የኢትዮጵያዊነት ልክፍት በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ

Wednesday, 23 August 2017 12:06

 

በጥበቡ በለጠ

 

‘ልክፍት’ የሚለውን ቃል በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከፍተኛ ፍቅርን እና መውደድን ልገልጽበት ፈልጌ ነው።

ዛሬ የምናያቸው ልክፍተኛ ኢትዮጵያዊያን ፀሐፊዎችን ነው። በተለይ ደግሞ ፅሁፎቻቸው እምብዛም ገበያ ላይ ባይገኙም በቤተክርስቲያንና በመስጊዶች እንዲሁም በሌሎች አብያተ መፃህፍት ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ፀሐፊዎችን ማለትም የተወሰኑትን ከዚህ በፊት “በኢትዮጵያ ፍቅር የተለከፉ ደራሲዎች” በሚል ርዕስ አስተዋውቄያችሁ ነበር። አሁንም ከነዚሁ በኢትዮጵያ ፍቅር ከተለከፉ ፀሐፊዎች ምድብ ውስጥ ‘ልክፍተኛ’ ኢትዮጵያዊንን በጥቂቱ መዘዝ እያደረኩ እንጨዋወታለን።

 

እነዚህ ‘ልክፍተኛ’  ኢትዮጵያዊያን መለያ ባህሪ አላቸው። ይህ ባህሪያቸው ኢትዮጵያ ሐገራቸውን የሃይማኖቶች መፍለቂያ፣ የስልጣኔ መጀመሪያ በማድረግ የተለያዩ ማስረጃዎቻቸውን ይዘው የሚቀርቡ ናቸው። ለምሳሌ እየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል፣ ወንጌልንም አስተምሯል ይላሉ። ቅድስት ድንግል ማርያምም ኢትዮጵያ ውስጥ ከመኖሯም በላይ ኢትዮጵያዊ ደም አላት ብለው የፃፉም አሉ።

 

አንዳንዶች ደግሞ እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ኢትዮጵያዊያኖች ወደ እየሩሳሌም ሔደው ለክብሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ ገፀ- በረከት አቅርበው መጥተዋል እያሉ በመፃፍ ኢትዮጵያን ገና ከእየሱስ መወለድ ጋር የሚያዛምዱበት አፃፃፍ አላቸው።

 

በዚህ ረገድ የሚጠቀሰው በዘመነ የአክሱም ስልጣኔ ውስጥ ከሚነሱት ነገሥታት መካከል ንጉሥ ባዜን ነው። ንጉሥ ባዜን እየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያን ለስምንት ዓመታት መርቷል። ከዚያም በሥልጣኑ ላይ እያለ እየሱስ ክርስቶስ ተወለደ። ባዜንም ከአክሱም ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ። የአለም ጌታ በመወለዱ የተሰማውን ደስታ ገፀ-በረከት በማቅረብ እጅ ነሳ። ባዜን እየሱስን ገና በአራስነቱ ያየ የኢትዮጵያ መሪ ነው። ንጉሥ ባዜን ወደ ሐገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለስምንት ዓመት ንጉሥ ሆኗል። ይሄን ታሪክ አክሱም ከተማ ውስጥ በስፋት ትሰሙታላችሁ። የአክሱምን ታሪክ የፃፉ ደራሲዎችም ደጋግመው የሚገልፁት ነው።

 

ታዲያ እዚህ ላይ ቆም ብለን የምንጠይቃቸውና የምናነሳሳቸው ሀሳቦች አሉ። አንደኛው ንጉሥ ባዜን እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ከመጣ፣ የክርስትና ታሪካችን ይቀየራል ማለት ነው። ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚባለው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢዛና እና በሳይዛና ዘመነ መንግስት ነው የሚለው አባባል ቀርቶ ወደ ኋላ እንድንመለስና እንድናስብ ያደርገናል። ባዜን ንጉሥ ነው። ይህ ንጉሥ የፈጣሪውን መወለድ ሔዶ አይቶ ተመልሶ ሲነግስ፣ የሚያምነው እምነት ክርስትና ነው። ስለዚህ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ነው ብሎ መናገር የሚያስችል ክፍተት ይፈጥራል።

