ጋብሮቮች እና አለቃ ገብረሐና

Wednesday, 19 March 2014 14:22

በጥበቡ በለጠ

 

ሁለቱም ስሞች የሚገርሙ ናቸው። በኢትዮጵያችን ውስጥ ጋብሮቮች እጅግ ተዋውቀዋል። እከሌ ጋብሮቮ ነው ከተበላ ከቆንቋናነት ጋር ይያዝና ነገር ግን ከዚያ የስግብግብነት ከሚመስል ሁኔታ ውስጥ የሳቅ እና የሀሴት እውነታዎችን እንሰማለን።

ለምሳሌ ጋብሮቮች የሚከተሉት ፀባይ አላቸው ይላል አረፈዓይኔ ሐጐስ።

- ቁርስ ሲጋብዙ የቢላዎቻቸውን ጫፎች ያግሉዋቸዋል። ቅቤ (ማርጋሪን) በደንብ መዛቅ እንዳይችሉ።

- ማንኛውንም ነገር ቀለም ሲቀቡ የሚለጥፉት ማስታወቂያ “ቀለም እንዳያበላሽዎ ይጠንቀቁ” የሚል ሣይሆን “ለቀለሙ እዘኑለት” የሚል ነው።

- አንዱ ጋብሮቮ ሌላውን “ውሻህ ዛሬም አንዷን ዶሮዬን በላብኝ” ይለዋል። ያም መለስ አድርጐ “እንኳን ነገርከኝ። ቀኑን ሙሉ ምንም የሚበላ ነገር አልሰጠውም” አለው።

እናም የጋብሮቮች ቀልዶች በጣም አስቂኞች፣ አመራማሪዎች ናቸው። ዕድሜ ልክ ቢያወሯቸው የማይሰለቹ ናቸው።

ባሌላ መልኩ ደግሞ ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ አለቃ ገብረሐና ብቅ ይላሉ። እርሳቸውም ተናገሯቸው የተባሉት ቀልዶች እነሆ የዘመነ ኬላን እየተሻገሩ ዛሬም ድረስ እኛንም ጭምር ያስቁናል።

ለምሳሌ አለቃ ገብረሐና ከታላላቅ መኳንንት ጋር ሲጫወቱ የሴት ነገር ተነሳና አለቃም “አንድ ቀን ከመኝታዬ ሌሊት ተነስቼ በጨለማ እየዳበስኩ ገረድ ስፈልግ የቤት ምሰሶ አገኘኝና ግንባሬን አለኝ” ብለው ዋሽተው ያስቋቸዋል። ይሄኔ አንዱ መኮንን “አባ ቆመጥ ይዘው እያወዘውዙ ቢሄዱ ኖሮ’ኮ ምሰሶ አይመታወትም ነበር” ብለው ቢያስቁባቸው፤ አጅሬ አብረው ስቀው “ጌታዬም ለካ ይህን ያውቁ ኖሯል?” በማለት አሽሟጠጡዋቸው።

እንግዲህ እነዚህን ሁለት አስቂኝ ስብዕናዎች በአንድ መፅሐፍ አካቶ ያቀረበልን አረፈዓይኔ ሐጐስ ነው። አረፈዓይኔ መፅሐፉን በሁለት በመክፈል አንደኛው “ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር” ይላል። ሁለተኛው ደግሞ “አለቃ ገብረሐና እና አስቂኝ ቀልዶቻቸው” በማለት አስፍሯቸዋል።

በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ቀልዶች ብቻ አይደሉም የቀረቡት። ስለ ጋብሮቮች ታሪክ እና ስለ አለቃ ገብረሐና ታሪክ ጭምር ነው። እናስ ጋብሮቮች እና አለቃ ገብረሐና ምንድን ናቸው?

