“ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ”

Wednesday, 30 March 2016 11:57

 

ክፍል ሁለት

በጥበቡ በለጠ

ታላቁ ደራሲ ዲፕሎማት እና አርበኛ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ የዛሬ 14 አመታት ግድም ዘለዓለማዊት ነፃና አንድ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የፃፉትን ፅሁፍ ማቅረባችን ይታወሣል። በዚያ ፅሁፍ ውስጥ ኢትዮጵያ መንግስት ከመሰረተችበት ዘመን አንስቶ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረሰ ያሣለፈቻቸውን ውጣ ውረዶች ከሚጣፍጠው ብዕራቸው አንብበናል። ዛሬ ደግሞ የዚያው ፅሁፍ ቀጣይ የሆነው መጣጥፋቸው ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ በሁዋላ ምን እንደገጠማት ያሳዩናል። ከአፄ ኃይለሥላሴ በኋላ ደርግ እና ኢሕአዴግ መጥተዋል። ደራሲ ሀዲስ እነዚህን ስርአቶች እንዴት ተመለከቷቸው? ምን ታዘቡ?  ምን ተሰማቸው? ጽሁፉን ስናነብ ብዙ ጉዳዮችን እናገኛለን።

 

ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአለም አቀፍ ሕግ ያጠኑት ታላቁ ደራስያችን ሀዲስ ዓለማየሁ፤ ኢትዮጵያን በበርካታ ጉዳዮች አገልግለው ያለፉ የምን ግዜም ባለውለተኛ ናቸው። ተዝቆ በማያልቀው የዕውቀት የሥራ እና የእድሜ ተሞክሯቸው የታዘቡትን ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ በሁዋላ ምን እንደሆነች እንዲህ ፅፈዋል።

 

ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ

ከሀዲስ ዓለማየሁ

ወታደሩ የመንግሥቱን ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ አሥራ ሰባት አመት ሙሉ በኢትዮጵያ የደረሰው ችግርና መከራ በረዥም ታሪክዋ ደርሶ የማያውቅ እጅግ መራራ ነው። በዚያ አስራ ሰባት አመት በኢትዮጵያዊያን መሀከል የተነሣው የእርስ በርስ ጦርነት የብዙ ኢትዮጵዊያን ሕይወትና ንብረት ያጠፋ ከመሆኑ ሌላ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ወጣቶችን የእድሜ ልክ አካለ ስንኩላን አድርጐ አስቀርቷል። በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ጥግ ፍለጋ ወደ ባዕዳን ሀገሮች እንዲሰደዱ አድርጓል። የተረፉትን ኢትዮጵያዊያን በድህነት አዘቅት ውስጥ ጥሎ በጠቅላላው አገሪቱን ለረሃብና ለከፋ ችግር ምሳሌ ሆና የምትጠቀስ አድርጓታል። ይህ የርስ በርስ ጦርነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያጠፋውን አጥፍቶ የተረፈውን ከዚህ በላይ በተመለከተው ጣእር ውስጥ የሚኖር ከመሆኑ አልፎ አሁን ከዚህ ሁሉ የባሰ ደግሞ ኢትዮጵያን ራሱዋን አንድነትዋና ህልውናዋ እንደተጠበቅ የሚኖር መሆን አለመሆኑን በሚያጠራጥር ደረጃ አድርሷታል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ወታደሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ልማት አፋጥኖ ለማሣደግ ብዙ ሺ አመታት የሀገሪቱን ነፃነትና አንድነት ጠብቆ ያኖረውን የርስ በርስ ጦርነት ጀመረ። የዚያ የርስ በርስ ጦርነት ተፈላሚዎች ልዩ ልዩ እንደመሆናቸው ምክንያቶቹም ልዩ ልዩ ሆነው ይገኛሉ። ከነዚህ ምክንያቶቹ አንዱ፣ “ርእዮተ ዓለም” /አይዲዮሎጂ/ ሁለተኛው፣ “የስልጣን ሽሚያ” /የስልጣን ሽኩቻ/ ሦስተኛው፣ “የብሔሮች ጉዳይ” /ብሔሮች የራሳቸው እድል በራሳቸው የመወሰን መብት/ የሚሉት ናቸው።

 

