የ75 ዓመት አዛውንቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

Wednesday, 08 June 2016 12:25

 

በጥበቡ በለጠ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የ75ኛ አመቱን ያዘ። 75 አመታት ብዙ ናቸው። የአንድ ሰው የመኖርያ ዕድሜ ጣሪያ ነው። አዲስ ዘመን የተባለው የኢትዮጵያ ጋዜጣም 75 አመቱ ትልቅ ነው። አንጋፋ ነው። በዚህ አንጋፋ ዕድሜው ምን ተማረ? ምን አወቀ? እንዴት አደገ? እድገቱ ለሌላው ትምህርት ነው? ዕውቀት ነው? ልምድ ነው? ከአንጋፋው እና ከእድሜ ጠገቡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ምን እንማራለን?

 

መቼም አንጋፋዎች ለተከታዮች ብዙ ያስተምራሉ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለታዳጊው የኢትዮጵያ ኘሬስ ምን የሚነግረው የሥራ ልምድ አለ? አንጋፋዎች ት/ቤቶችም ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ75ኛ አመቱ ምን ያወጋን ይሆን?

 

እርግጥ ነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመንግሥት ጋዜጣ ነው። ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ ነው። ከውልደቱ እስከ ሽምግልናው። በሕፃንነቱም ጀምሮ እስከ አሁን በወላጁ ቁጥጥር ስር ነው። አዲስ ዘመን ሦስት ወላጆች ተፈራርቀውበታል። ንጉሡ' ደርግ እና ኢሕአዴግ። ለመሆኑ ከነዚህ ወላጆቹ መካከል ማንን ይወድ ይሆን? ማነው በስርአት ያሣደገው? ማነው ለሙያው ክብካቤ ያደረገለት? ማነው ነፃነት የሰጠው?

 

አዲስ ዘመንን ጠጋ ብሎ የሆዱን የጠየቀው ይኖር ይሆን? እስከ አሁን ድረስ ያልነገረንን የሆዱን ምስጢር መቼ ይሆን የሚያወጋን?

 

አንድ ቀን ሒልተን ሆቴል አዳራሽ ውስጥ አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሸ ገ/ማርያም ለውይይት ተጋብዘው ነበር። ነጋሽ ገ/ማርያም በአሜሪካ ሀገር ተምሮ የመጣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ናቸው። እናም ስለ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወሬ ተነሣ። መድረክ ላይ ሆነው እንዲህ አሉ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጥርሡን ያወለቁት ጃንሆይ ናቸው። አስከ አሁን ድረስ ጥርስ የለውም። በድዱ ነው ያለው ብለው ነበር።

 

የነጋሽ ገ/ማርያም አባባል አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደ ጋዜጣ ድፍረት የለውም፤ መንግስት ሲሣሣት፣ ሲያጠፋ አይገስፅም፤ አያርምም፤ የመንግሥትን ተግባር ብቻ ነው የሚዘግበው ለማለት ፈልገው ነው።

 

አዲሰ ዘመን በመንግሥት ባጀት የሚተዳደር ጋዜጣ ነው። የፋይናንስ ችግር እንደ ሌሎቹ የግል ጋዜጦች አያንገዳግደውም፤ አይጥለውም። ታዲያ የገንዘብ ጀርባው እንዲህ ጠንክሮ ሣለ ምነው የጋዜጣው ጥራትስ አልጠበቅ አለ። የወረቀቱ ጥራት የወረደ፣ የቀለም ሕትመቱ 75 አመቱን የማያሣይ ነው። እዚህ ጐረቤት አገር ኬኒያ “The Standard” የተሠኘው ጋዜጣ እና ዑጋንዳ ያለው “Vision” የመንግስት ድርሻ ትልቅ የሆነባቸው ጋዜጦች ናቸው። የሕትመት ጥራታቸው፣ ተነባቢነታቸው… ግን ወደር የለውም።

 

አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደ 75 አመት የእድሜ ባለፀጋነቱ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት እና እጅ የማይጠፋ መሆን ነበረበት። ምክንያቱም በኝህ የዕድሜ ባለፀጋ ብዙ ቁም ነገር ለመቅሰም መሯሯጥ ነበረብን።

 

