“ዘለዓለማዊት ነፃና አንድ ኢትዮጵያ”

Wednesday, 23 March 2016 12:09

 

በጥበቡ በለጠ

 

ይህ ፅሁፍ የታላቁ ደራሲ፤ አርበኛ እና ዲኘሎማት፤ የክቡር ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ነው። ፅሁፉን ያዘጋጁት በእድሜያቸው የመጨረሻው ዘመን አካባቢ ነው። ስለዚህ እኔ በበኩሌ እንደ ኑዛዜ የማየው ፅሁፍ ነው። ምክንያቱም በፅሁፋቸው ውስጥ ምሬት አለ፤ ታሪክ አለ፤ ሀሣብ አለ፤ ርዕይ አለ፤ አደራ አለ። የፅሁፉ ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ ነች። የኢትዮጵያን ውጣ ውረድ ያወጉናል። ባለማወቅም ሆነ በማወቅ የሰራነው ጥፋት ኢትዮጵያን እንዴት እንደጐዳት ሀዲስ አለማየሁ በውብ ብዕራቸው ያወጉናል።

 

ይህን ፅሁፍ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ራሣቸው ናቸው የሰጡኝ። ጊዜው 1994 ዓ.ም ነው። ፅሁፉ 15 ገፆች ያሉት በድሮ ታይኘ የተፃፈ ነው። የሰጡኝም ጠይቄያቸው ነው። ጥያቄዬን ያቀረብኩት በወቅቱ እናዘጋጀው ለነበረው አዲስ ዜና ጋዜጣ ላይ የሚወጣ መጣጥፍ ካላቸው እንዲሰጡኝ ነበር። የድርጅታችሁን ሚዛን የሚደፋ ከሆነ ይህን ፅሁፍ ተጠቀሙበት ብለው ሰጡኝ። እቢሮዬ መጥቼ ሣነበው የታላቁ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ የተጠራቀመ እውቀት፤ ትዝብት፤ ቁጭት፤ ምሬት ወዘተ አለበት። አፃፃፉም ውብ ነው።

 

ይህ ፅሁፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ይገኛል። ሀዲስ ይህችን አለም በሞት ከተለዩ በኃላ የፅሁፍ ቅርሶቻቸው ለዩኒቨርሲቲው ሲሰጥ አብሮ የተሰጠ ነው። እናም የሟችን ድርሣን ይዞ መቀመጥ ሀጥያት ነው ብዬ እነሆ ዛሬም ከሀዲስ አለማየሁ ጥልቅ ብዕር ጋር አብራችሁ እንድትቆዩ እጋብዛችኋለው። ኑዛዜው ከእጄ ላይ እንዲወጣልኝ እነሆ እላችኋለው፡-

 

1.ዘለዓለማዊት ነፃና አንድ ኢትዮጵያ

ከሀዲስ ዓለማየሁ

ኢትዮጵያ ጥንታዊት ናት። ኢትዮጵያ፤ ጠላቶችዋና የነሱን ስብከት ተቀብለው ለጊዜያዊና ለግላዊ ጥቅም መሣሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፤ ከመቶ አመት ወዲህ የተፈጠረች አይደለችም። ኢትዮጵያ፤ ከብዙ ሺህ አመታት ጀምራ፤ ስመ ጥር ከነበሩት ቀደምት ሀገሮች መካከል አንድዋ ናት።