ሀ. ርዕዮተ ዓለም

የወታደር ደርግና ምሁራን አማካሪዎች ሥልጣን እንደያዙ የሚመሩበት “ርዕዮተ ዓለም” መጀመሪያ፡- “የኢትዮጵያ ሕብረሰባዊነት” ሁዋላ እሱን ትተው “ኮሚኒዝም ለሕዝብ መብትና እኩልነት የቆየ ርእዮት ዓለም ነው” እየተባለ ይሰበክለት የነበረ ከመሆኑም ሌላ መስኮብና ቻይናን ባጭር ጊዜ ከእርሻ አምራችነት ወደ ፋብሪካ አምራችነት ያራመደ ነው  ይባል ስለነበር ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡት ሀገሮችና እንዲሁም በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት ወደ ሁዋላ የቀሩት አገሮች መሪዎች የሚበዙት አገራቸውን አፋጥኖ ለማልማት የሚያስችላቸው ኮሚኒዝም መሆኑን አምነው መቀበላቸውን በማየት የኛ ምሁራንና የሱን ሃሣብ ደግፈው የቀድሞውን መንግሥት አውርደው ሥልጣን የያዙት ወታደሮች ኮሚኒዝም መመሪያቸው ያደረጉ በዚሁ ቀና መንፈስ ሊሆን ይችላል።

 

ነገር ግን እንኳንስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ወታደሮች፤ ከውጭ ሀገር ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየጨረሱ ተመልሰው ለደርግ አማካሪዎች ከሆኑት የኢትዮጵያ ምሁራንም በጣም የሚበዙት ስለ ኮሚኒዝም መጽሐፍ ካነበቡትና በቃል ከሰሙት ኘሮፓጋንዳ በቀር በመስኮብና በቻይና ዘለግ ላለ ጊዜ ኖረው ሕዝቦቻቸውን የሚኖሩበትን ሁኔታ የተመለከቱ አልነበሩም። ስለዚህ ኮሚኒዝም ከመሃፍና ከቃል ኘሮፖጋንዳ አልፎ በገቢር ሲተረጐም ምን እንደሚያስከትል ሳያውቁ አገራቸውን በጨለማ መንገድ መርተው በከፋ ችግር ውስጥ መጣላቸው ብርቱ በደለኞች የሚያደርጋቸው ነው። ነገር ግን እነሱ ለሰሩት በደል አሥራ ሰባት አመት ሙሉ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

 

በመሠረቱ ኮሚኒዝምም ሆነ ወይም ሌላ ርዕዮተ ዓለም ካንድ አገር ሕዝብ እምነት ባሕልና ልማት ደረጃ ጋር የማይስማማ በመሆኑ ሕዝቡ የማይቀበለው ቢሆንና በሀይል ቢጭኑበት አገርን ወደፊት በማራመድ ፈንታ ወደ ሁዋላ መጐተትን፤ በሀብት ፈንታ ድህነትን፤ በሰላም ፈነታ ሁከትን አስከትሎ መጨረሻ ወደ ታቀደው ግብ ሊያደርስ የማይችል መሆኑ ባለንበት ጊዜ እየታየ ነው።

 

ለ. የሥልጣን ሽሚያ

ወታደሩ ራሱን ደርግ ብሎ ሰይሞ ስልጣን እንደያዘ፣ ከምሁራኑ ተከፋፍለው ከሱ ጋር ለመስራት ሲስማሙ ሌሎች፣ ወታደሩ ስልጣኑን ለሠላማዊው ክፍል/ለነሱ/ አስረክቦ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ጠየቁ። ነገር ግን ወታደሩ ሥልጣን የማይለቅ መሆኑን ስለታወቀና ምሁራኑንም በጥያቄያቸው ስለፀኑ፣ ይህ የሥልጣን ሽሚያ/ የስልጣን ሽኩቻ/ ባስነሣው የእርስ በርስ ጦርነት እጅግ የሚያሰቅቅ እልቂት ከደረሰ በሁዋላ፣ ወታደሩ አሸንፎ ስልጣኑን ሲያጠናክር፣ ምሁራኑ በሀገር ውስጥም፣ ወደ ውጭ ሀገርም ተበተኑ። ከዚያ፣ መጀመሪያ ደርጉን አስወግዶ የመንግሥቱን ሥልጣን ለመያዝ ከተነሱት ምሁራን መካከል ይብዛም ይነስ በቡድን በቡድን ተደራጅተው የእያንዳንዶቹ ቡድኖች አላማ፡- እነሱ እንደሚሉት ደርግን አስወግዶ ሥልጣን መያዝ ሲሆን፣ ሌሎች ቡድኖቸ አላማቸው “የብሔሮች ጉዳይ” የሚባለው መሆኑን ገለፁ።

