የሕትመት መገናኛ ብዙሐን አጀማመርና ዕድገት በኢትዮጵያ

Wednesday, 17 August 2016 13:36

 

(ክፍል ሁለት)

በጥበቡ በለጠ

የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት

አፄ ኃ/ሥላሴ የሥልጣን መንበሩን ከተረከቡ በኋላም ይህ የሕትመት እንቅስቃሴ ቀጥሎ መዋሉን ነው የምንረዳው። ከዚህ ዘመነ መንግሥት በፊት የነበሩት የማተሚያ ቤቶች በዋናነት ይንቀሣቀሱ የነበሩት በእጅ ሲሆን ይህ ለጋዜጣ ሥራ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ማወቅ ተችሏል። በመሆኑም አፄ ኃ/ሥላሴ እ.ኤ.አ በ1923 ዓ.ም የማተሚያ ቤት እንዲከፈት አደረጉ። ይህም መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ የልዑል ራስ ተፈሪ ማተሚያ በመባል ይታወቅ ነበር። ማተሚያ ቤቱ በወቅቱ ሲቋቋም በ30 ያህል ሠራተኞች ገ/ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት በሚባል ሰው ተቆጣጣሪነት ይሠራ ነበር። ይህ ሰው በስዊድን ሚሲዮን በአስመራ  የተማረ ሰው ነበር። ይህ የማተሚያ ቤት ወዲያውኑ ብርሃንና ሠላም የሚል ሥያሜ  ወጥቶለት ጋዜጦችንና መፅሐፎችን ማተም ቀጥሏል። ይህ ዓመት በሕትመት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስራ የተሠራበትና ተጠቃሽ ዓመት እንደሆነ ይነገራል።

 

በዚህ መሠረትነትም በ1917 በማተሚያ ቤቱ ስም የተሠየመው ጋዜጣ መታተም ጀመረ። ይኸው ብርሃንና ሰላም የተባለው ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ይሠራ የነበረው ገ/ክርስቶስ ተ/ሀይማኖት የተባለው የማተሚያ ቤቱ ተቆጣጣሪ ሲሆን ጋዜጣው በሣምንት እየታተመ ይወጣም ነበር። ይህ ጋዜጣ በ500 ቅጂዎች ያህል ይታተም የነበረና የስርጭቱም ሁኔታ ይካሄድ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ይናገራል።

 

ከብርሀንና ሰላም ጋዜጣ መመስረት ጥቂት ጊዜ በኋላም በየሣምንቱ እየታተሙ የሚወጡ ጋዜጦች ቁጥር 3 ደረሰ። ሁለቱ ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው አእምሮ እና ብርሃንና ሰላም ሲሆኑ፣ ሶስተኛውና በፈረንሣይኛ የሚታተመው ኩሪየር ዳ ኢትዮጵ የሚባለው ነበር። ብርሃንና ሰላም በጊዜው ገናና የነበረ ጋዜጣ እንደነበር ስቴፈን ጋሴል The beginning of printing in Abyssinia በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። ይህንንም ለማስረዳት የብርሐንና ሰላም 500 ቅጂ ስርጭትን፣ ከአእምሮ የሁለት መቶ ቅጂ ጋዜጦችን በማወዳደር አቅርበዋል። ከብርሀንና ሠላም ማተሚያ ቤት ሌላ፤ ጐሐ ጽባህ በተባለው ማተሚያ ቤት ደግሞ ከሣቴ ብርሃን የሚባል ጋዜጣ እየታተመ ይወጣ እንደነበር ታውቋል። ይህ ግን ወዲያውኑ በፋሽስት ወረራ ምክንያት እንደተቋረጠ  ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰባት ያህል ማተሚያ ቤቶች በአዲስ አበባ እንደነበሩ ሪቻርድን ፓንክረስት Foundation of Education. በተባለው መጽሐፋቸው ጠቅሠዋል። እነዚህም ማተሚያ ቤቶች፡-

 

 

1ኛ የመንግሥት ማተሚያ ቤት የነበረውና አፄ ሚኒልክ የከፈቱት

2ኛ የኮሪ የሬ ደ ኢትዮፒየ ኘሬስ በ1906 ዓ.ም የተቋቋመው፣

3ኛ የአፄ ኃ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት የነበረው ብርሀንና ሰላም /1917/

