አጨቃጫቂው የአጤ ምኒልክ ጉዳይ

Wednesday, 05 March 2014 14:31

በጥበቡ በለጠ

         

መቼም ይህች ወርሃ የካቲት ብዙ የምናወራባት ወቅት ነች። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ጦርነት ያደረገችበትና ድልም ያገኘችበት የነፃነት ወር በመሆኑ ነው። በተለይ ደግሞ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ላይ አድዋ በጥቁር ህዝቦች ዘንድ የድል ቦታ ወይም ማማ እየተባለች ትጠራለች።

የአፍሪካን ታሪክ በማስተማር የሚታወቁት ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ሰሞኑን በስልክ እንዳነጋገርኳቸው ከሆነ የአድዋ ድል ታላቅ ድል የመሆኑን ያህል ገና ብዙ አልተወራለትም፤ አልተጮኸለትም ብለዋል። አድዋ የድል ቦታም ብትሆን የቱሪዝም መናሃሪያ መሆን ትችላለች ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ለብዙ መቶ ዓመታት በባርነት ሲሰቃዩ የኖሩት የአፍሪካ ህዝቦች ወደ ድል እንዲመጡ የመታገያ መሣሪያ ሆኖ ያገለገላቸው የአድዋ ድል ነው ሲሉ ተናግረዋል። ስለዚህ አድዋ የድል መዘከሪያ፣ የነፃነት ማሣያ፣ የመስዋዕትነት ስፍራ መሆኗን እያጮህን መናገር አለብን ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

እርግጥ ነው አድዋ ገና ብዙ ያልተሰራለት የቦታዎች ሁሉ አውራ ነው። አንዳንድ ጊዜ የምንከተላቸው የፖለቲካ መስመሮች ማንነታችንን እያኮሰሱት እና ስለ ራሳችን እንዳናወራ እየጋረዱን በማስቸገራቸው አድዋም የዚህ ሰለባ ሆኖ ቆይቷል። ግን አሁን አሁን ደግሞ ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ መነጋገሪያ እየሆነ መጥቷል። እናም በትውልዶች ውስጥ ዝንተዓለም መነጋገሪያ ሆኖ የሚኖረው አድዋ ዛሬም በጥቂቱ እናነሳሳው።

ባለፈ እሁድ በሸገር ሬዲዮ F.M 102.1 ላይ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ከታሪክ መምህሩ አቶ አበባው አያሌው ጋር በሬዲዮ ያደረገችው ውይይት ብዙ አጨቃጫቂ ጉዳዮችን አንስቶ አልፏል። አቶ አበባው ስለ አድዋ ጦርነት እና ስለ አድዋ ጀግኖች እያነሱ ያወሩት ነገር የተዛቡ አተያየቶች አሉት በማለት አስተያየቶች ሲቀርቡበት ተቃውሞዎችም በብዛት መምጣታቸውን የሬዲዮ ጣቢያው የእለቱ አስፈፃሚዎች ራሳቸው በአየር ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በዚያው በእሁድ ማለዳ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ማለትም ከF.M 97.1 ላይ የሚተላለፈው ‘የርዕዮት’ የሬዲዮ ፕሮግራም በሸገር ሬዲዮ ስለ አድዋ እየተሰራጨ ያለው ፕሮግራም የተዛነፈና የተዛባ መሆኑን በግልፅ ተናግሯል። ስለዚህ ለታሪክ የሚቆረቆሩ ትውልዶች እየመጡ ያሉበት ጊዜም ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

ለመሆኑ አቶ አበባው ሲናገሩ ህዝቡ ለምን ተቆጣ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። የአቶ አበባው ትንታኔ የአፄ ምኒልክ ጦር ሊሸነፍም የሚያችልባቸውን ሁኔታዎች መግለፃቸው ነው። አሸንፋለሁ ብሎ በሙሉ ወኔ የተጓዘ ሠራዊትን በዚህ በዚህ መንገድ ተዋግተው ቢሆን ይሸነፉ ነበር እያሉ ሲተነትኑ የትንታኔው መነሻ እና መድረሻ ልክ አይደለም ተብለው ብዙ ውግዘት ደረሰባቸው። የአቶ አበባው ሌላኛው ስህተታቸው ተብሎ የቀረበው የነገስታቱን ተገቢውን ስም እና ማዕረግ ያለመጥራት ሁኔታ ነው። አጤ ምኒሊክን እና እቴጌ ጣይቱን የመሣሠሉ ነገስታት ማዕረጋቸውን ሳይጠሩ ፈፅሞ ያልተለመደውን አጠራር ‘አንተ’ ‘አንቺ’ እያሉ ሆን ብለው በተደጋጋሚ መጥራታቸው አያሌ ተቃውሞ አድርሶባቸዋል። ይህንንም ሬዲዮ ጣቢያው ራሱ አየር ላይ ተናግሮታል።

