ጥላሁን ገሠሠን ሳስታውሰው…

Wednesday, 20 April 2016 13:08

 

በጥበቡ በለጠ

 

ይህ ከላይ የምትመለከቱት ፎቶ የጥላሁን ገሠሠ እና የኔ ነው። ፎቶው እኔ ስዘፍን ጥላሁን ገሠሠ የሚያዳምጠኝ ይመስላል። አስቡት፤ እኔ ዘፋኝ ሆኜ ጥሌ ሲያዳምጠኝ፤ ብቻ ይህን ፎቶግራፍ የተነሣነው ታህሳስ 4 ቀን 1995 ዓ.ም ነው። ቦታው መሿለኪያ በሚገኘው በጥላሁን ገሠሠ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ ውስጥ ባለችው በግሉ ቢሮ ውሰጥ ነው። 13 አመታት። ጊዜው ይነጉዳል። ጥሌ እራሱ ከተለየን ሰባት አመታት ተቆጠሩ። ልክ የዛሬ ሰባት አመት የኢትዮጵያው የሙዚቃ ንጉሥ ዜና እረፍቱ ተሰማ!

 

የዛሬ ሰባት አመት እሁድ ምሽት በትንሳኤ ቀን አርፎ፣ ሰኞ ማለዳ ላይ ሚያዚያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም ጥላሁን ገሠሠ ሞተ ሲባል ማን ይመን? ይሔን ወሬ እንዴት ማመን ይቻላል? ምክንያቱም ከሃምሣ ስድስት አመታት በላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እጅግ እየተወደደ የኖረ ጽምፀ መረዋ፣ ሐገር ወዳድ፣ በአቋሙ የሚፀና ምርጥ ከያኒ እንደዋዛ ተለየን ብለን እንዴት እንመን? ግን ዜናው መራር እውነት ነበር።

 

አንድ ከያኒ በሕዝብ ልብ ውስጥ ለዘላለም ከሚኖርባቸው ምክንያቶች መካከል ለሐገሩ፣ ለወገኑ ያለው ፍቅር እና ይሔንንም ፍቅሩን የሚገልፅበትም መንገድ ነው። ከዚህ አንፃር ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ የሐገር ፍቅር ሞዴል ነው። የጥላሁን መገለጫ ኢትዮጵያ ናት። ገና ከጥንት ከጥዋቱ ያቀነቀናት ዘፈኑ ዛሬም ሕያው ናት፡-

 

ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ

ኩራት ይሰማኛል ካንቺ መፈጠሬ

 

 እያለ የዛሬ 50 አመታት ዘፍኗል። የዘፈኗ ግጥም ደራሲ ኢዮኤል ዮሐንስ ነበሩ።

ጥላሁን የኢትዮጵያን ፍቅር ሲያዜም የፍቅሮች ሁሉ ታላቅ ፍቅር ሆኖ ኃይል አለው። እሱ ራሱ ኢትዮጵያን ሲጠራ ዐይኖቹ በአራቱም ማዕዘን ዕንባውን መቆጣጠር ይሣናቸዋል።

 

ትዝታው ገንፍሎ ዕንባዬ እያነቀኝ

የሀገሬ ሽታ ጠረኑ ናፈቀኝ

 

እያለ እያለቀሰ ይዘፍናል። እኛንም ያስለቅሰናል።

ጥላሁን ኢትዮጵያ የምትባልን ሐገር 56 አመታት ሙሉ በዜጐቿ ልብ ውስጥ ሲገነባ የኖረ ከያኒ ነው። ለምሳሌ ሐገሬ ኢትዮጵያ በሚለው ዘፈኑ ሌላ የፍቅር ዕንባውን እያነባ ነበር የሚዘፍነው፡-

 

ሐገሬ--ኢትዮጵያ--ለምለሟ አበባዬ

ሳይሽ እርግፍ እርግፍ ይላል ዕንባዬ

 

