“ለእኔ መሞት ይሻለኝ ነበር”

Wednesday, 29 June 2016 12:27

 

ፕ/ር አፈወርቅ ገ/እየሱስ

በጥበቡ በለጠ

በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያ ደራሲያን እና የኢጣሊያ ወረራ” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወሳል። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ በተለይም ይህን የግፍ ወረራ ለመመከት እና ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ደራሲዎች ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በቅርቡም ሚያዚያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በጋዜጠኛ ሕሊና አዘዘ ተጋብዤ ከደራሲ አበረ አዳሙ ጋር ሆነን 75ኛ አመት የአርበኞች በአልን መሰረት በማድረግ፣ የእለቱ ለት የኢትዮጵያ ደራሲያን በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ለማቅረብ ሞክረናል። በወቅቱ ለፋሽስት ኢጣሊያ ያደረውን አፈወርቅ ገ/እየሱስን በተመለከተ የተናገርኩትን መሰረት አድርጎ ወዳጄ የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ጥያቄ ጠይቆኝ ነበር። ለእርሱም ሆነ ለሌሎች አንባቢዎቼ የፕሮፌሰር አፈወርቅን ታሪክ ባጭሩ ላብራራ ነው።

በትምህርት ደረጃው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ላይ ደርሷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ “ነጋድራስ” የሚሰኘውን ማዕረግ ተቀብሏል። ይህ ሰው አፈወርቅ ገ/እየሱስ (ዘብሔረ ዘጌ) ይባላል። አፈወርቅ ገ/እየሱስ ጦቢያ የምትሰኘውን የልቦለድ መጽሐፍ በ1900 ዓ.ም ያሳተመ ደራሲ ነው። ጦቢያ በአፍሪካ ውስጥ በራስ ቋንቋ ከተፃፉ ልቦለዶች ሁሉ የመጀመሪያ ነች። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ መሠረት የጣለው አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ሌሎችንም መፃህፍት አሳትሟል። ሁለተኛ መጽሐፉ ደግሞ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በሚሰኝ ርዕስ አሳትሟል። ልዩ ልዩ አጫጭር ልቦለዶችን እና ታሪኰችን በመፃፍ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚወስድ ነው።

አፈወርቅ ገ/እየሱስ የተወለደው ጣና ውስጥ ከሚገኙት ደሴቶች መካከል “ዘጌ” ተብላ ከምትታወቀው ቦታ ሐምሌ 3 ቀን 1860 ዓ.ም ነው። አባቱ ገብረእየሱስ ድንቄ ሲባሉ እናቱ ደግሞ እመት ፈንታ ትሁን ይሰኛሉ። ገና በልጅነቱ ጣና ውስጥ የሚገኙትን ገዳማት የግድግዳ ላይ ስዕሎች እያየ እና በእነርሱ እየተመሰጠ ከዚያም የስዕል ፍላጐቱ እና ችሎታውም እያደገ መጥቶ የስዕል ብሩሽ ከእጁ የማይለይ ሰዓሊ ሆነ። በትምህርት አቀባበሉም እጅግ ተስፋ የተጣለበት ታዳጊ ሆነ።

አፈወርቅ ለእቴጌ ጣይቱ የቅርብ ዘመድ ነበር። እቴጌ ጣይቱም ጐንደር እያሉ በልጅነቱ አፈወርቅ ተሰጥኦ ያለው ታዳጊ መሆኑን ስለተገነዘቡ በ1875 ዓ.ም ከአጤ ምኒልክ ጋር ከተጋቡ በኋላ አፈወርቅን ወደ አዲስ አበባ አስመጡት። እዚህም አዲስ አበባ የስዕል ስራውን እየሰራ የቤተ-መንግስት ልጅ ሆኖ ቆየ። አጤ ምኒልክም አቅርበው ያጫውቱት ነበር። ልጁ አእምሮው ሰፊ ስለሆነ ወደ አውሮፓ ሄዶ ቢማር ብዙ ስልጣኔዎችን ወደ ሀገሩ ይዞ ይመጣል ብለው በማመን ሄዶ እንዲማር ተፈቀደለት።

