ጤፍ ከባሕላዊነት ወደ ዓለምአቀፋዊነት

Wednesday, 06 April 2016 12:20

 

በጥበቡ በለጠ

ጤፍ የኢትዮጵያዊያን ባሕላዊ ምግብ ነው እየተባለ ለብዙ ሺ አመታት አብሮን ቆየ። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን እጅ ወጥቶ የአለም ቁጥር አንድ ተፈላጊ ምግብ እየሆነ ነው። አለም ፊቱን ወደ ጤፍ አዙሯል። እኛ ዘንድ ደግሞ ከጤፍ ጋር ያለን ዝምድና በብዙ ምክንያት እያሽቆለቆለ ነው። ለዛሬ መነጋገሪያ ይሆነን ዘንድ “ጤፍ የኛ በረካ” በሚል ርዕስ ሰሞኑን የታተመው የበለቀች ቶላ መጽሐፍ ነው።

 

በቀለች ቶላ ስለ ጤፍ ጥቅም መናገር፤ መወትወት፤ ማውራት፤ መፃፍ ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። ጤፍ በንጥረ ማዕድናት እጅግ የበለፀገ ነው፤ በሐገራችን የእርሻ ባሕል ውስጥም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል እያለች ትናገር ነበር። ከአራት አመታት በፊትም ጥበብና እፎይታ በተሰኘ በሬዲዮ ፋና የሬዲዮ ኘሮግራም ላይ አቅርበናት የጤፍን ተአምራዊ ሊባል የሚችል ጠቀሜታ አያሌ ማስረጃዎችን እጠየቀሰች ታስረዳን ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአለም ታላላቅ የምርምር ማእከላት ስለ ጤፍ ጥቅም አጥንተው ይፋ የሆኑ መግለጫዎችን ሰጡ። የኘላኔቷ ግዙፍ ሚዲያዎች የሚባሉት እነ ኒው ዮርክ ታይምስ'ዋሽንግተን ፖስት' ቢቢሲ' ዴይሊ ሜል እና ሌሎችም እየተቀባበሉት ስለ ጤፍ ተአምራዊነት ዘገቡ።

 

በአሁኑ ወቅት የጤፍ ጉዳይ ለየት እያለ መጥቷል። ምክንያቱም ሌሎችም ሀገሮች እያመረቱት ይገኛሉ። ሲያመርቱት ደግሞ ወትሮም ከምናውቀው በተለየ መልኩ ነው።ለምሳሌ Costa Concentrados Levantinos የተባለ እ.ኤ.አ በ1887 ዓ.ም የተቋቋመ ኩባንያ AMANDIN በሚል የንግድ ስም ጤፍን በጁስ መልክ ፈሣሽ አድርጐት የሚጠጣ አድርጎት ይዞ መጥቷል። ጤፍ ግሉቲን ተብሎ ከሚጠራው በተለይ ስንዴ ውስጥ ከሚገኘው ንጥረ ነገር የፀዳ በመሆኑ የአለም ሕዝብ ከግሉቲን ነፃ (gluten free) እያለው ጤፍ ላይ ተረባርቧል። አንድ ኪሎ ጤፍም እስከ 200.00 የኢትዮጵያ ብር በውጭው ዓለም እየተሸጠ ይገኛል።

 

ዛሬ በአለም ላይ ስለ ጤፍ ጥቅም የሚነግሩን ከእኛ ይልቅ ሌሎች አለማት ሆነዋል። እነ በቀለች ቶላን የመሣሠሉ በኢትዮጵያ አዝእርት እና እፀዋት ላይ ጊዜና ጉልበታቸውን እውቀታቸውን የሚያፈሱትን ምሁራን ሚዲያዎቻችን ሰፊ ሽፋን ስለማይሰጧቸው ነገራችን ሁሉ ከእምቧይ ካብነትም በተጨማሪ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል ሆኖ ቀረ። በአሁኑ ወቅትም ጤፍ የኮፒ ራይቱ ጉዳይ ወደ አውሮፓ ደች ገብቷል። ጤፍ የኢትዮጵያ ልዩ መታወቂያዋ አዝእርት ሆኖ ሣለ ልክ ከአውሮፓ የተገኝ ይመስል ኮፒ ራይታችን ሲወሰድ ከዚህ በላይ ምን ያስቆጫል?!