 

አጥባቂ ፀሐፊዎቻችን በኢትዮጵያ ፍቅር የወደቁ ናቸው። ኢትዮጵያን የሁሉም ነገር መጀመሪያ አድርገው የማየትና የማሳየት አፃፃፍ አላቸው። ለምሳሌ በሃይማኖቱ ዙሪያ ብንሔድ እየሱስ ክርስቶስ ተሰዶ ወደ ግብፅ እንዲሄድ እንደተነገረው የሚገልፅ አንቀፅ አለ። ይህ አንቀፅ እንዲህ ይላል፡-

 

“እነርሱም ከሔዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳ። ህፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው” ማቴ.ምዕ3፣13

 

ይህን ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ መሰረት አድርገው የሚነሱ የኢትዮጵያ ፀሐፊያን እየሱስ ወደ ግብፅ ብቻ ሳይሆን የሄደው ወደ ኢትዮጵያም መጥቷል፤ ኖሯል ይላሉ። መነሻቸው ያውመፅሀፍ ቅዱስ ይሆንና ከኢትዮጵያም የተፃፉትን ሰነዶች እየዘረዘሩ ያስረዳሉ። ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፈ መዝሙር ምዕራፍ 68 ቁጥር 31 ላይ ያለውን ይጠቅሳሉ፡-

 

“የሰላም መልዕክተኞች ከግብፅ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያም ፈጥና እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”

 

ይህን ጥቅስ ወስደው ደራሲ አማረ አፈለ ብሻው “ኢትዮጵያ! የሰው ዘር የተገኘባት የእምነትና የሥልጣኔ ምንጭ ናት!” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ያብራራሉ። እንደ እርሳቸው አባባል እየሱስ የሰላም አባት ነው። ኢትዮጵያም ብትሆን ለሰላም እጆቿን የዘረጋች ናት። ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያውያኖች ፈጣሪ በተወለደ ጊዜ ተደስተው እጅ መንሻ ያቀረቡ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ እየሱስ በሽሽቱ ጊዜ ኢትዮጵያ መጥቷል ይላሉ ፀሀፊው።

 

የገድላት ጸሐፊዎችም ቢሆኑ ከአማረ አፈለ ብሻው ተመሳሳይ የሆኑ ፅሁፎችን ያበረክታሉ። ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከማርያም ከዮሴፍና ከመግደላዊት ማርያም ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መኖቸውን ደጋግመው ፅፈዋል። ለምሳሌ አያሌ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በኪሳቸውና በትራሳቸው ስር የሚያኖሯት ሰኔ ጎልጎታ የምትሰኘዋ አነስተኛ መፅሀፍ ናት። እዚህች መፃፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ነገሮች ውስጥ የሚከተለው አለ፡-

 

“ሄሮድስ በምቀኝነት ሊገድልህ በፈለገ ጊዜ አንተን በጀርባዬ አዝዬ አራት ዓመት ከአንዱ አገር ወደ አንዱ ተሰድጃለሁና አቤቱ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፀሎቴንና ልመናዬን ስማኝ”

ይላል። ይህን አንቀፅ የሚያብራሩ የእምነት ሰዎች “እመቤታችን ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ያለችው በመጀመሪያ ከእስራኤል ወደ ግብፅ፣ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የሚያመለክት ታሪክ ነው” ይላል።

 

የኢትዮጵያ ፀሐፊዎች በተለይም በእምነቱ ዙሪያ ያሉት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለመግለፅ አያሌ ማስረጃዎችን ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ እምነት ውስጥ ‘ማርያም’ ከፍተኛ የሆነ ቦታ አላት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትም ከመገለጫዎቿ ውስጥ ዋነኛው ለቅድስት ድንግል ማርያም የምትሰጠው ቦታና ክብር ነው። ይህ በማርያም ፍቅር መውደቅ በእጅጉ ተስፋፋ ተብሎ የሚታሰበውም አንድ ንጉሥ የሆነ ደራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ ካለበት ዘመን ጀምሮ ነው። ይህ ንጉስ አፄ ዘርአያቆብ ይባላል። የ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገናና ንጉሥ እና ደራሲ ነው። በርካታ መፃህፍትን ፅፏል። ከነዚያ ውስጥ አንዷ ተአምረ ማርያም ናት።