 እያለ አልቅሶ ያስለቅሰናል።

ጥላሁን ኢትዮጵያን የፍቅር ወጥመድ፣ የፍቅር መገለጫ፣ ተምሣሌት፣ አድርጐ በድምጹ፣ በፊቱ፣ በተክለሰውነቱ፣ በሁለመናው ይገልፃታል። ኢትዮጵያ የፍቅር ቁንጮ ሆና ብቅ ትላለች።

 

ክብሬ እናቴ ሐገሬ የእኔ መመኪያዬ፣

አንቺው ነሽ ኢትዮጵያ መከታ ጋሻዬ።

 

እያለ ሲያዜም አብሮት የማያነባ የለም። የዚህችን አገር ዜጐች በሐገራቸው ፍቅር እያስተሣሠረ፣ በጥበብ እያጣመረ፣ ኢትዮጵያን ያኖረ ታላቅ ከያኒ ነው። ሰው ለሀገሩ ኢትዮጵያ ራሱንም ማንነቱንም እንዲሰጥ የማድረግ አንዳች ኃይል ያላቸውን ዜማዎች እንዲህ እያለ ያንቆረቁራል፡-

 

“ጥቃትሽን ከማይ በሕይወቴ ቆሜ፣

ስለ ክብርሽ እኔ ልሙት ይፍሰስ ደሜ።”

 

ሐገር ማለት መስዋዕትነት የሚከፍሉላት ረቂቅም ግዑዝም ሆና የምትቀርብ ናት። ሰዎች ቢመጡም ቢሔዱ የጥላሁን ሐገር/ኢትዮጵያ/ ሁሌም እንደምትኖር፣ ገና… ገና ብዙ ዘመናት ታሪኳ፣ ገድሏ እንደሚዘከርላት ጥላሁን ያዜማል።

 

“ታሪክሽ ተወርቶ ባያልቅም ባጭሩ፣

በሕይወት ያሉት ሊቆች ይመሰክራሉ።

ጥንት ያለፉትንም በጀግንነታቸው፣

ታሪክ አይረሳውም ይነሣል ስማቸው።

 

ምን አይነት ግጥም፣ ምን አይነት ዜማ፣ ምን አይነት ድምፅ፣ ምን አይነት አቀራረብ እንደሆነ መግለፅ ያቅተኛል። ገጣሚው፣ ዜማ አውጭውና ድምፃዊው ፍፁም የተዋሃዱበት ልዩ ሙዚቃ። ኢትዮጵያ እየረቀቀች እየገዘፈች ወደ ላይ የምትወጣበትና ያረገች እስኪመስለን ድረስ ጥላሁን በእንባው እየታጠበ ይመሠክርላታል።

ጥላሁን ገሠሠ ለዚህች ኢትዮጵያ ብለን ለምንጠራት ታሪካዊት ሐገር እና የጀግኖች ደብር ለሆነች ምድር “አጥንቴም ይከስከስ” እያለ ሲያዜም ሁሌም ሰው አብሮት ያዜም ነበር።

 

አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት

ይህቺን አገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት

 

እያለ በታላቅ ወኔ፣ በታላቅ ግርማ ሞገስ ብቅ ሲል ምድር ቀውጪ ትሆን ነበር።

 

ጥንት አባቶቻችን ዛሬም ልጆቻቸው

ጀግንነት ወርሰናል ከደም ከአጥንታቸው።

ስለዚህ አንፈራም ግዴለንም እኛ

ቆርጠን ተነስተናል እኔን ትተን ለእኛ

 

ይህን የጥላሁን ገሠሠ አስገምጋሚ የሐገር ፍቅር ወኔ የሚሰማው ሴት ወንዱ፣ ሕፃን አዋቂው ሁሉ ሌላ የከፍታ መንፈስ ውስጥ ገብቶ ሲዋኝ ዛሬም በአይነ ሕሊናዬ ይመጣል።

 