4ኛ ጐሐ ጽባሕ በ1919

5ኛ ሔርሚስ ማተሚያ ቤት በ1919 የተቋቋመና ‘ለ ኢትዮጵፒየ ኮሜርሺያሌ’ የሚባል ጋዜጣን የሚያትም

6ኛ ሉክ /LOUC/ ማተሚያ ቤት በአርመናዊው ኤች ባግዳሳሪያን /H. Bagdassarian/

7ኛ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በ1927 ዓ.ም በሁለት ሌሎች አርመናውያን በኢ.ጀራሂያን እና ጂ. ጀራሂያን E. Djerrahian and G. Djerrahian   የተቋቋሙት ናቸው።

 

በዚህ ጊዜም ከሰባት የማያንሱ ጋዜጦች የነበሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራቱ በአማርኛ ቋንቋ የነበሩ ሲሆን፣ ሁለቱ በፈንሣይኛ እና አንዱ በጣሊያንኛ ቋንቋ ይታተሙ ነበር። የአማርኛ እትሞቹ ሶስት ሣምንታዊ ሲሆኑ፣ እነዚህም የመጀመሪያውና አንጋፋው አእምሮ ሲሆን፣ በአራት ገጽ ይታተም ነበር። ሌላው ብርሃንና ሰላም ሲሆን፣ በካሻዱያ የሚመራው የብላቴን ጌታ ህሩይ አጥቢያ ኮከብ ሁለቱም ባለ ስምንት ገጽ ናቸው። አጥቢያ ኮከብ የተመሠረተው በ1927 ዓ.ም ሲሆን በተከታዩ ዓመታት ከሳቴ ብርሃን የሚባል ባለ ስምንት ገጽ ወርሀዊ ጋዜጣ እንደተቋቋመ ማወቅ ተችሏል። ከውጭ ቋንቋ ጋዜጦችም በሣምንት ሁለት ቀን የሚወጣው ባለ ስምንት ገጽ ጋዜጣ ለ ኤሪዩሪ ዳ ኢትዮጲ የተባለና ለኢትዮጵያ ኮመርሽያል የተባለ ሣምንታዊ የፈረንሣይኛ ጋዜጣ ከ12 እስከ 14 ገጽ በመያዝ ይታተሙ ነበር። ኤል ኖቲዛሪዮ /EI Notiziario / የተባለ በየአስራ ምስት ቀኑ የሚወጣ የጣሊያንኛ ጋዜጣ ከ6 እስከ 8 ገጾችን በመያዝ ከ1926 ዓ.ም ጀምሮ መውጣት ጀምሮ ነበር። ከዚህ ውጭ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሁለት የውጭ ጋዜጦች መታተም ጀምረው ነበር። እኒህም የመጀመሪያው ኤቲዮፒኮስ ኮስሞስ /Aithiopikos Kosmos/ የተባለ በፒ.ኬ. ቨሪኒዮስ /P.K. vryennios ከ1920 እስከ 1924 ዓ.ም ድረስ የታተመው ሣምንታዊ ጋዜጣ እና ኢቲዮፒካ ኒያ /Aithiopika Nea/ የተባሉት ጋዜጦች ናቸው።

 

ከዚህ በላይ በጥቅሱ ለማየት የሞከርነው በሀገር ውስጥ የታተሙትን የህትመት ውጤቶች ሲሆን፣ ከሀገር ውጭ ኢትዮጵያዊ ጋዜጣዎች ከ1928 ዓ.ም በፊት ይተታሙ ነበር። ከነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ የታተመው በአውስትራላዊው ዶ/ር ኤሪክ ቬይንዚንግ /Dr. Eric Weinzing አንዳንዴ አይቶኘየን ኮረስፖንደንዝ /Aithiopien-Korrespondenz/ በመባል የሚታወቀው ነው። ይህ ጋዜጣ በጀርመንኛ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሣይኛ የተፃፉ መጣጥፎችን የያዘና ተከታታይነት በሌለው መልኩና በተለያዩ ቦታዎች የታተም ነበር። ለመጥቀስ ያህልም በፓሪስ፣ በቪየና በ1919፣ በአዲስ አበባ ከ1920-1921 በፓሪስ እስከ 1924 ይታተሙ ነበር። የዚህ ጋዜጣ ዋና ዓላማ ተደርጐ የተገለፀውም ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ዘንድ የበለጠ እንድትታወቅ ለማስቻልና ከሌሎች ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር የሚል ነበር። ከዚህ ሌላ ለ ኢትዮጵያ ኖቪል /Le Ethiopia Nauvell  በፈረንሣዊው A. Natailer እየተዘጋጀ በየሁለት ወሩ የሚቀርበው ሲሆን፣ ሌላው ኢትዮጵያ Ethiopia የተባለው ከፓሪስ የሚመጣው ወርሃዊ እትም ነበር።

