“ይሄን ምስኪን እስላም ያዙት’ኮ”

Wednesday, 13 April 2016 12:12

በጥበቡ በለጠ

ይህ ጽሁፍ የክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ ተብሎ የሚታቀውን የፖለቲካ ድርጅት የመሰረተና ከመሪዎቹም አንዱ የነበረ ነው።በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከአውሮፓ የከፍተኛ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሀገሩ የመጣው ክፍሉ፤ ከሞት አፋፍ ላይ በተአምር እየተረፈ ዛሬም ድረስ በህይወት ያለ የዚያ ትውልድ አደራጅና መሪ ነበር።ክፍሉ ላለፉት 36 አመታት እና አሁንም በውጭ ሀገር ነው የሚኖረው።ከኢሕአፓ አመራሮች በህይወት የቀሩት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ከነዚያ ውስጥ ክፍሉ አንዱ ነው። በህይወት በመኖሩ የኢሕአፓን ታሪክ ያ ትውልድ በሚል ርእስ በሶስት ተከታታይ ግዙፍ ቅጾች አሳትሟል። ቀደም ባለውም ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ The Generation የተሰኘ መጽሀፍ ስለ ኢሕአፓ ታሪክ አሳትሟል። መጽሀፎቹ በአንባቢያን ዘንድ በእጅጉ የሚፈለጉ ናቸው። ውስጣቸው ብዙ ታሪክ አለ። ትዝታ አለ። ትውልድ አለ። ሞት አለ። ስቃይ አለ። ፖለቲካው፣ አብዮቱ፣ ትግሉ፣ ሽኩቻው…..መአት ነገሮችን የያዘው የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ መጽሀፍ አስገራሚም የህይወት ገጠመኞችንም እናገኝበታለን። ዛሬ ለንባብ የምጋብዛችሁ ክፍሉ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ እንዴት ጠፍቶ እንደወጣ የተረከበትን አስገራሚ ገጠመኝ ነው።

***           ****          ****

ዘመኑ ራቅ ይላል። በ1969/70 ዓ.ም ላይ። የወጣት ሬሳ በየመንገዱ፤ በየጥጋጥጉና በየግድግዳው የሚጣልበት። እኔም አዲስ አበባን ለቅቄ መውጣት ነበረብኝ።ፎቶግራፋቸው በየማዕዘኑ ተበትኖ፤ በተገኙበት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከተወሰነባቸው ሰዎች መሀል አንዱ ነበርኩ። መንግስት የበተናቸውንና የተለጠፉትን ፎቶግፎች ማ እንዳየና ማ እንደሚያውቀኝና እንደማያውቀኝ ግምቱ እንኳን አልነበረኝም። ብቻ አንድ ነገር እንደነበረኝ አውቃለሁ። የወጣትነት ልበ ደፋርነት! አስታውሳለሁ ጥቂት ቀደም ሲል አንድ የማዘወትርበት ቡና ቤት የምትሰራ ሴት፤ ከእኔ ጋር ለሚገናኝ የኢህአፓ አባልን እንዳይቀርበኝ እንዲያውም መጥፎ ሰው ስለሆንኩ እንዲርቀኝ ትነግረዋለች። የት ታውቂዋለሽ ብሎ ይጠይቃታል። ቀበሌ ፎቶግራፌን እንዳሳያት ትነግረዋለች። በዚያ ጊዜ ቀበሌዎችበየቡና ቤት እየዞሩ ለቡና ቤት ሰራተኞች ፎቶግራፎች ካሳዩ በኋላ ድንገት ሰውዬው የሚመጣ ከሆነ ስልክ እንዲደውሉ መመሪያ ይሰጡ ነበር። ታዲያ ጉዋደኛዬ እንደእኔው በትግሉ ውስጥ ነበርና፤ ምስኪን ተራ ነጋዴ ነው። እሱን ማነው የሚፈልገው ብሎ ሊያሳምናት ሞከረ። ለእኔም ጉዳዩን አጫወተኝ። አስፈላጊውን ጥንቃቄ አደረግሁ።

 