ይሕም፣ በጥንታዊያን አክሱም ነገስታት ጊዜ፣ እዚያው አክሱም ላይ ተሰርተው ዛሬ ካሉት ሀውልቶች፣ በዚያው ግዜ የአክሱሞች የወደብ ከተማ በነበረችው በአዲሷ በየሀ፣ በሀውልቱና በሌሎች የታሪክ ቦታዎች ከተገኙት ቅርሶች የሚታይ ነው። እንዲሁም በኢትዮጵያ ነገስታት ዜና መዋዕልና በአድባራቱም፣ በገዳማቱም መዛግብት ብቻ ሣይሆን፣ በኦሪት መፃሕፍትና፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ አንድ ሺህ አመታት አካባቢ በነበሩት የጥንታዊት ግሪክ የታሪክ፣ የቅኔ ደራሲያን ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ከዚህም ሌላ፣ ኢትዮጵያ፣ የራሳቸውን ፊደል ቀርፀው፣ በራሣቸው ቋንቋ በየጊዜው የሆነውን እና የተደረገውን ለተከታታይ ትውልድ በፅሁፍ እንዲተላለፍ ለማድረግ ከቻሉት ጥቂት ጥንታዊያን አገሮች አንድዋ መሆንዋ በየጊዜው በስልጣኔ ቀደምት ከነበሩት አገሮቸ መሀከል አንድዋ እንጂ አሁን ከመቶ አመት ወዲህ የተፈጠረች ላለመሆንዋ ምስክር ነው። እነዲያውም በግሪኮች የሥልጣኔ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ፣ እጅግ ስመ ጥር የነበረች ከመሆንዋ የተነሣ፣ በአፍሪካ፣ ከግብፅ በላይ ላለውና ከዚያም አልፎ እስከ ሕንድ ድረስ ላለው ጥቁር ሕዝብ ሁሌ መጠሪያ የነበረች አገር ናት።

2. ኢትዮጵያ የቅኝ አገሮች ገዢ አይደለችም

ኢትዮጵያ፣ ልዩ ልዩ ጐሣ፣ ልዩ ልዩ ዘር፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ልዩ ልዩ እምነትና ባሕል ያላቸው ብሔረሰቦች ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር ናት። ብሔረሰቦች፣ ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ፣ በየጊዜው የገቡት ሴማውያንና እንዲሁም ከደቡብ የገቡት ካማውያን፣ ቀድመው በአገሪቱ ውስጥ በየክፍሉ ይኖሩ ከነበሩት ካማውያን ጋር እየተዋለዱና እየተዛመዱ የሚኖሩ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ፣ መጀመሪያ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ከየአቅጣጫው ሲመጡ በእንግድነት ተቀብላ፣ ኃላ ባለቤት አድርጋ የኖረች አገር ናት እንጂ፣ ጠላቶችዋ እንደሚያወሩትና፣ በዚያ ወሬ ለመነገድ የሚፈልጉ ሰዎች እንደሚለት፣ የቅኝ አገሮች ገዥ አይደለችም። እርግጥ፣ በቱርኮችና በአረቦች እርዳታ በተደረገው የግራኝ ወረራ ጊዜ፣ አፄ ልብነድንግል እና ልጃቸው አፄ ገላውዲዮስ ከሞቱ በኃላ፣ ማዕከላዊ መንግሥት እየተዳከመ በመሔዱ፣ አገሪቱ ተከፋፍላ፣ በየክፍሉ ባለቤቶች ወይም መሣፍንት ስትገዛ ቆይታ ነበር። ከዚያ፣ መጀመሪያ አፄ ቴዎድሮስ፣ ቀጥለው አፄ ዮሐንስ፣ ከዚያም አፄ ምኒልክ ከኒያ የተለያዩ ክፍሎች፣ የፈቀዱትን በሰላም፣ ያልፈቀዱትን በጦርነት እንገደና እንደ ጥንቱ አንድ እንዲሆኑ አድርገዋል። ታዲያ ይህ በምንም መንገድ “የቅኝ አገር ገዢ” የሚያሰኝ አይደለም።

