በፋሲለደስ ኪነት የደመቀው የመሐሙድ አህመድ የክብር ዶክትሬት፤

Wednesday, 01 June 2016 11:59

"ማመን አቅቶኛል። ብዙ ስራ ሰርቻለሁ ብል የማፍር አይደለሁም።

እግዚአብሔርን ግን አመሰግናለሁ"

ክቡር ዶክተር ማህሙድ አህመድ

ከሄኖክ ስዩም

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2007 ዓ.ም. የምረቃ በዓል ለአንጋፋው ድምጻዊ ለትዝታው ንጉስ ለማህሙድ አህመድ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶ ነበር። ያኔ ድምጻዊው በስፍራው አልነበረም። የህይወት ታሪኩ ሲቀርብ ከአሁን አሁን ወጣ ብለው በጉጉት የጠበቁት እድምተኞች ማህሙድን ሳይሆን ተወካዩን ነበር ያዩት።

ይህ ከሆነ ዓመት ከመድፈኑ በፊት ጎንደር ልዩ ድግስ ደግሳ፤ ከተማዋና ዩኒቨርሲቲው ተቀናጅተው አንጋፋውን ድምጻዊ ማህሙድ አህመድን ወደ ታሪካዊቷ ከተማ ጋበዙ። ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ሁለት ታላላቅ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶችን ጎንደር አስተናገደች።

በወርቃማው ዘመን፣ በአራቱም ማዕዘን ከያኒያን በፈሩበት፣ በየክፍለ ሀገሩ አስደናቂ የባህል ቡድኖች በተፈጠሩበት ዘመን ፋሲለደስ የባህል ቡድን ተፈጠረ። የያኔዋን የጎንደር ክፍለ ሀገር የባህል እሴቶች ሲያናኝ፤ እንደ ወሎ ላሊበላ፣ እንደ ጎጃም ግሽ አባይ በርካታ ምርጥ ከያኒያንን ለኢትዮጵያ ሲያበረክት ኖረ። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት እንደ ሌሎቹ ሁሉ ፋሲለደስም ፈረሰ።

ከዚያ በኋላ በየክፍለ ሀገሩ ወጥ በሆነ መልኩ ጠንካራ የባህል ቡድኖች መታየት አልቻሉም። ወሎ ላሊበላ ቀደመና ዳግም ተመሰረተ። ስኬቱ ናኘ። ብዙዎች ደስታቸው ወሰን አልነበረውም። የወሎ ላሊበላ ምስረታ ለግሸ አባይና ለፋሲለደስ የማንቂያ ደውል ነበር። ጎንደር የደውሉን ድምጽ ሰማች። ባለፉት አንድ ዓመት የከተማዋ ስራ የፋሲለደስ ባህል ቡድንን ዳግም ማደራጀት ነበር። ሰልጣኞች ተመልምለው የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና ተከታተሉ። ከአስራ ሁለት ወራት በኋላ የባህል ቡድን በይፋ ሊመረቅ ቀን ተቆጠረ። ይሄ ቀን የትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ የክብር ዶክትሬቱን በይፋ እንዲቀበል ከተቆረጠው ቀን ጋር አንድ ነበር። እናም ፋሲለደስ የታላቁን ድምጻዊ የክብር ዶክትሬት ሥርዓት አደመቀው።

አርብ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ጎንደር ከተማ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ አምባ አዳራሽ የተዘጋጀው ድርብ በዓል ደማቅ ነበር። ጋሽ ማህሙድ የክብር ዶክትሬቱን ሊቀበል ከአዳራሹ ተሰይሟል። የጎንደር ፋሲለደስ ባህል ቡድን ሊመረቅ በመድረኩ ተውቦ ቀርቧል። የባህል ቡድኑን ለማስመረቅ የኢትዮ-ጃዝ አባቱ ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ክቡር ዶክትር ዳዊት ይፍሩ፣ የቀድሞዋ የህዝብ ለህዝብ ዕንቁ ተወዛዋዥ እንየ ታከለ፣ የቀድሞ የፋሲለደስ ባህል ቡድን አባላት የነበሩ እንግዶችና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ታድመዋል።

መድረኩ ላይ የነገሰው የፋሲለደስ የባህል ቡድን ነው። ወጣቶቹ የቀድሞውን ዘመን እንመልሰዋለን በሚል ቁጭት መድረኩን ይውረገረጉበታል። የአዳራሹ ገጽታ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ትናንትናን በሚያስታውሱ ምስሎች ያሸበረቀ ነው።

