ንጉሥ ኃይለሥላሴ እና የራስታዎች እምነት

Monday, 02 May 2016 16:05

በጥበቡ በለጠ

 

የዛሬ ሃምሳ ዓመት በጃማይካዊያን ዘንድ እጅግ ልዩ ወቅት ነበረች። ምክንያቱም እንደ አምላካቸው የሚያዪዋቸውና የሚቆጥሯቸውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በዓይናቸው ያዩበት ዓመት ነው። ኪንግስተን ጀማይካ ውስጥ የራስታዎች መሲህ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ከሰማይ ወደ ምድር በአውሮፕላን ወረዱ። ምድር ቀውጢ ሆነች።

እ.ኤ.አ ሚያዚያ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የራስ ተፈሪያዊያን ዓመት ተብሎ ይጠራል። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በአይናቸው ያዩበት፣ እኚሁ ንጉስ ጀማይካን ከረገጡ በኋላ ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿ ተባርከዋል ብለው ያመኑበት ወቅት ነው። በዓለም ላይ ያሉ የራስ ተፈሪያዊያን ተከታዮች አብዛኛዎቹ መሲሃቸውን ለማየት ኪንግስተን ከተሙ። ታላላቅ ስም እና ዝና ያላቸው ሰዎችም ቀደም ብለው ኪንግስተን ገብተዋል። ግዙፎቹ የዓለማችን ሚዲያዎች ኪንግስተንን አጨናንቀዋል። ሰማዩ የራስታዎችን መሲህ ሊያመጣ ሲል ድንገት ዳመና ወረረው። ለበርካታ ዓመታት የዝናብ ቆሌ የራቀው ኪንግስተን እርጥብ ዝናብ ማውረድ ጀመረ። አየሩ ጀማይካ ላይ ተቀየረ። እውነትም መሲሁ መጣ ብለው የበለጠ አመኑ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ኪንግስተን ላይ ከምትታየው ቀስተ ደመና ጋር ተመሳሰለ። የሀገሬ ሰው የማርያም መቀነት የሚለው ቀስተ ደመና የኢትዮጵያም ሰንደቅ አላማ ነበር። ይህ ሰንደቅ አላማ ኪንግስተን ላይ በየቦታው ይውለበለባል። ራስታዎች ደግሞ የጭንቅላታቸው ቆብ፣ ልብሳቸውና መላ ተፈጥሮአቸውን ከዚህ ሰንደቅ አላማ ጋር የማያያዝ ልማድ አላቸው። እናም የካሪቢያኗ ሀገር ጀማይካ በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተሽሞንሙናለች። ሰማዩ ላይ እንደ እርጉዝ ምጥ አለ። ከዚያ ሰማይ ላይ የሚወርደው አውሮፕላን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ይዟል። ለራስታዎች የእምነታቸው መስተዋት። የችግርና የመከራቸው መግፈፊያ መሲህ ናቸው። እናም በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ እና በሞአ አንበሳ የተሽሞነሞነው ግዙፉ የኢትዮጵያ አውሮፕላን የኪንግስተንን አየር ሞላው።

የዚያን ጊዜ ፓሊሳዶስ አውሮፕላን ማረፊያ /Palisadoes Airport/ የሚባለውና አሁን ደግሞ Manley International Airport ላይ እጅግ በርካታ ሕዝብ ሰማዩን አንጋጦ ሲያይ ሽንጠ ረጅሙ አውሮፕላን እየተምዘገዘገ መጥቶ ከሠፊው መስክ ላይ አረፈ። ከዚያ በኋላ ፖሊስ የለ፤ ፀጥታ አስከባሪ የለ፤ ሁሉም ወደ አውሮፕላኑ ሮጠ። የመጣው ጉዳይ መሲሃቸው ነውና። ምድሯ ራደች።

የአውሮፕላኑ መሠላል መጥቶ ከተገጠመ በኋላ ጃንሆይ ከውስጥ ብቅ ሲሉ ኪንግስተን ጦዘች። የራስታዎች ደስታ የሚገለፀው በሙዚቃ ነውና ሬጌው በየቦታው ይቀልጥ ጀመር።