የሐገሬ ጀግኖች ሴት ወንዱ ታጠቁ

ከእንግዲህ ለጠላት አንተኛም ንቁ።

ጀግንነት እንደ ሆነ የአባቶቻችን ነው

ህብረታችን ፀንቷል ድል መምታት የኛ ነው።

 

የጥላሁን ገሠሠ እና የኢትዮጵያ ፍቅር የተገማመደ፣ የተሣሠረ፣ የተቆላለፈ ግን ደግሞ የጠነከረ አለት ነው። በምንም አይተካም።

አንድ ግዜ 1993 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ኢትዮጵ በተሰኘ ታዋቂ መጽሔት ላይ ቃለ-መጠይቅ ተደርጐለት ነበር። ጋዜጠኛው አንድ አስደንጋጭ ጥያቄ ለጥላሁን አቀረበለት። እንዲህም አለው፡-

 

ኢትዮጵ፡- አንድ ነገር ትዝ አለኝ። በ1985 ዓ.ም ይመስለኛል አንተ ወደፊት በሉለት ይለይለትን እየዘፈንክ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምስልህን ወደ ኃላ ሲመልስ ታይቷል። ያን ሁኔታ ስትመለከት ምን ተሰማህ?

 

ጥላሁን፡- እኔ ጥላሁን!? ---ጦር ግንባር ሆኜ ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ ወደፊት እንጂ ወደ ኃላ አልልም! የተንቀለቀለ እሣት ውስጥ ገብቻለሁ። ወደ ኃላ ያልኩበት ጊዜ የለም። ምናልባት ተቃራኒው ክፍል ያን ታክቲክ ይጠቀምበት ይሆናል እንጂ እኔ ወደፊት ብዬ ወደኋላ እየሸሸሁ ምን አይነት መዋጋት ይሆናል!-- በሀገሬ ላይ ለሚመጣው ነገር!--አሁንም ቢሆን ወደፊትም ቢሆን!ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማልል እንድታውቅ እፈልጋለሁ።

 

ኢትዮጵ፡- መልካም ጥላሁን !--አንተ የምትጨምረው ነገር ወይም ለማለት የምትፈልገው ነገር ካለ እድል ልስጥህ

ጥላሁን፡-ምንም የምጨምረው ነገር የለም። ግን አሁን አንተ ስትጠይቀኝ-- ትንሽ የተሰማኝና የደም ስሮቼን ልታቆመው የቻልከው በአሁኑ አነጋገርህ ነው። እና--

 

ኢትዮጵ፡- እኔ እኮ አይደለሁም ያ…

ጥላሁን፡- ገባኝ!-- ባዮቹም ቢሆኑ ደካሞች ናቸው። እኔ ወደኃላ ብዬም አላውቅም። ምናልባት ይሄን ለማለት የሚፈልግ ካለ ይበል። እኔ ግን ምን ግዜም!-- ደረቴን እንጂ ጀርባዬን ለጥይት ሰጥቼ አልኖርኩም። ያን ሁሉ--ለጥይት እየጋበዝኩ-- እኔ ራሴን ወደኃላ?!--እንዴት ይታሰባል?!---ሊሆን የማይችል ነገር ነው!

 

(ኢትዮጵ መጽሄት መጋቢት ወር 1993)

ጥላሁን ገሠሠ እንዲህ አይነት ወኔያም ከያኒ ነው። ጀግና ነው። በየጦር ግንባሩ እየሔደ ደረቱን ለጥይት ሠጥቶ የሚዘፍን ድምፃዊ አርበኛ ነበር።

 

በ1995 ዓ.ም እቢሮው ሔደን ቃለ-መጠይቅ ያደረግንለት ቀን ዛሬም ትዝ ትለኛለች። ከኔ ጋር ሁለት ጓደኞቼ አብረውኝ ነበሩ። አንዱ ጋዜጠኛ አብይ ደምለው ሲሆን ሁለተኛው ድሮ ጐበዝ የጋዜጣ አዘጋጅ የሆነውና አሁን ደግሞ የባንክ ሰራተኛ የሆነብን ሙሉጌታ አያሌው ነው። ከጥላሁን ጋር  ግማሽ ቀን ያህል ውብ ጊዜ አሣለፍን። ከዚያም በተደጋጋሚ እንገናኝ ነበር። ብዙ ቃለ-መጠይቅ አድርገንለታል። አሁንም ከአብይ ጋር ስንገናኝ የጥላሁንን ድምጹን እየሰማን ከትዝታው ጋር እናወጋለን።

