍ ከላዩ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል የበለጠ ቁርጠኛ ሆኖ ትግሉን ቀጠለ።

 

የአብርሃ ደቦጭ እና የሞገስ አስገዶም የቦምብ ውርወራ ትግሉን አቀጣጠለው። የአርበኞችን ወኔ የበለጠ አፋፋመው የሚሉ በርካታ አስተያየቶች አሉ።

 

ሌሎች ደግሞ ዳር ሆነው ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመለከቱ ሰዎች የሚሠጧቸውም አስተያየቶች በዋዛ የሚታለፉ አይደሉም። እንደ እነርሱ አባባል ከቦምቡ ውርዋሮ አለመቀናጀት ጀምሮ በተለይ በአብርሀ ደቦጭ ስብዕና ላይ የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አሉ።

 

አብርሃ ደቦጭ በትውልድ ኤርትራዊ ነው። ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን የተከታተለ ወጣት ነው። ትምህርቱን እንደጨረሰ የተቀጠረው ጣሊያኖች ዘንድ ነበር። ጣሊያንኛን ቋንቋን አቀላጥፎ የሚናገር ነበር። ይህን ስራውን የሚሰራውም በኢጣሊያ ሌጋሲዮን ነበር። እንግዲህ ስራዉ ከጦርነቱ በፊት ነው። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት።

 

ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር ስትል በወቅቱ ንቁ የነበሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ሕዝቡን እየሰበሰቡ ልንወረር ነው፤ ሁላችንም ታጥቀን ወረራውን ለመቀልበስ እንዘጋጅ እያሉ ንግግር ያደርጉ ነበር። ዛሬ ሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት የምንለውና በዚያን ወቅት ደግሞ የሐገር ፍቅር ማሕበር እየተባለ በሚጠራው አዳራሽ እንደ ተመስገን ገብሬ ያሉ የነቁ ኢትዮጵያዊያን ሕዝብ እየሰበሰቡ ኢትዮጵያዊነትን ይሰብኩ ነበር።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ ኢጣሊያ ስለ ኢትዮጵያ አቋም መረጃ እየደረሳት ለወረራው እየተዘጋጀች ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ለኢጣሊያ መረጃ የሚሰጥ ሰው አለ ተባለ። ይህ ሰው ማን ነው ተብሎ ይታሰብ ገባ። በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ሰላይ አለ ተብሎ ሲፈለግ አብርሀ ደቦጭ ተጠርጥሮ ታሰረ። ስለ ኢትዮጵያ መረጃ አሣልፎ ለጣሊያኖች ይሰጣል በሚል ተጠርጥሮ ታሰረ።

እዚህ ላይ ቆም ብለን ብዙ ጥያቄዎቸ መጠየቅ እንችላለን። አብርሃ ደቦጭ አገሩን ለፋሽስቶች አሳልፎ የሰጠ ነው? ታዲያ ለምን ታሰረ? አንድ ሰው አርበኛ የሚባለው መቼ ነው? አገር ካስወረሩ በኋላ አርበኝነት አለ? እነዚህን ጥያቄዎች ሁላችንም ለራሣችን እንያዝ።

 

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አስተዳደር ጐልተው የወጡ ፖለቲካዊ ችግሮችና ትግሎች በቅርብ ባለሟላቸው የሕይወት ታሪክ መነሻነት ሲገመገሙ በተሰኘው መጽሐፍ ውሰጥ ስለ አብርሃ ደቦጭ አና ሞገስ አስገዶም ጉዳይ ተጽፏል።  እንደ መጽሐፉ ገለፃ አብርሃ ደቦጭ የታሰረው አፈንጉስ ከልካይ በተባሉ ባለስልጣን ቤት ነው። በወቅቱ እንደ አሁን ዘመን እስር ቤቶች የሉም ነበር። እስረኛ ሰው ቤት ውስጥ ነበር የሚታሰረው። ለዚህም ነው አብርሃ ደቦጭ እሰው ቤት የታሰረው።

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አብርሃ ደቦጭ እንዴት ከእስር ተፈታ የሚለው ጉዳይ ነው። አብርሃ ደቦጭ ከእስር ነፃ የወጣው ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወርረው በተቆጣጠሩበት ወቅት እሱም ከእስሩ ተፈታ። ነፃ አውጠት።

ከእስር ነፃ ከወጣም በኃላ ጣሊያኖች ዘንድ በአስተርጓሚነት ተቀጠረ። እናም ከፋሽስቶች ጋር መስራት ጀመረ፤ ያውም የኢጣሊያ የፖለቲካ ቢሮ አስተርጓሚ እንደነበር መፃህፍት ያወሣሉ።