አዲስ ዘመን ጋዜጣን ስሙን ያወጡለት ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ናቸው ይባላል። ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት አባት የሚባሉ ወላጅ ናቸው። የመጀመሪያው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መስራችና አዘጋጅ ናቸው። “አግዐዚ” የተሠኘ ልቦለድ መጽሐፍ ደራሲ ከመሆናቸውም በላይ ከ25 በላይ መፃሕፍትን ያሣተሙ የኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍም አብሪ ኮከብ ናቸው። እንደ እርሣቸው አይነት ለሀገራቸው ግዙፍ አስተዋፅኦ ያደረገ ሰው የመሠረተው ጋዜጣ ነው። ጋዜጣው አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነፃነት የተመለሠ ቀን ንግግር ሲያደርጉ ይህ አዲስ ዘመን ነው ካሉት ንግግር ላይ የተወሰደ ነው ይባላል። ነገር ግን ከዚያ በፊት በእንግሊዝ አገር በሲልቪያ ፓንክረስት አማካይነት የሚታተም “New Times and Ethiopian News”  የተሰኘ ጋዜጣ ነበር። ይህ ጋዜጣ በአጭር አጠራር “New Times” ይባል ነበር። አዲስ ዘመን እንደ ማለት ነው። ስለዚህ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስም የወጣለት “New Times” ከተሠኘው የሲልቪያ ፓንክረስት ጋዜጣ ነው የሚሉ አሉ።

 

በዚህ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንደ ጳውሎሰ ኞኞ' ብርሃኑ ዘሪሁን' በዓሉ ግርማ የመሣሠሉ የኢትዮጵያ የብዕር ግርማ ሞገሶች ይፅፉበት የነበረ ነው። ብዙ ፅሁፎች የተስተናገዱበት ጋዜጣ ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚበራ ሌላ ጊዜ የሚደበዝዝ ታሪክ ያለው ጋዜጣ ነው።

 

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ የነፃነት ማሣያ ነው። ለምሣሌ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት የመንግሥት ጋዜጣ ሆኖ ይታተም የነበረው የቄሣር መንግሥት መልዕክተኛ የተሠኘው ጋዜጣ ነው። የሚታተመው በአማርኛ ነው። አዘጋጁ ኘሮፌሰር አፈወርቅ ገ/እየሡስ ዘብሔረ ዘጌ ነው። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መዳፍ ስር በወደቀችበት ወቅት የሚታተም ጋዜጣ። የኢትዮጵያን ነፃነት ሙልጭ አድርጐ በመግፈፍ ለፋሽስቶች አሣልፎ የሠጠ የባንዳዎች ጋዜጣ ነበር። ኢጣሊያ ከተደመሠሠች በኋላ ኢትዮጵያዊያኖች ነፃነታቸውን ለማሣየት አዲስ ዘመን የተሠኘ ጋዜጣ ማሣተም ጀመሩ። አዲስ ዘመን አፈጣጠሩ የሉዐላዊነት ማሣያ ነበር። ቀስ በቀስ ግን ኩርምት እያለ ግርማ ሞገሡን ሠብሠብ አድርጐ ቁጭ ብሏል።

 

አዲስ ዘመን ትንሣኤ ያስፈልገዋል። ሠዎች በያዘው ቁም ነገር ፈልገውት የሚገዙት መሆን አለበት። ኢትዮጵያን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላይ ማን ያውቃታል? ማንስ ይመሠክርላታል? ስለዚህ በየዕለቱ በጉጉት የምንጠብቀው ጋዜጣ እንዲሆን አዲስ ጥምቀት ያስፈልገዋል። ዜናዎቹ መሠረታዊ የዜናን ባሕርያት መያዝ አለባቸው። ኢትዮጵያን ከማጀት እስከ አደባባይ ሁለመናዋን እያየ አዳዲስ እና ትኩስ መረጃዎችን የሚመግበን መሆን አለበት።

 