 

ሐ. የብሔሮች ጉዳይ

“ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል እስከ መገንጠል ድረስ በራሣቸው የመወሰን መብት” የሚለው' ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣናቸው ከመውረዳቸው በፊት ጀምሮ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል፣ “ዘዬ” ሆኖ ሲነገር ይሰማ የነበረ ነው። እንዲህ ያለው ለአንድነትና ለሠላም ጠንቅ የሆነ ሀሣብ፣ በነፃ መንግሥታት ሕገ-መንግሥት የማይገኝ በመሆኑ፣ መሠረቱ ሲጠየቅ፣ ተማሪዎቹ “ሌኒን ብለዋል” ከማለት በቀር ሌላ ማስረጃ አያቀርቡም። ነገር ግን፣ የብሔረሰቦች የራስን እድል እስከ ነፃነት ድረስ በራስ የመወሰን መብት የታወቀ መሠረቱ ሌላ  ነው።

 

ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሁዋላ፣ ድል አድራጊዎች መንግሥታት፣ ሁለቱን የአለም ማሕበሮች/ሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታት ማሕበርን/ በየተራ አቋቁመው፣ ድል የተመቱትን መንግሥታት ቅኝ ግዛቶች፣ እኒያ በሁለት ማሕበሮች በሞግዚትነት እንዲጠየቁ አደረጉ። ማሕበሮቹ በፈንታቸው፣ ከአንዳንድ መንግሥታት ጋር ስምምነት እያደረጉ የሞግዚትነቱን ተግባር ለኒያ መንግሥታት ሲያስተላልፉ፣ በስምምነቱ ውስጥ ሞግዚት፣ አስተዳዳሪዎች፣ በሞግዚት ለሚያስተዳድሯቸው ብሔረሰቦች ሊያደርጉ የሚገባቸው ተዘርዝረዋል። በዚያ ዝርዝር ውስጥ፣ ከተመለከቱት ግዴታዎች አንዱ፣ ያለማምዱዋቸውና፣ ከዚያ በሁዋላ፣ ብሔረሰቦች በራሣቸው ምርጫ፣ ሙሉ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ሲጠየቁ እንዲሰጡዋቸው አስተዳዳሪዎች ግዴታ ገብተዋል።

 

ስለዚህ፣ “ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል በራሣቸው ለመወሰን መብት አላቸው” የሚባለው፣ መሠረቱ በዚህ እንደተመለከተው፣ ቅኝ ግዛት ለነበሩት ነው እንጂ፣ ለነፃ መንግሥታት ክፍለ አገሮች አይደለም። እንዲውም፣ የተባበሩት መንግሥታት ማሕበር ቻርተር፣ አንቀፅ 78፣ የሞግዚት አስተዳዳሪዎች በሞግዚትነት ለሚያስተዳድሯቸው ብሔረሰቦች ሊያደርጉ የሚገባቸውን ከዚህ በላይ እንደተመለከተው በዝርዝር ካስታወቀ በሁዋላ፣ “ይህ ከዚህ በላይ ስለ ቅኝ ግዛቶች የተባለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ማሕበር አባሎች ለሆኑ ነፃ መንግሥታት አገሮች አይሆንም” ይላል። ስለዚህ፣ “የነፃ መንግሥታት ክፍል የሆኑ ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል እስከ መገንጠል ድረስ በራሣቸው የመወሰን መብት አላቸው” የሚባለው፣ ሕጋዊ መሠረቱም፣ ተቀዳሚም የሌለው በመሆኑ፣ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባ አይደለም። እንዲሁም ከጥቅሙ እና ጉዳቱ ወገን ሲመለከቱት ኢትዮጵያንም ብሔረሰቦችንም ከመጉዳት በቀር፣ ማናቸውንም ስለማይጠቅም፣ በምንም መንገድ የሚቀበሉት አይደለም።