ወደ ጀመርኩት ጉዳይ ልመለስና አዲስ አበባን መልቀቅ ነበረብኝ። ለማደሪያነት ወደተዘጋጀልኝ ቤት ሄድኩ። መርካቶ መኪና ተራ አጠገብ ነበር ቤቱ። ቤት ማለት ይቻል እንደሆነ አላውቅም፤ በረት ልበለው!ደግሞ የከብት ማደሪያ አልነበረም። እንደመጋዘን መሳይ ነው።የደረቁ የከብት ቆዳዎች እዚህና እዚያ ተሰቅለዋል።መጋዘኑ በወጉ ግድግዳ አልነበረውምና ነፋስ ያስገባል። በዚያ በረት ውስጥ ያደርነው ሶስት ነበርን። አንደኛውና የቤቱ ባለቤት /የአባቱ መጋዘን ይመስለኛል/ ሙሂዲን ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ባልሳሳት አዛርያስ በሚል ስም ነው የተዋወቀኝ።ይኸኛው እስከ ቅርብ ጊዜ በአሜሪካ በአንድ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እንደነበር አውቃለሁ። የሁለቱም ስም የድርጅት እንጅ እውነተኛ ስማቸው አይመስለኝም። ሁለቱም በአዲስ አበባ የኢህአፓ ከፍተኛ አመራር አባላት ነበሩ። ያንን ሌሊት በጥንቃቄ አደርን። ሁለታችን ስንተኛ አንዳችን በመጠበቅ።

 

ጠዋት ላይ ተነሳሁና ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ መሳፈሪያ ሄድኩ። መናኸሪያውን ጨምሮ ዙሪያ ገባው በወታደርና በአሳሽ ቡድን ተጥለቅልቋል። የአሳሽ ቡድኑ ዋና ስራ በተቃዋሚነት የሚጠረጥሯቸውን መያዝ ነው። ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ መሳፈሪያ አመጣጣቸውም ተቃዋሚ ተሳፋሪዎችን ለመያዝ ነው ። እንደ እኔ ዓይነቱን ማለት ነው። ከያዙ በኃላ የፈለጉትን እርምጃ ይወስዳሉ። ደስ ካላቸው እዚያው ይገድላሉ። ጠያቂ የለባቸውም።የኢሕአፓ አባልን ገደለ ተብሎ ሰው አይከሰስም።አበጀህ ይባላል እንጅ።

 

ከበባ መኖሩን ስረዳ ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ውሳኔ መውሰድ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ዙሪያ ገባው ስለተከበበ ከዚያ መውጣት ከቶም የማይቻል እንደነበር ተገነዘብኩ። መሳፈሬን ተውኩና በአካባቢው እንደነበሩ ሌሎች ሰዎች ወሬ ተመልካች ለመሆን ወሰንኩ። እንደእኔው ብዙ ሰዎች ነበሩና እኔ የወሰድኩት እርምጃ ከሌሎች የተለየ አልነበረም። ወሬ የሚመለከቱ ሰዎች ምንም የሚፈሩት ነገር የለም የሚል ትርጉም ስለነበረው አሳሾቹ አያተኩሩባቸውም። አሳሾቹ አጠገብ ቀረብ ብዬ ስመለከት ዶ/ር ዓለሙ አበበን አየሁ። በህቡእ ትግል አብረን ሰርተናል። እንደ መሪ ከማያቸው ሰዎች አንዱ ሲሆን በፖለቲካ መደራጀት ስንጀምር እኔ የተሳተፍኩበትን የመጀመሪያ ቡድን የመሰረተው ዶ/ር ዓለሙ አበበ ነበር። በ1961 ዓ.ም እሱ ወደ ሀገር መግባቱ ነበርና እኛን አደራጅቶ መሄድ አስፈላጊ እርምጃ ነው ብሎ የገመተ ይመስለኛል። ታዲያ በ1969/70 ዓ.ም ሁኔታዎች ተቀያይረዋል። ዶ/ር ዓለሙ የመንግስት ወገን፤ እኔ ተቃዋሚ፤ እሱ አሳዳጅ፤ እኔ ተሳዳጅ፤እሱ አሳሽ፤ እኔ ታሳሽ ሆነናል።

 