ይሄ ስህተት የአቶ አበባው ብቻ ሳይሆን ቃለ-መጠይቅ አድራጊዋን ጋዜጠኛ መዐዛ ብሩንም ይመለከታል። አቶ አበባው ከማኅበረሰቡ እምነትና አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ሸርተት ሲሉ ማቃናት ይገባል። ምክንያቱም ሬዲዮ ነውና! ሬዲዮ በአንድ ጊዜ ለሚሊዮኖች ጆሮ የሚደርስ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ መሆኑን ለመዓዛ ብሩ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት እንደማለት ነው። ቢሆንም ግን ስህተት ተፈፅሟል!

የአጤ ምኒልክ ጉዳይ በእጅጉ እያስገረመን የመጣበትም ዘመን ነው። ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ሰው እያነሱ ከእርሳቸው ጋር የሚጣሉ ወገኖቻችንም መብዛታቸውን ሳንጠቅሰው የምናልፈው አይደለም። አሁን ያለንበት የኑሮ ሁኔታ፣ የዓለም ሁኔታ፣ የፖለቲካውና አጠቃላይ ህይወት የሚባለው ጉዳይ እንደማያስጨንቀን ሁሉ ዘለን አጤ ምኒልክ ዘንድ ሄደን እንዲህ አድርገውኛል እያልን ምሬት የምናቀርብ አለን። እንዲህ የሚማረሩ ሰዎች መኖራቸውን የሚያውቁ ደግሞ ጉዳዩን ቆስቆስ ያደርጉትና የጭቅጭቅ ማዕከል ያደርጉታል።

እኔ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ስህተት አልተሰራም ብዬ አላምንም። በሌሎች መንግሥታት ላይ እንደሚታየው ስህተት በእርሳቸው ዘመን ላይም ታይቷል። ግን ደግሞ እነዚህ ስህተቶች ትልልቁን አጀንዳ ማበላሸት እና ማደብዘዝ የለባቸውም። አጤ ምኒልክ በዘመናቸው ኢትዮጰያ በባርነት ስር እንዳትወድቅ ቅኝ እንዳትገዛ ታላቁን ተግባር ፈፅመዋል። ይሄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያኮራውና ሊያስደስተው የሚገባ ነው። መቼም በዚህ ድል የሚያኮርፍ ያለ አይመስለኝም።

አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ከአጤ ምኒልክ መነሳት ጋር ያገናኙታል። ‘ኢትዮጵያ መቶ አመቷ ነው’ እያሉ የሚናገሩ ሰዎችም አሉ። ለዚህ እንደ ማስረጃ የሚወስዱት ደግሞ አጤ ምኒልክ ደቡብ ኢትዮጵያን እና ኦሮሚያን ‘የወረሩበት’ ጊዜ ነው በማለት ነው። በርግጥ ቃሉ በራሱ አወዛጋቢ ነው። የተከፉ ሰዎች ‘ወረራ’ ሲሉት ነፃ አስተሳሰባቸውን የሚያራምዱ ደግሞ ‘ግዛት ማስፋፋት’ ይሉታል። አጤ ምኒልክን አፋቸውን ሞልተው ‘ወራሪ’ የሚሏቸው ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ‘እምዬ ምኒልክ’ በማለት ደግሞ እጅግ ሩህሩህነታቸውን የሚገልፁላቸው ሰዎች አሉ።

