የሰይፉ ፋንታሁን ነገር

Wednesday, 09 April 2014 12:29

ሰይፉ ፋንታሁን

EBS ቴሌቭዥን

ግሩም ኤርሚያስ

ዓለማየሁ ታደሰ

+

ብሮድካስት ባለስልጣን

በድንበሩ ስዩም

ከሰሞኑ ኢ.ቢ.ኤስ ተብሎ በሚታወቀው ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ አንድ ፕሮግራም ተላልፎ ነበር። ፕሮግራሙ የሰይፉ ፋንታሁን ሲሆን፣ በዚህ ፕሮግራም ላይ ደግሞ ሁለት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተጋብዘዋል። እነሱም አያሌ ፊልሞችን በመተወን የሚታወቀው ግሩም ኤርሚያስ እና የቴአትር ባለሙያ የሆነው አለማየሁ ታደሰ ናቸው። ግሩም ኤርሚያስ በዝግጅቱ ላይ ስለ ፊልም ሙያው እና በዚህ ሙያው ውስጥ ስለነበረው ቆይታ የተለያዩ ነገሮችን ተናገረ። በተለይ ደግሞ አንጋፋው አርቲስት አለማየሁ ታደሰ ወደዚህ ሙያ እንዳስገባውና ባለውለታው እንዲሁም እንደ ሞዴል አድርጎት እንደሚቆጥረው ግሩም ኤርሚያስ ተናገረ። ከዚህ በኋላ ደግሞ የገፀ-ባሪውን አይነት እንዴት እንደሚተውን ገለፀ። በተለይ “የተሰጠኝን ገፀ-ባሕሪ መስዬ ሳይሆን የምሰራው፣ ሆኜ ነው” እያለ ግሩም ተናገረ። በዚህ ንግግር ውስጥ አንድ ታላቅ ስህተት ፈፀመ። ስህተቱ ቴሌቭዥን ጣቢያውን ጨምሮ በዚያ ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን ሁሉ የሚያስጠይቅ ነው እየተባለ በመነገር ላይ ይገኛል።

ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ የሚሰጠውን ገፀ-ባሕሪ መስሎ ሳይሆን ሆኖ እንደሚሰራ በምሳሌ አስረዳ። አንድ ጊዜ የተሰጠው ባህሪ ሀሺሽ የሚጠቀም ወጣት ነበር። ታዲያ ይህን ወጣት ሆኖ ለመስራት እውነተኛውን ሀሺሽ ፈልጎ ማጨስ ነበረበት። እናም ያንን ሀሺሽ አስመጥቶ አጨሰ። ከዚያም በዚያ ሀሺሽ ነሆለለ። ቀባዠረ። ራሱን ሳተ። ተዝረከረከ። ግሩም ኤርሚያስ ይህን እውነተኛ ገጠመኙን በይፋ ከመናገሩ ባሻገር ቴሌቭዥን ጣቢያ ደግሞ በሀሺሽ የሰከረበትን እውነተኛ ምስል /Footage/ ለኢትዮጵያ ህዝብ በይፋ አሳየ። በዚያ ዝግጅት ላይ የታደሙት የሰይፉ ፋታሁን እንግዶችም እየሳቁ በደስታ ለግሩም ኤርሚያስ አጨበጨቡለት። ሁሉም በጋራ ሆነው ሀገራዊ ስህተት ፈፀሙ።