ልክ ዶክተሩን ሳይ አደጋሸተተኝ። እዚያው መኪና ተራ ፊት ለፊት ከሚገኝ አልቤርጎ ሄድኩና መኝታ ያዝኩ። ዘና ብዬ ወንበር እንዲሰጡኝ ጠየቅሁና ደጃፉ ላይ ተቀመጥኩ። ይህን ያደረግሁበት ምክንያትም የምሸሸግ እንዳይመስላቸውና እንዳይጠረጥሩ ለማድረግ ነበር። ልክ በራፉጋ ቁጭ ስል አጎቴ ከየት መጣ ከየት ሳልለው አጠገቤ ደረሰ። መሰወሬን የሚያዉቅ ቢሆንም እዚያ ቦታ በዚያ ሰዓት ምን አደርግ እንደነበረ ጨርሶ ሊገባው የሚችል አልነበረም። በአጠገቤ እያለፈ ዞር ብሎ እንኳን ሳያይ ሄደ። ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ገልመጥ አይልም። ፍዝዝ ብሎ ወደፊት ብቻ ነበር የሚመለከተው። ከላይ እስከታች ጥቁር ለብሷል። ሁለት ልጆቹን ቀይ ሽብር ቀምቶታል። አንደኛው መኩሪያ ተገኝ ይባላል። አቃቂ በሚገኝ የአብዮት ጥበቃ በዱላ ተቀጥቅጦ ነው የሞተው። መኩሪያን በቀበረ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነበር ሌላኛው ልጁ አሸናፊ ተገኝ ከሌሎች የኢህአፓ አባላት ጋር የተያዘው።የመንግስት ወታደሮች የተያዙትንልጆች አቶ ተገኝ ቤት አመጧቸው። አጎቴም ልጄ ሊፈታ ነው ብሎ ደስ ሳይለው አልቀረም። ልጆቹ ወደተያዙበት ክፍል ወስዷቸው። በሆዳቸው አጋደሟቸው። አቶ ተገኝም ወደ ክፍሉ እንዲገባ ተጋበዘ። ገብቶ ቆመ። ወዲያውኑ ወታደሮቹና አብዮት ጥበቃ አባላቱ የቶክስ እሩምታ ከፈቱ። ወጣቶቹ በሆዳቸው የተንጋለሉበት ቀሩ። አቶ ተገኝ የቆመበት ደርቆ ቀረ። አልጮኸም። አላለቀሰም።ትንሽ ቆየት ብሎ ሌሎች ህፃናት ልጆቹን ይዞ መጣና እነዚህንም ረሽኗቸው አለ። ከዚህ አጋጣሚ በኃላ ልሳኑ ተዘጋ። ታዲያ በአጠገቤ ያለፈው ይህ አጋጣሚ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኃላ ነበርና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ ገምቻለሁ። ላናግረው ፈለግሁ። ይሁንና ሁኔታውን እንዴት ሊቀበለው እንደሚችል መገመት ከባድ ሆነብኝና ተውኩት። አቶ ተገኝ አሳሽ ቡድኑን ከመጤፍ የቆጠረ አይመስልም። ብቻ ፍዝዝ እንዳለና ወደ ግንባር እየተመለከተ መንገዱን ቀጠለ። አሳሽ ቡዱኑም እስከ እኩለ ቀን ድረስ አካባቢውን ሲያምስ ውሎ ሄደ። ስራው ውጤታማ ይሁን አይሁን አላወቅሁም። እኔ ተርፌ ቤርጎዬ ገባሁ። አልወጣሁም። ተከርችሜ ውዬ አደርኩ። በበነጋው አውቶቡስ ተሳፈርኩ። ከእኔ ጋር ሌላ የኢህአፓ አባል ነበረና እየተጠባበቅን ነበር የምንሄደው።እንጂ በአደባባይ አንነጋገርም። ይጠብቀኛል፤ እጠብቀዋለሁ። ይህ ጓደኛዬ ኤርትራዊ ሲሆን ቤተሰቦቹ እስላሞች ነበሩ። የተሳፈርኩበት አውቶቡስ ጎሃ ጽዮን ደርሶ ለምሳ ውረዱ ተባልን። ጓደኛዬ ለምሳ ወዴት እንደሄደ አላወቅሁም። እኔ መኪናው ከቆመበት ራቅ ብዬ በመሄድ አንድ ምግብ ቤት ገብቼ ምሳ ጠየቅሁ። ከየት መጣ ከየት ሳልለው አንድ ሰው “አንተ የክርስቲያን ቤት ነውኮ” አለኝ። ዘወር ብዬ ስመለከት ሰውየውን ጨርሶ አላውቀውም። እኔ የነበርኩበት አውቶቡስ ውስጥ የነበረው ሰው መሰለኝ። ትዝ ሲለኝ ማንነቴን ለመቀየር ብዬ የእስላም ኮፍያ አድርጌአለሁ። የለበስኩትም ነጋዴ የሚያስመስል ሳሪያን ኮትና ሰፋ ያለ ሱሪ ነበር። ላየኝ ሰው የከሰረ የእህል ነጋዴ ነበር  የምመስለው። ሰውዬው ለምን እንደዚያ እንደተናገረ ወዲያው ገባኝና ያላወቀ በመምሰል “እረባክህ ቢስሚላሂ” አልኩኝ። ወደ በሩ ወጣሁና ሌላ ምግብ ቤት ፍለጋ ጀመርኩ። ሰውዬውም አምቦውሃ ገዝቶ ሲበር ሄደ።እሱ ሲሄድልኝ ኮፍያዬን አውልቄ በፊት ወደነበርኩት ቤት ተመልሼ በመግባት ምሳዬን በላሁ። አውቶቡስ ልሳፈር ስል ምግብ ማግኘት አለማግኘቴን ሰውየው ጠየቀኝ። ሌላ ቦታ ሄጄ በላሁ ብዬ ዋሸሁ።