 

ዛሬ ዜና ዕረፍቱ የተሰማበት ቀን ነውና እስኪ ስለ ጥላሁን ወግ እናውጋ። ጥላሁን የሕዝብ ልጅ ነው። ገና ከ13 አመቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እናትና አባት ሆኖ ያሣደገው ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ አንቀልባ ላይ ሆኖ ያደገ ነው። ታዲያ እንዲህም ሆኖ ጥላሁን ምስጢርም ነው። ተፈትቶ ያላለቀ። ሆድ ይፍጀው ሆኖ ኖሮ ያለፈ። ዛሬም ሆድ ይፍጀው የሆነ።

 

አንገቱ በስለት ተቆርጦ ከሞተ ደጃፍ እና አፋፍ ላይ በተአምር ተርፎ ሆድ ይፍጀው የሆነ ሰው ነው። ጥላሁንን ማን ነው አንገቱን የቆረጠው? ምስጢሩ ለሕዝብም ለሐገርም ሆድ ይፍጀው ሆኖ ቀርቷል። ግን እኮ መርማሪ አጥቶ ነው  እንጂ አደጋውን የፈፀመው አካል ይታወቃል። ጥላሁንን አንገቱን በስለት ያስቆረጠው አካል በፖሊስ የምርመራ ማሕደር ውሰጥ ይገኛል። በእለቱ ድርጊቱን የፈፀመው አካል ማን እንደሆነ የፖሊስ መዝገብ ውስጥ ይገኛል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። ግን ጥላሁን ገሠሠ ያንን አካል መግለፅ ስላልፈለገ ጉዳዩ ታፍኖ ዛሬም ድረስ አለ።

 

የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክን በተመለከተ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር፣ የኢትዮጰያ የሙዚቃ ንጉስ በሚል ርዕስ ጥላሁን ከሞተ በኃላ የችኮላ ስራ ሠርቶ አሣትሟል። ዘካሪያ አሕመድም የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ ከቤተሰቡ ያገኝሁት ሰነድ ነው ብሎ አሣትሟል። ኤሚ እንግዳ ደግሞ ጥላሁን ከሞተ በኃላ ‘The King’s Farewell’ የተሰኝ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርታለች። በአማርኛ የንጉሡ ሽኝት እንደ ማለት ነው። ሁሉም የራሣቸው ደካማና ጠንካራ ጐኖች ቢኖሯቸውም ‘የሆድ ይፍጀው’ ነገር እስከ አሁንም እንደ ተዳፈነ ነው።  

 

ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግ የመስዋዕትነት ትግል ካደረጉ ከያኒያን መካከል በግንባር ቀደምትነት ስሙ የሚጠራ ነው። ምክንያቱም ለሙዚቃ ጥበብ ትልቁን ድርሻ እያበረከተ ለዚህ ልፋቱ ደግሞ የሚያገኛት የወር ደመወዝ እጅግ አስገራሚ ነበረች።

 

ለምሳሌ በ1949 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ስለ ጥላሁን ገሠሠ የተፃፈውን ደብዳቤ መመልከቱ ብቻ ብዙ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። የፃፈው ደግሞ ባሕልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር ነው። እንዲህ ይላል፡-

“ስለ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ወልደ ኪዳን ከ1946-1949 ዓ.ም ቋሚ ሠራተኛ ስለመሆናቸውና በየወሩ የሚያገኙት ደሞዝ ልክ እንዲገለፅላችሁ በጠየቃችሁት መሰረት፣

