“ኢትዮጵያዊው” ወልደመስቀል ኮስትሬ

Wednesday, 18 May 2016 13:40

 በጥበቡ በለጠ

 

“ኢትዮጵያዊ” የሚለውን ቅፅል የተጠቀምኩት ወድጄ አይደለም። ተገድጄ ነው። ወልደመስቀል ኮስትሬን የምጠራበት ቋንቋ አነሰኝ። ምን ልበላቸው? ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ብንሆንም፣ አንዳንድ ለየት ያሉ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ከስማቸው በፊት ኢትዮጵያዊው እያልን የምንጠራቸው። ከነርሱ ውስጥ አንዱ ወልደመስቀል ኮስትሬ ናቸው።

ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር በሉሲ/ድንቅነሽ/ ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በአክሱም ሐውልቶቿ ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በቅዱስ ላሊበላ ሕንፃዎቿ ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በጐንደር የኪነ-ጥበብ ብልፅግና ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በሐረር ጀጐል ግንብ ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በጥንታዊ ታሪኳ ትታወቃለች። ኢትዮጵያ በወልደ መስቀል ኮስትሬም ትታወቃለች። ያውም በሌሎች አለማት ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ አላማ እያውለበለበች።

ወልደመስቀል ኮስትሬ በተሠማሩበት የአትሌቲክስ ሙያ በርካቶችን አሠልጥነው ውጤታማ ከማድረጋቸውም በላይ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ገዝፋ እንድትወጣ፣ የሐገሪቱ ሕዝብ መዝሙርም የአለም ሕዝብ ሁሉ እንዲዘምረው ያደረጉ የግዙፍ ሰብዕና ባለቤት ናቸው።

ወልደመስቀል ኮስትሬ በኢትዮጵያዊ አቋም እና ዲስኘሊን የታነፁ ናቸው። ያለሙትን ያቀዱትን ሐሣብ ከግብ ለማድረስ ቀን ከሌት የሚማስኑ ጐምቱ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የኢትዮጵያዊነትን የመተሣሠሪያ፣ የመገማመጃ፣ የመቆላለፊያ መድሃኒት የቀመሙ ሰው ናቸው። አትሌቲክስ ከሚባል ስፖርት ውስጥ ደራርቱ የምትባል፤ ኃይሌ የሚባል፤ የኢትዮጵያዊነት መሰብሠቢያ መድሃኒት የፈጠሩ ሰው ናቸው። እነዚህ መድሃኒቶች ናቸው እየተባዙ የኢትዮጵያዊነት ማማ የገነቡት። ፈጣሪው ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ይባላሉ። ብዙ በቶ ሺ ዶላሮችን እንክፈልዎት የእኛን አትሌቶች አሰልጥኑልን ሲባሉ ኢትዮጵያዊነቴስ ብለው በመጠየቅ አሻፈረኝ! የሚሉ ኩሩ ኢትዮጵያዊ! በምንም መደለያ ሀገራቸውን አሳልፈው ያልሰጡ፤ ተከብረው ሀገር ያስከበሩ የትውልድ ምሳሌ።

የኢትዮጵያዊነት ምሶሶን ያቆመ ብርቱ ሞተ አይባልም። አረፈ ነው። ሌሎችን ተክቶ አረፈ። በአለም ላይ አንዲት ሀገር አለች። ኢትዮጵያ የምትባል። ሁል ጊዜ ሩጫ በኖረ ቁጥር ከፊት ሆነው የድል ብስራት የሚያሰሙ አትሌቶች ያሏት። እነዚህ አትሌቶች የዚህችን ሀገር ሰንደቅ አላማ በየአለማቱ ሲያውለበልቡ፣ መዝሙሯን ሲያዘምሩ የሚታዩ ናቸው። የነዚህ አባት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ይባላሉ። አልሞቱም፤ አረፉ።

ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ የትውልድ መንደራቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የድሮው አስፋው ወሠን ይባል በነበረው ት/ቤት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ በት/ቤት ቆየታቸውም በ400፣ በ800 እና 1500 ሜትሮች ይወዳደ ነበር።

በ1956 ዓ.ም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት እድል አግኝተው ወደ ሐንጋሪ ሄዱ። እዚያም እየተማሩ በ500 እና በ10,000 ሜትሮች ት/ቤታቸውን እየወከሉ ይሮጡ ነበር። ሩጫና ወልደመስቀል አንዴ ተጋብተዋል። የሚለያቸው የለም።

በ1963 ዓ.ም የሐንጋሪ ትምህርታቸውን አጠናቀው በማስተርስ ድግሪ ተመረቁ። ከዚያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የስፖርት መምህር ሆኑ። ከዚሁ ጋር በተደራቢነት አትሌቲክስ አሰልጣኝም ሆኑ።

በ1966 ዓ.ም እንደገና ወደ ሀንጋሪ በመሔድ የማስተርስ ድግሪያቸውን ባገኙበት ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ድግሪያቸውን መማር ጀመሩ። በ1973 ዓ.ም በዶክተሬት ድግሪ ተመርቀው ወደ ሚወዷት ሀገራቸው ኢትዮጵያ መጡ።

ወደ ሐገራቸው ከመጡ በኃላ የአትሌቲክስ አሰልጣኝነታቸውን በመሉ ጊዜ ስራ ያዙት። ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ ስፖርት የዝነኞች ማማ ላይ ለማውጣት ቀን ከሌት ጣሩ። ስፖርተኞቻቸው በዲሲኘሊን እንዲታነፁ በግል ህይወታቸው ሁሉ ጣልቃ እየገቡ ሰው ፈጠሩ። በመጨረሻው በሩጫው አለም ኢትዮጵያ ገናና ስም እና ዝና ያላት ሀገር እንድትሆን አደረጉን። 28 የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን ማስገኘታቸውም ይነገራል። የኢትዮጵያዊነት ግዴታቸውን አብልጠው ሠርተውበት ያለፉ ጀግና ናቸው።

እሁድ ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም ያረፉት እና ትናንት ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል አያሌ ሕዝብ በተገኘበት የቀብር ስለ-ስርአታቸው የተፈጸመው ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ስማቸውና ተግባራቸው ለዘላለም በክብር ይኖራሉn

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15205 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us