እዚህ ላይ ስህተቱ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ስህተቱ ከመምሰል ወደ መሆን እለወጣለሁ የሚለው አስተሳሰብ በራሱ አነጋጋሪ ነው። አንድ ተዋናይ የተሰጠውን ገፀ-ባህሪ ፍፁም ወደ መምሰል ይጠጋል እንጂ እንዴት ፍፁም ወደመሆን ይሄዳል። ይህ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ብዙም አያስኬድም ምክንያቱም ደራሲው ራሱ የፃፈው እውነተኛ ሰው አይደለም። የልቦለድ ሰው ነው። ይህን የልቦለድ ሰው መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም። በአለማችን ላይ የተለያዩ የጦርነት ፊልሞች ይሰራሉ። ታንኮችን፣ መድፎችን፣ አውሮፕላኖችን ወዘተ በጦርነት ውስጥ እናያለን። እነዚያን ጦርነቶች እውነተኛ ጦርነቶች ማድረግ እንችላለን ወይ? ተኩሱ ሁሉ የመምሰል እንጂ የመሆን አይደለም። ብዙ ሰዎች በጦርነት ፊልም ውስጥ ሲሞቱ እናያለን። ያ ሞት እውነተኛ ሞት አይደለም፤ ለመምሰል ሞት ነው! የመሆን ሞት አይደለም። ግሩም ኤርሚያስ ይህን መሰረታዊ አካሄድ ይስትና መሆን ወደሚለው ፍልስፍና ገብቶ ሀሺሹን አጨሰው። ሀሺሹ አጦዘው። ያንን ጡዘት ለህዝብ ሰይፉ አሳየው።

ግሩም ኤርሚያስ አያሌ አድናቂዎች እና ወዳጆች ያሉት ተዋናይ ነው። የእርሱን አርአያ እንከተላለን ብለው ቀን ከሌት የሚዋትቱ ወጣቶች አሉ። እርሱ ታዲያ ለመሆን በሚል ፍልስፍና ሀሺሽ አጨሳለሁ እያለ በአደባባይ ይናገራል፤ ያሳያል። ይህ ማለት የብዙ አድናቂዎቹንና ተከታዮቹን መስመር ማሳቱ አይቀርም። ይህ ጉዳይ ወጣቶችን እንደ መበከል ይቆጠራል ብለው የፃፉበትም አሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አደንዛዥ እፅ መያዝ፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር፣ መሸጥ፣ መለወጥ ብሎም መጠቀም በኢትዮጵያ ህግ በከፍተኛ ደረጃ ያስቀጣል። ግሩም ኤርሚያስ ይህን ሀሺሽ ከየት አመጣው? ማን ነው ያዘዋወረለት? የሚሉት ጉዳዮች በራሳቸው አጠያያቂ ናቸው። በአደባባይ ማጨሱ ደግሞ ሌላው ወንጀል ነው። አንድ ብዙ ፊልሞች ላይ እየተወነ ያለ ታዋቂ ተዋናይ ሀሺሽ ወንጀል መሆኑን ሳያውቅ ተናግሯል ማለት ቢያሳፍርም፣ ነገር ግን በሚሊዮን ሕዝቦች ፊት ትልቅ ወንጀል ተፈፅሟል።

ሌላው አስገራሚ ነገር የአርቲስት አለማየሁ ታደሰ ጉዳይ ነው። አለማየሁ ታደሰ አንጋፋ ተዋናይ ነው። ለግሩም ኤርሚያስ ሞዴል ሆኖ ወደ ትወናው አለም እንዲገባ ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኖ አገልግሏል እየተባለ በዚያ መድረክ ላይ ተነግሮለታል። ታዲያ ግሩም ኤርሚያስ እንዲህ አይነት ስህተት ሲፈፅም፣ ስለ ሀሺሽ እና ትወና ሲያወራ አለማየሁ ታደሰ ምንም አላለም። ታዲያ ሞዴልነት፣ አንጋፋነት፣ አዋቂነት ምን ላይ ነው? ቢያንስ ቢያንስ ይሄ ጉዳይ ስህተት ነው። በቴሌቭዥን እንዳይተላለፍ ብሎ መናገር እንዴት አቃተው? ሀሺሽ ከወንጀልነት በላይም ማህበረሰብን በማወክ እና ሞራልን በማላሸቅ የሚታወቅ በመሆኑ አንድ የኪነ-ጥበብ ሰው ይህን ማህበራዊ ጠንቅ እንዴት አያውቀውም? እንዴትስ ምክር ቢጤስ አይሰጥም? የሚሉ ሃሳቦችን እንድናነሳ ግድ ይለናል።

