የሴት ጭንቅላት የሚያበቅለው ዘንፋላ ፀጉርን ብቻ ነውን?

Wednesday, 30 August 2017 12:37

 

በጌጥዬ ያለው

‹የሴት ብልሀት፤ የጉንዳን ጉልበት ይስጥህ!› ይላሉ የድሮ አባቶች የሚወዱትን ሰው ሲመርቁ። የዘንድሮ አባቶች ምናልባት ‹የጎግል ዕውቀት፤ የግሬደር ጉልበት ይስጥህ!› ብንል ነው።  እርስዎ ተመራቂውን ቢሆኑ የትኛውን ይመርጣሉ? በዘንድሮ አባቶች መመረቅ ወይስ በድሮ አባቶች? ሴት ጭንቅ፤ ጥብብ ያለ ጊዜ መውጫ ቀዳዳ ሲፈለግ ብልሀት አታጣም። ‹የሴትን መላ አይጥ አይቆርጠውም› ሁሉ ይባላል ጎበዝ ብልሀተኛነቷን ለመግለፅ ሲፈለግ። ታድያ ይሄ ብልሀተኝነቷ እንደ ጎግል ከየቦታው ለቃቅማ ለችግር ቀን የሰበሰበቺው ሳይሆን በተፈጥሯዋ የታደለቺው ነው። ምንጩ ሁልጊዜም ከውስጧ ነው። አይነጥፍም። ጉንዳን ከነፍሳትነቱ አንፃር ሲለካ እጅግ ጉልበተኛ ነው። ይህ የጓደኛውን ሬሳ መሸከም በመቻሉ ተረጋግጧል። ሰዎች ሰው ሲሞትብን አንድን ሬሳ የምንሸከመው ቢያንስ አራት ሰዎች ሆነን ነው። ጉንዳኖች ግን ለየብቻቸው በቂ ናቸው።

ታድያ ይሄ ጉልበታማ አያሰኛቸውም? ስለሴት እንጂ ስለጉንዳን ማውራት የዚህ ፅሁፍ አላማ ስላልሆነ የጉንዳኑን ጉዳይ በዚህ አልፈዋለሁ። ዞሮ ዞሮ እንስቶች የምጡቅ አእምሮ ባለፀጎች መሆናቸውን አባባሉ ያሳብቃል። ሆኖም በአብዛኛው ሴቶች ማዳመቂያዎች፣ ውበቶች፣ ጌጣጌጦች እንጂ ምሁራን ተደርገው ሲታሰቡ አይስተዋልም። በየመድረኩ የዝግጅት ማዳመቂያ፣ በየማስታወቂያዎች የምርትና አገልግሎት ማሻሻጫ፣ በየመጠጥ ቤቶች የወንዶች መዝናኛ ሲሆኑ ይስተዋላል። ሴት ልጅ ከወንዶች ይበልጥ ምቾት አዳኝ ተደርጋም ትታሰባለች። ብዙ ሴቶች ጠረጴዛቸው ላይ ውሃን ጨምሮ የምቾት መጠበቂያ ቁሳቁሶች አይለዩዋቸውም። ተረከዙ ረዥም ጫማ በመጫማት፣ አጭር ቀሚስ በመልበስ፣ ሰውነትን የሚያጋልጡ ሌሎች ልብሶችን በመልበስ እና ፀጉርን፣ ጥፍርን፣ ፊትን. . . በተለያየ ፋሽን በመዋብ የምቾትን ጫፍ መንካት ነፍሳቸው ነው። በየሕንፃው ተንጠላጥሎ፣ አቀበት ወጥቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ መሀንዲስ መሆን ደግሞ እርማቸው ነው። በተለይ በግንባታ አካባቢዎች መሰንበት ቀርቶ አንድ ቀን ማደር አይሆንላቸውም። ቢሮዎች አካባቢ በተረከዘ ሹል ጫማቸው ቆብ! ቀሽ፤ ቆብ! ቀሽ ማለት ግን እድሜያቸውን በአንድ አራተኛ የሚጨምርላቸው ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የአብዛኞቹ ሴቶች ባሕሪ ቢሆንም በምህድስና ቀርቶ በውትድርናም በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ድሎት ለምኔ ያሉ ኢትዮጵያዊ ሴቶች መኖራቸውም እሙን ነው። ዝግጅት ክፍላችን ከአብዛኞቹ ሴቶች ከተለየች እንስት መሀንዲስ ጋር በአዲስ አበባ ተደጋጋሚ ቆይታዎችን አድርጓል።

