የድምጻዊ ጸሐዬ ዮሐንስ እና የቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ሀ.ሁ…..

Wednesday, 07 September 2016 14:00

 

በጥበቡ በለጠ

ባለፈው ቅዳሜ ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአቤል ሲኒማ ውስጥ እጅግ የተደሰትኩበትን መርሀ ግብር በመታደሜ ነው ዛሬ ላወጋችሁ ብቅ ያልኩት። መርሀ ግብሩ የበጎ ሰው ሽልማት ነው። እነዚህ በጎ ሰዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው መልካም ተግባር ያከናወኑ ናቸው። አብዛኛዎቹ በሕይወት እያሉ ለዚህ ሽልማትና እውቅና መብቃታቸው ሌላው በጣም ጥሩ ጎኑ ነው። ይህ ሽልማትና እውቅና ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ መጓዝ መቻሉ በራሱ የወደፊቱን ተስፋ ያበራልናል። ምክንያቱም በሀገራችን ውስጥ በተለይ ሽልማትን በተመለከተ ሁሌ ብቅ እያለ ድርግም የሚልበትን ሁኔታ ላስተዋለ ሰው ይህ የበጎ ሰው ሽልማት ተስፋን ይሰጣል። ሽልማት የሚባለው መንፈስ ሁሉ የጠፋበት ዘመን ላይ ነበርን። በአንድ ጊዜ ብዙ ሺ ገበሬዎች ሚሊየነሮች ሆኑ ተብሎ ሲሸለሙ እናይና በአመቱ ደግሞ ብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን በአስከፊ ረሀብ ውስጥ ናቸው የሚል ዜና ይመጣል። እናም የሽልማት ትርጉሙ የጠፋብኝ ያን ሰሞን ነበር።

በዚህ በዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት ላይ 33 ኢትዮጵያዊያን ሽልማትና እውቅና አግኝተዋል። እሰየው ይባላል። ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ እለት የሚባል አባባልም በሀገራችን አለ። ውድ ኮሚቴዎች ደግ አድርጋችኋል። ደግ ደጉን ያድርግላችሁ!

ከሽልማቶቹ ውስጥ ለየት ያለው የቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ነበሩ። ዛሬ በሕይወት የሌሉት እኝህ የፊደልና የእውቀት አባት በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ እና አርበኝነት ውስጥ ግዙፍ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ከ30 ዓመታት በላይ ውብ ድምጽ ይዞ በክብር የቆየው ድምጻዊ ጸሀይ ዮሀንስ የ1970 ዓ.ም ቀዳማይ ዘፈኑን ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገሩ… እያለ ሲያቀነቅን የተስፋ ገብረስላሴን መንፈስ ከፍ አድርጎታል። የኛንም መንፈስ ከፍ አድርጎልናል።

ፊደሉን ሳየው መልሰው ያዩኛል

ሌላው ሲያነባቸው እኔን ይጨንቀኛል

የዘመድ ሰላምታ ሲመጣ ደብዳቤ

መርዶ እየመሰለኝ ሲደነግጥ ልቤ

ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገር…

(ጸሐዬ ዮሐንስ)

ስለ ተስፋ ገብረስላሴ አንዳንድ ነገሮችን እንጨዋወት። በሙዚቃ ጸሐዬ ያጅበናል።

አንድ ህፃን ልክ አራት አመት ሲሞላው ከፊደል ገበታ ጋር መተያየት ይጀምራል። ' በል፣ ' በል... እየተባለ ይረዳል። የዓለምን ምስጢር፣ ውጣ ውረድ በፊደሎች መቁጠር ይጀምራል። እነዚያ ፊደሎች እየሰፉ እየተገጣጠሙ ሲመጡ ቃል ሆነው ሀሳብ ያስተላልፋሉ። ሀሣብ ደግሞ ብዙ አይነት እውነታዎችን በውስጡ የያዘ ነው። የህይወት ጉዞ እንግዲህ ተጀመረ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በየቤታችን ውስጥ ሀሁ ያስቆጠሩን ማናቸው ብንባል ብዙ ሚሊዮኖች አንድ ላይ “ተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ” የሚል መልስ እንሰጣለን። ምክንያቱም በዚያ በጨቅላ ጭንቅላታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንበብ የጀመርነው ከሀሁ' ቀጥሎ የተስፋ ገ/ሥላሴ ስም ነውና። ዛሬም ድረስ በዚሁ የህይወት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያችንና ዜጐቿ እየቀጠሉ ነው። እናም ስማቸውን ትውልድ እየተቀባበለ እየጠራ እየተማረባቸው የዘመን ኬላን እየሰበረ የሚምዘገዘገው ስም ባለቤት ተስፋ ገ/ሥላሴ ማን ናቸው?