 

የጤፍ ታሪክ እንደሚያወሣው ከአምስት ሺ አመት በፊት በኢትዮጵያ እንደተገኘ ይነገራል። ኢትዮጵያዊያኖች ከሣር ዘሮች መካከል ይህን ተክል ለምግብነት መጠቀም ጀምረው ይህን ሁሉ ዘመንም ከቤታቸው ከማዕዳቸው ውስጥ ጠብቀው በማቆየታቸው አስገራሚ እንደሆኑ የተለያዩ ሚዲያዎች ገልፀዋል። ለምሣሌ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሣይኖር በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው ባሕላዊ ምግብ ሆኖ መቆየቱ አስገራሚ ነው ይሉታል።

 

ጤፍ ለጤና ተስማሚ፤ ከብዙ በሽታዎች የሚከላከል፤ የሰው ልጅ ጠባቂ እንደሆነም የስነ-ምግብ አጥኚዎች ይገልፃሉ። እንዲሁም ብለውታል፡-

Teff is a cereal first grown in Ethiopia 5000 years ago. It is rich in fiber carbohydrates and minerals (calcium, iron and magnesium). It is highly appreciated by sports practitioners for its properties in helping to restore energy levels.

 

ይህን የፃፈው ጤፍን እንደ ጁስ፤ እንደ ወተት አሽጐ የሚሸጠው ኩባንያ ነው። ጤፍ የዛሬ አምስት ሺ አመታት በኢትዮጵያ እንደበቀለ፤ በፋይበር ንጥረ ነገር የበለፀገ፤ በሀይል ሰጭ እና በሚኒራል የበለፀገ፤ ካልሲየም፣ አይረን እና ማግኒዚየምን የያዘ ምግብ መሆኑን ይገልፃል። በተለይ ለስፖርተኞች ከፍተኛ ሀይል ሰጭ ምግብ መሆኑን ኩባንያው ይመክራል። እንግዲህ ጤፍ ቀን ወጥቶለታል ማለት ይቻላል።

 

ዛሬ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከተሞች ፓን ኬኮች እና በርገሮች በጤፍ መሠራት፤ መበላት ጀምረዋል። ሚዲያዎቹ የኢትዮጵያ ጤፍ በመጪዎቹ ጥቂት አመታት ዋናው ተፈላጊ ምግብ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ፅፈዋል፡-

 

እኛ ምን እያደረግን ነው? የጤፍን ምርት እያሣደግን ነው? ትኩረት ሰጥተነው የወደፊቱ የሐገሪቷ ዋነኛው የኤክስፖርት ምርት ለማድረግ እየሠራን ነው? ለመሆኑ ግብርና ሚኒስቴር እና መንግሥትስ ስለ ጤፍ አጀንዳቸው ነው? እስካሁን ባየሁትና በታዘብኩት ነገር መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም ብለዋል። ነገር ግን እንደ በቀለች ቶላ አይነት ወኔያም እና የሐገር ተቆርቋሪዎች ስለ ጤፍ ብዙ እያስተማሩን ነው።

 

በቀለች ቶላ ከዚህ ቀደም በ2004 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ Injera Variety From Crop Diversity  ብላ ስለ ጤፍ እንጀራ መፅሃፍ አሣትማለች።

በአማርኛ ቋንቋ ደግሞ በአይነት እንጀራ የሚል መፅሐፍ ስለ ጤፍ እንጀራ መጽሃፍ አሣትማ አስነብባናለች።

 