የስህተቶችን ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ሰይፉ ፋንታሁን ነው። ሰይፉ ይህንን ፕሮግራም ሲሰራ የቀጥታ ስርጭት አይደለም። ተቀርፆና ተቀነባብሮ እንዲሁም ተገምግሞ የሚቀርብ ነው። እንደ አንድ የፕሮግራም አዘጋጅ ይህ የሀሺሽ ታሪክ ስህተት መሆኑን ማወቅ ነበረበት። ካልሆነ ደግሞ በማን አለብኝነት ፣ ማን ይጠይቀኛል በሚል ምክንያት የማህበረሰቡን ሞራል፣ ባህል፣ ሰላማዊ ሕይወት ማወክ መበጥበጥ ውስጥ ጭልጥ ብሎ ገብቷል ማለት ነው። ምናልባት ሰይፉ ፋታሁን በእስካሁን ቆይታው የተለያዩ ጉዳዮችን ሲያቀርብ ለህብረተሰቡ ማህበራዊ ደህንነት እና ባህላዊ አስተሳሰቦች የማይጨነቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ብዙ ስህተቶችን ሲፈፅም የሚከለክለው “ሀይ” የሚለው ሰው ወይም አካል ጠፍቷል። ለዚህም ነው አንድ በሀሺሽ የሚነሆልልን ሰው እንደ ምሳሌ አምጥቶ እንደ ልቡ ሲያስቀባጥረው ያመሸው።

የኢትዮጵያ የብሮድካስት ሚዲያዎች በአብዛኛው የተያዙት እንዲህ እንደ ሰይፉ ፋንታሁን ባሉ ለህዝቦች ባህልና ማንነት በማይጨነቁ ሰዎች ነወ። ባህልና አስተሳሰብን እየናዱ ታዋቂነትን እያተረፉ ያሉ ሰይፉ ፋንታሁኖች በዝተዋል። እንደፈለጉም ቢናገሩ የሚገስፃቸው ጠፍቷል። ጭራሽ በቴሌቭዥን ላይ አስነዋሪ ቃላቶችን እና ሀረጋትን ከመጠቀም ባሻገር በሀሺሽ ላይ ሞዴል የሆነን ሰው እስከማቅረብ ተደርሷል።