አጤ ምኒልክ እንዲህ የመወያያ አጀንዳ ሆነውም ብቅ ያሉበት ባለፉት 23 ዓመታት ውስጥ ነው። በተለይ በዘር ተደራጅተው የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ባሉበት ወቅት ጉዳዩ ካለገደብ ጦዘና በኋላ አጤ ምኒልክን የሚጠሉ ልጆችም ተፈጠሩ። ሐውልታቸው ሁሉ እንዲፈርስ በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር የተጠየቀበት ጊዜ ነበር። አጤ ምኒልክ ከሞቱ ከመቶ ዓመት በኋላ የመጣው ትውልድ እንዴት ወደኋላ ሄዶ ከእርሳቸው ጋር ግጭት ውስጥ ሊገባ ቻለ? መቶ ዓመት ወደኋላ ሄዶ መጣላትስ አሁን የሚያስፈልገንስ አጀንዳ ነው? ብለው በመጠየቅ ጉዳዩ ካለአግባብ ጦዟል የሚሉ አሉ።

በነገራችን ላይ እንደ ኦነግ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ መቶ አመቷ ነው ይሉ ነበር። የኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ ምኒልክ ኦሮሚያን ከወረሩ በኋላ ካለው ጊዜ ጀምሮ ነው የሚቆጠረው የሚሉ ናቸው። ግን እዚህ ላይ አንድ ፈታኝ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። ኦሮሚያ የዛሬ መቶ ዓመት ግድም አይደለም የተያዘችው ይላሉ። የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ነው በማለት ይከራከራሉ። እንደ ምሳሌም የሚጠቅሱት ገና በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በግራኝ አህመድ እንቅስቃሴ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የህዝቦች ፍልሰት ነበር። ከዚህ የህዝቦች ፍልሰት ውሰጥ ደግሞ ብዙ የኦሮሞ ህዝቦች ከምስራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ ኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተጉዘዋል ይላሉ።

በዚህ የኦሮሞዎች ጉዞ ወቅት በተለይ በወሎ እና በጐንደር ብሎም በጐጃም ውስጥ በርካታ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት መገኘትም አንድ ማስረጃ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ እና የኦሮሞ ህዝቦች ታሪክ የዛሬ መቶ ዓመት የጀመረ ሳይሆን በጣም የቆየ ታሪክ ያለው ነው ይላሉ ሃሳቡን የሚቃወሙ። በትንሹ የሚጠቅሱት የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ህዝቦችን ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉዞ ነው። እርግጥ ነው ይህ ታሪክ የህዝችን ቀደምት ትስስር የሚያሳይ ነው። ምኒልክ ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት በመምጣታቸው የተፈጠረ ታሪክ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ፖርቹጋላዊው ተጓዥ እና መልዕክተኛ የነበረው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እ.ኤ.አ በ1520 ዓ.ም አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለአራት ዓመታት ያህል ሀገሪቱን እየዞረ ካየ በኋላ በመጨረሻም ባሳተመው መፅሐፍ ውስጥ ያሉት እውነታዎች ብዙ የሚያሳምኑ ነገሮችን የያዘ ነው።

በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ግዛት ከአክሱም ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ መሆኑን ነው። ስለዚህ ምኒልክ ምናልባት ያደረጉት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ የቀድሞ ግዛቶች መልሰው የማሰባሰብ /Re-Union/ የማድረግ ስራ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ።

አጤ ምኒልክ ላይ ቅሬታ ወይም ጥላቻ ያላቸው ሰዎች በግልፅነት ነፃ ሆነው ውይይት ማድረግ አለባቸው። የጋራ መግባባት ታሪክ ላይ መድረስ ያለብን ወቅት ይመስለኛል። ምኒልክን የሚጠሉ እና ምኒልክን የሚወዱ በመሐላቸው ያለውን ክፍተት የሚሞሉበት ግልፅ የሆነ የውይይት መድረክ መኖር አለበት። በአንዲት ሀገር ውስጥ የነበረ ንጉስ ሁለት የተለያዩ ፅንፎች ታሪክ ሊኖሩት የሚገባ አይመስለኝም። አጤ ምኒልክ በጣም ክፉ እና በጣም ደግ ሊሆኑ አይችሉም። በሁለቱ አስተሳሰቦች መሀል ልዩነቱ ትልቅ ነው። ስለዚህ በመሀል የተረሳ የተዘነጋ ታሪክ አለ ማለት ነው። ሰባኪዎች ‘መሀሉ አይነገርም’ ይላሉ። እኛስ ስለ አጤ ምኒልክ መሐሉን እናውራ።