3. ኢትዮጵያ የነፃነት አምባ

ከዚህ በላይ የተመለከቱት ብሔረሰቦች እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ፣ በየክፍላቸው እንደየባሕላቸው፣ በንጉሶች፣ በአሚሮች፣ በሱልጣኖች ወዘተ እየተዳደሩና ሁሉም ባጠቃላይ፣ በማእከላዊ መንግሥት መሪ፣ “ንጉሰ ነገሥት” ወይም የነገሥታት ንጉሥ፤ እየተባለ ስያሜ የነበረውም በዚህም ምክንያት ነበር። የውጭ ጠላት ኢትዮጵያን ለማጥቃት በመጣ ጊዜ፣ ንጉሠ ነገስቱ የክተት አዋጅ ሲያውጁ እኒያ የየክፍሉ ነገሥታት/ንጉሥ፣ አሚር፣ ሱልጣን፣ ወዘተ… ጦራቸውን እያስከተቱ በንጉሠ ነገስቱ አስተባባሪነትና መሪነት ጠላትን ድል እየመቱ ከሙሉ አፍሪካ የኢትዮጵያ ነፃነት ብቻ ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር አድርገዋል። እነዚያ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች በማዕከላዊው መንግሥት መሪ በንጉሠ ነገሥቱ አስተባባሪነት ኃይላቸውን በአንድነት አስተባብረው የጋራ ጠላታቸውን ድል እየመቱ ባይመልሱ ኖሮ፣ በየጐሣቸው ተከፋፍለው ይኖሩ የነበሩትን ሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች አውሮፓውያን ቅኝ ግዛት እንዳደረጓቸው ሁሉ እነሱንም ነጻነታቸውን ገፍፈው ቅኝ ግዛት /ኮሎኒ/ ማድረጋቸው አይቀርም ነበር።

 

የአውሮፓ መንግሥት ከኢትዮጵያ በቀር አፍሪካን በሙሉ ተከፋፍለው፣ ሕዝቡን የእነሱ ተገዥ ባደረጉበት ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ኃይላቸውን በማስተባበር ለረጅም ጊዜ አስከብረውት የኖረው ነፃነት፣ ለራሣቸው ብቻ ሣይሆን፣ በጠቅላላው ለአፍሪካ ሕዝብ እና ከዚያም አልፎ፣ ለጥቁር ዘር ሁሉ መኩሪያ እንደነበር፣ ፋሽስት ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ፣ የአፍሪካ መሪዎች ለምሣሌ የጋናው ክዋሜ ንክሩማህ እንዲሁም ጆርጅ ኮድሞር፣ የኬኒያው ጆሞ ኬኒያታና ሌሎችም፣ በለንደን ተሰባስበው በጊዜው ለነበረው የአለም ማሕበር ጩኸታቸውን እና ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ በአሜሪካ እና በካሪቢያን አገሮች የሚኖሩት ጥቁሮች በገንዘብና በሰው ኢትዮጵያን የሚረዱበት ማሕበር አቋቁመው ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፣ በሕዝቦች ላይ የባርነት ቀንበር ለመጫን የመጡትን ወራሪዎች፣ ክንዳቸውን አስተባብረው እየመቱ ለረጅም ጊዜ ጠብቀው ያቆዩትን ነፃነት፣ ከራሣቸው አልፎ፣ በተለይ ለአፍሪካ ሕዝቦችና በጠቅላላው ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ተስፋና መኩሪያ መሆኑ የታወቀ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ማሕበር ለአፍሪካ አህጉር የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለማቋቋም ሲወስን፣ ዋና መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን መወሰኑ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት፣ የአፍሪካ የነጻነት ፋና ሣይጠፋባት የኖረች አገር መሆንዋን በመመልከት ለዚያ ክብር ያደረጉት መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት ማሕበርና በአፍሪካ የአንድነት ድርጅት ስብሰባ ተካፋይ የነበሩ የኢትዮጵያ መላክተኞች ይናገራሉ። ይህም ለኢትዮጵያ የተሰጠ ክብር የብሔሮቿ የረዥም ጊዜ የሕብረት ትግል ያስገኘው ነው።

 

እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ድረስ፣ ኢትዮጵያ በነፃነትዋ እና በአንድነትዋ ላይ ከቅርብ ጐረቤትና ከሩቅ ጠላት በቀጥታም ከውስጥ የተገዙ ቅጥረኞች በማስነሣትም ይሰነዘርባት  የነበረውን ጥቃት ለመቋቋም በነበራት ያላቋረጠ ትግል ምክንያት በፖለቲካም ሆነ፣ በኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ ልማት ወደፊት ሣትራመድ መቆየትዋ የማይካድ እውነት ነው። ለዚህ አይነተኛው ምክንያት ሠላም ማጣት ነው። በየጐሣቸው ተለያይተው ይኖሩ የነበሩትን ሌሎች የአፍሪካ ሕዝቦች በቀላሉ ቅኝ ግዛቶቻቸው ያደረጉ የአውሮፓ መንግሥታት፣ የብሔረሰቦቿን የተባበረ ኃይል በጦርነት አሸንፎ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ማድረግ የማይቻል መሆኑን ስለ ተረዱና መቀናናትም በመሐከላቸው ስለነበር የውስጥ ብጥብጥ በመፍጠር ስትደክም እና ስትወድቅ ለመከፋፈል ይዶለትባት ነበር። ለዚህ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን፣ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1906 ዓ.ም ለንደን ላይ፣ ኢትዮጵያን በካርታ ተከፋፍለው የተፈራረሙት ውል አንድ ምሣሌ ነው። ይህ ስምምነት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ጦርነት የወደቀ እንደሆነ፣ በኤርትራ እና በሱማሌ አጠገብ ያሉ አገሮች ለኢጣሊያ እንዲሆኑ፣ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ባለው የባቡር መንገድ አጠገብና ከባቡሩ መንገድ ምዕራብ ያሉት አገሮች ለፈረንሣይ እንዲሆኑ፣ በጌምድር፣ አባይ ያሉበት ጐጃምና ሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ለእንግሊዝ እንዲሆኑ፣ በዚያ ላይ ኢጣሊያ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኤርትራ እስከ ሱማሌ የባቡር መስመር ለመዘርጋት መብት እንዲኖራትና ባቡሩ በሚያልፍበት አካባቢ ያለው መሬት የስዋ እንዲሆን ነበር።

 

እኒያ ሦስት መንግሥታቶች፣ እንዲያ ያለ ስምምነት ከተፈራረሙ በኃላ፣ የኢትዮጵያን ከውጪው አለም ጋር መገናኛ እየተቆጣጠሩና፣ በውስጥ ብጥብጥ የሚነሣባትን ዘዴ እየፈጠሩ፣ የምትወድቅበትን ጊዜ ይጠብቁ ነበር። ስለዚህ አውሮፓውያን አፍሪካን ቅኝ ግዛት ለማድረግ ከተነሱበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ፣ ኢትዮጵያ የነፃነት ሕይወትዋን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ የቆመች ስለነበረች በፖለቲካ ኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት ወደፊት ልትራመድ አለመቻልዋ አያስገርምም። ነገር ግን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሌሎች ምሁራንም ከውጭ ትምህርታቸውን እየጨረሱ የሚመለሱትም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት ኃላ ቀር ለመሆንዋ ሙሉ በሙሉ ተወቃሹ መንግሥት መሆኑን አምነው ይነቀፋና የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ጀመሩ። በሁዋላ ያ የነቀፋና የተቃውሞ ድምፅ ይፋ እየሆነ ሄደ። በ1966 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ፣ ወታደሩ ተቃውሞውን በመደገፍ አፄ ኃይለሥላሴን አውርዶ ራሱን “ደርግ” ብሎ ሰየመና ሥልጣን ያዘ።

4. ኢትዮጵያ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት

አፄ ኃይለሥላሴ ሰው እንደመሆናቸው ከስህተትና ከጉድለት ሁሉ ነፃ የሆኑ ሰው ነበሩ ለማለት አይቻልም። በዘመነ መንግሥታቸው በጐም ክፉም ስራዎች ሰርተዋል። ነገር ግን የአፄ ኃይለሥላሴን ታሪክ እዚህ ለመፃፍ ቦታቸው ስላልሆነ እሱን ለታሪክ ፀሐፊዎች ትቶ ኢትዮጵያ በጊዜው ከምትገኝበት ሁኔታ ጋር ስለተዛመደች ብቻ ባጭር ማመልከት አስፈላጊ ይሆናል።

እስቲ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ስለተሠሩት መልካም ሥራዎች ከማመልከት በፊት በብዙ ተመልካች አስተያየት አይነተኛ ስህተቶችና ጉድለቶች ከተባሉት ለምሣሌ ያክል አንድ ወስደን እንመልከት፡-