 

ከጦርነቱ በፊትና በኋላ በጣም ብዙ ጋዜጦች በውጭ ሀገር ኢትዮጵያውያን በተመለከተ እንደተቋቋሙ ታውቋል። ከዚህ መሀልም ዘቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ የተባለ ጋዜጣ በዶ/ር መላኩ በያን አዘጋጅነት በኒወዩርክ ውስጥ ይታተም ነበር። ዶክተር መላኩ በያን አሜሪካ ውስጥ በህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁ ኢትዮጵያዊ ሲሆን በዘመናቸው ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ አንድነት የሚታገሉ ታላቅ ሰው ነበሩ። ፋሽስት ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ምድር ለማባረር ከታገሉ ታላላቅ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው። የእርሳቸውም ጋዜጣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ሌላው ለቮክስ ኢትዮ /La Voix DE l’Eth./ የተሰኘው ጋዘጣ ለአጭር ጊዜ ከ1928 እስከ 1929 በፈረንሣይ ይታተም ነበር።

 

 

በኢትዮጵያ የጋዜጣ ታሪክ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው በእንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ አርበኛ በሲልሺያ ፓንክረስት አማካይነት ይታተም የነበረው ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያን ኒውስ /New Times and Ethiopian News/ የተሰኘው ጋዜጣ ነው። ለሃያ ዓመታት ከ1929 ዓ.ም እስከ 1949 ዓ.ም ታትሟል። ይህ ጋዜጣ  በመጀመሪያ ለንደን ከተማ ውስጥ ይታተም ነበር። አላማው ኢትዮጵያን ከኢጣሊያ ወረራ ማላቀቅ ነበር። የትግል ጋዜጣ ነበር። ሲልቪያ ፓንክረስት ዋና አዘጋጅ ነበረች። እነ ተመስገን ገብሬ ከሱዳን ገዳሪፍ ሆነው እንደ ሪፖርተር ወሬ አቀባዮች ነበሩ። ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ በታሪክ ውስጥ ሁነኛ ቦታ የሚሰጠው የክፉ ቀን ደራሽ ጋዜጣ ነው። ዛሬ አዲስ ዘመን እያልን የምንጠራው የመንግስት ጋዜጣ ስያሜውን ያገኘው New Times ከተሰኘው የሲልቪያ ፓንክረስት ጋዜጣ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። እናም ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ የአርበኝነት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነት ጉዳዮች ላይ ከሰራቻቸው አበርክቶዎች ባልተናነሰ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥም ያበረከተችው ውለታ ገና ብዙ ዘመን ይዘከራል።

 

 