መስከረም 24 ቀን 1880 ዓ.ም ምፅዋ ደረሰ። ከዚያም በመርከብ ተሳፍሮ ኔፕልስ ወደብ ጣሊያን አገር ደረሰ። በመጀመሪያ የተማረው የጣሊያንኛን ቋንቋ ነው። ከዚያም Istituto Internazionale di Tomino በተባለ ኰሌጅ ትምህርቱን ቀጠለ። የአውሮፓንም ስልጣኔ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ተማረ። አፈወርቅ ወደ አውሮፓ ከመሄዱ ሦስት ዓመት በፊትም የአውሮፓ መንግስታት በርሊን ከተማ ተሰብስበው አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው ነበር። ሚያዚያ 25 ቀን 1880 ዓ.ም ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ጋር የውጫሌን ውል ተፈራረሙ። የኢጣሊያ ጋዜጦችም ፃፉበት። ጣሊያኖች ተደሰቱ። አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ደግሞ ውሉን ሲያነበው አንቀፅ 17 ችግር ያለበት እንደሆነ ተገነዘበ። አንቀፁ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ነው በማለት አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ለትምህርት በሄደበት ሮማ ውስጥ ተቃውሞ ማስነሳት ጀመረ። ይህ አንቀፅ የተጭበረበረ ነው በማለት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን ተቃውሞ ያስነሳው አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ነው።

የሸዋው ንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ በሙሉ ነገሱ። ይህን ንግስናቸውን ለማብሰር በደጃዝማች መኰንን ወ/ሚካኤል (በኋላ ራስ) የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አውሮፓ ሄደ። ለአፈወርቅም ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት። የልዑካን ቡድኑን አገኛቸው። ሁሉንም ነገር አጫወታቸው። የውጫሌው ውል አንቀፅ 17 ተጭበርብሯል አላቸው። ይህን አደገኛ ደባ መቋቋም ባለመቻሉም ለምኒልክ ደብዳቤ ፃፈ። በዚህ ብቻም አላቆመም፤ ትምህርቱን ጥሎ ከልዑካን ቡድኑ ጋር አብሮ ተመልሶ ወደ ሀገሩ መጣ። ይህም የሆነው ህዳር 26 ቀን 1882 ዓ.ም መሆኑን ታዋቂው ሰዓሊና ሀያሲ እሸቱ ጥሩነህ ፅፎታል።

ከዚህ በኋላ አፈወርቅ ገ/እየሱስ በለኰሰው ኀሳብ ምኒልክና ጣይቱም በመስማማታቸው እንዲሁም በተለይ ጣይቱ እጅግ በመበሳጨታቸው የአድዋ ጦርነት ተቀሰቀሰ። አፈወርቅ ገ/እየሱስም የአድዋን ጦርነት የመጀመሪያዋን ቀስቃሽ ኀሳብ በማመንጨት ዋነኛው ተጠቃሽ ነው።

ኢትዮጵያም የአድዋን ጦርነት በአንድ ቀን ድል አድርጋ ጥቁር ለመጀመሪያ ጊዜ የነጭን መንግስት አሸናፊ ተብሎ በዓለም መዝገብ ተፃፈ። የጦርነቱ ለኳሽም አፈወርቅ ገ/እየሱስ እንደሆነ ይታወቃል። ታዲያ ይህ ታላቅ ሰብዕና የነበረው ሰው ፋሺስት ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ስትወር የጣሊያኖች ባንዳ ሆኖ ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ለዘላለም እንዲገዙ ከጐናቸው ቆመ። የዚያን ወቅት ማለትም ከ1923 ዓ.ም እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ አፈወርቅ በኢጣሊያ የኢትዮጵያ ቆንሲል ነበር።

በኢጣሊያ የአምስት ዓመታት ወረራ ውስጥ አፈወርቅ በፋሽስቶች ዘንድ እጅግ የተከበረ ባንዳ ሆነ። ጣሊያኖችም የመጨረሻውን ማዕረግ ሰጡት። “አፈ ቄሳር” አሉት። በፕሮፌሰርነቱ፣ በነጋድራስነቱ ለሀገሩ ኢትዮጵያ ብዙ የታገለው ይህ ሠው እንደገና ደግሞ ለኢጣሊያኖች አድሮ “አፈ ቄሳር” ተባለ።

ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወርረው አምሰት ዓመታት በቆዩባቸው ጊዜያት ሁለት የአማርኛ ሕትመቶችን ለህዝብ ያሰራጩ ነበር። አንደኛው “የሮማ ብርሐን” የተሰኘ መጽሔት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “የቄሳር መንግስት መልዕክተኛ” የተሰኘ ጋዜጣ በአማርኛ ቋንቋ ይዘጋጁ ነበር። ፕሮፌሰር፣ ነጋድራስ፣ አፈ ቄሳር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ዋና አዘጋጅ ነበር። በእነዚህ ሕትመቶች ላይ ለኢጣሊያ ያደሩ ታላላቅ የኢትዮጵያ ፀሐፊያንና ደራሲያን ስራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር። ጣሊያን ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ የመጣ እንጂ ወራሪ አይደለም፤ አርበኞች በየጫካው እየተሯሯጣችሁ ከምትዋጉ ወደ ሠላም በመምጣት ከጣሊያን መንግስት ጋር ስሩ እያሉ ይፅፉ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ደራሲ ከበደ ሚካኤልም ይገኙበት ነበር።

ለዛሬ ጽሁፌ ግን ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከፃፋቸው እጅግ በርካታ አርቲክሎች መሀል “አርባ ዓመት አለጥቅም አለፈ” በሚል ርዕስ መጋቢት 4 ቀን 1930 ዓ.ም “የቄሳር መንግስት መልዕክተኛ” ከተሰኘው ጋዜጣ ላይ ያሰፈረውን እንድታነቡት እጋብዛችኋለሁ። የአድዋን ጦርነት የለኰሰ ይህ ታላቅ ደራሲ ከአርባ ዓመት በኋላ ደግሞ እንዴት ለጣሊያኖች እንዳደረ የሚያሳይ ጽሁፍ ነው። እንዲህ ይነበባል፤

“ከአድዋ እስከ ማይጨው ጦርነት ድረስ ልክ አርባ ዓመት ሆነ። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ከገባች ልክ ሃያ ሁለት ወር ሆነ። በዚያ በሃያ ሁለት ወር ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰራችውን ስራ ያደረገችውን መልካም የሚያስደንቅ ነገር ሁሉ አይቶታል። ትልቅ ተአምር ነው። ከምፅዋ እስከ ጅማ፣ እስከ ወለጋ፣ ከሐረር እስከ ጐንደር፣ ከጐንደር እስከ ቦረና፣ እስከ ሉግ፣ በየአገሩ ሁሉ የተሰራውን መንገድ በዓይናችን አየን። በዓይናችን ቀርቶ በወሬ ሰምተነው ቢሆን አናምንም ነበር። አውሪውንም አባይ እንለው ነበር።

“ከምፅዋ ጅማ ወይም ወለጋ ወይም ከፋ ወይም ሐረርና ጅጅጋ በእግር የሚጓዙት ሆኖ ቢሆን በአንድ ዓመት አይደረስም ነበር። ዛሬ ግን በኢጣሊያ ትጋት መንገድ ሁሉ ተሰርቶ ሐር የተነጠፈበት መስሎ ለስልሶ በካምዮንና በአውቶሞቢል ቢሆን ቀድሞ የአንድ ዓመት ወይም በአንድ ዓመት ተመንፈቅ ጉዞ አያልቅ የነበረው ጐዳና በሃያ አራት ሰዓት ይደረስ ጀመረ። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ሳትገባ ግን መንገድ መራቅ ብቻ አልነበረም። በረሃው ጥማቱ ሰውንም ከብቱንም ይጨርሰው ነበር።

“በደጋው ደግሞ ዝናብ ጭቃው ማጡ ከብቱን አጋሰሱን ውጦ ያስቀረው ነበር። እስንት አጋሰስ ጭነቱ ከማጥና ከዥቅዥቅ ተከቶ ለማውጣት ተቸግሮ ከዚያው ዓይኑ እያየ እስንቱ ሙቶ ሲቀር፣ ትንሽ ወንዝ ስንቱን ሠው እየጠለፈ ይወስድ ነበረ። የዛሬ ስምንት ዓመት አባይ በድንገት ሞልቶ ከጐጃም ወደ ሸዋ ለክህነት የሚሻገሩትን ሰባ ስምንት አሽከሮች (ወጣቶች) ታቦት ለማስባረክ የሚሄዱትን ቄሶች ጨምሮ ታቦት በጀርባቸው እንዳዘሉ ጠርጐ መውሰዱን ሁላችንም እናውቃለን። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ያገራችን ንጉሶች ምንም ቅር ሳይላቸው ለሚመጣውም ጊዜ ሠው ለማዳን አንድ ድልድይ ለመስራት ሳያስቡ ቀሩ። የኢጣሊያ መንግስት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀምበትን ሁሉ ነገር በጥቂት ጊዜ አደረገ። ተንግዲህ የሚያደርገው ነገር እንዴት ብሎ ይቆጠራል።