ይህ ሳምንት ልዩ በመሆኑ በጥቂቱ እናወጋበታለን። የራስታዎችና የኢትዮጵያ ቁርኝት በእጅጉ የጠበቀበት ወቅት በመሆኑ ትኩረት ልሰጥበት ወደድኩ።

ለመሆኑ ጃማይካዊያንና ኢትዮጵያን ምን እንዲህ አስተሳሰራቸው። በጃንሆይ እስከ ማምለክስ ድረስ ምን አመጣቸው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉት አደፍርስ አየለ የተባሉ ፀሐፊ በአንድ ወቅት እንደገለፁት፣ ባለፈው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ በአሜሪካ አህጉር የሚገኙ ጥቁሮች በነጭ ገዢዎቻቸው የሚደርስባቸውን ጭቆና በማጤንና የጥቁሩን ሕዝብ የከረረ የነፃነት ትግል በመገንዘብ ወደ አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ አሕጉራቸው ወደ አፍሪካ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንዳስተላለፉ የራስታ ንቅናቄ አባላት ይጠቅሳሉ ይላሉ ፀሐፊው። አክለውም፤ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኢትዮጵያዊነት፣ በኢትዮጵያ አምላክ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥታት ማዕከልነት የሚያምኑት ራስታዎች ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለእናት አገራችን እንሞታለን በሚል አቋም ለዘመቻው ዝግጁ እንደነበሩ ይገለፃል።

“አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ አምላክ፣ አንድ አላማ፣ አንድ እድል” የሚል ዕምነት ያላቸው ራስታዎች የምኒልክ ክለብ የተባለ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. በ1937 ዓ.ም የጀመሩትም የሰይጣን እና የጭቆና ኃይላት የሆኑት የ“ባቢሎን” መሪዎች (በፋሽዝም መልክ) ኢትዮጵያን መውረራቸው ስላስቆጣቸው መሆኑንም አጥኚው አቶ አደፍርስ ይገልፃሉ።

አጤ ምኒልክ ቀደም ሲል በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ ባርያ ፈንጋዮች ወደ አዲሱ ዓለም (አሜሪካ) የሸጡዋቸው ጥቁሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ያቀረቡት ጥሪ በራስ ተፈሪያውያን ማኅበረሰብ እምነት ማርክስ ጋርቪይን በመሳሰሉ የጥቁሮች መሪ ውስጥ አዲስ እምነት ፈጠረ። ራስ ተፈሪ ሠው ነኝ ቢሉም አምላክ ናቸው የሚል ፍልስፍና የተሠራጨው እርሳቸው በ1923 ዓ.ም እንደነገሡ ሰሞን ነው።

ራስታዎች በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና የቀደምት የሰው ልጅ መነሻነትዋ፣ በሥልጣኔ መሠረታዊ ቤት መሆንዋ፣ በኢትዮጵያ ታላቅነት፣ አንድነትና ገናናነት ታላቅ እምነት አላቸው። “ኢትዮጵያ አትበጣጠስም፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። ጥቁር ሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት፤ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠን ጽዮን ናት እንደሚሉ የአጥኚው ጽሁፍ ያስረዳል።

የራስ ተፈሪያዊያን እምነት ያስፋፋው ማርክስ ጋርቬይ ነው። ጋርቬይ የተወለደው እ.ኤ.አ ነሐሴ 7 ቀን 1887 ዓ.ም ሲሆን፤ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሳል እየሆነ መጣ። ምክንያቱ ደግሞ አባቱ መፃህፍት አንባቢ እና ተመራማሪ በመሆኑ የአባቱን ፈለግ እየተከተለ ገና በልጅነቱ አያሌ መፃህፍትን አነበበ። በዚህም ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን ፍትሐዊነት፣ እኩልነት እና ታሪክን ሁሉ ማወቅ ጀመረ። በወቅቱ ደግሞ ጥቁር የሆኑ ሕዝቦች እንደ ሰው ልጅ ፍጡር አይታዩም ነበር። እጅግ ተጨቁነው በባርነት ሰንሰለት ተሳስረው መከራ የሚያዩበት ወቅት ነበር። በንባብና በትምህርት እየዳበረ የመጣው ማርክስ ጋርቬይ ይህን አስከፊ ሕይወት ለመቀየር ተነሣ።

