ታሪካዊቷ ጐንደር ታሪክ ሰራች

Wednesday, 01 June 2016 12:11

 

በጥበቡ በለጠ

ባለፈው ሣምንት አንድ የሥልክ ጥሪ ከወደ ጐንደር መጣልኝ። ስልኩን የደወለልኝ በዚያው በጐንደር ዮኒቨርሲቲ መምህርና የባሕል ማዕከሉ ባልደረባ ሙሉቀን ዘመነ ይባላል። ሙሉቀን በትሁት እና በረጋ አንደበቱ አንድ ጉዳይ ነገረኝ። ድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪውን አርብ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም ሊቀበል ነው አለኝ። እውነት ለመናገር በእጅጉ ደስ አለኝ። ምክንያቱም በዚሁ በሰንደቅ ጋዜጣችን የዛሬ ሁለት አመት ግድም የክብር ዶክትሬት ድግሪ የተነፈገው መሐሙድ አሕመድ የሚል ሰፊ ፅሁፍ ማውጣታችን ትዝ ይለኛል። እናም ጐንደር ዩኒቨርሲቲ አምና ለመሐሙድ አሕመድ ዶክተሬቱን ቢሠጠውም መሐሙድ በስራ ምክንያት በሐሃር ውስጥ ባለመኖሩ በአካል ተገኝቶ አልተቀበለም ነበር። አሁን ግን መሐሙድ በተገኘበት ልዩ ሥነ-ሥርአት የክብር ዶክተሬት ድግሪ አሠጣጥ ሥነ-ሥርአቱ ተዘጋጀ። ስልኩን የደወለልኝን ሙሉቀንን በእጅጉ አመሠገንኩት። ስለ አጠቃላይ ዝግጅቱም ማብራሪያ ከሠጠኝ በኃላ ዝርዝር ጉዳዮችን ከፈለክ የዩኒቨርሲቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሴ ደስታ ዘንድ ደውለህ አነጋግር አለኝ። ወዲያው ደወልኩላቸው። እንደ አንድ ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላይ እንደፃፈ ሰው ለመሐሙድ ልዩ ዝግጅት መዘጋጀቱ ያስደሠተኝ መሆኑን ገልጬ የተለያዩ መረጃዎችን ጠየኳቸው። እርሣቸውም በደስታ መለሡልኝ። ያንን መረጃ ይዤ ስለ መሐሙድ አሕመድ አንዲት መጣጥፍ አዘጋጀሁና ጨረስኩ። ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ለምትታተመው ሰንደቅ ጋዜጣችን ላይ ላሣትማት በምንቀሣቀስበት ወቅት ሌላ ስልክ ከወደ ጐንደር ተደወለልኝ።

 

“በድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ የክብር ዶክተሬት ድግሪ አሠጣጥ ሥነ-ሥርአት ላይ ልትገኝልን ትችላለህ? አሉኝ።

“ያውም የጐንደር ሰው ጋብዞ?” ብዬ ጥሪውን በደስታ ተቀበልኩት። እናም አርብ ጠዋት ከአዲስ አበባ ጐንደር በ50 ደቂቃ የአየር በረራ ደረስኩ።

 

ጐንደር አየር ማረፊያ እንደ ደረስኩ የዩኒቨርሲቲው መኪና እየጠበቀኝ ነበር። ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰሠቦች ጋር ሆኜ ጉዞ ወደ ጥንታዊቷ የአፄ ፋሲል ታሪካዊ ከተማ ጐንደር አመራን።

 