የጋብሮቮ ታሪክ

ቱርኮች የቦልካንን ባህረ ገብ መሬት ባስገበሩበት ወቅት ቡልጋሪያዊቷ ወይዘሮ በዝሃና ልጆቿን ይዛ ከቬሊኮ ቱርኖቫ (የቡልጋርያ ርዕሰ ከተማ) እንደተሰደደች አፈ ታሪክ ይናገራል በማለት አረፈዓይኔ ፅፏል። ሲቀጥልም ከቡልጋሪያዊቷ ልጆች አንደኛው ራቾ ይባል ነበር። ቀጥቃጩ ራቾ የሰፈረውም በድንጋያማው ያንትሪ ወንዝ ዳርቻ ነበር። ራቾ የቆረቆራት መንደር በአሁኑ ጊዜ “ጋብሮቮ” ትባላለች። ለቆርቋሪዋ ራቾ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ፣ የጋብሮቮን ከተማ ሰንጥቆ የሚያልፈው ያንተራራ ወንዝ መሀል ባች ደሴት ላይ ሐውልት ቆሞለታል። ቀልደኞቹ ጋብሮቮዎች ሐውልቱ ስለቆመለት ስፍራ ሲያወሱ፣ “ምንም አይነት አገልግሎት ሊሰጥ የማይችል ቦታ ነው” ይላሉ።

የጋብሮቮች መሬት አሰቸጋሪ እና እህልም የማያበቅል በመሆኑ ህይወት መራራ የሆነችባቸው ናቸው። ስለዚህም ሳይሆን አይቀርም ጋብሮቮች የፈጠራ ሰዎች፣ ሠራተኞች፣ ዘዴኞች ሊሆኑ የቻሉት የሚል ግምትም በመፅሐፉ ውስጥ ይጠቀሳል።

የጋብሮቮች ምድር ዛሬ ዛሬ የሳቅና የደስታ ምንጭ እየሆነ የመጣበት ጉዳይ አለ። ከአፋቸው ጠብ የሚለው ሁሉ ትውልድን ሁሉ ያፍነከንካል። እናም እነርሱን ለማየት የሚጓዙ አያሌዎች እንደሆነ ይጠቀሳል።

የአረፈዓይኔ ሐጐስ መፅሐፍ በርቀት ከኢትየጵያ ሩቅ ማዶ የሚገኙትን ጋብሮቮች ተርጉሟቸው እያንዳንዳቸውን ታሪካዊ ቀልዶች ሲያቀርባቸው ያስቁናል። ምክንያቱ እንግዲህ አንድም ከኛ ባህልና እምነት ጋር የመያያዝ ጠባይ ይኖራራቸዋል ወይም ደግሞ ቀልዶቹ በራሳቸው አለማቀፋዊ /Universal/ ተቀባይነት ያላቸው በመሆኑ የሰው ልጅ በመሆናችን ብቻ የሚያስቁ ናቸው።

ለምሳሌ እለቱ ሞቃት በነበረበት ቀን ነው። እንዲያም ሆኖ ዲታው (ሀብታሙ) ጋብሮቮ እጅግ በተጨናነቀው ሦስተኛ ማዕረግ ተሳፍረው በባቡር ይጓዛሉ። ታዲያ ሀብታም መሆናቸውን የሚያውቅ አንድ ተሳፋሪ ጮክ ብሎ፤ “ቸርባጂ፣ እንዴት እርስዎ በሦስተኛ ማዕረግ ይሳፈራሉ?” ሲል ቢጠይቀው፣ “አራተኛ ማዕረግ ስለሌለ ነው ልጄ” በማለት መለሱለት የሚል ቀልድ በመፅሐፉ ውስጥ አለ። ይህ እንግዲህ የቁጠባን ህይወት ፍፁም ተግባራዊ ያደረጉ ህዝቦች መሆናቸውን ያሳያል።