 

-    በየወሩ ብር 30 ደሞዝ ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን

-    ቋሚ ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ያላገኘን መሆኑን እንገልፃለን”

ከሰላምታ ጋር

 

 

ጥላሁን ገሠሠ መድረክን እና ሕዝብን እንዲሁም ሀገርን እያስደሰተ የሚከፈለው የወር ደመወዝ 30 ብር ብቻ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ቋሚ ሠራተኛ ይሁን፣ አይሁን አይታወቅም። እርሱም ስለ ገንዘቡ እና ስለ ስራው ቅጥር የሚያስብ አልነበረም። የእርሱ ጭንቀት የተዋጣለት ሙዚቃን መድረክ ላይ መጫወት ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ በነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ተፅዕኖ ወደ ክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ እንዲቀላቀል ተደረገ። እዚያ ሲገባ በተወሰነ መጠን ደሞዙ ተጨመረለት። የህይወት ታሪኩን በሚገልፀው መፅሐፉ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ክቡር ዘበኛን ሲቀላቀል እንዲህ በማለት ገልጾታል።

 

“ለምሳሌ የእኔ ደሞዝ 40 ብር ሲሆን፣ እውቋና ሕዝብን ከመቀመጫው ትፈነቅለው የነበረችው የብዙነሽ በቀለ ደሞዝም 80 ብር ነበር። የእሷ እንዲያውም እጅግ ከፍተኛ ደሞዝ በመሆኑ እንቀናባት ነበር። በተረፈ ለቡድኑ ስም እንጂ ለግል ስምና ዝና ማን ተጨንቆ? ምክንያቱም ኑሮ በጣም ርካሽ ነው። ለምሳሌ ሽንጥ ሥጋ አምስት ብር፣ አንድ መለኪያ ውስኪ 0.05 ሳንቲም፣ ቆንጆ እራት 0.30 ሳንቲም፣ ኩንታል ማኛ ጤፍ 24 ብር፣ ኬክ 20 ሳንቲም መግዛት እንችላለን። ስለዚህ ደሞዝ ተጨመረ፣ ቀረ ምን ያስጨንቃል? ብሏል።

 

 

ጥላሁን ገሠሠ የኖረበትን ዘመን እያወደሰ፣ እያቆለጳጰሰ እያደናነቀ የኖረ ሰው ነው። ምንም መከራ እና ስቃይ ቢደርስበትም ተማሮ አይገልጸውም። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር በቂዬ ነው እያለ ምድረ ላይ ያለ ሀብት እና ንብረት ሳያፈራ ያለፈው። ሐብት ንብረቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እያለ ኖሯል።

 

እነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገው ሳይካላቸው ቀርቷል። ታዲያ በዚያ ወቅት ጥላሁን ገሠሠን የፀጥታ ሰዎች ወደ ኮልፌ በመሔድ በቁጥጥር ስር አዋሉት። ከዚያም ከኮልፌ እስከ አራተኛ ክፍለ ጦር ድረስ በሰደፍና በርግጫ እየደበደቡት አመጡት። ጥላሁን ምን ቢያደርግ ነው እንዲህ የተደበደበው ማለታችሁ አይቀርም። ጉዳዩ ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉት።

 

