ኢትዮጵያ ሆይ….

Wednesday, 25 January 2017 13:05

 

 

በድንበሩ ስዩም

 

ባለፈው እሁድ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በብሄራዊ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ የመጽሀፍ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። ለውይይት የቀረበው መጽሀፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መስራችና የፓርቲው ከፍተኛ መሪ በሆነው በክፍሉ ታደሰ አማካይነት በተጻፈው “ኢትዮጵያ ሆይ” የተሰኘው መጽሀፍ ነበር። ክፍሉ ታደሰ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ ስልስ ድጉስ /Trialogy/ እየተባሉ የሚጠሩትን ያ ትውልድ የተሰኙትን ሶስት ተከታታይ መጻሕፍትን አሳትሟል። መጻህፍቶቹ ደራሲው በመስራችነትና በከፍተኛ አመራርነት ሲመራው የነበረው ኢሕአፓ ምስረታውን እና የትግል ጉዞውን የዘከረባቸው የታሪክ ሰነዶች ናቸው። ክፍሉ ከዚህ ቀደምም በእንግሊዝኛ ቋንቋ The Generation በሚል ርእስ ዳጎስ ያለ መጽሀፍ አሳትሟል። መጻህፍቶቹ በየጊዜው እየታተሙ ሰፊ የሆነ አንባቢ ያላቸው ናቸው። የኢትዮጵያን የተማሪዎች ትግል በሰፊው የሚዳስሱ በመሆናቸው ለሀገሪቱ ታሪክ እንደ ትልቅ መረጃ ስለሚቆጠሩ ተቀባይነታውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ኢሕአፓን ከመሰረቱ የ1960ዎቹ ወጣት ምሁራን መካከል ዛሬ በህይወት ያሉት ሁለት ብቻ ናቸው። አንደኛው ክፍሉ ታደሰ ነው። ከዚያ ሁሉ እልቂት ተርፎ ያለፈውን ዘመን እንዲህ ነበር እያለ ለትውልድ ይዘክራል። አሁን በቅርቡ ያሳተማት ኢትዮጵያ ሆይ የተሰኘችው መጽሀፍም የትውልድ ዝክር ናት ተብላ ትጠራለች። ይህችም መጽሀፍ ልክ እንደቀድሞዎቹ ሁሉ ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘች እንደሆነች የሚያመለክተው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደጋጋሚ መታተሟ ነው። በመጽሀፏ አጠቃላይ ይዘት ላይ ዳሰሳ እንዲያደርግና የውይይት ሀሳቦችን እንዲያነሳ የተጋበዘው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ነበር። በዚሁ አያሌ ታዳሚያን በተገኙበት ስነ-ስርአት ላይ ጥበቡ በለጠ ይህን አቀረበ።

     ይህችን ኢትያጵያ ሆይ የተሰኘውን መጽሐፍ ሣነብ ደራሲው እንዲህ ይላል።

“ራሴን በተመለከተ ግን የሀዘኖች ሁሉ ሀዘን የገጠመኝ በምዕራብ ጐንደር ሲንቀሣቀስ የነበረው የኢሕአፓ ሠራዊት መሳሪያውን ቀብሮ ወደ ሱዳን ለመግባት በወሰነበት እለት ነበር። ሀዘኔ እስከ የሚባል አልነበረም። መሣሪያ ሣይሆን እነዚያ ከተማ የወደቁ ጓደኞቼን የቀበርኩ ስለመሠለኘ ራሴን ከእነሡ ጋር ማጐዳኘት ዳድቶኝ ነበር። ይሁንና ጽናት ትግል የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ሌላኛው እኔነቴ አሳስቦኝ ትግሉ ይቀጥላል፤ ሌላ አንድ ቀንም ይመጣል አልኩ” ይላል ደራሲው።

 

ቀጠል ያደርግና

“በ1972 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሰራዊት /ኢሕአሰ/ የነበረውን መሣሪያ ቀብረን ወደ ሱዳን ስንጓዝ ሰብለ የምትባል የምቀርባት የድርጅቱ አባል ይህንን ጫካ ለመጨረሻ ጊዜ ነው የማየው የሚል አስተያየት ስትሰነዝር ልቤ ስንጥቅ አለ። ተከራከርኳት። የአንተን አላውቅም እኔ እንደዚያ ነው የማስበው አለች። ፍርጥም ብላ። ያ ንግግሯ አዕምሮዬ ውስጥ በመቆየቱ ለብዙ ጊዜ ሲያቃጭል ቆየ። ብሸሸውና ላለማስታወስ ብሞክርም አልሆነልኝም። በመጨረሻም እንዳለችው ሆነ። እንደወጣን ቀረን” ይላል ክፍሉ ታደሰ።

 

“ያም ሆኖ ግን ሌላ አንድ ቀሪ ሕይወት ባገኝ እንደ ሂንዱዎቹ እምነት ሌላ ሠው ሆኜ ወደዚህ አለም ብመለስ ስህተቶቹንና ሕፀጾቹን አርሜ በኢሕአፓነቴ ያደረኩትን በሙሉ መልሼ አደርገዋለሁ። በምድር ላይ ለሰው ልጅ ክብርና ፍትሃዊ ስርአት ግንባታ አቅምንና ጉልበትን ከመለገስ በላይ ፍስሀ የሚሰጥ ጉዳይ የለም ብዬ አምናለሁና። አሁን በኖርኩት ሕይወቴ እንዳደረኩት የለውጥ ትግሉ ውስጥ ገና በልጅነቴ አልማገድም። ሀገሬንና ሕዝቡን በበቂ ሳላውቅ በ20 እና በ21 አመቴ ልምራ ብዬ አልነሣም።” ክፍሉ ታደሰ።

 

ይህ ደራሲ እንደገና ወደዚህች አለም ቢመለሰ አሁንም ኢሕአፓ ሆኜ ነው መቀጠል የምፈልገው ቢልም አንድ ነገር ደግሞ ነግሮናል። ኢሕአፓ ስህተቶች ሕፀፃች እንደነበሩበት ገልፃልናል። ከዚሁ ይለጥቅና በ20 እና በ21 አመት እድሜዬ የኢትዮጵያን ጉዳይ ተሸክሜ እጓዛለሁ፤ ኢትዮጵያን ለመለወጥ እነሣለሁ ብዬ አልሞክረውም ይለናል።

 

እዚህ ላይ ቆም ብለን ይህን ደራሲ ማሰብ እንችላለን። 416 ገፆች ያሉትን የአንድ ትውልድ ታሪክ ለመፃፍ ሲነሣ በውስጡ ብዙ ጥያቄዎች ተመላልሠዋል። ገና ከጅምሩ ኢትዮጵያ ሆይ ሲል ብዙ የሚያወጋን የሚያጫውተን ጉዳይ እንዳለው እንገምታለን።

 

እርሱ ያለፈበት ሕይወት በእጅጉ አስገራሚ ነውና ከየት ጀምሮ የቱጋ ያበቃል ብለንም ማሠባችን አይቀርም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲን ወይም እርሱ እንደሚጠራው ያን ትውልድ ለአዲስ አስተሣሠብና ለውጥ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ክፍሉ ታደሰ ነበር። ጽንሱ አድጐና ጐልምሶ ከፍተኛ የፖለቲካ ማዕበል ሲያስነሳም ክፍሉ ታደሰ ነበር። ማዕበሉ ሲተራመስ ክፍሉ ነበር። በዚያ ድብልቅልቁ በወጣው ማዕበል ውስጥ ሺዎች ወደቁ፤ ተሰው። ጓደኞቹ መስዋዕት ሆኑ ብቻ ሣይሆን አለቁ ማለት ይቻላል። የታለመው የታቀደው ሕልም አልሆነም። ክፍሉ የቆመበት ሜዳ ላይ ጓደኞቹ ተረፍርፈዋል። አልቀዋል። እናም እዚያ እልቂት ላይ ሆኖ እያሠበ ከ40 አመታት በኋላ ኢትዮጵያ ሆይ አለና ፃፈ። ኢትዮጵያ ሆይ የውስጥ ስሜትን ለዕውነት የተጠጋን የብዕር እስትንፋሰ ማጋሪያ ነው። የክፍሉ ታደሰ ኢትዮጵያ ሆይ በውስጡ ብዙ ታሪኮች አሉት። እጅግ አሣዛኝ ታሪኮች ሰቆቃዎች ለመቀበል የሚያዳግቱ እርምጃዎች ለቅሶዎች የኢትዮጵያን የዘመናት ውጣ ውረዶች እና አያሌ ጉዳዮችን ያወጋናል።