መንገድ ወደ ምሕንድስና

በእናቷ ኢራናዊት፤ በአባቷ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ነች። የተወለደቺው ጆርዳን፤ ከሶስት ወራት የጨቅላነት ዕድሜዋ ጀምሮ ያደገቺው ደግሞ ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ። አባቷ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሠሩ ሥለነበር በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመዘዋወር የሚያበቃ የነፃ ትኬት እድለኛ ነበረች። በዚህም ልዩ ልዩ ሀገራትን ጎበኘች። በአስደናቂ የምህንድስና ውጤቶች ላይ ተንሸራሸረቺባቸው። ስለምህንድስና ለማወቅ በር ከፈተላት። ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በቦሌ የሕብረተሰብ ትምህርት ቤት፤ ቀጥሎ ደግሞ በታዋቂው ናዝሬት ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተማረች። ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትንም ተቀላቀለች። ከአምስት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ በሲቪል ምህንድስና ከተመረቁ የዩኒቨርሲቲው ሶስት ሴት ተማሪዎች መካከል ሶፊያ አንዷ ነበረች።

 

 

የሐበሻዊቷ ምሕንድስና ፈረንጅ በሰለጠነባት ናሚቢያ

አፍሪካዊቷ ናሚቢያ በጀርመኖች ቀኝ ግዛት ሥር ነበረች። በዚህ የበሸቁት ደቡብ አፍሪካውያን ከጀርመን ጫማ ሥር ፈልቅቀው ሊያወጧት፤ ጀርመኖችን ሊያባርሩ ጦራቸውን መዝዘው ወደ ሀገሪቷ ገቡ። ሲያዩ ጎረቤታቸው ናሚቢያ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ነች። ጀርመኖችን የማበረር ወኔያቸው ይበልጥ ጨመረ። ስሜታቸው ገነፈለ። ዳግም እንዳይመለሱ አድርገውም በደማቸው ጠበል ረጭተው ሸኟቻው። ታድያ በሀገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ጥረው ግረው የሚኖሩ በርካታ ነጮም ነበሩ። አሁንም አሉ። ሀገሪቱ ሰላም ሆነች። በመጠኑም ቢሆን እኩልነት ሰፈነ። በናሚቢያ ውስጥ ባዩት አልማዝ እና ዩራኒየም የጎመጁት ደቡብ አፍሪካውያን ግን በዚያው ቀሩ። ናሚቢያ ከጀርመን ጫማ ሥር ብትጣም ደቡብ አፍሪካ እንደገና በቦቲ ጫማዋ ውስጥ በካልሲ አፍና አስገባቻት። ናሚቢያ ከዓመታት በኋላ ቦቲ ጫማውን ቀድዳ ወጣች።

 

 

በዚህ ወቅት የኢንጂነር ሶፊያ ወላጅ አባት የሥራ ጉዳይ በናሚቢያ እንዲኖሩ ጋበዛቸው። ሶፊያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሠራቺውን የዲግሪ ወረቀት ይዛ የናሚቢያን መሥሪያ ቤቶች ‹ቅጠሩኝ አብረን እንሥራ› አለች። በወቅቱ በሀገሪቱ የተማረ ሰው፤ ያውም የዲግሪ ባለማዕረግ ማግኘት ብርቅ ነው። የሀገሬው ሰዎች አልተማሩም ነበር። የቀለም ትምህርት በቀጥታ የሚያስፈልጋቸውን መሥሪያ ቤቶች ሁሉ የተቆጣጠሯቸው ፈረንጆች ነበሩ። ‹ሶፊያ በለጠ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ኢትዮጵያ› የሚል ፅሁፍ የሰፈረበት የሲቪል ምሕንድስና ዲግሪ የሐበሻዊት ሴት ፎቶ ግራፍ ተለጥፎበት በአንድ የናሚቢያ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ሲገኝ አጠራጣሪ ሆነ። ‹ኢትዮጵያ ማን ነች? የምን ዲግሪ ነው?› ተባለ።