“አዱአ ላይ ድል ከማድረግ ድል መሆን ይሻለን ነበር። ነገሩን መርምሮ ያላወቀ ሠው ኢትዮጵያ አዱአ ላይ ቀናት፤ ድል አደረገች ይል ነበረ። ብልህና መርማሪ ሠው ግን ኢትዮጵያ አዱአ ላይ ድል ሆነች እንጂ ድል አልነሳችም። ኢትዮጵያ የቀናት ማይጨው ላይ ነው። ስለምን? ኢትዮጵያ ከዛሬ አርባ ዓመት ጀምራ በኢጣሊያ እጅ ሆና ቢሆን በዚህ በጥቂት በሃያ ሁለት ወር በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው ሥራ በአርባ ዓመት ለመስራት ይቻል የነበረውን በኀሳብ ገመድ እምንለካው ቢሆን ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጅ አገር ታምር ትለመልም ትሰማ ትሰለጥን ነበር። ይሄ እርግጥ ነው። ዛሬ ማን ነው በኢጣሊያ መምጣትና ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ በመሆንዋ ደስ ያላላቸው? መንግስት ካቀረባቸው ከአጤ ኃይለስላሴ እና አብረው ተከትለዋቸው የሄዱትም ተከትለው በመሄዳቸውና በሞኝነታቸው መጠጠት አይቀራቸውም። ይሄ እርግጥ ነው። እንኳንስ ሌላ ምቀኝነትና ቅናት ባይኖር አጤ ኃይለስላሴም መጥተው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ተገባች ወዲህ የተሰራውን ሁሉ ዕፁብ ድንቅ የሚያዩ ቢሆን እስንት ደስ ባላቸው! እስንት ባደነቁ! እስንትስ ያለፈውን መንግስታቸውን በናቁ ነበር?

ሄት ነበርሽ?

“የትግሬው አጤ ዮሐንስ በህይወታቸው ሳሉ አንድ ጊዜ ደብረ ታቦር፣ አንድ ጊዜ ቦሩ ሜዳ፣ አንድ ጊዜ መቀሌ ወይም አዱዋ (አድዋ) ይከትሙ ነበር። አንድ ቀን ይላላ ወጡና አንዲት ለከተማ መስሪያ የምትሆን ቁብታ አዩና ደስ አለቻቸው። አስተዋሉ አስተዋሉና ሄት ነበርሽ? (እስከ ዛሬ ሳላስተውልሽ) አሉ ይባላል። ይህችው ቁበታ ዛሬም ሄት ነበርሽ ነው ስሟ። አሁን እንደዚሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢጣሊያ አገዛዝ እና በሚሰራው ነገር ደስ ስላለው ሄት ነበርሽ ኢጣሊያ እስከ ዛሬ ድረስ? ምነው ቀደም ብለሽ አትመጪም ኑሯልን እያሉ በመዘግየቷ ይጠጠታል። ደስታው ብዙ ነው። ስለምን የኢጣሊያ አገዛዝ ለድሃ ምቹ ነው፤ ትክክል ነው አላደላም። ገባር እንደ ቀድሞው ምጣድ አይሸከም። እህል አይጭን፤ ዱቄት አይፈጭ፣ አጥር አያጥር፣ ቤት አይሰራ፣ ማገር አይማግር፣ ድንኳን አይጭን - አይተክል። ይሄ ሁሉ መከራ አለበት። የኢጣሊያ አገዛዝ ሁሉ በሥርዓት፣ በትዕግስት፣ ሁሉ በደግነት። አፍ እንዳመጣ ያዙት ግረፉት የለ። ከሌባ በቀር እሰሩት የለ። ሁሉም በትክክል ሁሉም በፍርዱ ነው። በዚህ ሁሉ የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ማይጨው ካሳውን አገኘ። ተካሰ።”