 

የብሔረሰቦች መገንጠል የሚያስከትለው

ከሁሉ በፊት በኢትዮጵያ የሚኖሩት ብሔረሰቦች ተለያይተው የራሣቸውን ነፃ መንግሥታት የሚያቋቁሙ ከሆኑ፣ በኢትዮጵያ ፈንታ፣ የኒያ ብሔረሰቦች ብዙ ትናንሽ መንግሥታቶች ይኖራሉ እንጂ “ኢትዮጵያ አትኖርም” ማለት ነው። በልዩ ልዩ ጊዜ ከየአቅጣጫው፣ መጀመሪያ በአንድነት ገብተው፣ በሁዋላ ከሀገሪቱ ነዋሪዎች ጋር ባለቤቶች ሆነው የኖሩት ብሔረሰቦች፣ በኢትዮጵያ ፈንታ ትናንሽ ነፃ መንግሥታቶቻቸውን ሲያቋቁሙ፣ እሱዋ መጐዳት ብቻ ሣይሆን ጭራሹኑ ትጠፋለች ማለት ነው። ግን እነሱም አይጠቀሙም። እኒያ ሃይላቸውን በማስተባበር በክፉ ጊዜ ከብርቱ ጠላቶች ጋር እየተጋደሉ የኢትዮጵያን ነፃነትና አንድነት አስከብረው፣ ለራሣቸው ብቻ ሣይሆን፣ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ መኩሪያ እንድትሆን አድርገው ያኖሩ ብሔረሰቦች፣ ዛሬ ያ ክፉ ቀን አልፎ ደህና ቀን በወጣበት ጊዜ፣ እሱዋ እንድትጠፋ ማድረጉ፣ እነሱንም የሚጐዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም።

 

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አብረው እስከኖሩ ድረስ ሀብታቸውንና ኃይላቸውን እያስተባበሩ የውጭን ጠላት አሸንፈው በነፃነት እንዲኖሩ እንዲሁም፣ የሀብትና የእውቀት ሀይላቸውን በማስተባበር አገራቸውን የጋራ አልምተው፣ ድህነትን እና ሁዋላ ቀርነትን ለማሸነፍና የምቾት ኑሮ ለመኖር ይችላሉ። የየራሣቸውን ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ያቋቋሙ እንደሆነ ግን፣ ሁሉም የተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ባለመሆናቸው፣ ድህነትንና ሁዋላ ቀርነትን ለየብቻ ታግለው አሸንፈው፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ኑሮ በኩል የሚገጥማቸውን ችግር ለመወጣት አይችሉም። ከዚህ ሌላ፣ ምናልባትም ከዚህ የከፋ ደግሞ፣ ልዩ ልዩ ጐረቤት ብሔረሰቦች ነፃ መንግሥታቸውን ሲያቋቁሙ የሚገጥማቸውን ችግር፣ የወሰን፣ በየውስጣቸው የሚኖሩ ትናንሽ ጐሣዎች፣ የወንዝ፣ ውሃ እና ሌሎች የሚያገናኙዋቸው ነገሮች የሚያስከትሉት መዘዝ ነው። በተለይ  የወሰን ጉዳይ በጐረቤት ሀገሮች መካከል የሚያስነሣው ጥል ወደ ጦርነት መርቶ የሚያስተላልቅና መጨረሻው ምን እንደሚሆን፣ አስቀድሞ መገመት የማይቻል፣ በጣም የሚያስፈራ ነው።

 

የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ለቀው፣ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃነታቸውን እንዳገኙ፣ የአፍሪካ መንግሥታት ያንድነት ድርጅት ሲያቋቁሙ፣ ምንም እንኳ የአውሮፖ ቅኝ ገዥ አፍሪካን ሲከፋፍሉ፣ ክፍያው የጐሣን መስመር የተከተለ ባይሆን፣ “ቅኝ ገዥዎች የተካለሉት የጐረቤት ሀገሮች ወሰን የፀና ይሆናል” የሚል መግለጫ በቻርተራቸው አግብተው የተፈራረሙ፣ የወሰን ጥል የሚያስከትለውን መዘዝ በመፍራት ነው። በሱማሌ እና በኢትዮጵያ መሀከል በወሰን ምክንያት በየጊዜው፣ የመጨረሻው ደርግ ሥልጣን እንደያዘ የተነሱት ብዙ ጦርነቶች፣ ከሁለቱም ወገን የብዙ ሰው ሕይወትና ብዙ ሃብት ከጠፋ በሁዋላ፣ ጦርነቶችን ያስነሣው የወሰን ችግር አሁንም ፍፃሜ ሣያገኝ እንደተንጠለጠለ ሆኖ፣ አንዱ ወይም ሌላው ወገን የተመቸ አጋጣሚ አግኝቶ እስኪያነሣ የሚጠብቅ ነው። ስለዚህ፣ በወሰን ምክንያት፣ በጐረቤት መንግሥታት፣ በተለይ አዲስ በሚቋቋሙ ትንንሽ መንግሥታት መሀከል የሚነሣ ጦርነት፣ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ኑሮ ማሻሻል ሊውል የሚገባውን ሀብት እየበላ፣ ከሁለቱ የሚዋጉ ወገኖች ሕዝቦች የሚጨርሰውን ከጨረሰ በሁዋላ፣ የተረፉትን በድህነት አዘቅት ውስጥ የሚጥል በመሆኑ፣ በጠቅላላ ችግሩ ሊወጡት የማይቻል፣ “ሲጠጉ ገደል” ነው።

 

ዛሬ፣ በሀብት፣ በሀይልና በስልጣኔ ለየራሣቸው ገናና ታሪክ ያላቸው ታላላቅ መንግሥታት በሊቃውንታቸው አስጠንተው፣ ለየብቻ ከመኖር፣ ባንድነት መኖር የሚጠቅም መሆኑን በማመን፣ አንድ ለመሆን በሚሠሩበት ጊዜ፣ አንድ አገር አፍርሶ ብዙ ትናንሽ የጐሣ መንግሥታት ለመፍጠር ማሠብ፣ እኒያን ትናንሽ መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚጐዳ እንጂ የሚጠቅም አለመሆኑን፣ አሁን እዚህ እንደተመለከተው፣ የአለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ጠበብት ያረጋገጡት ነው። ባገራችን፣ በብዙ “ስም” ለተሰየሙት ቡድኖች ግን፣ ለጊዜው የታያቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተለያይተው የየራሣቸው ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ቢያቋቁሙ፣ በእያንዳንዱ ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ውስጥ በሚኖረው ሕዝብ ላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግር ሣይሆን፣ ለነሱ ለጊዜው የታያቸው፣ የነፃነትን ስም ማግኘትና፣ በዚያ ስም የስልጣን ባለቤት መሆኑ፣ ነው። የብሔረሰቦችን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ከማሻሻሉ ወገን ሲታይ ግን፣ ምን ግዜም ቢሆን፣ ለየብቻ ተነጣጥሎ ከመስራት፣ ሀብትን፣ እውቀትንና ሌላ ሀይልን ሁሉ ባንድነት አስተባብሮ መስራቱ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑ የታወቀ ነው።

 

በብዙ “ስም” የተሰየሙትን ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ፈርሶ በሱ ፈንታ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የየራሣቸውን ነፃ መንግሥታት እንዲያቋቁሙ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ ለየብሔረሰቡ የነፃነትን የክብር ስም መስጠቱ፤ ሁለተኛው እነሱ እንደሚሉት ከብሔረሰቦች መሀከል ያማራው ክፍል ሌሎችን ጨቁኖ መኖሩ ናቸው። ነገር ግን፣ ነፃነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፣ ዛሬ እነዚህ ቡድኖች አግኝተው የሚሰጡት፣ አዲስ ሣይሆን፣ ባለፈው ረጅም ታሪካቸው ከጠላት ጋር እየታገሉ ይዘውት የኖሩት ነው። እርግጥ፣ አገሪቱ አንድነትዋንና ነፃነትዋን ለመጠበቅ በነበረባት ያላቋረጠ ትግል ምክንያት፣ ይህ ረዥም የነፃነት ሕይወት፣ አንድ ብሔረሰብ ከሌላው ሳይለይ፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞውና ሌሎችም ሁሌ፣ የድህነትና የኃላቀርነት ኑሮ እየኖሩ ያሣለፉት ነው።

