ሁለት እጆቹን ያጣው ታላቁ ሰዓሊ-ወርቁ ማሞ

Wednesday, 01 February 2017 13:40

 

በጥበቡ በለጠ

 

ከአምስት አመት በፊት ነው። እዚህ አዲስ አበባ በሚገኘው ዘመናዊው የጥበብ ማዕከል ወደ ገብረክርስቶስ ደስታ የጥበብ ማዕከል ተጉዤ ነበር። እናም ይህ ማዕከል በየወሩ አንድ በጐ ተግባር መስራት ጀምሮ ነበር። በስዕል ጥበብ ውስጥ “ማን ምንድን ነው” /Who is who in Art/ በሚል ርዕስ ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊዎችን እያቀረበ ጥበባቸውንና የህይወት ተሞክሯቸውን ከታዳሚ ጋር ያቀራርባል። ይህ እጅግ የተከበረ ተግባር ነበር። በወቅቱ አዘጋጆቹን አድንቄ ጽፌ ነበር። አሁን እየሰሩበት መሆኑን እጠራጠራሉ። ቢሰሩበት ጥሩ ነበር።  በኛ ሀገር ከጠፋው አንዱ ነገር ባለሙያዎችን እና ህዝብን በአንድ መድረክ እያገናኙ ማወያየት ነውና።

በዚሁ በገብረክርስቶስ የጥበብ ማዕከል ውስጥ የህይወት ተሞክሮአቸውን ያካፈሉት ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ይባላሉ። ሰዓሊ ወርቁ ሁለቱም እጆቻቸው በአደጋ ምክንያት ተቆርጠዋል። በነዚህ በተቆረጡት እጆቻቸው ነው ሸራ ወጥረው፣ ብዕርና ቀለም ይዘው ዛሬ ለደረሱበት ታላቅ የጥበብ ባለሙያነት ደረጃ የበቁት።

 

 

በዚህ ውይይት ወቅት የነበረ አንድ ሰዓሊ እንዲህ አለ። የጥበብ ሰው፣ የፈጠራ ሰው “አንቱ” አይባልም፤ “አንተ” ነው የሚባለው ብሎ ተናገረ። ምክንያቱንም አስቀመጠ።  እግዚአብሔር ራሱ “አንተ” ነው የሚባለው አለን። ከእግዚአብሔር በላይ የሚከበር የለም። ግን የቅርበት እና የፍቅር መግለጫ ስለሆነ “አንተ” እንላለን። ስለዚህ እኔም ጋሽ ወርቁን “አንተ” ነው የምለው ብሎ ንግግሩን ጀምሯል። እኔም የዛሬውን የጥበብ እንግዳችንን ሰዓሊ ወርቁ ማሞን አንተ ነው የምለው።

 

 

ወርቁ ማሞ እንዴት እጆቹን ተቆረጠ? እንዴትስ ከዚያ በኋላ ተምሮ ያውም ረቂቅ ነፍስ ባለበት በስዕል ጥበብ እዚህ ደረጃ ደረሰ? አጠቃላይ ህይወቱስ እንዴት ነው በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መድረኩ ላይ ከነበሩት ውይይቶች ለዛሬ አጠር አድረጌ አቀርብላችኋለሁ።

ወርቁ ማሞ የተወለደው በ1927 ዓ.ም ነው። ዛሬ የ82 ዓመት ሰው ነው። በ12 ዓመቱ ግድም እዚህ ቸርችል ጐዳና አካባቢ የቆመ መኪና ውስጥ አንዲት በወረቀት የተጠቀለለች ነገር ያገኛል። ወረቀቱን ገላልጦ ሲያየው አንድ የማያውቀው ነገር ውስጡ አለ። ታዲያ ይሄ ነገር ደግሞ ምንድን ነው ብሎ መፈታታት ይጀምራል። አልፈታ ያለውን መታገል መቀጥቀጥ ድንገት ያልታሰበ ፍንዳታ አካባቢውን ያምሰዋል። ወርቁ ሲፈታታው የነበረው ነገር ቦምብ ኖሯል ለካ:: ሁለት እጆቹ ላይ ክፉኛ ጉዳት ያደርስበታል። ቤተሰብ ተጯጩሆ ወደ ሆስፒታል ይወስደዋል። እዚያም እንደደረሰ ዶክተሮቹ ያዩትና ሁለት እጆቹ ከጥቅም ውጭ ስለሆኑ መቆረጥ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ታላቅ ሀዘን። ምንም ማድረግ ስለማይቻል ቤተሰብም እየመረረውም ቢሆን የመጣውን ነገር መጋፈጥ ግድ ነበር። የጨቅላው ወርቁ ማሞ ሁለት እጆች ተቆረጡ። ሁሉም አዘነ። ሁለት እጆቹን ያጣ ሰው ከእንግዲህ ምን ይሰራል ብሎ።

 