ስለ አጤ ምኒልክ በቀደመው ዘመን የፃፉ ደራሲዎችን ስራዎች ማየትም ግድ ይላል። አብዛኛዎቹ ደራሲዎች ሰውየው ሀገራቸው ኢትዮጵያን ለማዘመን እጅግ ብዙ የዋተቱ መሆናቸውን ገልፀዋል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ የተሰኘው መፅሐፍ ሲገልፃቸው “… ምኒልክ ዘመናዊ ኢትዮጵያን የፈጠሩ ሰው ናቸው….” ብሏል ሲል ታሪክ ፀሐፊውና ጋዜጠኛው ጳውሎስ ኞኞ ጽፏል።

እንደ ጳውሎስ ገለፃ፤ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ እጅግ በጣም ስራ ወዳድ ሰው ነበሩ። ሥራ ወዳጅ በመሆናቸው ብዙው የስልጣኔ ሥራ ወደ አገራችን የገባው በምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው ይላል። አጤ ምኒልክ በዘመናቸው በኤሮፓ የነበረ የሥልጣኔ ሥራ ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርገዋል። ማስገባት ብቻ ሳይሆንም ሌሎችን ለማበረታታት የሚገባውን አዲስ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰሩት ወይም የሚጠቀሙበት ምኒልክ ራሳቸው ናቸው ይላል ጳውሎስ።

ደራሲው ጳውሎስ ኞኞ ስለ ሩህሩህነታቸውም ፅፏል። በችሎት ላይ የሞት ፍርድ የሚፈረድባቸውን ሰዎች ሞቱን እንዲያፀኑት ወደ ምኒልክ ዘንድ ጉዳዩ ሲመጣ ጭራሽ ምህረት አድርገው ሰውየውን በነፃ ያሰናብቱ ነበር። ይሄን ደግሞ በተደጋጋሚ አድርገውታል። ከነገሱ በኋላም መሳፍንቱንም ሆነ ባላባቱን በወዳጅነተና በፍቅር ስለተቃረቡት አብዛኛው ያለምንም ደም መፋሰስ ሲገብርላቸው እምቢ ያለውንም በጦር ኃይል እያስገበሩ፣ የወጋቸውንም መልሰው ስለሚሾሙ ፍቅር በዝቶ ከተበታተነችው ኢትዮጵያ ዛሬ ያለንበትን ኢትዮጵያን መሠረቱ በማለት ጳውሎስ ኞኞ ይገልፃቸዋል።

አያሌ ፀሐፊዎች ደግሞ የሚገልፁት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ልትወድቅ ስትል ፍፁም በሆነ የጀግንነት አመራር በዓለም ላይ ላሉ ጥቁሮች ሁሉ የመነቃቂያ ድል አድዋ ላይ ማድረጋቸው ተደጋግሞ ተፅፏል። ዛሬ ያለው ትውልድ ነፃነት ያለውና በቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀው በምኒልክ አማካይነት ነው፤ ስለዚህ ምኒልክ ለኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት ናቸው እያሉ የፃፉላቸውም አያሌዎች ናቸው።

     በመጨረሻም መደምደም የሚቻለው በአፄ ምኒልክ ዙሪያ ያሉት አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ጐኖች የሚቃኝ ምሁራዊ ውይይት፣ አውደ-ጥናት ነገር ያስፈልጋል በማለት ነው። ታሪክ ላይ ያኮረፉ ወገኖች እንዳይኖሩንም ውይይቱ አስፈላጊ ነው። የአዲስ አበባው ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል በሃምሳ ዓመቱ የመዘጋት አደጋ ቢያጋጥመውም የታሪክ ውይይታችን ግን ይቀጥል። ሌሎቻችሁም በዚህ ርዕስ ዙሪያ ሃሳባችሁን ብታካፈሉን ደስ ይለኛል። መልካም ቀን!

ይምረጡ
(12 ሰዎች መርጠዋል)
17561 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us