ጐንደር ከተማ ለበርካታ ጊዜያት ተመላልሻለሁ። ከዚያም አልፎ ተርፎ ከጓደኞቼ ከኤሚ እንግዳ እና ከአመለወርቅ ታደሰ ጋር ሆነን የጐንደርን ታሪክ ዶክመንተሪ ፊልም ሠርተናል። ከእኛ ጋር ሆነው በርካታ የፊልም ባለሙያዎችም በስራው ላይ ተሣትፈዋል። ፊልሙ የአንድ ሠአት ርዝማኔ ሲኖረው ርዕሡም “Gonder An African Civilization” ይሠኛል። በአማርኛ ጐንደር ቀዳማዊ የአፍሪካ ስልጣኔ የሚል ርዕስ አለው። ይህ ፊልም በ DVD ታትሞ የወጣ ሲሆን በአንዱ DVD ላይ በአማርኛ ወይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተመርጦ ፊልሙን መመልከት ይቻላል።

 

በዚሁ የአንድ ሰዓት ፊልም ውስጥ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች ስለ ጐንደር ትንታኔ ይሠጣሉ። ከነዚህም ውስጥ ታላቁ የታሪክ ተመራማሪ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ሪታ ፓንክረስት፣ የአፍሪካ ታሪክ ተመራማሪው ኘሮፌሰር አየለ በከሬ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ መምህር የሆነው ፋሲል ጊዮርጊስ፣ የጐንደር ታሪክ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አሜሪካዊው ኘሮፌሰር ላ ቬርሊ ቤርሊ፣ የቀድሞው ፕሬዘደንት የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አስተርጓሚ የነበሩት አቶ ግርማ በሻህ፣ የጎንደር ታሪክ ከፍተኛ ሊቅ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ እና ሌሎችም ጐንደር በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ እንዴት አብባ የወጣች ብርቅዬ ከተማ እንደነበረች ያብራራሉ። ይህ ፊልም በልዩ ልዩ ሀገሮች ከመታየቱም በላይ ለእኛም ብዙ ዕውቅናና ጥቅም አሠጥቶናል። እናም ጐንደር አንድ አካሌ ትመስለኛለች። ስሔድባት ልዩ ደስታ ይሠማኛል።

 

ከተያዘልኝ የማረፊያ ሆቴል/ኪኖ ሆቴል/ ወጥቼ ጥንታዊቷን ከተማ ጐንደርን ማየት ጀመርኩ። ናፍቆት ነዋ!

የጐንደር የኪነ-ጥበብ ቅርሶች ሁሌም ይደንቁኛል። ለየትኛው ቅድሚያ እንደምሠጥ ግራ ይገባኛል። እንደው ጸሎትም ለማድረስ ብዬ ወደ ብርቅዬው ቤተ-ክርስትያን ደብረ ብርሃን ስላሴ ተጓዝኩኝ። በባለ አራት ማዕዘን ሆኖ የተሠራው ይህ ቤተ-ክርስትያን በአለም የሥነ-ስዕል ታሪክ ውስጥ ልዩ የሆኑ የግድግዳ እና የጣሪያ ላይ ምስሎችን ይዟል። እነዚህ ምስሎች በሥነ-ስዕል ተመራማሪዎች የጐንደር ስነ-ጥበቦች /Gonderian Arts/ ተብለው ይጠራሉ። የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጥበብ አሻራዎች ናቸው።

 

የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ-ክርስትያን ስዕሎች በውስጣቸው ተምሣሌትን (Symbolism) ተብሎ የሚሠራው የጥበብ ስልት የሚያንፀባርቁ ናቸው። ለምሣሌ መላዕክትን ሲስሉ እግርና እጃቸውን አይስሉም። ጭንቅላታቸውንና ክንፋቸውን ነው። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ከመግባት በዚህ ተምሣሌትነት ይገልፃሉ። በዚህ ታላቅ ደብር ውስጥ የሚገኙ ሌሎቹ አስገራሚ ስዕሎች ደግሞ ኢትዮጵያዊ ለዛ እና መንፈስ በውስጣቸው ይዘዋል። እነ ቅድስት ድንግል ማርያም ኢትዮጵያዊ መልክ አላቸው። የኢትዮጵያ ንቅሳት አላቸው። መላዕክት በኢትዮጵያዊ መልክ እና ገፅታ ነው የተሣሉት። ክርስትናን አፍሪካዊ መልክ፣ ኢትዮጵያዊ መገለጫ አድርገው የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰአሊዎች ደብረ ብርሃን ስላሴ ላይ ድንቅ የጥበብ አሻራ አኑረዋል። እነዚህ ስዕሎች ሁሌም አዲስ ናቸው። አይደበዝዙም፤ አይወይቡም። ምክንያቱስ ምንድን ነው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል።