ከዚሀ ሌላ ስለ ዕፅዋት ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች ብላ መፅሃፍ ለልጆች አሣተመች። ቀደም ብላም ለኢትዮጵያ ገበሬዎች በማሰብና በመቆርቆር ለእንሰሣት እንክብካቤ የተሰኘ መጽሐፍ አሣትማለች። በየሰው ቤት መጥፋት የሌለበትንም ሕክምና በቤታችን፡- የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መጽሃኒት ብላ ግሩም የሆነ መጽሐፍ አሣትማለች።

 

እንደ በቀለች ቶላ አይነት ለወገን ለሐገር ተብሎ የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ። እሷ የተፈጠረችው ለሀገር ነው። እናም ዛሬ ደግሞ ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር ብላ መፅሃፍ ይዛልን መጥታለች። እውነትም በረካ።

 

በባሕላችን እንጀራ ይስጥሽ፤ እንጀራሽ ከፍ ይበል፤ እንጀራ ይውጣልሽ፤ እንጀራሽ ይለምልም እየተባለ ይመረቃል። ሕፃን ልጅ ተወልዶ ክርስትና ተነስቶ ሲመጣ እንጀራ ተዘርግቶ እሱ ላይ ይንከባለላል። እንጀራው የተቀና፤ ሕይወቱ የለመለመ እንዲሆን ነው። እናም በቀለች ቶላ ያ እንጀራ የሚሠራበትን ጤፍ እንዲህ ነው ብላ ልታሣውቀን ይህን መፅሃፍ አዘጋጀችው።

 

በበቀለች ቶላ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ቁም ነገሮች መካከል ጤፍ ለአውሮፓ ምግቦች እንዴት እየዋለ እንዳለ የምትገልፅበት መንገድ ነው። እንደ እርሷ ገለፃ የጤፍ ዱቄት ብቻውን ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከሌላ ዱቄት ጋር ተቀይጦ ለፒዛ፣ ለፒታ፣ ለፖን ኬክለኬ፣ ለመኮረኒ፣ ስፓጌቲ፣ ቴላቴሊ፣ ኖዱልስ፣ ላዛኛ እና ለሌሎችም ይሆናል ትላለች። ስታብራራም እጅግ የተወደዱት የአውሮፓ ምግቦች ፓስታ እና ማካሮኒን ትጠቅሣለች። እነዚህ ምግቦች አሠራራቸው የተለመደው ከስንዴ ነው። ፓስታን ወይም የማካሮኒ ዱቄትን ለማዘጋጀት ብዙ አማራጮች መኖራቸውን በማስታወስ በሚከተለው መልኩ አዘገጃጀቱን ፅፈዋለች።

·         የጤፍ ዱቄት ከስንዴ ዱቄት ጋር አመጣጥኖ ማዘጋጀት

·         የጤፍ ዱቄት ከአጃ ዱቄት ጋር አመጣጥኖ ማዘጋጀት

·         የጤፍን ዱቄት ከጠይሙ አጃ ጋር ትሪቲካሌ ዱቄት ጋር ማመጣጠን'

·         ጤፍን ከበክዊት ጋር በእኩል መጠን ቀይጦ አንድነት ማስፈጨት። /በክዊት የተክል አይነት ነው።/

እንደ በቀለች ገለፃ፤ ጤፍን እና በክዊት የተባለውን ተክል አብሮ በመቀላቀል ፓስታ እና ማካሮኒን የመሣሠሉ ምግቦችን አያሌ ጥቅሞች ባሉት በጤፍ መተካት እንደተቻለ ታብራራለች።

 

የጤፍ ምጥን ፍሌክስ Flakes

በበቀለች መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለ ፍሌክስ ነው። ፍሌክስ ለምሣሌ የተለመደው የበቆሎ ፍሌክሰ Corn Flakes ነው። ፍሌክስ በስሎ ያለቀለት ስለሆነ ማብሰል ሳያስፈልግ ወተት ወይም ሻይ በላዩ ላይ በማፍሰስ የሚበላ ነው። በቀለች ስትገልፅ ስነ-ምግቡም የተሻሻለ እና ተስማሚ የሆነ ፍሌክስ ለማዘጋጀት ጤፍ፣ አጃ እና በቆሎ በእኩል መጠን አመጣጥኖ ማዘጋጀት ይቻላል ትላለች።