 

ጊዜያት እየቆዩ እየረፈዱ እየደበዘዙ ሲመጡ ታላላቅ እውነታዎች እየተሸሸጉ አዳዲስ ጉዳዮች መፃፍ መነጋገር መጀመራቸው ደራሲውን አሣሠበው። እርሱ እየደጋገመ የሚጠራው ያ ትውልድ ታሪኩና ማንነቱ ባላዋቂ ብዕረኞች በጀብደኛ ፀሐፊዎች እርሱ እንደሚለው ደግሞ በዋሾዎችና በቀጣፊዎች እጅ ገባ። በዚህም ምክንያት ስለዚያ ትውልድ የሚፃፉና የሚነገሩ ጉዳዮች አሣሠቡት። እርሱ እንደሚለው ከሆነ ያ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሲል ሕይወቱን የሰጠ ወጣት አስክሬኑ የትም የተጣለ ወጣት ደሙ በጐዳና ላይ የባከነው ወጣት ታሪኩ በቀጣፊዎች እጅ መውደቅ የለበትም ብሎ ክፍሉ ታደሰ ኢትዮጵያ ሆይ ብሎ ተነሣ።

 

አሁን ባለው ትውልድ ውስጥም የሚነሱ ነጥቦች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታዩ ውስብስበ ችግሮች ምክንያቱ ያ ትውልድ ነው ብለው የሚወነጅሉ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ለነዚህም ለአዲሶቹ ትውልዶች ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያ ሆይ ብሎ ያወጋል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ክፍሉ የትግል አጋሮቼ ለሚላቸው ለያ ትውልድ ሰማዕት ማስታወሻ መዘከሪያ ይሆን ዘንድ ታሪካቸው ይኸውና ለማለት ኢትዮጵያ ሆይ በሚለው ትረካው ሀውልታቸውን ለማቆም ሞክሯል።

ይህም ሆኖ ግን ደራሲው ክፍሉ ታደሰ ስለዚያ ትውልድ ገና አልተፃፈም፤ ገና አልተጀመረም የሚል እምነት አለው። በዚህች ኢትዮጵያ ሆይ መጽሐፍ ውስጥ ደራሲው  ለያ ትውልድ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እና አክብሮት ያሣየበት ነው ማለት ይቻላል።

 

የኢትዮጵያን የዘመናት የታሪክ ውጣ ውረዶችን በመዘርዘር ያ ትውልድ የመጣበትን እና የሔደበትን የታሪክ ዑደት በኢትዮጵያ ሆይ ውስጥ ደራሲው ሊያሣየን ብርቱ ሙከራ አድርጓል። በቀጣዮቹም ጉዞዬ የደራሲውን ፅሁፍ አንኳር ጉዳዮች በማንሣት ለውይይት ክፍት አደርገዋለሁ።

በክፍሉ ታደሰ መጽሐፍ ውስጥ እና በሌሎችም የተለያዩ ድርሣኖች ውስጥ እንደምናገኝው ከሆነ ክፍሉ ታደሰ ያን ትውልድ ከፈጠረና ካደራጁ ከመሩ የ1960ዎቹ ወጣት ምሁራን መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነው።

 

አንድ ትውልድን ለማደራጀትና ለማታገል ክፍሉ ለምን ተነሣ? የደራሲው የክፍሉ ታደሰ በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ማዕበል እንዲመጣ ያስነሣው የኃላ ታሪክ ምንድን ነው? ብለን መጠየቅም ግድ ይለናል። በርግጥ ይሔን ጥያቄ ለሌሎችም ማንሣት እንችላለን። ዋለልኝ መኮንን ምን አስነሣው? ብርሃነ መስቀል ረዳን ምን አስነሣው? ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይን ምን አስነሣው? ዘሩ ክሽንን፣ ጌታቸው ማሩን ሌሎችንም ዝነኛ የዚያን ዘመን ወጣቶች ምንድን ነው ያስነሣቸው? ከእያንዳንዱ ሠው ጀርባ አንድ ጉዳይ ይኖራል። ብዙዎች እንደሚሉት በዘመኑ የታየው አለማቀፍ ሁኔታዎች በተለይ ደግሞ የሶሻሊስቱ ጐራ እንቅስቃሴ የተራማጅ ኃይሎች ታሪክ የተለያዩ ሐገራት አብዮት የወጣቱን ወኔ አነሳስተውታል፤ አሙቀውታል የሚባል አባባል አለ። የቻይና አብዮት መቀንቀን፣ የኢሲያ አብዮት፣ የቬትናም፣ ኩባ እና የመሣሠሉት የዘመኑ የአብዮት ትኩሣቶች ያን ትውልድ አነሣስተውታል የሚሉ ሀሣቦች ብዙ ጊዜ ይሠነዘራሉ።

 

ክፍሉ ታደሰ በመጽሐፎቹ ውስጥ ስለ ራሱ እምብዛም አይፅፍም። ሰፊውን ቦታ የሚሠጠው ለሌሎች ነው። ነገር ግን የክፍሉን ማንነት ከራሱ ብዕር በተወሠነ መልኩ የምናገኘው ከዚሁ ኢትዮጵያ ሆይ ከተሠኘው መፅሐፉ ነው። በዚሁ መፅሀፉ ውስጥ እንዴት አብዮት አቀጣጣይ ሊሆን እንደቻለ መነሻ ምክንያቱን ይገልፅልናል። እንዲህም ይለናል።-

 

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር። የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ተጨናግፎ ዋነኛ መሪዎቹ ተገለዋል። ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ግን ቆስለው ተያዙ። ከመሪዎቹ መሀል ሶስቱን ገድለው ሬሳውን አዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን አጠገብ ሰቀሉ። በአፄ ኃይለሥላሴ ስም እንምል የነበርነው እኔና ሁለት ጓደኞቼ ዳዊት ኅሩይና፣ ኤርሚያስ አማረ በስዕል ላይም ሆነ በሌላ ከክርስቶስ በስተቀር ሌላ የተሠቀለ አይተን አናውቅም ነበርና ጉዱን ለማየት ሔድን። እና ሰው ሲሠቀል የምናውቀው እንደ ክርስቶስ እጆቹን ዘርግቶ እንጨት ላይ ሲቸነከር ነበርና ልክ እዚያ እንደደረስን ያየነው የስቅላት ሁኔታ አስገረመኝ ። ሰዎቹ አንገታቸው ላይ ገመድ ገብቶ ተንጠልጥለዋል። በጥይት ስለተደበደቡም እግራቸው ቆስሏል። ተቦዳድሷል። ቆመን እያየን ሣለ ተመልካች የመሠሉን /ዛሬ ላይ ሆኜ ሣስበው ተመልካችም ላይሆኑ ይችላሉ/ ሁለት ሰዎች የተሠቀሉት ሰዎችን ቁስል በእንጨት መጓጐጥ ሲጨምሩ ራሳችንን መቆጣጠር አቅቶን ሳንማከርና ሳንነጋገር ሶስታችንም በአንድነት የተቃውሞ ድምፅ አሰማን። ሶስታችንም የ13 ወይም 14 አመት ልጆች ነበርን። ፖለቲካ ትርጉሙን እንኳን አናውቅም። ቦታው ላይ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች በእኛ ሁኔታ ተናደዱ። እነዚህ ዘመዶቻቸው ናቸው ብለው ሊደበድቡን መጡ። የተሰቀሉ ሬሳዎችን ይጠብቅ ወደነበረው ፖሊስ ዘንድ ሸሽተን በመሄድ ነፍሣችንን አተረፍን። ፖሊሱ ሰዎቹን አልደፈራቸውም። ብቻ ቶሎ ከዚህ ጥፉ ብሎ አባረረን። ከብዙ አመታት በኋላ ሳንማከርና ሳንነጋገር ሶስታችንም የአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ጠንካራ ተቃዋሚ የተማሪ ንቅናቄው ጽኑ አራማጅ ሆንን/ገጽ 68/

