ሰዓሊ ቱሉ ጉያ እና የጥበብ ጉዞው

Wednesday, 16 April 2014 13:41

በጥበቡ በለጠ

  

በኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ታሪክ ውስጥ አንድ አስገራሚ ክስተት አለ። ይህም ከአንድ ቤት ውስጥ ሶስት ታዋቂ ሰዓሊዎች መውጣታቸው ነው። ከዚሁ ከመዲናችን ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቅ በቀድሞው ምስራቅ ሸዋ አድአ ሊበን ወረዳ ደሎ ገ/ማህበር ውስጥ ማለትም ደብረዘይት (ቢሸፍቱ) አካባቢ ወ/ሮ ማሬ ጎበና እና አቶ ጉያ ገመዳ ተጋብተው ከወለዷቸው ልጆች ውስጥ ሶስቱ አንቱ የተባሉ ሰዓሊዎች ሆነዋል። እነዚህም ልጆች ለማ ጉያ፣ ቱሉ ጉያ እና አሰፋ ጉያ ናቸው። ዛሬ ከሰዓሉ ቱሉ ጉያ ጋር ቆይታ እናደርጋለን። የኪነ-ጥበብ ሰው ነውና አንተ እያልን ታሪኩን እናቀርበዋለን።

ሰዓሉ ቱሉ ጉያ የተወለደው መስከረም 16 ቀን 1939 ዓ.ም ነው። ገና በልጅነቱ ቤቱ ውስጥ የጥበብን ሀሁ ያየውና ምን እንደሚመስል የቀሰመው ከእናቱ ከወ/ሮ ማሬ ጎበና ነው። እናቱ የተለያዩ የአፈር አይነቶችን እየቀላቀሉ እና እየቀመሙ ቀለሞችን ይሰራሉ። ከዚያም የቤታቸውን ግድግዳ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው እውቀት በስዕል ያስጌጣሉ። ህፃኑ ቱሉ ጉያ ይሄን እያየ አደገ። የመስመሮችን ጉዞ እና ውህደት በቤቱ ግድግዳ ላይ እናቱ ሲሰሩ ተዋወቀ። ወ/ሮ ማሬ ለኢትዮጵያ ስነ-ጥበብ እድገት እየዘሩ ያሉትን አዝመራ ባያውቁትም በኋላ ታላላቅ የስነ-ጥበብ ሰዎች ከዚያ ቤት እያሸቱ መሆኑን ተግባራቸው ይነግረናል።

ጥበባዊ ውድድሮች በተማሪዎች መካከል መደረግ ካቆመ ቆየ። ኧረ እንዲውም እየጠፋ ነው። የኢትዮጵያን ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በስነ-ጥበብ፣ በስነ-ፅሁፍ፣ በስነ-ግጥም እና በልዩ ልዩ ርዕስ ጉዳዮች እያወዳደሩ መሸለም እና መምረጥ ወደፊት ምርጥ ትውልድ እንዲመጡ በር ከፋች ስራ ይመስለኛል። በአሁኑ ወቅት በሰፊው ተንሰራፍቶ ያለው የሴቶቹ የቁንጅና ውድድር ነው። ለዚህ የውድድር አይነት ተቃውሞ ባይኖረኝም፤ ሀገርንና ትውልድን የሚጠቅሙ ሌሎች የውድድር ዘርፎች ተረስተዋልና እነሱም እንዲነሱ በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እፈልጋለሁ።

በ1962 ዓ.ም ለነ ቱሉ ጉያ “አፖሎ 11” ጨረቃ ላይ ማረፏን ምክንያት አድርገው የስዕል ውድድር ያዘጋጁላቸው ትውልዶች አርቆ አሳቢዎች ነበሩ። ዛሬ ስንት የመወዳደሪያ ምክንያቶች እያሉ አልሰማም አላይም ብለን ረጅም እንቅልፍ ተኝተናል። እንንቃ ጎበዝ!