 

የማይደበዝዙበት እና የማይወይቡበት ምክንያት ሰአሊዎቹ ቀለማቸውን በሚበጠብጡበት ወቅት ነጭ ሽንኩርት እየለነቆጡ እየፈጩ አብረው ይቀላቅላሉ። ከዚህ በተጨማሪም እንቁላል ውስጥ ያለውን ነጩን ፈሣሽ አብረው ይደባልቁታል። በዚህ የተነሳ ቀለሙ ሁሌም እንደ መስታወት እያበራ ይኖራል። የሥነ-ጥበብ ተመራማሪዎቸ የስዕልን ታሪክ ሲያስተምሩ የጐንደር ጥበብ /Gonderian Art/ የሚሉት እነዚህንና ሌሎችንም አስደማሚ ጥበቦችን በማጥናት ነው።

 

ይህ የደብረብርሀን ስላሴ ቤተ-ክርስትያን በመጀመሪያ የታነፀው በአፄ አዲያም ሰገድ ኢያሱ/1674 ዓ.ም-1698 ዓ.ም/ ኢትዮጵያን ባስተዳደሩ ገናና ንጉስ ነው። ከዚያም በአደጋ ምክንያት ፈርሶ በኋላ በአፄ ዳዊት /1709-1713/ ኢትዮጵያን ባስተዳደሩት ጥበበኛ ንጉስ አማካይነት ታነፀ። ይህ ሁሉ ጥበብም የተንፀባረቀው በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው።

 

ጐንደርን እንዲህ እያየኃት ሰአቴ ወደ ሌላኛው ታላቅ መርሃ ግብር ነጐደ። ከሃምሣ አመታት በላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ጥፍጥ፣ እምር ብሎ የኖረው ተአምረኛው ድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ የክብር ዶክተሬት ድግሪውን ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ ሊቀበል ነው። መንገዶቹ ሁሉ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሊያመሩ ነው። ትልቁ ድምፃዊ ጐንደር ገብቷል።

 

የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ማዕከል አባላት ወደ አረፍኩበት ሆቴል መጥተው ወሠዱኝ። ከተንጐማለለው ዩኒቨርሲቲ ቅፅር ግቢ ውስጥ የመሐሙድ ፎቶዎች በየስፍራው ተበራክተው ይታያሉ። ውብ ሙዚቃዎቹ በሰፊው ተለቀዋል። የመሐሙድ ክብር ደምቆ ይታያል።

 

የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የአስተዳደር ሰዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ተማሪዎች አዳራሹን ሞልተውታል። ታላቁ ድምፃዊ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ባለ ዘንካታ ቁመቱ፣ ጐምላሌው መሐሙድ አሕመድ ከነ ግርማ ሞገሱ ታጅቦ መጣ። አዳራሹ ውስጥ ያለው ታዳሚ በሙሉ ከመቀመጫው ተነስቶ በጭብጨባና በእልልታ ተቀበለው። እጅግ የደመቀ የደስታ ስሜት በሁሉም ታዳሚያን ላይ ይነበብ ነበር።

 

 ከሙሐሙድ በስተጀርባ ተቀምጨ ስለ እሱ ማሠብ ጀመርኩ። ምን አይነት ስብዕና የተላበሠ ሠው ነው? እያልኩ መገረሜን ቀጠልኩ። ከትንሿ ስራ ከሊስትሮ ተነስቶ ዛሬ ሐገሩ ኢትዮጵያን በታላላቅ መድረኮች የሚያስጠራ ግዙፍ ስብዕና የተለበሠ ከያኒ ነው።