ለምሳሌ፣ በቤት ውስጥ ለማዘጋጀት እንኳን ይቻላል ብላለች። ይህም በሚከተለው መልኩ ነው።

·         ጤፍን በሸክላ ምጣድ አብስሎ ማመስ

·         በቆሎውን ለ48 ሰዓት መዘፍዘፍና፣ ለ36 ሰዓት ማጐንቆል፣ መቀቀል፣ ማድረቅ፣

·         አጃን ለ10 ሰዓት መዘፍዘፍ፣ ለ12 ሰዓት ማጐንቆል፣ መቀቀል፣ ማድረቅ፣

ሁሉንም ቀይጦ ማስፈጨት። ይህ የበሰለ ዱቄት ነው። ይህንን ዱቄት በስሱ በውሃ በማቅጠን በሚመች ቅርፅ ማውጫ አውጥቶ በፀሐይ ሙቅት ማድረቅ። ይህ የጤፍ ምጥን ፍሌክስ ምንም ስኳር ሣይደረግበት ጣፋጭ ይሆናል። ከውጭ ሀገር የሚገቡት የፍሌክስ አይነቶች በውድ ዋጋ እንደሚሸጡ የታወቀ ነው። የተመጣጠነ የጤፍ ፍሌክስ ፋብሪካን ማቋቋም እንዴት ያለ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል አርቃችሁ ገምቱ ትለናለች ደራሲዋ በቀለች ቶላ ጤፍ የኛ በረካ በተሰኘው መፅሐፍዋ

 

የጤፍ ዱቄት ለኬክ ስራ

በቀለች ስትፅፍ፤ ኬኮች በብዙ አይነት ይጋገራሉ ትላለች። የኬክ ባልትና በሁሉም የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች ሞልቶ መትረፉንም ታስታውሠናለች። ሆኖም ኬኮች ሁሉ የሚጋገሩት በተለምዶ በዋናነት ፉርኖ ዱቄት የሚባለው ከፋብሪካ የተገኘ የስንዴ ውጤት እና የተለያዩ ቅመሞች፣ ወተት፣ እንቁላል፣ በአንድነት ተደርጐ ነው። ነገር ግን ኬክ፣ ፓንኬክ፣ ማፈን፣ ዋፍልስ፣ ብስኩት፣ ፒዛ፣ እና ሌሎችንም ከጤፍ ዱቄት ወይም ጤፍ ከፉርኖ ዱቄት ጋር ተመጥኖ ማዘጋጀት ይቻላል ትላለች። ለማዘጋጀትም የተመጠነውን ጤፍ እንዴት መጠቀም እንዳለብን በሚከተለው መልኩ አስቀምጣዋለች።

·         ጤፍ ከሩዝ ጋር በእኩል መጠን ተቀይጦ፤/1፡1/

·         ጤፍ ከአጃ ጋር ተመጣጥኖ ተፈጭቶ /2፡1/

·         ጤፍ እና አማራንተስ ቀይጦ ማስፈጨት፤/3፡1/

·         ጤፍ እና በክዊት የተባለውን ተክል በእኩል መጠን ማስፈጨት፤/1፡1/

እንደሚገባ ትገልፃለች። እናም ጤፍ የኛ በረካ ወደ ዘመናዊ የሰው ልጅ የአመጋገብና የአጠቃቀም ምዕራፍ ውስጥ እየገባ መሆኑን ከበቀለች መጽሐፍ ውስጥ መረዳት እንችላለን።

 

