የአበራሽ በቀለ “የማለዳ ወጥመድ” መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል

Wednesday, 15 June 2016 12:23

በጥበቡ በለጠ

 

በ14 አመቷ ተጠልፋ፣ ተደፍራ፣ በኋላም ከጠላፊዋ ቤት አምልጣ ስትወጣ ጠላፊዋ ተከታትሏት አደጋ ሊያደርስባት ሲል ጠብመንጃ ተኩሳ ጠላፊዋን የገደለችው አበራሽ በቀለ የማለዳ ወጥመድ የተሰኘ መጽሐፍ አሳተመች። ይህ መፅሐፍ ስለ አበራሽ በቀለ የሕይወት ውጣ ውረድ የሚተርክ እንደሆነ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ያዘጋጀው ኢጋ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ለሰንደቅ ጋዜጣ በላከው መግለጫ ጠቁሟል።

አበራሽ በቀለ ሰው በመግደል ወንጀል ገና በ14 ዓመቷ የታሰረች ሲሆን ከዚያም የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ከአበራሽ ጎን በመቆሙ ከእስር ነፃ እንድትወጣ ትልቅ ርብርብ ተደርጎላታል። በተለይ ዛሬ በሕይወት የሌሉት የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ እታገኝ ለሜሳ፣ ለአበራሽ በቀለ በነፃ ጥብቅና ቆመውላት ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ነፃ አውጥተዋታል።

ይህ የአበራሽ በቀለ የሕይወት ውጣ ውረድ አሳዛኝ በመሆኑ የBBC ቴሌቭዥን ጎበዝ የዶክመንተሪ ፊልም ሰራተኛ የሆነችው ጋዜጠኛ ቻርሎቴ “The School Girl Killer” የተሰኘ ፊልም ሰርታ በBBC አስተላለፈችው። የአበራሽን ታሪክ በወቅቱ ለ BBC የካሜራ ቀረፃም ያደረገው ኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሙያ አበበ ቀፀላ እንደነበር ይታወሳል። በቅርቡም በዘረሰናይ ብርሃነ መሐሪ አማካይነት “ድፍረት” የተሰኘ ፊልም በአበራሽ በቀለ ሕይወት ዙሪያ ለመስራት ቢሞክርም መጨረሻው ግን አልሰመረም። ፊልሙ ብዙ ውዝግቦችን አስነሳ። ከዕይታም ታገደ።

   ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የአበራሽ የሕይወት ታሪክ የማለዳ ወጥመድ በሚል ርዕስ የታተመው። ነገ ከ11፡00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቅ ኢጋ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ለሰንደቅ በላከው መግለጫ አውስቷል። የመጽሐፍ አንባቢዎችና ወዳጆችም በስፍራው ተገኝታችሁ መታደም እንደምትችሉም ተነግሯል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11208 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us