የኢትዮጵያ ፊደሎችን ወደ ሥዕል የቀየረው አርቲስት

Wednesday, 01 February 2017 13:37

 

ሠዓሊ ወሰኔ ወርቄ ኰስሮቭ

 

በጥበቡ በለጠ

“የስዕሌን እስቱዲዮ ገዳም ብዬ ነው የምጠራው። አዕምሮዬን ያፀዳል። እጣን አንዳንድ ጊዜ አጨስበታለሁ። ኅብረተሰቤን አስብበታለሁ። ግን ብቻዬን ነው የምነጋገረው። ለምሳሌ በምናብ መርካቶ እገባለሁ። መርካቶን እስቱዱዮዬ ውስጥ አመጣዋለሁ። ማሲንቆ ገራፊውን፣ ሁሉንም እያመጣሁ ከእነርሱ ጋር እነጋገራለሁ” ይላል ሠዓሊ ወሰኔ ወርቄ ኰስሮቭ። ይህን ሠዓሊ የዛሬ 13 ዓመት በአካል ያስተዋወቀችኝ የጀርመን የባህል ተቋም የፕሮግራም ኃላፊዋ ወይዘሮ ተናኘ ታደሰ ነች።

 

ወሰኔ ማን ነው?

ወሰኔ ማን ነው ብሎ መጠየቅ ግምት ውስጥ ይከታል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ገናና ከሆኑት የኢትዮጵያ ሰዓሊያን መካከል አንዱ ነውና። የሥዕል ስራዎቹ እጅግ ግዙፍ በሚባሉት የዓለማችን ሙዚየሞችና ጋለሪዎች ውስጥ በክብር የተቀመጡለት ከያኒ ነው። ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በስዕል ጥበብ ሙያ በማስተርስ ዲግሪ የተመረቀው ወሰኔ፣ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኰሌጆች ውስጥ ስዕልን ሲያስተምር ቆይቷል።

 

 

የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ በ1943 ዓ.ም ነው። እነ ወሰኔ ቤት ጥበብ በራሷ የተወለደችባት ስፍራ ነች ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ታላቅ ወንድሙ እስክንድር ቦጎሲያንም ስለተወለደ። ሁለት የኢትዮጵያ የጥበብ አውራዎች የፈለቁበት ዘርና መንደር።

 

 

ወሰኔ በ1964 ዓ.ም ከሥነ-ጥበብ ት/ቤት ተመርቋል። ኤግዚቢሽን ያሳየው ገና ተማሪ ሳለ ነበር። ከዚያም በርካታ ስዕሎቹን ለእይታ አቅርቧል። ቀጥሎም በ1970ዎቹ ወደ አሜሪካን ሀገር በመሄድ ከፍተኛ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ኑሮውንና ሥራውን እዚያው አድርጐ ቆይቷል።

 

 

ከሀገሩ እና ከህዝቡ በአካል ርቆ የቆየው ወሰኔ ከአመታት በፊት እዚህ አዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ውስጥ በርካታ ስዕሎቹ ለህዝብ እይታ ቀርበዋል። እኔም ወደ ስፍራው ተጓዝኩ እና ስዕሎቹን ጐበኘሁ። እስከዛሬም ድረስ የወሰኔ የስዕል  “ምርኩዞች” አልተቀየሩም። እሱ ሁልጊዜ ስዕል ሲስል የኢትዮጵያን ፊደላት በመጠቀም ነው። ከ“ሀ” እስከ “ፐ” ያሉትን ፊደላት እና ቁጥሮች በመገነጣጠል፣ ብቻቸውን በማቆም፣ በማስተኛት፣ በመገልበጥ፣ በማጣመር፣ በማጋደም ... በላያቸው ላይ የቀለም ብርሃን እየረጨባቸው የውስጥ ሀሳቡን ይገልፅባቸዋል። የኢትዮጵያ ፊደላት የወሰኔ መጠሪያ ናቸው። ወይም ደግሞ የወሰኔ ስም ሲጠራ እነ “ሀሁ” ብቅ ይላሉ።

 

 

እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ፊደል በወሰኔ ውስጥ ቅርፅ አለው። ስሜት አለው። ትርጉም አለው። ለምሳሌ ታላላቅ ነገሮችን መግለፅ ሲፈልግ ማለትም ደጃዝማቾችን፣ ጀግኖችን ማሳየት ከፈለገ እነ“ጀ” እነ“ደ” ብቅ ይላሉ። ሸበላነትን፣ ለግላጋነትን በነ“ሸ” እና “ሰ” ይጠቀማል። እነዚህ ፊደላት ለወሰኔ ግርማ ሞገስ አላቸው። ኃይልንና ግዙፍነትን ያሳይባቸዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ ፍርሃትን፣ አይናፋርነትን፣ አንገት መድፋትን ለማሳየት እንደ“የ” አይነት ፊደላትን ይጠቀማል። ግልፅነትን፣ ደፋርነትን፣ እራስን አጋልጦ ደረትን መስጠትን ለማሳየት ወሰኔ “ተ”፣ “ቸ ” የመሳሰሉ ፊደላትን በስዕሎቹ ውስጥ ያሳያል። ደርባባነትን፣ የሀገር ባህል ልብስ አድርጋ እስክስታ የምትወርድን ሴት ወይዘሮ ለማሳየት “ቀ” ን ይጠቀማል። በአጠቃላይ ፊደላቱ የወሰኔ ታላላቅ ሀሳቦች የሚፈልቁባቸው ጥይቶች ናቸው። ፊደላትን ነው እንደ መሣሪያ እየተጠቀመ ስሜቱን የሚገልፀው።

ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ሲመጣ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት ነበር። በዚያን ጊዜ እንደነገረኝ ከሆነ ወደ አራት ሺ ያህል ስዕሎችን መሳሉን አጫውቶኛል። ይህ እንግዲህ እጅግ አምራች የሚባል የጥበብ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

 

 

በጋዜጠኝነቴና በግሌ የተለያዩ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ ሳደርግ የቀረፅኩበትን ካሴት አልጥልም። ምክንያቱም የአንዳንዱ ኢንተርቪው ሁልጊዜ እንደ ሙዚቃ እየተከፈተ የሚደመጥ በመሆኑ ነው። ለብዙ ጊዜ ከማዳምጣቸው ውስጥ ሰለሞን ደሬሳን፣ በቀለ መኮንን፣ ከአመታት በፊት ያረፈውን ሠዓሊ ዮሐንስ ገዳሙን፣ ገጣሚና ሠዓሊ ከበደች ተክለአብን፣ መስፍን ሀብተማርያምን፣ ፊርማዬ ዓለሙን እና ሌሎችም በርካታ ግለሰቦች አሉ። ድምፀ ወፍራሙ ወሰኔ ወርቄም ላለፉት 14 ዓመታት በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ንግግሩን እየሰማሁ ብዙ ነገሮችን እንዳስብ እንድመራመር አድርጐኛል። ቴፔ ውስጥ የቀረው ድምፁ የብዙ ሀሳቦች ማመላከቻ ሆኖ አገልግሎኛል።

 

 

ወሰኔ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “አንድን ፊደል ስዕል ነው ብሎ ለእኔ ለመወሰን ብዙ ውጣ ውረድ አለው። ምክንያቱም ፊደል ስዕል ነው ብሎ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመግባባትም በጊዜው ችግር ነው። ቡና ሲጠጡ፣ ገበሬው ሲያርስ፣ ቆንጆ ሴት ቁጭ ብላ፣ ሰውየው ማሲንቆውን ይዞ ሲጫወት ነበር የሚሳለው። ይሄን ድሮ ሰራን። እንግዲህ አንድ ሰው ደግሞ ገንጠል ይልና እዚህ ውስጥ የተደበቀ ነገር አለ ብሎ ይገባል። እኔ እዚህ ውስጥ ያገኘሁት ፊደልን ነው። ከእነዚያ ፊደላት ጋር እንግዲህ ስንጨቃጨቅ እስከአሁን ድረስ አብረን አለን” በማለት ይናገራል።

 

 