ከላይ ለማየት እንደሞክርነው እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ በርከት ያሉ ጋዜጦች መውጣት ቢችሉም ከ1928 ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አልቻለም። ይህም ሊሆን የቻለው በአምስት ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራ ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከ1928-1933ዓ.ም በቆየው የኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ የኢትዮጵያ መገናሃ ብዙኃን እንቅስቃሴ እድገት ለአምስት ዓመት ያህል ተስተጓጉሏል። በመሆኑም ከዚህ በፊት የነበሩት የሀገሪቱ የኅትመት ውጤቶች ችግር ላይ ወደቁ። ከዚያም የኢጣሊያ የኘሮፓጋንዳ ማሠራጫ የነበሩት የቄሣር መንግሥት መልዕክተኛ እና የሮማ ብርሃን የተባሉት ጋዜች ወደ ሕትመት መጡ። የነዚህ ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ የነበሩት ፕሮፌሰር/ነጋድራስ/ አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዘብሄረ ዘጌ ናቸው። እኚህ ሰው በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ አለም ውስጥ የመጀመሪያውን ልቦለድ ጦቢያን ያሳተሙ ታላቅ ሰው ነበሩ። የተማሩት ኢጣሊያ ውስጥ ነው። የውጫሌን ውል ጣሊያኖች አዛብተው የጻፉትን ያጋለጡ ትልቅ ሰው ነበሩ። ምን እንደነካቸው ሳይታወቅ በ1929 ዓ.ም ለኢጣሊያ ባንዳነት አደሩ። ታላቁ ሰብእናቸው ተገፈፈ። ግን በታሪክ ውስጥ በጋዜጣ አዘገጃጀት ክፍል የባንዳ ቢሆንም የሚጠቀስ ስራ አበርክተዋል።

 

 

በሌላ በኩል ደግሞ ባንዲራችን የተሰኘው የጦር ሜዳ ጋዜጣ በአማርኛና በአረብኛ ይሠራጭ ነበር። ይህ ጋዜጣ ዓላማው የኢትዮጵያን አርበኞች የጦር ሜዳ ውሎ ማብሠሪያ ነበር። ይህ ባንዲራችን የተሠኘው ጋዜጣ ከጠላት መባረር በኋላ 1933 ዓ.ም ላይ ስሙን ወደ ሰንደቅ ዓላማችን ቀይሮ በየሣምንቱ መታተም ቀጥሏል። ከላይ የተጠቀሰው የወራሪው መንግሥት ልሣን የነበረው የቄሣር መንግሥት ጋዜጣ በአብዛኛው ስለ ቄሣር መንግሥት ገናናነት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቄሣር ለጥ ሰጥ  ብሎ መገዛት እንዳለበት የሚያሳስብ ይዘት ያለው ጋዜጣ ነው።

 

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት በሀገር ውስጥ የነበሩት ጋዜጦች ቢታገዱም በጐረቤት ሀገሮች በአማርኛ ቋንቋ እየታተሙ ወደ ሀገር ውስጥ በሥውር የሚሠራጩ ጋዜጦች ነበሩ። ምናልባትም እኒህን ጋዜጦች የሚያዘጋጁት እንደ ተመስገን ገብሬ ያሉ በስደት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ሣይሆኑ አይቀሩም ተብሎ ይገመት ነበር። ከዚህም መሀከል ከላይ የአርበኞች የትግል ጥንካሬ በመግለጽ በኩል የጠቀሰነው ባንዲራችን በኋላም ሰንደቅ ዓላማችን የተሰኘው አንዱ ነበር። ባንዲራችን እስከ ጥር 1933 ዓ.ም ድረስ በካርቱም ውስጥ ሀያ ስምንት ጊዜ ታትሞ በሀገር ውስጥ እንደተሠራጨ የተፃፉ ጽሑፎች ያስረዳሉ። ከነፃነት በኋላም ከሚያዚያ 1 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በሣምንት ሁለት ጊዜ ረቡዕና ቅዳሜ ዕለት እየታተመ መውጣቱን ቀጥሎ ነበር።

 