እንጀራ ለጤፍ ተስማሚ እንዲሆን

እንጀራን እንደ ሰው ፍላጐት እና ጤንነት ተስማሚ አድርጐ መጋገር እንደሚቻልም በመጽሐፏ ውስጥ ተገልፆአል። ለምሣሌ ለጤናው በብረት እና ካልሲየም ማዕድን የዳበረ ምግብ ያስፈልግሃል የተባለ ሰው ከፍተኛ ካልሲየምና የብረት ምጥን እንዲኖረው ሰርገኛ ወይም ቀይ ጤፍ ላይ ቀይ ዳጉሣ፣ አማራንተስ /ካቲላ/' ሽንብራ፣ አኩሪ አተር፣ ካሳቫ፣ ተመጣጥኖ የተጋገረ ምጥን እንጀራ ቢያገኝ ይሻለዋል በማለት ሙያዊ ምክሯን ትለግሣለች ።

 

በብረት እና ካልሲየም ማዕድን የዳበረ ምግብ እንድትበላ የተባለ ሰው ዝቅተኛ የካልሲየምና ዝቅተኛ የብረት ምጥን ህላዊ እንዲኖረው በሩዝ ላይ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስ ወይም ጐደሬ ተመጣጥኖ የተጋገረ ምጥን እንጀራ ቢያገኝ ይሻለዋል ትላለች ደራሲዋ።

 

የተሻለ ካልሲየም ኖሮት ነገር ገን ብረቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያስፈለገ እንደሆነ ነጭ ጤፍ ላይ የጐደሬን ሥር ድርቆሽ ወይም የደረቀ ቆጮ መጣጥኖ ማዘጋጀት እንደሚረዳም ትገልፃለች።

 

አነባበሮ ወይም እንጀራው ከፍ ያለ ኘሮቲን እንዲኖረው ጤፍ ላይ ጥቁር ስንዴን፣ አኩሪ አተር፣ ሽንብራ ወይም ካቲላን አመጣጥኖ መጨመር።

 

አነባበሮ ወይም እንጀራው ዝቅተኛ ኘሮቲን እንዲኖረው ነጭ ጤፍ ላይ ሩዝ፣ በቆሎ ወይም ማሽላ መጨመር፣ ከቶም ጥራጥሬ መተው ነው። የጨጓራ ሕመም ያለበት ሰው አንድ ለሊት ተቦክቶ የተጋገረ የበቆሎ እንጀራ እንደሚስማማውም በቀለች ቶላ ትገልፃለች።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ ብዙም ያልተነገረለት የጤፍ ችግርና ቀውስ ስለሚያመጣም ጉዳይ በቀለች ፅፋለች። ለምሣሌ ጤፍ በአለም የተደነቀበት በማዕድን ይዞታው ጭምር ነው። በብረት፣ በካልሲየም እና በሌሎችም ማዕድናቱ ሀብታምነት ነው። በአገራችን ኢትዮጵያም የከተማ ነዋሪዎች በስፋት የሚመገቡት የጤፍ እንጀራን ነው። ታዲያ ለምንድን ነው ብዙ ሰዎች በአጥንት መሣሣት (ኦስቶኘሮሲስ Osteoporosis) የሚጐዱት? በማለት በቀለች ቶላ ትጠይቃለች። ምክንያቱ ምን ይሆን? እንጀራ እየተመገብን በላዩ ላይ ምን ጨምረን እየበላን ነው? ምን ጨምረን እየጠጣን ነው? የጤፍን ንጥረ ምግብ ጠቀሜታ ከጥቅም ውጭ ያደረግነው ምን ጨምረን ነው? ይህ ነው ትልቅ አገራዊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው ትላለች በቀለች ቶላ። ስታብራራም፡-

 