ከዳይሬክተርነት ደረጃ ጀምሮ ወደ ታች መሥሪያ ቤቱን የተቆጣጠሩት ፈረንጆች ለጎሪጥ አይተው ዝም አላሉም። የሶፊያን የዲግሪ ወረቀት ለተጨማሪ ምርመራ ወደ እንግሊዝ ላኩት። ሶፊያ ከዚህ ምርመራ በኋላ ከሀገሪቱ የሥራና ትራንስፖርት ሚንስቴር ጋር የቅጥር ውል ተዋዋለች። በቃ! በሥራና ትራንስፖርት ሚንስቴር ውስጥ በረዳት መሀንዲስነት የሙያ መደብ በቋሚነት ተቀጠረች። ነገር ግን መሥሪያ ቤቱ አስደሳችና ሰላማዊ አልነበረም። የበላይነት እና የበታችነት ስሜቶች ወረውታል። ባለሙያዎች በሙያ ብቃታቸው፣ ልምዳቸው እና ክህሎታቸው ሳይሆን በዘራቸው፣ በቀለማቸው እና በፆታቸው ከፍ እና ዝቅ ብለውበታል። ይህ ሂደት ኢንጂነር ሶፊያ ላይ በሁለት መልኩ ዥልጥ ብትሩን ጣለባት። በምሕንድስና እውቀቷ ከሌሎች ብትልቅ እንጂ የማታንሰዋ ሶፊያ በነጭ የቅርብ አለቆቿ እና ባልደረቦቿ ዘንድ በሴትነቷ እና በሐበሻዊ ቀለሟ ምክንያት ዝቅ ተደረገች። አለቆቿ ከንቀታቸው የተነሳ ጥቃቅን ሥራዎችን ነበር የሚያዝዟት። ከተላላኪነት ፈቅ ያላለ ሥራ ያሠሯታል። የሥራ ቀኑን ሙሉ መረጃዎችን ወደ መረጃ ቋት ስታስገባ ትውላለች። ምክንያቱም አፍሪካዊት በዚያ ላይ ሴት ስለሆነች በአለቆቿ ዘንድ ለሌላ የምሕንድስና ሥራ አትመጥንም ተብሎ ይታሰባል።

 

 

በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ወረቀት ላይ በሰፈረው የሙያ እርከን እንኳን ከእርሷ በታች ለሆኑ ነጭ ሰራተኞች የተሻለ እድልና ትኩረት መሰጠቱ ነው። ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ በዚህ ሁኔታ ልቧ እየበገነ፣ ደሟ እየገነፈለ፣ መላ ሰውነቷ በንዴት ርር ቅጥል እያለ ለስድስት ወራት ያህል ታገሰች። ከዚህ በኋላ ግን ፈረንጁ አለቃዋን አቤቱታና ወቀሴታ ልታሸክመው ተዘጋጀች። የኃሳቧ መንደርደሪያም አጭር ጥያቄ ነበር። ‹‹አለቃዬ ሆይ በሥርህ ላለን ሠራተኞች ቢሮ ስትመድብ መሥፈርትህ ምንድን ነው?›› አለቺው። ተከታዩን ጥያቄ ያላወቀው አለቃ ‹‹በሙያችሁ የደረጃ እርከን ነው የምለካው።›› ሲል መለሰ። ‹‹ታድያ ከእኔ የደረጃ ርከን በታች ላለ ፈረንጅ የቴክኒክ ባለሙያ ምን የመሰለ ቆንጆ ቢሮ ሰጥተህ፤ የደረጃ ርከኔ ከቴክኒክ ባለሙያው በላይ ለተፃፈው ረዳት መሀንዲሷ ከቤተ ሙከራ ክፍል አጠገብ የተወሸቀ፤ ከከብቶች በረት እምብዛም ያልተሻለ ቢሮ መሥጠትህ ለምን ይሆን?›› ተባለ።

