ጥቂት ስለ “ሳተናው እና ሌሎች …”

Wednesday, 11 October 2017 12:54

 

የመጽሐፉ ርዕስ        ሳተናውና ሌሎች…
የመጽሐፉ አይነት     የአጫጭር ልቦለዶችና የግጥም ስብስብ
ጸሐፊ                   ጋዜጠኛና ደራሲ ደረጀ ትዕዛዙ

 

አስተያየት፡- ከዘመዴ

 

ደራሲው ከጅምሩ ተደራሲያንን ወደ ንባብ የጋበዘው የመጽሐፉን መታሰቢያነት «የጥበብ ስራዎችን በብዕራቸው እያረቁ የኢትዮዽያ ስነ ጽሑፍ ያብብ ዘንድ ለተጉ አርታኢያን እና በሰላ ትችታቸው ደራሲያንን እየገሩ ትክክለኛውን መንገድ ላመላከቱ ሃያሲያን ይሁንልኝ» ሲል ባሰፈረው የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው። 128 ገፅ ያለው መጽሐፉ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ስምንት አጫጭር ልቦለዶች እና አርባ አንድ ግጥሞችን አካቷል። በ55 ብር ከ75 ሣንቲም የመሸጫ ዋጋ ለንባብ በቅቷል። ይህ ወጥ ስራ፤ የተለያዩ ማህበረሰባዊ እውነታዎችን እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ዳሷል።
የፈጠራ ስራ እምብዛም በማይስተዋሉበት በዚህ ወቅት ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው የጋዜጠኛና ደራሲ ደረጀ ትዕዛዙ «ሳተናው እና ሌሎች…» የአጫጭር ልቦለዶች እና የግጥም ስብስብ ስራ፤ ንባብን ሊጋብዙ ቁም ነገሮችን ይዟል። ከይዘት፣ ከቋንቋ፣ ከታሪክ አወቃቀር፣ ከስነ ጽሑፍ አላባውያን አጠቃቀም አንጻር በጥልቀት ተንትኖ የመጽሐፉን ምንነት ለመበየን የሐያሲያን ደርሻ እንደሆነ ትቼ፤ እኔ የወፍ በረር ቅኝቴን እንዲህ በምሳሌ ላመላክት። የተለያዩ ዘመናት የጋዜጠኝነት ተግባር ምን እንደሚመስል በንፅፅር ያቀረበበት «ሳተናው» የተሰኘው አጥር ልቦለድ ምንም እንኳ የበቃ እና የነቃ ቢሆን ጋዜጠኛ ሙያውን የሚስትበት ወይንም የሚታለልበት አጋጣሚ እንደሚኖር የሚያመላክት ነው።


ጋዜጠኛ በሙያዊ ተግባሩ ሁሌም ሃሳብ እየያዘ እንደሚኖር፣ ሙያዊ ኃላፊነቱ እንደሚያስጨንቀው፣ ሁሌም የስሜት መዋዠቅ ውስጥ እንደሚኖር ያሳያል። ደራሲው በጋዜጠኝነት ህይወት ውሰጥ ሲኖር ልምዱንና አስተውሎቱን እንዳላባከነ በልቦለዱ ውስጥ ይታያል። «ታታ» በተሰኘው ልቦለድ ስሜትን ፈታ የሚያደርግ፤ ከዚያም አልፎ ሳቅን የሚያጭር ነው። በልጅነት የአብሮነት ሕይወት ውስጥ የሚስተዋሉ ገጠመኞችን በማራኪ አቀራረብ ተቀምጧል። ልቦለዱ አንድ ከገጠር ወደ ከተማ የመጣ ብላቴና ከከተሜ ልጆች ጋር ሲገጥም የሚያየውን አበሳና የእሱ የአልሸነፍም ባይነት የሚፈጥረው አካላዊና ዓዕምሯዊ ሹኩቻ ታሪክ ልብ እያንጠለጠለ ይወስዳል። አካባቢያዊ ተፅዕኖ በማንነት እና በውስጣዊ አቅም ላይ ሊፈጥር የሚችለውን እክል ሰብሮ የወጣው ዋና ገፀ ባህሪው ታታ፤ አሜሪካን አገር ድረስ ሄዶ ብዙ ቆይቶ ሲመለስ እነዚያ ሲያዋክቡት የነበሩትን የከተሜ ልጆች በፍቅር ሲፈልግ ይታያል።