ታላላቅ ስብዕና ያላቸው ፀሐፊያን እንደ ድሮው፣ እንደቀደመው ዘመን ዛሬም አዲስ ዘመን ላይ እንዲፅፉ ዘመኑ የሚጠይቀውን ወረት ሁሉ ማሟላት ግድ ይላል። ጥሩ ጥሩ አምዶች መከፈት አለባቸው። የተለያዩ ድምፆች በሚዛናዊነት የሚነበቡበት ጋዜጣ ማድረግ ይቻላል። አሁን እየሠሩ ያሉ አዘጋጆችና ጋዜጠኞች ይህን ለማድረግ ብቃቱ አላቸው። ነፃነት ግን ሊሠጣቸው ይገባል። ጋዜጣውን ለማሣደግ የሚያስቡትን ሁሉ እንዲያደርጉ ድጋፍ ሊደረግላቸው ግድ ነው። ከዚያም፣ መልካም ውጤት ማየት እንችላለን። የአዲስ ዘመን፣ አዲስ ዘመን ማየት አለብን። መልካም የ75ኛ አመት በአል ይሁንላችሁ ስል አንድ የወደድኩትን የአዲስ ዘመን ፅሁፍ እየጋበዝኳችሁ ነው። ፅሁፉን የላከልኝ የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ መምህሬ ደረጀ ገብሬ ነው። ርዕሡ ማቸነፍስ የሰውን ልብ ይላል። ፀሐፊው ታሪኩ ቀንአ ይባላሉ። ይህን ፅሁፍ ሰኔ 16 ቀን 1983 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አሣትመዋል። ኢሕአዲግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በ24ኛ ቀኑ የታተመ ፅሁፍ ነው። ታሪካዊ ነው። በውስጡም የያዘው ትምህርታዊ ነው። ብታነቡትስ፡-

 

ማቸነፍስ የሰውን ልብ!

 

ከታሪኩ ቀንአ

 

ዴሞክራሲ ቃሉ ይጥማል፤ ተግባሩም። ለምን? ቢሉ ፍትሕና ርትዕን፣ የግላዊና የድርጅት መብትና ነፃነትን፣ ዕድገትና ብልጽግናን ማለም ያስችላልና። ለምን? ቢሉ የሕሊና ርካታና የአንደበት መፈታትን፣ በመፃፍ አለመታቀብን፣ በራስ የመተማመንን፣ በመፈቃቀድ የሚፈጠር አንድነትና የእውን ፍቅርን ያመጣልና ነው። ለምን? ቢሉ የተለያየ አመለካከትና መስመር ተከታይ ድርጅቶችና ግለሰቦችን መድረክ ላይ በማምጣት በግልጽ ውይይት የጋራ ግንዛቤ ማስያዝና ለብዙኃን ድምጽና ፍላጎት መገዛትን ያስገኛልና ነው።

 

ኢሕአዴግ ቅል እንደገባው ለዚህ ዓይነቱ ዴሞክራሲ በመታገል ያለማሰለስ ተግባራዊነቱን ያሳያል የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ላይ የምንጠያየቅ አይመስለኝም።

 

ታዲያ ሀሳብን በነቀፌታም ይሁን በመደገፍ፣ በግልጽ ማስቀመጥ፣ ለሕዝብ ማስደመጥ፣ ለውይይት ማቅረብ፣ የዴሞክራሲያዊ አንዱ ገጽታ በመሆኑ እኔም እንኳን አንደበቴን ፈታልኝ፣ ልጓሜ ወለቀልኝ፣ ነፃ ሆኜ እንዳልጽፍ በእጄ ላይ የተጠመጠመው ሰንሰለት ተበጠሰልኝ በማለት ጥቂት ነጥቦች ወርወር ማድረግ ፈለግሁ።

 

መቼም ደርግን ውስጥ ውስጡን ቦርቡሮ ቅንቅን የበላው እንጨት በማድረግ ምን ከስልጣን ላይ እንደደረበው ሁላችንም እናውቀዋለን። ደርግ በመጀመሪያ ሲመጣ ላዩን በ“ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” ስም የሰላም መጋረጃ ተጋርዶ፣ ሃሳዊ የአንድነት ሸማ ተላብሶ፣ በጊዜያዊ “የታሪክ ባለአደራነት” የሥልጣን ርካብ ተቆናጦ፣ ብዝበዛና ጭቆናን ‘ከነሰንኮፉ ነቅሎ ሊጥል’ ቃል ገብቶ ስለነበር ከፋም ለማም ተቃዋሚ ቢኖርም ደጋፊው ብዙ ነበር። እየቆየ በጉልበት የመሥራት የጭቃ ጅራፉን ሲያመጣው፣ የራሱ ድርጊት ገመናውን እያጋለጠው ሲሄድ ምልዐተ ሕዝቡ ምንነቱን እያወቀው ሄደ እንጂ።