የዛሬ 40 ዓመት በኢትዮጵያ ተማሪዎች ዘንድ አሸናፊ ሆኖ የወጣው ቱሉ ጉያ፤ የራሱ የሆነ የአሳሳል ዘይቤዎች አሉት። እነዚህ የሚያተኩርባቸው ዘይቤዎች በሰዎች የእለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴዎች ላይ፤ እንዲሁም ደግሞ በህብረተሰቡ ባህላዊ ቅርስ ላይ ነው። እራሱ ቱሉ የመጣበት አካባቢ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) አያሌ ባህላዊና መንፈሳዊ ድርጊቶች የሚከናወኑባት፤ በተለይ ደግሞ በኦሮሞ ልዩ ልዩ እሴቶች የደመቀች አካባቢ በመሆኗ ቱሉ ጉያ የሀገሩን በርካታ የባህል ሀብቶች ቀስሟል። እነዚህን ሀብቶች ነው በስዕል ጥበቡ እየመነዘረ የሚጠቀምባቸው። ለነገሩ አንድ የኪነ-ጥበብ ሰው የተሟላ ትጥቅ አለው የምንለው በተለይ ማንነቱን ሊያሳዩ የሚችሉ የራሱ ባህላዊ መገለጫዎቹን ይዞ ሲቀርብ ነው። እናም ቱሉ በቂ ትጥቅ የታጠቀ የጥበብ ሰው ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የቱሉ ጉያ የአሳሳል ዘይቤ ብዙዎች ያልሞከሩበትን አንድ ሌላ መንገድ የሚከተል ነው። ይህም ጥበብን የህብረተሰብ ችግር መፍቻ /Applied Art/ የሚሰኘውን የጥበብ መስክ በስፋት የሚከተል ሰዓሊ ነው።

አያሌ ጥበበኞች ጥበብን እንደ ችግር መፍቻ አድርገው ሲጠቀሙበት አይታይም። ይልቅ ጥበብ ለጥበብ /Art for Art Sake/ በሚለው ጎዳና ላይ ናቸው። ሁለቱም ፍልስፍናዎች የራሳቸው የሆነ ዝርዝር ትንታኔዎች አሏቸው። አንዱ ከሌላው ይበልጣል የሚል አካሄድም የለም። ጥበብ ውቅያኖስ ስለሆነ ሁሉም በሚመቸው መንገድ መጓዝ ይችላል። መድረሻው ግን ዘላለማዊ የምናብ ዓለም መፍጠር ነው። በዚህ የምናብ ዓለም ውስጥ የሚገባ ደግሞ ተጠቃሚ ይሆናል። ካየውና ከተገነዘበው የምናብ ዓለም ውስጥ የሚገባ ደግሞ ተጠቃ ይሆናል። ካየውና ከተገነዘበው የምናብ ዓለም ውስጥ ወስዶ በእውነታው ዓለም ላይ ሲጠቀምበት የጥበብ ሕግ ታስገድዳለች። ምክንያቱም የጥበብ ሰዎች የምናብ ዓለም ሰዎች ናቸው። እነሱ የምናብ አለማቸው የፈጠሩትን እኛ አይተን ተገንዝበን ነው ወደ ውስጣዊ ማንነታችን ከተን የምንጠቀምበት።

የቱሉ ጉያ አሳሳል ግን ምናቡ የሚያስገድደው ወደ ህብረተሰብ ችግር መፍቻ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። ከአንድ የጥበብ ስራ ማህበረሰቡ መጠቀም አለበት። ሰዓሊ ቱሉ ህብረተሰቡ በህይወቱ፣ በኑሮው እንዲሻሻል እና ዓለምን ከዛሬ ነገ እንዲያሻሽላት በቀጥታ መንገድ የሚያሳይ ሰዓሊ ነው።

ለዚህም ይመስላል ቱሉ ጉያ ረጅሙን የጥበብ ህይወቱን ከህፃናት እስከ አዋቂዎች ድረስ እያስተማረ የገፋው። ህይወቱ መምህርነት ነው። የነገዎቹን ጥበበኞች የማፍራት ተልዕኮ ነው ያለው። ለዚህ ተግባሩ ስኬት ደግሞ ገጠር ውስጥ ሁሉ እየሄደ ነው የሚያስተምረው። አያሌ ልጆችን አስተምሮ ወደ ጥበቡ ዓለም አስገብቷል።

