ደቡብ አፍሪካዊቷ እንግዳዬ

Wednesday, 22 March 2017 12:38

 

በጥበቡ በለጠ

ሰሞኑን በከፍተኛ የስራ ውጥረት ውስጥ እያለሁ አንዲት ትልቅ እንግዳ ከደቡብ አፍሪካ መጣችብኝ። ትልቅ ባለውለታዬ ነች። ሐገርዋ ደቡብ አፍሪካ የዛሬ 13 አመት ለትምህርት ስሄድ በሐገርዋ አብራኝ ተምራለች። የወራት የደቡብ አፍሪካ ቆይታዬንም እንዳይሰለቸኝ ያደረገች ትጉህ ጋዜጠኛ ነች። ቀስተ ዳማናዊትዋ ደቡብ አፍሪካን /The rainbow nation/  እንደ ራሴ አገር መስላ የታየችኝ እንደዚህች አይነት መልካም ሰዎች በውስጥዋ ስላሉ ነው። የሐገርዋን ደቡብ አፍሪካን ታሪክ ጠንቅቄ እንዳውቅ ያደረገችውን ይህችን ጉብል ዛሬ እስዋንና ስራዋን አስተዋውቃችኋለሁ።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ዜል ኤልሲ በአፍሪካውያን ‘ባሪያዎች' ላይ ዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ላይ ነች። ሀገሯ ደቡብ አፍሪካ ሙሉ ዙሪያዋን በህንድ ውቂያኖስ የተከበበች ሀብታም ሀገር ብትሆንም በዚህ ውቅያኖስ መታጠሯ ደግሞ ሌላም ጉዳት አስከትሎባት ኖሯል። ይህም ከዛሬ 300 አመት በፊት ጀምሮ በውሃ ላይ የጉዞ መሠረታቸውን አድርገው የሚጓዙ ሀገር አሳሾች ከአውሮፓ ተነስተው ሲያስሱ አንድ ለም የሆነ ምድር ያያሉ። ለብዙ ወራት መሬት ሳያዩ፣ መሬትም በጣም ስለናፈቀቻቸው ለማረፍ ሲሉ የመርከባቸውን መልህቅ ያቺ በደስታ ወዳዪት ምድር ላይ ጣሉ። መሬቷንም ሄደው ሳሙ። ምድር ሆይ የተባረክሽ ነሽ አሏት። ለእረፍት ቁጭ ያሉባት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ናት። መሬቷ ለም ነው። በውስጧ እምቋ የያዘው ደግሞ ተአምር ነው። የዓለም የከበሩ ማዕድናት ሁሉ የሚገኙት በዚህች ቦታ ነው። አውሮፓውያኑን ገረማቸው። ዛሬ “ፖርት ኤልዛቤት” ተብላ በመትታወቀው የደቡብ አፍሪካ የጫፍ ከተማ የገቡት ሰዎች ወደ ውስጥ መስረግ ጀመሩ።

 

ደቡብ አፍሪካ እነርሱ ከመጡባት አውሮፓ በላይ በመአድናት የተንቆጠቆጠች በወርቅ፣ በአልማዝ፣ በሜርኩሪ፣ በታንታለም ወዘተ. የከበረች ምርጥ ምድር በመሆኗ የአውሮፓ ሰፋሪዎች ከያሉበት ተጠራሩ። እየተከማቹ መጡ። ከተለያዩ ሀገሮች በመምጣታቸውም የአንድ የአውሮፓን ሀገር የቅኝ ግዛት መንግሥት ማቋቋም አልቻሉም። ወይ የእንግሊዝን፣ ወይ የፈረንሣይን፣ ወይ የኔዘርላንድን ወዘተ. መንግሥት ብሎ መመስረት ከባድ ሆነባቸው። ምክንያቱም ሁሉም ገናና የአውሮፓ አገሮች ደቡብ አፍሪካን የዛሬ 300 አመት ከበዋታልና ነው። ስለዚህ የሰፋሪዎች (settlers) መንግሥት መሠረቱ። ከሁሉም ሀገሮች የተውጣጡት ፈረንጆች የነጮች መንግሥት አቋቋሙ። ከዚህ በኋላ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን የመከራና የሲኦል ኑሮ ጡጫውን አጠንክሮ ሲመጣ፣ ለነጮቹ ደግሞ ገነት ምድር ላይ ተቋቋመች። ተፈጥሮም በሰው ልጆች ላይ የምትከተለውን ህግ አዛብታ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ለ300 አመታት እጅግ በድላቸው ኖረች።