ፈረንጁ አለቃ ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ አላገኘም። ደነገጠ። የድፍረት አጠያየቋ ገረመው። ስሜቱ ተዘበራረቀ። ይህ ፈረንጅ ምናልባትም ‹አፍሪካውያን በዛፍ ጥላ ሥር ነው ያደጉት› የሚል በአውሮፓውያን ታሪክ ነጋሪዎች የተንሸዋረረ ተረታተረት ሰምቶ ይሆናል። ሳይቸግረው ከበረት የሚመሳሰል ቢሮ መስጠቱ ሶፊያ ከአክሱም፣ ከላሊበላ እና ከጎንደር አስደናቂ የግንባታ ባለታሪክ ሕብረተሰብ ውስጥ መፍለቋን አለማወቁ ይሆናል። የድፍረት አጠያየቋ ግን ፈረንጆች ከሚሠሩበት የሚመሳሰል ቢሮ እንዲሰጣት አስገደደው። ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ ደግሞ ከአዲሱ ቢሮዋ ገብታም ዝም አላለቺም። አሁንም የእኩልነት ጥያቄ አነሳች። ከሙያ ችሎታዋ ጋር የሚመጣጠን ሥራ እንዲሰጣት ጠየቀች። አፍ አውጥታ ‹‹ጎበዝ መሀንዲስ ነኝ። ለአብዛኞቹ ነጭ መሀንዲሶች ቶሎ ቶሎ የምታደርገውን የሙያ እርከን ማሻሻያ እኔም ላይ አድርገው እንጂ፤ ምን ነካህ!›› አለች።

 

 

አቶ አለቃ እዚ ላይ ጥሩ ምላሽ አልሰጠም። ሶፊያም በዚህ አልተበገረቺም። ጥያቄዋን ይዛ ወደ አለቃዋ አለቃ አመራች። ‹‹አምስት ዓመት ሙሉ በአነስተኛ ደሞዝ በረዳት መሀንዲስነት አገለገልኩ። በሙያ እርከን ከእኔ በታች ያሉ ነጭ ባልደረቦች የሙያ የደረጃ እድገት ሲያገኙ እኔ ግን ነጭ ስላልሆንኩ ባለሁበት አለሁ። የምንለካው ምንሕንድስናን በተሸከምንበት የአእምሮ ስፋታችን ልክ ነው ወይስ በቆዳ ቀለማችን? ወይስ በፆታች?›› አለች። የአለቃዋ አለቃ ጥቁር ነው። እየመራሁት ነው በሚለው መሥሪያ ቤቱ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሸፍጥ ሲሰራ አለማወቁ ገረመው። ለምን ቶሎ አልነገርሽኝም ነበር ሲል ተበሳጨ። ወድያኑ የኢንጂነር ሶፊያን አለቃ ወደ ቢሮው አስጠራው። አጭር ጥያቄ እና መልስ ተደረገ። ‹‹ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ ሥራዋን በአግባቡ እየሠራች ነው ወይ?›› አለው።

‹‹አዎ በትክክል እየሠራች ነው።›› አለ። ‹‹ልታሻሽላቸው የሚገቧት ጉዳዮች አሉ ወይ?›› ‹‹አይ የለም።›› ‹‹ታድያ ለሌሎች የደረጃ ዕድገት ስትሰጥ ለእርሷስ ለምን አልሰጠኃትም?›› አለው። አቶ አለቃ ቢቸግረው፤ የሚመልሰው ቢያጣ ‹‹አይ ወጣት ስለሆነች ባለችበት ትንሽ እንድትሠራ ጥሩ ይሆናል ብዬ ነው።›› ብሎ ተገላገለ። በሁኔታው የበሸቀው የበላይ አለቃ ግን ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ቺፍ ኢንጂነር አድርጌያታለሁ›› ሲል ትዕዛዝ አስተላለፈ። ከዚያም ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ ሥራዋን እየቀጠለች ቀስ በቀስ ዛሬ በናሚቢያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ አስተዳድር ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ለመሆን በቃች። አሁንም የምትሠራው በዚሁ መሥሪያ ቤት፤ በዚሁ የሥራ ሓለፊነት ላይ ነው።

ሙስናን የመዋጋት ፍዳ

ውድ አንባቢያን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ጉዳይ ራሷ ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ ትተርክልናለች። በሕይዎቷ ውስጥ ያጋጠማትን እያጋጠማት ያለውን እውነተኛ ታሪክ በሚጣፍጥ ሀቀኛ አተራረኳ ታጫውተናለች። ከእኔ ጋር በታሪኩ የመጨረሻ ክፍል እንገናኛለን። 