 

ከ50 አመታት በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በልዩ ተስረቅራቂ ድምፁ ጥዑመ ዜማዎችን እያንቆረቆረ ሲያስደስት ኖሯል። መድረክን ለረጅም ሰአት ካለ ድካም በመቆጣጠር የመንፈስ ማበልፀጊያ የሆኑትን ሙዚቃዎቹን ሲያሠማን የኖረ የጥበብ ባለውለተኛችን ነው። ሐገሩ ኢትዮጵያ ስትቸገር በሙያው ለማገለገል ከፊት ወጥቶ የሚሠለፍ ነው። የሐገር ፍቅርን በሕዝቦች መንፈስ ውስጥ የሚያሠርፁ ዜማዎችን አቀንቅኗል። ፍቅረኞችን ይበልጥ የሚያቀራርቡ የሚያፋቅሩ ዜማዎችን ተጫውቷል። ሐገሩ በጠላት ስትወረር ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ በየአውደ ውጊያው ላይ አነቃቅቷል፤ ወኔ ጨምሯል። እንደ ጨው ዘር የትም የተበተነው ኢትዮጵያዊ ዘንድ እየሔደ፡-

 

መቼ ነው ዛሬ ነው

ነገ ነው ሀገሬን የማየው?

እያለ የሐገር ፍቅር ስሜትን ይበልጥ የሚያስተሣስር፣ ተቆርጦ እንዳይወድቅ የሚያደርግ የአንድነት ማሠሪያ ገመድ ነው መሐሙድ አሕመድ።

 

እጅግ የደመቀው የጐንደር ዩኒቨርሲቲ መድረክ እንደገና ቀልቤን ሰረቀው። ስለ መሐሙድ ይወራል፤ ይተረካል። ከዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ውስጥ አቶ ሰለሞን አብርሃ ስለ መሐሙድ የሕይወት ታሪክ ያወጋሉ። ዶ/ር ስንታየው ወልደሚካኤል የመሐሙድ ዘፈኖች ምን አይነት ትንግርት እንዳላቸው ያወጉናል። የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማሕበር ኘሬዘዳንት ክቡር ዶ/ር ዳዊት ይፍሩ፣ የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ አባት የሚባለው ክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ሌሎችም ስለ መሐሙድ አውርተው አልጠግብ አሉ።

 

በመጨረሻም መሐሙድ ወደ መድረክ ወጥቶ ከሃምሣ አመታት በላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ በክብር ላገለገለበት አስተዋፅኦ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬቱን አጐናፀፈው። አዳራሹ ፍፁም በሃሴት ተዋጠ። ጭብጨባው እልልታው ናኘ። ፈረንጆቹ “A Living Legend” የሚሉት መሐሙድ፣ ሙያዊ ክብሩን ተጐናፀፈ። መሐሙድ በሕይወት ያለ ሕያው ምስክር!

ሽልማቱ ከክብር ዶክተሬቱ በተጨማሪ የአፄ ቴዎድሮስን ምስል የሚያሣይ ትልቅ ፎቶግራፍም ነበር። ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። መሐሙድም በሙዚቃ ችሎታው በየሔደበት እያዜመ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ አንድ አድርጓል። ለተምሣሌቱ ሲባል የቴዎድሮስ ምስልንም ተሸለመ።

 

መሐሙድ የአይኖቹ ግድቦች ዕንባ አቀረሩ። ደስታ፣ ትዝታ፣ መአት ነገሮች ተግተልትለው መጡበት።

ይህን ያደረገልኝ እገዚአብሔር ይመስገን አለ። ከዚያም አዳራሽ ውስጥ ያለውን ሠው ሁሉ ማዘመር ጀመረ።

 