ከዚህ በኋላ ደቡብ አፍሪካ የባሪያ ንግድ እጅግ የሚጧጧፍባት፣ ሀብቷ የሚመዘበርባት እና በጣም የሚገርመው ደግሞ የተቋቋመው የነጮች መንግሥት ለራሱ እንዲመቸው ለማድረግ ሀገሪቱን ከየትኛውም የአውሮፓ ከተማ ለማስበለጥ እየገነባ የነበረው መሠረተ ልማት ዛሬም ድረስ እነ ኬፕታውንና ደርባንን የመሰሉ ውብ ከተሞች አውሮፓ ውስጥ ማግኘት እንዳይቻል አድርገዋል።

ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስ። ዜል የዛሬ 300 አመት ደቡብ አፍሪካ ከረገጡት ነጮች የዘር ሐረግ የምትመዘዝ ናት። ከአንዱ ገናና ሀገርም የመጡት ፈረንጆች ቤተሰብ ብትሆንም ወደኋላ ሄዳ ያንን የዘር ግንዷን ቆጥራ መመፃደቅ አትፈልግም። እርሷ የምታውቀው ደቡብ አፍሪካዊት መሆኗን ብቻ ነው። የቆዳዋ ቀለም ፈረንጅ ቢሆንም ሌላ የምታውቀው የለም። ሀገር ወዳድ ደቡብ አፍሪካዊት ዜል።

 ዜል የምታስገርም ሴት ነች። ስትናገርም እንዲህ ትላለች፡- እናትና አባቴ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ በምትሰቃይበት ወቅት ከጥቁሮች ጋር ሆነው የዘር መድልዎን ሲያወግዙ የኖሩ ናቸው። ሠልፍ የሚወጡት ከጥቁሮች ጋር ነው። በዚህ ብቻም አላቆሙም። በተለይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ሁሉም ጥቁሮች ከነ ኬፕታውን፣ ደርባን፣ ፕሪቶሪያ፣ ጆሀንስበርግ፣ ፖርት ኤልዛቤት ወዘተ. እንዲወጡ ይደረጋል። ምሽቱን ለነጮቹ ይለቃሉ። በምሽት ከተሞች ውስጥ የተገኘ ጥቁር ይታሰራል ይገደላል። ይህ መከራ ለ300 አመታት ኖሯል። ግን የዜል ቤተሰቦች የጥቁሮቹ የትግል አጋሮች በመሆናቸው እንደ ጥቁሮቹ ሁሉ ማታ ማታ ከከተሞች ውጪ ከጥቁሮች ደቡብ አፍሪካዊያን ጋር በመሆን ነው የሚኖሩት። እናም የማንዴላው ANC አባላት መካከል የዜል ቤተሰቦች በጣም የታወቁ ናቸው። ዜልም ተወልዳ ያደገችው በጥቁሮች መካከል ነው።

ደቡብ አፍሪካ ነፃ ስትወጣ እንደ ዜል ቤተሰቦች አይነት የሆኑ በርካታ ነጮች በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ክብርና ሞገስ አግኝተዋል። ዜልም ብትሆን የቤተሰቦቿ ልጅ ናትና ነብስ ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ ልዩ አትኩሮቷ ጥቁሮች ላይ ነው።

ዛሬ ዜል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ታዋቂ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት። በምትሰራበት SABC (South African Broadcast Corporation) ውስጥ ልዩ ትኩረቷ የጥቁሮች ህይወት ቢሆንም፣ ማንዴላ የፈጠሯትን የጥቁሮችና የነጮች ሀገር የሆነችውን ደቡብ አፍሪካም የቀለሞች ውህደት ወደ ሌላ ስልጣኔ እንዲያሸጋግራት ደፋ ቀና እያሉ ከሚሠሩ ታታሪ ሰዎች መካከል አንዷ ናት። ነጮች ባለፉት 300 እና ከዚያም በላይ በነበሩት ዘመናት ውስጥ በጥቁሮች ላይ ያደረጉትን በደል በማስታወስ ይህም እንዳይደገም ትምህርታዊ በሆነ መልኩ በጥንቃቄ ስራዋን የምትወጣ ባለሙያ ናት።