የአውሮፓና የእንግሊዝ እግርኳስ፣ ኢንተርኔት ወይንም ማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስ ቡክ በማህበረሰባችን ውስጥ የጊዜ፣ የገንዘብ እና የአዕምሮ አጠቃቀም ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ በግልፅ የሚስተዋል ጉዳይ ነው። ይህ ሁነት በተለይ በወጣት ተጋቢዎች ላይ እየፈጠረ ስላለው ውጥንቅጥ የአብሮነት ሕይወት በጥሩ ሁኔታ ያመላከበት ስራው በ«መንታ ፍቅር» ልቦለድ ላይ እናገኛለን። ዕይታው የመባነን ስሜትም ይፈጥራል። ቅናትና በቀልን በ«ጉማጅ ፀጉር»፣ ቀብቃባነትን በ«ብሬ ቡራቡሬ» ልቦለዶች ላይ ልብ በሚያንጠለጥል ትረካ እናገኛለን። ደራሲው ምናበ ሰፊ መሆኑን የሚያሳዩለት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮችና ዕውነታዎች በተለየ ዕይታ ማቅረብ መቻሉ ነው።


እዚህ ላይ የወቅቱ ፈታኝ አገራዊ አጀንዳ በልቦለዱ ውስጥ መካተት መቻሉም ይጠቀሳል። በ«ሰውየው» ልቦለድ ስራው። ዛሬ በተለያዩ መንግስታዊ መስሪያቤቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ከአሁን አሁን፣ ከዛሬ ነገ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወይንም የፖሊስ መጥሪያ ደረሰኝ እያሉ መባተታቸው አልቀረም። እዚህ ስጋት ውሰጥ ያሉት ደግሞ በሙስና ወንጀል እጃቸው ያደፈ፣ ህሊናቸው የጎደፈ ሰዎች ናቸው። ይህን ዕውነታ ደረጀ በብዕሩ ሲከሽነው ተራ ስብከት ወይንም የሆይሆይታውን ዘመቻ አጋዥ አድርጎ አይደለም። በጥበባዊ ቃላት ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታውን አመላከተበት’ጂ። በአጠቃላይ ደራሲው ጥሩ ስራ ይዞልን ቀርቧል። በቀላል አቀራረብና በሚጥም ቋንቋ አንባቢን የመያዝ አቅም ያለው መጽሐፍ አበርክቷል። በአቀራረቡ ሁሉም ልቦለዶቹ እጅግ በጣም አጫጭር ናቸው።


ጎላ ባለ ፊደል (Font) የተጻፉ ሆነው እያንዳንዳቸው በአማካኝ ስምንት ገጽ የያዙ ናቸው። አፍንጫ፣ ፀጉር፣ ቁመና… እያለ የገጸ ባህሪያትን ማንነት ለተደራሲው ለማሳየት ብዙ አልደከመም። «ተደራሲው ያግዘኝ» አይነት ይመስላል። አንዳንድ የስነ ጽሑፍ ጠቢባን «… እንዲህ አይነት የአጻጻፍ ስልቶች በዘመናዊ ልቦለድ አጻጻፍ የሚመከሩ ናቸው» ይላሉ። ደራሲው በተወሰኑ ልቦለዶቹ ላይ ከገፀባህሪያት ንግግር (dialogue) ይልቅ ትረካ ላይ አተኩሯል። ይህ ምናልባት ተመካሪ የአፃፃፍ ስልት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ንግግር አንዱ የሥነ ጽሑፍ ውበት ገላጭ ስልት እንደሆነ ማመኑ ግድ የሚል ይመስለኛል። ከዚህ ሌላ እንደ «እድናለሁ» እና «ምን ይዋጠኝ?» የተሰኙ ልቦለዶቹ ሁሉ ቀጥታ የሚነግሩ፣ የሚመክሩ ወይንም የሚሰብኩ አሥር ሃይማኖታዊ ግጥሞች በመጽሐፉ ተካተዋል። የጭብጣቸው ተመሳሳይነት ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ይመስላል።