 

ስለ አብርሃ ደቦጭ ብዙ መታወቅ መዘርዘር ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከነዚህ መካከል የጋብቻው ሁኔታ ነው። በወረራው ወቅት ጣሊያኖች ዘንድ እየሰራ ሳለ ያገባት እና ትዳር የመሰረተው የአርበኞች ቤተሰብ ከሆነችው ከወ/ሮ ታደለች እስጢፋኖስ ጋር ነው። ይህች ሴት የታላላቆቹ የኢትዮጵያ አርበኞች የነ ራስ መስፍን ስለሺ፤ የነ ራስ ደስታ ዳምጠው፤ የነ ደጃዝማች አበራ ካሣ የመሣሰሉት ሰዎች የቅርብ ዘመድ ናት።

 

ሰዎች ይህን ጋብቻ በሁለት ፅንፎች ይተነትኑታል። አንደኛው ፅንፍ ጋብቻው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነው፤ ጣሊያኖች ስለ አርበኞች መረጃ ለማግኘት ሲሉ አብርሃ ደቦጭ የአርበኞች ቤተሰብ የሆነችውን ልጅ እንዲያገባ አስበውበት የተደረገ ነው የሚሉ አሉ።

 

ሌሎች ደግሞ አብርሃ ደቦጭ የአርበኛ ልጅ በማግባቱ ልቡ ከፋሽስቶች ከድታ ወደ አርበኞች ተቀላቅላለች ይላሉ። ከጋብቻው በኋላ ጣሊያኖች ላይ አደጋ ለማድረስ ለራሱ ቃል እንደገባ የሚያመላክቱ መረጃዎችም አሉ። የኢጣሊያን ባንዲራ እያወረደ ይጥል ነበር የሚሉ መረጃዎች አሉ።

 

ጉዳዩን በሌላ አቅጣጫ የሚያዩ ሠዎች ደግሞ ጣሊያን የአዲስ አበባን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ምክንያት ፈልጐ በነ አብርሃ ደቦጭ በኩል ያቀናጀው የቦምብ ውርወራ ነው የሚሉ አሉ። በተለይ በ1937 ዓ.ም የታተመው የአምስቱ የመከራ አመታት አጭር ታሪከ በተሰኘው መፅሃፍ ይህን ጥርጣሬ ሰፋ አድርጐት ፅፎታል። ቦምብ ተወረወረብኝ በሚል ሰበብ ለ40 አመታት የቋጠረውን ቂም በአዲሰ አበባ ሕዝብ ላይ መአቱን አወረደበት እያሉ ትንታኔ የሚሰጡም አሉ።

 

እነ አብርሃ ደቦጭ ቦንቡን ከወረወሩ በኋላ በስምኦን አደፍርስ ሹፌርነት አዲስ አበባን ለቅቀው መውጣታቸው ይነገራል። ያቀኑት ደግሞ ወደ ሰሜን ሸዋ ወደ ፍቼ አካባቢ ወዳሉት አርበኞች ዘንድ ነው። ከነራስ መስፍን ስለሺ ዘንድ ሔዱ። ግን በታሪክ እንደሚወሣው እነ ራስ መስፍን ስለሺ፣ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም እነርሱ ዘንድ ሲመጡ አላመኗቸውም። ተጠራጥረውም አሠሯቸው። ጣሊያን የላከብን ሰላዮች ይሆናሉ በሚል ምክንያት ታሰሩ።

 

እነ አብርሃም ደቦጭ ከነ ራስ መስፍን ስለሺ እስር ቤት የተለቀቁት አንድ የሚመሰክርላቸውን ሰው አግኘተው ነው።

እነ አብርሃም ደቦጭን መስከረው ከእስር ያስፈቷቸው በጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ ይባላሉ። እርሣቸው ሲመሰክሩ እነዚህ ሁለት ሰዎች ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ለመጣል እንዳሰቡ ቀደም ሲል ነግረውኛል፤ አደጋ ለመጣል አስበውበት ነው ያደረጉት፤ ስለዚህ ለኢጣሊያ ስለላ እየሰሩ አይደለም በማለት መሰከሩላቸው። በዚህም ምክንያት እነ ራስ መስፍን ስለሺ ሁለቱንም ቦምብ ወርዋሪዎች ከእስር ፈቷቸው።

 