እናም Slave Coast Line በሚል ርዕስ በተለይ የባህር በር ያላቸውን ወይም የነበራቸውን ሀገሮች በመዞር ዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ላይ ነች። ደቡባዊውንና ምዕራባዊውን አፍሪካ በርካታ ጥናት ያደረገች ሲሆን ብዙም ያልገፋችበት ምስራቅና ሰሜን አፍሪካን ነበር። እነሆ ዛሬ ከዚህች ምርጥ አፍሪካዊት ጋር ቆይታ እናደርጋለን።

ዜልን የማውቃት በህይወት አጋጣሚ በተከሰተ ገጠመኝ ነው። የዛሬ አስራ ሶስት አመት ከሰባት የአፍሪካ ሀገራት ተውጣጥተን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የትምህርት ዕድል ተሰጥቶን ተሰባስበን ነበር። በቁጥር 11 ነን። ከነዚህ ውስጥ ሁለት ደቡብ አፍሪካዊያን ነበሩ። አንዱ ሴፖ የተባለ ጥቁር አፍሪካዊ የSABC ጋዜጠኛ ሲሆን ሁለተኛዋ ዜል ናት። አብዛኛዎቻችን ከተለያዩ ሀገሮች የመጣን ቢሆንም እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ የማይረሳውን የደቡብ አፍሪቃን ውብ ፍቅር ልቤ ውስጥ የከተቱት እነዚህ ሁለት ወጣት ጋዜጠኞች ነበሩ።

የህንድ ውቅያኖስን ታኮ የሚገኘውና ከፖርት ኤልዛቤት በመኪና የሁለት ሰዓት ተኩል መንገድ የሆነው እና የደቡቦች ደቡብ የሚባለው ግርሀም ስታውን ከተማ ውስጥ ግዙፉ ሮድስ ዩኒቨርስቲ ከተለያየ ባህልና ታሪክ ውስጥ ተመዘን የወጣን ጋዜጠኞችን ሰብስቦናል። ከመካከላችንም በቀለም ፈረንጀ የነበረችው ዜል ፍፁም ትህትና እና የሰው ፍቅር የሰጣት እናቶች እንደሚሉትእርብትብት ናት።

በቆይታችንም ወቅት እያንዳንዳችን የወደፊት ርዕያችንና እየሠራንም ስላለናቸው ጉዳዮች ተወያይተናል። ከሁሉም ለየት ያለው የዜል ፕሮጀክት ነበር። ድርጅቷ SABC በመደበላት በጀት ደቡባዊና ምዕራባዊ አፍሪካን የባሪያ ፍንገላ ታሪክ ሰርታ መጨረሷንና ወደፊትም ወደኛዋ ታሪካዊት ምድር ምስራቅ አፍሪካ እንደምትመጣ ቀልድ የሚመስል ጨዋታ አወጋችን።

ትምህርታችን ካለቀ በኋላ ሁላችንም ወደየመጣንበት ተበታተንን። ግን ሁል ጊዜ መፃፃፋችን (E-mail) መደራረጋችን አልቀረም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን ዜል ኢትዮጵያን እንደ ጦስ ዙሪያዋን ስታስስ ነው የቆየችው። አንድ ጊዜ ሞሮኮ ነኝ ትላለች። ሌላ ጊዜ አልጄሪያ፣ ቀጥሎ ግብፅ፣ ከዚያ ሱዳን፣ ከዚያ የመን፣ ቀጥላም ሱማሌ ላንድ፣ ኬኒያ እያለች ታሪክ መቆፈር ከጀመረች ቆየች።