ሌላው አሳዛኝ ነገር በፕሮግራሙ ላይ ታዳሚ የሆኑት እንግዶች ናቸው። እነዚህም እንግዶች ክስተቱን በሳቅና ሁካታ እንደዋዛ ማለፋቸው እንዴት ነው ነገሩ ያሰኛል። ምክንያቱም አንድ በሀሺሽ የናወዘ ሰው፣ ሀሺሽ አጨሳለሁ እያለ እያወራ ያለን ሰው እያጨበጨቡለት እና እየሳቁለት፣ እያሳሳቁለት በዝግጅት ላይ መታደም አሳዛኝ ነው። ከእነርሱ መሀል አንዱ እንኳን ተነስቶ ይሄ ማህበራዊ ጠንቅ ነው። ለሀገር አይበጅም! ብዙ ወጣቶችን ይበክላል! ስህተት ነው! እንዲህ አይነት ዝግጅት ላይ መታደም አልፈልግም! የሚል ሰው እንዴት ከመካከላቸው ጠፋ? ሰዎቹ ዝም ብለው የሰይፉ ፋንታሁንን ስህተት አድማቂዎች ናቸው ማለት ነው? ይህ ጉዳይ በእጅጉ አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ከግሩም ኤርሚያስ፣ ከአለማየሁ ታደሰ፣ ከሰይፉ ፋንታሁን እና ከታዳሚው በላይም ሌላ አንድ አሳዛኝ እና አስተዛዛቢ ተቋም አለ። ይህም ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ነው። ቴሌቭዥን ጣቢያው ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አንድ አማራጭ ሚዲያ ሆኖ መገኘቱ በጣም ጥሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን እንዲህ እንደ ሰይፉ ፋንታሁን አይነት ፕሮግራም ቀርቦ ሀገር ላይ ትልቅ ውድቀት ለማምጣት በሚያሰፈስፍበት ወቅት አብሮ አጫፋሪ መሆኑ አስደንጋጭ ነው። ባለኝ መረጃ መሰረት ቴሌቭዥን ጣቢያው ፕሮግራሞች አየር ላይ ከመዋላቸው በፊት ይመለከታቸውና ሲያምንባቸው ነው የሚተላለፉት። የሰይፉ ፋንታሁንን የሀሺሽ ፕሮግራም ቴሌቭዥን ጣቢያው ተመልክቶ ነው ያሰራጨው ብሎ መናገር ይቻላል። ይህ የሚጠቁመን ነገር ቢኖር ቴሌቭዥን ጣቢያውን የሚመሩት ሰዎቹ የአስተሳሰብ ደረጃቸው ገና መሆኑን እና የኢትዮጵያን ህግ፣ ባህል እና እሴት አለማወቃቸውን ነው። እንዲሁም ደግሞ በቴሌቭዥን ላይ ምን አይነት ይዘቶች ናቸው አለመተላለፍ ያለባቸው የሚለውን ሃሳብም አያውቁትም። ይህ ካልሆነ ደግሞ ምንም ብናደርግ የሚጠይቀን አካል የለም ብለው ደፍረዋል ማለት ነው። ይህ ሁሉ ካልሆነ ደግሞ ፕሮግራሙን ሳያዩ ሰይፉ ፋንታሁን ብቻ አቀነባብሮት የተላለፈ ነው ማለት ነው፤ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም።

ሌላው ተጠያቂ አካል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ነው። ይህ መስሪያ ቤት ትግስተኝነቱ የሚደንቅ ቢሆንም ነገር ግን እንዲህ አይነት ማህረሰባዊ ጠንቆች በቴሌቭዥን ሲተላለፉ ዝም ብሎ መመልከቱ አስተዛዛቢ ነው። የሰይፉ ፋንታሁን ፕሮግራሞች ለማህበረሰቡ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴት፣ አስተሳሰብ፣ ምግባር በፍፁም የሚጨነቁ አይደለም። ይህ ደግሞ እያደገ የሚመጣው የሚፈራ አካል ባለመኖሩ ነው። ከዚሁ ጋር ተደምሮ ደግሞ የእውቀት ጉዳይም አብሮ ይነሳል። ድንገት ሚዲያውን የተቆጣጠሩ አላዋቂዎች በዝተዋል። ከእነርሱ ደግሞ ብዙ ሙያዊ ነገሮችን መጠበቅ የዋህነት ነው።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ማድረግ አለበት ብዬ የማስበው ሚዲያውን ለተቆጣጠሩት ሰዎች ስልጠና እና የምክር አገልግሎትም ማቅረብ አለበት። አንዳንድ ሰዎች አቅማቸው ሚዲያውን ማራመድ የሚችሉበት የእውቀት ክህሎት የላቸውም። ነገር ግን ስፖንሰር ስላገኙ ብቻ በተለይ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ላይ ወጥተው ብዙም የማያስኬድ ከመስመር የወጣ ዝግጅት እያቀረቡ ይገኛሉ። እንዲህ አይነት ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ እየመጡ ነው። ብሮድካስት ባለስልጣም ዝምታውን ትቶ እውቀት ላይ የተመሰረተ ስልጠና፣ የሙያ ማሻሻያ እየሰጠ የብቃት ማረጋገጫ ወረቀት መስጠት አለበት። ይህ የብቃት ማረጋገጫ ደግሞ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ላይ የሚሰሩት ሰዎች ማግኘት አለባቸው። ካለብቃት ሁሉም ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ላይ ቂጥ እያለ ኢትዮጵያዊነትን የሚያፈርሱ በርካታ ዝግጅቶች እየቀረቡ ነው። ስህተቶች ሲፈጠሩም ሥልጣኑን ተጠቅሞ ተገቢውን እርምት እንዲወስድ ማድረግ አለበት።