ገና ስራ ሲጀምር (በ1963 ዓ.ም ማለት ነው) በአርሲ ክፍለ ሀገር ውስጥ በሶስት መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የስዕል መምህር ሆኖ ነው። እዚያ አርሲ ውስጥም እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ በመምህርነት ቆይቷል። ከ1969 ዓ.ም እስከ 1974 ዓ.ም ደግሞ በጭላሎ አውራጃ ትምህርት ማዕከል የኦፕሮፕሪዬት ሊኒር ቴክኒሽያን ሆኖ ሰርቷል። ከዚያ በስዕል መምህርነትና የጭላሎ አውራጃ ትምህርት ማዕከል ተጠሪ ሆኖ እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ ሰርቷል። ስለዚህ ከስነ-ጥበብ ት/ቤት አምስቱንም አመት አንደኛ እየሆነ የጨረሰው ቱሉ ጉያ ወደ ገጠር ወርዶ የኢትዮጵያን ልጆች በጥበብ እንዲበለፅጉ ያደረገ ምናልባትም ጎንደር ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያስተማረውን እውቁን ሰዓሊ ጣፋን ሳረሳ ቀዳሚው ሰው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ብቁ የስዕል ተማሪ ሆኖ አዲስ አበባ ላይ የሙጥኝ ብሎ ተቀምጦ ቢሆን ኖሮ አያሌ የውጭ ሀገር ትምህርቶችን ያገኝ ነበር። ግን እርሱ ያደረገው፣ ያለውን እውቀት ይዞ ወደታች ወርዶ የጥበብ ሀሁ ባልደረሰባቸው ስፍራዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቆየ።

ቱሉ ጉያ ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ የመጣው በጥር ወር 1979 ዓ.ም ነው። እዚህም በየካቲት 66 ፖለቲካ ትምህርት ኢኒስትቲቲዩት የኦዲዮቪዥዋል አገልግሎት ኃላፊ ሆኖ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም ድረስ ሰርቷል። በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ደግሞ ይህ ት/ቤት ተዘጋ።

የሰዓሉ ቱሉ ጉያ ህይወት ግን ጥበብ ነውና የርሱ ዓለም ከመስመሮችና ከቀለሞች ጋር መኖር ነው። እናም ከህዳር ወር 1984 ዓ.ም ጀምሮ በየካቲት 12 ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የትምህርት ማዕከሉ ተጠሪ ሆኖ እስከ መስከረም 1994 ዓ.ም ድረስ ሰራ። ይህ ት/ቤት የቀድሞው ስሙ እቴጌ መነን ሲሆን በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ተማሪ በዚሁ በእቴጌ ስም ነው የሚጠራው። ቱሉ ጉያም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ ወጣ።

ቱሉ ጉያ ከ1962 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም በአውራጃ፣ በክፍለ ሀገር፣ በሀገር አቀፍ እና በብሔራዊ ደረጃ አያሌ ሽልማቶችን አግኝቷል። ለምሳሌ በ1969 ዓ.ም 2ኛው የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦችና የአፍሪካውያን የኪነትና የባህል ክብረ በዓል ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ በብሔራዊ ኤግዚቢሽን ዝግጅት በስዕል ሙያ ተካፍሎ የምስክር ወረቀት አግኝቷል። ከዚህ ሌላ እድሜውን ሙሉ ሲያስተምር በመኖሩ በ1976 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ ምስጉን የትምህርት ባለሙያ የመሆን ከትምርት ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

የቱሉ ጉያ የጥበብ ስራዎች ለህዝብ እይታ መቅረብ የጀመሩ ከአርባ ዓመታት በፊት ነው። ለምሳሌ በ1961 ዓ.ም በበልቬር አርት ጋሪ አዲስ አበባ ውስጥ ለብቻው ኤግዚቢሽን ከፍቶ አሳይቷል። በ1962 ዓ.ም በታህሳስ ወርም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ከታላቅ ወንድሙ ከሰዓሊ ለማ ጉያ ጋር ሆነው ኤግዚቢሸን ከፍተው አሳይተዋል። በዚህ ጊዜ በክብር እንግድነት የተገኙላቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን ነበሩ። ይሄ የሚያሳየው የሰዓዎቹ ስራዎች ምን ያህል ክብር የሚሰጠው እና ደረጃውን ከፍ ያለ መሆኑን ነው። ቱሉ ጉያ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ እጅም በሙያው የተሸለመ አንጋፋ ሰዓሊ ነው።