 

ደራሲውን ወደ ተማሪዎቸ ንቅናቄ ውስጥ ዘው ብሎ እንዲገባ ምክንያት የሆነው የነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ አሠቃቂ የግድያ እና የስቅላት ድርጊት ነው።

በሌላ መልኩ ደግሞ ይኸው ደራሲ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለ አንድ ሕንፃ ሲሠራ የቀን ሰራተኛ ሆኖ በመቀጠር የሰራተኛውን ሕይወት ያየበትና ስሜቱ የተለወጠበት ሁኔታንም ያሣያል። ከዚያም በ21 አመቴ መንግስት እቀይራለሁ፤ ስርዓት እቀይራለሁ ብዬ ተነሣሁ ይላል ክፍሉ።

በነ ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ አሠቃቂ የስቅላትና የግድያ ድርጊት ለለውጥ ተነሣስቶ ወደ ተማሪዎች ትግል የገባው ይህ ደራሲ ቀጥሎም ያየው ነገር ለትግል ከተነሣሣበት ምክንያት የበለጠ መራራ ሆኖ ገጠመው።

 

የተማሪዎች ትግል እየተቀጣጠለ መሬት ላራሹ ጥያቄም ሥር እየሠደደ የዲሞክራሲና የዘመናዊ አስተዳደር ጥያቄዎች እየተስፋፉ ሲመጡ ኢትዮጵያ በለውጥ አብዮት ተጥለቀለቀች። ወታደራዊ ለውጥ መጣ። ንጉሡ ወርደው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተመሠረተ። በተማሪው እና በደርግ ስርዓት መካከል መቃቃሩ ልዩነቱ እየጐላ መጣ። በመጨረሻም ወደለየለት ፀብ ተገባ። ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ታወጀ ቋንቋው መሣሪያ መተኮስ ሆነ መነጋገር መወያየት ቀረ። አሸናፊው ኃይል ማለት ተኩሶ መግደል እስኪመስል ድረስ ነገሮች ጦዙ።

 

በዘመነ ቀይ ሽብር ወቅት የተሠሩ ወንጀሎችን መርምሮ ለፍርድ የሚያቀርብ ልዩ ዐቃቤ ሕግ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ መቋቋሙ ይታወቃል። ዐቃቤ ሕጉ በወቅቱ የሠበሠባቸውን ማስረጃዎች አንድ ላይ ጠርዞ በማሣተም ርዕስ ሠጣቸው። ርዕሡ ደም ያዘለ ዶሴ ይሰኛል። ከዚህ ደም ካዘለ ዶሴ ውስጥ የተወሠኑ ታሪኮችን ደራሲው ያስነብበናል።

 

ደራሲው የነ ጀነራል መንግስቱ ስቅላት አስቆጭቶት ወደ ትግል ቢገባም በእርሡ የትግል ዘመን ደግሞ ይሔ ተፈፀመ።

 

ጉዳዩ የተፈፀመው በሸዋ ክፍለ ሐገር በጨቦና ጉራጌ አውራጃ በቸሀ ወረዳ የጉብሬ ከተማ ነው። ገስግስ ገብረ መስቀል የተባለ የተፈቀደለት ገዳይ በነበረበት ግዛት ነው። ተማሪ ወልደአብ ደንቡ አስፋው ገገብሳና ደሳለኝ ተዋጀ በዚህ ወረዳ የገስግስ ገብረመስቀልና ጓደኞቹ ሰለባዎች እንደሆኑ ሰነዱ ያሣያል። ሶስቱም በከበባ ሚያዚያ 15 ቀን 1970 ዓ.ም ከተያዙ በኋላ ገስግስ ገብረመስቀልና ግብረ አበሮቹ ፊት ቀርበው ጉብሮ ከተማ ተወስደው እንዲገደሉ ታዘዘ። በመጀመሪያ የተገደለው ተማሪ ወልደአብ ደንቡ ነው። አደባባይ ላይ በጥይት ተደብድቦ ተገደለ። ከዚያም አስክሬኑ ላይ ወልደአብ ደንቡ ይህ ነው የሚል ፅሁፍ ለጥፈው መንገድ ላይ ጣሉት። እለቱ የገበያ ቀን ነበር። ወልደ አብ ደንቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ አመት የቋንቋ ተማሪ ነበር። /ገጽ 64/

 

ገብሬ የተባለችው ይህች ከተማ እንኳንስ ትጥቃዊ እንቅስቃሴ ሊደረግባት ይቅርና የረባ ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን ሊካሔድባት የምትችል አይደለችም። ወጣቶቹ በተረሸኑ ጊዜ 1ኛ ደረጃ ተማሪ የነበረውና የልዩ ዐቃቤ ሕግ 80ኛ ምስክር የሆነው የወልደአብ ደንቡ ወንድም ሰለሞን ደንቡ ሁኔታውን ያስታውሣል፤

 

ወንድሜ ወልደአብ ደንቡ ከጓደኞቼ ከአስፋው ገገብሳ ቤት ተጠልለው እንዳሉ በአበራ በቃና ጠቋሚነት ተይዘው ጉባሬ ከተማ መጥተዋል። በወቅቱ አሞራ ሜዳ የተባለው ቦታ የእናት ሐገር ጥሪ ዝግጅት ስለነበር የወረደው ባለስልጣኖችና የበአሉ ተሣታፊ ሕዝብም እዚያ ይገኝ ስለነበር እየደበደቡ ወደዚያ ወሰዷቸውና ለገስግስ ገብረመስቀል ካሣዬ በኋላ ውሣኔ አግኝተው ይመስለኛል መልሠው ጉባሬ ከተማ አምጥተው በቀበሌው እስር ቤት አሣደሯቸው ። ጧት ሚያዚያ 19 ቀን 1970 ዓ.ም በግምት ከንጋቱ 12 ሰዓት ቤታችን ሆነን የተኩስ ድምፅ ሠማን። በዚያ ቀን ወደ ት/ቤት ስሔድ ወንድሜ ወልደአብ ደንቡ ተገድሎ አስክሬኑ ከቀበሌው ጽ/ቤት ፊት ለፊት ካለ አስፋልት መንገድ ላይ ተጥሎ አይቼ ዝም ብዬ በማለፍ ት/ቤት ገባሁ። ከዚያም የሕዝብ መዝሙር በማሠማት ተማሪዎች ተሰልፈን እያየን

 

ይፋፋም ቀይ ሽብር ይፋፋም

አሁን የቀረን እዥና ጉመር ይቀጥላል

እነሙር ነቅተናል ተደራጅተናል

ኢዲዩን ደምስሰናል

ኢሕአፓን ለጅብ ሰጥተናል

ከእንግዲህ ወዲያ ማን ይደፍረናል።

 