በርግጥ ዛሬ የምናወራው እንደ አባትም እናትም ሆኖ ያሳደገንን የፊደል ገበታ አዘጋጅተውልን ወደ ማይቀረው ዓለም የተሰናበቱትን እኝህ ሰው ታላቅ የታሪክ ውቅያኖስ ያላቸው ናቸው። ከዚያ ታሪካቸው ነው ጭልፍ እያደረግን የምንጨዋወተው።

ዛሬ የብዙ ጥበበኞች እና የጥበብ አድናቂዎች መታደሚያ የሆነው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን ከመሠረቱት ጐምቱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ቀኛዝማች ተስፋ ገ/ሥላሴ በሰሜን ሸዋ በቡልጋና በረኸት ተድላ ማርያም ወረዳ ክታብ ወይራ አክርሚት ከተባለ ቀበሌ ከአባታቸው ከመምህር ገብረ ሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሥዕለ ሚካኤል ወልደ አብ በ1895 ዓ.ም ታህሳስ 24 ቀን ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ፊደል ቆጠሩ። ወላጆቻቸው ታዲያ ከትምህርቱ ይልቅ ከብቶች እያገዱ እንዲያገለግሏቸው በመሻታቸው አያታቸው መምህር ቢልልኝ ከወላጆቻቸው ነጥቀው እንዲያስተምሩላቸው ለመምህር ገብረ አብ ወስደው ሰጧቸው።

መምህር ገብረ አብም የቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ የአያታቸው የመምህር ወልደ አብ ደቀ መዝመር ስለነበሩ በደስታ ተቀበሏቸው። ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ በመምህር ወልደ አብ ዘንድ ንባብ፣ ዳዊትና ውዳሴ ማርያም መልክአ ማርያምና መልክአ ኢየሱስ ሰአታት ዘሌሊት አጠናቀው ተማሩ። ግብረ ዲቁናንም በሚገባ አጥንተው እንደጨረሱ አዲስ አበባ መጥተው ከአቡነ ማቴዎስ ዘንድ የዲቁና ማዕረግ ከተቀበሉ በኋላ ተመልሰው አገራቸው ቡልጋ ገብተው በአክርሚት ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን በዲቁና ማገልገል ጀመሩ።

ከዚሁ የ80 ቀን መታሰቢያ ከተዘጋጀላቸው ጽሁፍ ታሪካቸውን መረዳት እንደሚቻለው “አባታቸው መምሬ ገብረ ሥላሴ ቢልልኝ ከቅስና ሙያቸውና ከግብርና ሥራቸው ውጭ በትርፍ ጊዜያቸው ብራና እየፋቁ ከዕፅዋት ቀለም እያነጠሩ የፀሎትና ለአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጡ መጽሀፍ ድጓና ሌሎችንም መፃህፍት ይፅፉና ያበረክቱ ስለነበር እሳቸውም በቤተ-ክርስቲያን አካባቢ በግብረ ዲቁና እያገለገሉ ሳለ የወላጅ አባታቸውን አሠረ ፍኖት በመከተል የፍየል ቆዳ በእንጨት ወጥረው እየፋቁ፣ በመድመፅ እየደመፁ፣ ብራናውን በወሳፍቻ እያሰመሩ፣ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፀዋት እያነጠሩ በመቃ ብዕር እየፃፉ፣ የዘወትር ፀሎት ስአታት ዘሌሊት ገበታ ሐዋርያ ሌላም መፃህፍትን እየፃፉ በማራባት ወገናቸውን ጠቅመው ራሳቸውም መጠቀም ጀምሩ” ይላል።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ የ15 አመት ወጣት በነበሩበት ወቅት በ1909 ዓ.ም አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ የሚገኙት ከአጐታቸው ከሊቀ ጠበብት ዘንድ መጥተው ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት ካደረጉና ከተማውንም ከተለማመዱ በኋላ በጊዜው በአዲስ አበባ የዕፅዋት ችግር ስላልነበረ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፀዋት እየቀመሙና እያነጠሩ በዚያው በመቃ ብዕር ቀርፀው በ1910 ዓ.ም የፊደላትን ሆሄያት እየፃፉ በዝርግ ክርታስ እየለጠፉ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ላራዳ በማዞር አንድ ፊደል በአንድ መሐለቅ መሸጥ ጀመሩ በማለት ዛሬም ድረስ ሆነ ወደፊትም ስማቸውን በክብር የሚያስጠራው ስራቸው መወሳት ይጀምራል።