ከእስር ከተፈቱስ በኋላ ምን ሆኑ የሚለው ጉዳይ ሌላው አንገብጋቢ ነገር ነው። ብዙ ፀሐፊዎች አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምን ጣሊያን አስገድሏቸዋል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ መንገደኛ ኢትዮጵያዊ /ለጣሊያን ያደረ ባንዳ/ ገድሏቸዋል ይላል። በታሪክ ውስጥ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ አለፈ። በታሪከ ውስጥ የተጠናቀቀ የሕይወት መዕራፍ የሌላቸው ባተሌዎች ናቸው።

 

ፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ ከጥንት እስከ ዛሬ በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ አንድ የሚያስደነግጥ ነገር ፅፏል። የሚያስደነግጠው ጉዳይ አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ይገልፅና የሚከተለውን ፅፏል፡-

 

 ይፋ ያልወጡ መረጃዎች እንደሚያስረዱት ግን ከነ ሻለቃ/ራስ/ መስፍን ስለሺ እንደተለዩ የመጡት ወደ አዲሰ አበባ ነው። በምን ዘዴ እንደሔዱ ባይታወቅም ከነፃነት በኋላ እነ አብርሃ ደቦጭ በጣሊያን ዋና ከተማ በሮም ይኖሩ እንደነበር በወቅቱ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን መናገራቸው ታውቋል/ገጽ451/

 

ይህ ታሪክ የተፃፈው 740 ገፆች ባሉት በፋንታሁን እንግዳ መፅሐፍ ውስጥ ነው። አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ ሮም ውስጥ መታየታቸውን ማን ነው የፃፈው? የፋንታሁን ምንጭ ማን ነው?  መረጃውን ከየት አገኘው? ብሎ መጠየቅም ግድ ይለናል።

 

ይህ ታሪክ እውነት ከሆነ ደግሞ እጅግ የሚገሙ ሁኔታዎቸ ውስጥ ልንገባ ነው። ፋንታሁን እንግዳ መፅሀፉን ሲያዘጋጅ አያሌ ድርሣናትን አገላብጧል። ስለዚህ እነማን እንዲህ አይነት ታሪክ እንደፃፉ መግለጽ ይጠበቅበታል።

 

አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም በሚያዚያ ወር 2008 ዓ.ም በስማቸው ቴምብር የታተማል። እንዲህ ቴምብር እንዲታተምላቸው የሆነው ደግሞ አርበኞች ናቸው ስለተባለ ነው። አንዳንድ የውዥንብር ታሪኮች ሲቀርቡ ግራ የሚያጋቡ ጉዳዮች አሉ። ዛሬ በሕይወት የሌሉት እነዚህ ሁለት ወጣቶች ታሪካቸው በስርአት ተሰብስቦ መፃፍ አለበት።

ሁለቱንም ቁጭ ብዬ ረጅም ሰአት አሰብኳቸው። ቦምብን የሚያህል ነገር በ1929 ዓ.ም እጃቸው ላይ ይዘው ወደ ግራዚያኒ የገሰገሱት እነዚሀ ወጣቶች ያበጠው ይፈንዳ፤ የረጋው ወተት ቅቤ እንዲወጣው ይናጥ፤ ያሉ ይመስለኛል። አገሩን ናጡት። ትግሉ ተቀጣጠለ። የፋሽስቶችም ግብአ- መሬት ተቃረበ። ቀጥሎም የቅኝ ግዛት ሕልሙም ሞተ። ስለዚህ እኔ በበኩሌ አርበኛ የሚለውን ቅፅል ልተወው እና አብርሀ ደቦጭን የትግል አቀጣጣይ ኢንጂነር ነው ብለው ይቀለኛል።

ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣልያ ጦርነት በተሰኘ መጽኀፉ የሚከተለውን ብሏል፡-

 

አብርሃ ደቦጭ ኢጣልያንኛ ተምሮ ስለነበር አዲስ አበባ ባለው በፋሺስት ፖለቲካ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ ጀመር። በዚህ ጊዜ፣ ከሞገስ አስገዶም ጋርም ጓደኛ ሆኑ - ሞገስ አስገዶም የሚኖረው ስብሃት ከሚባል ጓደኛው ጋር ነው፤ ስብሃት ደግሞ የሚሰራው ከጀርመን ኮንሱላር ሚሲዮን ውስጥ ነው።

 