በወርሃ ጥር አንድ ሰፊ E-mail  ፃፈችልኝ። የፃፈችው ባጭሩ እንደሚገልፀው“ሀገርህ ኢትዮጵያ የምትገርም ናት፤ በየሄድኩባቸው ቦታዎች ታሪክ አላት። የእርሷ ስም በሁሉም ቦታ አለ። ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ በባርያ ንግድ ትታወቃለች። የሚገርመው ግን ሌሎች ሀገሮች በአውሮፓውያን ቅኝ ተገዝተው ነበር፤ የባሪያ ፍንገላ የሚደረገው። ያንተ ሀገር ግን የራሷ ነገሥታት በነፃነት ቢኖሩም ግን የባሪያ ንግድ ያጧጡፉ ነበር። አሁን አንድ ትልቅ ውለታ ዋልልኝ። መቼም እንዳስቸገርኩህ አውቃለሁ። በመጋቢት ወር ላይ ሀገርህ ኢትዮጵያ እመጣለሁ። እስከዚያው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የባሪያዎች ታሪክ ወይም ፍንገላ የተፃፉ ዶክሜንቶች ካሉ አጭር ጥናት ስራልኝ። ወሮታውን ስመጣ እከፍላለሁ” ይላል።

እኔ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ የሀገሬን ታሪክ ሳነብ ሆን ብዬ ባርነት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ነበር? በማለት አስቤውም ሆነ አንብቤው አላውቅም። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ባርነት ላይ ዜል አሳሰበችኝ። የት ልሂድ? ምን ላንብብ? ለዜል ደግሞ፣ አይደለም የባሪያን ታሪክ፣ ባሪያ ቢሆኑላት የማታስቀይም ልበ ንፁህ ደቡብ አፍሪካዊት ነች።

ከወርሃ ጥር የጀመርኩ እስካሁን ድረስ የሀገሬን የባሪያ ፍንገላ ታሪክ እየፈለኩ ነው። ሰውዬው “የአላህን መኖር በምን አወክ?” ሲባል የመለሰው መልስ “ያላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ” ብሎመመለሱ ይነገራል። እኔም ባርነትን እንዲህ እለፋበታለሁ ብዬ አልሜውም አላውቅም። እናም የዜል መምጫ እየደረሰ ነው። የኔ የባርነት ጥናት ደግሞ እራሴውኑ አስገርሞኛል። እጃችን ላይ የነበረውን ታላቅ ታሪክ ሳንሠራበት ሩቅ ሀገር ተወልዳ ያደገችው ባይተዋሯ ዜል ታላቅ ዶክመንተሪ ልትሠራበት ነው። በእርግጥ የዜል ስራ ለራሷም ሆነ ለሀገራችን እውቅና ጉልህ ሚና ቢኖረውም የኛ ህይወት ግን ክፉኛ ያሳዝነኝ ገብቷል። እነ ዜል ከደቡብ አፍሪካ ተነስተው በየሀገሩ እየዞሩ ታላላቅ ዶክመንተሪዎች ሲሠሩ እኛ ኢትዮጵያዊያን የሚያስጨንቀን ነገር የጨው መወደድ፣ የበርበሬ መናር፣ እና ልዩ ልዩ ሀሳቦች ናቸው። የሀሳቦች ልማት ማምጣት አለብን።

ለመሆኑ ምን ተጠንቶ ነው ዜል የምትመጣው? ዜል ከኔ የምትፈልገው የባሪያ ንግድ በየትኞቹ ነገሥታት ዘመን ላይ ነበር? የባሪያስ ገበያ የነበረው የት ነው? የባሪያዎች ማህበራዊ ታሪካዊ ህይወት ምን ነበር? የባሪያ ንግዱን ይረከቡ የነበሩ ነጋዴዎች እነማን ነበሩ? ወዘተ. የሚል ነው። በእርግጠኝነት እንዲህ ነው ብሎ መናገር የሚያስችል ታሪክ ለመፃፍ የሚያስችሉ መረጃዎችን ላለፉት ሦስት ወራት መሰብሰቤ አልቀረም። ታላቁን የሀገራችን ታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን መጻህፍት ማንበብ ግድ ብሎኛል። ግን እንዴት ሆኖ ነው ዶከመንተሪ ፊልም የሚሆነው እያልኩ ሳሰላስል ቆይቻለሁ። ብዙ ዘዴዎችን ብቀይስም ዜል እሱ አያሳስብህ፤ እውነተኛውን ታሪክ ግን አደራጅልኝ አለችኝ። የኔ ችግር የምስል ችግር ነው። ፊልም ምስል Image! Image! Image! ይባላልና ነው።