ፋሽስት ኢጣሊያ ከሀገር ከተባረረች በኋላም አንድ ተጨማሪ የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጣ እንደተመሠረተ ማየት ይቻላል። ይህም ጋዜጣ እስካሁን በሕትመት ላይ ያለው አዲሰ ዘመን ጋዜጣ ነው። በጊዜው ንጉሱ የተቋረጠውን የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥልና ሕዝቡ በአዲስ መልክ እንዲነሣሣ መሻታቸው ይህንንም የሚያስፈጽምላቸው ጋዜጣ ስላስፈለጋቸው አንድ ጋዜጣ እንዲቋቋም አዘዙ። ሰብስቤ ዓለሙ ስለ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አመሠራረት ባደረጉት ጥናት ላይ እንደገለፁት ንጉሡ ትዕዛዙን ያስተላለፉት በጊዜው ለነበሩት ጋዜጠኛ ለወልደ ጊዩርጊስ ወልደ ዮሐንስ ነበር። ወ/ጊዩርጊስም ሌሎች የበታች ሹሞችንና ጋዜጠኞችን ሰብስበው አዲስ ይውጣ ለተባለው ጋዜጣ ስም ብርሀንና ሰላም ይባል ሲል ሀሣብ አቀረቡ። ተሰብሣቢዎቹም በርዕሱ ላይ ተቃውሞ በማሰማታቸው ወ/ጊዩርጊስ ያዘጋጅት ርዕስ ካለ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። ወ/ጊዩርጊስም አዲስ ልደትና አዲስ ዘመን የተሰኙ ሁለት ርዕሶችን አቀረቡ። ከብዙ ክርክር በኋላ አዲስ ዘመን የሚለው ስም የተሻለ መስሎ ስለተገኘ ለጋዜጣው ተመረጠ። ንጉሡም ስያሜውን ስለአፀደቁት አዲስ ዘመን ተብሎ ተሰየመ የሚል  እንደምታ ያለው ጽሑፍ ቀርቧል።

 

በዚህ መሠረትም አዲስ ዘመን ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ወጣ። በዚህ ጋዜጣ የመጀመሪያ ገጽ ላይም ይህ ቀን ላዲሲቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ቀን መክፈቻ ነው ሲሉ ግርማዊነታቸው ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በተናገሩት መሠረት አዲስ ዘመን ተብሎ ተሰየመ የሚል ቃል ተጽፎ ይገኛል። ይህ ጋዜጣ ከግንቦት 30 ቀን 1933 እስከ ታህሳስ 1954 ድረስ በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ሲታተም ቆይቶ ከታህሣሥ 1951 ጀምሮ በየቀኑ /ከሰኞ በቀር/ እየታተመ እስከ አሁን በማገልገል ላይ ይገኛል።

 

አዲስ ዘመን በኋላም በስያሜው የቀድሞውን ቃል አዋጅ ነጋሪ ለመዘከር የተሰየመውና የመንግሥትን ደንቦችና ሌሎችንም ኦፊሴላዊ መግለጫዎችን እትም የሚያወጣው የመንግስት ጋዜጣ ነጋሪት ጋዜጣ በሚል ተሰይሞ በ1935 ዓ.ም በይፋ ታትሞ መውጣት ጀምሯል።

 

ሌላው ደግሞ የዚሁ አዋጅ ነጋሪ እንግሊዝኛዊ ስያሜ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ በ1935 ዓ.ም ተቋቁሞ ይገኛል። የዚህ ጋዜ አዘጋጅ የነበረው እንግሊዛዊው ጆን ሲምኘሰን ሲሆን፣ ለውጭ ሀገር አንባቢዎችና ጐብኝዎች ጠቃሚ የዜና ምንጭ እንዲሆን ስለ ኢትዮጵያና ስለሕዝቧ ለብዙ ሰዎች ማስተማር እንዲቻል… ወዘተ ለመሣሠሉት ተግባሮች ታስቦ የተጀመረ ጋዜጣ ነው። ሔራልድ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያን አዘጋጆች መዘጋጀት የጀመረው ከሕዳር 14 ቀን 1951 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

 

 

ከዚህ ውጭ ከነፃነት በኋላ በ1933 ዓ.ም መታተም የጀመረውና ለውጭ ዲኘሎማቶች የወሬ ምንጭ እንዲሆን ታስቦ መንግሥት በሁለት ቋንቋዎች በአንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ የሚያሣትመው ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ይገኛል። በተጨማሪም በጊዜው አያሌ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሕትመት ላይ ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ብርሃንና ሰላም 1934 ዓ.ም፣ የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ 1945 ዓ.ም፣ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ 1948 ዓ.ም፣ መነን 1948 ዓ.ም፣ ወታደርና ዓላማው፣ ድምጸ ተዋህዶ፣ ዜና ቤተ-ክርስቲያን 1939 የመሣሰሉት ከብዙ በጥቂቱ  የሚጠቀሱ ናቸው።