የመርሐ ጥበብ ማተሚያ ቤት እንደተቋቋመ “እውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚለውን ኃይለ ቃል አርእስት በመስጠት ፊደልን፣ ፊደለ ሐዋርያትንና አቡጊዳን በሦስት ረድፍ እያዘጋጁ በማሳተም በመላ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመሩ። እናም በመላ ገጠሪቱ የሚኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊደል ሆሄያት ጋር ዓይን ለዓይን ተያየ።

የብርሐንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቋቋም ከሽያጩ ሩብ እየከፈላቸው የጋዜጣና የበራሪ ጽሁፎችን ሽያጭ በኮንትራት በመያዝ መሸጥ መጀመራቸውን ያለፈ ታሪካቸው ያወሳል።

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ ባላቸው ፅኑ ፍላጐት የተነሳ በ1921 ዓ.ም በዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በቤተ-ክህነቱ ግቢ ውስጥ ቦታ ሰጧቸው። ከዚያም በሰው ሃይል የሚሠራ የማተሚያ ማሽን ገዝተው ከፊደል ጀምሮ ያሉትን የንባብ መሣሪያ የፀሎትና የሃይማኖት መፃህፍትንና እንዲሁም ከራሳቸው አዕምሮ የሚፈልቀውን የስነ-ጽሁፍ፣ ግጥሞችና እንደነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ያሉ የዘመኑ ታዋቂ ደራሲያን የፃፉትን ግጥሞችንና የጊዜውን ሁኔታ የሚጠቁሙ ዝርው ጽሁፎችን በበራሪ ወረቀቶች እያተሙ መሸጥ ጀመሩ።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ በተለይም የሚታወቁበት ሌላው ገጽታቸው ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር በምትዘጋጅበትና እንቅስቃሴም በጀመረችበት ወቅት ህዝቡ ተደራጅቶ ወራሪዎችን እንዲከላከል ከነ ዮፍታሐ ንጉሤ ጋር በመሆን ብዙ የሠሩ ባለውለታ ናቸው። በተለይም ደግሞ በትጋታቸው የተነሳ በእጃቸው ባስገቡት የህትመት መሣሪያ የተነሳ በራሪ ፅሁፎችን በማተም “ኢትየጵያ ልትወረር ነው። ልጆቿ የሆናችሁ ሁሉ ተነሱ አድኗት” እያሉ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከአርበኞች ማህደር ውስጥ ስማቸውን በወርቅ ቀለም የሚያፅፍላቸው ነው።

በተለይም ደግሞ በነበራቸው የስነ-ግጥም ችሎታ ልክ የዛሬ 79 አመት ከኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፀረ-ፋሽስታዊ ትግል እንዲያካሂዱ የሚከተለውን ወኔ ቀስቃሽ ግጥም ጽፈዋል።

 

ከባህር እየወጣ መጣልን ዓሣው፣

በሰይፍ እየመተርን ባረር እየቆላን ፈጥነን እንብላው

ጥንት አባቶቻችን ምግባቸው ይህ ነው፣

ምነው ያሁን ልጆች ዝምታው ምንድነው?