ሀ. ስህተት

አፄ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ፈረንጆች በደረሱበት የሥልጣኔ ደረጃ አፋጥኖ ለማድረስ ከመቸኮላቸው የተነሣ ይሁን ወይም ከዕውቀት ማነስ ባንድ አገር ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገሪያ የሚሆነው የታሪክ፣ የባሕል፣ የኑሮ ስልትና እነሱን የመሣሰለው ያገሩ መለያ የሆነው ሁሉ ሳይሰናዳና ያን የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ሣይኖሩ የፈረንጅ ት/ቤቶች እየተከፈቱ ወጣቶች ገብተው  እዚው ያገኙትን ብቻ እንዲማሩ መደረጉ ስህተት ነበር። በኒያ የፈረንጅ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሁሉ የተማሩትን አምነው ተቀብለው የፈረንጅ ያልሆነውን ሁሉ የሚያስንቅና የሚያስጠላ ስለነበር በፈረንጅ ትምህርት ቤቶች የተማሩት ሁሉ የተማሩትን አምነው ተቀብለው የፈረንጅ የሆነውን ሁሉ የሚያደንቁና የሚወዱ፣ ስለ ሀገራቸው ከፈረንጆች ከተማሩት ክፉ በቀር የሚያውቁት መልካም ስላልነበር የሀገራቸው የሆነውን ሁሉ የሚንቁና የማይወዱ ሆኑ። “ስለዚህ በ1966 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቀስቅሰው የአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት እንዲወድቅና የወታደሮች ደርግ ሥልጣን እንዲይዝ ካደረጉት አይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ይህ የተማሪዎች አገራቸውን አለማወቅ ነው” ማለት ይቻላል።

ለ. ጉድለት

ኢትዮጵያን አሁን በምትገኝበት ሁኔታ እንድትደርስ ካደረጉዋት የአፄ ኃይለሥላሴ አይነተኛ ጉድለት አንዱ ለሥልጣናቸው እጅግ ቀናተኛ የነበሩ በመሆናቸው ነው።

ከሳቸው በቀር ለኢትዮጵያ ደህንነት በተናጠል ይሁን ወይም በድርጅት መልክ መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ እንዲያ ያሉትን ሰዎች በማደፋፈርና በማበረታታት ፈንታ ለሥልጣናቸው ተካፋዮች መሆን የሚፈልጉ ወይም ሥልጣናቸውን የሚቀሙዋቸው መስለው እየታዩዋቸው እንዲያውም ጥብቅ ክትትል እንዲደረግባቸው ያደርጉ ነበር። ስለዚህ እሳቸው ሲያልፉ ወይም በእርጅና ምክንያት ማሰብና መስራት ሲያቅታቸው የጀመሩትን መልካም ሥራ በአዲስ ኃይል የሚቀጥል የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮ ኘሮግራሙን ሕዝብ ያወቀለት የፖለቲካ ድርጅት በዘመነ መንግሥታቸው ስላልነበረ ደክመው ሲሸነፉ የሥልጣናቸው ዕድሜ ለማራዘም ያደራጁት የወታደር ደርግ ሥልጣናቸውን ቀምቶ ያዘ።

እዚህ በተመለከቱትና በሌሎች አነስተኛ ስህተቶችና ጉድለቶች አንፃር በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለኢትዮጵያ የተሰራው መልካም ሥራ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባና የሚናቅ ሣይሆን የሚደነቅ ነው ለማለት ይቻላል።

እንደ እውነቱ ከሆነ “ዘመናዊት ኢትዮጵያን” የምትባለው ማለትም “በዘመነ መሳፍንት” ከተፈፀመ በኃላ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የወታደር ደርግ የመንግሥቱን ሥልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ባገር ውስጥ ይሁን በአለም አቀፍ አቁዋምዋ ባፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በደረሰችበት ከፍተኛ ደረጃ ደርሳ አታውቅም።

 

ካፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ባገር ውስጥ ባፄ ምኒልክ ጊዜ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ከተዘረጋው የባቡር መንገድ በቀር ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ የምድር የባሕር ወይም ያየር መገናኛ አልነበረም። ከቤተ-ክህነት ትምህርት ቤት በቀር የዘመናዊ ትምህርትና የጤና ጥበቃ አገልግሎት አልነበረም። በበጀት የሚተዳደሩ አገር አስተዳዳሪዎችና ዳኞች በበጀት የሚተዳደር ብሔራዊ የጦር ሠራዊት አልነበሩም። ሁሌም በኢትዮጵያ ሕዝብ ትከሻ ላይ ተጭነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ደሞዝ አድርገው ነበር የሚኖሩ። አገር አስተዳዳሪዎች ዳኞችና የጦር ሠራዊት ከሕዝቡ ትከሻ ወርደው ወይም ሕዝቡን ደሞዝ አድርገው መኖራቸው ቀርቶ በበጀት እንዲተዳደሩና ሕዝቡ ባመት የተወሰነ ግብር ብቻ ለመንግሥት እንዲከፍል የተደረገው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር። ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ተከፍተው በሙያው የተመረቁ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ለሕዝባቸው አገልግሎት ለመስጠት እንዲበቁ የተደረገው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት ነበር። የሚበቃውን ያክል ባይሆኑም በሙሉ ኢትዮጵያ ሀኪም ቤቶች የጤና ጣቢዎችና ክሊኒኮች ተቋቁመው ለሕዝቡ የጤና ጥበቃ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው ባፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት ነበር። የምድር የባሕርና ያየር መገናኛዎች ተፈጥረው ባገር ውስጥ የኢትዮጵያን ክፍላተ ሀገር እርስ በርሣቸው በውጭ ኢትዮጵያን ከብዙ የአለም ክፍሎች ጋር ማገናኘት የተቻለው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር።

 

የአውሮፖ መንግሥታት አፍሪካን ቅኝ ግዛት ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መውጪያና መግቢያ የሆነው የባሕር በርዋ ተዘግቶባት ኤርትራ ካካልዋ ተገንጥላ ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ባንዱዋ በኢጣሊያ ተይዛባት ከኖረች በሁዋላ የባሕር በርዋ ተከፍቶ እንደገና ከውጭው አለም ጋር ለመገናኘትና ኤርትራም እንደገና ወደ እናት አገርዋ ተመልሣ አንድ ለመሆን የበቃችው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር።

 

የተባበሩት መንግሥታት ማሕበርና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስሪያ ቤቶቻቸውን አዲስ አበባ አድርገው ኢትዮጵያን ለአፍሪካ አሕጉር የፖለቲካና የዲኘሎማሲ ማዕከል እንድትሆን የተደረገው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር። የንግድ፣ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪ፣ ባንኮችና የመድን ድርጅቶች ተቋቁመው የውጭ ባለካፒታሎች ገንዘባቸውን እየያዙ ገብተው ሥራ ተስፋፍቶ ሲከፈትና በየስራዉ ዘርፍ የተማሩ ብዙ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ሀብት ባለቤት ሊሆኑ የበቁ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር።

 

ሕገ-መንግሥት ተመስርቶ በሕዝብ የሚመረጡ አባሎች የሚገኙበት ሕግ አውጪ ፓርላሜንት ተቋቁሞ የፍርድና የአስተዳደር ተቋሞች በሕገ መንግሥት የተመደበውንና ፓርላሜንት ያወጣውን ሕግ ተከትለው መስራት የተጀመረ  በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር። ከዚህ ሁሉ ሌላ የኤርትራ ፌዴሬሽን ከፈረሰ በሁዋላ የኤርትራ  ነፃ አውጪ ድርጅት የተባለው ቡድን በሰሜን ኤርትርያ ንቅናቄውን እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ በሙሉ ሰላም የሰፈነባትና ሕዝብዋም በሥራ የተሠማራባት አገር ሆና ነበር።

 