ኒውትሪሽናል ሂሊንግ ከተባለ መፅሐፍ ካነበብኩት አንድ ምሣሌ እነሆ ትላለች። ሻይ እና ቡና ሰውነት የካልሲየም ማዕድን ወደ ሰውነት እንዳይሰርግ/እንዳይወሰድ/ ያግዳሉ ይላል። በዚህ መሰረት የምንመገበው የጤፍ እንጀራ የቱንም ያህል በማዕድን የበለፀገ ቢሆን እኛው በላዩ ላይ በምንጠጣው ሻይ እና ቡና ምክንያት አይጠጋንም ማለት ነው ስትል አዲስ አተያይ አምጥታለች ደራሲዋ። ለአጥንት መሣሣት እራሣችንን ያጋለጥነው በተመገብነው እንጀራ ላይ ስንትና ስንት ሲኒ ቡና ወይም ሻይ መጠጣታችን አንዱ ነው ማለት ይቻላል በማለት ደራሲዋ በቀለች ቶላ ለበርካታ ጊዚያት ልዩ ልዩ ጉዳዮችን መርምራ የደረሰችበት ውጤት ያሣያል። በዚህ ዘመን እንደ ማወቅ፣ እንደ መራቀቅ፣ አድርገነው በቁርስ፣ በምሣ እና በእራት ላይ ቡና ሻይ--ሌላም ጠቃሚ ያልሆኑ መጠጦች ምግቦች የጉዳታችን ምንጮች እንደሆኑ በቀለች ቶላ ትጠቁመናለች። አቤት እግዚኦ! ስለ ጤና ስትሉ! ለቡና እና ሻይ ሰዓት አብጁለት፤ ከምግብ ሰዓት ቢያንስ እስከ 4 ሰዓት ራቅ አድርጉት ብላ ትመክረናለች።

በሌላ መልኩ ደግሞ ይኸው በማዕድናት የበለፀገ ነው የምንለው ጤፍ የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆን ከሌሎች ሰብሎች ጋር ተቀላቅሎ ለምግብነት ቢቀርብ የበለጠ ጠቀሜታው እንደሚጐላ ደራሲዋ ትገልፃለች። ጤፍን ከበቆሎ፣ ከሩዝ፣ ከማሽላ፣ ከዳጉሣ ወዘተ ጋር መቀላቀል ጥቅሙን ከፍ ያደርገዋል ብላ ፅፋለች። በተለይ ከዳጉሣ ጋር! የዳጉሣን ጥቅም ከዚህ ቀደም ሰምተነው ወይም አንብበነው በማናውቀው ሁኔታ በቀለች እንዲህ ትገልፀዋለች።

 

ዳጉሳ/የእህል አውራ/፤ በወይና ደጋ እና እርጥበት ቆላማ ማሽላ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ይበቅላል። በአንድ የምርት ወቅት የሚዘመር የእህል ዘር ሲሆን አበቃቀሉ የአክርማ ሣር ይመስላል ትላለች። የሚያፈራው አናቱ ላይ እንደ ጣት በተዘረጉት መስመሮቸ ውስጥ ነው። ዳጉሣ ነጭ፣ ቀይ፣ ቀይ-ቡኒ እና ጥቁር ወይም ቀይ እና ነጭ ቅይጥ አይነትዎች አሉት። ነጩ በገበያ ላይ በብዛት አይገኝም። ነጩ ምናልባትም የሚገኘው በሰሜን ጐንደር አዲአርቃ ወረዳ ውስጥ፤ በትግራይ ቆላማ አካባቢዎች እና በባሕርዳር ዙሪያ ይሆናል። ቀዩ ወይም ቀይ ቡኒው በጐጃም፣ በወለጋ በቅርቡ ደግሞ በሻሸመኔ ዙሪያ በብዛት ይገኛል።