 

የደርግ ፖለቲካ ጉልበት ሆነና አረፈው። በጉልበት የሰውን አእምሮና ልብ ሊያቸንፍ ሞከረ። ጉልበት ደግሞ ከጊዜ በኋላ ጉልበተኛን ያሰለስላል እንጂ ፋይዳ የለውም። ማቸነፍ የሰውን ልብ፤ በተግባር በሚተረጉም እውነተኛና የህዝብን ስሜትና ፍላጎት በሚስብ የህዝብ ፕሮፓጋንዳ። ህዝብ በሚያምንበትና ህዝብ ድምጹን ሊሰጥለት በሚችል ሐቀኛ ሀሳብ ላይ የተንተራሰና ከእብሪትና ድንፋታ፣ ከውሸትና መልቲነት የተላቀቀ ህዝባዊ ቅስቀሳ በማካሄድ፣ ማቸነፍስ የሰውን ልብ፣ ማቸነፍስ ህሊናን ነበር። ይህ ካልሆነ ጉልበት የትም አያደርስም፤ ኢሕአዴግ! ይህን ከደርግ ይማረዋልና ጠንቀቅ!

 

ደርግ በተለይ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅላችሁ የሚል ፈሊጥና አፋኝነቱ ለእርስ በእርስ ጥላቻና ጦርነት ዳርጎ አንጀታችንን አድብኖ ወደ አረማሞ ከለወጠው በኋላማ በስመአብ! ስሙንም መስማት አስጠላን። እኛ የምንናገረውን “የለም እንዲህ ማለታችሁ አይደለም” በማለት የራሳችንን ሀሳብና ፍላጎት ለራሳችን ሊተረጉምልን ተነሳ። ውር ውር የሚሉት ተራ ሽፍቶች ናቸው እንጂ ሀገር ሰላም ነው ሲለን ኖረ። ብቻ ምን አለፋችሁ፣ ብዙ የውሸት አኩፋዳ አንጠልጥሎ በየቦታው ዞረ። እኮ! እናንተም ይህ እንዳይገጥማችሁ ጠንቀቅ!

 

አቤት በየጊዜው የገባው ቃል የሰጠን ተስፋ! በህልም የሚቆጠር ብር፤ የምኞት እንጀራ ሆኖ ቀረ እንጂ። ህዝብ ደግሞ የሚፈፀም ተስፋና ራቁቱን የቀረ ውሸት ሲደጋገምበት፣ ዛሬ የተባለ ነገር ነገ ሲካድ፣ የራስ ጥፋት በሕዝብና “በፀረ-ህዝቦች ሲመካኝ ሀሰተኛና ጉቦኛ ተመስግኖ ሀቀኛና ትጉ ዜጋ ሲወገዝና ሲሾፍበት አክ እንትፍ” ይላል።

 

ደርግ ሌላው በሽታው “እኔ የጠላሁትን ሁሉ ጥሉልኝ፤ እኔ የምወደውን ብቻ ውደዱልኝ” ነው። በግድ እኮ ነው። አያበግንም? ታዲያ! ይች ይች መጥፎ መርዝ የተቀባች መርፌ ሆነችና፤ ህዝቡ ደግሞ እሱ ያላመነበትን የጥላቻ መርዝ በግድም ሆነ በውድ በመርፌ በደምስሩ ውስጥ ማስገባት አልወደደምና ደርግን እንቅር አድርጎ ትፍት! አሁንም ይችን ጠንቀቅ!

 

ኢሕአዴጎች! መውደድ ያለባችሁ አመስጋኛችሁን ብቻ አይደለም፤ ስልጣን ስለያዛችሁ፤ (ጊዜያዊ ቢሆንም) የኃይል የበላይነት ስላለም ብዙ አድርባይና የአርጋጅ አናጓጅ ሊኖር ይችላል። ያለ ይሉኝታ ስህተታችሁን እየጠቆመ የህዝብ ብሶት የት ላይ እንዳለ እያሳየ የህዝብ ፍላጎትና አስተያየትን ነፃ በሆነ መልክ እያመለከተና ገንቢ ሃሳብ እየሰጠ፣ ክፉ ክፉን፣ የቂም በቀሉን ሳይሆን የሰላሙንና የአስማሚውን ጎዳና ፈር እየቀደደ፣ የቋሻሪነትና የተንኳሽነትን ባህሪ ፈለጉን እያጠፋ፣ እድገታችሁ ሳይቋረጥ ወደ ፊት እንድትገሰግሱ፣ የህዝቡን አመኔታ እንድታገኙ የሚያደርጋችሁን ሰው ውደዱ።