 

 

. . . ይኸውልህ፤ በአንድ ወቅት የሀገሪቱ በጀት በየዘርፉ ተከፋፍሎ ሲመደብ የመንገድ ወጭ ጥናቶችም ይሠሩ ነበር። ጥገና የሚያስፈልጋቸውን መንገዶች የጉዳት መጠን እና ለመጠገን የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን አጥንቼ አቀረብኩ። ምን ያህል መንገዶች ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ። ምን ያህሉ አደጋ ላይ እንደሆኑ። ካላቸው ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ብሎም የጉዳት መጠን አንፃር የትኞቹ መንገዶች ቅድሚያ መጠገን እንዳለባቸው የናሚቢያ መንገዶችን አጥንቼ የጥናቱን ዝርዝር ጉዳይ በአግባቡ ጠርዤ ለአለቃየ ሰጠሁት። ይሄ ጥራዝ አስራ አንድ አመታት የደከምኩበት ቢሆንም ተጠናቆ ከገባ በኋላ ግን ወደ ተግባር ሳይገባ የአለቃየ ጠረንጴዛ ላይ ቁጭ ብሎ መንፈቅ ሞላው። ከዚያም ለምን ብየ ጠየቅሁ። አለቃየም ‹‹የአንቺ ጥናት ለአንድ መንገድ ጥገና  60 (ስልሳ) ሚሊዮን የናሚቢያ ዶላር ማውጣት አለብን ይላል። ኮንትራቱ ግን የወጣው 240 (ሁለት መቶ አርባ) ሚሊዮን ተብሎ ነው።

 

 

ስለዚህ ያቀረብሺውን ጥናት ተግባራዊ ማድረግ አልችልም።›› አለኝ። ስልሳ ሚሊዮን እንደሚበቃው ማስረጃዎችን እያቀረብኩ ላረጋግጥለት ሞከርኩ። በመጨረሻም ሀቁ እየገባው አልቀበልሽ ሲለኝ ያዘጋጀሁት ሰነድ አንድም ችግር እንደሌለበት ገባኝ። ይልቁንም እርሱና አንዳንድ ባልደረቦቹ ተደራጅተው ሙስና እየሠሩ እንደሆነ ገባኝ። ከሥራ ተቋራጩ ጋር ተመሳጥረው፤ ‹በአንተና በእኛ ይቅር እንጂ› ተባብለው መንገዱን ለመጠገን የሚያስፈልገው ስልሳ ሚሊዮን የናሚቢያ ዶላር ሳለ ሁለት መቶ አርባ የናሚቢያ ዶላር በማድረግ ሰነዱን ከተፈራረሙ በኋላ ቀሪውን መቶ ሰማንያ ሚሊዮን የናሚቢያ ዶላር ለየግል ኪሳቸው ሊከፋፈሉት እንደሆነ ከሁኔታቸው በግልፅ ተረዳሁ።

 

 

ከዚያም ቀጥታ ገንዘብ ወደ ሚመድበው የሀገሪቱ መንገዶች ፈንድ ፅህፈት ቤት አመራሁ። ጉዳዩን ነገርኳቸው። የፅህፈት ቤቱ የቦርድ አባላት የጥናት ወረቀቱን እንዳቀርብላቸው ጋበዙኝ። ለሁለት ሰዓታት ያህል አፍታትቼ አብራራሁላቸው። ሰዎቹ የሕዝብ ገንዘብ እየዘረፉ እንደሆነ አሳየኋቸው። ቀጥሎ ከገንዘብ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ጉዳዩን እንዳስረዳ ተጠራሁ። ለገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትሩ አብራራሁለት። ሰነዶችን ዘርግፌ አሳየሁት። ሚንስትሩ ለመንገዶች ፈንድ ፅህፈት ቤት ደብዳቤ ፃፈ። ለካ እኔ ሳይገባኝ ሚንስትሩ እና አንዳንድ የመንገዶች ፈንድ ፅህፈት ቤት የቦርድ አባላት ከአለቃየ ጋር ተደራጅተው ሙስና ይሠሩ ኖሯል። ለካስ እሳት ላይ ተዘፍርቄ ነው እሳትን ሳማ የቆየሁት።