በማተሚያ ቤት ደረጃም የአ.አ የንግድ ም/ቤቶች፣ አርቲስቲክ፣ የንግድ፣ የሸዋ፣ የሴንትራል፣ የመርሐ ጥበብ፣ የትንሣኤ፣ የተስፋ ገብረስላሴ፣ የኢትዮጵያ፣ የቅ/ጊዮርጊስና የኮከብ ማተሚያ ቤቶች ይጠቀሣሉ።

 

በዚህ ዘመን እስከ 1950ዎቹ አጋማሽ ድረስ የሕትመት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ የሚገኝበት ወቅት ሲሆን በዘመኑ ከፍተኛ የሕትመት ምርት የተገኘበት ወቅት እንደነበር ማጤን ይቻላል። አሁን በመንግሥት የመገናኛ ብዙሀንነት የሚታወቁት ጋዜጦች የዚህ ዘመን ውጤቶች መሆናቸውንም ልብ ይሏል።

 

ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የአፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ውጥረት ላይ የነበረበት ወቅት ነው። የገበሬዎች ተከታታይ አመጽ፣ የተማሪዎች ጉምጉምታ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ … ወዘተ የመሣሠሉት ክስተቶች የመንግሥቱን ሕላዊ እያሣጠሩት መጥተው ወደ ለውጥ በመገፋፋት የአፄውን መንግሥት ከሥልጣን በማውረድ በሀገሪቱ የወታደራዊ አገዛዝ እንዲሠፍን ሁኔታዎች የተመቻቹበት ወቅት ነው 1950ዎቹ። ቀስ በቀስ ንጉሱ ስርአት ተገረሰሰ። አብዮት መጣ። አዲስ የአብዮት መዝሙሮች ተቀነቀኑ። ኢትዮጵያ ወደ ያልታሰበ ጎዳና መጓዝ ጀመረች።

 

ፕሬስ ከ1966-1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ

ይህ ዘመን ከላይ ገረፍ ገረፍ አርገን በጠቃቀስናቸው አብይ ሁኔታዎች ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሀገሪቱን ሲገዛ የነበረው ንጉሣዊ አገዛዝ የወደቀበትና በምትኩም ወታደራዊ አገዛዝ የሠፈነበት ወቅት ነው። ደርግ በ1966 ዓ.ም ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በተለይ ለአገዛዙ ያመቸው ዘንድ የተለያዩ መዋቅሮችን መዘርጋት የጀመረበት ወቅት ነበር። በዚህ ዘመን በተለየ መልኩ በመጥፎ ሁኔታ የሚዘከረው የነጭ ሽብርና የቀይ ሽብር ጭፍጨፋዎች የተካሔዱበት ሀገሪቱ ተከታታይ በሆነ ድርቅ የተጐዳችበት፣ ሀገሪቱ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን መከተል የጀመረችበት፣ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል በወቅቱ ተገንጣይ ከተሠኙ ቡድኖች ጋር ከፍተኛ ውጊያ ይደረግ የነበረበት፣ እንደ አፄው ዘመን መንግሥት ያልተሣካ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበት ወቅት መሆኑ ከሚጠቀሱት አጠቃላይ ክስተቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

ይህንን ሁኔታ መሠረት በማድረግ በወቅቱ የነበረውን የመገናኛ ብዙኃን እንቅስቃሴ ስንመለከት ሁሉም የመገናኛ ብዙኋን በሠራተኛው ፓርቲ ቁጥጥር ስር በማስታወቂያና ብሔራዊ መምሪያ መሪነት መንቀሣቀስ የጀመሩበት ወቅት ነው።

በ1969 ዓ.ም ደርግ የኢንፎርሜሽን ዘርፎችን ለመቆጣጠር እንዲያመቸው ከድርጅትነት ወደ መምሪያ ዝቅ አድርጐ በተማከለ አሠራር እንዲወድቅ ወስኖ የሚቆጣጠረውን አካልም ማስታወቂያና መርሃብሔር ሚኒስቴር ብሎ እንዲሰየም አደረገ። (ልሣነ ማስታወቂያ ገጽ-17)

 