ከ1912 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወረ ጥቁሮችን ማደራጀት እና ለእኩልነታቸውም እንዲታገሉ መቀስቀስ ጀመረ። የቅስቀሳውንም መጠሪያ እየቀያየረ እና ማደራጀት በሚያስችለው መንገድ ሁሉ ይሰይም ነበር። ለምሳሌ Black nationalism (ጥቁር ብሔርተኛ) ወይም Pan Africanism (የአፍሪካ ጥምረት፣ ታላቅነት) እያለ ይጠራ ነበር።

ታዲያ ለነፃነትም ምሳሌ ያስፈልጋልና የነፃነት ተምሳሌት ሆና በወቅቱ ለነበሩ ጥቁሮች የምትቀርበው ኢትዮጵያ ነበረች። ጥቁር ሁሉ በባርነት ስር በወደቀበት ወቅት ለትግል ማነሳሻ ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗ በታሪክ ተፅፎ ይገኛል። በተለይ ደግሞ አድዋ ላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዢዎች ላይ ያሳረፉት በትር ጭቆናን እና ባርነትን አሽቀንጥሮ መጣያ ምሳሌ ተደርጐ በጥቁሮች አንደበት ተደጋግሞ ተነሣ። በነገራችን ላይ በዚያን ወቅት ጀማይካዊያን ቅኝ ገዢዎችን “ሰይጣን” ናቸው በማለት ይጠሯቸው ነበር። ሰይጣን ማለት ኮሎኒያሊስቶች ናቸው የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው። በአፄ ምኒሊክ የሚመራው ጦር ታቦታትን ይዞ አድዋ ላይ ከትሞ፣ ፀሎት አድርጐ፣ ወደ ጦርነት ገብቶ፣ በግማሽ ቀን ውስጥ የኢጣሊያን ሠራዊት ድምጥማጡን አጠፋ። ሰይጣን ተሸነፈ ተብሎ በአሜሪካ ባሉ ጥቁሮች በተለይ በጀማይካዎች ዘንድ ታመነ። ያሸነፈው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ነው። እነማርክስ ጋርቬይ በኢትዮጵያ ላይ ማመን ማምለክን መቀስቀሻ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። የአድዋ ድል የእምነት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያም የመላው ጥቁር ሕዝቦች የትኩረት አቅጣጫ ሆነች።

እንዲህ ምሳሌ ሆና ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ ተመልሳ በኢጣሊያኖች ወረራ ሥር በ1928 ዓ.ም ወደቀች። የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ተቆጣጠረ። ንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣናቸው ተነስተው ተሰደዱ። አገር አልባ ሆኑ።

አርበኞች ቅኝ ገዢዎችን (በጀማይካዊያን አጠራር ሰይጣኖችን) ለመፋለም በዱር በገደሉ ገቡ። ጥቁሮች ሁሉ ተስፋ ያደረጉባት የነፃነት ምድሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ስትወረር የሞራል መነካት አስከትሎባቸው ነበር። መሲሁ ከምስራቅ በኩል ከኢትዮጵያ ይመጣል እያሉ እምነትን ማቀንቀን የጀመሩት ራስ ተፈሪያዊያን ግራ የተጋቡበትም ዘመን ነበር። ግን በአምስት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ አርበኞች በተስፋፊዎችና በቅኝ ገዢዎች ላይ ድልን ተጐናፅፈው ነፃነታቸውን መልሰው ሲቀበሉ የጥቁሮቹ የእምነት እና የነፃነት ትግል በከፍተኛ ደረጃ ተነቃነቀ።

ሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግርም “ነብይ” አሰኛቸው። የራስ ተፈሪያዊያን እምነት እየጐለበተ መጣ። ማርክስ ጋርቬይ የጥቁር ሕዝቦችን አንድነትና ለነፃነታቸው የሚደረገውን ትግል በመምራት በእጅጉ የታወቀ ሰው ነው። Negro Improvement Association and Pan African Communities League ወይም የጥቁሮች ብልፅግና ማኅበርና የአፍሪካ ማኅበረሰብ የጥምረት ሊግ እያሉ ትግሉን አፋፋሙት። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በዓለም አደባባይ ከነ ግርማ ሞገሳቸው ገዝፈው ብቅ አሉ። ዝናቸው ናኘ። ጥቁር ሕዝብን ሁሉ መሰብሰብ ጀመሩ። የአፍሪካን አንድነት ለመመስረት ተነስተው መሠረቱት። ጀማይካውያን ቀደም ሲል መሲሁ ጥቁርን ይሰበስባል የሚል እምነትም ያቀነቅኑ ስለበር ውስጣቸው ያለው ነገር ሁሉ እውነት ሆነላቸው። ስለዚህም በጃንሆይ ማመን ለራስ ተፈሪያውያን ዋነኛው ማጠንጠኛ ሆኖ አረፈው።

 

የራስታዎች እምነት

ራስታዎች በእምነታቸው ጽኑ ናቸው። እንዴት በሰው ታምናላችሁ ሲባሉ አይቀበሉም። ኃይለሥላሴ ሰው አይደሉም መሲህ ናቸው የሚል እምነት አላቸው። መሞታቸውንም አይቀበሉም። በአንድ ወቅት ራሳቸውን ንጉሥ ኃይለሥላሴን የዓለም ጋዜጠኞች ስለዚሁ ጉዳይ ጠይቀዋቸው እኔ መሲህ ሳልሆን ሰው ነኝ ብለዋል። ጀማይካዎቹ ደግሞ አመኑባቸው። ምን ይደረግ እምነት የራስ ነውና እንጠብቅላቸዋለን። በአጠቃላይ ግን በአንድ ወቅት የራስታዎች እምነት ተብሎ የተፃፈ ጽሁፍ አግኝቼ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ለጥፌው ይገኛል። እናም እምነቱ 11 ነጥቦችን ይዘረዝራል። እነሡም፡-

1.  ራስታዎች እርስ በርሳቸው ሲወያዩና በቡድን ሲነጋገሩ ይውላሉ። ወንድማማች ይባባላሉ። አለዚያ ግን ማዕከላዊ የሆነ መዋቅራዊ፣ ድርጅታዊ ወይም ሕግጋት፣ ነባቤ አእምሮ የላቸውም። አባላቱ ሊከተለቸው የሚገባ የሃይማኖት ሥርዓቶች የሉአቸውም።

2.  መዋቅር የሌለው የዚህ ሃይማኖት መገለጫ የሚሆነው ሕያው የሆነ አምላክ በእያንዳንዱ ሠው ውስጥ መስረፅ ነው። እያንዳንዱም ሠው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚገናኝ ይገልጣል። የእያንዳንዱ ሠው አካል መከበር የሚገባው ስለሆነ ቤተክርስትያን ወይም ሌላ የአምልኮ ስፍራ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ። እያንዳንዱ ሠው በውስጡ አምላክ ስላለው ክፉውንና በጐውን ሊወስን እንደሚችል ይገልፃል።

3.  የራስ ተፈሪያውያን እምነቶች ማዕከላዊ ነጥቦች ሁለት ናቸው። አንደኛው ራስ ተፈሪ (ቀ.ኃ.ሥ) ሕያው አምላክ መሆናቸው ሲሆን፣ ይህም በብዙ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅስ የተደገፈ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ጥቁር ለመሆኑ በማስረጃነት ይቀርባል። የአምላክ ጥቁር መሆን ለራስ ተፈሪያውያን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። ጥቁረቱ ከቅድስና ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይቀርባል። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የእንቅስቃሴው ማዕከልነት የመጽሐፍ ቅዱስን ድጋፍ ያገኘ እና የተረጋገጠ መሆኑን ያምናሉ። በተለይም የንጉሡ ጥቁርና ኢትዮጵያዊ መሆን እምነታቸውን የበለጠ ያጠነክረዋል። መጽሐፍ ቅዱስም አምላካቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚወለድ ያረጋግጣል ብለው ያምናሉ።