እነዚህ ልቦለዶችና ግጥሞች በተለየ በሌላ መንፈሳዊ የልቦለድና የግጥም መድብል ቢወጡ መልካም ይሆን ነበር። በተለያዩ ዘመናት የተፃፉ ከመሆናቸው አንፃር በግጥሞቹ ውስጥ አንዱ ከሌላው በግላጭ የሚታይባቸው የብስለት ልዩነት አለ። «ዼጥሮስ ያባነነው ዶሮ»፣ «ኖሮ ያልኖረ»፣ «ባይተዋር» እና «ዓለም ላንቺ!» የተሰኙ የቅርብ ጊዜ ግጥሞች ብስለት እንደሚታይባቸው ሁሉ፤ «ቆምጣጣ ፍቅር»፣ «ማሪኝ»፣ «የልቤ ሳቅ» የመሳሰሉት ግጥሞች ከቃላት ጋጋታ በስተቀር ግጥምነታቸውን የሚያጎላ እምቅ የሃሳብ ብስለት ጎምርቶ አልታየባቸውም። በጥቅል ዕይታ ግን የአብዛኛው ግጥሞች አሰነኛኘት፣ ከተለመደው የሳድስ ፊደላት አጠቃቀም ወጣ ብሎ በውድ ቃላትና ፊደላት ቤት አመታታቸው፣ ሪትም መጠበቃቸው፣ ዜማ ሰጪነታቸውና ጠንካራ መልዕክታቸው የመጽሐፉን ዋጋ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።


አልፎ አልፎ በግጥሞቹም ሆነ በልቦለዶቹ የፊደልና የስርአተ ነጥብ ግድፈት መታየቱም አልቀረም። ምናልባት መጽሐፉ ዳግም የመታተም ዕድል ከገጠመው ይህ ሁሉ ይስተካከላል የሚል እምነት አለ። ሽፋኑ እጅግ በደመቀ ቀይና ሰማያዊ ቀለም አሸብርቋለ። ይህ አይነት አቀራረብ ብዙውን ጊዜ በልጆች መጽሐፍት ላይ የሚመከር ነው፤ ደራሲው ይህን ሲያደርግ የውስጥ ቁምነገሩን እንዳይጋርድበት ስለምን አልተጠነቀቀም? ያስብላል። በጥቅሉ መጽሐፉ በተለያየ መልኩ የሰው ልጆችን ባህሪያት፤ ማለትም ቅንነትን፣ ክፋትን፣ ትዕግስትን፣ እምነትን፣ ተንኮልን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን ወዘተ ዳሷል። በጥሩ የአሰነኛኘት ጥበብ ግዙፍ አገራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችንም በጥልቅ ሃሳብ ዳሷል። ሊነበቡ ከሚመከሩ የፈጠራ ስራዎች አንዱ ነው ለማለት ያስደፈራል።


የአሳታሚን ደጅ ጥናት ችሎ፣ የማሳተሚያ ገንዘብን ቋጥሮ፣ የማከፋፈሉን አበሳ ታግሶ እንዲህ ጥበብን ለተደራሲ ለማድረስ መታተር ምስጋና የሚያሰጥ ነው እላለሁ። ያም ሆኖ ይህ መጽሐፍ ከተወሰኑ አከፋፋዮችና መጽሐፍ መደብሮች ሌላ በአዟሪዎች እጅ እምብዛም አለመታየቷ «ለምን ይሆን?» ያስብላል። እዚህ ላይ ከመጽሐፍት ገበያ ጋር የሚያያዝ ውስጤ የሚብላላን አንድ ሃሳብ አንስቼ ምልከታዬን ልቋጭ። አንዳንድ ጊዜ ጥበባዊ ስራ ጊዜና ወቅት አላቸው የሚያስብል ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ዛሬ ጥበባዊ ስራና ንባብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኗቸውን ያበረቱት የሶሻል ሚዲያዎች ብቻ አይደሉም። የአከፋፋዮች፣ መጽሐፍት አዟሪዎችና የሽያጭ መደብሮችም ጭምር እንጂ። «እንዴት?» ቢሉ እነዚህ የንግድ ዘርፎች ከገቢ ጥቅም አንፃር ስም ያላቸው ሰዎችን መጽሐፍት ተመራጭነታቸውን በማጉላት ማሻሻጣቸው ነው።


