ሐገር ማለት ቢራ አይደለም

Wednesday, 13 April 2016 12:09

 

በጥበቡ በለጠ

 

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በቴሌቪዥን የማየው የቢራዎች ማስታወቂያ እያሣሠበኝ መጥቷል። የቢራን ምርት በኢትዮጵያዊነት፣ በጀግንነት፣ በአይነኩኝም ባይነት፣ በተከበረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ ማስተዋወቅ እየተለመደ መጥቷል። ኢትዮጵዊነትን ከቢራ ጋር ማቆራኘት እየቆየ ሲሔድ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ሁላችሁም የራሣችሁን ግምት መውሰድ ትችላላችሁ።

ግን ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ይህ ጥያቄ ለዘጠና ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ቢቀርብ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል?አሁን በቅርቡ በተደጋጋሚ በተላለፉት የቢራ ማስታወቂያዎች አማካይነት ከሔድን ሐገር ማለት ቢራ ነው የሚል መልስ ልናገኝ እንችላለን። እርግጥ ነው ቀልድ ይሁን የምር ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጂ ሕፃናት በሚማሩበት በአንድ ክፍል ውስጥ በዚህ በአድዋ 120ኛ አመት መምህሩ ተማሪዎቹን አንድ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል አሉ። ጥያቄው በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን የተዋጉባቸው መሣሪዎች ምንድን ናቸው? የሚል ነበር። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ቢራዎች እየጠሩ መልስ ሰጡ ብሎ አንዱ ወዳጄ የሠማውን አጫወቶኛል። ጉዳዩ የተጋነነ ወሬ አይደለም። እውነት ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ማስታወቂያዎቹ በልጆች አእምሮ ውስጥ ይህን የሀገርን እና የቢራን ቁርኝት ሊፈጥሩ ይችላሉ። የኢትዮጵያ የብዙ ሺ አመታት ታሪክ የሚያስተዋውቀው በማጣቱ ይኸው ቢራዎች እየተረባረቡበት ነው።

ጥያቄውን ለሁለተኛ ጊዜ ላቅርበው፤ ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ከሦስት አመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ውስጥ ተጋብዤ ነበር። የተጋበዝኩበት ምክንያት መቀሌ ከተማ ሕዳር 29 ቀን ለሚከበረው የብሔር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ለሕዝብ የሚቀርበውን ቴአትር አይተን እንድንገመግመው፤ አስተያየት እንድንሰጥ ነው። ይህ እንግዲህ ቴአትሩ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት ተጣርቶ እንዲወጣ የተደረገ ሙከራ ነው። ሙከራውን በጣም አደንቃለሁ።

ቴአትሩ ሐገር ማለት--- የሚሰኝ ነው። ደራሲዎቹ አሁን የብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ጓደኛዬ ተስፋዬ ሽመልስ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ከበደ ናቸው። ቴአትሩ ሙዚቃዊ ነው። በቴአትሩ ውስጥ ዋና ገፀ-ባሕሪ የሆነችው፤ የተወከለችው፤ ኢትዮጵያን ሆና የተሣለችው ገፀ-ባሕሪ ሐገር ማለት እናንተ ናችሁ ትላለች። ሐገር ማለት ሰው ነው ትላለች። ሐገር ማለት አፋር ነው፤ ሐገር ማለት ሐረሪ ነው፤ ሐገር ማለት ሲዳማው ነው፤ ሐገር ማለት እያለች በዚያ ቴአትር ላይ እያዜመች ትተውናለች። ሐገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ነው ሀገር ትለናለች። የቴአትሩ ዋና ማጠንጠኛው ሐገር ማለት ሰው ነው የሚለው ጉዳይ ነው።