በ1995 ዓ.ም ጥላሁን ገሠሠ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት ለአዲስ ዜና ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ባይወልዱኝም እንደ አባት እና ወላጅ ሆነው ስርዓት ይዤ ለተሻለ ደረጃ እንድበቃ ብዙ የጣሩልኝ ሰው ናቸው። እኔም ወላጆቼ በቅርበት በአጠገቤ ስለሌሉ እርሳቸውን እንደ አባት ነበር የምቆጥራቸው። ከርሳቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረኝ። በዚህ የተነሳ እና በዘመኑ “ጩኸቴን ብትሰሚኝ” እያልኩ ዘፍኜ ነበር። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ከመፈንቅለ መንግስቱ መክሸፍ በኋላ እኔም ተይዤ በጥፊ፣ በርግጫ፣ በሰደፍ እየተመታሁ ከኮልፌ እስከ አራተኛ ክፍለ ጦር ድረስ መጣሁ። እዚያ ስደርስ ጀነራል ፅጌ ዲቡ ተረሽነው አስከሬናቸው አስፋልት ላይ ተዘርግቷል። እርሳቸውም በጣም የማከብራቸውና የማደንቃቸው ሰው ነበሩ። እንደተራ ሰው መንገድ ላይ ተዘርግተው ሳይ የራሴን ድብደባ እና ሕመም ረሳሁት። ይዘውኝ የመጡት ወታደሮች መንገዱ ላይ የተዘረጉት አስክሬኖች ላይ ውጣባቸው አሉኝ። ይህ እንዴት ይሆናል ብዬ ብጠይቃቸው አናቴን በሰደፍ መቱኝ። ከዚያ ያደረኩትን አላውቅም። በመጨረሻም እስር ቤት ተልኬ ብዙም ጉዳት ሳይደርስብኝ ተለቅቄያለሁ” ብሏል።

 

ጥላሁን ገሠሠ በርካታ ችግሮች በሕይወቱ ላይ እየተጋረጡ ሲመጡ ተቋቁሞ የኖረ ነው። ሀገሩ ኢትዮጵያን አንድም ቀን የመክዳትና የመራቅ ሁኔታን ሳያሳይ አፈሯን፣ ምድሯን፣ ህዝቧን፣ ታሪኳን፣ ማንነቷን እያወዳደሰ 68 ዓመታት ኖሮባት በክብር የተሸኘ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ ብሔራዊ አርማቸውን እንዲወዱ፣ ብሔራዊ ማንነታቸውን እንዲያከብሩ፣ የሀገር ፍቅር ዜማዎችን ሲያቀነቅን የኖረ እና ኢትዮጵያ ሐገሩን ከፍ ከፍ ሲያደርግ የኖረ ተወዳጅ ድምፃዊ ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ የሀገሩን ዜጎች ሁሉ በያሉበት እየዞረ የሚያስደስት ተወዳጅ ከያኒ ነው። ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በሚካሄደው የኢትዮጵያዊን የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ከምስረታቸው ጀምሮ ለ17 ተከታታይ አመታት አንድም ጊዜ ሳያቋርጥ ወደ አሜሪካ እየሔደ ተሰባስበው የሚጠብቁትን የሀገሩን ልጆች ያስደስት ነበር። የሚገርመው ይሄ ብቻ አይደለም። በስኳር ሕመም የተነሳ አንድ እግሩ ከተቆረጠ በኋላም ያስለመድኳቸውን ሙዚቃ አላቆምም ብሎ በዊልቸር እየተገፋ ወደ መድረክ ወጥቶ አዚሟል፤ አስደስቷል። በዊልቸር እየገፋው ወደ መድረክ ያመጣው ደግሞ እጅግ የሚወደው የሙያ ጓደኛው መሐሙድ አህመድ ነው።

 

 

አንድ ወቅት ማለትም በ1995 ዓ.ም የሙያ ጓደኛው የሆነው መሐሙድ አህመድ ለጥላሁን ገሠሠ ያለውን ወዳጅነት ስጠይቀው የሚከተለውን ብሏል። “እኔና ጥላሁን አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ሔደን ነበር። ወሊሶ አያቱ አሉ። እርሳቸውጋ ተጫውተን ስንወጣ ጥላሁን ገሠሠን ሰላም የሚለው ሰው በዛ። በረንዳ ላይ ከሁሉም ጋር ይጫወታል። በዚህ ጊዜ አያቱ እኔን ወደ ጓሮ ወሰዱኝና ሳር ከመሬት ነጭተው በእጄ አሲያዙኝ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ። “በምድር የሰጠሁክን በሰማይ እቀበልሃለሁ። ጥላሁን እናትም አባትም የለውም። እህት ወንድም የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። ልጄን አደራ። አንተ ነህ ወንድሙ፤ አንተ ነህ ያለኸው! ብለውኛል። ይሔን ታሪክ ለጥላሁን ገሠሠ ነግሬው አላውቅም። ገና ዛሬ ለናንተ መናገሬ ነው። ግን ሁልጊዜ ይሄ አደራ አብሮኝ ስላለ ጥላሁን ገሠሠ በሄደበት ሁሉ እኔ ከጀርባው አለሁ። የአደራ ጓደኛዬ ነው። (ከለቅሶ ጋር)