በየመደብሮች፣ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ፊት ለፊት የሚታዩት የእነዚህ ሰዎች መጽሐፍቶች ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ ጥበብ በጥቂት ሰዎች አስተሳሰብ እንዳትመራ፣ አንባቢያን በእነሱ የአመለካከት ተፅዕኖ ስር እንዳትወድቅ ስጋት ያሳድራል። ዛሬ ዛሬ እንደሚስተዋለው የፖለቲካና የታሪክ መጽሐፍት ጊዜያቸው ነው። ወጎች እና ሙያዊ መጽሐፍትም ተፈላጊነታቸው በርትቷል። ምን ያህል ይሄዳሉ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አንድ ነገር ሆኖ፤ አነስተኛ ገፅ ያላቸው የግጥም መጽሐፍትም በገበያው ፉክከር ውስጥ እየተፍጨረጨሩ መሆኑ ይታያል። እንደ እኔ አስተውሎት በዚህ ዘመን (ካለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ሊባል ይቻላል) የረጃጅም ልቦለዶችና የአጫጭር ልቦለዶች ስራ ገበያውን አልገዙትም። ለምን? የሚለው ጥያቄ የአጥኚዎችን ምላሽ የሚያሻ ሆኖ፤ በእኔ ትዝብት የአከፋፋዮች፣ የሸያጭ መደብሮች እና የአዟሪዎች አድሏዊ ተፅዕኖ ነው ለማለት እደፍራለሁ።
ምክንያቱም አንባቢያን ሊመሰጥባቸው፣ ጥበባዊ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑን ሊገነዘብ የሚችልባቸው መጽሐፍት አሉና። እንዲህ ያሉ መጽሐፍት ቢወጡም ገበያው ስላላበረታታቸው በየስርቻው እንዲሸጎጡ ግድ ብሏል። ረጅምና አጫጭር ልቦለዶች እንዲሁም ግጥሞች ጥበባዊ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው። እኔ እንደሚገባኝ ዋናው የጥበባዊ ስራ መለኪያዎችም እነዚህ የስነ ጽሑፍ ውጤቶች ናቸው። እንደ ፍቅር እስከመቃብር፣ እንደ ጉንጉን፣ ሰመመን፣ ከአድማስ ባሻገር …የመሳሰሉ መጽሐፍትን የሚመጥኑ ሰራዎች ዛሬም የሉም አይባልም። የዚህን ዘመን የአንባቢያን እና የገበያውን ሁኔታ በመፍራት ደራሲያን ለህትመት አላበቋቸው ይሆናል እንጂ «ይኖራሉ» ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም ስነ ጽሑፍም ከሰዎች አስተሳሰብና የንቃተ ህሊና ዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚያድግ ነውና።


ደራሲያን ያንን አቅም አውጥተው ወደ አንባቢያን ዘንድ ለመድረስ ያሉባቸው መሰናክሎች እንዳይራመዱ ካላደረጋቸው በስተቀር ደራሲያን ዘንድ እወቀቱ፣ ክህሎቱ፣ አቅሙም አለ። ምንም ጥርጥር የለውም። «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር። በዚህ ከፍተኛ አድሏዊነት የገበያ ፉክክር ውስጥ የፈጠራ ስራውን ይዞ ወደ አንባቢያን ለመድረስ የጣረው ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጀ ትዕዛዙ መጽሐፉ ጥበባዊ ዋጋው ቀላል የሚባል አይደለም። ከተጽዕኖው ባለፈ ገበያውን ሰብሮ የመውጣቱ አቅም በመጽሐፉ ጥንካሬ ቢወሰንም፤ የደራሲው ብርታት ግን ለሌሎች አርአያነት ያለው ነው ለማለት እደፈራለሁ።


ደረጀ በመጽሐፉ መግቢያ ከልጅነቱ ጀምሮ በጋዜጦችና ራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ሲያደርግ የነበረው ነጻ ተሳትፎ ለፈጠራ ሥራ ብሎም ለጋዜጠኝነቱ ሙያ ጥሩ መንደርደሪያ እንደሆነው፤ በፈጠራ ስራ ደረጃ መጽሐፉ የመጀመሪያ ሥራው መሆኑን፣ ለቀጣይ ስራ እንደሚተጋም ገልፆም ነው ወደ ንባቡ የጋበዘው። የታዋቂው ጋዜጠኛ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪውን ዻውሎስ ኞኞ የሕይወት ታሪክ ግሩም አድርጎ አዘጋጅቶ እንዳስነበበን ሁሉ አቅሙ ሌላም ድንቅ ስራ ያመጣልናል የሚል ተስፋን ያሳድራል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16003 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1083 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us