ሲከዱት የማይክድ፣ ሲጠሉት የማይጠላ የለም

“ሰው ሆኖ የገዛ አገሩን፣ የገዛ ወንዙን፣ እንደናት እንደባቱ አድርጐ የማይወድ የለም። ይሄ ከተፈጥሮ የመጣ ነገር ነው። ማንም ያውቀዋል። ነገር ግን ያገር ፍቅር መበርታቱ ድሃው አዛኝ ገዢ ሲያገኝ ጊዜ፣ ትክክል ፈራጅ ሲያገኝ ጊዜ፣ ታላቅና ታናሽ ወዳጅና ጠላት፣ ኃይለኛና ሰነፍ፣ ድሃና ሐብታም ሳይለይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ሳያጓድል የሚፈርድ ንጉስ ሲያገኝ ጊዜ ነው። ከእግዚአብሔር በታች ታቦት
እና የአባት ሀገር ናቸው የሚወደዱና የሚመለክባቸው። ሃይማኖትን የሚያበረታ ታቦትንና አገርን የሚያስከበር መልካም ንጉስ ነው። ታቦትን እና አገርንም የሚያስረክስ ንጉስ ነው። ታቦት ተረከሰ ደግሞ ንቁዝ የዱር እንጨት የወንዝ አለት ነው። እንደገና እስቲባረክ ድረስ ሊቀድሱበት አይበቃም።

“የተቀደሰችውን ኢትዮጵያን ያረከሷት ንጉሶችና ባለሟሎች አገረገዥዎች መኳንንቱ መሳፍንቱ ናቸው። ህዝቡን፣ ገባሩን መናቅ ብቻ አይደለም፤ ወሰንተኛ እንጂ ታገሩ ኢትዮጵያ የተወለደ አያስመስሉትም ነበር። ህዝቡን ከአገሩ ፍቅር ያፈራቀቁት እነሱ ናቸው። ከኢትዮጵያ የተፀነሱ እና የተወለዱ እነሱ ብቻ እንጂ የቀረው ህዝብ ከመጣበት አያውቅም ነበር። ወይም ከሠው አይቆጥሩትም ይንቁት ነበር።

“ስለዚህ ቤት ካልበሉበት ባዶ ድንኳን የረከሰ ቤተ-ክርስትያን አካል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን ሁሉ ጡር ያንን ሁሉ ግፍ እየተሸከመ ሲኖር ቆይቶ በመጨረሻ አመረረና እንባውን ወደ ሰማይ እየረጨ ኸረ በቃ በለን፤ ኸረ የውነተኛው ለድሃ የሚያዝን ፍርድ የማያጓድል ንጉሥ አውርድልን አምላካችን እያለ እግዚአብሔርን ለመነ፣ ተማጠነ። እግዚአብሔርም ምንም ዝግተኛ ቢሆን ጆሮው ሰሚ፣ ልቡ ሰፊ፣ የነገሩትን የማይረሳ ነውና ኑሮ ኑሮ አሁን ገና ይሄው ታላቅ የማያዳላ ለትንሽ ለታላቅ የማይል የማያዳላ ሚዛን ንጉስ ከንጉስም ንጉስ፣ የኢጣሊያን ንጉስ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ቄሣር አድርጐ ሰጠነ። ለዚህ ለትክክል ንጉስ ለዚህ ለኢጣሊያ ንጉስ፣ ለኢትዮጵያ ቄሳር እኛም በቅንነት በነብይነት በታላቅ መታመን ማገልገል መገዛት ይገባናል። እንዲህ እንደሆነ በጣም እንጠቀማለን። ኢትዮጵያም ለዘላለሙ ያልፍላታል፤ ለዘላለሙ የታደለች ትሆናለች።” በማለት ይህ ታላቅ የኢትዮጵያ ደራሲ ፅፏል።