እውነት ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ሀገር ማለት ሰው ብቻ ነው ብዬ በግሌ አላምንም። ምክንያቱም ሀገር በጣም ረቂቅ ጉዳይ ነው። ለምሣሌ ኢትዮጵያ ከምትባለው ሀገር ወጣ ብለን ሌላ ሀገር እንኑር። በውጭ ሀገር በመቆየታችን ምን ይሆን የሚናፍቀን? በርግጥ ሁላችንም አንደስሜታችን የምንናፍቀው ነገር ይለያያል። አንዳንድ ሰው ያደገበት፣ የቦረቀበት ሜዳው፣ ዳገቱ፣ ሸንተረሩ ሊናፍቀው ይችላል። ሌላው ደግሞ የሚዋኝበት ወንዝ ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ደግሞ ምግቡ እንጀራው፣ ጮማው፣ ሽሮው፣ ጨጨብሣው፣ ቅቤው ድልሁ-- ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ከብቱ፣ እንስሣቱ፣ ፈረስ ግልቢያው ወዘተ ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ሰው ሊናፍቀው ይችላል፤ ወንድሙና እህቱ፣ እናቱ፣ አባቱ፣ ጓደኛው--። ስለዚህ ሀገር ማለት እነዚህና ሌሎች ብዙ ሚሊየን ነገሮች ማለት ነው። ሀገር ማለት ሰው ብቻ አይደለም! ሀገር ረቂቅ ነው።

ዛሬ ዛሬ ሀገር ማለት ቢራ እየሆነ በመተዋወቅ ላይ ነው። የሐገራችን ቢራዎች ሀገርን የምርታቸው ማስተዋወቂያ እያደረጉት መጥተዋል። ምናልባት ስለ ሀገር የሚያወራ በመጥፋቱ ይሆን? ሀገር ስለምንለው ጉዳይ ምስክር ሲጠፋ፣ ድምፁን ከፍ አድርጐ የሚናገር፣ የሚያወጋ በመክሰሙ ቢራዎች አጀንዳውን ይዘው መነሣታቸው ይሆን? ያውምኮ በግጥም እና በታሪክ ላይ እየተቀኙ ነው የሚያቀርቡት።

የቢራ ማስታወቂያዎች እየገረሙኝ ከቆዩ አመታት እያለፉ ነው። ለምሣሌ የሸገር ሬዲዮ 102.1 ባለቤቶች እና ጋዜጠኞች የሆኑት ተወዳጆቹ መአዛ ብሩ እና ተፈሪ ዓለሙ ቢራን ሲያስተዋውቁ ስንሰማ ድንቅ ይለናል።---“ከተማ ያደምቃል፤ ፀብ ያርቃል!”--እያሉ ቢራን ያስተዋውቃሉ። አይገርሙም?

እውነት ግን ቢራ በምን ተአምር ነው ፀብ የሚያርቀው? ሰው እንዳይጣላ፣ እንዳይጋጭ ቢራ መጠጣት አለበት? ላለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ እርቅ የሚል ፖለቲካዊ ጥያቄ መቀንቀን ከጀመረ ቆይቷል። ቢራ ፀብ ያርቃል ከተባለ ትርጉሙ ብዙ ነው። የፀባችንን ጉድጓድ ሁሉ ይደፍናል። እናም ቢራ እንጠጣ ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። ይህን ቢራ ፀብ ማራቁን በተመለከተ ማስታወቂውን የሰሩልን ታላላቅ ጉዳዮችን በሬዲዮ የሚያቀርቡልን ጐምቱ ባለሙያዎች መሆናቸው ሀዘናችንን ያብሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ወርቅነህ ጣፋ ሰሞኑን ይህን የቢራዎች የተሣሣተ ማስታወቂያ በተመለከተ የተናገሩት ጉዳይ አለ። ለምሣሌ “ከሺ ሰላምታ አንድ ሜታ!” የሚሰኘውን የማስታወቂያ ገለፃ ጠቅሰው ተችተዋል።

 

በጣም የሚገርመው ቢራን ከሺ ሰላምታ አስበልጦ ማቅረብ፣ ቢራን ፀብ ያርቃል ብሎ መናገር ብቻ አይደለም ስህተቱ፤ ይሔን ስህተት ተቀብሎ ለዘጠና ሚሊየን ሕዝብ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን የሚያስተላልፈው ጣቢያ ምን አይነት አስተሣሰብ በውስጡ ቢኖረው ነው? ብዬም እጠይቃለሁ። ማሕበራዊ ኃላፊነትን (Social Responsibility) ያለመወጣት ችግር በሰፊው ይታያል።