መቼም የሀገራችን ታሪክ ለመፃፍ ስንነሳ ከየት እንደሚጀመር ግራ ያጋባል። ግራኝ መሀመድና ተከታዮቹ አብዛኛዎቹን የሀገራችንን የታሪክና የእምነት ሰነዶች ስላወደሟቸው ታሪካችንን የምንመዘው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አይቶን ሄዶ ብዙ ስለፃፈብን ፖርቹጋላዊው ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው።

አልቫሬዝ በዘመኑ በአይኑ ያየውን ሲገልፅ ባሪያዎቹ በግብርና፣ በሸክም፣ በቤት ስራ ጌቶቻቸውን እንደሚያገለግሉጽፏል። መልካቸው የጠቆሩም ሰዎች ባሪያዎች እንደሚባሉ ጠቁሟል። አብዛኛዎቹም ከደቡብና ምዕራባዊ ኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚመጡ የፃፈ ሲሆን የሚደርስባቸውንም መከራ አብራርቷል። በዚያን ዘመን ባሪያዎች ይኮላሹ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል። ፀሐፊዎቹ እንደሚሉት ባሪያዎቹ ሲኮላሹ በህይወት ከሚተርፈው ይልቅ የሚሞተው እንደሚበልጥ ገልፀዋል።

ባሪያዎች እንደ ዕቃ ገበያ ላይ ታስረው ይሸጡ ነበር። እጅና እግራቸው አምልጦ እንደሚጠፋ እንስሳ ታስሮ ለገበያተኛ ይቀርቡ ነበር። በዚሁ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ የባሪያ ንግዶች እንደነበሩ Marco Polo-The Travels of Marco Polo መጽሐፉ ገልጿል። በዚያን ዘመን ማለትም በ17ኛው መቶ ተጓዥ የነበረው ጣሊያንያዊው Giacomo Baratti u1670 The Late Travels of S.Giacoma Baratti in to the Remote Country of the Abyssinian በተሰኘው መጽሐፉ የቱርክ ወታደሮች ክርስትያን የሆኑትን ኢትዮጵያዊያን ባሪያዎች እየገዙ እንደሚወስዱ ያትታል።

በሁለቱ ፀሐፊዎች አባባል ደንበኛ የባሪያ ንግድ መጧጧፊያ ቦታ የነበረችው በቀይ ባህር፣ ዘይላ፣ በርበራ ማለትም በኤደን ሰላጤ ወደ ዓረብ ሀገራት ይጓጓዙ እንደነበር ጽፈዋል።

በግዕዝ የተፃፈው ገድለ ዜና ማርቆስም ወደ ሀገራችን ለንግድ የሚመጡትን የገበያውን ሁኔታ ጽፏል።

ሃርጊጐ - ከምፅዋ በተቃራኒ በኩል የምትገኝ የባሪያ ንግድ ወደብ ነበረች።

ቤይሉል - ከአፋር በስተደቡብ የምትገኘ የባሪያዎች መነገጃ እንደነበረች በ1648 ዓ.ም የየመኑ መልዕክተኛ አንባሳደር ሀሰን ኢብን አህመድ አል-ሃይሚ የአቢሲኒያን ነጋዴዎች ሁኔታ ፅፎበታል።

ዘይላ - በምስራቅ በኩል የምትገኝ ናት። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፖርቹጋሉ ፀሐፊ Bernando Pereira  ተመልክቶ እንደፃፈው የዝሆን ጥርስና የባሪያዎች ገበያ ማየቱን ገልጿል።

በርበራ - እስካሁን የሚያገለግል ወደብ ነው። በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው Nicolode conti  የገበያውን ሁኔታ በሰፊው ገልጿል።

ዳሞት - ይህች ደግሞ እዚህ ጐጃም ውስጥ የምትገኝ ቦታ ናት። ባሪያዎች ከያሉበት ተሰባስበው የሚሸጡባት የሀገር ውስጥ የገበያ ማዕከል እንደነበረች አልቫሬዝ ገልጿታል።

እንፍራንዝ - ጎንደር ውስጥ ያለች ወረዳ ነች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከሸዋ ወደ በጌምድር ሲዘዋወር የባሪያ ንግዱም ማዕከልነት ወደዚያው ተሸጋገረ። ቦታው ለሱዳን ቅርብ በመሆኑ እንፍራዝም ለባሪያ ንግድ መቀባበያ አመቺ ቦታ እንደነበረች ፈረንሣዊው ፖንሴት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገልጿል።