 

ሰውየው ለምንና እንዴት ሊያውቀኝ እንደቻለ በመጠራጠሬ አውቶቡሱ ውስጥ ምን ያህል እስላሞች እንዳሉና እነማን እንደሆኑ ቀስ ብዬ አጠናሁ። እኔ ልለያቸው የቻልኩት ስምንት ያህሉን ነበር። እነዚህ ጨርሶ የማላውቃቸውና የማያውቁኝ እስላሞች ለእኔ በህይወት መትረፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።ዝርዝሩን ወደኃላ አነሳዋለሁ። አውቶቡሱ ጉዞ ቀጥሎ ብዙም ሳንርቅ አውቶቡሱ በረሃ ላይ ተሰበረ። እኔና ጉዋደኛዬ በጥቅሻ ተነጋገርንና ራቅ ብለን ሄደን ምን እናድርግ አልን። ሰው እንደሚሆነው ለመሆን ወሰን። ከጓደኛዬ ተለይቼ አውቶቡሱ ወደነበረበት ሄድኩ። አልተሰራም።ሙስሊም የሃይማኖት ወገኖቼ ሲፈልጉኝ ነበር። ለካስ ገና ከሩቅ ሲያዩኝ “የት ጠፋህ አንተ እስላም” ብለው ምግብ ጋበዙኝ። በላሁ። እስላሙ የኢህአፓ ጉዋደኛዬ የሚላስ የሚቀመስ አላገኘም። እኔ ስጋበዝ ያያል። ዝም ነው እንጅ ምን ሊያደርግ ይችላል።

 

አሁንም አውቶቡሱ አልተሰራም። ምሳ ሰዓት ደረሰ። እስላም ወዳጆቼ ምሳ ጋበዙኝ። በላሁ። የለመደች ጦጣ አሉ፤ ተነስቼ ልሄድ ስል ያ መጀመሪያ የእስላም ቤት ነው ያለኝ ሰው ሰላት እናድርግ/እንስገድ/አለኝ። ዓይኔ ፈጠጠ። ከደርግ ተሸሽጌ ለ26 ወራት አዲስ አበባ በተቀመጥኩበት ጊዜ ብዙ ቦታ ረግጫለሁ። ጉራጌ እስላሞች ቤት ኑሬአለሁ። ሰላት ሲያደርጉ አይቻለሁ። ይሁንና ስነ-ስርዓቱን ጠንቅቄ አልተረዳሁም። ታዲያ አሁን ሰላት እናድርግ ሲለኝ ሰውዬው ባልተጠረጠረው እንዳለው ሆነ።