ጋብሮቮች የሺኛካን ሠርጥ ሲያቋርጡ ጫማቸው እንዳያልቅባቸው የተራራ መጫሚያ ጫማ ይከራያሉ ይባላል። የቤት ቁሳቁሳቸው ብዙውን ጊዜ የሚሰራው ከእንጨት ነው። ምክንያቱም የሸክላ እቃዎች አምስት አመት ያህል ሳይሰበሩ ሊያገለግሉ አይችሉምና። በብዙ ጨው ታሽቶ የተጠበሰ አሳ መብላት ያዘወትራሉ፤ ይህም ጥቂት በልተው ብዙ ውሃ በመጠጣት ሆዳቸው ይሞላ ዘንድ ነው። ጋብሮቮዎች ሲኒማ ቤት ገብተው የሦስተኛ ማዕረግ ቲኬት ይገዛሉ። ሙቀትና ወበቅ በሚበዛበት ወራት የፊት ማራገበያ ፋሽን በነበረበት ዘመን ጋብሮዎች ማራገቢያውን ከማወዛወዝ ይልቅ ጭንቅላታቸውን ማወዛወዝ ይመርጡ ነበር። ለምን ማራገቢያው ቶሎ እንዳያልቅባቸው ነዋ። የእነዚህ ሰዎች የእግር ኳስ አሠልጣኞች ግቢ ጠባቂዎቻቸውን ሲያለማምዱ፤ “ኳስ ጐል ገብታ መረቡ የተበጠሰ እንደሆነ የመረብ ዋጋ ከደመወዝህ ይቆረጣል” ይሏቸዋል ይባላል።

ጋብሮቮዎቹ የትዳር ጓደኛ ሲፈልጉ ለልብሷ ብዙ ጨርቅ የማትፈጀዋን ቀጭን ልጃገረድ ይመርጣሉ። ሲጋራ ሲለኩሱም አንዷን ክብሪት ለሁለት ሰንጥቀው ነው የሚለኩሱት። ሁለት ጊዜ እንዲጠቀሙበት።

አረፈዓይኔ ሐጐስ ከፃፋቸው የጋብሮቮ ምድር ቀልዶች ውስጥ አንዷ ደግሞ እንዲህ ትላለች። የጋብሮቮው ሚስት የቤቷን ግድግዳና ኮርኒስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኮላ እየቀባች ቤቷን በፅዳት ትጠብቅ ነበር። ይሁን እንጂ ባለቤቷ አንደዜ፣ “ግድግዳዎቹን መቀባትሽን ብትተይው ይሻላል። ክፍሎቹ በጣም እየጠበቡ ናቸው” ብሎ ሲገልፅላት ተስምቷል።

የነዚህ አስቂኝ ህዝቦች ታሪክ አያልቅም፤ ብዙ ነው። ተርጓሚውም ዘርዝሮ አስቀምጧቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችን ውስጥ በንግግር ችሎታቸውና ቀልድ ተዋዝቶ ከሚመጣላቸው ግለሰቦች መካከል ታሪክ ሁሌም የሚያስታውሳቸው አለቃ ገብረሐናን ነው። እኚህም ሰው እንደ ጋብሮቮዎች ዓለማቀፍ እውቅና አያገኙ እንጂ በሀገራቸው ህያው ናቸው። አረፈዓይኔ ሐጐስም የኚህን ሰው የህይወት ታሪክ በመፅሀፉ ውስጥ አስፍሯል።

ገብረሐና ደስታ ተገኝ በደብረታቦር አውራጃ ፎገራ ወረዳ ናበጋ ጊዮርጊስ በምትገኝ ስፍራ በ1814 ዓ.ም መወለዳቸው ይነገራል። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ከዚያም ወደ ጐጃም በመዝለቅ የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በኋላም ወደ ሀገራቸው ጐንደር በመመለስ ፀዋትወ ዜማን፣ አቋቋምን፣ ድጓንና የመፃህፍት ትርጓሜን ተማሩ። ገብረሐና ትምህርታቸውን እንደጨረሱ መምህራቸውን ዐቃቤ ስብሐት ገብረመድህንን “የኔታ እንግዲህ ይምከሩና ያሰናብቱኝ” ቢሏቸው፤ “ምን ቀረህ ብለህ ነው? ሁሉን አውቀሀል፤ ብቻ የደናቁርት ጓደኛ አትሁን?” አላቸው። ገብረሐናም ልዩ ስብዕና እያመጡ ሄዱ።

