በፒ-ስኩዌሮች የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የታሰበውን ያህል ተመልካች አልተገኘም:: ሦስት ድምፃውያን ቀርተዋል

Thursday, 03 October 2013 19:08

 

በቃና ኢንተርቴንመንት እና በአስታር አድቨርታይዚንግ አዘጋጅነት ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ ይቀርባል ተብሎ የተሰረዘው የፒ-ስከዌሮች የሙዚቃ ድግስ ወደ ቅዳሜ (መስከረም 11 ቀን 2006) ከተዛወረ በኋላ አዘጋጆቹ የጠበቁትን ያህል ሰው እንዳላገኙ ተነገረ። ከ10 እስከ 15 ሺህ ሰዎች ተጠብቀው የነበረ ሲሆን፤ በአዳራሹ የተገኘው ታዳሚ ግን ቁጥሩ እጅግ ያነሰ መሆኑ ታውቋል።

 

ቅዳሜ ዕለት ከሙዚቃ ድግሱ በፊት ፒ-ስኩዌሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመድረክ በሚቆዩባቸው ሦስት ሰዓታት ውስጥ ከ15 በላይ ሙዚቃዎችን እንደሚጫወቱ ያስታወቁ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ሲደርሱ በነበረው አቀባበል መደሰታቸውን በመግለፅ፤ የዋዜማው የሙዚቃ ድግስ ባለመሳካቱ ከይቅርታቸው ባሻገርም ሕዝቡን በሙዚቃ ስራቸው ለመካስ መዘጋጀታቸውን ተናግረው ነበር።

 

በቅዳሜው ምሽት የሙዚቃ ድግስ ላይ ከፒ-ስኩዌሮች በተጨማሪ ድምፃዊያን ጃሉድ፣ ሀመልማል አባተና ታደለ ገመቹ በመድረኩ የተገኙ ሲሆን፤ በዋዜማው ዝግጅት ወቅት ስማቸው ተካትቶ የነበሩት ድምፃዊት ዘሪቱ ጌታሁን (እንቁጣጣሽ)፣ ናቲ ማን እና ተስፋዬ ታዬ አለመገኘታቸው ታውቋል። በዕለቱ የመግቢያ ትኬት ፈላጊው ቁጥር ከፍ ቢልም በጥቁር ገበያው ምክንያት የታሰበውን ያህል ማስተናገድ ሳይቻል ቀርቷል።

Last modified on Saturday, 01 February 2014 15:57
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11504 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us