ፕሬስ ነፃ መሆን አለበት ከሚሉት ወገኖች አንዱ ነኝ። ነፃነት ሲባል ደግሞ ምን ማለት ነው የሚለውም መመለስ አለበት። የፕሬስ ሰዎች የተማሩ፣ በሙያቸው ስልጠናና እውቀት የወሰዱ፣ የሀገራቸውን እና የአካባቢያቸውን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል የሚያውቁ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን አለባቸው። ከዚህ ሌላም የሚዲያውን ባህሪ በትክክል የተገነዘቡ መሆን ይገባቸዋል። ለምሳሌ እንደ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ያሉት የብሮድካስት ጣቢያዎች ባህሪያቸው ምንድንነው? የሚለውን በስርዓት ማወቅ አለባቸው። በአንድ ጊዜ ለሚሊዮን ህዝቦች በስርጭት የሚረሱ እነዚህ ተቋማት ላይ የሚሰራ ሰው ምን አይነት ክህሎት ያስፈልገዋል የሚለው አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ብሮድካስት ሚዲያ እጅግ ከባድ ከሚባሉት የሚዲያ ተቋማት አንዱ ነው። ስህተትን ማረሚያ ጊዜ የሌለው ነው። በአንድ ጊዜ ለሚሊዮኖች ከተሰራጨ በኋላ እንደ ተዛማጅ በሽታ የሚሰራጭ ወይም እንደ ፍቱን መድሃኒት ለፈውስ የሚያበቃ ነው። ታዲያ ይህን ባህሪውን ጠንቅቀው የሚያውቁ እና የተማሩ ሰዎች ሊያስተዳድሩት፣ ሊይዙት ይገባል። በእና ሀገር ሁኔታ እውቀት እንጦሮጦስ የገባ ይመስላል። ማንም ሰው የሬዲዮ ፕሮግራም ሊኖው እና የመሰለውን ነገር ሊያስተላፍ ይችላል። ይሄ ደግሞ በነ ሰይፉ ፋንታሁን ፕሮራም በተደጋጋሚ ታይቷል።

ስለዚህ ብሮድካስት ባለስልጣን በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን ስርጭቶች ላይ ለተሰማሩ ስህተት ፈፃሚዎች መጀመሪያ ትምህርትና ስልጠና ቢሰጥ፣ ቀጥሎ ደግሞ መገሰፅ፣ ቢቀጥል ደግሞ ለሀገር እና ለህዝብ አይበጁም የሚላቸውን እስከ ማገድ ቢደርስ የተሻለ ይሆናል። ካለበለዚያ እንደ ሰይፉ ፋንታሁን ያሉ የሀሺሽ ፕሮራሞችን እያጨስናቸው በየቤታችን ቁጭ ማለታችን ነው።

ከላይ የሰፈረው ፅሁፍ በሙሉ የማይመለከታቸው አካላትም እንዳሉ ልብ ሊባል ይገባል። በተለይ በሬዲዮና በቴሌቭዥን ስርጭቶች ላይ በጣም ጥሩ የሆኑ ፕሮግራሞችን አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን ይህ ትችት አዘል ፅሁፍ አይመለከተውም እነርሱን እያመሰገንን የሚወቀሰውን ነው ለይተን ያወጣነው። ለማንኛውም ሁሉም የተሻሉ ፕሮግራሞች እንዲሆኑ እመኛለሁ።

Last modified on Wednesday, 16 April 2014 12:11
ይምረጡ
(13 ሰዎች መርጠዋል)
15005 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us