4.  ጥቁር ሕዝብ በኢትዮጵያ እንደሚሰበሰብና ጥቁር ሕዝብ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው ብለው ያምናሉ። ጥቁር ሕዝብ በሙሉ በተባበሩት የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥታትን በኢትዮጵያ ማዕከልነት ማቋቋም እንዳለበትም መታገል አለብን ይላሉ።

5.  “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እውነተኛይቱ የአፍሪካ ጽዮን አድርጐ መርጧታል። የጥንታዊ የሠው ዘር መፍለቂያ የዓለም ሥልጣኔ መነሻ ናት።”

6.  በራስታዎች እምነት መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተፃፈው በአማርኛ ቋንቋ በድንጋይ ላይ ነው። አውሮፓውያን አማርኛን አስተካክለው ስለማያውቁ ትርጉሙን ማበላሸታቸውንም ይገልጣሉ።

7.  የምዕራብን ሥልጣኔ “ባቢሎን” ይሉታል። የጭቆና ምንጭ፣ የባርነት መንስኤ ነው ይላሉ። በሌላ አገላለፅም ባቢሎን ማለት ጨቋኝ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ መንግሥትና የጥቁሩ ሕዝብ መጨቆኛ መሣሪያ ሁሉ ማለት ነው።

8.  መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ ለማስረዳት የሚሞክሩት ኢትዮጵያ የጥቁሮች ገነት መሆንዋን ነው። እግዚአብሔር ሕያው እንደመሆኑ ሁሉ፣ በሰዎች ውስጥ ማደሩን ይገልጣሉ። እውነተኛይቱም ገነት በምድር ላይ እንደምትገኝ ያብራራሉ።

9.  ስለ ሞት ያላቸው እምነት ደግሞ ለየት ያለ ነው። ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደገና ይወለዳሉ የሚል ቀጥታ አገላለጥ ባይኖራቸውም በብዙ ትውልድ ዘመን በልዩ ልዩ ቅርፅ እንደገና እንደሚከሰቱ ያምናሉ። ስለዚህ ሙሴ፣ ሰለሞን፣ ዮሐንስ መጥምቁ…. አንድ ሰው ናቸው፤ እነሡም ጥቁሮች ናቸው ብለው ያምናሉ።

10.በራስታ እምነት ወንድ በሴት ላይ የበላይነት አለው። ሴቶች ወንዶችን ወደ ፈተና የማያገቡዋቸው ናቸው የሚል አሉታዊ አመለካከት አላቸው። ይሁንና ሴት የባልዋ ብቻ ንግስት ናትም ይላሉ። የወሊድ ቁጥጥር የመጽሐፍ ቅዱስን ፍልስፍና እንደሚቃረን፣ የእስራኤልን ዘር አበዛዋለሁ የሚለውን መለኮታዊ ቃል እንደሚፃረር ይገልጣሉ።

11.ራስታዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማና የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት የሆነ ቀለም ያደመቀው ልብስ፣ መልበስን እንደ ፍልስፍናቸው ማብራሪያ ይቆጥሩታል።

በአጠቃላይ ሲታይ ራስታዎች ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው። የኢትዮጵያ አፈር የተባረከ ነው ይላሉ። ምድሪቱ ፀጋ ናት የሚሉ አሉ።

ሰሞኑን የጀማይካዊ ኪንግስተን ከተማ የሃምሳ አመት ታሪክ በደማቅ ሁኔታ አክብራለች። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኪንግስተን የረገጡበትን ቀን። አያሌ ዶክመንተሪ ፊለሞች ይህንኑ ቀን መሠረት አድርገው ተሠርተዋል። በርካታ መፃህፍት ታትመዋል። ሙዚቃዎች ተቀንቅነዋል።

ከሰሞኑ በተከበረው ሃምሳኛ ዓመት ላይ የንጉሥ ኃይለሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል ኤርሚያስ ሣህለሥላሴ በከብር እንግድነት ተገኝተው ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ተሰጥቶታል።n  

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15771 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us