ተጨፍልቀው ያለቁት ሕፃናት በኢትዮጵያ

Wednesday, 15 June 2016 12:29

 

በጥበቡ በለጠ

ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም አንድ ጥሪ ነበረኝ። ጥሪው በደራሲ እንዳለጌታ ከበደ የተዘጋጀው የበዓሉ ግርማን ሕይወቱን እና ስራዎቹን የሚያስቃኘው መጽሐፍ ለሁለተኛ ጊዜ ውይይት የሚቀርብበት ቀን ነው። ቦታው ወመዘክር ነበር። እኔና ጓደኛዬ አብረን ለመሔድ ተገናኘን። ሰአቱ ስላልሞላ ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው ቸርችል ሆቴል ጐራ ብለን ቡና ጠጣን። መኪናችን እዚያው እንደቆመች እግራችንን እናፍታታ ብለን ወደ ሜጋ አምፊ ቴአትር አካባቢ ሔድን። ልክ እዚያ እንደደረስን ያልተጠበቀ ድንገተኛ ዶፍ ዝናብ ያዘን። ሮጠን ወደ ቀድሞው ሜጋ አምፊ ቴአትር  ተጠለልን። ዝናቡ አላቆም አለ። ጐርፉ ከላይ እየተንደረደረ ይመጣል። አካባቢውን ጭጋግ ወረሠው። እኔ በተፈጥሮዬ አየሩ እንዲህ ጭጋግማ ሲሆን አልወድም። ቅፍፍ ይለኛል። ብቻ ስለ ጐርፉ፣ ዝናቡ፣ ጭጋጋማነቱ፣… እያሠላሠልኩ እያለሁ ድንገት አንድ ነገር ትዝ አለኝ። እዚያ የቆምኩበት ቦታ ልክ የዛሬ 16 አመት ታላቅ ሀዘን የመታው ዕለት ነበር። 14 ሕፃናት በአንዲት ቅፅበት ውስጥ ያለቁበት ጊዜ ነው። ግንቦት 28 ቀን 1992 ዓ.ም። እዚይው አካባቢ ነበርኩ። 14 ሕፃናት ሲያልቁ። ያንን አሠቃቂ አደጋ አይቻለሁ። አእምሮዬ በሐዘን ተመታ። በትዝታ አለቀሥኩ። 14ቱ ሕፃናት ትዝ አሉኝ። አሣዛኝ የኢትዮጵያ ልጆች። መረሣት የሌለባቸው ግን ድንገት አስታወሰኳቸው። ሀዘኔ በረታ።

 

የቆምኩበት ቦታ ጥንት ሰይጣን ቤት ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ነው። አጤ ምኒልክና ባለሟሎቻቸው ተሠብስበው ፊልም ያዩበት ነው። ፊልሙን ያሣያቸው ፈረንሣዊው ቻርልስ ማርቴል የሚባል ሠው ነው። ሉሚየር ከሚባሉ ከፈረንሳይ የፊልም ኩባንያ የመጣ ነው። የፊልሙ ኘሮጀክተር ተከፍቶ ሲታይ እየሱስ ክርስቶስ ይታያል። የሚኒልክ ባለሟሎች ተነስተው እመሬት ላይ ተደፉ። እየሡስ ራሡ እዚያ ቤት የገባ መሠላቸው። በኃላ አጤ ምኒልክ በስንት ጉትጐታ ባለሟሎቻቸውን ገስፀው ከተደፉበት መሬት ላይ እንዲነሡ አደረጓቸው። ይሔ ሲኒማ ነው። እውነት አይደለም አሉዋቸው። እውነትም እየሡስ በውን የለም ነበር። የተሠወረም መሠላቸው። ከዚያ በኋላ ያንን ቤት ሰይጣን ቤት አሉት። እኔም እዚያ ሰይጣን ቤት ቆሜ የዛሬ 16 አመት ስላለቁት ሕፃናት እያሰብኩ ለጓደኛዬም አወራሁለት። እርሡም ክፉኛ በሐዘን ተመታ።

 

ቴአትር ቤት ውስጥ ያለቁ ሕፃናት ሁሌም መዘከር እንዳለባቸው እገምታለሁ። ሠው የሚዝናናበት፣ ቁም ነገር የሚገበይበት ቦታ ላይ 14 ሕፃናት ነፍስ ረግፏል። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

 

ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም ሻዕቢያ መቀሌ ውስጥ በአይደር ት/ቤት ላይ በአውሮኘላን ቦምብ በመጣል ሕፃናትን ይጨፈጭፋል። ይህ ከባድ ሀዘን ነበር። ከዚያም በአመቱ ማለትም ከነሐሴ 17-21 ቀን ትምህርት ሚኒስቴር ድሬዳዋ ውስጥ አንድ ጉባኤ ያካሒዳል። በዚያ ጉባኤ ላይ ከተነሡት ነጥቦች መካከል ግንቦት 28 ቀን 1992 ዓ.ም ት/ቤቶች ዝግ እንዲሆኑና ሕፃናቱ እንዲዘከሩ ውሣኔ ላይ ይደረሣል። እነዚህን የአይደር ት/ቤት ተማሪዎችን በሻዕቢያ ጀት ያለቁትን ሕፃናት ለመዘከር ሜጋ አምፊ ቴአትር የተሠባሠቡ ሕፃናት 14ቱ በሌላ አደጋ ሞቱ። አሣዛኝ ሞት። ግን እንዴት ሞቱ?

 

በዚያ ዕለት የወረዳ 2 ት/ቤቶች የአገር ሉአላዊነት ማስከበር በዓል ግንቦት 28 ቀን 1992 ዓ.ም በሚል የገቢ ማሠባሠቢያ የሙዚቃ በዓል በሜጋ አምፊ ቴአትር ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህም የተነሣ በአካባቢው ያሉት የአፍሪካ አንድነት' የካቴድሪል' የአብዲሣ አጋ' ለመስከረም 66 /የአለም ብርሃን/ እና ለቅድስት ሥላሴ ት/ቤቶች ትኬት ይሠራጫል። ቲኬቱ ዋጋው ሁለት ብር ነው። ይሄን ትኬት ወላጆችና ልጆች ገዝተው ግንቦት 28 ቀን 1992 ዓ.ም ሜጋ ተሠባሠቡ። ከጥዋቱ 4 ሠአት ጀምሮ ሕፃናትና ወላጆች እጅግ ተበራክተው የሙዚቃ ድግስ ላይ ሊታደሙ ጓጉተዋል። ድንገት ዶፍ ዝናብ መጣ። አዳራሹ አልተከፈተም። የሚከፍት ጠፋ። ዝናቡ በረታ። መላወሻ ጠፋ። ሕፃናቱ ወላጆች በዝናቡ ክፉኛ ተመቱ። ጭንቀትና ስቃዩ በዛ። ይህ ጭንቀት ያስጨነቃቸው የሜታ አምፊ ሠራተኞች የአዳራሹን በር ከፈቱት። ሕዝቡ ወደ አዳራሹ ለመግባት ሌላ ግፊያ እና ትርምስ ውስጥ ገባ። ከፊት የነበረች እንዲት ሴት ሁለት ልጆችዋን ይዛ ለመግባት ስትሞክር ከነ ልጆችዋ ወደቀች። ከኃላዋ ያለው ሕዝብ ልጆችዋን እየጨፈላለቀ ሔደ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሌሎችም ሕፃናት ወደቁ። ሕዝቡ እየጨፈለቃቸው ሄደ። ገደላቸው። 14 የኢትዮጵያ ሕፃናት የዚያችን ቀን ተጨፈላልቀው ሞቱ። ዝናቡን ለመሸሽ ሲባል ተጨፈለቁ። ዛሬ እነዚህ ልጆች በሕይወት ቢኖሩ ግማሹ 26፣ ግማሹ 25 እና ሌላው የ24 አመት ወጣቶች ይሆኑ ነበር።

 

መቀሌ ውስጥ በሻዐቢያ የተጨፈጨፉትን ሕፃናት ለመዘከር የተሠባሠቡ የአዲስ አበባ ሕፃናት በኢትዮጵያዊያን ተጨፍልቀው ሞቱ። እኒህ ልጆች የተረሡ ይመስለኛል። እኔም ድንገት በተፈጠረ ሁኔታ ነው ያስታወስኳቸው። እነዚህ ሕፃናት ቅን ሠማዕታት ናቸው። ሌላውን ጓደኛቸውን ሊዘክሩ ወጥተው ያለቁ። ሁለት መንታ ልጆች በአንድ ቀን የሞቱበት። ፎቶዋቸውን ፈልጌ የ11ዱን ሕፃናት አግኝቻለሁ እንዘክራቸው።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15187 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us