ወሰኔ ሲያብራራ፤ “አንዳንድ ፊደሎች አሉ ብቻቸውን ማሲንቆ ሲመቱ የምታያቸው፣ ግጥምም ናቸው ስትመለከታቸው። ሰዓሊው እንዴት አድርጐ ነው እነዚህን እንደ ብልት እየቆራረጠ፣ እየገጣጠመ፣ በቀለም እያጫፈረ ያ ፊደል በዓይንህ ላይ ሲበታተንብህ በየአቅጣጫው ሁሉ ያለውን ስሜት ሲሰጥህ አዲስ የአሰራር መንገድ ነው። ከኢትዮጵያ አልፎ የውጭ ሀገር ዜጐች የሚያዩት የቀለሙን አነካከርህን፣ ፊደሎቹ መወፈራቸውንና መክሳታቸውን፣ ገላጭነታቸውን፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ሁሉ ነው። ከእነዚህም ፈዛዛ እና ደካማ ፊደሎች ሁሉ አሉ። የሚደበቁ የሚፈሩ ፊደሎች አሉ። ለምሳሌ እነ“ቀ”ን ብትመለከት ሁለት እጃቸውን ሽንጣቸው ላይ አድርገው ማን ነው የሚደርስብን የሚሉ ናቸው። እነ“የ” ደግሞ አጐብሰው የሚሄዱ ይመስላሉ። ሁሉም የኢትዮጵያ ማንነት የሚገኘው ፊደሏ ውስጥ ነው። ከዚህ ውስጥ እንግዲህ እያወጣህ እያወረድክ ለማሳየት መሞከር ነው” ይላል ወሰኔ።

 

ይህ አንጋፋ ሠዓሊ የሰራቸው እነዚህ በኢትዮጵያ ፊደሎች ላይ የተመሠረቱ ስዕሎቹ ለምሳሌ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚገኘው በግዙፍነቱ እና በጐብኚዎቹ ብዛት በሚታወቀው በስሚስቶኒያን ኢኒስቲቲዩት ሙዚየም ታይተውለታል። ለምሳሌ በዓለም ላይ ስሙን እጅግ ከፍ ካደረጉለት ስራዎቹ መካከል “የኔ ኢትዮጵያ” /My Ethiopia/ የተሰኘው ስዕሉ ለወሰኔ ተጠቃሽ ነው። ይህ ስዕሉ ኒውዮርክ ጋለሪ ውስጥ ሲታይ ከፍተኛ በሚባል ዋጋ ተገዝቷል። ከዚያም በተለያዩ ሙዚየሞች እየተዘዋወረ ታይቶለታል። የአርቲስቱንም ስምና ዝና እጅግ ካጐሉት ስራዎቹ መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ ይጠቀሳል። “የእኔ ኢትዮጵያ” ስዕሉ 132 x 112 cm ሲሆን የተሰራውም እ.ኤ.አ 2001 ዓ.ም ነው። በውስጡም የፊደላት ኀብረት ተቀናጅተው አንድነትን፣ ባህልን፣ ማንነትን፣ ማኅበረሰብን የገለፀበት ልዩ ስራው ነው። የበርካታ መገናኛ ብዙሃንን እና የጥበብ ሰዎችን አስተያየት እና አድናቆት የጋበዘ ስዕል ነው።

ከዚህ ሌላም “ሰባኪው” /The Preacher/ የተሰኘው ስዕሉም ከታላላቆች የጥበብ ጐራ የተመደበ ነው። ይህ ሰባኪው ስዕል ስለ ሃይማኖት ሰባኪው አይደለም የሚያሳየው። ይልቅስ የሰውን ልጅ ህይወት፣ ማንነቱን፣ ስብዕናውን የገለፀበት ነው።

“ሰምና ወርቅ” /Wax and Gold/ ሌላው የወሰኔን ማንነት ካጐሉት ስዕሎች መካከል አንዱ ነው። ስዕሉ የኢትዮጵያን ሥነ-ግጥም ሁለት ፍች እና ከዚያም በላይ እንዳለው ያሳየበት ነው። ወርቅ በእሳት ተፈትኖ በሰም ቅርፅ ሲቀመጥ የሚታይበት ነው። “Contemporary Art From the Diaspora” በሚሰኘው መፅሐፍ ውስጥ ወሰኔ በዓይን የሚታይ ሥነ-ግጥም ደራራሲ /ሠዓሊ/ ነው ተብሏል።