ጨዋታው እንዲህ ነው። የገጠር ሰው ነው። ከሚስቱ ይፋታል።ትከሰዋለች። ከቀጠሮ ቀን በፊት አቦካቶው/ጠበቃው/ ይመክረዋል። እንዲህ ሲሉህ እንዲህ በል፤ ይህንን ሲጠይቁህ ይህንን መልስ እያለ ቀኑ ደረሰና ሰውዬው ዳኛ ፊት ቀረበ። ስሙን ተጠየቀ። መለሰ። የሚስቱን ስም ተጠየቀ። ወደ መሬት አቀረቀረ። ወደ ላይ አንጋጠጠ። ትንሽ ቆየ። የሚስት ስም ከየት ይምጣ!? እንደ አብዛኛው የገጠር ሰው ሚስቱን በስሟ ጠርቷትም አያውቅም። አንቺ ነው የሚላት። ታዲያ ወደ አቡካቶው ዞር ብሎ “ጌታው ባልተጠረጠረው መጡብን” አለ ይባላል።

 

እኔ ባላሰብኩትና ባልጠረጠርኩት መንገድ ፈተና ገጠመኝ። ሰላት የማያደርስ እስላም ምን ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ባላገናዝብም ገበናዬ ሊጋለጥ ሆነ። እጅግ ፈጣን በሆነ መንገድ አሳማኝ መልስ መስጠት ነበረብኝ።“ጉዞ ላይ ሰላት ማታ ብቻ ነው የማደርገው” አልኩት። ይመነኝ አይመነኝ አላወቅሁም። ብቻ አየት አደረገኝና ስግደቱን ቀጠለ። ከአጠገቡ ራቅሁ። ተጠራጥሮአል መሰለኝ ጥቂት ቆየት ብሎ የት እንደምሄድ ጠየቀኝ።“ጎንደር” አልኩት። ከእነማን ዘንድ አለኝ። የሆነ ሰው ስም ሰጠሁት። አወቀው።“ክርስትያን ነውኮ” አለኝ።“የጋብቻ ዘመድ” ነው አልኩት። አሁንም አመለጥኩ ወይም ያመለጥኩ መሰለኝ።

 

አውቶቡሱ ተሰርቶ ጉዞውን ቀጠለ። ጎንደር ከተማ ከመድረሳችን በፊት ጥቂት ኪሎሜትር ሲቀረን የአብዮት ጥበቃ አባላት አስቆሙን። ሰው ሁሉ ከአውቶብስእንዲወርድ ከተደረገ በኃላ እየተፈተሸና መታወቂያውን እያሳየ እንዲገባ ተደረገ። እኔና ሌላ አንድ ሰው አትሳፈሩ ጠብቁ ተባልን። እንዳልሳፈር የከለከለኝ የአብዮት ጥበቃ ሃላፊው ሽባባው የሚባል ነበር። መታወቂያ ደብተሬን አልተጠራጠረም። መታወቂያ ደብተሬ ከሰሜን ሸዋ ከአንድ ትንሽ የገጠር ከተማ/ገምዛ/ የወጣች ናት። ያጠራጠረው መሸኛ ደብዳቤው ነው። የፋይል ቁጥር የተስተካከለ አልነበረም። ወይም የሚጎድለው ነገር ነበር። ሽባባው ስለችግሩ ጠየቀኝ። ማንበብና መፃፍ የማልችል ምስኪን ሰው ሆኜ ቀረብሁ።“እኔ ምን አውቃለሁ የሰጡኝን ነው ተቀብዬ የመጣሁት” አልኩ። ሌላው አውቶቡስ ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለው ሰው ለጦርነት ጅጅጋ ዘምቶ የመጣ ዘማች ነው። አዲስ አበባ ደውሎ እንደሚያጣራ ሽባባው ነገረን።

 