ዳጉሣ በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሰጠው ለጠላ መጠጥ ብቻ የተተወ ነው። ነገር ግን ከዚህ ወደ ህንድ የተወሰደው ዳጉሣ እንዴት ያለ አልሚ ምግብ ይሠራበታል በማለት በቀለች ታስቆጨናለች። ቫንደና ሼቫ/ታዋቂዋ ሕንዳዊት የኦልተርኔት ኖቤል ባለሎሬት/አንድ ቀን አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሸ ባደረገችው ንግግሯ ውስጥ እንዲህ ብላ ነበር፡- “ዳጉሣን ከናንተ አገር ቅድመ-አያቶቻችን ወደ ሕንድ አመጡት። እጅግ የተወደደ ምግብ ይሠራበታል። እናንተ ግን አባት አልባ እህል አደረጋችሁት---” አለች። መቼም ያን እለት ንግግሯን ለመስማት እዚያ የነበረው ሰው ትዝ ይለዋል። ከነምልክቱ ለምን እና እንዴት እንደሆነ ባላውቅም የዚያን እለት እሷ ንግግር እያደረገች ሣለ አንድ ትልቅ ድመት ከጣሪያ ላይ ከመድረኩ ፊት ተምዘግዝጐ ወደቀ። እኔ ደንግጨ ከምፅፍበት ቀና ስል ድመቱ በፍጥነት ተነስቶ ከመድረክ ኋላ ገባ። ቫንዳና ከቶም ንግግሯን አላቆረጠችም ነበር በማለት በቀለች ታስታውሣለች። ጉዳዩ ትልቅ ነው። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ሔዳ ሕንድን በምግብ ንጥረ ነገር ስላበለፀጋት ዳጉሣ ነው።

 

ዳጉሣ ድርቅን በእጅጉ መቋቋም ይችላል ትላለች በቀለች። በ2007 ዓ.ም በተከሰተው የዝናብ እጥረት ሌሎች ሰብሎች ተበላሽተው ሣለ ዳጉሣ ልምላሜውን እንደጠበቀ መቆየቱንም ታስታውሣለች። ለምሣሌ በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ በሻሸመኔ ዙሪያ ባሉት ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ የነበረው የዳጉሣ ልምላሜ ልዩ እንደነበር ትገልፃለች።

 

ዱጉሣ እጅግ ጠቃሚ ምግብ መሆኑን ታሣስበናለች። የያዘው የካልሲየም እና ብረት ማዕድን ከጤፍ በእጅጉ ይበልጣል ትላለች። ጤፍ በካልሲየም እና ብረት የበለፀገ ነው የሚሉት የዳጉሣን ይዘት ባለማወቃቸው ነው። በአገራችንም ሆነ በአለም ደረጃ እውቅና የሚገኝበት ዘመን ሩቅ አይሆንም በማለት የመፅሃፉ አዘጋጅ በቀለች ቶላ ትገልፃለች።

 

ጤፍ ከሌሎችም ሰብሎች ጋር ተቀላቅሎ እንዴት ለጤና ተስማሚ እንደሚሆን የበቀለች መጽሐፍ ያስረዳናል። መፅሐፏ ስለ ጤፍ እና ተጓዳኝ ንጥረ ነገሮቹ ሰፊ እውቀት ከማስጨበጡም በተጨማሪ ሁላችንም ስለ ራሣችን ስለ ሀገራችን ስለ ታሪካችንም ማወቅ የሚገቡንን ጉዳዮች ሰብሰብ አድርጐ የያዘ ነው።

 

ደራሲዋ በቀለች ቶላ የጤፍን ሃያልነት እና ጠቀሜታን ብቻም አይደለም የፃፈችው። በጤፍ ጉዳይ ላይ ጐልተው የታዩ የሚታዩ ችግሮችንም ገልፃለች። እነዚህን ችግሮች በሰባት ክፍሎች ዘርዝራ ፅፋለች፡-

 

አንደኛ፡- ዛሬም ቢሆን ጤፍ የሚታረሰው፣ በሚዘራው፣ የሚታጨደው እና የሚወቃው እጅግ አድካሚ       በሆነ አሠራር ነው። ይህ የገበሬውን ቤተሰብ አባላት ድካምና እንግልት እጅግ ያበዘዋል። እንዲሁም የቤት እንስሣትን በእርሻ  እና በውቅያ የሚያሰቃይ ሂደት አለው።