 

 

የገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትሩ ዘርግፌ የሰጠሁትን ሰነዶች ጥርቅምቅም አድርጎ እንዲያሸሻቸው ለአለቃዬ መልሶ ሰጠው። አለቃዬ ደግሞ ተጫወተብኛ! ተባብረው ፍዳየን አበሉኝ። በነገር ማዕበል ታምሜ ሁለት ጊዜ ሆስፒታል ገባሁ። ቤተሰቤ ተረበሸ። ሰበብ ፈልገው የስነ ምግባር ጉድለት አለባት ብለው ከሥራ ገበታየ ሊያሰናብቱኝ ነገር ፈተሉ። ሴራ ጎነጎኑ። ሸረቡ። አንዷን ሀቅ በሺህ ቅጥፈቶች ተበተቧት። የሥራ ማሰናበቻ ደብዳቤ ሊሰጡኝ ተዘሰናድተው ቀጣዩን ማለዳ እየጠበቁ እያለ ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ የቤቴ በር ተንኳኳ። እኔ ደግሞ አለቃየና አጋሮቹ ሊያጠቁኝ እቤ ይመጡ ይሆናል ብዬ ፈርቻለሁ።

 

ከባለቤቴ ጋር ወጥተን በሩን ስንከፍት ‹‹ከፕሬዚደንት ሳምኔውማ ቢሮ ነው የመጣሁት›› የተረጋጋ ሰውየ በተረጋጋ መንፈስ በፕሬዚደንት ፅህፈት ቤት ውስጥ የምጣኔ ኃብት ዘርፍ ሓላፊ መሆኑን የሚገልፅ መታወቂያ አያሳየኝ መሰለህ! ‹‹ፕሬዚደንቱ ጉዳይሽን ሰምተው ሂድና መርምር ብለውኝ ነው።›› ሲለኝ በል ና ግባ አልኩና ስሰበስባቸው የኖርኩትን ሰነዶች ሁሉ ወክውኬ አስነበብኩት። ኮንትራት ሲፈራረሙ፣ ዋጋ ያለአግባብ ሲያገዥፉ . . .  እየቀዳሁ የሰበሰብኳቸውን  ሰነዶች ሁሉ ሲያነብ በጣም ገረመው። 

 

 

ከዚያም ‹‹ፕሬዚዳንቱ ሊያዩሽ ይፈልጋሉ።›› አለኝ። መታወቂያውን ሳይ ያመንኩትን ሰውየ አሁን ጠረጠርኩት። ይሄ ነገር እውነት ነው ወይስ ሊጠልፉኝ ፈልገው ነው ብዬ እየተጨነቅሁ የሚሆነውን ለማየት እሺ አልኩ። በማለዳ የሥራ ማሰናበቻ ደብዳቤ ተዘጋጅቶ መሥሪያ ቤቴ ውስጥ እየጠበቀኝ፤ አለቃየ የእኔን በበሩ ማለፍ እየተጠባበቀ ሳለ እኔ በባለሥልጣን መኪና ከሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጋር ልተዋወቅ ወደ ቤተ መንግስት ሄድኩ። በአጋጣሚ እኛ ስንደርስ ፕሬዚደንቱ የእርሻ ማሳቸውን ሊጎበኙ ወጥተው ስለነበር ጠበቅን። ምሳ ሰዓት ላይ ፕሬዚደንቱ መጡ ‹‹የምትነግርህ ጉዳይ አለ ተብየ ነው። ምንድነው የምትነግሪኝ? ለማኛውም ቅድሚያ ግን ምሳ እንብላ።›› አሉ። የምሳ ስነ ስርዓቱ ላይ በክብር ከእሳቸው ጎን እንድቀመጥ አደረጉ። ‹‹ይሄ የእኛ ምግብ ነው። እንጀራ አይደለም። እንደምትወጂው ተስፋ አደርጋለሁ።›› እያሉ እያጫወቱኝ በላን። እንጀራ እንደሚወዱም ነገሩኝ። ከዚያም ወደ እሳቸው ቢሮ ገባንና ጉዳዩን አንጠፍጥፌ አብራራሁላቸው። ሰነዶቹን አሳየኋቸው።