የባህሩ ዓሣ ወጥቶ ከጐሬው፣

አጥማጁ አንቆ እንጂ ስጋውን ይብላው።

በማለት በመላው ኢትዮጵያ ፅፈው አሠራጭተው ታጋዮች እንዲነቃቁ አድርገዋል።

ተስፋ ገ/ሥላሴ የዛሬ 16 ዓመት ከሚወዷት ኢትዮጵያ በሞት በተለዩበት ወቅት ተፅፎ ከቀረበው የህይወት ታሪካቸውና እንዲሁም በይፋ ከሚታወቀው የአርበኝነት ህይወታቸው ሰውየው በጣም ብርቱ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።

በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦርነት ባወጀችበት ወቅት ጠላት አንዳንድ የኢትየጵያን ባለስልጣናት ባላባቶች አገራቸውን ለማስካድና በስለላ ስራ ለማሰማራት በገንዘብ እየደለለ የማታለል ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ ቀኛዝማች ተስፋገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የዓፄ ምኒልክን ፎቶ ግራፍ የፅሁፋቸው አርማ በማድረግ በአድዋው ጦርነት ጊዜ ጀግኖችና ታማኞች የምኒልክ የጦር አበጋዞች የጐራው ገበየሁና ደጀዝማች ታፈሰ አባ ትንታግ፣ ባልቻ አባነፍሶ የኢትዮጵያ ጋሻ መከታ በመሆን በአላጌ በመቀሌ በአድዋ የሰሩትን የጀግንነት ሙያ በመከተል በታማኝነት የዜግነት ግዴታ መወጣት እንጂ ለገንዘብ ብሎ አገር ለጠላት አሳለፎ መስጠት እጅግ አሳፋሪ መሆኑን በመግለፅ የሚከተለውን ግጥም አቅርበዋል።

 

... የተረገመ ነው አገሩን የካዳ፣

ክብሩን ነፃነቱን አበሻን የጐዳ።

ከኢትዮጵያ ከሐበሻ ጠላት ጉቦ የበላችሁ፣

የትነው የምትበሉት አገር ሳይኖራችሁ።

ያልታመኑ ሌቦች ከሹመት ተሽረው፣

አገሪቷን ይምሩ ታማኞች ተመርጠው።

ይህን ግጥም ፅፈው በመላው ኢትዮጵያ እንዲሠራጭ አደረጉ። በዚህም የተነሳ ባለስልጣናቱ አብዛኛዎቹ ሆድ ባሳቸው አጉርመረሙ። እናም ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴን የሚጐዱበትን የህግ ክፍተት መፈለግ ጀመሩ።

በወቅቱ ማንኛውም በፅህፈት መሣሪያ ማሽን ተባዝቶ የሚሠራጭ ፅሁፍ የፅህፈት ሚኒስቴር ሳያየውና ሳይፈቅድ ወደ ህዝብ ማስገባት እንደማይቻልና ወንጀልም እንደሆነ የሚደነግግ ህግ ወጥቷል። ንጉሠ ነገሥቱም ጉዳዩን ሳያውቁት ነው ተፅፎ የተሠራጨው። እናም ተስፋ ገብረ ሥላሴን መጉጃ መንገድ ተገኘ።

ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከሆነ ከከተማው ከንቲባና የፀጥታው አስከባሪ በባላምባራስ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ እጅ ታስረው እንዲቀርቡ ሲታዘዝ በከተማው የማይገኙ ቢሆን ግን የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ደጃዝማች ገብረማርያም ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴን ካሉበት ቦታ አስፈልገው አስረው እንዲያቀርቡ ታዘዙ።

በየክፍላተ አገሩ ታትሞ የተሰራጨው ፅሁፍም ተለቅሞ እንዲመጣ ታዘዘና መፅሀፍ ሻጮችም ሁሉ ከተሠራጨው ፅሁፍ ጋር ተይዘው ታሰሩ። ይህ እንግዲህ የበጅሮንድ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም “ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያ” የተሰኘው ተውኔታቸው በ1913 ዓ.ም በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ከታገደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ የመንግሥት ዘመቻ የተደረገበት የተስፋ ገብረ ሥላሴ ፅሁፍ ነው ማለት ነው። ሀሳብን የመግለፅ መብት አፈና ሀገራችን የጀመረችባቸው አስቀያሚ ደንቦች ናቸው።