 

ስንት የሴራ ተሞዳሟጅና በእናንተ የጓዳ በር ገብቶ በአንበሳ በር አጋፋሪነቱን ቀጥሎ ጊዜያዊ ጥቅም ለመመንቸፍ የሚጣደፍ አልጠግብ ባይ አለ መሰላችሁ! “ሆይ ሆይ” ያለ ሁሉ በእውን የኢህአዴግ ደጋፊና ተጋዳይ አይደለም። ከዘመመ የሚዘም፣ ከነፈሰ የሚነፍስ የራሱ የሆነ አቋም የሌለው ስለመሆኑ ሚዛናችሁ ሳያሳልስ ቢፈትነው ያገኘዋል። ደርግ እንዲህ አይነቱን አድር ባይና ተሞዳሟጅ ባለሟል በማድረጉ ነው ‘መካሪ ያጣ ንጉስ ያለ አንድ ዓመት አየነግስ’ ተረት የደረሰበት። እናንተም የደጋፊያችሁን ብቻ ሳይሆን የነቃፊያችሁንም ሀሳብና ትችት በማውጣት ለእርምት የተዘጋጃችሁ ለመሆናችሁ አሳዩና የሰውን ልብ ለማቸነፍ ጣሩ።

 

ሰማችሁ ወይ? ሰላምና መረጋጋትን በዜና ማሰራጨት በሰፊው ተያይዛችሁታል። ሕዝቡ የጠማውን ሰላም ለመቀበል ወይም ከራሱ ለማግኘት እያማጠ ነው። አጋቹም ሰላም ሲያምጥ ሌላውን እየወረፈ ከሆነ ሰላሙ ሊወለድ አይችልም። የአፈነገጠን፣ የአኮረፈን፣ የደነገጠና የበረገገን ወደ ራስ ለማምጣት ስድብና ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅና ማስደንገጥ አይደለም። ይህማ የደርግ ባህርይ ነው። ለብልህ አይነግሩም፣ ለአንበሳ አይመትሩም ቢሆንም፣ ደግ ደጉን ያናግራችሁ። እናንተን ጠላት ያለ መጥፎ መጥፎውን ይለፍልፍ እንጂ የመንግሠትን መንበር የያዘማ ታጋሽ፣ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት’ኮ! ምን እንደምትባሉ አውቃችኋል? “የደርግ ፖለቲካ ተገልብጦ መጣ!” ነው።

 

ቅራኔአችሁን በድርጅታችሁ ልሳኖች ብታወጡ ሳይበጅ አይቀርም። መቼም ዴሞክራሲ አይደል! የዜና ማሰራጫው የሁሉም ተቃዋሚ ቡድኖች ሁሉ ነው። ይበልጥ ደግሞ የሰላም ፈላጊው ሕዝብ ነው። ሕዝቡ የማንም አቡካቶነት አይፈልግም። የሚያናግረው ጠፍቶ፣ ዴሞክራሲው ትፍኖበት እንጂ ራሱ ለራሱ የሚለው አለው። አሥራ ሰባት ዓመት አፈሙዝ ተደቅኖበት አሁንም አፈሙዝ እያየ መናገር ስለማይፈልግ እንጂ። ታጋዮቻችሁ ተግባቢና ሩህሩህ፣ ሥነ ሥርዓት አክባሪ ቢሆኑም በያዙት ጠመንጃ ላይ ሕዝቡ ፍርሃት አለበት። የአፈሙዝ ፎቢያ!