ይሁን እንጂ በየትኛውም የልጇ የህይወት ዕጣ ፈንታ ውስጥ የማትጠፋው እናት የወርቁም እጆች ከተቆረጡ በኋላ ታላቁን ተግባር ማከናወን ጀመሩ። ሁለት እጆች የሌሉትን ልጃቸውን ልዩ ልዩ ነገር እንዲሰራበት እንዲሞክርበት አደረጉ። በተለይም ልጃቸው እርሳስና እስክሪብቶ ይዞ ወረቀት ላይ እንዲሞነጫጭር ቀን ከሌት የሚያደርጉት ጥረት ከቀን ወደ ቀን እጅግ ተስፋ ሰጭ ሁኔታ አዩበት። ሁለቱ የተቆረጡት የወርቁ እጆች በጥምረት ሆነው ብዕር ይዘው መፃፍ ጀመሩ። የፈለገውንም ምስል ይስልበት ጀመር። ታላቅ እመርታ። እናም ት/ቤት ገባ። በትምህርቱም ትጉህ ተማሪ ሆነና አረፈው።

 

 

በአንድ ወቅት ሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲማር የርሱ ሰፈር ደግሞ ወደ ፓስተር አካባቢ ነበር። ከፓስተር ወደ ሜክሲኮ እየመጡ ለመማር መንገዱ ሩቅ ነው። በዚያ ላይ እንደዛሬው በነዋሪዎችና በቤቶች የተጥለቀለቀ መንደር ሳይሆን ጫካ ይበዛበት ነበር መንገዱ። እናም ያንን ጫካ እያቋረጡ መምጣትም ከበድ ስላለው አንዳንድ ጊዜ ማርፈድ ጀመረ። ሲደጋግም ያዩት የትምህርት ቤቱ ኃላፊ ቅጣት ብለው በሰሌዳ ላይ ሁለተኛ አላረፍድም የሚል ሀሳብ ያለበት ጽሁፍ ደጋግሞ እንዲጽፍ ያዙታል። እርሱም የተሰጠውን ቅጣት ተገበረው። የሚገርመው ነገር እርሱ የሁለት እጆች ጣቶች ሳይኖሩት የሚፅፈው ከሰውየው የእጅ ጽሁፍ በጣም ይበልጥ ነበር። እናም ቀጭውን አስደነቀው።

 

በስዕል ችሎታው ከቀን ወደ ቀን እመርታ እያሳየ የመጣው ወርቁ ማሞ፣ በመጨረሻም ስነ-ጥበብ ት/ቤት ገባ። የስዕል ጥበብን እንደሙያ ተምሮ ተመረቀ። የሚደነቅ ሰው ሆነ። ስራዎቹ መወያያ ሆኑ። ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሩሲያ ተላከ። በሩሲያም ቆይታው በስዕል ጥበብ በማስትሬት ድግሪ ተመረቀ። ሩሲያ እያለም ተራ ተማሪ ሳይሆን እጅግ ጐበዝ ሰዓሊ ከሚባሉት ተርታ የተመደበ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል።

 

ሰዓሊ እና ቀራፂ በቀለ መኰንን ስለ ወርቁ ማሞ ሲናገር፤ ሩስያ ውስጥ የስዕል ተማሪዎች ደካማ ከሆኑ፤ እንዲበረቱ ለማድረግ እንደ ወርቁ ማሞ እጃቸውን እንቁረጠው ይሆን? ይባል ነበር ብሏል። ይሄ አባባል ሰውየው ምን ያህል እጅ ካላቸው ሰዎች እንኳን እንደሚበልጥ የሚያሳይ ነው።

 

ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ራሱ ሲናገር፤ የእጆቼ መቆረጥ ለበጐ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱንም ሲያስቀምጥ፤ የእኔን መቆረጥ አይተው በዚህ ላይ እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩ ሰዓሊ መሆኔን ሲያዩ ብዙዎች ተበረታተዋል። እኔን አይተው ጠንክረዋል። እኔን አይተው የማይቻል ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል። በርትተዋል። ስለዚህ የእኔ እጆች መቆረጥ ለብዙዎች ጥንካሬን ስለፈጠረ ለበጐ ነው ብሎ የሚያስብ ነው ወርቁ ማሞ።

 

 

ከሩሲያ መልስም እዚሁ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት መምህር ሆነ። ከቀዳሚዎቹ የስነ-ጥበብ መምህራን ምድብ ውስጥ የሚካተት ነው። በዚህም አያሌ ተማሪዎችን አስተምሯል። ዛሬ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ላይ ስመ-ጥር ሰዓሊያንን ያስተማረ ታታሪ ምሁር ነው።