ጎንደርን ከፋሲለደስ ኪነት ለይተው ማየት ህመም ሆኖ የሰነበተባቸው ሰዎች በሚያዩት ነገር ደስታቸው ወሰን አጥቷል። ኪነታችን ፈረሰ ብለው ተስፋ የቆረጡ የትናንት ከያኒያን እንባ ባቀረረው አይናቸው ሳይሞቱ አዲስ ነገርን ተመልክተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አብረሃ ወደ መድረኩ ወጡ። የፋሲለደስ መመረቅ የታላቁ ድምጻዊ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት መቀናጀቱ ሆን ተብሎ ታላቅ ታሪክ ጥሎ ለማለፍ የተደረገ መሆኑን አበሰሩ። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአንጋፋውን ድምጻዊ የትዝታውን ንጉስ የማህሙድ አህመድን የህይወት ዘመን ቱሩፋት መዝኖ ለክብር ዶክትሬት እንዴት እንዳጨው የሚያስረዳ የአርቲስቱን ሙያዊ አገልግሎትና የህይወት ዘመን ውጣ ውረድ የሚያስቃኝ ማስታወሻ አነበቡ። አርቲስቱንና የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች ለክብር ዶክትሬቱ አሰጣጥ ወደ መድረክ ጋበዙ። ክቡር ዶክተር ማህሙድ አህመድ በፋሲለደስ ኪነት ቡድን ዜማ ታጅቦ ወደ መድረኩ ወጣ።

የክብር ዶክትሬቱን እንዲሰጡ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የመንግስት ፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ተጋበዙ። አዳራሹ በደስታ ድምጽ ተደበላለቀ።

ክቡር ዶክተር ማህሙድ አህመድ የክብር ዶክትሬቱን ሙሉ ልብስ ለበሰ። የክብር ዶክተር ማዕረግ ባለቤትነቱን የሚያረጋግጠውን ሰነድ ተቀበለ። አይኖቹ እንባ አቅረው ነበር። ፋሲለደስ ባህል ቡድን ለስለስ ባለ የባህል ሙዚቃ የድምጻዊውን የትዝታ ዜማ እየተጫወተ ነው። ድምጻዊው ለመናገር ወደ መነጋገሪያው ቀረበ።

"ማመን አቅቶኛል። ብዙ ስራ ሰርቻለሁ ብል የማፍር አይደለሁም። እግዚአብሔርን ግን አመሰግናለሁ" ከዚህ በላይ የጻፈውን ወረቀት አላነበበውም። ለግማሽ ምዕተ ዓመት ከህዝቡ ጋር ባስተሳሰረው ስርቅርቅ ድምጽ እግዚአብሔር ይመስገን የሚለውን መዝሙር መዘመር ጀመረ። ድባቡ ሌላ ሆኗል።

ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ሁሌም ከጎኔ ለሆነችው አለና "አልማዝ አልማዝዬን" አቀነቀነ፤ በርካታ ታላላቅ ሰዎችን ያፈራው የፋሲለደስ ባህል ቡድን በዚህ ቀን ለምረቃ በቅቶ ከእሱ ጎን በመቆሙ የተሰማውን ደስታ ገለጸ። ንግግሩ በራሱ ዜማዎች ታጅቦ ሳይጠገብ አለቀ።

የስጦታ ሥነ-ሥርዓቱ ቀጥሎ አንድ ትልቅ ፍሬም ታሽጎ ተበረከተለት። መድረኩ ላይ እሽጉን ፈታው፤ በትልቁ የአጼ ቴዎድሮስ ምስል ነበር። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አብረሃ ይህ ንጉስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ታላቅ መስዕዋትነት የከፈለ ነው። አንተም የኢትዮጵያን ህዝብ በሙዚቃህ አንድ ለማድረግ ያበረከትከውን አስተዋጽኦ ታላቅ ቦታ ሰጥተን ይህንን ለመታሰቢያነት ሰጥተንሃል አሉት። ዓይኖቹ እንባ አቀረሩ። አሁን መዝፈንም መናገርም አልቻለም። የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስትን የሚያሳይ የቅርጽ ስጦታ አበረከቱለት። ማህሙድ አህመድ በክብር ዶክትሬት ፋሲለደስ ኪነት ቡድን በትንሳኤ የተመረቁበት በዓል የግማሽ ቀን ይሁን እንጂ ትዝታው የዘለዓለም ነበር።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
15272 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us