አፈወርቅ ገ/እየሱስ ምንም እንኳ የኢጣሊያን ኃያልነት የሚያመለክቱ ጽሁፎችን በቄሣር መንግስት መልዕክተኛ ላይ ቢያሰፍርም፣ አንድ ለሀገራችን አዲስ ጉዳይ እግረመንገዱን አስተዋውቋል። ጋዜጣው ዘመናዊ የጋዜጣ አዘገጃጀት ቅርፅ የያዘ ነበር። ከእርሱ በፊት የነበሩት ጋዜጦች የማይከተሉትን ቅፅ፣ ቁጥር፣ ቀን፣ የተዋጣለት የቋንቋ አጠቃቀምን ወዘተ በተግባር ላይ አውሏል። የዚህ ታላቅ ደራሲ የህይወት መጨረሻው ክፍል እጅግ በአሳዛኝ ሁኔታ ተጠናቋል። የቋንቋ እና የሥነ-ጽሑፍ ምሁሩ ዶ/ር አምሣሉ አክሊሉ፣ አጭር የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በሚል ርዕስ በፃፉት ጥናት፣ የአፈወርቅን የመጨረሻ የህይወቱን ክፍል በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውታል።

“አፈወርቅ ገ/እየሱስ ነፃነት እንደተመለሰ የኢጣሊያ ፕሮፖጋንዳ መሣሪያ በመሆናቸው ተይዘው በመጀመሪያ ሳይፈረድባቸው በፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደመስቀል መኖሪያ ቤት ከታሰሩ በኋላ ፈፅመውታል የተባለው ወንጀል ምን እንደሆነ በሕግ ተረጋግጦ አስፈላጊውን ፍርድ እንዲያገኙ ለመንግስት ስላመለከቱ ጉዳዩ ለፍርድ ቀርቦ በኋላም ለዙፋን ችሎት ቀረበ። ዳኞች ከተቹበት በኋላ በሞት እንዲቀጡ ሲበይኑ ጥፋትህን ታምናለህ ተብለው ሲጠየቁ “ምንም ጥፋት የለብኝም፤ የሸዋ ፍርድና የጉንዳን መንገድ ነው። አንዱ ያለውን ተከትላችሁ ነው፣ አዎ ያላችሁ” ካሉ በኋላ ንጉሱ የሞቱን ቅጣት አሻሽለው ወደ እድሜ ልክ እስራት ተለውጦለታል ብለው ሲያስታውቁ በችሎት ተሰብስቦ የነበረው ህዝብ ሁሉ ለጥ ብሎ እጅ ሲነሳ ነጋድራስ አፈወርቅ ግን ቀጥ ብለው ቆመው ቀሩ” በማለት ዶ/ር አምሳሉ ይገልፃሉ። ጽሁፋቸውንም ሲቀጥሉ የሚከተለውን አክለዋል።

“እዚያ ከነበሩት አፈንጉስ ዘውዴ፤ ‘ምነው ነጋድራስ ምህረት ሲደረግልህ እጅ አትነሳም እንዴ?' ቢሏቸው፤ ‘አፈወርቅ ይታሰር ተባለ እንጂ ይፈታ ተባለ እንዴ? ለምንድን ነው እጅ የምነሳው? ለእኔ መሞት ይሻለኝ ነበር። ይህ ምህረት ሳይሆን ከሞት የከፋ የቁም ስቃይ እንድቀበል የተደረገ የግፍ ፍርድ ነው።' ብለው መልስ ሰጧቸው” ሲሉ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ፅፈዋል።

ታላቁ የአፍሪካ ደራሲ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከተፈረደበት በኋላ ጅማ ውስጥ ልዩ ስሙ ጅሬን በተባለ ቦታ ታስሮ ብዙ ጊዜ ቆየ። በመጀመሪያ እነዚያ ብዙ ያነበበባቸው ዓይኖቹ፣ ከጐንደር እስከ አዲስ አበባ፣ ከዚያም አውሮፓ ሄዶ ስልጣኔን የተመለከተባቸው ዓይኖቹ ፈሰሱ። ታወሩ። ጤናውም ታወከ። ቤት ንብረቱ ተወረሰ። ሊያሳትማቸው ያዘጋጃቸው ልዩ ልዩ ጽሁፎቹ ከጥቅም ውጪ ተደረጉ። ቤተሰቡ የሚበላው የሚጠጣው አጣ፤ ነጣ። በመጨረሻም ያ ታላቅ ደራሲ እዚያች እስር ቤት ውስጥ ከሰውና ከአጫዋቾቹ እንደተገለለ ብቻውን ሆኖ መስከረም 14/15 ቀን 1940 ዓ.ም በ79 ዓመቱ ዓለምን ተሰናበተ። 

    

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1032 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us