 

አፄ ዘርአያዕቆብ ተአምረ ማርያምን ሲፅፍ በልዩ ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ የማርያምና የልጇ የእየሱስ ስም የተፃፈው በወርቅ ነው። የእነሱ ስም ወርቅ ቀልጦ በወርቅ ቀለም እየተነከረ የተፃፈ ነው። በዚህ ብቻም አያበቃም። አፄ ዘርአያዕቆብ ለማርያም ያላቸውን ፍቅር ለመግለፅ የአይኑን የእንባ ፍሳሽም ከወርቁ ጋር እየተላቆጠ ተአምረ ማርያም ተፅፏል። እናም በኢትዮጵያ ንጉሥ እንዲህ አይነት ፍቅርና ከበሬታ የተሰጣት ማርያም በኢትዮጵያዊያኖች ዘንድም በእጅጉ ሰርፃ ገብታ የኑሯቸው መሰረት ሆናለች።

 

ማርያም በኦርቶዶክሶች ውስጥ በጣሙን በቅርበትና ሲበዛም የቤተሰብ አባልነት ድረስ ያህል አብራ በውስጣቸው የመኖርን ያህል የምትጠቀስ ነች። የዚህ ፍቅር እያየለ መምጣት ይመስላል። ማርያም በኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ የእምነት ደረጃ ላይ የደረሰችው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖራለች የሚባለው አፃፃፍም የበለጠ ቅርበቷን አጠንክሮታል። ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያዊ ደም አላት እያሉ የፃፉ ደራሲዎችም አሉ።

 

የጎንደርና የጐጃም ግዛት እንደሆነ የሚነገርለት የጣና ሐይቅ አለ። በዚህ ሐይቅ ውስጥ አያሌ ደሴቶ፤ አሉ። እነዚህ ደሴቶች የእምነት ስፍራዎች ናቸው። ለምሳሌ ጽላተ  ሙሴ ከእየሩሳሌም የዛሬ ሶስት ሺ አመት ሲመጣ መጀመሪያ ያረፈው በጣና ሐይቅ ውስጥ ባሉት ደሴቶች ውስጥ እንደሆነ ይነገራል። ዛሬም ቢሆን እጅግ የከበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐይማኖት ቅርሶችና ታሪኮች የሚገኙበት ውብ ስፍራ ነው። የኢትዮጵያ ፀሐፊዎች ማርያም፣ ልጇ እየሱስ፣ ዮሴፍና መግደላዊት ማርያም በነዚህ የጣና ደሴቶች ውስጥ እንደኖሩ ፅፈዋል። እኔም በአንድ ወቅት ወደ ጣና በሔድኩበት ወቅት እየሱስ ክርስቶስ ይቀመጥበት የነበረበትን ቦታ፣ ይውልበት የነበረበትን ስፍራ ወዘተ ቀሳውስቱ አሳይተውኛል። ይህ ታሪክ ከየት መጣ? ፈጠራ ነው? ወይስ እውነት? ወይስ ገና መመርመር ያለበት ሀቅ?ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል። ቦታው የሚስጢር ቦታ ነው!

በኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊ ሰዎች የተደረሰው መልክአ ሚካኤል የተሰኘው ድርሳን በርካታ ነገሮችን በውስጡ ይዟል። ከነዚህ ውስጥ ለዛሬ እንደመነሻ ያደረኩትንም የእምነታችንን ጉዳይ ይገልፃል። እንዲህም ይነበባል፡-

 

“አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከድንግል ማርያም ተወልደህ ሄሮድስ ሊገድልህ በፈለገ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተሰደህ በጣና ደሴት ለአራት አመት ስትኖር ኢትዮጵያን ባርከህ በጎንህ የፈሰሰውን ደምና ውሃ በሊቀ መልአኩ በቅዱስ ዑራኤል አማካይነት በሐገሪቷ ላይ እረጭተህ፣ ተራሮቿን ባርከህ ወንዞቿን ቀድሰህ፣ የእህል በረከት ይውረድላት፣ ወተትና ማር የሚፈስስባት አገር ትሁን ብለህ ኢትዮጵያን ለናትህ ለማርያም አስራት አድርጌ ሰጠሁሽ ስትል ቃል ኪዳን የገባህላትን አስበህ በደላችንን ይቅር ብለህ ከረሀብ ከበሽታ ከጦርነት አድነህ ሰላምና ፍቅርን አንድነትን እንድትሰጠን እንለምንሀለን” በማለት የመልከአ ሚካኤል ድርሳን ፀሐፊዎች ይገልፃሉ።