አብርሃ ደቦጭ የኢጣልያኖችን የግፍ አሰራር እና ትእዛዝ እያየ ለጓደኞቹ ያጫውት ነበር። እንዲህ አይነቱን ጨዋታ ብዙ ጊዜ የሚጫወቱት ስብሃት ከሚሰራበት ከጀርመን ኮንሱላር ሚሽን ውስጥ ነው። ጀርመን፣ የኢጣልያ መንግስት ደጋፊና ወዳጅ ስለነበር በእነ አብርሃም ደቦጭ መሰብሰብ ጠርጣሪ የለም ነበር።

 

ይህም ብቻ ሳይሆን አብርሃ በኢጣልያ ፖለቲካ ቢሮ ውስጥ የሚሰራ ሰው ስለነበር ከውጭ ያለው ሰው በክፉ አይን እያየው ስለሚጠላው የሚያጫውተው ቀርቶ የሚያስጠጋውም አልነበረም።

ይህን የመሳሰለው ነገር ሁሉ አብርሃን ያስቆጨዋል። ኢጣልያኖችን ለመበቀልም ቆረጠ። ጫማ አውልቆ በባዶ እግሩ መሄድ ጀመረ። ጫማ ማድረግ የተወበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩት። አንደኛው፣ እግሩን ለማጠንከር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ያን የተቀደደበትን ጫማ መለወጫ በማጣቱ ነበር። ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ ኒውስ ይባል በነበረው ጋዜጣ ላይ አልአዛር ተስፋ ሚካኤል እንደፃፈለት "አብርሃ ደቦጭ ጫማ በሌለው እግሩ እግሩ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ አስር እና አስራምስት ኪሎ ሜትር እየራቀ መሄድ ጀመረ። በሄደበትም ጫካ ውስጥ ድንጋይ እየወረወረ ስለ ቦምብ ኣጣጣል ማጥናትና ክንዱን ማጠንከር ጀመረ።" ብሎለታል።

አብርሃ ደቦጭ ጥናቱን ጨርሶ በራሱ መተማመን ሲጀምር የቤት እቃዎቹን በሙሉ ሸጠ። ሚስቱንም ደብረ ሊባኖስ ወስዶ አስቀመጠ።

 

የኢጣልያ ልዑል፣ ልጅ ስለወለደ በአዲስ አበባ በቤተ መንግስቱ ለልጅቱ መወለድ ምክንያት የደስታ ሥጦታ ለማድረግ መወሰኑን ሰማ። በዚያም ቦታ በግራዚያኒና በተከታዮቹ ላይ ቦምብ ለመጣል ወሰነ። ይህንኑ ውሳኔውንም ለሚያውቃቸው ኢትዮጵያውያን ነገረ። ለበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ፣ ለብላታ ዳዲ፣ ለቀኛዝማች ወልደ ዮሃንስ፣ ለደጃዝማች ወልደ አማኑዔልና ለሌሎቹም ጉዳዩን ነግሮ ጥሪው ከተደረገበት ቦታ እንዳይወጡ ኣስጠነቀቃቸው። እነኚያ ከአብርሃ ደቦጭ ማስጠንቀቂያ የተነገራቸው ሰዎች አብርሃ ደቦጭን እንደሰላይ ቆጥረው "ዞር በል ወዲያ" አሉት እንጂ ሃሳቡን አልተቀበሉትም።

የካቲት ፲፪(12) ቀን ፲፱፻፳፱(1929) ዓ.ም. አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም በዓሉ ከሚደረግበት ቦታ ቀደም ብለው ደረሱ። ከበዓሉ ቦታ ከመሄዳቸው በፊት አብርሃ ደቦጭ ቤት ውስጥ ሳንቃው ወለል ላይ የኢጣልያን ባንዲራ አንጥፈው ዙሪያውን በሚስማር መትተው ነበር የወጡት።

 

ሁለቱም በኪሶቻቸው ቦምብ ይዘዋል። ማርሻል ግራዚያኒ ለተሰበሰበው የአዲስ አበባ ህዝብ ንግግር ሲያደርግ የያዙትን ቦምብ ወረወሩበት። አምልጠውም ከግቢው ውስጥ ወጡ። አምልጠው ከወጡ በኋላ ከአርበኛው ከራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄደው ተደባለቁ። ለራስ አበበም ምን አድርገው እንደመጡ ኣጫወቷቸው። ጥቂት ጊዜ ከራስ አበበ ዘንድ ቆይተው ወደ ሱዳን ለመሻገር መፈለጋቸውን ነግረው አስፈቀዱ። የሱዳን ጉዟቸውን ጀምረው ሱዳን ሊገቡ ሲሉ ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
9095 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us