የሚል ዘፈን በድርጅታዊ መንገድ ተዘጋጅቶ ተሰጥቶን እየጨፈርን ከት/ቤት ወደ አስክሬኑ እንድንሄድ ተደርጓል። ከመሔዳችን በፊት በሠልፉ ላይ አቶ ታደሰ መንገሻ  ገብረጊዮርጊስ ስራቱና እንድሪያስ ቡታ ሆነው ስሜን ጠርተው በማውጣት በታጣቂዎች ካስያዙኝ በኋላ ለተማሪዎቹ የሰባት ቤት ጉራጌ ቀንደኛ መሪ የሆኑት እነ ወልደአብ ደንቡ ስለተገደሉ እንኳን ደስ ያላችሁ፣ የዛሬው ቀን የምናሣልፈው በትምህርት ሣይሆን በሆታና በጭፈራ ነው በማለት እኔን እያዘመሩ ከኃላ ተማሪዎቹ እየተከተሉ ወንድሜ አስክሬን ዘንድ ደረስን። አስክሬኑ ሣልረግጥ በሁለት እግሬ መካከል አድርጌ ሳልፍ አቶ እንድሪያስ ቡታ ማጅራቴን በመያዝ በትዕዛዝ አጠራር “ሰለሞን በማለት ሬሳ እኮ የሚረገጠው እንዲህ ነው” በማለት በወንድሜ አስክሬን ላይ ቆመበት። ከዚያም ሣልወድ በግድ የወንድሜን አስክሬን ሆዱ ላይ ረግጨ አልፌያለሁ።

 

በሁለት ረድፍ የሚሔዱ የትምህርት ቤቱ ሁለት ሽፍት ቁጥራቸው በግምት 2 ሺህ 200 የሚደርስ ተማሪዎችና ለገበያ የተገኘው ሠው ሁሉ አስክሬኑን እንዲረግጥ ተደርጓል። /ገጽ 66/

 

በደራሲው ክፍሉ ታደሰ የ13 አመት ልጅ ሳለ 1953 ዓ.ም የነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ የስቅለት ቅጣት ልቡን ነክቶት ወደ ተማሪዎች ትግል ቢቀላቀልም እርሱ አድጐ በሚመራው ፓርቲ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ደግሞ በቀይ ሽብር ዘመቻ ወቅት እንዲህ ባለ አሠቃቂ ግድያ ያልፋሉ።

ኢትዮጵያ ሆይ… መፅሃፍ ብዙ ጉዶችን ይዛለች። አስፈሪ (Horror) ፊልም የሚመስሉ በርካታ የዚህችን አገር ጉዞ ታስነብበናለች። ታሪካችን ነውና አሁንም ደም ካዘለው ዶሴ ጥቂቱን ልጥቀስ፡-

 

ይህ ደግሞ በደቡበ ክልል የተካሔደ ነው። ከታወቁት የደርግ አባላት መሀከል አንዱ የሆኑት መ/አ ጴጥሮስ ገብሬ እንደሆኑ ክፍሉ ይገልፃል። ሌላው ሻለቃ ጥሩነህ ኃብተስላሴ ነበሩ። ይህ የደርግ ቡድን ፀረ አብዮተኛ ያላቸው የኢሕአፓ አባላትን በጥይት መግደል አላረካ ስላለው ሌላ ዘዴ መቀየሡን ክፍሉ ያስረዳል። ስለዚሁ ሁኔታም ከአቃቤ ሕግ የተገኘውን መረጃ በዚህ ሁኔታ ይተርከዋል፡-

 

ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ እስረኞች ከታሠሩበት ደረስን። አቶ ደጉ ደወሌ የሰባት እስረኞች ስም የያዘ ማስታወሻ ይዞ እርሱ እና ሌሎች ባለስልጣኖች እስረኞቹን በገመድ እንዲያስሩ አዘዙ። /የመኪና ጉዞ ተጀመረ/። ኦሞ ወንዝ ድልድይ ስንደርስ መኪናዎቹ ቆሙ። ሚሊሻዎች ከመኪና ከወረዱ በኋላ በድልድዩ ላይ ሆነው ሟቾችን ከእነ ሕይወታቸው ኦሞ ወንዝ ውስጥ እንዲጥሉ ተደለደሉ። እነ ደጉ ደወሌ ተባብረው ከመኪና እያወረዱ ወደ ወንዙ ከነ ሕይወታቸው ተራ በተራ ጣሉዋቸው። እስረኞቹ ሲጣሉ የተለያየ ንግግር ያደርጉ ነበር። ከእስረኞቹ መካከል ቦጃ የተባለው ከወንዝ ውስጥ ለመውጣት ብቅ ጥልቅ ሲል ደጉ ደወሌ እና ቴጋ ተማም በተከታታይ ተኮሱበት፤ ተመታና ውሃው ውስጥ ሰመጠ። ውሃው የወሠዳቸው መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ በመጣንበት ሁኔታ ተመለስን ይላል ምስክሩ።

 

ኢትዮጵያ ሆይ… አያሌ የሞት አይነቶችን ደም ካዘለው ዶሴ ውሰጥ እየመዘዘች በግሩም ትረካ ታቀርባለች። እየታነቁ የተገደሉ ተገርፈው የሞቱ በጅምላ የተረሸኑ ከእስር ቤት እየተለቀሙ ደማቸውን ያፈሠሱ የዚህች ሀገር አንጡራ ዜጐች ታስታውሣለች።

 

ቆም ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ደራሲው ያመቻቸናል። እውነት እነዚህ ወጣቶች ሕይወታቸውን የገበሩበት አላማ ምንድን ነው? ጽናታቸው ከየት መጣ? የመስዋዕትነቱ ዋጋ ምንድን ነው?

 

በሌላ መልኩ ደግሞ መጨካከኑስ ከየት መጣ? የአንዲት አገር ልጆች እንዲህ የሚጋደሉበት ምክንያት ምንድን ነው? መራራ ግድያዎች መነሻቸው ምንድን ነው? ገዳይ ከየት ባገኘው ጭካኔ ነው ወንድሙ ላይ እንዲህ አይነት እርምጃ የሚወስደው? እያልን ጉዳዩን ከብዙ ነገሮች አንፃር እንድናየው በዚህ አጋጣሚ መናገር እወዳለሁ።

 

ኢትዮጵያ ሆይ… መጽሐፍ ብዕሯን በዋናነት አሹላ የተነሳችው በሻ/ል ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ እኛና አብዮቱ /2006/ ብለው ባሳተሙት መጽሐፍ፣ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ /2007/፣ ዶ/ር ነገደ ጐበዜ ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት /2014/ እና ገስጥ ተጫኔ የቀድሞው ጦር /2006/ መፃሕፍት ላይ ነው።

 

እነዚህ መፅሃፎች የኢሕአፓን ወጣት ታጋዮች ታሪክና መስዋዕትነት አበላሽተዋል፣ አቆሽሸዋል በሚል መነሻነት የራሱን ማስረጃ እያቀረበ እነ ሻ/ል ፍቅረስላሴን ክፉኛ ይሞግታቸዋል። በተለይ ሻ/ል ፍቅረስላሴ በወቅቱ ለተፈጠረው እልቂት እምብዛም ፀፀት እንደማይሠማቸው ገልፀዋል በማለት ክፍሉ ታደሰ የጓደኞቹን ሰቆቃ በመተንተን ረጅሙን ጊዜ ወስዷል። ደርግ እና መኢሶን ለኢሕአፓ ወጣቶች እልቂት የመዘዙት እና የሳቡትን ምላጭ እየተነተነ ይጓዛል። እየዞረ መጥቶም የወንጀሉ ዋነኛ አድራጊ ፈጣሪዎች እነርሡ መሆናቸውን ያትታል።

 

የክፍሉ ታደሰ ኢትዮጵያ ሆይ… ወደ ኢሕአፓ ጉያም በጥልቀት በመግባት አንድ ሰው ታነሣለች። ይህ ሰው ያን ትውልድ ካደራጁ እና ግንባር ቀደም ታጋዮች ከሆኑት መካከል ስመ ገናና ነው ብርሃነ መስቀል ረዳ

 

ብርሃነ መስቀል ረዳ ትንታግ ተናጋሪ እና ፈጣን አዕምሮ የነበረው የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር ነበር። ከድርጅቱ ጋር ቀስ በቀስ በሀሣብ መግባባት ባለመቻሉ በመጨረሻም ከአመራር መንበሩ ላይ ገሸሽ በመደረጉ የተበሣጨ የሚመስለው ብርሃነ መስቀል ረዳ የራሱን አንጃ እንደመሠረተም ኢትዮጵያ ሆይ-- ትተርካለች።