ሌሎች የገበያ ማዕከሎችን በዘመኑ በአይናቸው ብሌን የተመለከቱ ፀሐፊያን ያስረዱናል። ኢትዮጵያ ከስልጣኔዋ ወደ ቁልቁል ልትንደረደር በተዘጋጀችበት ጊዜ ወደ ጎንደር መጥቶ እቴጌ ምንትዋብ ቤተ-መንግሥት ውስጥ አምስት አመት ተቀመጠ የሚባለው እስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ ከ200 አመታት በፊት በፃፈው Travel to discover the source of the Nile በተሰኘው መፅሐፉ ይሸጡ የነበሩት ባሮች አብዛኞዎቹ ክርስትያኖች እንደነበሩና ይጋዙ የነበረበትም ስፍራ ወደ ሙስሊም አገሮች መሆኑን ገልጿል። እንደ ብሩስ አባባል ከሆነ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በጎንደር ቤተ-መንግሥቶች ባሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ አያሌ ባሪያዎች እንደነበሩ ያየውን ጽፏል። ከነዚህ ውስጥ የ17 እና የ18 አመት ወጣት የሆኑትና ንቃት የሚታይባቸውን ባሪያዎች የጎንደር ነገሥታት ልዩ ልዩ ትምህርትና ስልጠና ይሰጧቸው እንደነበር ጀምስ ብሩስ ጽፏል።

ጎንደር የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ከሆነች በኋላ ደግሞ ወደዚያ ለሽያጭ የሚጋዙት ባሪያዎች መብዛት ጀመሩ። ቀጥሎ ደግሞ ጭራሽ መዋለድ ሁሉ ጀመሩ። በ1624 ዓ.ም ከነገሡት ከአፄ ፋሲል ጀምሮ እስከ አፄ ኢዮአስ ድረስ ባሉት 150 አመታት ውስጥ ጎንደር ውስጥ የተከማቹት ባሪያዎች የዘር ግንድ ሁሉ እንደነበራቸው በ1898 ዓ.ም ፈረንሣዊው Antoine d'Abbadi Geographic de 1'Ethiopia በተሰኘው መጽሐፉ ገልጿል። እንደ አባዲ አባባል ከሆነ የባሪያዎቹን የመጀመሪያ ተጋቢዎች እናትና አባታቸው ወይም የመጀመሪያ ወላጆቻቸው 'ቀናጅ' እንደሚባሉና የነርሱ ልጆች ደግሞ 'አመለጥ'ሲባሉ፣ የልጅ ልጆች ደግሞ 'አሰለጥ'ይባሉ ነበር ሲል ገልጿል። እንዲሁም ደግሞ የነርሱ ወላጆች የሆኑትን ማለትም የባሪያዎቹ 1/8ኛ የዘር ግንድ የሚባሉት 'ፈናጅ'ተብለው እንደሚጠሩ አባዲ ገልጿል።

ሩፒል በ1838 Reise in Abyssinian በተሰኘው መፅሀፉ እንደገለፀው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበሩ ባለፀጋ ቤተሰቦች ውስጥ በርካታ ባሪያዎች እንደነበሩና ህይወታቸውንም ጽፏል።

Pearce Nathaniel በ1820 በፃፈውA small but True Account of the ways and manners of the Abyssinians  በተሰኘው መጽሐፉ በ1831 ዓ.ም The life and Adventures of Nathaniel Pearce  ተብሎ በታተመለት መጽሐፉ ውስጥ ስለ ሀገራችን የባሪያ ታሪክ ተፅፏል። በታሪኩ ውስጥ እንደተገለፀው ነገሥታቱ ራሳቸው የባሪያን ንግድ የሚቃወሙ አልነበሩም። ፒርስ ራስ ወልደሥላሴን በመጥቀስ፣ እኚህ ባለስልጣን ራሳቸው በርካታ ባሪያዎች በዙሪያቸው ነበሩዋቸው ብሏል።

ጐባት u1850 Journal of a Three Year's Residence in Abyssinia በተሰኘው ፅሁፍ ውስጥ እንደገለፀው በሰሜን ኢትዮጵያ ከወንዶች ይበልጥ ሴቶች በባርነት ላይ እንደነበሩ ፅፏል። አንድ ሰው ባለጠጋ ነው የሚባለውም ብዙ ባሪያዎች ሲኖሩት እንደሆነ ፅሁፉ ያብራራል።