ከወርቁ ማሞ ታዋቂ ስዕሎች ውስጥ ዛሬ የት እንደሚገኝ ያልታወቀው “አድዋ”  የሚሰኘው ስዕሉ ነው። አድዋ ሦስት ሜትር በስድስት ሜትር ሆኖ የተሰራ እጅግ ግዙፍ ስዕል ነው። ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ከያሉበት ተሰባስበው ለቅኝ ገዢዎች አንንበረከክም ብለው በዚህች ፕላኔት ላይ ያሳዩትን የጀግንነት ውሎ የሚያስታውስ ስዕል ነው። ስዕሉ ታላቅ የሀገሪቱ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን ያለበት ቢታወቅ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ጠፍቶስ ቢቀር ይሄን ስዕል ራሱ ወርቁ ማሞ እንደገና ሊሰራው አይችልም ወይ ተብሎ በሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ አማካይነት ተጠይቆ ነበር። ወርቁ ማሞም ሲመልስ እንዲህ አይነት ትልቅ ስዕል በአሁኑ ወቅት ለመሳል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጐማ ኮሚሽን መሆን አለብኝ ብሏል። በተረፈ ስዕሉን መሳል አያቅተኝም ብሎ የ82 ዓመቱ አርቲስት ወኔ ባለው መልኩ ተናግሯል። እርግጥ ነው እንዲህ አይነት ታላላቅ ስዕሎች የሀገሪቱ ቅርሶች ናቸውና እንዲያውም በቅድሚያ ለሰዓሊያን ተከፍሏቸው ነበር መሳል የሚገባው። በሙዚየም ውስጥ ቢቀመጡም የቱሪስቶችን ዓይን ከመሳባቸውም በላይ የሀገሪቱ ትልልቅ ታሪኮችም ናቸውና። ደግሞም በአድዋ ላይ ደም፣ አጥንትና ህይወት ገብረው ሀገራችንን ላቆዩልን ጀግኖች አያቶቻችን ማስታወሻ የሚሆን እንዴት እኛ ለአሁኖቹ ትውልዶች ስዕል እንኳ አናቆያቸውም። ዛሬ ነገ ሳንል ከወርቁ ማሞ ጐን መቆሚያችን ሰዓት አሁን ይመስለኛል።

 

 

ወርቁ ማሞ ከሩሲያ ማስትሬት ዲግሪውን ይዞ እንደመጣ በስነ-ጥበብ ት/ቤት መምህር ቢሆንም ለብዙ አመታት ደመወዙ ሳያድግለት በ500 ብር ብቻ መከራውን ሲያይ ኖሯል። ነገር ግን ያለውን እውቀት ምንም ሳይሰስት እስከ ዛሬ ድረስ ለተማሪዎቹ እያካፈለ እንደሆነ ሁሉም ሰዓሊዎች ይመሰክራራሉ። ግን ለምን 500 ብር ሆነ ደመወዙ? ነገሩ እንዲህ ነው። ሩስያ ውስጥ አምስት አመታት የስዕል ጥበብ ሲማር ማስተርስ ዲግሪ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን የመመረቂያ ወረቀታቸው ሲሰጥ ዲፕሎም ይላል። እዚህ አዲስ አበባ ያሉ “የትምህርት ባለሙያዎች” ደግሞ አንተ የተመረከው በዲፕሎም እንጂ በማስትሬት አይደለም ብለው በስነ-ልቦናም ሆነ በገንዘብ በኑሮው ሲጐዱት ኖረዋል። ይሁን እንጂ በሩሲያ የትምህርት ስርዓት እንደዚያ አይነት የምረቃ ወረቀቶች ሲሰጡ ዲፕሎማ ነው የሚሉት። ይህ ማለት የተማሩት በዲፕሎም ደረጃ ነው ማለት አይደለም። የሚሰጠው ወረቀት ስም ዲፕሎም እንጂ ትምህርቱ ግን ዝርዝሩ ማስተርስ እንደሆነ ነበር። ወርቁ ማሞ ሰሚ ባለማግኘቱ ችግርን ተሸክሞ አያሌ ጥበበኞችን አፍርቶ ዛሬ ኢትዮጵያ በርካታ ሰዓሊያንን ልታፈራ ችላለች።

 

 

ወርቁ ማሞ ዛሬም የራሱ የሆነ የስዕል እስቱዲዮ የለውም። ከዚህ አልፎም የሳላቸውን ስዕሎች የሚያስቀምጥበት ቦታ የለውም። የሚያስቀምጠው ሰው ጋር በአደራ መልክ ነው። ይሄ ታላቅ ሰዓሊ በሀገራችን ውስጥ በስዕል ጥበብ ችሎታው በአንድ ወቅት ተሸላሚ ቢሆንም፤ ሽልማቱም ሆነ ዝናው መሠረታዊ ችግሮቹን ሊቀርፉለት አልቻሉም። ስለዚህ ይህን ታታሪ የጥበብ ወዳጅ ከጐኑ ልንቆምለት ይገባል።

 

 

የወርቁ ማሞ እርካታ ያስተማራራቸው ልጆች በስነ-ጥበቡ ዘርፍ የተሻለ ደረጃ ደርሰው ማየት ነው። ዛሬ በሚያስተምርበት አቢሲኒያ የስዕል ት/ቤት ውስጥ በርካታ ወጣት ሰዓሊያንን እያፈራ ነው። ወርቁ ማሞ በሀገራችን ውስጥ ካሉት የጥበብ አርበኞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። ተማሪዎቹ የነበሩት እና ዛሬም ታላላቅ ሰዓሊያን የሆኑት በቀለ መኰንን፣ ዮሐንስ ገዳሙ እና እሸቱ ጥሩነህም ያረጋገጡት ይሄንን ነበር።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
16704 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 911 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us