በጤና ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በመገናኛ፣ ወይም በሌላ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት አማራው ከሌሎች ብሔረሰቦች የተሻለ፣ ወይም ሌሎች ብሔረሰቦች፣ ከአማራው የከፋ አገልግሎት አግኝተው አያውቁም። ስለዚህ በብዙ “ስም” የተሠየሙት ቡድኖች የሚሠጡዋቸው ምክንያቶች እውነት ካለመሆናቸው ሌላ፣ የብሔረሰቦች ነፃ መንግሥታት አቋቁሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚበቁ አይደሉም። ከብሔረሰቦች መካከል አንዱ ያየለ፣ ሌላው የበደለ አይደሉም እንጂ፣ መስለው ቢታዩ እንኳ፣ የሁሉም መብት በትክክል የሚጠበቅበትን መንገድ መሻት ነው እንጂ፣ ከነዚህ ብሔረሰቦች፣ ብዙዎችን በአንድነት እየተቀበለች አስተናግዳ፣ ሁዋላም ባለቤት አድርጋ የኖረችና፣ ብሔረሰቦችንም በፈንታቸው ኃይላቸውን አስተባብረው ከውጭ ጠላት ጋር እየታገሉ በነፃነት ያኖሩዋትን ታሪካዊ አገራቸውን አሁን ለማጥፋት መነሣት፣ ለዚህ አድራጐት ባለቤት በሆኑት ክፍሎች ላይ፣ በተከታታይ ትውልዶች የሚያስፈርድባቸው፣ እነሱም ሁዋላ የሚያስፀጽታቸው ይሆናል።

 

ደግሞ ከዚህ ሌላ ሊረሳ የማይገባው አቢይ ነገር፣  ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሴማውያንም፣ ሁዋላ ከደቡብ ከገቡት ካማውያንም፣ መጀመሪያ ሲገቡ አገሪቱን ባዶዋን ያገኙዋት መሆናቸው፣ እስከዚያ ድረስ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” አስኝተው ያኖሩዋት የካም ነገዶች በየቦታው የነበሩባት መሆናቸው ነው። እነዚህ ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ፣ እንዲሁም ከደቡብ የገቡት፣ መጀመሪያ በእንግድነት፣ ኃላ ባገሪቱ ከነበሩተ ነዋሪዎች ጋር ተዋልደውና ተዛምደው፣ ባለቤት ሆነው ነው አብረው የኖሩ። ታዲያ፣ የሚያስገርመው ደግሞ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን አጥፍተው የየራሣቸውን ነፃ መንግሥታት መፍጠር ከሚፈልጉት የሚበዙት፣ እኒህ መጀመሪያ በእንግድነት ገብተው፣ ሁዋላ ባለቤት የሆኑት ክፍሎች ናቸው።

 