እርግጥ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይህ ሁሉ ተደርጐ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ እድገትዋ ከአውሮፓና ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር መተካከል ይቅርና አልተቀራረበችም። ገና ሁዋላ ቀር ከሚባሉት ሀገሮች አንድዋ ነበረች። ነገር ግን ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ጥንታዊት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ ያላወቁ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ለእነሱ መሣሪያ የሆኑት ወታደሮች ያን በሁሉም በኩል የተደረገውን ደህና እርምጃ፣ የአውሮፓና ሌሎች ያደጉ አገሮች ከደረሱበት ከፍተኛ ደረጃ ጋር ሲያመዛዝኑት በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ስላገኙትና ስላላጠገባቸው ከምንም አልቆጠሩትም። ስለዚህ ኢትዮጵያ በረዥም የነፃነት ታሪክዋ ነፃነትዋንና አንድነትዋን አስከብራ ለመኖር ከውጭ ጠላቶችና በውጭ ጠላቶች ከተገዙ ከውስጥ ቅጥረኞች ጋር የነበረባት ያላቋረጠ ጦርነት ላስከተለባት ሁዋላ ቀርነት በዩኒቨርሲቲ ምሁራንና መሣሪያዎች በሆኑዋቸው ወታደሮች ፊት ዓይነተኛ ተጠያቂው አፄ ኃይለሥላሴ ሆነው ተገኙ። ለኢትዮጵያ ካርባ ዓመት ባልበለጠ የሥልጣን እድሜያቸው ብዙ በጐ ብዙ መልካም ሥራ እንዲሰራ አድርገው፣ በሁሉም በኩል ጥንታዊት የነበረችውን ዘመናዊት እንድትሆን ደረጉትን አፄ ኃይለሥላሴን፣ እንደ ክፉ አድራጊ፤ ሁዋላ ቀርነታቸውን እንዲያዩ አስተምረው አይናቸውን የከፈቱላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና መሳሪያዎቻቸውን ወታደሮች፤ ላልበደሉት የተጠራቀመ እዳ ከፋይ አድርገው ለእሣቸው የማይገባ ውድቀትና ሞት ሲደርስባቸው የኖሩትን አገረ ገዥዎች ዳኞችና መሰሪውን ወታደር ከትከሻው አውርደው ባመት የተወሰነ ቀላል ግብር ብቻ ለመንግሥት እንዲከፍልና ለተረፈ ሀብቱና ጉልበቱ ባለቤት ሆኖ በመጠኑ ኑሮውን እንዲያሻሽል ያደረጉለት የባላገር ሕዝብ እንኩዋ፣ እንዲዘፍን ሲታዘዝ፣ “እምቢ ፣አሻፈረኝ!” ብሎ በማልቀስ ፈንታ፣ መዝፈኑ የሚያስገርምም የሚያሣዝንም ነው።

5. ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ

ወታደሩ የመንግሥቱን ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ አሥራ ሰባት አመት ሙሉ በኢትዮጵያ የደረሰው ችግርና መከራ በረዥም ታሪክዋ ደርሶ የማያውቅ እጅግ መራራ ነው። በዚያ አስራ ሰባት አመት በኢትዮጵያዊያን መሀከል የተነሣው የእርስ በርስ ጦርነት የብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወትና ንብረት ያጠፋ ከመሆኑ ሌላ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ወጣቶችን የእድሜ ልክ አካለ ስንኩላን አድርጐ አስቀርቷል። በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ጥግ ፍለጋ ወደ ባዕዳን ሀገሮች እንዲሰሰዱ አድርጓል። የተረፉትን ኢትዮጵያዊያን በድህነት አዘቅት ውስጥ ጥሎ በጠቅላላው አገሪቱን ለረሃብና ለከፋ ችግር ምሳሌ ሆና የምትጠቀስ አድርጓታል። ይህ የርስ በርስ ጦርነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያጠፋውን አጥፍቶ የተረፈውን ከዚህ በላይ በተመለከተው ጣእር ውስጥ የሚኖር ከመሆኑ አልፎ አሁን ከዚህ ሁሉ የባሰ ደግሞ ኢትዮጵያን ራሱዋን አንድነትዋና ህልውናዋ እንደተጠበቀ የሚኖር መሆን አለመሆኑን በሚያጠራጥር ደረጃ አድርሷታል።