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የመንግሥትና የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ይመዘግባል፤ ያስተዳድራል፤ ይቆጣጠራል፤ በተጨማሪም የራዲዮና የቴሌቪዥን፣ የኦዲዮ ቪቶዋል አገልግሎትና አገራዊ ዜናዎችን /Domestic News/ የሚዘግበውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ይቆጣጠራል። የዜና ይዘቶች በሚ/ር ደረጃ ባሉ የመረጃ ክፍሉ ኮሚቴ አባሎች ደንብና ሥርዓት የሚታዘዙ ነበሩ። በመንግሥት በኩል በህትመት ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባትና መሠራጨት ላይ የሚደረጉ ገደቦችም ሌላ የማቀበያ ዘዴዎች ነበሩ።

 

ለምሣሌ ያህልም በ1970ዎቹ የመገናኛ ብዙሀን በሀገሪቱ ስለደረሰው የድርቅ ሁኔታ በተለይም ደግሞ በስሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ስለነበረው ሁኔታ መዘገብ አይችሉም ነበር። ለዚህ ምክንያትም ሕዝቡ ስለድርቁ የማወቅ ዕድል አላጋጠመውም ነበር። ለዚህ  መገናኛ ብዙሃን ነፃ በሆነ መንገድ ሀሣባቸውን ከመግለጽ የመንግሥቱ የኘሮፖጋንዳና የቅስቀሣ መሣሪያ በመሆን የሕዝቡን የማወቅ የማስተማርና የማዝናናት ሁኔታ ሳያሟሉ ቀሩ።

 

 

እኒህን ሁኔታዎች ከተመለከትን በኋላ ፊታችንን ወደ ጋዜጦች መለስ ያደረግን ንደሆነ በዚህ ዘመን የምናገኛቸው ብቸኛ ዕለታዊዎች ቀድሞ በተጠቀሰው ዘመን የተቋቋሙት የአማርኛ ቋንቋ አዲስ ዘመን እና የእንግሊዝኛው ቋንቋው ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ናቸው። አዲስ ዘመን በወቅቱ በ30.000 ቅጂዎች የሚታተምና አንዳንዴ በተለያዩ ምክንያቶች ወይም የመንግሥት ክብረበዓላት ማለት ይቻላል በእጥፍ አድጐ የሚታተም ነበር። የእንግሊዝኛው ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድ ደግሞ በ6500 ቅጂ የተወሰነ አካሄድ  ነበረው። ከዚህ ውጭ በትግረኛ ቋንቋ የሚታተም ህብረት የተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ በአስመራ ከተማ የነበረ ሲሆን ይህ ጋዜጣም ወደአራት ሺህ ቅጂዎች አካባቢ ይሠራጭ ነበር። አራት ሣምታዊ ጋዜጦች በማስታወቂያና መርሃብሔር መምሪያ ይታተሙ ነበር። እኒህም አል ዓለም በአረብኛ ቋንቋ፣ በሬሣ በኦሮምኛ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያ እና የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ሁለቱም በአማርኛ ቋንቋ ነበሩ።  ሌላው በዘመኑ ተጠቃሽ የነበረው ሳምንታዊ ጋዜጣ ከፍተኛ ቅጂን በማሣተም ይታወቅ የነበረውና በሠራተኛው ፓርቲ /ኢሠፓ/ ይታተም የነበረው ሠርቶ አደር ጋዜጣ ነው። የዚህ ጋዜጣ የሥርጭት መጠን ወደ 100,000 (መቶ ሺ) አካባቢ ይደርስ እንደነበር ይገለጻል። ፓርቲው በተጨማሪ መስከረም መጽሔት Theoretical quarterly ያሳትም ነበር። ፖሊስና የወታደሩ ክፍልም በሁለት ሣምንት የሚወጣ ህትመት ሲኖራቸው፣ የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንም በበኩሏ ማዕዶት እና ትንሣኤ የሚባሉ ሁለት የህትመት ውጤቶች ነበሯት።