 

ብርሃነ መስቀል ረዳ ከድርጅቱ ከወጣ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ገጠር ውስጥ ገብቶ ትግል እንደጀመረ፣ ብዙም ሣይገፋበት ለእስር ተዳርጐ ሕይወቱ በአስከፊ ሁኔታ ትቀጠፋለች። ይሁን እንጂ ብርሃነ መስቀል በደርግ እስር ቤት እያለ የሰጠው ቃል ነው በሚል 98 ገጽ የተፃፈ ሰነድም አለ። በዚህ ሰነድ ውስጥ ያሉትን ገለፃዎች ክፍሉ ታደሰ ይጠራጠራቸዋል። አንዳንዱንም ይቀበላል። ግን ለብርሃነ መስቀል የትግል ብቃትና ችሎታ መመስከሩን አላቆመም። ከዚያ ጀግና ሠው ከብርሃነ መስቀል ረዳ ይሔ ቃል ይወጣል ብዬ አላምንም ሁሉ እያለ ፅፎለታል። ብርሃነ መስቀል የተማሪዎችን የትግል አካሔድ የተሳሳተ መሆኑን የሚያስረዳ ቃል ሰጥቷል በሚል ብዙዎች ይህን ጀግና ከታሠረ በኋላ ሰጠ በተባለው ቃል እየመዘኑት ነው። ነገር ግን አንድ ሠው እስር ቤት ውስጥ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ስለማይታወቅ ቃሉ በርግጥም የርሡ ይሁን አይሁን በዚያ መመዘን የለበትም የሚሉት አሉ።

 

ብርሃነ መስቀል ረዳ በ1930 ዓ.ም በትግራይ ገጠራማ ቦታ ነው የተወለደው። እድገቱ ደግሞ ደሴ ከተማ የነበረ ሲሆን የሚኖረውም አጐቱ ቤት ነበር። አጐቱ ዳኛ እንደነበሩ ይነገራል። ብርሃነ መስቀል በ1955 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጣም ጥሩ ወጤት አምጥቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይገባል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ዋና አራማጅ ሆኖ ይጠቀሣል። መሬት ላራሹ በሚል ርዕስ የተቃውሞ ሠልፍ አደራጅቶ በ1957 ዓ.ም ተማሪዎችን ይዞ የወጣ ነው። ከተወሠኑ የተማሪዎች እንቅስቃሴ አራማጆች ጋር ሆኖ ከዩኒቨርሲቲው ለአንድ አመት ተባረረ። ከዚያም ከጓደኞቹ ጋር አውሮኘላን ከባህር ዳር ጠልፎ ወደ ካርቱም ኮበለሉ። ከዚያም ወደ አልጀርስ ሔደው የተማሪዎቹን ትግል አስፋፉት ለኢሕአፓ መመስረት ከዋነኞቹ አንዱ የሆነውና የተማሪዎችን ትግል ያፋፋመው ብርሃነ መስቀል ረዳ ፍፃሜው ብዙ አልሠመረለትም። ክፍሉ ታደሰ ግን ያ ጀግና -- እያለ ይጠራዋል።

 

ኢትዮጵያ ሆይ መጽሐፍ አያሌ አሣዛኝ ታሪኮችን ይዛለች። በመጽሐፏ ውስጥ ከሚገኙ ታሪኮች ከእንባችን ጋር እየተናነቅን ከምናነባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው መሪ የሆነው የዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ክስተት እና ሕልፈት ነው።

 

ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ ብሎ የፃፈውን ታሪክ ማስታወሻነቱን ለዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ነው የሰጠው ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነው። አንደኛው የትግል አጋሩ ስለነበርና የቅርብ ምስጢረኞችና ወዳጆች ስለነበሩ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ተስፋዬ ደበሣይ የኢሕአፓ ቆራጥ መሪ በመሆኑና ሕይወቱንም አሣልፎ በመስጠቱ ምክንያት ዘላለማዊ ዝክር ሠጥቶታል።

 

በተስፋዬ ደበሣይ ታጋይ የኢሕአፓ ግንባር ቀደ መሪ አርቆ አሣቢና ትሁት ቢሆንም ይህን/ያ ትውልድ/ን መጽሐፍ ለእሡ መዘከሩ በፖለቲካ ትግሉ ካበረከተው ድርሻ በመነሣት አይደለም። በቀይ ሸብር ሊመቱ ተደግሶላቸው ለነበሩ ቁጥራቸው በርካታ የወቅቱ ታጋዮችን ለማዳን ጥረት ሲያደርግ እሱ ራሡ በመውደቁ ነው። መጋቢት 14 ቀን 1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ አሠሣ ሊደረግ እንደታቀደ ኢሕአፓ ተረዳ ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ታጋዮች ከአዲስ አበባ መውጣት እንዳለባቸው ታመነበት። ከጊዜ አንፃር ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት በኢሕአፓ ድርጅታዊ መዋቅር አማካይነት ማካሔድ እንደማይቻል ደግሞ ግልጽ ሆነ። ተስፋዬ ማንንም ሳያማክር ኃላፊነቱን ለራሱ ጠሰ። አሰሳው ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረው ቀኑን ሙሉ አዲስ አበባ አውቶቡስ ጣቢያ በመዋል ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ታጋዮችን በመገናኘት የሚሸሸጉበትን የሸዋ ከተማ ስምና እዚያም ሲደርሱ ከአካባቢው የኢሕአፓ መዋቅር አባላት ጋር የሚገናኙበትን ምስጢራዊ ቃል ሲሰጥ ዋል። እሱ ግን በርካታ የድርጅት አባላትን በመከራ ጊዜ ትቶ መሔድ አልሆንልህ አለው። አዲስ አበባ ቀረ። የመከራ ፅዋውንም ከዚያ ከቀሩት ጋር አብሮ ሊጎነጭ ወሰነ። በዚያን ጊዜ ተስፋዬ ወደ ሸዋ የገጠር ከተሞች ከሸኛቸው ከብዙዎች ታጋዮች መሀል በርከት ያሉት አሁንም በሕይወት አሉ። ተስፋዬ ደበሣይ ግን-- ተስፋዬ የቀይ ሽብር ሰለባ ብቻ አይደለም። ከቀይ ሽብር መዓት ሌሎችን ለማዳን ራሱን አሳልፎ የሰጠ ታላቅ መሪ ነው” ይለዋል ክፍሉ ታደሰ።

 

ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ ከአባቱ ከአቶ ደበሣይ ካህሳይ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ምሕረታ ዳዶ ዑማር በ1933 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ በምትገኘው አሊቴና በመባል የምትጠራው የገጠር ከተማ ተወለደ። ተስፋዬ ደበሣይ ትምህርቱን በአዲግራት እና በመቀሌ ከተሞች ከተማረ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኢጣሊያ ኡርባኒአና ዩኒቨርስት ተልኮ በፍልስፍና የዶክተሬት ድግሪውን ተቀብሎ የመጣ ፈላስፋ ነበር።

 

ከትምህርቱ በኋላ በማስታወቂያ ሚኒስቴርና በተለያዩ ቦታዎች ሲሰራ የቆየው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሣይ በኋላ ደግሞ ሙሉ በመሉ ጊዜውን ለኢሕአፓ አመራርነት ሰጥቶ በስመጨረሻም በቀይ ሽብር ዘመቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ከፎቅ ላይ ተከስክሶ ሕይወቱ አልፋለች። የተከሰከሰበት ሕንፃ አምባሳደር ፊልም ቤት ፊት ለፊት ካለው ኪዳኔ በየነ ከሚባለው ሕንፃ ላይ ነው። እጅ ከመስጠት ተከስክሶ መሞትን የመረጠ የፍልስፍና ሊቅ ነበር።

 