 

ሁለተኛ፡- ጤፍ በዋናነት ለእርሻ ይውላል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ከተማ ነዋሪዎች ያለ ጤፍ ሌላው ሰብል እንጀራ የሚሆን አይመስላቸውም። እንጀራ ዱቄት ከጤፍ ሌላ በብዙ አማራጭ በብዙ   መጠን ተመርቶ መቅረብ ነበረበት። የእንጀራ ምጣድ እና የእንጀራ ጋገራ ቴክኖሎጂ እራሱ ብዙ መሻሻል ይቀረዋል።

 

ሦስተኛ፡- የጤፍ ምርት እና ምርታማነት የሚፈለገውን ያህል አልተሻሻለም። እኛ ባለንበት ስንረግጥ ሌሎች ሀገራት ከእኛ በበለጠ ምረታማነትን አሻሽለው አምርተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

 

አራተኛ፡- ለጤፍ እርሻ፣ ለጤፍ ዘር በመስመር መዝሪያ ለማረሚያ የተሻሻለ የእጅ መሣሪያ ወይም ማሽን የለም። ለማጨዳ፣ ለመውቂያ፣ ለማበጠሪያ የተሻሻለ ነገር የለም። ያው ድሮ የነበረው ነው። በሌሎች አገራት ለጤፍ አመራረት እና ለጤፍ ምግብ አሠራር ብዙ እደ ጥበባት ሥራ ላይ ውለዋል። በእኛ ዘንድ አይታወቅም።

 

አምስተኛ፡- ጤፍ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚገኝበት የአለም ሰብል/ምግብ/ሆኗል። እኛ ወደ ገበያው ለመግባት ገና ብዙ ይቀረናል።

 

ስድስተኛ፡- ጤፍ ላይ ሰፊ ትምህርት አይሰጥም። ገበሬውን ያካተተ የጐሉ ጥናቶች አልተደረጉም።

ሰባተኛ፡- ጤፍን ለአገሪቱ ገፅታ ግንባታ በደንብ አልተጠቀምንበትም ትላለች በቀለች ቶላ

በቀለች ቶሎ እነዚህን በጤፍ ላይ የጐሉ ችግሮችንም ለመቅረፍ ምን ይደረግ ብላ የመፍትሔ ሃሣቦችን ሠንዝራለች።

 

ከነዚህ መፍትሔዎች መካከል አድካሚ የእርሻ ስራን በአዲስ እና በተሻሻለ አሠራር መቀየር እንዳለበት ትጠቁማለች። ይህም አስተራረስን የሚያቃልል ቴክኖሎጂ፤ በመስመር መዝራትን የሚያፋጥን ማሽን፤ አረምን የሚያቀል ዘዴ፤ አጨዳን፣ ውቅያን፣ ብጠራን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎቸ፤ ጤፍን በበልግ ዝናብ በመስኖ አመቱን ሙሉ እና በስፋት መዝራትን ያካተተ ስራ በትጋት መስራት እንደሆነ ትጠቁማለች። በሌላ መልኩም የጤፍ ምርታችንን አሻሽለን በአለም ገበያ ተሣታፊ መሆን የሚያስችል ሥራ ተግቶ መጀመር እንደሚያስፈልግም ትገልፃለች፡ በውጭ ሀገራት የዳበሩ የጤፍ አመራረትን ለእኛ ሀገር በሚያመች መንገድ መጠቀም ሌላው አማራጭ መሆኑንም ትጠቁማለች። ከዚህ ሌላ ጤፍ የኢትዮጵያ ልዩ መለያ ስለሆነ በአለም አቀፍ መድረኮች በሰፊው ማስተዋወቅ እንደሚገባ ደራሲዋ በቀለቸ ቶላ አፅንኦት ሰጥታ ትገልፃለች።n

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
11835 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us