ከዚሀ ጋር በተያያዘም የተስፋ ገብረ ሥላሴ ቤተሰቦችም ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደረገ። መኖርያ ቤታቸውም ሳይቀር ታሸገ። ተስፋ ገብረ ሥላሴ ደግሞ ለስራ ጉዳይ ሐረርጌ ጨርጨር ሄደው ነበርና እዛው ያሉበት ቦታ ተያዙ። በሰንሰለትም ታስረው በቀጥታ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ፊት ቀረቡ። ንጉሡም ጠየቁ። ለመሆኑ ይህንን ፅሁፍ የት ሆነህ ፅፈህ ነው ያሰራጨኸው አሏቸው። ተስፋም መለሱ። አቡነ ቄርሎስ ግቢ አሉ። ጉዳዩ አሳሳቢ ሆነ። የሀገሪቱ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስም ተጠሩ።

ጃንሆይም እዝን ብለው አባታችን እንደምን በብፁዕነትዎ ግቢ ወንጀል ተሠራ' ብለው ጠየቋቸው። ጳጳሱም መንፈሣዊ ልዕልና የነበራቸው ሲሆኑ እንዲህም ብለው መለሱ። “አገራችሁን አትክዱ ከጠላት ጉቦ አትቀበሉ ብሎ ስለሰበከ ይህም ወንጀል ነው?” ሲሉ መልስ ሰጡ።

ጃንሆይም የፅሁፍ ነገር በደንብ መጣራት አለበት በማለታቸው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብጥያ ወርደው እንዲቆዩ ተደረገ። ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ስድስት ወራትን በእስር ማቀዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያም በፃፈው ስነ-ግጥም ለመጀመሪያ ጊዜ በእስር ፍዳ ያየ ፀሀፊ በመባል በታሪክ ተመዝግበዋል።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ ከእስር የተፈቱት የኢጣሊያ ፋሽስቶች እየገፉ በሚመጡበት ጊዜ ሁለተኛ ያለመንግሥት ፈቃድ አንዲህ አይነቱን እያተመ ለህዝብ እንዳያሰራጭ ሁለት ዋስ ጠርቶ ይፈታ ተባሉና ምህረት ተደርጐላቸው ከእስር ተፈቱ።

ከዚያም ወራሪዎች ሰሜናዊ ኢትዮጵያን እየያዙ ሲመጡ እና የሽብር ወሬዎችን ሲነዙ ተስፋ ገብረ ሥላሴ በደረሰባቸው እንግልት ተማረው ቁጭ አላሉም። ወዲያውም 'የኢትዮጵያ ፋና' የሚል በራሪ ወረቀት እየፃፉ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን እንዲከላከሉ አበክረው ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያም በፋሽስቶች እጅ ስትወድቅ መጀመሪያ ከታሰሩ ሰዎች መካከል ተስፋ ገብረ ሥላሴ አንዱ ናቸው። ለኢጣሊያ ያደሩ ባንዳዎች ህዝብን ቀስቃሽ ፅሁፎችን ያሰራጭ ነበር ብለዋቸው ጠቆሙ። እናም ጉዳያቸው ተጣርቶ ግራዚያኒ ፊት ችሎት ላይ ቀረቡ። ባጋጣሚ የቀረቡባቸው የማስረጃ ፅሁፎች ዋና ዋናዎቹ ባለመሆናቸው ከግራዚያኒ መንጋጋ ለጥቂት አመለጡ።

ሞገስ አስገዶም እና አብረሃም ደቦጭ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ሲወረውሩ ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት አላቸው ተብለው አደጋ እንዳይደርስባቸው ቤተሰብ ወዳጅ ወተወታቸው። እናም አፍንጮ በር አካባቢ የተቀበረ የመንግሥት መሣሪያ መኖሩን ስለሚያውቁ ከታማኝ ነጋዴዎች ጋር ተነጋጋረው እሱን አስወጥተው ወደ ቡልጋ በመጓዝ ከአርበኞች ጋር ተቀላቅለዋል።

ቀኛዝማች ተስፋ በጦር ሜዳው ትግል ውስጥም ሳሉ እንግሊዝ ሀገር ካሉት ከጃንሆይ ጋር ይፃፃፉ ነበር። አንዴ ግን አብረዋቸው ጠላትን ይፋለሙ የነበሩት ራስ አበበ አረጋይ እኔ ሳላውቅ እንዴት ደብዳቤ ትፃፃፋለህ ብለው እንዳሰሯቸውም በታሪክ ተመዝግቧል። ባጋጣሚ ደግሞ ፋሽስቶች ያንን የጦር ግንባር ሲያጠቁ ተስፋ ገብረ ሥላሴን እስር ቤት ያገኛቸዋል። አዲሳባ ይዘዋቸው መጥተው ለረጅም ቀናት በእስር ድጋሚ አሰቃይዋቸው። በኋላም ተፈተው ከአርበኞች ትግል ጋር ተቀላቀሉ።