 

ያዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ወታደሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ልማት አፋጥኖ ለማሣደግ ብዙ ሺ አመታት የሀገሪቱን ነፃነትና አንድነት ጠብቆ ያኖረውን የርስ በርስ ጦርነት ጀመረ። የዚያ የርስ በርስ ጦርነት ተፈላሚዎች ልዩ ልዩ እንደመሆናቸው ምክንያቶቹም ልዩ ልዩ ሆነው ይገኛሉ። ከነዚህ ምክንያቶቹ አንዱ፣ “ርእዩተ ዓለም” /አይዲዮሎጂ/ ሁለተኛው፣  “የስልጣን ሽሚያ” /የስልጣን ሽኩቻ/ ሦስተኛው፣ “የብሔሮች ጉዳይ” /ብሔሮች የራሳቸው እድል በራሳቸው የመወሰን መብት/ የሚሉት ናቸው።

ሀ. ርዕዮተ ዓለም

የወታደር ደርግና ምሁራን አማካሪዎች ሥልጣን እንደያዙ የሚመሩበት “ርዕዮተ ዓለም” መጀመሪያ፡- “የኢትዮጵያ ሕብረሰባዊነት” ሁዋላ እሱን ትተው “ኮሚኒዝም ለሕዝብ መብትና እኩልነት የቆየ ርአዩት ዓለም ነው” እየተባለ ይሰበክለት የነበረ ከመሆኑም ሌላ መስኮብና ቻይናን ባጭር ጊዜ ከእርሻ አምራችነት ወደ ፋብሪካ አምራችነት ያራመደ ነው  ይባል ስለነበር ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡት ሀገሮችና እንዲሁም በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት ወደ ሁዋላ የቀሩት አገሮች መሪዎች የሚበዙት አገራቸውን አፋጥኖ ለማልማት የሚያስችላቸው ኮሚኒዝም መሆኑን አምነው መቀበላቸውን በማየት የኛ ምሁራንና የሱን ሃሣብ ደግፈው የቀድሞውን መንግሥት አውርደው ሥልጣን የያዙት ወታደሮች ኮሚኒዝም መመሪያቸው ያደረጉ በዚሁ ቀና መንፈሰ ሊሆን ይችላል።

 

ነገር ግን እንኳንስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ወታደሮች ከውጭ ሀገር ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየጨረሱ ተመልሰው ለደርግ አማካሪዎች ከሆኑት የኢትዮጵያ ምሁራንም በጣም የሚበዙት ስለ ኮሚኒዝም መጽሐፍ ካነበቡትና በቃል ከሰሙት ኘሮፓጋንዳ በቀር በመስኮብና በቻይና ዘለግ ላለ ጊዜ ኖረው ሕዝቦቻቸውን የሚኖሩበትን ሁኔታ የተመለከቱ አልነበሩም። ስለዚህ ኮሚኒዝም ከመጻህፍና ከቃል ኘሮፓጋንዳ አልፎ በገቢር ሲተረጐም ምን እንደሚያስከትል ሳያውቁ አገራቸውን በጨለማ መንገድ መርተው በከፋ ችግር ውስጥ መጣላቸው ብርቱ በደለኞች የሚያደርጋቸው ነው። ነገር ግን እነሱ ለሰሩት በደል አሥራ ሰባት አመት ሙሉ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

 

በመሠረቱ ኮሚኒዝምም ሆነ ወይም ሌላ ርዕዮተ ዓለም ካንድ አገር ሕዝብ እምነት ባሕልና ልማት ደረጃ ጋር የማይስማማ በመሆኑ ሕዝቡ የማይቀበለው ቢሆንና በሀይል ቢጭኑበት አገርን ወደፊት በማራመድ ፈንታ ወደ ሁዋላ መጐተትን በሀብት ፈንታ ድህነትን፣ በሰላም ፈንታ ሁከትን አስከትሎ መጨረሻ ወደ ታደቀደው ግብ ሊያደርስ የማይችል መሆኑ ባለንበት ጊዜ እየታየ ነው።

(ይቀጥላል)n

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
11694 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us