ተማሪ ገብረሐና በሀያ ስድስት አመታቸው ጐንደር ውስጥ ሊቀ ካህናት ሆነው ተሾሙ። በዚህ ጊዜ አንዲት ጐንደሬ ዘንድ ጠበል ተጠርተው ቢሄዱ የሚወጡት ሰዎች ሁሉ “ጠላው ጥሩ አይደለም” ሲሉ ይሰሙና ተመልሰው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። ሴትየዋም በመቅረታቸው አዝና ቤታቸው ሄዳ “ምነው አለቃ ጠበል ጠርቼዎት ሳይመጡ ቀሩ? ብትላቸው፣ “ኧረ መጥቼ ሰው ግም፣ ግም ሲል ጊዜ ነው የተመለስኩት” አልዋት ይባላል።

በዚህ መፅሀፍ ውስጥ ከወጡት ያለቃ ቀልዶች መካከል፣ አንዲት አጠር፣ ደልደል ያለች ደባካ መሳይ ጐረቤታቸው ደግሞ “አባ ሰው ሁሉ ድንቼ፣ የኔ ድንች እያለ ያቆላምጠኛል” ብትላቸው፤ “አዬ ሞኝት፣ እውነት መስሎሽ ነው? ድንቼ የሚሉሽ ሊልጡሽ እንጂ፤” ብለዋታል።

ሰንበት ብላ ይህችው ድንቡሼዋ ጐረቤታቸው አዲስ ልብሷን ልታስመርቅ እየሮጠች ወደ ቤታቸው ስትመጣ አመለጣትና ሽታው ቤቱን አወደው። አባ ገብረሐና ግን እንዳላወቀ ሰው “በውሃ ይለቅልሽ፤ ጥሎሽ ይሂድ” ብለው ከመረቋት በኋላ “እንግዲህ ይህችን ከሰው ዘንድ ስትደርሺ ብን እያደረግሽ ኩሪ” ብለው አሰናብተዋታል።

የአለቃ ገብረሐና ጨዋታ ያንሆለላቸው አንድ ደጃዝማች አባ ገብረሐናን ወዳጅ ያደርጓቸዋል። በየጊዜው ቤታቸው እየወሰዱም ያበሏቸው፤ ያጠጧቸው ነበር። እንደተለመደው አንድ ቀን እራት ጋብዘዋቸው ጮማ እየቆረጡ ሲያወጉ ደጃዝማች ግብዣውን ያሳመሩ መስሎአቸው “ይብሉ እንጂ፣ ሰው እኮ ደስ የሚለው የደገሰውን ሲበሉለት፣ የወለደውን ሲስሙለት ነው” ቢሏቸው፣ አባ ብድግ ብለው የደጃዝማቹን ቆንጅዬ ልጅ ሳም፣ ሳም፣ ደጋግመው ሳም አደረጓት። “ምነው አባ?” ብለው ቢጠይቁቸው፣ “ምግቡን እስከሚበቃኝ ተመገብሁ። የወለደውን ሲስሙለት ደስ ይለዋል ስላሉኝ ደግሞ ለርስዎ ስል የሚወዷትን ልጅዎን ሳምኩልዋ እንጂ አጠፋሁ?” በማለት መለሱላቸው።

አለቃ ገብረሐና ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ አፄ ዮሐንስ ከአፄ ዮሐንስ እስከ አፄ ምኒሊክ ድረስ ከመንግሥታት ጋር ሁሉ በቀልዳቸው እየተዋዙ የኖሩ ናቸው።

አለቃ ሰክረው ከአንዲት ሴት ጋር ተዳርተው ስላፈረሱ ወደ ትዳር አለም ገቡ። ወ/ሮ ማዘንጊያን አገቡ። ከዚያም ጋብቻቸው ስርቆሽና ጠብ የተደባለቀበት ነበር። ከሁሉም በላይ ግን አለቃ ቀልድና ለዛ ያለው ጨዋታ ወዳድ ስለነበሩ ጠባያቸውም ሆነ ኩርፊያቸው ለዛቢስ አልነበረም።