 

የእነዚህ ፅሁፎች አዘጋጆች በሐገራችን ሥነጥሑፍ ውስጥ እምብዛም አይጠቀሱም። ነገር ግን ከእምነት ባሻገር ያለው የአፃፃፍ ቋንቋቸው የታሪክ ትረካቸውና ስዕላዊ ገለፃቸው ልዩ ውበት አለው።

ለምሳሌ ድርሳን ዑራኤል የሚባል የቤተ-ክርስትያን መጽሀፍ አለ። ይህን መጽሐፍ በደንብ እንድናነበው ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ድርሳኑ ውስጥ የቀረበው ማስረጃ ወይም ታሪኩ ነው። ድርሳኑ ምን እንደሆነ በሚከተለው ውብ ቋንቋ ይተርከዋል፡-

 

      “ይህ ድርሳነ ዑራኤል እመቤታችን ድንግል ማርያም ለኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታዋና ህዝቦቿን የነገሥታቷም የቅርብ ረዳት የሆነ ለቅዱስ ዑራኤል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ሀብተ ረድኤትና የገቢረ ተአምራት ጸጋ ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እየነገረች ከጻፈ በኋላ ከጌታ እየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል ጋር የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ መካነ መቃብር በሆነው በደብረ ጎልጎታ አስቀምጦት ሲኖር የብሐንሳው ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስ፤ በኢየሩሳሌም ጉብኝቱ ጊዜ የእየሩሳሌም ቤተ-መፃሕፍት ወመዘክር ጠባቂ ከአባ ቦኮኮ ዘንድ አግኝቶ በደቀ መዝሙሩ በአባ ጌዲዮን ፅርዕ፣ ቋንቋ ወደ ግዕዝ አስተርጉሞ በቅዱሳቱ በኢትዮጵያ ነገሥታት በአብርሓ ወአፅብሐ፤ ዘመነ መንግስት ለኢትዮጵያዊው ማለት ለአክሱሙ ሊቀ ካህናት ለእንቦረም በክብር የአስረከበው የድርሳን መፅሀፍ ነው” በማለት አዘጋጆቹ መግለጫ ይሰጣሉ።

 

 ይህ አፃፃፍ በውስጡ ያለው አባባልና ገለፃ በራሱ ሰፊ ነው። አያሌ ጉዳዮችን ያነሳል። በተለይ የማርያምን እና የኢትዮጵያን ወዳጅነት የበለጠ ያጎላዋል። ድርሳኑን እርሷ እንደፃፈችው ይገልፃል። ወደ ድርሳኑ ውስጥ ስንገባ ደግሞ አያሌ አስገራሚ ነገሮችን እናገኛለን።

 

      “እናቴ ሆይ! በዚህች በምባርካት አገር በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎች እስከ አለም መጨረሻ ድረስ አስራት ይሆኑልሽ ዘንድ ሰጥቼሻለሁ። እናቴ ሆይ! አሁንም ወደዚያ አገር እንሂድ ዘንድ ተነሺ፤ ደሴቶችዋ የተቀደሱ ፣ ወንዞችዋ ያማሩ፣ ውሃዎቿ የጠሩ፣ ዛፎችዋና ተራራዎችዋ የተዋቡ ናቸውና አሳይሻለሁ አለኝ” (ገፅ 17-18)

 

እነ ማርያም፣ እነ እየሱስ እነ ዮሴፍና መግደላዊት ማርያም ኢትዮጵያ መጥተው ምን አዩ? ምን አሉ? ድርሳኖቹ ምን ይላሉ? ብዙ ታሪኮች አሉ። እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ ገና ብዙ እንጨዋወታለን።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15976 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 923 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us