በዚሁ በ1962 ዓ.ም በጥር ወር በአስመራ ከተማ የስዕል ኤግዚቭሽን ለብቻው ከፍቶ አሳይቷል። የስዕል ጥበብ በስፋት እና በጥራት በማቅረቡ በየግዜው ኤግዚቢሽኖች የማዘጋጀት ብቃቱ እየጎለበተ መጣ። በ1964 ዓ.ም በሰኔ ወር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አሁንም ለብቻው ኤግዚቢሽን ከፍቶ የጥበብን ታዳሚ በስዕሎቹ አስደምሟል። ከነዚህ ሌላ ቱሉ ጉያ ኤግዚቢሽኖን ያሳየባቸው ስፍራዎች የሚከተሉት ናቸው።

 • በ1965 ዓ.ም ህዳር ወር በአሊያንስ ኢትዮ ፍራሲስ በህብረት
 • በ1965 ዓ.ም መጋቢት ወር በራስ ዳርጌ ት/ቤት አዳራሽ የብቻ ዝግጅት
 • በ1967 ዓ.ም ሰኔ ወር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በህብረት
 • በ1968 ዓ.ም ጳጉሜ ወር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በህብረት
 • በ1969 ዓ.ም ናይጄሪያ ሌጎስ በህብረት
 • በ1972 ዓ.ም በቼኮንዝሎቫኪያ ፕራግ በህብረት
 • በ1975 ታህሳስ ወር በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በህብረት
 • በ1975 በጅማ ከተማ ጊቤ አዳራሽ በህብረት
 • በ1982 ዓ.ም ነሐሴ ወር በብሔራዊ ሙዚየም በህብረት
 • በ1983 መጋቢት ወር በብሔራዊ ሙዚየም በህብረት
 • በ1984 ዓ.ም ሚያዚያ ወር በአስኒ ጋለሪ አዲስ አበባ የብቻ ዝግጅት አቅርቧል።

ቱሉ ጉያ ይህን ያህል የስዕል ጥበብ ችሎታ እያለው ለምንስ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ወደሆነው ሀገራት ሄዶ አልተማረም የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለነገሩ በ1962 ዓ.ም ከሩስያ ሀገር ጋር ተፃፅፎ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ እድሉ ላንተ ብቻ አይሰጥም ተብሎ ቀረበት። እንደገና በ1966 ዓ.ም ሌላ የትምህርት እድል አገኘ። አሁን ደግሞ የግብርና ሰዎች ሄደው ይማሩ ተብሎ ሥዕል ወደ ግብርና ተቀየረበት። ለሶስተኛ ጊዜ ሌላ እድል ቢያገኝም አሁን ደግሞ በራሱ ምክንያት ተወው። የግራፊክስ ትምህርት ግን ለአንድ ዓመት ያህል በ1958 ዓ.ም ከጀርመናዊው ፕሮፌሰር ሀንሴን ባህያ ዘንድ ተምሯል። የሚገርመው ግን እርሱ በጣም ደስተኛ የሆነበት በርካታ ጥበበኞችን አስተምሮ ላለቀ የሙያ ደረጃ ማድረሱ ነው።

የቱሉ ጉያ ስራዎች ብዙ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ በብሔዊ ሙዚያም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ጽ/ቤት፣ በደብረዘይት ሙዚየም፣ በፈረንሳይ፣ በሲውዲን፣ በእስራኤልና በአሜሪካ አገር በግለሰቦች እጅ ስራዎቹ በብዛት ይገኛሉ። በአቶ ዙቤር መሐመድ እጅ ከ50 በላይ ስብስብ ስራዎቹ ይገኛሉ።

ሰዓሊ ቱሉ ጉያ ከወ/ሮ አበበች ገና ጋር ትዳር መስርቶ 3 ወንድ ልጆችና 2 ሴት ልጆችን በጋራ አፍርቷል። ከልጆቹ መካከል ብስራት ቱሉ የተባለው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት በግራፊክስ ኮምኒኬሽን በቢ.ኤ ዲግሪ ተመርቋል። የሰዓሊ ቱሉ እናት የዘሯት የስዕል ጥበብ ከልጃቸው አልፋ የልጅ ልጅ ጋር ደርሳለች። የጉያ ቤተሰብ የጥበብ ጉዞ ይቀጥላል። ቱሉ ጉያም ዛሬ 67 ዓመቱ ነው። አሁንም ከወዳጁ ከጥበብ ጋር እየኖረ ነው።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
13156 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us