ለምሳሌ በሕዝብ ዘንድ በሙዚቃው ልዩ ቃና በእጅጉ የሚወደደው ጋሽ አበራ ሞላ (ስለሺ ደምሴ) “ያምራል ሀገሬ” የሚሰኝ፤ ነብስን የሚገዛ ሙዚቃ ሰርቶ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል ብዙም ሳይቆይ ይህን የመሰለውን ሙዚቃውን ለቢራ ማስታወቂያ ሲያውለው ሳይ፤ አርአያ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ሰዎች እየተመናመኑብኝ መጡ።

 

የቢራ ጉዳይ የአዲስ አበባን ስታዲየም ሣይቀር እንደ ካንሰር ወርሮት ይገኛል። የሲጋራን ማስታወቂያ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከአለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች እንዲወገዱ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እርሳቸው ከ25 አመታት በፊት ከዚህች አለም በሞት ሲለዩ የራሣቸው ሀገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታዲየሟ በመጠጥ ቤቶች ተወረሮ ቢራና ድራፍት እንደልብ የሚጠጣበት ቦታ ሆኗል። ብሔራዊ ቡድናችንም ውጤት እየራቀው ከውድድር ውጭ እየሆነ ከመጣም ቆይቷል። ድሮስ በአሸሼ ገዳሜ እና በአልኮል ከተከበበ ብሔራዊ ስታዲየም ውስጥ ምን አይነት የድል ውጤት ሊገኝ ይችላል?

 

ሌላው በጣም አስገራሚው ጉዳይ የብሔራዊ ቡድናችን ስም እና ቢራ ተመሣሣይ መሆናቸው ነው። ዋልያዎቹ ስፖንሰር የሚደረጉት በዋልያ ቢራ ነው። ለመሆኑ ብሔራዊ ቡድናችን እና የቢራው መጠሪያ ለምን ተመሣሣይ ሆነ? በኢትዮጵያ የንግድ ስያሜ ውስጥ ተመሣሣይ ስሞች ፈፅሞ አይፈቀድም። ዋልዎቹ እና ዋልያ ቢራ እንዲህ መመሣሠላቸው ብሔራዊ ቡድናችንም ከቢራ ጋር መቆራኘቱ ተገቢ ነው ትላላችሁ? ይድነቃቸው ተሰማ ይህን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? የወቅቱም የኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌደሬሽን ለኘሬዘዳንትነት የተመረጡት አቶ ጁነይዲን ባሻ ቀድሞ የሐረር ቢራ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ የነበሩ ናቸው። ምርጫውም ከወደ ቢራ አካባቢ መሆኑ ትንሽ ያስገርማል። ምናልባት የእርሣቸው የቀድሞ ኃላፊነታቸው ተፅዕኖ አድርጐ ይሆን ብሔራዊ ቡድናችን እና ስታዲየማችን በቢራ ንግድ እና ስም የተሳሠሩት።

 

ባጠቃላይ ሲታይ የቢራ ማስታወቂያዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኃላፊነት በጐደለው መልኩ እየተሰሩ ይገኛሉ። ይህንንም ድርጊታቸውን ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢዎቻችን ካለምንም ተቃውሞ ለአድማጭ ተመልካቾች እያስተላለፉ ነው። በጉዳዩ የተቆጣው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሚዲያዎቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልኮላቸዋል። ከረፈደም ቢሆን እርምጃው መውሰዱ ተገቢ ነው።

 

ሳጠቃልለውም፤ እርግጥ ነው ቢራ ፋብሪካዎች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖራቸው ድርሻ ቀላል አይደለም። ብዙ የስራ እድል ከፍተዋል። እኔ እንኳን የማውቀው የቀድሞው ሐረር ቢራ ፋብሪካ ውስጥ በርካታ የሐረር ከተማ ነዋሪ ስራ እየሰሩ ይተዳደሩበታል። ቢራ ለመዝናናትም ያገለግላል። ግን ሐበሻ ቢራ እና ዋልያ ቢራ በሚያስተዋውቁበት ደረጃ ከሀገር ጋር አይቆራኝም።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
15545 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us