ሀሪስ በ1844 ዓ.ም The Highlands of Ethiopia በተሰኘው መፅሀፉ ደግሞ ሸዋ ውስጥ በእያንዳንዱ ገበሬ ቤት ሁሉ ባሪያዎች እንደነበሩ ገልጿል። ከዚህ ሌላ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ እህል ብቻ የሚፈጩ 300 ሴት ባሪያዎች እንደነበሯቸው ተገልጿል። ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጠላ ጠማቂዎች፣ ውሃ ቀጂዎች፣ እንጨት ፈላጮች ወዘተ. ነበሩ ብሏል።

ፕራፕግ በ1867 ዓ.ም Travels Researches and Missionary Labors በተሰኘው መጽሐፉ በ18 አመቱ ስለተሸጠው ባሪያ የሚያስታውሰውንጽፏል። ዲልቦ ከተባለው እናርያ አካባቢ ካለው ስፍራ በባርያ ፈንጋዮች የተያዘው ወጣት ወደ ማግራ ተወሰደ። ከዚያም አጋብጃ በተባለ ስፍራ በአርባ አሞሌ መሸጡን ጽፏል። ቀጥሎም ገዥው ጐና ወደተባለው የሶዶ አካባቢ ወሰደው። ገዥው እንደገና ሊያትርፍበት እንደገና ገበያ ላይ አስቀመጠው። አንዱ የባርያ ገበያተኛ መጣና አትርፎ ገዛው። ከዚያም እራሱ ደግሞ ወደ ሸዋ የደራ ገበያ አምጥቶት 80 አሞሌ ሸጠው። ከዚያም ሌላው ገዢ ደግሞ ወስዶት ከፍተኛ ገበያ አለበት ተብሎ ከሚጠራው አልዩ አምባ ከተባለው ስፍራ ሸጠው። አሁን ገና ባሪያውም በገንዘብ ተሸጠ። ይህም 12 ማርያ ትሬዛ ነበር ያወጣው። ገበያው እንዲህ እየተቀባበለው በመጨረሻም ንጉሥ ሳህለሥላሴጋ ተሽጦ እንደመጣ Krapf ፅፏል። ይህን ሳነብ ባሪያን ምን ያህል ተወዳጅ ቢሆን ነው ብዬ አስበዋለሁ።

ለመሆኑ የባርያ ንገድን ነገሥታት ለምንድን አላስቆሙትም? በዚያ በሩቁ ዘመን ፍትሃነገሥት የነገሥታት ህግ የተሰኘ መጽሐፍ አለ። እርሱስ ስለዚህ የባርያ ንግድ ምን ይላል? በእርግጥ ፍትሃነገሥት የባርያን ንግድ አጥብቆ ይቃወማል። ክርስትያኖች ባርያን መሸጥና መለወጥ እንደማይገባቸውጽፏል። እ.ኤ.አ በ1607-32 የነገሡት አፄ ሱስንዮስ የባርያ ንግድን የሚቃወሙ ነበሩ።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እየተጋዙ ወደ አውሮፓና ኤዥያ ተሽጠው በመጨረሻ ደግሞ ከአንበሳ ጋር እያፋለሟቸው ይዝናኑባቸው ነበር። “ሰቆቃው አፍሪካ”ሊባል የሚችል ዘመን አፍሪካውያን አሳልፈዋል። ዛሬ ጥቁሯ ግብፅ፣ ጥቁሯ ህንድ፣ ጥቁሯ አሜሪካ... የዚያን ጊዜ ታሪኮች ናቸው።

ለመሆኑ ሃይማኖቶች ክርስትናና እስልምና ስለ ባርነት ምን ይላሉ? ሀገራችን ኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በገጠሯ ውስጥ የባሪያ ንግድ ታጧጡፍ ነበር። 1970-71 ላይ ነው የቆመው የሚሉ አሉ። ጉዳዩን ወደ ውስጥ እየገባሁበት ነው። በመረጃ አግዙኝ። ዜል ልትመጣብኝ ነው። የባሪያዎች ደምና ነብስ እንዳይወቅሰን የምናውቀውን እንስጣት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16542 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 780 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us