እግዚአብሔር ይመስገን

እግዚአብሔር ይመስገን

ለዚህ ያደረሠን

ለዚህ ያደረሠን

እግዚአብሔር ይመስገን

 

የሚለውን ኦርቶዶክሣዊ ዜማ ሲያቆረቁረው የአዳራሹ ድባብ ልዩ ስሜት ውስጥ ገባ። እልልታ! ጭብጨባ! ደስታ! አብሮ መዘመር ቤቱን ሞላው።

 

መሐሙድ በጐንደር የምሽት ክለብ ውስጥ

ጐንደር ትልቅ እንግዳ መጥቶባታል። የመጣው ሠው ደግሞ በሙዚቃው አለም ውስጥ እላይኛው ማማ ላይ የሚቀመጥ ነው። ስለዚህ የጐንደርን የባሕል ምሽት ቤቶችን መሐሙድ እንዲያይ ተጋብዞ አርብ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም በአፄ በካፋ የምሽት ክለብ ውስጥ ገባ። የምሽት ክለቡ ጐንደርን ሊጐበኙ በመጡ እንግዶችና በጐንደር ነዋሪዎች ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዋልታና ማገር የሆነው ሠው ይመጣል የሚባል ወሬ ነበር። እናም መሐሙድ ገባ። ቤቱ በሀሴት ተዋጠ።

 

መድረኩ ላይ የሚጫወቱት ድምፃዊያን ዜማቸውን ቀየሩ። ውብ የሆኑትን የመሐሙድን ዜማዎች ማቀንቀን ጀመሩ።

ለምን ይሆን ቃል እንደ ዘበት

ያደረግነው ሁሉ በልጅነት

ፍቅር እንደ ፈሣሽ ሆኗል ወይ

ለምን ተዘነጋሽ ተረሳሽ ወይ

ተረሳሽ ወይ

 

የሚለውን ዘፈን ሲዘፈን፣ በዚያ ክለብ ውስጥ ያለው ሠው በሙሉ ከመቀመጫው ተነሣ። ፊቱን ወደ ሙሐሙድ አዞረ። ዘፋኙ ሮጦ ሔደ። ከመሀሙድ ፊት ለፊት መዝፈን ጀመረ። መሐሙድም ከመቀመጫው ተነሣ። አዳራሿ ቀውጢ ሆነች።

 

እንዴተ ይረሳል--

እንዴት ይረሳል--

ተረሳሽ ወይ--

እየተባለ ጐንደር አረበረበች።

ማን ብዬ ማን ልበልሽ፣

ምኑን ትቼ ማን ልበልሽ፣

ፍጹም ድንቅ ልጅ ነሽ፤

ድንቅ ልጅ ድንቅ ነው ውበትሽ፣

ከዋክብት ናቸው አይኖችሽ፣

አቤት ቅርጽ ስራው ከናፍሮችሽ፣

ፈገግ ስትይ ልዩ ነው ጥርስሽ።

እያሉ የጎንደር የምሽት ክለብ ድምጻዊያን ቤቱን በአንድ እግሩ አቆሙት። መች በዚህ ብቻ አቆሙ፡-

የፍቅር ወጥመድ ነው መላው ሁሉ ገላሽ

ምክንያት አጣሁኝ በምን ሰበብ ልጥላሽ

 

እያሉ የመሐሙድን ብርቅዬ ዘፈኖች አቀነቀኑ። መሀሙድ እረፍት አጣ። ይህ ሁሉ ሰው በእርሱ ደስታ ውስጥ ገብቶ አብሮት ይደሰታል። ጎንደሮች በእጅጉ አስደሰቱት። በእጅጉ አከበሩት። ይህን ያደረጉት ሁሉ ትልቅ የታሪክ ተግባር አከናውነዋል። ምስጋና ይገባቸዋል።n

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
15584 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us