ዶ/ር ኃይሊ ፊዳ

ይህ ሰው መኢሶን የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /ፓርቲ መሪ ነበር። በርካቶች እንደሚመሰክሩለት የሊቆች ሊቅ ነው ይሉታል። በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ከተነሱ የለውጥ አቀንቃኞች መካከል አንዱ እሱ ነበር።

 

የገነት አየለ የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች በተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ አምባገነኑ የቀድሞ ወታደራዊ መሪ የዶ/ር ኃይሌ ፊዳን ሞት እንኳን በቅጡ እንደማያውቁ ይናገራሉ። ሞተ እንዴ? ማን ገደለው እያሉ እንደ አዲስ፣ አስገዳዩ  ጠያቂ ሆነው ቀርበዋል። ደሙ ደመ ከልብ የሆነ ምሁር ነው ኃይሌ ፊዳ።

ታስሮ እና ማቆ ከዚያም የተረሸነ ኢትዮጵያዊ የተገደው ሐምሌ 1971 ዓ.ም ነው። አፈሩን ገለባ ያድርግለት። ወደፊት ስለዚሁ የፖለቲካ መሪ እና ምሁር ግለ-ታሪክ አጫውታችኋለሁ።

 

ሀይሌ ፊዳ ኩማ የተወለደው በወለጋ ክፍለ ሀገር ሆሮ ጉድሩ አውራጃ ነው። የመጀመሪያ ድግሪውን ከአ.አ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ፋክልቲ ካገኘ በኋላ ለጥቂት ጊዜ በሐረርጌ የደደር ከተማ በመምህርነት ሠራ። ከዚያም በውጭ ሀገር ነፃ ስኮላርሺኘ በማግኘቱ ወደ ጀርመኗ የሀምቡርግ ከተማ ተጓዘ። ሁለተኛ ድግሪውን ከያዘ በኋላ በጂኦፊዚክስ ሳይንስ ከሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ከያዛ በኋላ እዚያው ማስተማር ጀመረ። ሀይሌ በውጭ ሳለ ከአንዲት ፈረንሣዊት አንድ ልጅ እንዳለውም ይነገራል።

 

ዶ/ር ሠናይ ልኬ

በደርግ ውስጥ ይሰራ የነበረ ወጣት ምሁር ነበር ሠናይ ልኬ። በተለይ ደግሞ የሕዝብ ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ይሰራ ነበር።

ደርግ እንደሚገልፀው ዶ/ር ሠናይ ልኬ በ1969 ዓ.ም የተገደለው በፀረ ሕዝብ ሴረኞች በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ከቆሰለ በኋላ በሆስፒታል ውስጥ ነው። ዕድሜው ደግሞ 33 ነበር።

 

ዶ/ር ሠናይ ልኬ የተወለደው በወለጋ ክፍለ ሐገር በዮብዶ ከተማ ውስጥ በ1936 ዓ.ም ነበር። የልጅነት ጊዜውን በጎሬ ከተማ ነው ያሳለፈው። በ1934 ዓ.ም እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ጎሬ ከተማ በሚገኘው በጎሬ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ገብቶ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ት/ቤት ቆይቶ አስረኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርት አጠናቀቀ። ከዚያም በ1954 ዓ.ም ደብረዘይት በሚገኘው የስዊድን ኤቫንጀሊካል ገብቶ 11ኛን እና 12ኛን ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ጨረሰ።

 

ከዚያም ወደ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገብቶ የመጀመሪያውን ዓመት በከፍተኛ ማዕረግ አለፈ። ቀጥሎም የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ ሔደ። እዚም ላፋዩት ከሚባል ኮሌጅ ለሶስት ዓመታት ተምሮ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ በድግሪ በከፍተኛ ማዕረግ ተመረቀ።

 

ከዚያም በ1958 ዓ.ም የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በበርክሊ ከፍተኛ ትምህርቱን እንዲቀጥል ስኮላርሺኘ ሰጥቶት በ1964 ዓ.ም በ28 ዓመቱ የዶክትሬት ድግሪውን አግኝቷል። ከዚያም ወደ ሀገሩ መጥቶ የፖለቲካ አቀንቃኝነቱን ቀጠለበት።

 

ደርግ ውስጥ ከገቡት የፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል አንዱ ነው የሚባለው ዶ/ር ሰናይ ልኬ በጥይት ተመትቶ ነው የሞተው። በወቅቱ ፀረ-አብዮተኛ ይባል የነበረው ደግሞ ኢሕአፓ ነበር። እውን ዶ/ር ሠናይን የገደለው ማን ነው? ገና ያልተነገረ ይፋ ያልሆነ ወሬ ነው። እነዚህ ዶክተሮች ትንታግ የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ። ሁሉም ብቅ አሉ፤ ተማሩ፤ ፍክትክት ብለው ወጡ። ሀገርና ወገን ብዙ ሲጠብቅባቸው ጭልምልም ብለው ጠፉ

 

ኢትዮጵያ ሆይ-- የብዙ ነገሮች የውስጥ ስሜት መግለጫ መጽሐፍ ናት። ደራሲው ወጣት እያለ የዛሬ 40 አመታት በፊት የነበሩ ጓደኞቹን ያስታውሣል። ግማሹ ከኤርትራ ክፍለ ሀገር የመጣ ነው። ለኢትዮጵያ አብዮት ብለው ተሰውተዋል ይላል። ከ40 አመት በኋላ ደግሞ ብዙ ነገሮች ተለዋውጠው ሲያይ ኢትዮጵያ ሆይ እያለ እዚያ ውስጥ ያጫውተናል።

 

ያልተዘመረላቸው በሚል ርዕስም ሕይወታቸውን የገበሩ ታላላቅ የኢሕአፓ ስብዕናዎችን እያነሣሣ ይዘክራቸዋል። ደርግ ውስጥ ሆነው ለኢሕአፓ የሚሠሩ ሠዎችንም እያነሣሣ መስዋዕትነታቸውን ይዘክራል።

 

በሴቶች ማሕበራት አደረጃጀትና ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራትን የመጀመሪያዋን የሴቶች አስተባባሪ ማሕበር መሪን ንግስት ተፈራን ይዘክራል። የቀይ ሽብር ሰላባ የሆነችው ንግስት ከበባ ተደርጐ ልትያዝ ስትል በደርግ እጅ ከመውደቅ ይልቅ የሲያናይድ እንክብል/መርዝ/ በመዋጥ ራሷን ሰዋች ይላል ክፍሉ። ዳሮ ነጋሽም በ1969 ዓ.ም በተካሔደው በመጀመሪያ አሰሳ ላይ ወደቀች ይላል።

 

ባጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ሆይ ገና ብዙ የሚጻፍባት እንደሆነች መገንዘብ ይቻላል። ይህችኛዋ ቅፅ አንድ ናት። ገና ቅፅ ሁለት ትቀጥላለች። ምናልባትም ቅፅ ሦስት ድረስ ሁሉ ሊሔድ እንደሚችል አያያዙ ፍንጭ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ጉዳይ አያልቅም። ይሔው ስንቶቹ ምሁሮቿ ልጆቿ አልቀውባት እሷ ግን አለች።

 

የኢትዮጵያ ጉዞ በደራሲያን እና በፖለቲከኞች እይታ ምን እንደሚመስል በዚሁ በኢትዮጵያ ሆይ ላይ እናገኛለን። ያ ትንታግ ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ገሞራው በረከተ መርገምን ያሕል ግጥም ፅፎ ወደ መጨረሻው ግን ወደ ተስፋ መቁረጡ የደረሠ መሠለው። ወታደራዊ ስርዓት እንደመጣ ካገሩ ተሰዶ ብዙ ፍዳ አየ። ተስፋው ጨለመ። እናም እንዲህ ሲል አሰበ። የማይፋቅ መርገምት አለብን አለ።

 