ወድያኑ ከፊቴ ላይ ለሚንስትሩ ስልክ ደወሉ። ሚንስትሩ ግን እየሰማሁት ጉዳዩን አላውቅም ብሎ ዋሸ። በመጨረሻም እንደዚህ ዓይነት የሙስና ጉዳዮችን የሚከታተል ተቋም በፕሬዚደንት ፅህፈት ቤቱ ሥር ተቋቋመ። የእኔ ጉዳይ በየመገናኛ ብዙኃኑ መነጋገሪያ ሆነ። ‹‹ፈርተን ትተነው እንጂ እኛም እናውቅ ነበር። አንቺ ደፋር ስለሆንሽ ነው ይሄን የተጋፈጥሽው›› የሚሉ ሰዎች በረከቱ። ሕዝቡ መንገገድ ላይ ሳይቀር እያቆመ አይዞሽ እያለ ያበረታታኝ ጀመር። ከገንዘብ ሚንስቴር ሚንስትሩ ጀምሮ ወደ ታችኛው የሥልጣን ያሉ ሙሰኞቹ ሁሉ እስከ ቅርብ አለቃየ ድረስ ከሥራቸው ተሰናበቱ። አባላቱ ተሰናብተው የመንገዶች ፈንድ ፅህፈት ቤት ቦርድ ፈረሰ። መሥሪያ ቤቱ ውስጥ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ ተመደበልን። እኔም በሥራ መደቤ ቀጠልኩ።

 

የመንገድ ሀብት አስተዳድር ሥርዓት

የሴት ጭንቅላት የሚያበቅለው ዘንፋላ ፀጉርን ብቻ አለመሆኑን እና አፍሪካውያን ከነጮች እኩል መሆናቸውን ያስመሰከረቺው ኢንጂነር ሶፊያ በለጠ ከላይ የቀረበው ታሪኳን ስታጫውተኝ እንባ እየተናነቃት ነው። የደስታና የሀዘኔታ እንባ እፍን እፍን እያደረጋት ነው። የደረሰባት እንግልት ቢያስከፋትም በድል ስለተወጣቺው ደግሞ ተደስታለች። ፈገግታዋም የመደሰት አይሉት የመከፋት እንደ ሞናሊዛ ፈገግታ ግራ የተጋባው ግን ደግሞ የሚያምር ነበር። ኢንጂነሯ ወይዘሮ ሶፊያ በለጠ ከባልደረቦቿ ጋር በመተባበር የመንገድ ሀብት አስተዳድር ሥርዓት (Road Asset Management System) የተባለ አሠራር ፈጥራለች።

 

 

ይህ አሠራር በየጊዜው እየተሻሻለ ላለፉት 25 ዓመታት በናሚቢያ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን በአሠራሩም ምጣኔ ኃብትን (የመንገድ ምጣኔ ኃብት)፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን እና ራሱን ምሕንድስናን ያማከለ ነው። ኮምፒዩተርን በመጠቀም መረጃ ይሰበስባል። የሰበሰበውን ይተነትናል። የተነተነውን ግልፅ አድርጎ ለሚመለከተው ባለሙያ ወይም የሥራ ሓላፊ ያስተላልፋል። በዚህም የአሠራር ግልፀኝነትን በማስፈን ተናባቢ መረጃን የሚሠጥ ነው ትላለች ኢንጂነሯ።

 

 

እንደ ኢንጂነር ሶፊያ ገለፃ ይሄ የአሠራር ሥርዓት ለየትኛው መንገድ ግንባታ ወይም ጥገና ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገው፣ የትኛው መንገድ ምን ያህል እንደተጎዳ፣ ካለው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ብሎም ከጉዳት መጠኑ አንፃር የትኛው መንገድ መቼ መጠገን እንዳለበት፣ የትኛው መንገድ ምን ዓይነት እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው በአግባቡ ለማወቅ የሚያስችል ነው። ብቁ ሥራ ለመሥራት ትክክለኛ ለኬትን ለማግኘት እና ግልፀኝነትን ለተላበሰ መልካም አስተዳድር ይጠቅማል። አሠራሩ ወደ ኢትዮጵያም እንዲመጣ ኢንጂነር ሶፊያ ከሚመለከታቸው የዘርፉ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመወያየት ላይ ነች።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
15991 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1032 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us