 

በሌላ በኩል እኮ እንወዳችኋለን። የፈጠራችሁልን ሰላም እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይምሰላችሁ። በደርግ የሰለቸንን ስድብና ማጥላላት ነው የማንወደው። ቅዋሚ ለምን ተነሳበን አትበሉ። የዴሞክራሲ ውስጣዊ ባህርይ ነው። ጠልታችሁ ለማስጠላት አትሞክሩ። ሕዝቡ በድርጊቱ አይቶ ይጥላው። እንዲህ ማድረጋችሁ ተቃዋሚዎቻችሁን ታስወድዳላችሁ። እድብ ብትሉ፣ ብትታገሱ ግን፣ ለካ በእነዚህ ሰዎች ላይ እስከዛሬ የሰማነው ሁሉ የስም ማጥፋት ዘመቻ ኖሯል ያስብልና ከፍተኛ ድምፅና ድጋፍ ታገኛላችሁ። ሕዝቡ በጣም ወደደን፣ ተቀበለን አትበሉ። በሰላም መስፈን፣ በትጋት መሥራትና፣ በሰዎች ሕሊና እረፍት፣ እንደልብ ያለፍርሃት በመናገር በመጻፍ ተንፀባርቆ ይምጣ እንጂ።

 

ዴሞክራሲን እያሰፈነ ነው ብላችኋል። ታዲያ በሰላምና መረጋጋት ኮሚቴ፤ እንዲሁም በአጋዥ ታጣቂዎች ምርጫ ላይ ዴሞክራሲን አልገደባችሁም እንዴ? ወንጀለኛም ንጹህም’ኮ በሕዝብ ውስጥ ከሕዝብ ጋር ነው የኖሩት፤ ያሉት። ያውቃቸዋል። እሱ፤ ሕዝቡ የፍርድ ሚዛኑን ይስጥ እንጂ እናንተ ዙሪያውን አጥር ለምን ትሰሩበታላችሁ? ደርግም፤ ፊውዳል፣ ኢህአፓ፣ ሻዕቢያ፣ ሕወሓት፣ ወዘተ… እያለ ገደበ። እናንተም፤ “ኢሠፓ፣ ወታደር፣ የድሮ ቀበሌ ተመራጭ፣ የአብዮት ጥበቃ፣ ጡረተኛ፣ ወዘተ…” አላችሁ።

 

በመሠረቱ፤ እውነት እንናገር ከተባለ ኢሠፓ በተቋም ደረጃ ከፈረሰ ቆይቷል። ኢሠፓ የፈረሰው በራሱ የአፋኝነት ባሕርይ ምክንያት ካድሬው ከከዳው በኋላ ነው። ቢያንስ ሁለት ዓመት። ኢሠፓ ቢሮ እንጂ አባል አልነበረውም ማለት ይቻላል። እና እየከለከላችሁ ያላችሁት የግለሰቦችን የዜግነት መብት ነው። ውርዴ አደረጋችኋቸው። ሕዝቡ ውድድ ሲሉት ይጠላል፤ ጥላ ሲሉት ይወዳል። ምክንያቱም ከእርሱ ፍላጎት የመነጨ አይደለማ። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ከእንግዲህ ባለመድገም የሰውን ህሊና፤ የሰውን ልብ አቸንፉ። ማቸነፍ ከተባለ ማቸነፍ የሰውን ልብ! ጠመንጃና የጉልበት ፖለቲካ ለደርግም አልሆነም።

 

ሕዝብ አይናቅ፤ ሕዝብ ይከበር። አታወቅም አይባል። እስቲ ሁሉንም ለሕዝቡ! የብሔረሰብ፣ የጎሳ፣ የብሔር ጥላቻ፤ ብቻ ምንም ይባል ምን፤ በሕዝብ መካከል ጥላቻ የለም። ጥላቻውን በመካከሉ ሊፈጥሩበት የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ብለ የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ችግርም ካለ ሕዝቡ በራሱ ባህላዊ ሽምግልናና ውይይት ይፈታዋል።

 

ሕዝቡ የሚፈልገው ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን ነው። እስከ አሁን የሠራችሁትን አያሌ በጎ ነገር ችላ ማለቴ አይደለም። ከእሱ በጎ ነገር ችላ ማለቴ አይደለም። ከእሱ ይልቅ መንቀፍ ያለብኝን ባስቀድም ይበልጥ ሕዝባዊ መልካችሁን እያጎላችሁ ማምጣት ያስችላችሁ ይሆናል ብዬ በማሰብ ነው እና ተቃዋሚ እንዱፈጠር እናንተ ምክንያት እንዳትሆኑ ትንሽ የተባለው ትልቅ ይሆንና በመንፈስ ላይ ያለው ሰላም ሲደፈረስ ይችላል። ዘላቂውን ሰላም ያበላሸዋል፤ ግን የእኛ ምኞት ይህ አይደለም።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11628 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us