ገሞራው ሲፅፍ እንዲህ አለ፡-

“አበው እንደሰጡኝ ምላሽ ከሆነ የማይፋቅ መርገምት አለብን የሚል ነው። የወረደብንን መርገምትም ምንነት ሊያብራሩ ከትናንትናው ምዕተ አመት መገባደጃ ምዕራፍ ዘመን ላይ ይጀምራሉ። ከነገስታቱ የነአፄ ቴዎድሮስን እርግማን የነአፄ ዮሐንስ የነ አፄ ምኒልክ የነ አፄ ኃይለስላሴ ከሕዝባውያኑ ደግሞ የነ አቡነ ጴጥሮስ የነ በላይ ዘለቀ የነ መንግስቱ ነወይ እርግማን ይጠቅሳሉ።

 

ቴዎድሮስ ሐገር አንድ ላድርግ ብለው ቢነሱ ካህናት ሳይቀሩ በመስዋዕት ውስጥ የእባብ ጭንቅላተ አድርገው ሊገድሏቸው እንደሞከሩና በተለይም ለመንገስ ሲሉ የራሳቸውን ሀገር ሰው የሆኑት አፄ ዮሐንስ የጠላት ጦር /እንግሊዞችን/መቅደላ ድረስ እየመሩ አምጥተው ሊያስገድሏቸው ሲዘጋጁ በማወቃቸው ይችን የኢትዮጵያ ኩሩ ነፍስ የውጭ ጠላት አይገድላትም ብለው ራሳቸው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሊገድሉ ሲሉ ኢትዮጵያ ወንድ አይብቀልብሽ ብለው ረግመዋታል።

 

ቀጥሎም ኢትዮጵያ ከመጣበት ወረራ ለማዳን ከደርቡሽ ጋር አፄ ዮሐንስ በተፋጠጡ ጊዜ የሸዋው አፄ ምኒልክና የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት ለእርዳታ እንዲደርሱላቸው ጠይቀው ባለመምጣታቸው የጦርነቱ አውድ ገብተው አንገታቸው ተቆርጦ ከመሞታቸው በፊት ኢትዮጵያ ዘር አይብቀልብሽ ብለው ረግመዋል።

ከዚያም አፄ ምኒልክ ልጆቻቸው ያዩት የነበረውን የልጅ ልጃቸውን አቤቶ ኢያሱን ለማንገስ ፈልገው ልጄን ተቃውሞ ለዙፋኔ የማያበቃ ቢኖር ጥቁር ውሻ ይውለድ ብለው በመርገማቸው ያው እንዳየነው ንጉስ ተፈሪ ኢያሱን ገድለው ዙፋኑን ቢወርሱ ያን ፋደት የደርግ ጥቁር ውሻ ወልደው አንድ ንፁህ ትውልድ አሰበሉ። ራሳቸው ንጉስ ኃይለስላሴ በተራቸው ከሞቀ ዙፋናቸው ወርደው 4ኛ ክፍለ ጦር ታስረው ሳሉ ምግብ ተመግበው ከጨረሱ በኋላ ታጥበው ፎጣ ለማድረቂያ ሲጣቸው እምቢ ብለው ጣቶቻቸውን ወደ ታች አድርገው የታጠቡበትን ውሃ እያንጠባጠቡ ይህን አስተምሬው የከዳኝን ትውልድ ደሙን እንዲህ አንጠብጥብልኝ እያሉ መርገማቸውን ያየ የሰፈሬ ሰው በደብዳቤ ገልፆልኛል።

እንዲሁም አቡነ ጴጥሮስ ለጠላት ጣልያን የሚገዛ ውግዝ ይሁን፣ መሬቷም ሾክ አሜከላ ታብቅል ብለው ሊረሸኑ አቅራቢያ ረግመዋል። በላይ ዘለቀም መስቀያው አጠገብ እንዳለ አንቺ ሀገር ወንድ አይውጣብሽ ብሎ ተራግሟል። ጀኔራል መንግስቱም ከተሰቀለበት የተክለሃይማኖት አደባባይ ላይ ሕዝብ እየሰማው አንቺ አገር ብሎ በማማረር ተራግሞ አልፏል። ወዘተ

እንግዲህ እኛ የዛሬዎቹ ይህ ሁሉ የግፍ፣ ፍዳና የመከራ የመቅሰፍትና የመአት ማዕበልና ናዳ የሚወርድብን ያን ሁሉ ርግማን ቆጥሮብን ይሆን? /ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ጥር 1993 ኢትዮጵ መጽሄት/

የኢትዮጵያ ነገር ግራ ያጋባል። ኃይሉ ገ/ዮሐንስ እርግማን አለብን ሲል ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ደግሞ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሾተላይ አለባት ይላል። ፀጋዬ ገ/መድህን በ1984 ዓ.ም ባዘጋጀው ሀሁ ፐፑ በተሰኘው ተውኔቱ ነጋ እና አራጋው በተሰኙት ሁለት ገፀ-ባሕሪያት ስለ ኢትዮጵያ አና ዲሞክራሲዋ እንዲህ ይላል።

ነጋ፡-

“እናታችን ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሾተላይ ናት መሰለኝ። ዲሞክራሲን በስድሳ ስድስት ወልዳ በላች። አስቀድሞም በሃምሳ ሶስት አስጨንግፏታል። ብትወልድም ብትገላገለውም ለዘለቄታ አያደርግላትም። የማሕፀን መርገምት አለባት። የዲሞክራሲ ሾተላይ ናት ኢትዮጵያ። በስድሳ ስድስትማ ወዲያው ማግስቱን መፈክር ተፎከረላት። አብዮት ልጆቿን ትበላለች ተባለላት ተሸለለላት። የዲሞክራሲ ሾተላይ እናት በላኤ ሰውነቷን መላው የአለም ሕዝብ አስጠንቅሮ አወቀላት።”

 

በኔ ግምት ግን በዚህ ዘመን ላይ እንደሚኖር ሰው ብዙ የፖለቲካ ምስቅልቅል እንዳላየ ሠው ሆኜ እንደ አንድ የሥነ-ጽሑፍ ባለሙያ እንደ አንድ የሀገሬን የታሪክ ጉዞ እንደሚከታተል ሠው ሆኜ ነገሮችን ስመዝን ኢትዮጵያ ተስፋ አላት። ከጠመንጃ ውጭ ባለ መነጋገርና መግባባት መጨቃጨቅ ላይ ትኩረት ከሠጠነው ተስፋችን የለመለመ ነው። በያ ትውልድ ላይ በርካቶች በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ፅፈዋል። እነዚህን መፃሕፍት ለማንም ሣናዳላ እኩል ማንበብ አለብን።

 

ስለ ያ ትውልድ ታሪክና ማንነት ከክፍሉ ታደሰ በኋላ የተለያዩ ፀሐፈት እንደየግንዛቤያቸው መፃሕፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል። ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ ያህል የኘሮፌሰር ገብሩ ታረቀን መጽሐፍ ማስታወሰ እንችላለን። The Ethiopian Revolution:- war in the Hom of Africa የተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ያ ትውልድ ጥናት አድርገው ያዘጋጁት ነው።

ሌላው ደግሞ ዓለም አስረስ የተባሉ ፀሐፊ ያዘጋጁት መጽሐፍም ተጠቃሽ ነው። History of the Ethiopian Student Movement (in Ethiopia and North America): its impact on intemal Social Change,1960-1974 ይሰኛል። መጽሐፉ በተለይ በውጭ ሐገራት ውስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ ትግሉ መፋፋም ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ይዘክራል።

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቀደም ብለው ከተፃፉት የያ ትውልድ መዘክሮች አንዱ ጆን ማርካኪስ እና ነጋ አየለ ያዘጋጁት Class and Revolution in Ethiopia የተሰኘው መፍሐፍ ነው። የአብዮቱ ሞቅታ ባልቀዘቀዘበት ወቅት የታተመ መጽሐፍ በመሆኑ በሰፊው ተነቧል።

 