ኢህአፓው ጓደኛዬ ደነገጠ። አጠገቡ የተቀመጠውን ሰው ከሁኔታው ባለስልጣን ወይም የፀጥታ ሰራተኛ ይሆናል ብሎ ገመቶ ነበርና “ይሄን ምስኪን እስላም ያዙትኮ”ይለዋል። ለሾፌም ተመሳሳይ ነገር ነገረ። እስላሞቹም ግልብጥ ብለው ከአውቶቡሱ ወረዱ። ይሄ ምስኪን እስላም ምን አደረገ እያሉ። ሽባባው የሚበገር አልሆነም።አልለቃቸውም አለ።እስላም ወገኖቼ፤ ሾፌሩ፤ የፀጥታ ሠራተኛው ሁሉም በአንድነት ተንጫጩ። እኔ ነገር ዓለሙ የዞረበት ነጋዴ መስዬ ጥጌን ይዤ ቆሜአለሁ። ለሚያየኝ ሳላሳዝን አልቀርም። ሽባባው ልቡ ራራ።“ሂድ ግባ ለሁለተኛው እንደዚህ ዓይነት ወረቀት ይዘህ እንዳትንቀሳቀስ!” አለኝ። እሺ አልኩ። ሽባባው ፊቱን ወደ ሚሊሽያው አዙሮ “አንተን አለቅህም! ገና ከአዲስ አበባ አጣራለሁ” አለው። ሚሊሽያው ሰውነቱ ፈርጠም ያለ ሲሆን እንደ ሽባባው ያለ የመንደር አውደልዳይ እኔን ዘማቹን እንዴት ሊጠይቀኝ ይችላል የሚል ስሜት አድሮበታል መሰለኝ ሽባባው የሚጠይቀውን በስነ-ስርዓት አይመልሰም። ያበሻቅጠዋል። የአካባቢው ንጉስ ነኝ ብሎየሚያስበው ሸባባው፤ ስለተደፈረ በጣም ተናደደ።እልህ ውስጥ ገባ። ነገርን ነገር እየወለደ ሚሊሽያውም ተናደደ። ተሳደበም። ሚሊሽያው  ቀረ። አውቶቡሱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሾፌሩም ጭምር ለእሱ መቅረት ቁብ አልሰጡም። አውቶብሱም ተንቀሳቀሰ። ሁሉም ደስ አለው። ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ምስኪኑ እስላም የውይይት ርእስ ሆነ።

 

ጎንደር ከተማ ነው።የተለያዩ ስራዎች አከናውኜ በከተማው ከታወቀ አንድ ኢህአፓ አባል ጋር እየተወያየን በጉራንጉር መንገድ እንዳለን ከበስተኋላዬ ድምጽ ሰማሁ። እኔን አልመሰለኝም። ገልመጥ ብዬ ካየሁ በኃላ መንገዴን ቀጠልኩ። ብቻ ከአንድ ሱቅ በራፍ ላይ አንድ ሰው ቆሞ አየሁ። ሰውየው ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጣራል። ሰውዬው ተጠጋን።“አንተ እስላም፤ አንተ እስላም” ይላል። እኔ እስላምነቴን ረስቼዋለሁ። ለማንኛውም ተጠራጠርኩና ዳግመኛ ዞር አለኩ። አብሮኝ የነበረው የኢህአፓው ሰውም እንደእኔው ዞር ብሎ ቆመ። አንተ እስላም እያለ ይጣራ የነበረው ሰው ወደ እኔ መምጣቱን በቅጽበት አቆመ።የቆመበት ደርቆ ቀረ። እረ!እረ! አለ። ከላይ እንደገለጽኩት አጠገቤ የነበረው በጎንደር የታወቀ የኢህአፓ አባል ነበር።ደግሞም እስላም ነበር። የአውቶቡሱ ጓደኛዬን እኔ ከዚህ ሰው ጋር ስሄድ ማየቱ ጭንቅላቱን መታው መሰለኝ ምንም አላለም። ፊቱን አዙሮ ተመልሶ ወደ ሱቁ ገባ።ተከተልኩት።ሰላም ልለው። ሰላምታዬን አልመለሰልኝም። ምን ያሰላስል እንደነበረ ግን ገምቻለሁ። እንደ እንቆቅልሽ ሆነውበት ለነበሩ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኝ አልቀረም።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
7128 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us