“የላሊበላ ሀሳብ” የተሰኘው ስዕሉም ሰፊ ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ነው። ወሰኔ ስለዚሁ “የላሊበላ ሀሳብ” ስለተሰኘው ስዕሉ ሲናገር 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ሲመራ እና አስደናቂ የጥበብ ውጤቶችን አበርክቶ ያለፈው ንጉስ ላሊበላ ልዩ ሰው መሆኑን ይገልፃል። እንደ ወሰኔ አባባል በዚያ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላሊበላ ይህን ሁሉ የጥበብ ውጤት ሲያበረክት መጀመሪያ የፃፈው ወይም ንድፍ የሰራበት ቁሳቁስ አልያም ፕላኑን ያስቀመጠበት “ሸራራ” ወይም “ሸማ” አልያም እንጨት ወይም ድንጋይ ይኖራል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የሰራባቸው መገልገያዎች በተግባር አልተገኙም። ወሰኔ ደግሞ እነዚህን የላሊበላ ንድፎችን ለማግኘት በሀሳብ ይጓዛል። የሀሳብ ጉዞ - ጥበበኛውን ንጉስ ላሊበላን ለማግኘት። ከንጉሱ ጥበብ ጋር አብሮ ለመኖር መጓዝ። መሔድ ...

 

 

ወሰኔ በስዕሎቹ ኢትዮጵያን ካስተዋወቀበት አንዱ ስለ ቅዱስ ያሬድ ዜማ የሰራው ስዕሉ ነው። ከነቤትሆቨን፣ ሞዛርት፣ በፊት ያሬድ በሙዚቃ ጥበብ የናኘ መንፈሳዊ ሰው መሆኑን ወሰኔ ይናገራል። በዓለም ላይ እኩልነት ስለሌለ የነ ሞዛርት ስም ቀድሞ ይጠራል እንጂ የፕላኔታችን የዜማ ሊቅ ያሬድ ነው ይላል ወሰኔ። እናም ይህ ስዕሉ የያሬድን ማንነት ለዓለም እያስተዋወቀ ያለበት ነው።

 

 

“ጠጅ በብርሌ” የተሰኘው ስዕሉም ሀገርኛ ማንነትን ያስተዋወቀበት ነው። በኢትዮጵያ ፊደሎች ኅብረት የጠጁን ማር ለማሽተት የሰራሁት ነው ይላል ወሰኔ። ስዕሉ የኢትዮጵያን የባህል መጠጥ አሰራራር የሚገልፅ ነው።

 

 

“Sprit of Ancestors” የተሰኘው ስዕሉም የሀገሩ ኢትዮጵያ ህዝቦች የጥንቱ መንፈሣዊ ጥንካሬያቸውና ብርታታቸው ኃያል እንደነበር አሳይቶበታል። “አቢሲኒያ” የሚሰኘው ስዕሉም በዚሁ ምድብ ተጠቃሽ ነው።

ወሰኔ ሲናገር ስዕል ለመሳል፣ የጥበብ ሰው ለመሆን፣ የህይወትን ገፅታ፣ ምንነት ለማወቅ ዓይን ሁሉንም ነገር ማየት አለበት ይላል። “እኛ ሰዎች ሁለት ዓይን ብቻ አይደለም ያለን፤ ብዙ ናቸው። እነዚህን ዓይኖቻችንን ከጭንቅላታችን ውስጥ እያወጣን አካባቢያችንን በጥንቃቄ ማየት ከቻልንበት፣ ዓይተንም ወደ ውስጣችን አስገብተን ማስወጣት ከቻልን ጥሩ ነገሮችን ማፍለቅ እንችላለን” ይላል።

 

 

ወሰኔ ወርቄ ኰስሮቭ ከሚታወቅበት የአሳሳል ዘዬ አንዱ ነገሮችን እየቆረጡ፣ እየገለበጡ፣ ከአንዱ ገንጥሎ ሌላው ላይ በመሰካት፣ መደዴውን የሚታየውን አፍርሶ ሌላ ሠርቶ ማሳየት ... እንዲያ እያደረገ የጥበብን ልዩ ልዩ ገጽታ የማቅረብ ኃይል አለው።

 

 

ለምሳሌ ገና ወጣት ሳለ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ተማሪ ሆኖ የጀመረው አሳሳል አለ። ወሰኔ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