በ1933 ዓ.ም በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች ኢጣሊያን ከትምክህት ወረራዋ አጨናግፈው ሀገራቸውን ተረከቡ። ቀኛዝማች ተስፋም ወደ ሰላማዊ ሀገራቸው ሊመለሱ ሆነ። ግን በሰው ጉልበት ይሰራራ የነበረው ያ የፅህፈት መሣሪያቸው፣ ያ ኢትዮጵያዊያኖችን” ሲያነቃቃ እና ሲያስተምር የነበረ ማተሚያቸው በጣሊያኖች ተወርሶ ለሌላ ማተሚያ ቤት ተሰጥቶ ነበር። እርሳቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ በአዲስና በጋለ መንፈስ ተነሳስተው “ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” በማለት በሌላ ማተሚያ ቤት እያሳተሙ የወገናቸውን እውቀት ለማጐልበት ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል።

ከዚያም የህትመት መሣሪያ ከውጭ በማስመጣት የበለጠ በእጥፍ አድገው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ኢትዮጵያዊው ጉተንበርግ ናቸው። የህትመት ማሽንን ከመጠቀም አልፈው ይጠግኑታል፣ ያስተካክሉታል። ፋና ወጊ የማተሚያ መሣሪያ ባለቤት ናቸው።

በተለይም ደግሞ ለሀገራቸው ካበረከቷቸው ታላላቅ ስራዎች ውስጥ እኔን ሁሌም እንዳከብራቸው የሚያደርገኝ በልዩ ልዩ ጊዜ በወራሪዎች የተዘረፉ የኢትዮጵያ አብያተ-ክርስቲያናት ቅርሶች ተረስተው እንዳይቀሩ በተለያየ ዘመን እያሳተሙ በስፋት አሠራጭተዋል። ቅጂያቸው በጣም ትንሽ የሆነ ቅዱሳት መፃህፍት የብራና ፅሁፎችን በመፅሀፍ መልክ እያደረጉ ለታሪክ ትተው አልፈዋል።

የፅሁፍ ስራ፣ የፊደል ቆጠራ፣ የንባብ ችሎታ፣ ሲያሳድጉ፣ የሚሊዮን አማኞች የነፍስ ምግብ ሲያዘጋጁ የኖሩት እና ኢትዮጵያ በእውቀት አደባባይ ባለውለታዬ ብላ የምትጠራቸው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም በተወለዱ በ97 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ይህንንም በጐ ተግባራቸውን በመመልከት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በመቶ አመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ከፍተኛ ውለታ ከዋሉ ግለሰቦች መካከል በግንባር ቀደምትነት መርጧቸው ረቡዕ ግንቦት 29 ቀን 1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አዳራሽ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው ሽልማት እንዲሰጥ አድርጓል።አሁን በቅርቡ ከሀምሌ 14 እስከ 18 2008 ዓ.ም በተካሄደው ንባብ ለሕይወት በተሰኘው ትልቅ የመጻህፍት አውደ-ርእይ ላይ በሕይወት ባይኖሩም የሰሯቸው ድንቅ ተግባራት ዘላለማዊ ስለሚያርጋቸው “ተስፋ ገብረስላሴ ሕያው ናቸው” በማለት ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ነሀሴ 28 ቀን 2008ዓ.ም በተካሄደው የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ስነ-ስርአት ላይ ተስፋ ገብረስላሴ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። የእርሳቸው ስም ሲነሳም መድረኩ እጅግ ደምቋል። ድምጸ መረዋው ከያኒ ጸሐዬ ዮሀንስ “ማንበብና መጻፍ…” የተሰኘውን የ1970 ዓ.ም ዘፈኑን ሲያንጎራጉረውማ ታዳሚያን በደስታ ሲቃ ውስጥ ገቡ።¾

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
15904 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 96 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us