ማጠቃለያ

ከዚሀ በላይ ከ1-6 ቁጥሮች የተዘረዘሩትን ለማጠቃለልና ወደፊትም ሊደረግ የሚገባውን ለመጠቆም ያክል፣ ከዚህ የሚከተለውን ባጭሩ ተመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊትና በየጊዜው ከየአቅጣጫው የመጡትን ልዩ ልዩ ነገዶች እየተቀበለች፣ በውስጥዋ ከነበሩት ብሔረሰቦች ጋር እየተዋለዱና እየተዛመዱ፣ ባሉበት ሆነው እንዲኖሩ ያደረገች እንጂ ከመቶ አመት ወዲህ የተፈጠረችና፣ የሌሎችን አገር ወርራ ቅኝ ግዛት ያደረገች አየደለችም። በውስጥዋ የሚኖሩት ብሔረሰቦችም/አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ወዘተ/ ተባብረው ነፃነታቸውንና አንድነታቸውን ለመጠበቅ ከውጪ ጠላት ጋር እየታገሉ ሁሉም በድህነት፣ ወይም አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ ሆኖ አያውቅም። ከኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መሀከል አማራው ገዥና ጨቁዋኝ፣ ሌሎች ተገዥዎችና ተጨቁዋኞች ሆነው የኖሩ አስመስለው የሚያወሩ፣ በኢትዮጵያዊያን መሀከል ስምምነቱ ጠፍቶ ወደ መለያየት እንዲደርሱ የሚፈልጉ ጠላቶችዋና፣ ይህን የተንኮል ወሬ፣ አምነውም ይሁን ሣያምኑ ተቀብለው፣ ለየብሔረሰቡ ነፃ መንግሥታት ገዥዎች ለመሆንና የሥልጣን መወጣጫ፣ መሣሪያ ማድረግ የሚፈልጉ የልዩ ልዩ “ቡድን” መሪዎች ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፣ ከዚህ በላይ በቁጥር 6 እንደተመለከተው፣ በወሰንና በሌሎች የጋራቸው በሆኑ ጉዳዮች በየጊዜው በሚነሣ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የብዙ ሰው ሕይወትና ብዙ ሃብት በማጥፋት ፈንታ ሠላም አግኝተው፣ በተናጠል ማድረግ የማይቻለውን፣ የሀብትና የዕውቀት ኃይላቸውን በማስተባበር፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሯቸውን አልምተው፣ ከቤተሰብ ማሕበር ወደ መንደር ማሕበር፣ ከመንደር ማሕበር አልፎ ወደ አለማቀፋዊ ማሕበር በመሻገር ላይ መሆኑ ይታያል። ታዲያ በዚህ ጊዜ፣ ብሔራዊ ማሕበርን አፍርሶ ወደ መንደር ማሕበር ለመመለስ ማሰብ የታሪክን ጉዞ ወደ ኃላ ለመመለስ እንደማሰብ የሚቆጠር ይሆናል።

 

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ አንድነትና የብሔረሰቦችዋን ተገቢ ጥያቄ ለማስማማት፣ የመንግሥቱን ሥልጣን በሁለት ከፍሎ፣ አንደኛው የመካከለኛው መንግሥት ሥልጣን፣ በጠቅላላው፣ የኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት የሚጠበቅበትን፣ ብሔረሰቦች፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ፣ እርስ በርሣቸው የሚገናኙበትና፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ፣ ከውጭው አለም ጋር የምትገናኝበትን ሁኔታ የሚመለከት ይሆናል። የብሔረሰቦች ሥልጣን፣ በየክልላቸው ውስጥ፣ የፖለቲካን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሯቸውን ማስተዳደርና፣ ከዚያ ማስፈፀሚያ፣ ከክልላቸው ውስጥ ግብር መሠብሰብን፣ እንዲሁም ከፈለጉ፣ በየክልላቸው ውስጥ ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንና ሌላ የግል መለያቸው የሆነውን ሁሌ የመጠበቅና የማዳበር መብት ይመለከታል። የማዕከላዊውን መንግሥትና የብሔረሰቦችን ሥልጣን አከፋፈል ለመጠቆም ያክል እዚህ የተመለከተው፣ ብሔረሰቦች ሁሉ ተካፋይ የሚሆኑበት የማዕከላዊው መንግሥት ምክር ቤት በዝርዝር በሚያወጧቸው ሕጐች የሚወሰን ይሆናል።

 

የመንግሥቱ ሥልጣን በሁለት የተከፈለ መሆኑ፣ የሕዝቡን መብት የሚጠብቅና በሕግ የተወሰነ ይሁን እንጂ፣ እንዲሁ በቆየ ልማድ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ፣ ብሔረሰቦች በየክልላቸው በኩል፣ የዘር መስመራቸውን ተከትለው በሚወራረሱ ገዥዎችና እነሱ በሚሾሙዋቸው መኳንንት ነበር የሚተዳደሩት። ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የነበራቸው ግኑኙነት፣ በገዥዎቻቸው በኩል ነበር። ያሁኑ አካፋፈል ከጥንቱ የሚለየው የማዕከላዊው መንግሥትና የብሔረሰቦች መብትም፣ ግዴታም ተዘርዝሮ በሕግ የሚወሰን መሆኑ ነው። ይህ አይነት የሥልጣን አከፋፈል፣ በዘመናዊ አነጋገር፣ የፌዴሬሽን ሥርአት የሚባለው ነው። ፌዴሬሽን ሥርአት፣ የኢትዮጵያ አንድነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለብሔረሰቦች የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ልማትንም ሰላምንም የሚያመጣ በመሆኑ ለሁለቱም ወገኖች የሚበጅ ነው።n

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
10704 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us