 

 

ጥላሁን ገሠሠ ሌላም አስገራሚ ትውስታ አለው። በዚሁ በ1995 ዓ.ም በሰጠው ቃለ -መጠይቅ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያምን በጣም እንደሚወዳቸው ተናግሯል። ለምን ወደድካቸው ተብሎም ተጠይቆ ነበር። ሲመልስም እርሳቸው ለእሱ (ለጥላሁን ገሠሠ) አክብሮትና ፍቅር እንዲሁም አድናቆት ስለነበራቸው እንደሆነ አውስቷል። በተለይ ጦር ሰራዊቱ ወደሚገኝበት ግንባር እነ ጥላሁን ገሠሠ ሊዘፍኑ በሚጓዙበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ ጥላሁን ገሠሠን ይጠሩትና ምክር እንደሚሰጡት፣ አንዳንዴ ደግሞ እራትም ሆነ ምሳ በቤተ-መንግስት እንደሚጋብዙት ጥላሁን ገሠሠ ተናግሮ ነበር። በነዚህ ምክንያቶች ለፕሬዝዳንት መንግስቱ ፍቅር አለኝ ብሏል።

 

 

የጥላሁን ገሠሠን የሕይወት ታሪክ በሚዘክረው መፅሀፍ ውስጥ ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ ደቡብ አፍሪካ ሆስፒታል ውስጥ እግሩ ተቆርጦ ነበር። በዚህ በእግሩ መቆረጥ ክስተት ውስጥ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። ጥላሁን እንዲህ ያስታውሰዋል።

“የአንድ ቀኑ የስልክ ጥሪ ግን የሚደንቅ ነበር። ካረፍንበት ሆቴል ምሳ ለመብላት ሮማን ተሽከርካሪ ወንበሬን እየገፋች ወደ ምግብ አደራሹ ሄድን። እንደደረስንም ከምግብ በፊት የምወስዳቸውን መድሃኒቶች ሮማን እረስታ ኖሮ ለማምጣት ተመልሳ ወደ መኝታ ክፍላችን እንደደረሰች ስልኩ መጮኽ ይጀምራል። አንስታም ‘ሀሎ’ ስትል የሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ረዳት እንደሆነና ሊቀመንበር መንግስቱ እኔን ማነጋገር እንደሚፈልጉ ይነገራታል። እሷም ከአምስት ደቂቃ በኋላ መልሰው እንዲደውሉ ትነግራቸውና ስትበር ወደ አለሁበት በመምጣት፣ “ሊቀመንበሩ በስልክ ሊያነጋገሩህ ይፈልጋሉ” አለችኝና ይዛኝ ወደ መኝታ ክፍላችን ሔድን። እንደገባንም ስልኩ ይጮኻል። ሮማን ስልኩን አንስታ አቀበለችኝና ሃሎ! ስል፣ “መንግስቱ ኃይለማርያም ነኝ ጓድ ጥላሁን! እንኳን እግዜር አተረፈህ” አይዞህ! ለሀገርህ በሚገባ ሰርተህበታል” ከዚህ በኋላ ማራቶን አትሮጥበት፤ ተወው ይቆረጥ! በርታ አሉኝ። ማመን ነው ያቃተኝ። እኔም ስለ ደወሉልኝ ምስጋናዬን አቅርቤላቸው በዚሁ ተለያየን።n

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
11883 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us