ራንዲ ባልስቪክ የተባሉ ሰው ደግሞ Haile Selassie’s Student: Rise of Social and Political consciousness በሚል ርዕስ ስለ ክፍሉ ታደሰ ትውልድ ጽፈዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ምህዋር እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላደረጉት የ1960ዎቹ ወጣቶች ፍልስፍና ላይ ትኩረት የሚያደርግ መጽሐፍ ነው።

ሌላው አሰገራሚ መጽሐፍ ራውል ቫሊዲስ የፃፉት Ethiopia the Unknown Revolution የተሰኘው ሲሆን የታተመው ደግሞ ኩባ ነው። መጽሐፉ የኢትዮጵያን አብዮት አወንታዊ በሆነ መልኩ እየገለፀ የሚተርክና አያሌ መረጃዎችንም የሚሰጥ ነው።

አብዮት ተቀጣጥሎ ትውልድ ሁሉ በፍሙ እና በነበልባሉ ሲቀጣጠል በዓይናቸው ያዩት ደግሞ ዴቪድ ኦታዋ እና ማሪና ኦታዋ የተሰኙ አሜሪካውያን ናቸው። እነዚህ ሰዎች በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ነበሩ። ያዩትን የታዘቡትን Ethiopia:- Empire in Revolution ብለው መጽሐፍ አድርገውት ለንባብ አብቅተውታል።

 

ኘሮፌሰር መሳይ ከበደ Radicalism and Cultural Dislocation የሚሰኝ መጽሀፍ አሳትመዋል። የእርሳቸው ጽሁፍ የሶሻሊዝም እንቅስቃሴ በቀጣይ ኢትዮጵያ ላይ ያመጣውን ልዩ ለዩ ተፅዕኖ አሳይቷል። እኚሁ ምሁር ሌላው ያሳተሙት መፅሐፍ Ideology and Elite Conflicts: Autopsy of the Ethiopian Revoltion የተሰኘ መጽሐፍ ሲሆን እርሳቸውም እስከ ደርግ ፍፃሜ ድረስ የነበረውን በምሁራን መካከል የታየውን የአመለካከት ልዩነት ያሳዩበት መጽሐፍ ነው።

 

ዶናለድ ዶንሃም የተባሉ ሰውም 20 ዓመታት አጥንቼው ነው የፃፍኩት የሚሉት Marxist Modem የተሰኘው መጽሐፍም የኢትዮጵያን የለውጥ አብዮት የሚዳስስና በተለይም የተማሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው።

 

ኤድዋርድ ኪሲ የተሰኙ ፀሐፊም Revolution and Genocide in Ethiopia and Cambodia በተሰኘው መፍሐፋቸው በኢትዮጵያ እና በካምቦዲያ ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ ከዘር ማጥፋት ድርጊት ጋር አገናኝተውት እያነፃፀሩ ያቀረቡበት መጽሐፍ ነው።

 

ኢትዮጵያዊው ፀሐፊ ዶ/ር አንዳርጋቸው ጥሩነህ በዚሁ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ The Ethiopian Revolution 1974-1987 A Transformation from an Aristocratic to a Totalitarian Autocracy በሚል ርዕስ የአብዮቱ መምጣት መንስኤው ምን እንደሆነ እና ያስከተለውንም ወጤት ለማሳየት ሰፊ ጥረት አድርገዋል።

 

ባቢሌ ቶላም To Kill a Generation በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የትውልድ አልቂት በጥሩ ሁኔታ ያሳየበት መጽሐፍ ነው።

በዚሁ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ከተጻፉ የእንግሊዝኛ ጽሁፎች መካከል Documenting the Ethiopian Student movement:- An Exercuse in Oral History የተሰኘው መጽሀፍም በኘሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተዘጋጅቷል። መጽፉ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የሚባሉ አፍአዊ ታሪኮችን ሰብስቦ ለመሰነድ የሞከረ ነው።

ጳውሎስ ሚልኪያስም Haile Selassie, Western Education, and Political Revolution in Ethiopia የተሰኘ መጽሀፍ በማዘጋጀት ልዩ ልዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴና ስለ ደርግ አንዳንድ ምስጢራትን የጻፉበት ሰነድ ነው።

ሪስዛርድ ካፑስንስኪ የተባለ የፖላንድ ጋዜጠኛም The Emperor:- Downfall of an Autocrat በሚል ርእስ መጽሀፍ አሳትሟል። መጽሃፉ የጃንሆይን ውድቀት ከቅርብ አገልጋዮቻቸው እየጠየቀ የተዘጋጀ ነው። ከዚሁ መጽሐፍ ጋር ተመሳስሎ ያለው ሌላው መጽሀፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖረ የሚነገርለት ፓትራክ ግሊስ የጻፈው  the Dying Lion:- Feudalism and Modemization in Ethiopia የተሰኘው መጽሀፍ ነው። የጃንሆይን ስርአተ-መንግስት የመውደቅያ ምክንያቶች በዝርዝር የጻፈበት ነው።

 

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የነበረን ነጠላ ታሪክ ማለትም በአንድ ሰው ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ከተጻፉ መካከል የሕይወት ተፈራ Tower in the Sky የተሰኘው መጽሀፍ ይጠቀሳል። ሕይወት የኢሕአፓ አመራር አመራር አባል የነበረውን የፍቅረኛዋን የጌታቸው ማሩን ሁኔታና በአጠቃላይ በፓርቲውና በዘመኑ ስለነበረው ጉዳይ ጽፋለች። መጽሀፏን በአማርኛም ቋንቋ በጌታነህ አንተነህ አስተርጉማ አቅርባለች። መጽሀፏን በአማርኛም ቋንቋ በጌታነህ አንተነህ አስተርጉማ አቅርባለች።

 

የአስማማው ኃይሉ ከጐንደር ደንቢያ እስከ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተሰኘው መጽሐፍና የኢሕአሠን ታሪክ የዘከረበት መጽሐፍ በውብ አፃፃፉ የተመሰገነበት ነው።

በዘመነ ኢሕአዴግ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሀርቃ ሀሮዬም በደቡብ ክልል ስለነበረው የኢሕአፓ እንቅስቃሴ ከግል ገጠመኛቸው በመነሳት መጽሐፍ አሳትመዋል። የኃይለማርይም ወልዱ ህለፈተ አንጃ ወክሊክ ዘ ኢሕአፓ /2006/ አሳትሟል። በቅርቡም ከኒያ ልጆች ጋር የተሰኘች ውብ መፅሐፍ ታትማለች።

በዘመኑ ከኢሐአፓ በተፃራሪ የቆሙትና ከደርግ ጋር አብሮ በመስራት ለውጥ እናመጣለን ያሉት የመላው የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ አመራር የሆኑት አንዳርጋቸው አሰግድ በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ ብለው ስለትውልዳቸው ዘክረዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርምም ትግላችን በሚል ርዕስ የእሳቸውን የአገዛዝ ዘመን ሊያስረዱ የሞከሩበት መጽሐፍም ታትሟል። የሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ እኛ እና አብዮቱ። የሌሎች የዘመነ ደርግ ፖለቲከኞችና ጦር ሠራዊቶች ብዙ ጽፈዋል። ከወጣትነት እስከ አሁንም ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ዶክተር መረራ ጉዲና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች የሀይሉ ሻወል ሕይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ ሌሎችንም በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ፀሀፊያንን ጨምሮ ዛሬ በኢሕአዴግ ፓርቲ ስር የተሰባሰቡ ፀሐፊያንም ስላሳለፉት የ1960ዎቹ ታሪክ ጽፈዋል።

 

ያንን ዘመን ወደ ፈጠራ ስነ-ጽሁፍም በማምጣት የባየ ንጋቱ የማይቸነፍ ፀጋ የካሕሳይ አብርሃ የአሲመባ ፍቅር፣ የቆንጂት ብርሃኑ ምርኮኛ እና ሌሎችም ፀሐፊያንን እና ጽሁፎቻቸውን መጠቃቀስ ይቻላል።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
17215 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1062 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us