ታዲያ አንድቀን ከባለቤታቸው ጋራ ለቅሶ ውለው በጣም ርቧቸው ይመለሳሉ። ቤት እንደደረሱም “በይ እስቲ ቶሎ ብለሸ የምንበላውን አምጭልን” ብለው የሚበላ ሲጠባበቁ ማዘንጊያ ጓዳ ገብተው ቀለጡ። አለቃ ነገሩ ገርሟቸው “ማዘንጊያ ኧረ ማዘንጊያ” እያሉ ሲጣሩ ማዘንጊያ በትልቁ ጐርሰው ኖሮ “አቤት” ማለት ተስኗቸው “ወላዲተ አምላክ! ምነው ድመት ሆንሽ?” አሉዋቸው።

አለቃ ከማዘንጊያሽ ጋር ፀብና አተካሮ አበዙ። በኋላም ከአንዲት ጐረቤታቸው ጋር መቅበጠም ጀመሩ። ወ/ሮ ማዘንጊያ ገበያ የሚሄዱበትን ቀን ጠብቀውም ወዳጃቸውን እቤታቸው ያመጧታል። ህፃኑ ልጃቸው ተክሌ መደብ ላይ ተኝቶ ነበር። ታዲያ ወዳጃቸውም ልጅዋን ይዛ መጥታ ኖሮ ከተክሌ ጋር እንዲጫወት መደቡ ላይ አስተኝታው ሳለ ወ/ሮ ማዘንጊያ እቃ ረስተው ነበርና እየተጣሩ ሲመጡ ሰምታ በድንጋጤ የራሷን ልጅ ትታ ተክሌን ይዛ ሸሸች። ጉድ ተፈጠረ። ማዘንጊያ የጐረቤታቸው ልጅ መሆኑን አወቁና ነገሩ ገባቸው። አለቃ ደንግጠው ኩምሽሽ ብለዋል። ይሄኔ አጅሪት ልጁን አንስተው የሚንቀለቀለውን እሳት እያመለከቱ፣ “አሁን እዚህ ልጨምረው? አንቱ ቀላል?” እያሉ አለቃን እያዋከቡ ቢያሸብሯቸው፣ በተሰበረ አንደበት “ተይ ማዘንጊያ እዚያም ቤት እሳት አለ” በማለት አስጣሏቸው። ወዲያውም ባለቤታቸው እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ሠላም ወረደ።

የትንሳኤ ሰሞን ነውና በዚህ ወቅት አለቃ ያጋጠማቸውን አንድ ቀልድ እናስቀምጥ። የፋሲካ ሰሞን ወ/ሮ ማዘንጊያ ስራ በዝቶባቸው ሲንጐዳጐዱ አጋጣሚ አገኘሁ ብለው አጅሬ ተንደርድረው ጐረቤት ወዳጃቸው ዘንድ ይሄዳሉ። ዳሩ ግን አጉል አጋጣሚ ይሆንባቸውና አባወራው ጉብ ብሎ፣ ሰው ግጥም ብሎ ሞልቶ ያልጠራ ጠላ እየተጠጣ ሲጫወቱ ይደርሳሉ። ምንተእፍረታቸውን ጥቂት ተጫውተው “እንኳን አደረሳችሁ” ብለው ሊወጡ ሲሉ ውሽሚት “ይጫወቱ እንጂ ምን አስቸኮልዎ?” ብትላቸው፣ “የለም ቸኩያለሁ። ባል ሲወጣ እመጣለሁ” ብለዋት ወደ ቤታቸው ሄዱ። ባል-በአል ማለታቸው ነው።

አረፈዓይኔ ሐጐስ የእነዚህን የጋብሮቮዎች እና የአለቃ ገብረሐናን አስቂኝ ታሪኮች ሰብስቦ ያቀረበበት መፅሐፍ በሙሉ ስሜት ተነባቢ ነው። ማን ያውቃል አንድ ቀን ደግሞ የአለቃ ታሪክ በፊልም ተቀርጾ ብቅ ይል ይሆናል።   

ይምረጡ
(45 ሰዎች መርጠዋል)
16780 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us