 

“ትዝ ይለኛል ከስዕል ት/ቤት ልመረቅ አንድ ዓመት ሲቀረኝ ሰዎች ቡና ሲጠጡ፣ ቤተ-ክርስትያን ሲሔዱ፣ መንገድ ላይ በጐች ሲሔዱ መሳል ለእኔ አልተስማማኝም። መጥፎ ነው ማለቴ ግን አይደለም። ስለዚህ አንድ ነገር መፍጠር ፈለኩኝ። አንድ የሆነ ረቂቅ /አብስትራክት/ ነገር ልስራ ብዬ የቤተ-ክርስቲያኑን ስዕል ወሰድኩ። እንግዲህ እነ ማርያምን፣ እነ ዮሴፍን ወሰድኩና ፊደሉን ደግሞ እንዲሁ በቃ በራሴው የተለያዩ ፊደሎች እየፃፍኩ እያቀነባበርኩ በመሳል እነማርያምን ዮሴፍን ክንፋቸውን ወስጄ ጭንቅላታቸው ላይ፣ ዓይናቸውን አውጥቼ ጉንጫቸውጋ አደረኩኝ። ያ ሲሆን ትንሽ ችግር ፈጠረብኝ። ትዝ ይለኛል ከ 42 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኬኔዲ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ ነበር ኤግዚቢሽን የከፈትኩት። በጣም ወጣት ነበርኩ። ብዙ አጥባቂ አማኞች ተቃወሙኝ። ያው ያለህን ነው ሰባብረህ የምትሰራው። እንደምታውቀው እኔ ያሉኝ የኢትዮጵያ ፊደሎች ናቸው። እንዳለ አይደለም ወስጄ የምፅፈው። ጐኑን እንደ ቃርያ ቆርጬ የማጋጠምና አዲስ የሆነ የስዕል እሳቤ ነው በስዕሎቼ የማሳየው። ሀይማኖት ስለሚነካ ፀብ ውስጥ ገባሁ። በኋላ ወደ አሜሪካ ሔድኩ።

 

እዚያም ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ስገባ አማካሪዬ መላዕክቶቹን ተዋቸውና ፊደላቱን ያዛቸው አለኝ። እኔም ፊደላቱን አንዴ ስጠመዝዛቸው፣ ሳስተኛቸው፣ ስደራርባቸው፣ ስለጥፋቸው፣ የተለያዩ አይነት ቀለማት ስቀባቸው ቆየሁ። እንደገና ወስጄ ሳሳይ ሲስቁብኝ፣ አንዳንዴ ጥሩ መንገድ መጥተሀል፣ ይዘሃል እያሉ ሲያሞግሱኝ፣ ያ ነገር በየጊዜው በራሴው ስሜት እየተራገጥኩ እየወጣሁ መጨረሻ ላይ እነዚህ ፊደሎች ከኔ ጋር መነጋገር ጀመሩ። “ሀሁ” የቆጠርኩባቸው ፊደሎች ሌላ ነገር እየያዙ መውጣት ጀመሩ። ፊደላቱ ለእኔ መሣሪያ ሆኑኝ። እንደ ቢላ እና ሹካ፣ ከዚያም አልፎ እንደ ቲማቲም እና ሽንኩርት ሆኑ። ይቆረጣሉ፣ ይቆራረጣሉ። ዛሬ በዓለም ላይ ሀገሬንም እኔንም ያስጠራሉ። ከእኔ ጋር የትም ይጓዛሉ” በማለት ይገልፃቸዋል ወሰኔ ወርቄ ኰስሮቭ።

 

 

ሐገርኛ፤ ኢትዮጵያዊኛ የሆኑትን የወሰኔን ስራዎች በጣም እወዳቸዋለሁ። ምክንያቱም ቁጭ አድርገው ያሳስቡኛል። ከወሰኔ ወርቄ ኰስሮቭ የስዕል መንፈስ ጋር እንዳወራ ያደርጉኛል፣ ያጨቃጭቁኛል፣ የስቆጡኛል፤ እጠይቃለሁ፣ እመልሳለሁ። የጥበብ ተጓዥ ያደርጉኛል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
17011 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1037 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us