በወቅቱ የነበረው የጋዜጦች ሥርጭት የተመለከትን እንደሆነ በቂ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስችላል። ይህም በዋናነት በትራንስፖርት እጥረት እንደነበር ነው የምንረዳው። በጊዜው ከነበሩት 101 አውራጃዎች ውስጥ አርባ አምስት ያህሉ ዕለታዊ ጋዜጦችን የማንበብ ዕድል የላቸውም ነበር። ከነዚህ የህትመት ውጤቶች ውስጥ አዲስ አበባ ከሁለቱ ዋና ጋዜጦች 50 በመቶውን ስትወስድ፣ በእንግሊዝኛ ከሚታተመው ደግሞ 80 በመቶውን ትወስድ ነበር። እዚህ ላይ ግን ከትራንስፖርት ችግር ባሻገር ማጤን የቻልኩት ሌላ ነገር አለ። ይህም ምን ያህል ነው ማንበብ የሚችለው ህዝብ የሚለውን ነው። በእርግጥ የዘመኑ አንድ አብይ ባህሪ ማንበብና መፃፍ የሚችለው ሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ነው። ይኸውም በዋናነት በመሠረት ትምህርት ዘመቻ አማካኝነት የተደረገ ለውጥ ሲሆን ይህንን ያህል ማስመካት ደረጃ ላይ አድርሶ የሚያናግር ግን አልነበረም። በመሆኑም ከትራንስፖርት እጥረት ባሻገር የሕዝቡ በወጉ አለመማር የጋዜጣዎችን ተነባቢነት እንደሚቀንሠውና ይህም በወቅቱ የተከሠተ ጉዳይ እንደ ነበር ነው የተረዳሁት።

ከዚህ ሌላ በወቅቱ በመንግሥት በኩል የሚደረጉትን የቁጥጥር ጫናዎች ተቋቁመውና ጥሰው ወደሀገሪቱ የሚገቡ አያሌ የህትመት ውጤቶች ነበሩ። ይህም ሊሆን የቻለበት ዋናው ምክንያት በዋና ከተማዋ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መ/ቤቶች በዋናነት በከተማዋ የመኖራቸው ጉዳይ ነው።

 

ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የውጭ የዜና ወኪሎች ከአዲስ አበባ ዘገባዎቻቸውን ያስተላለፉ ነበር። አጃንስ ፍራንስ ኘሬስ AFP እና ሬውተርስ Reuters የዜና ዘጋቢዎች ነበሯቸው። ነገር ግን የሁለቱም የዜና ወኪል ዘጋቢዎች በ1970ዎቹ ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ ተደርገዋል። ከዚህ ሌላ ታስ /Tass /APN እና (USSR) And (Germany ANSA (Italy) Tanjug (Yougoslavia) Preensa Latina (Cuba) እና Xinhua News Agency (China) የተባሉ የዜና ወኪሎች ነበሩ። የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚ/ር ለውጭ ጋዜጠኞች የመግብያ ፈቃድ የሚሠጥ ሲሆን የጋዜኞቹ እንቅስቃሴ ግን በከፍተኛ ሁኔታ በክትትል ሥር የነበረበት ወቅት ነበር።

 

በግንቦት 1981 ዓ.ም የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለመዘገብ የመጡ ሁለት የBBC ጋዜጠኞችና አንድ የሬውተር ፎቶግራፍ አንሺ ያለምንም ምክንያት ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ ሲታወስና ከላይ ከተባረሩት ከአጃንስ ፍራንስ ኘሬስና ከሬውተርስ ዘጋቢዎች ጋር ደምረን ስናየው በወቅቱ የነበረው መንግሥት ከምዕራባውያን ጋር የነበረው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ የሚወሣ እንዳልሆነ ይታመናል።

 

ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የነበረውን የሕትመት እንቅስቃሴ የተመለከትን እንደሆነ ከአብዮቱ ፍንዳታ በፊት የነበረው ሠፊ የሕትመት እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየከሠመ መጥቶ ጥቂትና በጣት ሊቆጠሩ ከሚችሉት የሠራተኛው ፓርቲ ኘሮፓጋንዳ ማካሔጃዎች በስተቀር እንዳይታተሙ ታግደዋል። ከነዚህም መሀከል መነን መጽሔት አዲስ ስዋርን፣ ኢትዮጵያን ሚረር፣ ጐህ፣ ሲጠቀሱ ከላይ ላነሳነው የኘሮፓጋንዳ ሥራ ማስረጃነትም የሠርቶ አደርን ከአሥራ አምስት ቀን ወደ ሣምንታዊነት መለወጥና የቅጂ ብዛት በእጥፍ የማደጉን ሁኔታ ማጤን ይቻላል።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
15784 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us